ፍልስፍና

“የአፍሪካ ፍልስፍና” ከወዴት ነው (የአፍሪካ ፍልስፍና ተግባራዊ ፋይዳዎች)

የአፍሪካ ፍልስፍና እጅግ በጣም ሰፊ ርዕሰ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉንም መዳሰስ ከባድ ነው። በዓለም ታሪክ ጉዞ ሂደት ውስጥ አፍሪካውያን ያካበቷቸው ዘመን ተሻጋሪ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች በቁሳዊና መንፈሳዊ ሕይወታቸው ውስጥ ተንጸባርቀዋል። ምንም እንኳን አውሮፓውያን ልሂቃን አፍሪካውያንን በዓለም የታሪክ ሂደት ውስጥ ምንም አስተዋጽኦ ያላበረከቱ ኋላ ቀር ህዝቦች ናቸው ሲሉ ቢኮንኑም፣ በተቃራኒው የዓለም የአስተሳሰብና ቁሳዊ እድገት ውስጥ የአፍሪካውያን አስተዋጽኦ ትልቅ ነው የሚሉም አሉ። ክርክሩንና ሙግቱን በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ አይተናል። ተገቢውን የአጠናን ዘዴ ከተከተልን ደግሞ እጃችን ባዶውን እንደማይመለስና በአፍሪካ ምድር የጥልቅ አስተሳሰብ ውጤቶችን ማግኘት እንደምንችል የታወቀ ነው። በሁለተኛውና ሦስተኛው ክፍል ጽሑፎች መገንዘብ ችለናል። በዚህ ጽሑፍ የአፍሪካ ፍልስፍና ምን ምን ተግባራዊ ፋይዳዎች ሊኖሩት ይችላሉ? የሚለውን ጥያቄ ለማየት እንሞክራለን።

ዓለማችን በርካታ ማኅበረ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የአካባቢ መራቆት፣ የአየር ለውጥ ችግሮችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች። እነዚህ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች የሰው ልጆችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለውታል። የዓለማችን ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጭዎችም ለእነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማግኘት ሌት ተቀን ይታትራሉ። ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እድገት ሁሉንም የሰው ልጆች ችግር ለመፍታት ይሞክራል። የአፍሪካውያንም ችግር የዚሁ የግዙፉ የዓለም ችግር አንዱ አካል ነው። በታሪካዊ ዳራ (የባሪያ ንግድና የቅኝ ግዛት ጠባሳዎችና ቅሪቶች)፣ በመልክአ ምድራዊ (የሰሃራ በረሃ መስፋፋትና ጂኦፖለቲካዊ እውነታዎች)፣ በባህል ብዝሃነት፣ በውስጥ ፖለቲካ፣ በውጭ ጫናዎች ወዘተ ምክንያት የአፍሪካውያን ሕይወት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው። በዚህም የጉስቁልናና የሰቆቃ ሕይወት የህዝቦች እጣ ፈንታ እየሆነ ይገኛል።

የግዙፉ የዓለም ህዝቦች ችግር አንዱ አካል በመሆኑ ዓለማቀፋዊ ችግር መፍቻ ዘዴዎችን በመጠቀም ችግሩን ለማቃለል መሞከሩ የግድ ነው። ነገር ግን ዘመናዊና አውዳዊ ይዘታቸው ከአፍሪካ ችግርና የማኅበረሰቡ ሥነ-ልቡና፣ የባህልና የሃይማኖት ነጽሮተ ዓለም፣ የሕይወት መስተጋብርና የርስ በርስ ግንኙነት ጋር በቀላሉ የማይጣጣሙ ዘዴዎችን ብቻ በመጠቀም የአፍሪካውያንን ችግር በዘላቂነት መፍታት አይቻልም። በአፍሪካውያን ጓዳዎች ውስጥ ለዘመናት የበለጸጉ የአስተሳሰብና የተግባር ፍልስፍናዎች እንዳሉ ባለፈው አይተናል። እነዚህን ዘመን አይሽሬ ባህላዊ እውቀቶች ከዘመናዊ የሳይንስና የፍልስፍና እሳቤዎች ጋር በማዋሃድ የአፍሪካን ችግሮች መፍታት ያስፈልጋል። ለመሆኑ ዋና ዋናዎቹ የዘመናችን የአፍሪካ ችግሮች የትኞቹ ናቸው? ከዚህ ቀጥሎ ጥቂቶቹን እንመልከት:-

