ከቀንዱም ከሸሆናውም

የአዲስ አበባ ህንፃዎችና ህፀፆች

መዲናችን አዲስ አበባ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ህንፃዎች እንደ አሸን የሚፈሉባት ከተማ ሆናለች። የህንፃዎቹ ግንባታ ባይጠላም ከግንባታ እስከ አጠቃቀም የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ህፀፆች ግን ሊታረሙ ይገባል። ችግሮቹ የትየለሌ ቢሆኑም በዚህ ዕትማችን ጥቂቶቹን ቆንጠር አድርገን እንመለከታቸዋለን።

ዝብርቅርቁ የህንፃ ከፍታ፣

 በበርካታ ከተሞች ህንፃዎች ሲገነቡ የህንፃ ከፍታ ግምት ውስጥ የሚገባባቸው ሂደቶች አሉ። የህንፃ ከፍታ ሲባል ተቀራራቢ ርዝመት ያላቸው ህንፃዎችን በአንድ አካባቢ እንዲገነቡ ማድረግ ማለት ነው። ይህ አይነቱ የሕንፃ አደራደር ለአንድ ከተማ ከሚያበረክተው ውበታዊ እሴት በተጨማሪ፤ አንዱ ህንፃ በሌላው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንዳያሳድር ያደረጋል። ተመሳሳይ ከፍታ የሌላቸው ህንፃዎች በአንድ አካባቢ ሲገነቡ ከፍተኛ ቁመት ያላቸው ህንፃዎች ተመጣጣኝ ቁመት የሌላቸውን ህንፃዎች በቂ አየርና ብርሃን እንዳያገኙ ያደርጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በቁመት አነስተኛ የሆኑት ህንፃዎች ምንም ያህል ውበት ቢኖራቸው በአካባቢያቸው ባሉ ግዙፍ ህንፃዎች ከተከበቡ ኪነ ውበታቸው ጎልቶ የሚወጣበት እድልም አነስተኛ ነው።

 የአንድ ከተማ ግንባታ በጥሩ መሪ ፕላን የሚመራ ከሆነ በጥሩ አቀናባሪ የተቀናበረ ሙዚቃ ያህል የራሱ ቃና እና ትርጉም የሚሰጥ ፍሰት ይኖረዋል። የከተማው መንገዶች፣ ህንፃዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎችና ሌሎች ክፍሎች እርስ በእርሳቸው ይናበባሉ። ባጭሩ የአንድ ዘመናዊ ከተማ ግንባታ በጥልፍ ወይንም በመሬት ምንጣፍ ላይ እንደሚታይ የራሱ የሆነ ኪናዊ ቋንቋ ያለው ዲዛይን ወይንም ፓተርን ባለቤት ነው። በመሆኑም በአንድ በሰለጠነ ከተማ ያለ ምክንያት የሚካሄድ አንዳች አይነት ግንባታ የለም።

ሁሉም ግንባታና ልማት የሚከወነው በመሪ ፕላኑ ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ብቻ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ምን አይነት ህንፃ የትኛው ቦታ ላይ እንደሚገነባ በሚገባ ይታወቃል ማለት ነው።

እናም ባደጉት ሀገራት ያሉት ከተሞች የውበት ሚስጥር በመጀመሪያ በትክክለኛ ጥናት ላይ የተመሰረተ ማስተር ፕላን ባለቤት መሆናቸው ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው ደግሞ ማስተር ፕላኑን ያለ አንዳች መዛነፍ መሬት ላይ እንዲወርድ መደረጉ ነው። በዚህ በኩል መዲናችን አዲስ አበባ አልታደለችም። አዲስ አበባ ባለፉት ዓመታት በታሪኳ ከአስር ያላነሱ ማስተር ፕላኖች ባለቤት ብትሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ስትታይ ግን በአንድም ማስተር ፕላን የተመራች ከተማ አትመስልም።

 በከተማዋ ሁሉም ነገር የሚገነባውና የሚፈርሰው በነሲብ ነው። እንደማሳያ ያህልም ቀደም ሲል ወደ ተነሳንበት የህንፃ ከፍታ ጉዳይ እንመለስ። በአይነ ህሊናችን ወደ ልደታ አካባቢ እንጓዝ። ልደታና አካባቢው እስከ አብነት መዝለቂያው ድረስ በከፍተኛ የህዝብ ጥግግት የተጨናነቀና ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የሚኖርበት አካባቢ እንደነበር አካባቢውን የሚያውቅ ሰው ያስታውሰዋል። ሆኖም “መልሶ ማልማት” በሚለው አሰራር መሰረት የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲነሱ ከተደረገ በኋላ ቦታው ለኮንዶሚኒየም ግንባታና ለሌሎች አልሚዎች እንዲለይ ተደረገ።

የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ባለ አራት ፎቅ (ጂ+4) ሲሆኑ በአንፃሩ በኮንዶሚኒየሞቹ ዙሪያ በባለሀብቶች የተገነቡት ህንፃዎች ደግሞ በአብዛኛው ከስምንት እስከ አስር ፎቅና ከዚያ በላይ ርዝመት ያላቸው ናቸው። በግንባታ ማጠናቀቂያ ውበት በኩልም በባለሀብቶቹ የተገነቡት ህንፃዎች ከጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በብዙ እጥፍ ውበታቸው ጎልቶ ይታያል። እናም በቁመትም ሆነ በውበት በዙሪያቸው ባሉት የግለሰብ ህንፃዎች የተበለጡት የልደታ ኮንዶሚኒየም ህንፃዎች፤ በተለያየ አቅጣጫ ሲታዩ አካባቢውን የማይመጥኑ ሆነው ይታያሉ።

 ይህ ሊሆን የቻለው ውበት አንፃራዊ በመሆኑ ነው። በመሆኑም ህንፃዎቹ በተከበቡባቸው ሌሎች ግዙፍ ህንፃዎች አንፃር ሲታዩ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ማንም ሰው “ያለቦታቸው የተገነቡ” ናቸው ብሎ የህሊና ፍርድ እንዲሰጥ ያስገድዱታል። የአዲስ አበባ ከተማ ችግር ይህ ነው። ይህንን እንደማሳያ ተመለከትን እንጂ ከተማዋ በመሰል ችግር የተከበበች ናት። በቆዩ አካባቢዎች ያሉ የጥንት ቪላ ቤቶች በየሰፈሩ እየፈረሱ ህንፃ ሲቆምባቸው ተመሳሳይ የግንባታ አለመመጣጠኖች ይታያሉ። በሳር ቤት፣ በቦሌ፣ በበቅሎ ቤትና በመሳሰሉት አካባቢዎች ያሉ ቪላ (መኖሪያ) ቤቶች መሃል እየፈረሱ ወደ ፎቅነት የሚለወጡት ቤቶች የአካባቢውን ገፅታ ወጣ ገባ እያደረጉት ይገኛሉ። ህንፃዎቹ በቤቶቹ መሀል መገንባታቸው ቤቶቹ በቂ ብርሀን እንዳያገኙ፣ ለአይን እንዲከብዱና ውበታቸውም እንዲጠፋ አድርጎታል። ይህ ብቻ ሳይሆን የሚገነቡት ህንፃዎች ከፍታ፤ የሌሎችን ቤቶች ሙሉ የግቢ ገፅታ በቀላሉ የሚያሳዩ መሆናቸው በራሱ ደግሞ ግላዊ ህይወትን (Privacy) የሚጋፋ ሆኖ ይታያል።

 ህንፃዎቹ በመኖሪያ ቤቶች መሀል እንዲገነቡ መደረጋቸው ሌላኛው ፈተና ደግሞ ለንግድ አገልግሎት በተለይም በአብዛኛው ለፔንሲዮን አገልግሎት መዋላቸው ነው። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ሲታዩ የአንድ ከተማ መስተጋብር ከኪነ ህንፃ ውበትና ከግንባታ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከማህበራዊ ሳይንስም ጭምር መታየት ያለበት መሆኑን ነው።

 የህንፃ ከፍታን ጠብቆ ተመጣጣኝ ግንባታን የማከናወን እንቅስቃሴ የሚታየው ከኢትዮጵያ ሆቴል፣ በብሔራዊ ቴአትር እስከ ሜክሲኮ ባለው መስመር አዳዲስ በሚገነቡት የባንክ እና የኢንሹራንስ ህንፃዎች ግንባታ ነው። አካባቢው በሌሎች ያደጉ ሀገራት ፋይናንሺያል ስትሪት እንደሚሉት ወይንም በአሜሪካኖቹ ዎል ስትሪት እንደሚባለው ይመስላል። ለማንኛውም በእነዚህ አካባቢ ያለው ግንባታ ከ30 እስከ 46 ፎቅ ከፍታ ያለው ግንባታ በመሆኑ በአንድ አካባቢ ግንባታው መከናወኑ ከሚኖሩት ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ባሻገር በኪነ ህንፃ ጥበብም የተመጣጠነ የህንፃ ከፍታ አስፈላጊነትን በሚገባ ለማሳየት ይረዳል።

