አድባራተ ጥበብ

ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ማን ናቸው

በዓለም የአስተሳሰብ እድገት ታሪክ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች ጥረቶቻቸውና ሐሳቦቻቸው ወደ ቀጣዩ ትውልድ ወይም ወደሌላው የዓለም ማኅበረሰብ እንዲዳረሱ ጥረት ይደረጋል። በአውሮፓውያን የትምህርት ባህል የሊቆቻቸውን ሥራዎች በመተንተን፣ በመተርጎም፣ በመሞገት፣ በማሻሻል ወዘተ ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ አንዱ የምሁራን ግዴታ ነው። የበርካታ ፈላስፎችና የጥበብ ሰዎች ሥራዎች የጊዜንና የቦታን ድንበር የሚሻገሩትበተከታዮቻቸው አስተዋጽኦ ነው።

ይህ ባህል በኛ አገር ብዙም የተለመደ አይደለም። ጭራሹን አይታወቅም ባይባልም የሚጠበቀውን ያህል አልዳበረም። እንዲያውም አሞግሶ ከመጻፍ፣ መልካም አሳቦችን እንዲቀጥሉ ለአንባቢው ተደራሽ ከማድረግ ይልቅ መተቸትና ማጣጣል ይቀናናል። ይህ ሲሆን ደግሞ መወቃቀስና መጠቋቆም እንጅ አብሮ መበልጸግ፣ በሐሳብ መፋፋት እና የሥልጣኔ ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም። የጋራ ተግባቦትን በመናድ የኋላ ቀርነት ሕይወትን መምራት እጣ ፈንታችን እስኪመስል ድረስ እየገጠመን ያለው እክል አንዱ መንስኤም ያለፈን በጎ ነገር ከማሞገስ ይልቅ ሙት ወቃሽነታችን ስለሚያይል ይመስለኛል። ከሃይማኖታዊ አስተምህሮና ከባህል መወራረስ ውጭ አካዳሚያዊ፣ ፍልስፍናዊና አዲስ አስተሳሰቦች ቀጣይነት ሳይኖራቸው ከጀማሪው ትውልድ ብዙም ሳይሻገሩ ጫጭተው ይቀራሉ። ለዚህም ምስክሮችን መጥቀስ ይቻላል። በጥንት ጊዜ የውጭ የፍልስፍና ሥራዎችን ወደ ግዕዝ የመተርጎም ባህሉ በነአባ ሚካኤል ዘመን 16ኛውን ክፍለ ዘመን ብዙም የተሻገረ አይደለም። በኢትዮጵያ የፍልስፍናና የአስተሳሰብ ተራማጅነት ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱት የደቂቀ እስጢፋኖስ ገድል ከተቀበረበት የተነሳው ከ600 ዓመታት በላይ ዘግይቶ ነው፤ የፈላስፋው የዘርዓ ያዕቆብ አስተምህሮ ከደቀ መዝሙሩ በኋላ ዘመንን ተሻግሮ እንዲቀጥል ዱላውን የተቀበለው የለም። የአውሮፓውያንን ሥልጣኔ ታዝበው ወደ አገራቸው ለማስገባት ሙከራ ካደረጉ ቀደምት ልሂቃን ውስጥ በቅድምና የሚጠቀሰው የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ትችቶች አሁንም ድረስ ሰሚ ጆሮና አስተዋይ ልቡና ያገኙ አይመስልም።

በሳይንሱ በኩል ከአገር በቀል እውቀት ሳይንሳዊ ፈጠራ ያስገኘውን የዶክተር አክሊሉ ለማን ፋና የተከተለ ኢትዮጵያዊ መኖሩን አልሰማሁም። በፖለቲካ ረገድ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ፋና ወጊ የነበረው አጼ ቴዎድሮስ በወቅቱ የሚረዳው ባለማግኘቱ መጨረሻው ጥፋት ሲሆን ከሱም በኋላ የመጡት ምኞቱን የተረዱለት አይመስልም። አገር በቀል የሆነውን እውቀት ከዘመናዊው ሳይንስ ጋር ለማዋኃድና ለማስታረቅ ሙከራ ሲደረግ አይታይም። በተቃራኒው የዘመናችን ትምህርት የውጭውን በመሸምደድ ላይ የተጠመደ፣ አምልኮ አውሮፓዊነት ላይ ሙጥኝ ያለ እስኪመስል ድረስ ለባህሉ እንደሚመጥን ተደርጎ ባለመተርጎሙ ጥፋቱ እንደሚያይል የማርክስና ሌኒን ፍልስፍናን እንደወረደ ለመተግበር መሞከሩ ያመጣውን ጥፋት መገንዘብ ይቻላል።