 ብዝሃነትን ያለ ማስተናገድና የዘረኝነት ችግሮች:- ሁሉም (አብዛኛዎቹ) የአፍሪካ አገራት ባለ ብዝሃ ባህል ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቋንቋ ተናጋሪዎችና የተለያየ ባህል፣ እምነትና ታሪካዊ ዳራ ያላቸው ህዝቦች በአንድ የፖለቲካ መዋቅር የሚመራ አገር ውስጥ ይኖራሉ። በዚህም የታሪካዊ ዳራ ተቃርኖዎች፣ የቋንቋና ባህል ልዩነቶች፣ የኢኮኖሚያዊ ዘይቤና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ልዩነቶች (ለምሳሌ አርብቶ አደርና አርሶ አደር ማኅበረሰቦች ቢጎራበቱ ገበሬው ጫካውን መንጥሮ እህል መዝራት ይፈልጋል፣ ከብት አርቢው ደግሞ ጫካውን፣ ሳሩንና ቅጠሉን ይፈልገዋል፤ በዚህ መካከል መቃቃር፣ መጋጨት ይኖራል)፣ የሃይማኖት ልዩነቶች በነዚህ የአንድ አገር ህዝቦች መካከል ወይም በሁለት አገሮች አጎራባች አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች መካከል ብዝሃነትና ልዩነት የወለዳቸው ግጭቶች ይስተዋላሉ። በዚህም የአካባቢውን ሰላም፣ የህዝቦችን ደኅንነት ይጎዳዋል። መፈናቀልና ስደት፣ ሞትና ጉስቁልና የበርካታ ህዝቦች እጣ ፈንታ ከመሆኑም በላይ በርካታ አገራት ተከፋፍለው፣ ድንበራቸው የጦርነት ቀጠና እየሆነ ይገኛል። የሱዳንን መከፋፈልና የቅርብ ጊዜውን የሩዋንዳን የዘር ፍጅት፣ በሃገራችንም እየገጠመን ያለውን የዘረኝነት ዓይነ ጥላ መመልከቱ በቂ ነው።

የመሪዎች አምባገነንነት:- ለዘመናት አፍሪካን ከቅኝ ነጻ ለማውጣት፣ ወይም የሚዋጉላቸውን ህዝቦች ከጨቋኝ አገራዊ አገዛዞች ለማላቀቅ በርካታ ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ስማቸው በዓለም መድረክ የገነነ የነጻነት ታጋዮችን በአፍሪካ ማኅጸን አይተናል። ነገር ግን የነዚህ ጦርነቶች ውጤት የብዙሃንን ደም ከማፍሰስ፣ ሕይወታቸውን ከመቅጠፍ፣ አካላቸውን ከማጉደል የዘለለ የተፈለገውን ያክል የአፍሪካውያንን ሕይወት ሲለውጥ አልታየም። በተቃራኒው የትናንት የነጻነት ታጋዮች፣ የመልካም አስተዳደር ተቆርቋሪ ዲሞክራት ታጋዮች፣ የዛሬ አምባገነኖች እንዲሆኑ የተደላደለ ወንበርን ፈጥሮላቸዋል። “The Beautiful Ones Are Not Yet Born” እንዳለ ጸሐፊው መልካም መሪዎች ገና አልተወለዱም። መሪዎችና አጃቢዎቻቸው የተንደላቀቀ ኑሮ እየኖሩ ዜጎች በችጋር አለንጋ እየተገረፉ የመልካም አስተዳደር ችግር ከሁሉም አገልግሎቶች እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።

