ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአኙዋዎች “አጌም” ‹ንጉሥ ይገረፋል፤ ሰማይ ይታረሳል!›

በዚህ ርዕስ በቀረበው በአራተኛው ክፍል አጌም (ህዝባዊ ዐመፁ) የሚከተላቸውን ውጥረት የተሞላባቸው ደረጃዎችና ርምጃዎች ምን እንደሚመስሉ ተመልክተናል። የአጌሙ መሪዎችም ደም መፋሰስን በማስወገድ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚወስዷቸው የጥንቃቄ መንገዶች ምን እንደሆኑና ከዚህ በተቃራኒም ዐመፀኛው ኜያ (ንጉሥ) ወይም ኳሮ (የአካባቢ አለቃ) የአጌሙ ውጤት ወደየት እንደሚያመራ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ህዝባዊ ዐመፁን ለማክሽፍ እስከ መጨረሻዋ ቅፅበት ድረስ በበኩሉ ጀቡራዎቹን እና ቲያንጊዎቹን (ማለትም በባህሉ መሠረት የመጣው ቢመጣ ፈፅሞ ይክዱታል ተብለው የማይጠበቁ በአንድ ወራት አብረው የተወለዱ የእድሜ እኩዮቹን) በማስተባበርና በማስታጠቅ ዝግጅት የሚያደርግ መሆኑን አይተናል። ይሁንና የአጌሙ መሪዎች የጥንቃቄ መንገዶችን ለማስታወስ ያህል፡-

1ኛ/ በማንኛውም ሰዓት በድንገት ከቡራው (ከቤተ-መንግሥቱ) ገብተው ወይም ከቡራው ውጭ ዐመፀኛውን ኜያ ወይም ኳሮ በሚገኝበት በየትኛውም ቦታ በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚችሉ በሚስጥር የተዘጋጁ ፈጥኖ ደራሽ ህዝባዊ የጦር ቃፊሮችን በቅርብ ርቀት አስጠግቶ ከአጌሙ መሪዎችም ትዕዛዝ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ ማድረግ፤

 2ኛ/ በተለይም የቡራውን ጀቡራዎች (ዘቦች) በከንቱ የህዝብ ደም ከማፍሰስ በመታቀብ ከአባቶች መናፍስት ከሚወርድ አሸኒ (እርግማን) ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ ከቅዱስ አጌሙ ጎን እንዲቆሙና ድጋፍና ትብብራቸውን በገቢር እንዲያሳዩ በተገኜው አጋጣሚ፣ በተለይም በወላጆቻው ወይም በቅርብ የቤተሰቦቻቸው አባላት አማካይነት ምክርና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው በማድረግ ከጀቡራነት አገልግሎት ውጭ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤

3ኛ/ ጀቡራዎችን ጨምሮ ከቡራው ውስጥ በሚገኙ በሌሎች ደጋፊዎች በኩል በየቅፅበቱ የኜያውን ወይም የኳሮን የልብ ትርታ በማዳመጥ (በመሰለል) እንቅስቃሴና ስልት በዕይታ ውስጥ ማስገባት፣ ወዘተ. መሆናቸውን ተመልክተናል።

በዚህ የመጨረሻ ክፍል ትኩረት ሰጥተን የምንመለከተው የአጌሙ ዓላማ ስኬቶችና ውጤቶች ምንድን ናቸው? ኜያው ወይም ኳሮው በቁጥጥር ሥር ከዋለ የሚደርሱበት ቅጣቶች ምን ይሆናሉ? የት፣ በምን ሁኔታና እንዴት ይከናወናሉ? የቅጣቱ ባህላዊና ማህበራዊ አንድምታዎች ምንድን ናቸው? እኛስ ከባህላዊ ትውፊቱ ምን እንማራለን? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ነው።

የአኙዋ ታሪክና ልምድ እንደሚያሳየው ኜያውን ወይም ኳሮውን በቁጥጥር ሥር የማዋል እርምጃ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ውጤቱ ስኬታማ ከሆነ ሰላምን መልሶ ያሰፍናል። ስኬታማ ካልሆነ ደም መፋሰስን፣ በአጠቃላይም፣ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያስከትል በአደጋ የተከበበ ድርጊት በመሆኑ ነው። ስለዚህ የአጌሙ መሪዎች እርምጃውን እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የመምራትና ተፈላጊውን ኜያ ወይም ኳሮ ባልተጠበቀ ቦታና ጊዜ አስቀድሞ በሚስጥር በተዘጋጁ ህዝባዊ የጦር ቃፊሮች አማካይነት በቁጥጥር ሥር የማዋል ጥበብና ከባድ ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው።

