ከቀንዱም ከሸሆናውም

የታሪክና የባህል አሻራ ስለሆኑት ጌጣጌጦች በጥቂቱ

ጌጥ እንደወርቅ፣ ብር፣ ነሐስ፣ ኒኬል ከመሳሰለው ብረታ ብረት፤ እንደ ሉል፣ ጥርስ፣ አጥንት፣ የባሕር ውስጥ ዓሣዎች ቅርፊት ከመሳሰሉ እንስሳት፣ ከእንጨት፣ ከከበሩ ድንጋዮች የሚሠሩ ለግል ጥቅም፣ ለስጦታ፣ ለሽልማት፣ ለማስታወሻ የሚሰጡ ጌጦች፣ ችሎታ ባለው አንጥረኛ የሚሠሩ ናቸው። ወርቅም ሆነ አልማዝ፣ እንጨትም ሆነ ቅርፊት የጠቢቡ የፈጠራ ሥራ ካልታከለበት ጌጥ ሊሆን አይችልም። የጥንት ውበቱ እና ይዘቱ ከኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ ይሄዳል። ጥንት የነበሩት አልባሳት፣ የጦር መሪዎች ሜዳሊያዎች፣ ሽልማቶች፣ ከዘመናዊው ጋር ጭራሹኑ የተለዩ ናቸው ባይባልም፤ አንድ ናቸው ተብለው ግን አይወሰዱም። የጌጣጌጥ ሥራ ምንም እንኳን የዕድሜውን ያህል ባይመጥቅም ታሪኩ የ40 ሺ ዓመት ዕድሜ እንዳለው ይታወቃል።

ሰው በጌጣጌጥ መጠቀም እንዴት እንደጀመረ ከዚህ ጊዜ ነው ተብሎ ማስቀመጥ ቢያስቸግርም በዚህ ረገድ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ከእንስሳት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከሚገኙ ውጤቶች በአንገቱ፣ በእጁና በእግሩ እያሠረ መጠቀም ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ይገመታል። በዚህም መሠረት እንደሉል፣ የእንስሳት፤ በተለይም የባሕር ውስጥ እንስሳት ቅርፊት በሐረግ፣ በልጥ፣ በቃጫ ወይም በጭረትና በቆዳ የተንቆጠቆጡ ጌጦች ለውበት ማድመቂያ ይውሉ ነበር።

ዛሬም ቢሆን በባሕር ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎችን እንደዛጎል ሉል የመሳሰሉትን መልካቸውን ሳይለውጡ ሲጠቀሙባቸው ይታያል። ከባህር ርቀው የሚኖሩ ሰዎችም ቢሆን ለንግድ ከሄዱ ሰዎች በግዥም ሆነ በስጦታ መልክ በማግኘት ያምሩባቸዋል። ይሁንና ከባሕር ዳርቻ ርቀው የሚገኙ የጥንት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቀሙት ከቀንድና ከእንጨት፣ እንዲሁም በእጃቸው ከሚሠሯቸው ውጤቶችና የብረታ ብረት ማእድናት ነው። ማእድናቱ መውጣት ሲጀምሩ እንደወርቅ፣ ብር፣ ነሐስ፣ ኒኬልና የመሳሰሉትን ጌጥ ማበጀት እንደጀመሩ ሊታወቅ ተችሏል።

 ሰዎች በእግራቸው መራመድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደዛሬው ባማረና በተስተካከለ መልክ እንኳን ባይሆን እንዳለ ወይም አነስተኛ ለውጥ በማድረግ የላባ፣ የአጥንት፣ የዛጎል እና የተለያዩ ቀለሞች ያሏቸው ዶቃዎችን ከውብ ድንጋዮች እየሠሩ ይጠቀሙ ነበር። በተለይም በተለያዩ ቀለማት የተሠሩት ጌጦች ውበትን እየጨመሩ በመታየታቸው፤ በዚያው መጠን ጊዜውና የሰው ልጅ የደረሰበት ስልጣኔ የበለጠ ውብ እየሆኑ በአገልግሎት ላይ እንዲዉሉ ሆነ። ቀስ በቀስም ጌጣጌጦቹን የሰዎችን ማህበራዊ ሁኔታ፣ ደረጃ፣ ክብርና ማዕረግ በሚገልጽ መልኩ መጠቀም ተጀመረ። ለምሳሌ የሕብረተሰብ መሪዎች፣ ባለጸጋዎች፣ ተራ ሰዎችና ባሪያዎች የሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች ተለይተው ይታወቁ ነበር። ለምሳሌ ባሪያዎች የሚያደርጓቸው ጌጦች ጌቶቻቸው እነማን እንደሆኑ የሚያመለክቱ ሊሆኑ ሲችሉ ልዕልቶችና ልዑላን፣ ባለጸጋዎችና ጀግኖች፣ ሕጻናትና አዋቂዎች ከሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች ይለዩ ነበር። ጌጣጌጥ እንደየአገሩና አህጉሩ ባህል የሚለያይ ቢሆንም፤ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር የሚደረጉ ናቸው። አንዳንዶቹም ለብልቶቻቸው ይጠቀሙባቸው እንደነበር ይታወቃል።