 ኢ-ፍትሐዊ የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም:- ማኅበራዊ ፍትህ አለመኖር፣ እኩል የተፈጥሮ ሐብት ተጠቃሚነት ችግር አንዱ የአፍሪካውያን የወቅቱ ፈተና ነው። በሃብታሙና በድሃው መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት በሰዎች መካከል እኩልነት ጠፍቶ ሰው ሰራሽ በሆነ የኑሮ ውድነትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዜጎች ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ሃብት ወይም አገር ያፈራችውን ጸጋ እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ይፈጥርባቸዋል። በዚህም የኑሮ ደረጃ ልዩነት (class difference) የዘመናችን ትልቁ ፈተና ሆኗል። በዘመድ አዝማድ ወይም በፖለቲካዊ ታዛዥነት ጥቂቶች ባልሰሩት በአቋራጭ ሲከብሩ ሌት ተቀን የሚለፉት ድሃዎች ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የሰቆቃ ሕይወት ኑሯቸውን ይገፋሉ። በዚህም በዜጎች መካከል አለመግባባት፣ መቃቃርና የባይተዋርነት ስሜት ይፈጠራል። በርካቶች በስደት በበረሃ፣ በውቅያኖስ፣ በታጣቂዎች ሕይወታቸው ይቀጠፋል።

 የአካባቢ መራቆትና ተደጋጋሚ ድርቅ:- አፈር በመግፋት የሚኖረው አብዛኛው የአፍሪካ ድሃ ገበሬና፣ ከብት በማርባት የሚተዳደረው አፍሪካዊ በበረሃዎች መስፋፋትና የዓለም ሙቀት በመጨመሩ ምክንያት ችግሩ እየሰፋ ይገኛል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ከማዋል ይልቅ መሪዎቹ ለፖሊሲዎች ለውጥና ለፖለቲካ አጀንዳዎች ማስፈጸሚያነት የሚቀርብላቸውን የእርዳታ ስንዴ እንደአማራጭ ይወስዱታል። ያንንም በአግባቡ ስለማያከፋፍሉት ለድሃው ችግር መፍቻ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረችበት የመሰለው የአፍሪካ ህዝብ መሪዎችም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመፍታት ሲሰሩ አይታዩም።

ሌሎች ተቋማዊና አስተሳሰባዊ ችግሮች:- በየወቅቱ እየተለዋወጠ ካለው የቴክኖሎጂ እድገት ጋር እኩል ለመራመድ የሚንደፋደፉት የአፍሪካ አገራት ወይ ነባሩን ባህላቸውንና አገር በቀል እውቀታቸውን አልያዙ፣ ወይም ከዘመናዊ ሥልጣኔ ተጠቃሚ አልሆኑ ከሁለት ያጣ ሆነው ይገኛሉ። በየመስሪያ ቤቶቹ የሚተዋወቁት አሰራሮች በሰራተኞቹ ዘንድ ሳይለመዱ እነርሱን የሚያስንቅ አዲስ አሰራር ይመጣል። ያንን ለመልመድ በስልጠናና በስብሰባ የሚባክነው ጊዜ መስሪያ ቤቶቹ ለተገልጋዮቻቸው ከሚሰጡት ጊዜ ጋር የሚመጣጠን አይደለም።

