አድባራተ ጥበብ

የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል የ ዓመታት ጉዞ 18

በመስከረም/ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም እትማችን ከአንጋፋዋ የጥበብ ሰው ከዓለምፀሃይ ወዳጆ ጋር ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል። በዚሁም ወቅት የዓለምፀሃይ የመድረክ ህይወትና የመሪነት አስተዋጽኦ የሚገለጥበትን፣ በተለይም በስደት ዓለም የተጋችበትን የጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል ራሱን አስችለን እንደምንመለስበት ቃል መግባታችን አይዘነጋም። በዚህም መሰረት ስለማዕከሉ እንቅስቃሴዎች ያጠናቀርነውን ጽሑፍ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

በነሐሴ ወር 1993 ዓ.ም. በአሜሪካዋ የዋሺንግተን ከተማ የተመሰረተው ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም 18ኛ ዓመቱን በደማቅ ሥነ ሥርዓት አክብሯል። በታዋቂዋ የመድረክ ባለሙያ ዓለምፀሐይ ወዳጆ ፋና ወጊነት በግጥም ንባብ የጀመረው ይህ ማዕከል ዛሬ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ከባህላቸውና ከታሪካቸው ጋር የሚያገናኝ ሁነኛ መድረክ ሆኗል። ገጣሚ ቴዎድሮስ አበበ የማዕከሉን አስተዋጽኦ ከገለጸበት ሥራው የሚከተሉትን ስንኞች እናገኛለን።

 የጽሑፍ የጥበብ ጮራ፣ ልባችንን እንዲያሞቀው

 የቋንቋችን ፊደል ቅኔ፣ ገጻችንን እንዲያደምቀው

የእኛነታችንን ምጥቀት

 የግኝታችንን ጥልቀት

 የሥነ ቃል ውርሳችንን ግዙፍነት፣ ክቡርነት

የኢትዮጵያን ቅርስ ጸጋ፣ የታሪኳን ስፋት፣ ግዝፈት . . .

እንድናስብ እንዳንረሳ፤ እንድንማር እንድናውቀው

 የስደት ዘመን ጉዟችን፤ የአበው ድምፅ እንዳይርቀው

አጉል ባህል እንዳይሰርቀው

 ግድየለሽነት እንዳያንቀው

 የስንኝ የድርሰት ማዕድ፤ የተውኔት የዜማ ድግስ

 ገበታው እንዳይጓደል፣ የኪነጥበብ ውድ ቅርስ

 ከወር ወደ ወር፤ ከዓመት ዓመት፣ እያስደሰተ፣ እያሳቀ

 እያስተከዘ፣ እያስደነቀ …

 ኢትዮጵያዊነትን አግንኖ፤ ታሪክ ባህሏን አንግሶ

 የግጥምን የጽሑፍን ፍቅር፤ በየሰዉ ልብ ለኩሶ

የተኛን ብዕር ቀስቅሶ

የድርሰት ካባ አልብሶ

ይኸው ደረሰ ለአስራ [ስምንቱ]

 እንደጣፈጡን ዓመታቱ . . .

 ይደግ፣ ይጠንክር፣ ይበርታ፣ ብርሃን ዘኢትዮጵያ መብራቱ

የኪነት ሀብት ውርስ ጥላ፣ የጥበብ ቤታችን ጣይቱ።

 ማዕከሉ በአስራ ስምንት ዓመት ጉዞው 215 ወርሃዊ የግጥም ምሽቶችን አሰናድቷል፤ 3,547 ያህል አንጋፋና ወጣት ገጣሚያንና ደራሲያንንም አስተናግዷል። 43,600 ታዳሚዎች ደግሞ ዝግጅቶቹን ተከታትለዋል። ላለፉት ስምንት ዓመታት ደግሞ ከአማርኛ በተጨማሪ በኪስዋሂሊኛ፣ በአረብኛ፣ በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጻፉ ስራዎች የሚቀርቡበትን ዓመታዊ የአፍሪካ የስነግጥም ምሽት በመስከረም ወር ውስጥ በማዘጋጄት ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ ሚናውን ተጫውቷል።

