አድባራተ ጥበብ

ጸሐፍት፣ መጻሕፍት እና አንባብያን

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በዚህ ዘመን በአገራችን የሚታተሙ መጻሕፍት፣ ጸሐፍትና አንባብያን ጉዳይ ጤናማ አዝማሚያ ላይ እንዳልሆነ በግሌ ስለታዘብሁ ነው። በርግጥ ይህ የግል ትዝብት ነው። ትዝብቴ ግን ምክንያታዊ እንጅ እንዲሁ የግል አስተያየት አይደለም። ወደ ተለያዩ ያገራችን ክፍሎች ለሥራ በምሄድበት ወቅት ያለችኝን “ትርፍ” ጊዜ በመጠቀም አብያተ መጻሕፍትን ዞር ዞር ብሎ የማየት፣ መጻሕፍት አዟሪዎችን ሸክማቸውን እንደያዙ “የማስቸገር” ልምዱ አለኝ። እናም በዚህ ወቅት ያጋጠሙኝ ነገሮች ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ሆኑኝና የዘመናችን መጻሕፍት፣ ጸሐፍያንና አንባብያን ምን ይመስላሉ? የሚል የውይይት መነሻ መጫር ፈለግሁ።

 “መጽሐፍን በሽፋኑ መገምገም አይቻልም።” በከፊል ትክክለኛ አባባል ነው። ሰውን በልብሱ መገምገም ከንቱነት እንደሆነ ሁሉ መጻሕፍትንም በሽፋናቸው መገምገም ቂልነት ነው። አንዳንድ “መጻሕፍትን” ግን በሽፋናቸው መገምገም አይቻል ይሆን? መጽሐፍ በሽፋኑ ምን ይይዛል? የሽፋን ስዕል፣ የደራሲውን ማንነት፣ እንዲሁም ርእሱና አንዳንዴም አታሚውን ድርጅትና የታተመበትን ዘመን፣ በመጽሐፉ ዙሪያ አስተያየት የሰጡ አካላትን ማንነትና የሰጡትን አስተያየት ይይዛል። እነዚህ ነገሮች ታዲያ ወደ መጽሐፉ መግቢያ በሮች ስለሆኑ በትንሹም ቢሆን የመጽሐፉን ይዘት አይጠቁሙም ትላላችሁ? እኔ ግን ከበሩ ሆነህ የሸተተህ ወጥ ጣእሙ ምን እንደሆነ እንደሚገመተው ሁሉ የመጽሐፉን ሽፋን ማየቱ ስለይዘቱ ለመገመት የራሱን ድርሻ ይወስዳል እላለሁ። ሽፋኑን አይተህ ቀልብህን የሳበውን መጽሐፍ፣ የመጀመሪያውን ገጽ ገልጠህ ይዘቱን ልታይ ትገደዳለህ፣ ወይ ትገዛዋለህ ወይ ታልፈዋለህ። እናም በትንሹም ቢሆን አልገመገምኸውም ማለት ነው?

 የዘመናችን በርካታ ጸሐፍትም ጉዳይ ከዚሁ አይዘልም። እንዲሁ በስሜት ተነድተው የሚጽፉ አይጠፉም። አንዳንዶቹ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ከሚሰጧቸው አስተያየቶች በመነሳት በመጽሐፎቻቸው የሚያስተላልፉትን “እውነት” መገመት አያዳግትም። የአንባብያኑን ሁኔታ ለመገመት ምን ዓይነት መጻሕፍት ገበያውን ተቆጣጠሩት? የሚለውን መዳሰስ በቂ ባይሆንም የራሱን ድርሻ ግን ይወስዳል። ጸሐፊ፣ መጻሕፍትና አንባቢ የሚመጋገቡ ስለሆኑ አንዱ ሌላኛውን መቆጣጠር ይችላል። አንድ መጽሐፍ፣ “መጽሐፍ” ለመባል የያዘው ሐሳብ የዘመንና የቦታን ድንበር መሻገር ሲችል ነው። ጸሐፊውም በዘመንና ቦታ ጭጋግ ግርዶሽ ተራርቀው የሚገኙ የሰው ልጆችን ማገናኘት የሚችል ነው። በኔ ትዝብት የመጻሕፍት ገበያውን የተቆጣጠሩት በርካታ የቅርብ ዘመን መጻሕፍት እንኳን ዘመንና ቦታን ሊሻገሩ የወንዝና የቋንቋን ልጓም መበጠስ የሚችሉ አልመሰለኝም። አንዳንዶቹማ እንዲያውም የራሳቸውን ወሰነ ምድር ለማበጀት ትልልቅ ግንብ የገነቡ ይመስላሉ፣ በሽፋናቸው የመፍረድ መብቱ ከተሰጠኝ። እነሱን መተንተን ወይም መተቸት አይደለም የዚህ ጽሑፍ ቁም ነገር። ይልቁን ስለጸሐፍት፣ መጻሕፍትና አንባቢዎች ትንሽ ነገር ለማለት ነው። የሰለጠነ ማኅበረሰብ ግንባታ ባንድም በሌላም በጸሐፍያኑ የሐሳብ ምጥቀት፣ በመጽሐፎቻቸው ዘመንና ቦታን ተሻጋሪነት፣ እንዲሁም በአንባብያኑ ብስለትና ስክነት ላይ ይመሰረታል ባይ ነኝ። ለዚህ ነው ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ለዛሬ መነጋገሪያ ይሆነን ዘንድ ይዤ መምጣቴ።