 እንዳለመታደል ሆኖ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ አውሮፓዊ በሆነ የትምህርት ሥርዓትና የካሪኩለም ይዘት የተቃኙ ስለሆኑ በመምህራኑም ሆነ በተማሪዎቹ ላይ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። አንዳንዶቹ እንደሚተቹት የአፍሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በገንዘብ ለሚደጉሟቸው ገዥ ፓርቲዎች ርእዮተ ዓለም አስፈጻሚዎችና፣ በእጅ አዙር ለሚዘውሯቸው የውጭ ተቋማት የፖለቲካ ግብ ማስፈጸሚያ እንጂ ከህዝቡ ጋር የማይተዋወቁ ባይተዋር ደሴቶች ናቸው ይሏቸዋል። ይህ ደግሞ በድህረ ቅኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካውያን ላይ የሚደረግ የአእምሮ (የህሊና) ቅኝ ግዛት (Mental Colonization) ነው። የትምህርት ተቋማት በራስ የሚተማመኑ ምክንያታዊ ዜጎችን ከመፍጠር ይልቅ ከራሱ ባህል የተፋታ፣ ከዘመናዊ ሳይንስም ወደ ኋላ የቀረ በህሊና ንውዘት ውስጥ ያለ መንፈሰ

“እንዳለመታደል ሆኖ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሳይቀሩ አውሮፓዊ በሆነ የትምህርት ሥርዓትና የካሪኩለም ይዘት የተቃኙ ስለሆኑ በመምህራኑም ሆነ በተማሪዎቹ ላይ ስር ነቀል የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም”

ደካማ ትውልድ እያፈሩ እንደሆነ ቢያንስ ጠቋሚ ምልክቶች አሉ።

እነዚህና በርካታ ጥቃቅን ችግሮች ተደማምረው የአፍሪካውያንን ኑሮ የሰቆቃና የኋላ ቀርነት ኑሮ እንዲሆን አድርገውታል። ችግሮች ዓለማቀፋዊ ቢሆኑም በተለየ ደግሞ አፍሪካውያን የውስጣዊም የውጫዊም ችግሮች ተጠቂዎች ሆነዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሲፈለግም ከዘመናዊ መንገዶች ጎን ለጎን ለዘመናት በህዝቦች ሲተገበሩ የነበሩ የአስተሳሰብና የፍልስፍና ጥበቦችንም ማካተት ግድ ይላል። እዚህ ላይ ነው የአፍሪካ ፍልስፍና ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ የሚሆነው። ለየትኞቹ ችግሮች የትኞቹ አስተሳሰቦች ያስፈልጋሉ? የሚለው ጥልቅና ዝርዝር ትንታኔ የሚያስፈልገው ነው። ነገር ግን ባለፈው ያየናቸው አንዳንድ ተምሳሌታዊ የአፍሪካ ፍልስፍናዎች ተገቢው ግምትና ቦታ ከተሰጣቸው ዓይነተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ። የተወሰኑትን ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት።

 የኡቡንቱ ፍልስፍና የመቻቻልና የአብሮ መኖር ፍልስፍና ነው። ሰዎች በማንነታቸው (በባህል፥ በሃይማኖት፥ በቋንቋ) ተቧድነው በሚጫረሱበት አህጉር እንደ ኡቡንቱ ዓይነቶቹ ዘመን አይሽሬ እሳቤዎች ከዘመናዊ የመቻቻል ፍልስፍናዎች ጋር ተቀይጠው ቢቀርቡ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ። “ሰው ሰው የሚሆነው ሌሎች ሰዎች ስላሉ ነው፤ እኔነት እውን የሚሆነው እኛነት እስካለ ድረስ ነው” የሚሉት ፍልስፍናዎች በቋንቋና ነገድ ጥብቆ የታጠረውን አስተሳሰብ በመግፈፍ ትልቁን ህብረት መመልከት ያስችላል። ያ ትልቅ ኅብረትም ሰውነት፣ ሰው መሆን ነው። በማንነት ቅዤትና በዘረኝነት እርኩስ መንፈስ የሚሰቃዩትን ሰው የሚባል ምንነት እንዳለ ማሳየት ማርከሻ መድኃኒቱ ነው። ልዩነቶችን በሆደ ሰፊነት አስተናግዶ ለዘመናት አብሮ መኖር የበርካታ አፍሪካውያን ማኅበረሰቦች መገለጫ ነው። በዘመነ መሳፍንት ወደ ኢትዮጵያ የመጣ አርኖ ሚሼል ዳባዴ የተባለ ተጓዥ “በኢትዮጵያ ተራራዎች ቆይታዬ” በሚል ርእስ ገነት አየለ አንበሴ ተርጉማ በ2009 ዓ.ም ባሳተመችው መጽሐፉ ስለ ኢትዮጵያውያን ተቻችሎ መኖር ሲመሰክር እንዲህ ይለናል:-