 በአጭሩ፣ ጌጣጌጦች አንድ ሰው ማህበረሰቡ የሰጠውን ወይም ተጠቃሚው እራሱ ለግሉ የሰጠውን ደረጃ፣ የየትኛው ጎሳ፣ እምነት ወይም ማህበረሰብ አባል መሆኑን ለማመልከት፣ ከዓይነ ጥላ ወይም ከሌሎች ችግሮች ለመታደግ፣ ፍቅርን፣ ሐዘንና ደስታን ለመግለጽ ሊጠቀምበት ይችላል። ከዚህም ባሻገር ሰዎች ጌጣጌጥን የባለጸግነት መግለጫ አድርገው እንደሚጠቀሙበትና ለጋብቻ ለሚጠይቁት ወይም ለሚጠየቁት መክፈያ ያደርጉት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በዚህ ረገድ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ጥንታዊው ጌጥ በሞናኮ የተገኘው ሲሆን፤ ይህም ጌጥ 25ሺህ ዓመታት ያህል ዕድሜ ሊኖረው እንደሚችል ተገምቷል። በኢራንና በሌሎች የሜዲትራንያን አገሮች ከክርስቶስ ልደት ከ3000-400 እንደነበረ ሲታወቅ፤ በተለይም በሱመር የተገኘው የጥንታዊ ነገሥታት በአንባሬ አስከሬን የተቀመጠ አካል ላይ የተገኘው የራስ፣ የአንገት፣ የጣት፣ ወዘተ ጌጣጌጥ እንደዋና መረጃ ተደርጎ ይወሰዳል። በዚችው አገር ዳሪያ ኑር (ማለትም የባህር መብራት) እየተባለ ይጠራ የነበረ የከበረ ድንጋይ (አልማዝ) በጌጣጌጥነት ይጠቀሙበት እንደነበር የሀገሪቱ የጌጣጌጥ ታሪክ ያስረዳል።

ጥንታውያን ግብጾችም ከወርቅ፣ ከብርና ከሌሎች ማዕድናት የተሠሩ

“ሕንድ ጌጣጌጦችን ከዕለት ተዕለት ሕይወትና እምነት ጋር የተያያዘ እንዲሆን በማድረግ የምትጠቀስ አገር ስትሆን፤ ከእርሷም ጋር እንደፓኪስታን፣ አፍጋሃኒስታን ባንግላዴሽ የመሳሰሉ አገራትም ተመሳሳይ ተግባር አላቸው”

ጌጣጌጦችን ይጠቀሙ እንደነበረ በመቃብሮች ውስጥ ከተገኙ የነገሥታት አጽሞች መረዳት ይቻላል። የግብጽ ነገሥታት ስም ሲነሳ በውስጡ ግብጽን ይገዙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉበት ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ጥንታዊ የአክሱም ነገሥታት የወርቅ፣ የብር፣ የነሐስና የብረት ብር ነበራቸው ሲባል ጌጣጌጥም ይጠቀሙ እንደነበረ ይጠቁማል።

 በባህሬን በ170ሺህ የቀብር ስፍራዎች በተደረገው ጥናት ከ4000-300 ቅድመ ዓመተ ልደቱ ለክርስቶስ የተሠሩ ጌጣጌጦች ተገኝተዋል። በግሪክ የተገኙት ጌጣጌጦች ደግሞ እስከ 1200 ቅድመ ልደቱ ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሠሩ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ሲሆኑ፤ እነዚህም ጌጣጌጦች ዘውዶችን፣ የጆሮ ጉትቻዎችን፣ ቀለበቶችን፣ የአንገት ጌጦችንና የግሪክ አማልክት ምስሎችን የሚወክሉ ናቸው።

ሕንድ ጌጣጌጦችን ከዕለት ተዕለት ሕይወትና እምነት ጋር የተያያዘ እንዲሆን በማድረግ የምትጠቀስ አገር ስትሆን፤ ከእርሷም ጋር እንደፓኪስታን፣ አፍጋኒስታንና ባንግላዴሽን የመሳሰሉ አገራትም ተመሳሳይ ተግባር አላቸው። ሕንድ ከሌሎች በዙሪያዋ ካሉ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ቀዳሚ እንደሆነች ሲነገር፣ ከአውሮፓና ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጋር በዘረጋችው የንግድ መሥመር ምክንያት የጌጣጌጥ ምርቷን ለማስተዋወቅ የታደለች አገር ናት።