፩. ጸሐፍት

ስለመጻሕፍት ሲነሳ የመጻሕፍቱን ደራሲዎች መዘንጋት አይቻልም። ደራስያን ከማስተባቃት፣ ከተመስጦና ማሰላሰል፣ ከሕይወት ልምድ፣ ከረጅም ዘመናት ጥናትና ምርምር፣ እንዲሁም ከጥሩ የንባብ ልምዳቸው ያገኙትን እውቀትና ሐሳብ ለሌሎች ለማካፈል ጽሕፈትን ወይም ንግግርን ይጠቀማሉ። አንዳንዶቹ ጥሩ ተናጋሪ ሲሆኑ የመጻፍ ተሰጥኦ የሌላቸው ናቸው። እነርሱ የተናገሩትን ጥሩ አድማጭና የመጻፍ ችሎታ ያለው ሲጽፈው ድርሰታቸው ለሌሎች ይዳረሳል። ለምሳሌ ሶቅራጥስ በሕይወት ዘመኑ ምንም ነገር አልጻፈም ይባላል። ፕሌቶ የተባለ ተማሪው በርካታ መጻሕፍትን ሲጽፍ በዋና ገጸ ባሕርይነት ሶቅራጠስን ሲጠቀም የፍልስፍና ታሪክ ጸሐፍት የፕሌቶ ቀደምት ሥራዎች የሶቅራጥስን ሐሳቦች የያዙ ናቸው ሲሉ ይደመድማሉ። ሌሎቹ ደግሞ የመጻፍ ችሎታ የተካኑ ሲሆኑ ንግግር ላይ እስከዚህም ናቸው። ጥቂቶች ሁለቱንም ክህሎት በምልዓት የተቸሩ ናቸው።

 አንድን ጸሐፊ ጥሩ ደራሲ የሚያሰኘው ጥንቅቅ ካለ የቋንቋ አጠቃቀሙና የአገላለጽ ክህሎቱ በተጨማሪ ዘመን ተሻጋሪ፣ የቦታ ድንበር የማይገድበው አስተሳሰብ መያዙ ነው። የሚጽፈው ነገር ስሜት ቀስቃሽና አንድን ወገን ብቻ የሚኮረኩር ሳይሆን እውቀት ጨማሪ፣ ምሥጢር ገላጭ፣ የሁሉንም ሰዎች መንፈስ የሚቀሰቅስ ርህራሄ ልቡናንና ንቃተ ሕሊናን የሚያጎናጽፍ ሲሆን ነው። ወልደ ሕይወት የተሰኘ የዘርዓያዕቆብ ደቀ መዝሙር ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ስለ ጻፈው ሐተታ ሲናገር “ከብዙ ዘመን ጥንቁቅ ሐተታ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ልቤን ንጹህ አድርጌ ከጸለይሁ በኋላ ስለምጽፍ ከልቡናችን ጋር የማይስማማውን ምንም አልጽፍም።” ብሎናል። የብዙ ዘመን ጥንቁቅ ሐተታ በምርምርና በልምድ፣ በተመስጦ የታገዘ እውቀት ነው። በፈጣሪ ፊት ልብን ንጹህ አድሮጎ መጸለይ በራሱ ወይም በሰቂለ ኅሊና ማስተባቃት ለጽሑፍ ወይም ለንግግር መልካም ግብዓት ያስገኛል። የወልደ ሕይወት ጸሎት እውቀት በምክንያትና በምርምር ብቻ የማይደርስባት ስለሆነ የፈጣሪን አጋዥ ኃይልና ጥበብ ገላጭነትን ያመሰጥራል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ከልቡናችሁ ጋር የማይስማማ ነገር አልጽፍም ብሎናል። ምንም እንኳ ለጸሐፊው የተገለጠለት ለራሱ እውነት የሚመስለው ነገር ቢኖርም የአንባቢዎችን ልቡና ቀድሞ ማድመጥ መቅደም እንዳለበት ያሳየናል። ይህም አንባቢን መረዳት ነው።