 “ከአውሮፓ የመጣው ተጓዥ ግር የሚለው አንድ ነገር አለ። በሚያልፍበት አካባቢ የሚያየው አንድ ህዝብ መካከል ከሌላ ቦታ ተሰዶ የመጣ የሌላ አካባቢ ሰው፤ ቤተሰብ፤ እንዲያውም አንዳንዴ መንደር ሙሉ ሰው ከነባሩ ጋር ሰፍሮ ሲኖር ማየቱ ነው። ከነባሩ ነዋሪ ጋር በዘር ወይም በጎሳ የማይዛመድ ፍጹም የተለየ ብሔር ቢሆን እንኳን ተቀላቅሎ ለመኖር አንዳች ችግር አይፈጥርበትም። ለመልካም አብሮ የመኖር ዘዴ የነባሩን ነዋሪ ወይም ብሔር ሕግና ልማድ አክብሮ መስሎ መኖር ብቻ ሲጠበቅበት በበኩሉ አያት ቅድመ አያቶቹን ሳይክድ ማንነቱን ሳይረሳ ጥንታዊ ልማዱን ሳይሽር መኖር ይችላል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ባንድ አካባቢ የተለያዩ ባህልና ልማድ ያላቸው ጎሳዎች በጉርብትና በሰላም ሲኖሩ ማየት የምንችለው።” (ገጽ 73)  ስለ ሰላም ክብርና ታላቅ ዋጋ በርካታ የአፍሪካ ህዝቦች ትልቅ ግምት የሰጡት ነው። ለዘመናችን የጸጥታ ችግሮች መፍትሄ ከሚሆኑት ዘመናዊ ፖሊስ እና የወታደር ሚና በተጨማሪ (በበለጠም ሊሆን ይችላል) አፍሪካውያን የራሳቸው የሆነ ሰላምን የማስጠበቅ መንገድ አላቸው። ፍልስፍናው በቀደምት አባቶች ወደ ግእዝ ተተርጉሞ የሚገኘው ጠቢቡ እስክንድስ ስለ ሰላም እንዲህ ይላል: “peacemaking is itself the water that extinguishes the fire, […] that drives away evil thoughts; it burns the eyes of the devil; it renders all anger ineffectual; it is itself called the daughter of Most High.” በእንደዚህ ዓይነቶቹ የተጻፉና በቃል የሚነገሩ ትውፊቶች እየተመሩ በሰላም የኖሩ ህዝቦች አሁንም ሰላማቸውን የሚያውከውን ነገር መፍትሄ ለማበጀት የመሳተፍ እድሉን ቢያገኙት የሚጠበቀውን ያክል ውጤት ማምጣት ይቻላል።

እንደኦሮሞ ያሉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ለሰላምና ተቻችሎ ለመኖር እንዲሁም ስለ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የራሳቸው ትውፊትና ፍልስፍና አላቸው። በዘመናዊ መንገድ ከሚደረገው የዲሞክራሲ ዲስኩር የማይተናነስ የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት የቻሉ፣ በዚያውም ራሳቸውን ሲያስተዳድሩ የኖሩ አፍሪካውያን አሁን በአምባገነን መሪዎች ጠንካራ ክንድ ሲደቆሱ ማየት የዘመናችን ትልቅ ቅሌት ነው።