ከ5000-8000 ለሚሆኑ ዓመታት በባህልና በፖለቲካ ተቀባይነት በነበራት ሕንድ ስልጣኔዋን የጀመረችው ኢንደስ ተብሎ በሚታወቀው ሸለቆዋ ሲሆን፤ በዚህም የስልጣኔ ጮራ የፈነጠቀበት ሀገር ከ2100 ቅድመ ልደቱ ለክርስቶስ የብረታ ብረት ሥራ ይታወቅ እንደነበር ጥንታዊ የሀገሪቱ ታሪክ ያመለክታል። ሕንዶች በተለይም የከበሩ ድንጋዮችን በእሳት በማጋል ቀለማቸውን እንዲቀይሩ የማድረግ፣ ቅርጻቸውን የመለዋወጥና የማሠሪያ ቀዳዳ የማበጀት ጥበብ ተክነው ነበር። በሒንዱዎች እምነት ወርቅና ብር የተቀደሱ ማዕድናት ሲሆኑ፤ ወርቅ ጸሐይንና ሙቀቷን፣ ብር ደግሞ ጨረቃንና ቅዝቃዜዋን ይወክላሉ። በዚህም ምክንያት ነገሥታትና ተራው ሰው በወርቅና በብር ጌጦች አደራረግ በሕግ የተለያየ ደረጃ እንዲኖረው ተደርጓል። ለምሳሌ ወርቅን በእግራቸው ማሰር የሚችሉት ንጉሡ እና የንጉሣዊ ቤተሰብ አባላት (ማሐረጃዎችና ቤተሰቦቻቸው) ብቻ ናቸው።

ከሕንድ በተጨማሪ፣ ቻይና በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በጌጣጌጥ ሥራዋ የታወቀች ሀገር ናት። የቻይና የጌጣጌጥ ሥራ ከተፈጥሮ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። እንደ ዝሆን፣ ነብር፣ ጎሽና ዘንዶ ያሉ እንስሳት ለዚህ ተግባር በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

 ቻይናዊዋ ሕጻን

 ጥንታውያኑ ሮማውያንም ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከብረታ ብረቶች በተጨማሪ ከተለያዩ የከበሩ የድንጋይ ማዕድኖች ጌጣጌጦችን ይሠሩ እንደነበር ጥናቶች ያመለክታሉ። ይልቁንም በክንዶቻቸው ያሥሯቸው የነበሩ ጌጣጌጦች ከሌሎች ለየት ያሉ እንደነበሩ ይነገራል።

 የባይዛንታይን ሥርወ መንግሥትም (በ330ዎቹ ልደቱ ለክርስቶስ) በሥሩ ግሪክን፣ ግብጽን፣ መካከለኛው ምሥራቅን፣ ከፊል ራሺያን እና ከፊል ሰሜን አፍሪካን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ይገዛ ስለነበር፤ የእነዚህን አገሮች የጌጣጌጥ አሠራር ጥበብ አበልጽጎት እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያም ከአራቱ የዓለማችን ኃያላን አገሮች አንዷ ስለነበረች በዚያ ዘመን ተመሳሳይ ጌጣጌጦችን ትጠቀም እንደነበር መገመት ይቻላል። ይህም ወደፊት በሚደረጉ የአርኪዎሎጂ ምርምሮች እንደሚረጋገጥ አያጠያይቅም። የሚሠራውን ጌጥ ንጉሥ እንጂ ሌላ አያደርገውም።

በደቡብ አሜሪካም ከ5000 ዓመት ጀምሮ ሕብረተሰቡ ከልዩ ልዩ ነገሮች የተሠሩ ጌጣጌጦችን ይጠቀም ነበር። በተለይም አዜቲክ፣ ማያውያንና ሚክስቴክስ፣ ሞቻ የሚባሉት በዚህ ረገድ ጥንታዊ ታሪክ እንዳላቸው ይታወቃል።

ፔሯውያንም የአፍንጫ፣ የጆሮ፣ የደረት፣ ጌጣጌጥ በማድረግ ይታወቃሉ። አዜቲክ ነገሥታትና የሃይማኖት አባቶች ወደ አደባባይ በሚወጡበት ጊዜ አብዛኛው ሰውነታቸው በጌጣጌጥ ይሽፈን ነበር ይባላል።

 የሞቻ የጆሮ ጌጥ ከ1-800 ከክርስቶስ ልደት በኋላ

ሮበርት ማክኬ የተባለ ተመራማሪ ስለኢትዮጵያ ጌጣጌጦች ታሪክ አፍሪካን አርትስ ቅጽ 7፣ ቁጥር 4 ላይ እ.ኤ.አ. በ1974 በታተመ ጆርናል ላይ (ከገጽ 36-39) ማስፈሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ (UCLA James S. Coleman African Studies Center) ሌሎች ጥናቶች እንደሚያረጋግጡትም በኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጊዜ አንስቶ ጌጣጌጦች ከብዙ የማዕድናት ዓይነቶች እንደሚሠሩ ግልጽ ነው።