 መንገድና ህንፃ፤ ያንዱ ልማት ለሌላው ጥፋት፣

 ሌላው ከአዲስ አበባ ከተማ የህንፃዎች ግንባታ ጋር ተያይዞ እንደተግዳሮት የሚታየው ከከተማዋ የመንገዶች ግንባታ ጋር አብረው የማይሄዱ መሆናቸው ነው። በተለይ ህንፃዎቹ ከዋናው መንገድ በምን ያህል ርቀት መገንባት አለባቸው? የሚለው ጉዳይ ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል። አብዛኞቹ የአዲስ አበባ መንገዶች በተለይ ከስፋት አንፃር ሲታዩ ከደረጃ በታች ናቸው።

 በተለይ ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ሰፊ የትራፊክ ፍሰት ከማስተናገድ አንፃር ሲታዩ መንገዶቹ መስፋት ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም አሁን ባለው የከተማዋ ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ የከተማዋ ህንፃዎች የተገነቡት ቀጣይ የመንገድ ማስፋፊያን ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ፣ ከፊት ለፊታቸው በቂ ቦታ ሳይተው እዚያው መንገዱ ሥር ነው።

 እናም ይህ ሁኔታ ሲታይ በመዲናችን አዲስ አበባ አሁን ያሉትን መንገዶች አስፍቶ የትራፊክ ፍሰቱን ጤናማ ለማድረግ የሚቻልበት እድል አነስተኛ መሆኑን ነው። አንድ ማሳያ እንውሰድ። በቦሌ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በኩል ከኤድና ሞል ጀርባ ወደ ዓለም ሲኒማ የሚያወጣ አንድ መንገድ አለ። መንገዱ ከመነሻው በቂ ስፋት ያልተሰጠውና በዚህ አካባቢ በመንገዱ ግራና ቀኝ የተገነቡት ህንፃዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገነባ ባለመሆኑ በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የተሽከርካሪዎች ፍሰት መጨናነቅ ይታያል።

 መንገዱን ለማስፋት እንዳይቻል ደግሞ ህንፃዎቹ የተገነቡት እዚያው የመንገዱ አፍንጫ ሥር ነው። እናም አሁን በቦታው ከሚታየው ችግር አንፃር “ህንፃዎቹን አፍርሰን መንገድ እናስፋ” ካልተባለ በስተቀር አሁን የሚስተዋለው የትራፊክ መጨናነቅ ወደፊትም በስፋት ተስፋፍቶ ይቀጥላል። የትራፊክ ፍሰቱ ከመንገዱ አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ በዚያው መጠን እድሜው እያጠረ ነው የሚሄደው።

 ከዚህ በኋላ መንገዱን እናስፋው ቢባል እንኳን በድሃ ሀገር ኢኮኖሚ በወሰን ማስከበር ስም ህንፃዎችን እያፈረሱ መንገድ መገንባት የማይቻል ነው። እናም አሁን ከተጠቀሰው አካባቢ በተጨማሪ ሌሎች በህንፃዎች ግንባታ ምክንያት በቀጣይ የመስፋት እድላቸው ዜሮ የሆኑ በርካታ የአዲስ አበባ መንገዶች መኖራቸው ግንዛቤ ውስጥ ሊከተት ይገባል።

ግንባታ ሳይጠናቀቅ ለአገልግሎት ማዋል፣

 በአዲስ አበባ ከተማ የህንፃ ግንባታ ሂደት ከሚታዩት ችግሮች መካከል አንዱ ግንባታዎቹ ሳይጠናቀቁ ለአገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ ነው። ይህ አይነቱ ችግር በከተማችን በስፋት ይታያል። ይህ እየሆነ ያለው ከህንፃ ግንባታ እስከ አጠቃቀም ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በሚገባ ለመቆጣጠርና ለመከታተል የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ የወጣው የህንፃ አዋጅ ቁጥር 621⁄2001ን በመተላለፍ ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት አንድ ህንፃ ሳይጠናቀቅ አገልግሎት መስጠት ይቅርና ከተጠናቀቀ በኋላ እንኳን ቢሆን ከሚመለከተው አካል የመጠቀሚያ ፈቃድ ካላገኘ በስተቀር ማናቸውንም አገልግሎቶች መስጠት አይችልም።