ማኅበረሰቡ እኩይ ምግባራትን የሚያወግዝባቸው የራሱ የሆኑ መንገዶች አሉ። ሲጀምር ቃላዊና ጽሑፋዊ ትውፊቶቹ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መርሆዎቹ በሙሉ የሚያሳዩት መልካም ሥነ-ምግባርና የተስተካከለ ሰብዕና በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲረጋገጥ ነው። ጀግናን፣ ታታሪን፣ ታማኝና ጨዋን ማበረታታት፤ ሌባን፣ ውሸታምን፣ ፈሪንና ሰነፍን ደግሞ መንቀፍ የብዙ  አፍሪካ ማኅበረሰቦች መልካም እሴቶች ናቸው። ከቃላዊ ትችት (ቅኔ፣ ምሳሌያዊ አነጋገር፣ ዘይቤ፣ አሽሙር) እስከ ማኅበረሰባዊ መገለል የሚያደርሱ ቅጣቶችን በጥንታዊ የማኅበረሰብ ባህሎች ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ማኅበራዊ ትውፊቶች ከዘመናዊ የሥነ ምግባር መርሆዎች፣ የህግ ድንጋጌዎች ጋር ተዋህደው ቢተገበሩ መልካም ማኅበራዊ መስተጋብር ያለበት ዘመናዊ ማኅበረሰብ ማረጋገጥ ይቻላል።

ስህተት ተፈጽሞ፣ ፍርድ ተጓድሎ፣ ወገን ተበድሎ ሲገኝ ማኅበረሰቡን አሳታፊ የሚያደርጉ የመፍትሄ ሂደቶች በበርካታ የአፍሪካ ማኅበረሰቦች ዘንድ የታወቁ ናቸው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የሚተገበረውን የአፈርሳታ ሥርዓት፣ የሽምግልና ሂደቶች ወዘተ ማየቱ በቂ ነው። የችግሩን ትክክለኛ መንስኤ ከማወቅ ጀምሮ እስከ የመፍትሄ ሂደቱ ድረስ ፍጹም ታማኝ በሆኑ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ባላቸው አካላት ስለሚካሄድ ሙስናንና ግልጽ ያልሆነ አሰራርን ለማስወገድ ዓይነተኛ ዘዴዎች ናቸው። ከውጤታማነትና ቀጣይ ማኅበራዊ መስተጋብርን ከመጠበቅ አንጻር በደል የሰራው ሰው ከተበዳዩ ጋር ታርቆ ማኅበረሰቡን የሚቀላቀልበት መንገድ ቂም በቀልንና ጥላቻን ለመቀነስ ትልቅ ጥንቃቄ ይደረጋል። አብዛኛዎቹም ውጤታማ ናቸው።

 እንደዚህ ዓይነቶቹ የእርቅና የፍርድ ሂደቶች ለዘመናዊ ህግ አውጭዎችና የዳኝነት ሂደት ትልቅ ትምህርትን ይሰጣሉ። ከማኅበረሰቡ ባይተዋር የሆኑ ዘመናዊ ዳኞች፣ ለማኅበረሰቡ ቋንቋ ግልጽ ያልሆኑ የህግ አንቀጾች የሚያመጡት ፍትህ ለጊዜው ወንጀለኛውን ቢቀጣው እንጅ ተበዳዩን አያረካውም። ችንዋ አቸቤ Things Fall Appart በተሰኘው መጽሐፉ ነጭ ዳኞች በማኅበረሰቡ ውስጥ በተነሱት የመሬት ጉዳዮች ላይ ፍርድ ሲሰጡ ህዝቡ እንዴት ይሳለቅባቸው እንደነበር ሲገልጽ “እኛ ስለመሬታችን ያለንን ግምት፣ አስተሳሰብ የማያውቅ ዳኛ እንዴት በመሬት ጉዳይ ላይ ፍርድ መስጠት ይችላል?” በማለት ነበር። በተመሳሳይ ደሳለኝ ራህማቶ በወሎ ገበሬዎች ዘንድ የመሬት ስሪት አዋጅና ክፍፍል የሚያደርጉትን የመንግሥት አካላት፣ በመንግሥት ህግ መሰረት የመሬት ቅሬታዎችን የሚፈቱ ዳኞች ከኅብረተሰቡ የህግ እውቀት የራቁ፣ ከነባሩ ትውፊት ያፈነገጡ እንደነበሩ ያስረዳል። ገበሬዎቹም በፍርድ ሂደቱና በውጤቱ ደስተኞች አይደሉም።