ጥሩ ደራሲ ቀናና ታማኝ ነው፤ ለስሜቱ ታማኝ፣ ለእውነት ታማኝ፣ ለአንባቢው ታማኝ የሆነ ነው። ሩህሩህና ለሰብአዊነት ተገዥ ነው፤ የሚጽፈው ጽሑፍ የሰው ልጆችን ተግዳሮቶች የሚያቃልል፣ ደስታቸውን ከፍ የሚያደርግ፣ ያለማወቅ ጭጋጋቸውን የሚገፍ መሆን እንዳለበት ያምናል። እነዚህ የፈጣሪነትን ድርሻ ይይዛሉ፤ ፈጣሪ ውብ ዓለምን እንደፈጠረ ሁሉ እነዚህ የሰው ሕይወት የሚመራባቸውን ውብ ሐሳቦች ይወልዳሉ። የመጻፍ አያናቸው ሲነሳ ወደ ሰማየ ሰማያት በሰቂለ ሕሊና ወጥተው፣ ወደ ጥልቁ ወርደው በንስር ዓይን በርብረው የደረሱበትን የአብርሆት ፍንጭ ለአንባቢዎቻቸው የሚቸሩ ናቸው። ጥሩ ደራሲ ለጋስ ነው:- የደረሰበትን እውቀትና እውነት በመቁንን አይከፍለውም፣ ለነከሌ በነ እከሌ ላይ ልጻፍ አይልም። ለሁሉም የሚዳረስ ምግበ ኅሊና፣ ጥበበ አእምሮ በችሮታ ያድላል። ጥሩ ደራሲ ወገንና ነገድ የለውም። ይህ ጸሐፊ የሚተቸው ውሱን ወገኖችን አይደለም። የሚተች ከሆነ አጥፊዎችንና ጠፍሮ የያዘውን ገዥ መንፈስ ነው። ጥሩ ደራሲ የነጻነት ታጋይ፣ የሰው ልጆችን በጎነት በፊት አውራሪነት የሚመራ ነውና የሚታገልላቸው ውሱን አባላት የሉትም። ለሁሉም የሰው ልጆች በጎነት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሰፊ የነጻነት ድር ይዘረጋል እንጂ።

ከሁሉም በላይ ግን ጸሐፊ ድልድይ ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የበለጸጉ የአስተሳሰብ ውርሶችን በመተቸት ወይም በመደገፍ የበለጠ ተሻሽለው እንዲቀርቡና የዘመኑን መንፈስ እንዲወክሉ የሚያደርግ። ለዚህም ጥሩ ጸሐፊ ውስጥ ጥሩ አንባቢነት አለ። ጥሩ አንባቢ እንደምን ያለ ነው? የሚለውን ከታች በሰፊው እናየዋለን። በእንደዚህ ዓይነት ደራሲዎች የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው የዘመንና የቦታን ድንበር፣ ግንብ በርግደው የሚያልፉት። በሁሉም የሰው ልጆች ቋንቋ የመተርጎምና የሁሉንም አንባብያን ዓይነ ህሊናና እዝነ ልቡና የመሳብ መግነጢሳዊ ኃይል ይኖራቸዋል።

ዓለማችን እንደነዚህ ዓይነቶቹን በርካታ ደራሲዎች አፍርታለች። በድርሰታቸው አድማስ ተሻጋሪነት በዜግነት የማይወሰኑ በሁሉም የሰው ልጆች ልብ ውስጥ የተደላደለ ምቹ ቦታ የተቸራቸው ናቸው እነዚህ። ከፈላስፎቹ ፕሌቶ፣ ሶቅራጥስና ኮንፊሽየስ ተጠቃሽ ናቸው። ከልቦለድ ደራሲዎቹ ውስጥ የጥንቱ ሆሜርና የቅርብ ዘመኑ ሼክስፒር ምሳሌዎች ናቸው። ከሐዋርያቱ እነ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ነብዩ ሙሐመድ እና መሰሎቹ ዘመንና ቦታ ያልገደባቸው ናቸው። ምን ዓይነት መጻሕፍትን ቢያበረክቱ ነው ስማቸው ከመቃብር በላይ የዋለው?