 ኜያው ወይም ኳሮው በማንኛውም ዘዴ በቁጥጥር ሥር በዋለ ጊዜ በቅድሚያ በቡራው ውስጥ የተቀመጡትን የንግሥና ማለትም የህብረተሰቡን ሥልጣንና ሉዓላዊነት የሚወክሉ ተምሳሌታዊ ቁሳቁሶችን ቆጥሮ እንዲያስረክብ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ በህዝቡ ዘንድ በትረ-መንግሥቱን ተገዶ በውርደት እንደለቀቀ መቆጠር ብቻ ሳይሆን በባህል የታወቁ ቅጣቶችን ለመቀበል ይገደዳል። የቅጣት ዓይነቶችና የአፈፃፀም ሁኔታዎችም ቀጥለው የተጠቀሱትን ይጨምራሉ።

 ቅጣቶችን ስንመለከት፡-

 1. ሚስቱ/ሚስቶቹ እና ሀብቱ በሙሉ ይወረሳሉ። እነዚህም ቀጥሎ ለሚመረጠውና ለሚተካው ኜያ ይተላለፋሉ።

 2. ባጠፋው ጥፋት መጠንና ደረጃ በሀገር ሽማግሌ ተወስኖ 40፣ 50፣ 60፣ 70፣ 80 … የጅራፍ ግርፋት ይፈረድበታል።

3. በደንቡ መመሠረት ግርፋቱ የሚካሄደው በይፋ ወይም በአደባባይ ትንሽ ትልቁ የአገሩ ሕዝብ ተጠርቶ በተገኜበት ወይም በተሳተፈበት ሥነ-ሥርዓት ነው።

 4. የግርፋቱ ሥርዓተ-ክዋኔ በዚህ ሁኔታ ከተከናወነ በኋላ ከተገረፈበት አካባቢ ለቆ ሩቅ ወደሆነ እና የእናቱ ወገኖች ወደሚገኙበት ቦታ ሄዶ እንዲኖር ይደረጋል።

 5. በዚህ ሁኔታ ከሥልጣን ላይ በመውጣት የሀገሩን ባህል አርክሶ፣ በገዛ ፈቃዱ ተዋርዶ፣ የለቀቀ በመሆኑ ከእርሱ የተወለዱ ልጆች፣ የልጅ፣ ልጅ ልጅ፣ ልጆቹ፣ እሰከ መጨረሻው ድረስ ለሹመት (ለኜያነት ወይም ለኳሮነት) መመረጥ እንደማይችሉ (outcast እንዲሆኑ) ይደነገግበታል፣ ወይም ይደነገግባቸዋል።

መረዳት እንደሚቻለው ቅጣቶቹ እጅግ በጣም ከባድ ናቸው። ቢሆንም ዐመፀኛው ኜያ ወይም ኳሮ እነዚህን ለመሰሉ ቅጣቶች ከመዳረጉ በፊት ባህሉ ያበጃቸውንና የሚደግፋቸውን መልካም አማራጮች የመጠቀም ዕድል እንደነበረው ስንረዳ ደግሞ፡- “አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ፣ ኋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ!” ተብሎ የሚነገረውን የአባቶች ምፀታዊ አባባል ያስታውሰናል። ይህን በዚህ እንለፈውና ወደ ማጠቃለያው እናምራ።

አኙዋዎች ሁለት ዋና ዋና ባህላዊ የሰላም መንገዶች እንዳሏቸው በተከታታይ በቀረቡት እትሞች አይተናል። አንደኛው “ክወር” ሲሆን አገልግሎቱ በህብረተሰሰቡ አባላት መካካል የሚፈጠሩ ቀላልና ከባድ ግጭቶችን በጆዶንጎ (በሀገር ሽማግሌ) አማካይነት ለመፍታት የሚከናወን ትውፊታዊ መንገድ ወይም ዘዴ ነው። ሁለተኛው “አጌም” ሲሆን በህዝብና በባህላዊ መሪዎች መካከል የሚፈጠር ግጭት መፍትሔ የሚያገኝበት ትውፊታዊ መንገድ መሆኑንና ከሁለት የመፍትሔ አማራጭ መንገዶች እንደ ሁኔታው አንዱን ሊከተል እንደሚችል አይተናል።

አንደኛው የመፍትሔ አማራጭ መንገድ አጌሙ ከበሰለ በኋላ የሀገር ሽማግሎች ጥፋት ወደተገኘበት ኜያ ወይም ኳሮ ሄደው የህዝቡን ጥያቄዎች ይፋ ባደረጉለት ጥቂት ቀናት ውስጥ ጥያቄዎችን ተቀብሎ በመመርመር ደንቡን ተከትሎ ህዝቡን በመጥራት፡-