 ዘመናዊ የመድኃኒት ቴክኖሎጂ የሰው ልጆችን ጤንነት በማስጠበቅ በኩል ረጅም ርቀት ተጉዟል። በኢኮኖሚ አቅማቸው ጠንካራ የሆኑ ሰዎች “አካላቸውንና ጾታቸውን” እስከ ማስቀየር የሚያደርስ ቴክኖሎጂ እንዳለ እያየን ነው። “ነፍስ መፍጠር ብቻ ነው የቀራቸው” የሚለው የገጠሬው አነጋገር እውነትነት ያለው ነው። ነገር ግን ባህላዊ የሕክምና ዘዴዎችም ይፈወሳሉ ያላልናቸውን በሽታዎች ማከም የሚያስችሉ ብልሃቶች እንዳሉ እውነት ነው። እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስና ነቀርሳ (Cancer) ያሉ ከባድ በሽታዎችን ሳይቀር የሚፈውሱ የባህል ባለ መድሃኒቶችን በየትኛውም የአፍሪካ ክፍል ማግኘት እንችላለን። የሥነ-ልቡና እና የአንጎል በሽታዎችን (Mental diseases)፣ ከባባድ ቀዶ ጥገና የሚያሻቸውን እንደ ኪንታሮት ያሉ ስር ሰደድ ሕመሞችን በቀላሉ የሚፈውሱና የሚያከስሙ ባለመድኃኒቶችን ማግኘቱ ቀላል ነው። የተሰበረ የሚጠግኑ ወጌሾች ሜዲካል ዶክተሮችን ያስንቃሉ። ከጸበል ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመድኃኒት ቅመማ የሚጠይቁ የባህል ሕክምናዎች ለዘመናችን የጤንነት እክሎች የራሳቸውን ድርሻ ይወስዳሉ።

 ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ አፍሪካውያን ለተፈጥሮ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ አጥኝዎች ይጠቁማሉ። ተፈጥሮ የተቀደሰች እንደሆነችና መሬት ከትውልድ ወደ ትውልድ የምትተላለፍ የአባቶች ቅርስ ስለሆነች ያለ አግባብ መበደል እንደሌለባት ያምናሉ። እነዚህ ቅድስናን የተፈጥሮ፣ የሰው ልጆችና የፈጣሪ ማዕከላዊ መገለጫ ያደረጉ ባህላዊ እውቀቶች የደን ጭፍጨፋንና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል የራሳቸው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

በአፍሪካ ጓዳዎች የሚገኙ የአስተሳሰብና የተግባር ትውፊቶች ከላይ የተገለጹትን አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ መከራከር አይቻልም። የአፍሪካን ሰማይ ስናስስ ባዶ እጃችንን አንመለስም እንዳለ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ እጓለ ገብረዮሐንስ የአፍሪካን ጓዳ ጎድጓዳ ብናስስ ለዘመናችን የጤና፣ የፍትሕ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሰላም፣ የመከባበር፣ የመልካም አስተዳደር፣ አስተሳሰብንና የባኅሪያዊ ቀናነትን፣ መልካም ሰብዕናንና ሰዋዊ ክብርን ልናረጋግጥባቸው የሚያስችሉን ፍልስፍናዎችን እንደምናገኝ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ዋናው ጉዳይ ባህላዊ እውቀት ከዘመናዊ እውቀት ጋር እንዴት መዋሃድ ይችላል? ይህንን ማድረግስ የማን ድርሻ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መቻላችን ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top