 ሆኖም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በመዲናችን አዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች በግንባታ ላይ ያሉ ህንፃዎች ባሉበት ደረጃ አገልግሎት መስጠት የተለመደ ሆኗል። ይህ ለከተማ ገፅታም ሆነ ለአገልግሎት ጥራት የሚመች ሆኖ አይታይም። ከዚህም በተጨማሪ በግንባታ ላይ ያሉ ህንፃዎች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ግንባታውም ጭምር ጎን ለጎን የሚካሄድበት ሁኔታ ስላለ በተከራዮችም ሆነ አገልግሎቱን በመፈለግ ወደ ህንፃው ጎራ በሚሉ ሰዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ሁኔታም ይኖራል። እናም አዋጁ በወጣበት መንፈስ መተግበር ካልቻለ በስተቀር ይህንን ሥር የሰደደ ችግር ከመሰረቱ መቅረፍ አይቻልም።

ኋላቀር የግንባታ ሥርዓት፣

በኢትዮጵያ የህንፃ ግንባታ የሚታየው ሌላው ችግር በግንባታው ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሀብት ብክነት መኖሩ ነው። ይህ ከፕሮጀክት

“በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በተለይም በመዲናችን እየተገነቡ ያሉት ህንፃዎች ግን እየተገነቡበት ባለው ዓመት ያለውን የማህበረሰብ የሥልጣኔ አሻራ የሚያንፀባርቁ ሆነው አይታዩም”

አስተዳደር እንደዚሁም ከአቅም ጋር የተያያዘ ነው። በአዲስ አበባ በሚገነቡ ህንፃዎች የግንባታ ግብዓቶች የህዝብ መንገዶችን መዝጋት፣ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስና ለእግረኛው ብሎም ለአሽከርካሪው ምቾት መንሳት የተለመደ ባህል ከሆነ ዋል አደር ብሏል።

ችግሩ “የቦታ ጥበት ነው” እንዳይባል በአዲስ አበባ ከተማ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ህንፃዎችን የሚገነቡ ቻይናውያን አንዳች አይነት ችግር ሲፈጥሩ አይታዩም። እንደማሳያ ያህልም በአዲስ አበባ ከተማ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በራሳቸው በቻይናውያን እየተገነባ ያለውን ግዙፉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት የህንፃ ግንባታ መመልከት ይቻላል።

 ህንፃው 48 ወለሎች አሉት። የግንባታ ቦታው በመንገድ የተከበበ ሲሆን ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰትም የሚታይበት ነው። ሆኖም ህንፃው የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ከዛሬ ሶስት ዓመት ጀምሮ 48ኛ ወለል እስከደረሰበት እስከዛሬው ዕለት ድረስ በአካባቢው ላይ የሚታይ አንዳች አይነት የግብዓት መዝረክረክ፣ የመንገድ መዘጋትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች አይታዩም። የአፍሪካ ህብረትም ሆነ ሌሎች በመዲናችን በቻይናውያን እየተገነቡ ያሉ ህንፃዎች በግንባታ ወቅት አካባቢያዊ መጨናነቅ ሲፈጥሩ አይታይም።

በአንፃሩ በኢትዮጵያውያን ሥራ ተቋራጮች የሚገነቡ አነስተኛ ህንፃዎች እንኳን ሳይቀሩ መንገድ በአሸዋና ጠጠር ሳይዘጉ፣ አካባቢውን ሳይበክሉና የተላላፊ መንገደኞችንም ሆነ የአሽከርካሪዎችን ምቾት ሳይነሱ ግንባታቸው የሚከናወንበት ሁኔታ የለም። ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንገዶችን ጨምሮ በርካታ መሰረተ ልማቶች ጉዳት ሲደርስባቸው ይታያል። ከዚህም ባለፈ የግንባታ ግብዓት ብክነትም አንዱ ችግር ነው።