 በቴያትር ዘርፍ ደግሞ 62 ቴያትሮችን አዘጋጅቶ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በካናዳና በአውሮፓ ከተሞች በድምሩ በ373 መድረኮች አቅርቧል። በዝግጅቶቹ ላይ 71 ፕሮፌሽናልና 103 አማተር ባለሙያዎች በድምሩ 174 ተዋንያን ተካፍለውበታል። 184,900 ተመልካቾች ደግሞ ትርኢቶቹን ታድመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በስነግጥም፣ በቋንቋ፣ በቴያትር ዝግጅት፣ በትወና፣ በፊልም ስራ፣ በመገናኛ ብዙሃንና በፈጠራ ጽሑፍ ላይ ያተኮሩ 17 ዓመታዊ ወርክሾፖችን በማዘጋጀት የእውቀትና የልምድ ልውውጥ መድረኮችን ፈጥሯል። ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት የሚሰጥ የንባብ ቤትም አቋቁሟል።

 ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወጣት የሥነጥበብ ባለሙያዎችን በማስተባበር “ጣይቱ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ላለፉት ሰባት ዓመታት የጋራ የሥነፅሁፍ ምሽቶችን በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይና በተመሳሳይ ቀን እንዲካሄዱ አድርጓል። ጠቅላላ የዝግጅት ወጪያቸውንም ሸፍኗል። በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአውስትራሊያ የተለያዩ ከተሞች መሰል የሥነጥበብ ክበባትና ማህበራት እንዲደራጁ የሙያ ድጋፍና ማበረታቻ ሰጥቷል። ማህበራቱም ከ3-15 ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠሩ ናቸው።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ማዕከሉ ከ6ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ወጣቶችን ዓርብና ቅዳሜ እያሰባሰበ በሚያስፈልጋቸው የትምህርት አይነት ድጋፍ ያደርግላቸዋል። አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን የሆኑባቸውን ተማሪዎች በተለይም አዲስ የመጡትን ከአሜሪካ የትምህርት ስርዓት ጋር በማስተዋወቅና ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃቸውን ውጤት እንዲያመጡ በመርዳትም ላይ ይገኛል። የበጎ ፈቃድ ድጋፉን የሚሰጡትም በተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

ማእከሉ 64 አንጋፋና ታዋቂ የስነጥበብ ባለሙያዎችን ከአሜሪካ፣ ከኢትዮጵያና ከተለያዩ ሃገራት በመጋበዝ ከማዕከሉ ቤተሰቦች ጋር እንዲወያዩና ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ አድርጓል። ዝርዝሩ አንጋፋዎቹን ኢትዮጵያውያን ባለቅኔዎች፣ ፀሐፌ ተውኔቶች፣ ደራሲያን፣ መምህራን፣ አዘጋጆች፣ ተዋንያን፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ ወዘተ. የሚያካትት ሲሆን ፀጋዬ ገ/መድኅን፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ማሞ ውድነህ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ደበበ እሸቱ፣ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ዘውዴ ረታ (አምባሳደር)፣ ሰለሞን ዴሬሳ፣ አያልነህ ሙላት፣ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር)፣ አምሃ አስፋው፣ ቀለመወርቅ ደበበ፣ ጠለላ ከበደ፣ ተክሌ ደስታ፣ አበበ አዲስ፣ መልካሙ ተበጄ፣ በሃይሉ መንገሻ፣ አዱኛው ወርቁ (ፕሮፌሰር)፣ ታደሰ አደራ (ዶ/ር)፣ ኃይሉ ፉላስ (ዶ/ር)፣ ፍቅሬ ቶሎሳ (ዶ/ር)፣ ጌትነት እንዬው፣ ነቢይ መኮንን፣ ተስፋዬ ሲማ፣ አበባየሁ ታደሰ፣ ትዕግስት ንጋቱ፣ ተመስገን አፈወርቅና ቴዎድሮስ ለገሰ አሉበት። ለማዕከሉ የአስረኛ ዓመት ክብረበዓል ተጋብዞ ወደዋሺንግተን ዲሲ ተጉዞ የነበረው አንጋፋ ደራሲ አያልነህ ሙላቱ ወደሃገሩ እንደተመለሰ በጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ብሎ ነበር።ጣይቱ የባህል ማዕከል ኢትዮጵያውያንን ያሰባስባል፤