፪. መጻሕፍት

የጽሕፈት ክህሎትና ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ ታሪክን ሰንዶ ለማስቀመጥ፣ መረጃን ለመለዋወጥ፣ እውቀትን ለማስተላለፍ ወዘተ የሚጠቀምበት መንገድ ነው። የሰው ልጅ አስተሳሰቡንና ተዘክሮቱን ለማስቀመጥ የተለያየ መንገድ ይጠቀማል። ፊደልና የሰዋሰው ሥርዓት ከመፈጠሩ በፊት አስተሳሰቡን በቅርጻቅርጽና በሥዕል መልኩ ያስቀምጥ ነበር። የተለያዩ ህዝቦች የተለያየ የጽሑፍ ባህልና የአጻጻፍ ዘዴ አላቸው። የወረቀት ቴክኖሎጂ ከመምጣቱ በፊት ጽሑፍ ድንጋይ ላይ፣ እንጨት ላይ፣ ፓፒረስ (ከዛፍ ልጥ)፣ በብራና ይቀመጥ ነበር። ኋላ ላይም በወረቀት ጥራዝ፣ በመጻሕፍት መልኩ ሐሳብን ማስቀመጥ ተለመደ። ጽሕፈት በእጅጉ ከተስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የየእለት ክዋኔዎችና ዜናዎች በበራሪ ጽሑፍ፣ በጋዜጣና በመጽሔት መልኩ ካንዱ ወደ ሌላው ይተላለፉ ነበር። እነዚህ በብዛት ወቅታዊ ጉዳዮችንና ወዲያው ተነበው ወዲያው የሚረሱ ዓይነት መረጃዎችን ነው የሚይዙት። ሬድዮና ቴሌቭዥንን ባይተኩም ለመረጃ ልውውጡ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በርግጥ በአጫጭር ገለጻዎች የሚካተቱት የመጽሔት፣ የጋዜጣ ጽሑፎችና የሬድዮና የቴሌቭዥን ንግግሮች ተደምረው ወደ መጻሕፍትነት ሊያድጉ ይችላሉ፣ በዚህ መልኩ የበለጸጉ መጻሕፍትንም አይተናል።

የመጻሕፍት ዓላማና ይዘት ግን ከዚህ ይለያል። ቀደም ሲል በብራና አሁን ደግሞ በወረቀት ገጾች ላይ የሚከተበው ጽሑፍ መጽሐፍ ለመባል ይህ ነው የሚባል መቁረጫ መስመር ባይኖረውም በኔ አስተያየት ግን ከጋዜጦችና መጽሔቶች የሚለይባቸው ዋና ዋና ነጥቦች አሉት። ከነዚህም ውስጥ:-

 ሀ. በዘመንና በቦታ ያልተገደበ አስተሳሰብን የሚያንጸባርቅ ጥልቅ ምርምሮችን የያዘ። ከያዘው ሐሳብ አንጻር ሲታይ የሰውን ስነ ልቡና ቆንጥጦ በመያዝ፣ የሕይወትን ትርጉም፣ የተፈጥሮን ምሥጢር የሚፈትሽና የሚያብራራ አንባቢዎችን የማይመርጥ ሐሳብ የያዘ ጥራዝ ነው። እነዚህ ከልቦለድ እስከ ፍልስፍናና ሳይንስ መጻሕፍትን የሚያካትቱ ናቸው። በይዘታቸው የዘውግ ገደብና የርእሰ ጉዳይ ውሱንነት ሳይኖራቸው ፍካሬ ዓለማትና ንጻሬ ህሊናን ያብራራሉ፣ ይሞግታሉ። የፕሌቶ ሪፐብሊክ፣ የሆሜርና የሼክስፔር ስራዎች በዚህ የሚመደቡ ሲሆኑ አድለር እንዳለው እንደነዚህ ዓይነት መጻሕፍት በብዙ ዓይነት መልኩ ይተረጎማሉ። የባህልና የማኅበረሰባዊ አውዶችን በመሻገር ለሁሉም ሰዎች የመንፈስ መነቃቃትና የእውቀት መፋፋት ግብአት ይሆናሉ።

ለ. በአንድ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ የተካኑ ባለሙያዎች ሐሳባቸውንና ግኝታቸውን የሚያንጸባርቁበት ሙያዊ ሙግትን የሚያብራራ ነው። መጻሕፍት አንድን ርእሰ ጉዳይ በበለጠ ለማስረዳትና በዚያ ርእሰ ጉዳይ ታሪክ የራሳቸውን ምዕራፍ ይይዛሉ። በዚያ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ጥናት የሚያደርግ ሰው እንደ ማጣቀሻ በማገልገል አንዴ ተነበው ብቻ የሚጣሉ ሳይሆኑ በያዙት ሙግት ጥንካሬ ለአድናቆት ወይም ለትችት ሁሌም ራሳቸውን ያጋለጡ የእውቀት ክምችቶች፣ የሐሳብ መወራረሻ፣ የዱላ ቅብብሉ አካላት ናቸው። ባብዛኛው Subject matter based መጻሕፍት ሲሆኑ በትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ለትምህርት ማስተማሪያነትና ማጣቀሻነት ይውላሉ። የነዚህ መጻሕፍት ታላቅነት የሚወሰነው በተነሱበት ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ያካተቱት ታሪካዊ ዳራና በተጻፉበት ዘመን ያሉትን ሙግቶች ባስተናገዱበት አግባብ ነው።