 ሀ) ጥፋት የሌለበት መሆኑን ገልፆ፣ ተከራክሮና አስመስክሮ ንጽህናውን አረጋግጦ ሥልጣኑ እንደያዘ መቀጠል፤

 ለ) ጥፋት መሥራቱን አምኖ ህዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ፣ ለወደፊት ከጥፋቱ ታርሞ መሻሻል በማሳየት ማገልገል እንደሚችል በእውነተኛ ልቦና በመጠየቅ ይሁንታ ከተሰጠው ሥልጣኑ እንደያዘ መቀጠል ናቸው።

ሁለተኛው በኜያው ወይም ኳሮው ዐመፀኛ ጠባይ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱትን የመፍትሔ አማራጮች በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ የኃይል ርምጃ በመውሰድ ከሥልጣኑ ማስወገድ ነው።

በባህሉ መሠረት “አጌም ግብ መትቷል” የሚባለው ከላይ በተጠቀሱት በአንደኛው ወይም በሁለተኛው መንገድ በተጠናቀቀ ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ በአኙዋዎች እምነት ሰላም ተመልሶ ይደሰታሉ። ከመደሰታቸው የተነሳም በህብረተሰቡ ላይ ያወርዱታል ተብሎ ይፈራ የነበረውን “አሼኒ” በምርቃንና በፀጋ ያውዱታል።

እንደተመለከትነው አጌም በግብታዊነት የሚነሳና በደመ-ነፍስ የሚከናወን አይደለም። ምክንያቱም መነሻ ምክንያት አለው። ዓላማና ግብ አለው። የክንዋኔ ስልትና ደረጃዎችን የተከተለ ነው።

 ስለዚህ በግብታዊነት የሚካሄድ ሳይሆን ሥርዓትን የተከተለ ነው። በመመጨረሻም ከአኙዋዎች የአጌም ባህል ምን እንማራለን? ወይም ምን ትምህርታዊ አንድምታዎችን እንቀስማለን? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። አንድምታዎች ብዙ ናቸው። ሆኖም እንደሚከተለው የተነሱትን ሦስት ዋና ዋና ነጥቦች በመጥቀስ ማጠቃለል እንችላለን።

 1ኛ/ በአኙዋዎች ባህል መሠረት ሥልጣን የህዝብ ነው። ባህላዊ መሪዎች ለሥልጣን የሚበቁት ደንቦችን በተከተለ የህዝብ ተሳትፎና ምርጫ ነው። ይህ የምርጫ ክንዋኔም በባህሉ አካልነት የተዋቀረና “ሮኒ” በሚል ፅንሰ- ሀሳብና ስያሜ ይታወቃል፤ ይሠራበታል። ይህን የመሳሰሉ ትውፊታዊ እሴቶች ጠቃሚ አንድምታ አላቸው። ይህም በሀገራችን ለዲሞክራሲ እድገትና ሥርፀት ባህላዊ መሠረትና ምንጭ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ የመሆናቸው ጠቀሜታ አንዱ ምሳሌ ይሆናል።

 2ኛ/ በአኙዋ የ“ሮኒ” የምርጫ አካሄድ መሠረት ለኜያነት ወይም ለኳሮነት የታጨን አንድ የህብረተሰብ አባል የመሪነት ብቃት ከሚያገለግሉት ዋነኛ መመዘኛ መሥፈርት አንዱ የግል ታሪክ መሆኑን አይተናል። ይህም በሮኒው የክንዋኔ ሂደት ላይ ቀርቦ ለመሪነት ብቁ መሆን አለመሆኑ በህዝብ ውይይት፣ ክርክርና ስምምነት ከተደረገ በኋላ ነው ግለሰቡ ለሥልጣን የሚበቃው። ይህ ባህላዊ አሠራርም እንደዚሁ የሚያመለክተው በተሳትፎና በስምምነት ላይ የተመሠረተ የዲሞክራሲ ሂደት ፅንሰ-ሀሳብን ሲሆን ለእድገት ልናውለው የሚችል ትውፊታዊ ዘዴ ያለን መሆኑን ነው።

3ኛ/ በዚህ ሁኔታ በአኙዋ ባህል መሠረት አንድን መሪ በምርጫ ለሥልጣን እንደሚያበቃ ሁሉ እንዳሻው እንዳይሆን – እንዳይፈልጥ – እንዳይቆርጥ፣ የሥልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ እንዳለው አይተናል። ይህም በበኩሉ የሚያመለክተው ባህሉ የመልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት፣ የተጠያቂነት፣ ወዘተ፣ ፅንሰ-ሀሳቦች በውስጡ ያከተተና ለእድገት እንደ መሠረት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል እሴት መሆኑን ነው። በጥቅሉ እነዚህን የመሳሰሉ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ድንቅ ባህላዊ ትውፊቶች፡ – እውቀቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሕጎችና ደንቦች፣ ወዘተ፣ ተጠንተው ለዘመናዊ ሕግ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለዲሞክራሲ፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለደህንነትና ለአእምሯዊ ልማት ማዋል እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ይሆናል ብየ አምናለሁ። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top