 የግንባታ ግብዓት ብክነት ከፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ከኋላ ቀር የግንባታ ሥራና ሁሉን ነገር በወረቀት ላይ ጨርሶ ወደ ሥራ ካለመግባት ጋር የተያያዘ ነው። በተለይ ወደ ግንባታ ከገቡ በኋላ ሃሳብን መቀያየር ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ የሀብት ብክነትን እየፈጠረም ይገኛል። የግንባታ ግብዓቶች የጥራት ጉድለትም አንዱ በግንባታ ሂደት ለሚፈጠር ብክነት ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

 የዘመን ቀለም አልባዎቹ ህንፃዎች፣

 አንድ ግንባታ የተገነባበት ዘመን የሥልጣኔ አሻራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በአንድ ወቅት የሚገነቡ ህንፃዎች የዚያን ዘመን ማህበረሰብ የአስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ፍልስፍና እና እምነት እንደዚሁም የአኗኗር ዘይቤና የሥልጣኔ ደረጃ ያሳያሉ። የአክሱምን ኃውልቶች የሚያይ ጎብኚ ከአክሱም ጀርባ በጊዜው የነበረውን ስልጣኔ በምናቡ መቃኘት ይችላል። ላሊበላም ሆነ ፋሲል፣ የጀጎል ግንብም ሆነ ሌሎች ግንባታዎች ሲታዩ ከግንባታቸው ጥበብ ጀርባ ብዙ የሚናገሩት የዘመን ማስረጃ አላቸው።

 የሮም ከተማ የጥንት ህንፃዎች በጊዜው የነበረውን የሮማውያን ስልጣኔ በሚገባ የሚያሳዩ የሚገለጡ መጻሕፍት ናቸው። የሥልጣኔውንም ሂደት በጊዜ ቅደም ተከተል በሚገባ ያሳያሉ። ስድስት ኪሎ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዋና ህንፃ ከግቢው በር ጀምሮ ለተመለከተው ሰው፣ የብሔራዊ ቴአትርን ህንፃ ላስተዋለ ሰው፣ ማዘጋጃ ቤትን በሚገባ ለመረመረ፣ የኢትዮ-ጂቡቲን የለገሀር ባቡር ጣቢያ ህንፃ ላየ ሰው፤ በመዲናችን አዲስ አበባ በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ ምን አይነት የግንባታ ሥልጣኔ ዝንባሌዎች እንደነበሩ መረዳት ይችላል። በጊዜው የተገነቡት ህንፃዎችም ሆኑ ሀውልቶች የዘመኑን አሻራ ትተው ያለፉና የጊዜውን ቀለም የሚያንፀባርቁ ናቸው።

 በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በተለይም በመዲናችን እየተገነቡ ያሉት ህንፃዎች ግን እየተገነቡበት ባለው ዓመት ያለውን የማህበረሰብ የሥልጣኔ አሻራ የሚያንፀባርቁ ሆነው አይታዩም። እነዚህ ግንባታዎች የዘመናቸውን የእሳቤ ቀለም የያዙበት ሁኔታ የለም። ከዲዛይን እስከ ግንባታ ሂደት ዘመናቸውን የሚናገሩ አይደሉም። ቀለም አልባዎችና የተዘበራረቁ ናቸው።

አንድ ሰው ፀጉሩን አፍሮ ያበጠረ፣ ቤል ሱሪ ያደረገና የሸሚዙን የላይኞቹን ቁልፎች ፈታ አድርጎ ደረቱን እያሳየ የተነሳውን ባለጥቁርና ነጭ ቀለም ፎቶግራፍ ቢያሳየን ከፎቶው ተነስተን ዘመን መቁጠር እንጀምራለን።

 በሙዚቃ ደረጃም ቢሆን የአርባዎቹ፣ የሥልሳዎቹ፣ የሰባዎቹ፣ የሰማንያዎቹ እያልን ዘፈኖቹን ስንደረድራቸው ዘፈኖቹ የየዘመኑን የሙዚቃ እድገት ለውጥ እንድናይ ይረዱናል። ይህ ሊሆን የቻለው ሙዚቃዎቹ የየዘመናቸውን ማህበረሰብ የእድገት ደረጃ ቀለም የያዙ በመሆናቸው ነው። በኢትዮጵያ ኪነ ህንፃ ታሪክ ግን በተለይ ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት እንደ አሸን የፈሉት ህንፃዎች፤ ምንም አይነት የዘመን ተናጋሪነት አሻራ አይታይባቸውም። የተዘበራረቁና ቀለም አልባ ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top