 ሐ. የፖለቲካ፣ የባህልና የሃይማኖት ርዕዮተ ዓለማትን የያዙ የአንድን ማኅበረሰብ የአስተሳሰብ መካዘን ለሌላው የሚያስተላልፉ ዓይነት መጻሕፍትም አሉ። ዓላማቸው አንድን ሐሳብ በባለቤቶቹ ዘንድ እንዲሰርጽ ማድረግ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ወደ ማኅበረሰቡ አዲስ የሚቀላቀሉትን ለመስበክ እንደመመሪያ ያገለግላሉ። መጽሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርዓን እንዲሁም እነርሱን ለማብራራት በእምነቱ መምህራን የሚጻፉት መጻሕፍት በዚህ ምድብ ይካተታሉ። ባብዛኛው እምነትንና የአንድን ማኅበረሰብ ሥነ-ልቡናዊ አባልነት መሠረት ያደረጉ ስለሆኑ በምክንያት መሞገት ወይም በቀላሉ ማጣጣል አይቻልም። ሕይወትን በምሉዕነት ለመግለጽ በሚያደርጉት ጥረትም የራሳቸው ዶግማና ቀኖና አላቸው። ለሁሉም ነገር መልስ ለመስጠት ሙከራ ከማድረጋቸውም በላይ ተዓምራዊነትንና ልዕለ ተፈጥሮ ኃይልን እንደ አጋዥ የመሞገቻና የማሳመኛ ምርኩዝ ስለሚጠቀሙ እነዚህን መጻሕፍት በቀላሉ ማጣጣልም ሆነ በሙሉ ልብ ለመቀበል ከባድ ይሆናል። ቢሆንም መጻሕፍቱ ይዘውት ከተነሱት መሠረታዊ የሰው ልጆች ጥያቄና ጥያቄውን ለመመለስ ከሚከተሉት መንገድ አንጻር መጻሕፍቱን ከድንቅ መጻሕፍት ምድብ ያስመዘግባቸዋል።

መ. የሥነ ልቡና ምክረ ሐሳብን የያዙ መጻሕፍት። እነዚህ ደግሞ ከሰው ልጆች ስነ ልቡናዊ ችግር ጋር በተያያዘ በአብዛኛው የሰው ልጅ ተግዳሮቶች መንስኤዎችና መፍትሔዎች ላይ መላ ምት ያቀርባሉ። ከሰዎች የተናጠል ተሞክሮ በመነሳት ስለአጠቃላዩ የሰው ልጆች ሁለንተናዊ ሥነ-ልቡናዊ ውቅር የሚያትቱ መላምቶችን ይተነትናሉ፣ ያብራራሉ። ስሜትን ለመረዳት፣ የስሜት ነጸብራቆችን ለውጦች ለማስተናገድ እንዲሁም ሥነ-ልቡናዊ ህውከቶችን በመተንተን የመፍትሄ መንገዶችን  የሚጠቁሙ ናቸው።

ሠ. ተግባራዊ መመሪያዎች ላይ መሠረት ያደረጉ። አስተዳደር፣ የልጅ አስተዳደግ ወይም የንግድ ሥርዓት ላይ ወዘተ ሙያዊ ማብራሪያ ወይም የተሻለ መላምት የሚያቀርቡ መጻሕፍት ናቸው። መነሻቸው ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ሳይንስ፣ ሥነ-ልቡና፣ ባህልና ማኅበረሰባዊ ትውፊት ወይም የሕግ መሠረት ያለው ሆኖ ለተግባራዊ እርምጃዎች በቀላል ቋንቋ ይቀርባሉ። ትእዛዝና ብያኔ የያዙ ቢሆኑም ጭፍንና አስገዳጅ ሳይሆን በምርምርና ጥናት ላይ የተመሰረተ ስለሆነና እንደየሁኔታው የሚሻሻሉ ሲሆኑ መጻሕፍቱን ከድንቅ መጻሕፍት ተራ ያሰልፋቸዋል። ከላይ

“ሁሉም ባይባልም የማይናቅ ቁጥር ያላቸው የዘመናችን ጸሐፍት በገንዘብ ፍላጎት ወይም ባነገቡት የርዕዮተ ዓለም ፈረስ የሚነዱ እንደሆኑ መታዘቡ ቀላል ነው። መጽሐፎቻቸውም ጥሩ አንባቢን የሚገፈትሩ፣ የዘመንና የቦታን ድንበር የማይሻገሩ፣ የቋንቋን ካብ መናድ የማይችሉ እውቀት ገላጮች ሳይሆኑ ስሜትን ቀስቃሾች ናቸው”