እነዚህ ምሳሌዎች የሚያሳዩን በትምህርት ባህላችን ላይ አንዳች ክፍተት እንዳለ ነው። ለምንኖርበት ዘመንና ለመጭው ትውልድ መልካም ሕይወት እና የሥልጣኔ መንገድን ለመቀየስ በትውልዶች እና በባህሎች መካከል መልካም

“የጋራ ተግባቦትን በመናድ የኋላ ቀርነት ሕይወትን መምራት እጣ ፈንታችን እስኪመስል ድረስ እየገጠመን ያለው እክል አንዱ መንስኤም ያለፈን በጎ ነገር ከማሞገስ ይልቅ ሙት ወቃሽነታችን ስለሚያይል ይመስለኛል”

ተግባቦት እንዲፈጠር መደላድል ማበጀት የትምህርት ተቋማት ተቀዳሚ ዓላማና የምሁራን ኃላፊነት ነው። በኛው አገር የትምህርት ታሪክ ይህንን ነገር አናስተውለውም። በዘመናችን ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ “የለውጥ ፋና ወጊዎች በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ በእንግሊዝኛ ያሳተመው መጽሐፍ ሊመሰገን ይገባዋል። የአስተሳሰብ ምህዋራችንን የሚዘውሩና የዘመኑን መንፈስ በደንብ ተረድተው የመንፈሱን የአነፋፈስ ፍጥነትና አቅጣጫ ለማስተካከል ጥረት የሚያደርጉትን የዘመን ፈርጦች መዘከር፣ የተከተሉትን መንገድ በጎነቱንና ክፍተቱን መመልከት፣ መልካም ሐሳባቸው ቀጣይነት እንዲኖረው የብርሃን ችቦውን ተቀብሎ ወደፊት መግፋት ያስፈልጋል። ያ ካልሆነ ሊቁ እጓለ እንደሚሉት የነፈሰው ንፋስ እያላጋ መንፈሳቸውን የሚረብሻቸው፣ የአቅጣጫ መጠቆሚያቸው የጠፋባቸው በእውር ድንብር የሚጓዙና ምንም ሳያደርጉ የሚያልፉ የመከነ ትውልድ አባላት መፈጠራቸው አይቀሬ ነው።

 ዘመን የራሷን መድኃኒተኞች እንደምትፈጥር ሁሉ ያንን ተገንዝበው አሁንን በጥልቀት ነገን በርቀት መመልከት የሚችሉ ታዳጊዎችን ማግኘት ይቻላል። እነዚህን የዘመን ፈርጦች ሊቁ “ሕመምተኞች” ይሏቸዋል። “የልቡና ግለት ያላቸው፣ የመፍጠር የማስገኘት ካሁኑ ድንበርና ወሰን የማለፍ ፍቅርና ወይም ብርቱ ሥሜት ያላቸው ሰዎች ባገኘች ጊዜ ዘመን መልካም ወላድ ሴት ነች። የሊህ ጀግኖች ምኞት እንደ ሕመም ማለት ነው። ቅስፍ አድርጎ ይይዛቸዋል። የነዚህን ሰዎች [passion] ሕመም እንበለው። ያለ ሕመም በዚህ ዓለም አንዳች ትልቅ ነገር አልተፈጠረም።” (1956፣ ገጽ 42)። እነዚህ ሕመምተኞች ከዘመኑ ችግር ነጻ የሚያወጣንን ሐሳብ እህ ብለው አምጠው የሚወልዱት ናቸው። በቁጥር ብዙ ባይሆኑም ዘመኑን በመወከል ግን ከመንጋዎች በላይ ከፍ ብለው የሚታዩ ተምሳሌታዊ ወኪሎቻችን ናቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ፈርጦች የሚያፈልቋቸው ሐሳቦች ዘመን ተሻጋሪ፣ የቦታ ገደብ የማይበግራቸው በሰዎች ሁሉ ልቡናና ሕሊና የተደላደለ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው።

 በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ ውስጥ በባህላዊውም በዘመናዊውም ትምህርት ተኮትኩተው ካደጉት ውስጥ ለዛሬ ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስን መርጫለሁ። በዚህም አጭር የሕይወት ታሪኩን በመዳሰስ ከጻፋቸው ሁለት መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ ዘመን ተሻጋሪና ለወቅታችን ሁኔታ ጠቃሚ የሚሆኑትን ሐሳቦች እየመዘዝሁ ለመተንተን እሞክራለሁ። ሊቁ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ብዙ የተዘነጋ ሊቅ ነው። የግል ሕይወቱ በሰፊው ባይጻፍልንም እንዲሁ በየቦታው የተጻፉ አጫጭር ጽሑፎች እንደሚገልጹልን በእውቀት ፍቅር የነደደ፣ በሰብአዊነት ሥሜት የተመሰገነ፣ አገር ወዳድ ሊቅ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በጻፋቸው መጻሕፍቱ ውስጥ ደግሞ የአስተሳሰብ ልሕቀትንና ጸባየ ሠናይነትን በሰዎች ላይ ለመዝራት ሳይታክት የሚታትር እንደሆነ ያሳያል። ለመሆኑ እጓለ ማን ነው? የጻፋቸው ጽሑፎቹስ የሐሳብ ማጠንጠኛቸው ምንድን ነው? ተደራስያኑስ እነማን ናቸው? የሚሉ ዓበይት ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይታችንን እንጀምረው። በሚቀጥሉት ክፍሎች ስለ ግል ሕይወቱ እና ስለጻፋቸው ሁለት መጻሕፍት (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ 1956 ዓ.ም እና ብጹዓን ንጹሐነ ልብ፡- የክርስትያን ሥነ-ምግባር መሠረት 1983 ዓ.ም) ይዘት ፍልስፍናዊ ዳሰሳና ትንተና ተደርጓል። የሊቁን ሐሳብ በመቻኮልና በማሳጠር እንዳንበድለው ሰፋ ያለ ዳሰሳ ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል። ዋናው ቁም ነገር አንባቢውን ከመጽሐፎቹ ጋር ለማስተዋወቅና የሊቁን ፍልስፍናዊ አቀራረብ በሙያዊ አተያይ ለመተንተን ስለሆነ ለውይይት መነሻ የሚሆን ሐሳብ ነው የቀረበው።

 1.አጭር የሕይወት ታሪክ

በዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ጥልቅ ምርምርና ጥናት ተደርጎ የተጻፈ የተሟላ ሐተታ አልገጠመኝም። በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ዓውደ ሰብ” በተሰኘ መርሐግብሩ ላይ ስለ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሕይወትና አስተሳሰብ ጥሩ ዝግጅት አቅርቦ ተመልክቻለሁ። ስለ ሕይወቱ በተወሰነ መልኩ ተሰንዶ ያገኘሁት መረጃ በዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ የተጻፈው አጭር የሕይወት ታሪኩን ነው። ዶክተር ሥርግው አጭር የሕይወት ታሪኩን “ብጹዓን ንጹሐነ ልብ: የክርስቲያን ሥነ-ምግባር መሠረት” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንደገለጹልን (ገጽ 166-170) በየካቲት 6 ቀን 1924 ዓ.ም ከአባቱ መምሬ ገብረ ዮሐንስ ተሰማና ከእናቱ ከወይዘሮ አመለወርቅ ሀብተ ወልድ በአዲስ አበባ ተወለደ። በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት ድረስ ከተማረ በኋላ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ወንበር ዘርግተው ያስተምሩ ከነበሩት መሪጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘንድ ዜማና ድጓን ተምሯል። በቅድስት ስላሴ ትምህርት ቤት አስኮላውን በመከታተል እስከ ስምንተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ በ1943 ወደ ግሪክ አገር ሄዶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። የማንበብ ፍቅሩ የመጻሕፍት ቀበኛ ወይም ሱሰኛ እንዲሆን አድርጎታል። በተለይ ለፍልስፍና የተለየ ፍቅር ነበረው። ይህም ኋላ ላይ በመጽሐፎቹና አስተሳሰቦቹ በስፋት ተንጸባርቋል። እጅግ ንግግር አዋቂ እንደነበረም የተመሰከረለት ነው። ለትምህርት የነበረው ፍቅርም የተመሰከረለት ነው። “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘው መጽሐፉ እራሱ እንደሚነግረን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እውቀቱን ከፍ ሊያደርግለት በሚችል ተግባር ላይ የተጠመደ ነበር። “እንደ እድል ሆኖ በአቴናም በጀርመን አገርም በት/ት ቤት በነበርኩ ጊዜ በርግጥ የሚያኮሩ ጓደኞች ነበሩኝ። ከነርሱ ጋር በመወዳደር፣ በመፎካከርና በመከራከር በየጊዜው እየተሻሻለ ከሚሄድ የእውቀት ጎዳና የደረስኩ ይመስለኛል።” (ገጽ 10)