“የጣይቱ ማዕከል … ደግነት የሚታየው… አርቲስቱ ከሚፈልገው በላይ በመስጠት ሳይሆን አርቲስቱ ከጣይቱ የሚፈልገውን በማግኘቱ ይመስለኛል”

“የጣይቱ ማዕከል በአገርኛው ኪነጥበብ ተደራጅቶ ብቅ ያለው የሃገር ፍቅር ይዞ ለሚያንገላታው የህብረተሰብ ክፍል ተስፋ ለመሆን አስቦ ነው። መንፈሱን ለማረጋጋት ብሎ ነው። የታመቀ የሃገር ፍቅር ስሜቱን እንዲወጣ ለማድረግ ነው። በእርግጥ የጣይቱ ማዕከል ይህን ተልዕኮ በሚገባ የተወጣ ይመስለኛል። የጣይቱ ማዕከል የሚያዘጋጀው ወርሃዊ የኪነጥበብ ምሽት የዲያስፖራው የስሜት መተንፈሻ ሆኗል።

“የጣይቱ ማዕከል የበሰሉ የጥበብ ሰዎችን ያቀፈና በእነሱም የሚመራ ማዕከል መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ከሁሉም በላይ አመራሩ በውስጡ ያቀፋቸውን የጥበብ ባለሙያዎች ስሜት በሚገባ የሚገነዘብ ይመስለኛል። የጥበብ ሰዎች እርስ በርስ ከመተቃቀፋችን ይልቅ በመካከላችን ያለውን ማቀፋችን የተጠበቀ እውነታ ቢሆንም፣ በጣይቱ ማዕከል ግን ጎልቶ የሚታይ ሀቅ ሆኖ አላገኘሁትም። … እንደሚታወቀው የጥበብ ሰው ባንድ ጊዜ ሁለት ነገሮችን ያፈቅራል። አንደኛዋ በሕሊናው ውስጥ ፈጥሮ የጨረሳት ጥበብ ስትሆን ሁለተኛዋ ደግሞ ገና ያልተወለደችዋ ፈጠራው ናት። በነዚህ ሁለት ውብ እሴቶች መካከል ተወጥሮ የሚገኘው ከያኒ በሚፈጽማቸው ጥቃቅን ስህተቶች ሊወነጀል ፈጽሞ አይገባውም። እዚህ ላይ የጣይቱ ማዕከል … ደግነት የሚታየው… አርቲስቱ ከሚፈልገው በላይ በመስጠት ሳይሆን አርቲስቱ ከጣይቱ የሚፈልገውን በማግኘቱ ይመስለኛል። … የጣይቱና የከያኒያኑ ግንኙነት ማለፊያ ነው ባይ ነኝ። በማዕከሉና በጥበቡ ሰዎች መካከል ያለው መከባበር የሚያኮራ ነው።”

 የሌሎች ታዋቂ ደራሲያንና የኪነት ሰዎቻችን ሥራና ህይወትም በጣይቱ መድረክ በስፋት ተዘክሯል። ከነዚህም መካከል ነጋድራስ ተሰማ እሸቴን፣ ከበደ ሚካኤልን፣ ሀዲስ ዓለማየሁን፣ መንግስቱ ለማን፣ ብርሃኑ ዘርይሁንን፣ አቤ ጉበኛን፣ መላኩ አሻግሬን፣ በዓሉ ግርማን፣ ስብሃት ገ/እግዚአብሔርን፣ ሰለሞን ተሰማን፣ ዮሐንስ አድማሱን፣ ዳኛቸው ወርቁን፣ ደበበ ሠይፉን፣ ገ/ክርስቶስ ደስታን፣ አሥራት አንለይንና፣ አሰፋ ጫቦን መጥቀስ ይቻላል።

በስመጥሩዋ የአድዋ ጀግናና የሃገር ባለውለታ በእቴጌ ጣይቱ ስም የተሰየመው የባህልና የትምህርት ማዕከል ባለፉት 18 ዓመታት ላደረገው አስተዋጽኦ የበርካቶችን ዕውቅና ያገኘ ሲሆን 45 ሽልማቶችንና የምስክር ወረቀቶችንም ከከንቲባዎች፣ ከሃገረ ገዥዎችና ከተለያዩ የማህበረሰብ ተቋማት ተቀብሏል። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top