የተዘረዘሩትን ልዩ ልዩ መጻሕፍት አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ባሕርይ የዘመንና የቦታን ገደብ ተቋቁሞ ሊሻገር የሚችል ሐሳብ መያዛቸው ነው። ከጥቃቅን የየለት እንቅስቃሴዎች ጀምሮ እስከ ልዕለ ተፈጥሮ (እግዚአብሔር፣ አላህ) ባህርያት ድረስ የሚተነትኑ ሲሆን የሚያነባቸውን ሰው ሐሳብ ሰቅዘው በመያዝ የሰውን ልጆች የእውቀት ጉጉት ለማርካት በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከቋንቋ ገደብ ውጭ አንባቢን የማይለዩ ሲሆን አንድ ጽሑፍ ለአቅመ መጽሐፍ ደርሷል ማለት እንችላለን። ስለ ድንቅ መጻሕፍት የአድለርን አስተያየት በማስቀመጥ እናጠቃልል:-

 “Great books are those that contain the best materials on which the human mind can work in order to gain insight, understanding and wisdom. Each in its own way raises the reccurent basic questions which men must face. Because these questions are never completely solved, these books are the sources and monuments of a continuing intellectual tradition.

 …. They are the rare perfect acheivments of sustained excellence. Their beauty and clarity shows that they are masterpieces of the fine as well as the liberal arts. Great books … transcend the provincial limits of their origion. They remain as world literature. They must pass the test of time.”

ከዚህ በተጨማሪ እንደ አድለር አገላለጽ ድንቅ መጻሕፍትን ሁሉም በቀላሉ ሊያነባቸው አይችልም። ምክንያቱም ከያዙት ሐሳብ ክብደትና ከሙግታቸው ጠጣርነት የተነሳ የሰዎችን ትዕግስትና የማሰብ ምጥቀትን ስለሚጠይቁ ነው። በርግጥ የመጻሕፍቱ ድንቅነት ለሁሉም በቀላል ቋንቋ ከመቅረባቸው ይመነጫል። ከባዱን ነገር በቀላል አቀራረብ መያዛቸው መጻሕፍቱን ድንቅ ያደርጋቸዋል።

የያዙት ርእሰ ጉዳይ ግን ማንኛውም “ተራ ሰው” አንብቦ ከሚረዳው በላይ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የተነሱበትን ርእሰ ጉዳይና ያነሷቸውን ጥያቄ በእርግጠኝነት እና የመጨረሻውን መልስ በመመለስ አይቋጩም። ይልቁን እንድናስብ፣ እንድንመራመርና በርእሰ ጉዳዩ ላይ እንድንከራከር ወይም እንድንወያይ ህሊናችንን የመቀስቀስ ሚናን ይጫወታሉ። ከዚህ ውጭ ስሜትንና ያንድ ቡድን ወቅታዊ አጀንዳ፣ የጥላቻና ሌሎቹን የማጥፋት እቅድ፣ የቂም በቀል ዶሴ አጭቀው የያዙትን የወረቀት ክምሮች “መጻሕፍት” ናቸው ለማለት አያስደፍርም። እንደዚህ ዓይነቶቹን ነው በመግቢያዬ ላይ ሽፋናቸውን አይተን መገምገም እንችላለን ያልሁት። ታዲያ ምን ልንላቸው እንችላለን?

 ፫. አንባብያን

ጥሩ መጽሐፍና መልካም ደራሲ ካለ ጥሩ አንባቢም ሊኖር ግድ ይላል። ገበሬው በደንብ ካረሰ፣ በሬው እና የእርሻው እቃ በደንብ ከገጠሙ መሬቱ ልሞ መልካም እህል ይሰጣል። ያ ካልሆነ ድንጋይ ላይ የበቀለ ሰብል መሆኑ ነው። በተመሳሳይ የተጻፈው ጽሑፍ ጥሩ አንባቢ ካላገኘ ሐሳቡ አየር ላይ እንደተበተነ ይቀራል ማለት ነው። ጸሐፊነት ፊደልን ቆጥሮ ብእርና ወረቀትን አገናኝቶ መጫር አይደለም ብለናል። አንባቢነትም ፊደላትንና ቃላትን አገጣጥሞ አረፍተ ነገርን ማነብነብ አይደለም። ይህንን ብዙ አንባቢ ልንለው እንችላለን። በዓመት ውስጥ ያነበባቸውን መጻሕፍት ዝርዝር ከመቁጠር በዘለለ ያነሱትን ርእሰ ጉዳይ የሚዘነጋና በርሱ የእውቀት ሕይወት ላይ ቅንጣት ታክል ለውጥ ያላሳየውን አነብናቢ ከጥሩ አንባቢ ጎራ መመደብ አይቻልም። ጥሩ አንባቢነት የራሱ የሆኑ መስፈርቶች አሉት። አንባቢነት የራሱ የሆኑ ኃላፊነቶችን የያዘ ነው። ከነዚህ ውስጥ:-