ይህንን የእውቀት ጉጉቱንና የፍልስፍና ፍቅሩን ለማርካትም በጀርመን አገር ቦን ዩኒቨርሲቲ ከታላላቅ መምህራን የፍልስፍና ትምህርትን መከታተል ጀመረ። ባገኘው አጋጣሚ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ እንደ ሃይዲገር እና ያስፐርስ ያሉ ታላላቅ የፍልስፍና መምህራንን ትምህርት ካሉበት ድረስ እየተጓዘ ተከታትሏል። ሥራው ላይ እንደተስተዋሉት ከቀደምቶቹ ፈላስፎች ለፕሌቶ የተለየ ፍቅር ሲኖረው ጀርመናዊው ኢማኑኤል ካንት እና ሄግልም በሥራዎቹ ላይ ጫና እንዳሳደሩ ይስተዋላል። ከባለ ቅኔዎቹ ዳንቴን፣ ጆሴፍ ቮን አይሸንዶርፍን፣ ሽለርንና ዮሐን ዎልፍጋንግ ቮን ጎቴን ይወድ እንደነበር ሥርግው ይነግረናል፣ በጽሁፎቹም ውስጥ ከሥራዎቹ ቀንጨብ አድርጎ ተርጉሞ አስነብቦናል። ግጥም ወዳጅ እና ራሱም ገጣሚ መሆኑ፣ በግጥሞቹም ላይ የነዚህ ባለ ቅኔዎች የአጻጻፍ ስልት ተንጸባርቋል። ክርክርና ውይይትን አብዝቶ የሚወደው ሊቁ በክርክር ወቅት ቁጣን በማስወገዱ እና ሲቆጡም አለሳልሶ ወደ በጎ የክርክር መንፈስ በመመለስ ሃሳብንና የሐሳቡን ባለቤት ለይተን መመልከት እንዳለብን አርአያ ይሆን እንደነበር አጭር ታሪኩን የጻፈልን ስርግው ይመሰክራል።

 በቦን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ለማስተማር እና ለትምህርት ዘዴ ከፍ ያለ ጉጉት ስለነበረው የእንግሊዝኛ እውቀቱን ለማጎልበት በርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ ከቆየ በኋላ በ1953 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። በቅድስት ሥላሴ የፍልስፍና መምህር ሆኖ እያገለገለ በሬድዮም አስተሳሰቡን ለህዝብ ያሰማ ነበር። ራሱም እንደሚነግረን የነዚህ ንግግሮች ስብስብ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚል ርእስ በ1956 ዓ.ም በመጽሐፍ መልክ ለመታተም በቅቷል። “በኢትዮጵያ ሬድዮ “መምህር አብራራው” በመባል የሚታወቀውን ፕሮግራም ስያሜውን የሰጠና ፕሮግራሙን የጀመረ” ዶክተር እጓለ መሆኑን ስርግው ይነግረናል። “በዚህም በኢትዮጵያ አስተሳሰብና በምዕራብ አስተሳሰብ መካከል ድልድይ ሠርቷል።” (ገጽ 169)።

 ሊቁ ዘመናዊ ትምህርት ካፈራቸው አዋቂዎች በቅድሚያ ከሚጠቀሱት ጎራ የሚመደብ ነው። ከ1956-1970 በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዋና ጽሐፊነት፣ በአማካሪነት እንዲሁም በመምሪያ ኃላፊነት አገልግሏል።ሚያዝያ 8 ቀን 1964 ዓ.ም ከወይዘሮ እህትአፈራሁ ተስፋዬ ጋር በቁርባን ተጋብቶ ሦስት ልጆችን ማፍራት ችሏል። ከሕዳር እስከ ሰኔ 1970 ደግሞ በበርሊን የኢትዮጵያ ኢምባሲ አማካሪ ሆኖ አገልግሏል። በ1972 ጡረታ የወጣ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተራኪው ይነግረናል።

በ1983 ዓ.ም ባደረበት ሕመም ምክንያት በአዲስ አበባ እና በናይሮቢ ሕክምናውን የተከታተለ ቢሆንም መጋቢት 23 ቀን በዚያው ዓመት በናይሮቢ አርፎ ቀብሩ በመጋቢት 26 ቀን 1983 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

 ከላይ በጠቀስኩት ወደ አንድ ሰዓት የሚጠጋ ባለ ሁለት ተከታታይ ክፍል የቴሌቭዥን ዝግጅት ላይ ስለ እጓለ የግል ሕይወት፣ አስተሳሰቡ፣ ዓላማዎቹና ሥራዎቹ ጥሩ መነሻ የሚሆን መረጃ እናገኛለን። ከዚህ ውስጥ ትምህርት ወዳድነቱ፣ ስለ እውቀቱ ምንጭ፣ ከዘርፉ ምሁራን (ከፍልስፍናና ነገረ መለኮት ሊቃውንት) እንዲሁም ከአብሮ አደጉ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ስለ እጓለ የተሻለ ግንዛቤን ይሰጠናል። ጥሩ ንግግር አዋቂው ሊቅ፣ የነገረ መለኮት፣ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የሥነ- ጽሑፍና የሥነ ትምህርት ፍቅር ነበረው።

1 Comment

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top