 1. ያነበበውን ተረድቶ ለሌሎች ማስረዳት (መምህርነት) ወደሌላ ቋንቋ መተርጎም፣ የከበደውን ሐሳብ መተንተን፣ ማፍታታት፣ ጽሑፉን መዳሰስና በቀላል ቋንቋ ለሌሎች ማስተላለፍ የሚችል። ጥንታዊው ሮማዊ ተርጓሚና ደራሲ ሲሴሮ (ችቸሮ) በጥሩ አንባቢነቱ የሚጠቀስ ነው። የጥንታዊያኑን ግሪካውያን አሪስጣጣሊስና ፕሌቶን ፍልስፍናዎች ወደ ላቲን ቋንቋ በመተርጎም ከመጥፋት የታደጋቸው ብቻ ሳይሆን አውዳዊ ተግባራዊነት እንዲኖራቸው ነፍስ የዘራባቸውም ጭምር ነው። በመካከለኛው ዘመን እነዚህን ድርሰቶች የዓረብ ፈላስፎች ወደ ዓረቡ ዓለም አስፋፍተዋቸዋል። የፍልስፍና አምላክ ሲሴሮን ያክል ታላቅ አንባቢ ባያስነሳ ኖሮ የግሪኮቹ ፍልስፍና ተረት ተረት ሆኖ በቀረ ነበር።

 2. መተቸት ወይም መሞገት (ሐያሲነት) በሚነበበው ጽሑፍ ውስጥ ዝንፈቶች፣ ተቃርኖዎችና እኩይ ዓላማዎችን በማጋለጥ ለእውነት ዘብ የመቆም ድፍረትን ይይዛል፤ አንባቢ ተች (ስህተት ፈላጊ ብቻ ሳይሆን የሚደነቀውን የሚያደንቅ የሚነቀፈውን የሚነቅፍ፣ ለሐሳብ መሻሻልና መበልጸግ ዘብ የቆመ) መሆን አለበት። ያነበበውን ሐሳብ በመሞገት አማራጭ ሐሳብን ይዞ መቅረብ መቻል አለበት። አሪስጣጣሊስ የጥንት የግሪክ ፈላስፋ ነው። ከፕሌቶ እግር ቁጭ ብሎ ከተማረ በኋላ “ዲግሪውን” ሲይዝና ሲመረቅ ከፕሌቶ የተለየ አማራጭ ፍልስፍናን ማራመድ ሲጀምር እንዲህ በማለት ነው:- “ፕሌቶ የተከበረ አስተማሪዬ ነው፣ እውነት ግን እጅግ የተከበረች ናት።” በማለት “አፈንጋጭ” ሐሳብን ይዞ መጣልን። እናም የአውሮፓን ፍልስፍና ሁለት ዓምድ ሆነው በሁለት እግሩ ያቆሙት ይኸው የመምህሩና የደቀ መዝሙሩ ተቃራኒ ሐሳቦች ናቸው። አሪስጣጣሊስ ተች አንባቢ ነው። ኢትዮጵያዊ ዘርዓ ያዕቆብም በኦርቶዶክስ አስተምህሮ እስከ መጨረሻው እርከን የተማረ ሊቅና በቤተ ክርስቲያኗ ባህል መሠረት ወንበር ዘርግቶ ማስተማር የጀመረ ነበር። ኋላ ላይ የፍልስፍናውን ዓምድ ለማቆም የበቃው በተች አቀራረብ ለእውነት ዘብ የቆመ በመሆኑ ነው።

የሀገራችን ሰዎች

“በእግዚአብሔር ረድኤት ጥበበኞች እንዲሆኑና እውነትንም ወደማወቅ እንዲደርሱ እኔ የጀመርሁትን አንተ ፈጽመው። ሐሰትን እንዳያምኑ፣ ዐመጻንም ተስፋ እንዳያደርጉ ከከንቱ ወደ ከንቱ ፈጽመው እንዳይሄዱ እውነትን ይወቁ እንጂ ወንድሞቻቸውንም ይውደዱ። እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጉት፣ ከንቱ በሆነው ሃይማኖታቸው ከእንግዲህ ወዲህ አይጣሉ”

  3. ከዚህ በተጨማሪ የዓላማ ቀጣይነትን ኃላፊነት መሸከም (ድልድይነት) የሚችል ነው ጥሩ አንባቢ። አንድ አንባቢ የተጀመረው ሐሳብ አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ እንደ ዘመኑና ዓውዱ በመረዳት የጎደለውን በመጨመር ሐሳቡ ምሉዕና ወደፊት ቀጣይ እንዲሁም ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል። አንባቢነት ከትናንቱ ጸሐፊ የዛሬው አንባቢ ለነገው ትውልድ የሚያስተላለፈው የተወጠነ ጅማሮን ወይም የተቆረጠ ሐሳብን የማስቀጠል ኃላፊነትን ይጠይቃል።

ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ለደቀ መዝሙሩ ይህንን የጥሩ አንባቢ ሚና በሚከተለው መልኩ ገልጾታል። “ከእኔ በኋላ የሚመጡት እንዲያውቁኝ ግን ይህንን እስከ ሞቴ ድረስ በእኔ ዘንድ ተደብቆ የኖረውን እጽፍ ዘንድ ወደድሁ። ከሞትሁ በኋላ አስተዋይና ተመራማሪ ሰው ቢገኝ ከእኔ ሐሳብ ላይ ሐሳቡን ይጨምርበት ዘንድ እለምነዋለሁ።… የሀገራችን ሰዎች በእግዚአብሔር ረድኤት ጥበበኞች እንዲሆኑና እውነትንም ወደማወቅ እንዲደርሱ እኔ የጀመርሁትን አንተ ፈጽመው። ሐሰትን እንዳያምኑ፣ ዐመጻንም ተስፋ እንዳያደርጉ ከከንቱ ወደ ከንቱ ፈጽመው እንዳይሄዱ እውነትን ይወቁ፤ ወንድሞቻቸውንም ይውደዱ። እስከ ዛሬ ድረስ እንዳደረጉት፣ ከንቱ በሆነው ሃይማኖታቸው ከእንግዲህ ወዲህ አይጣሉ።”

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ማኅበራዊ ትችት፣ የእውነትና የጥበብን አስፈላጊነት፣ ለመጭው ትውልድ ማሰብን፣ የሰዎች ስምምነትንና ህብረትን በጠቅላላው በትውልዶች መካከል የመንፈስ ትስስርን ለመፍጠር የሚደረግን ጥረት እናያለን። መልካም አንባቢም ይህንን የመንፈስ ትስስርና ባንድ ዘመን በሚኖሩ “በባህልና በሃይማኖት ልዩነት” በሚጋጩ ወንድማማቾች መካከል ሕብረትን የሚያሰፍን ሐሳብን ለማስቀጠል ካነበበው ለህዝቡ የሚያካፍል እንደሆነ ያሳየናል። ጥሩ አንባቢ እንግዲህ ትናንትን ከዛሬ የሚያገናኝና ወደ ነገ የሚሸኝ መልካም ድልድይ ነው። ይህም ብቻ አይደለም። የዛሬ ጥሩ ጸሐፊ የትናንት ጥሩ አንባቢ እንደሆነ ሁሉ፣ የዛሬ ጥሩ አንባቢም የነገ ጸሐፊም ጭምር ነው። ስለዚህ ጥሩ አንባቢ ማለት በሚያነበው መጽሐፍ ውስጥ ይዘቱን ብቻ ሳይሆን የአገላለጽን ብልሃት፣ የቋንቋን አጠቃቀም፣ የሙግትን አሰዳደር መማር የሚችል ነው።

 ከላይ የተነሱ ነጥቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም ባይባልም የማይናቅ ቁጥር ያላቸው የዘመናችን ጸሐፍት በገንዘብ ፍላጎት ወይም ባነገቡት የርዕዮተ ዓለም ፈረስ የሚነዱ እንደሆኑ መታዘቡ ቀላል ነው። መጽሐፎቻቸውም ጥሩ አንባቢን የሚገፈትሩ፣ የዘመንና የቦታን ድንበር የማይሻገሩ፣ የቋንቋን ካብ መናድ የማይችሉ እውቀት ገላጮች ሳይሆኑ ስሜትን ቀስቃሾች ናቸው። አንባቢዎቻቸው ደግሞ ሐሳቡን ቀድመው የሚያውቁት እንዲሁ ለጸሐፊዎቹና ለሚያራምዱት ሐሳብ በቲፎዞነት ቅድሚያ የሚሰለፉቱ ናቸው።

የመልካም ማኅበራዊ መስተጋብርና ምክንያታዊ ማኅበረሰብ ግንባታ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ቢሆንም የመጻሕፍቱ ዓለም ለዚህ ዓላማ አንዱ ግብረ ኃይል ነው። በዚህም የአንድን ማኅበረሰብ ስልጣኔና መልካም ተግባቦት ለማረጋገጥ የመጻሕፍቱ ጥራት፣ የጸሐፊዎቹ ጠቢብነትና የአንባብያኑ ብስለት የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዘመናችን መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው ድንቅ መጻሕፍት? የሚለውን ለአንባቢ በመተው በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ከተጻፉ ታላላቅ ድርሰቶች ውስጥ የትኞቹ ዘመን ተሻጋሪ እንደሆኑ የተመረጡ መጻሕፍትን በመዳሰስ ለመተንተን እሞክራለሁ። ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top