የኢትዮጵያ የጌጣጌጥ ሥራዎች

 የሰው ልጅ ብረት ካገኘ በኋላ ሕይወቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዴት እንደተለወጠ ማውሳቱን ትተን በጌጣጌጥነቱ አንጻር ብንመለከተው ከዚያን ጊዜ አንሥቶ የተያያዘና ራሱን የቻለ ሰፊ ታሪክ እንዳለው እንገነዘባለን። ከብረታብረቶች አንዱ የሆነው ወርቅ ለመጀመሪያ ጊዜ (ምናልባት በሜሶፖታሚያ ከ3000 ዓ.ዓ በፊት) ሲገኝ፤ በቀላሉ ለማጣጠፍና ወደ አስፈላጊው ቅርፅ ለመለወጥ የሚቻል ነበር። ይህ የወርቅ ፀባይ ሊመሳሰል የሚችለው ትንሽ ሞቅ ካለ የንብ ሰም ጋር ነው። ጠባዩ በቀላሉ ለመተጣጠፍ፣ ለመድቦልቦል፣ ለመጠፍጠፍ፣ እንደገና ደግሞ ለመዘርጋትና በዓይን ሊታይ እስከማይችል ድረስ ለመለጠጥ በመቻሉ የሠራተኞችን ስሜት ሳበ። በአሁኑ ጊዜም ከተለያዬ ብረታ ብረት ጋር በመቀላቀል እጅግ ጠንካራ እየሆነ ሊሠራ የሚችለውን ያህል 0.0001 ሳንቲ ሜትር ያህል ይቀጥናል። ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር በመዋሐድም ውሃ፣ አረንጓዴ፣ የደረቀ ቅጠል፣ ግራጫ፣ ሰማያዊና የመሳሰሉ ቀለማትን ይይዛል። ከወርቅ ቀጥሎም ብር ለጌጣጌጥነት የሚመረጥ የብረታ ብረት ዓይነት ነው።

ብር፣ ከብረታ ብረቶች ሁሉ በላቀ ሁኔታ ወደፈለጉት ዓይነት ቅርፅ ሊለወጥ የሚችል ነው። የምዕራባውያን ጠበብት ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በትንሹ ኤስያ ሂሳርሊክ በሚባለው ስፍራ ነው። ይህም ስፍራ ሆሜር በትሮይ ከተማ የጠቀሰው ስፍራ እንደሆነ ተመልክቷል። ይህ ማእድን የተገኘው በዘመነ ሔለን ሲሆን፤ በ17ኛው፣ በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ለጌጣጌጥ ሥራ ከፍተኛ ስፍራ ነበረው። በተለይም እንደ አልማዝ ለመሳሰሉት የከበሩ ድንጋዮች የፈርጥ ማስቀመጫ በመሆን የሰጠው አገልግሎት በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

 ከወርቅና ከብር ቀጥሎ የጌጣጌጥነት አገልግሎት የሚሰጠው ማዕድን ፕላቲኒየም ሲሆን፤ ይህም ማዕድን በብዛት የማይገኝ ቢሆንም በንጣቱ፣ በቀላሉ በመታዘዙ፣ አሲድ በቀላሉ የማይበግረው በመሆኑ ከፍተኛ የእሳት አደጋ ቢደርስበትም እንኳን እንደሌሎቹ ማዕድናት በቶሎ የማይቀልጥ በመሆኑ ይመረጣል። ከወርቅ ከብርና ከፕላቲኒየም በተጨማሪ እንደ አልማዝ አምበር፣ ፐርል፣ ሩቢስ፣ ኮሩንደም፣ ኤመራልድ፣ ቤርል፣ ክርስቶቤል፣ ቶፓዝ፣ ዚርኮን የመሳሰሉት ሁሉ ለጌጣጌጥነት ሥራ ይውላሉ። ይሁንና እነዚህ የተጠቀሱት ሁሉ ጥራትና ደረጃ እንዳላቸው ደግሞ መታወቅ አለበት። ከነዚህ በጣም ዝቅ ብለው የሚታዩት ደግሞ ኮራል፣ መስተዋት፣ እንጨትና ሴራሚክስ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከፕላስቲክ ግሩም ድንቅ ጌጣጌጦች በመሠራት ላይ ናቸው።

የጌጣጌጥ ሥራዎች ከምንም ይሠሩ ከምን አብዛኛውን ጊዜ የሚያንጸባርቁት የየሀገሩን ባሕል ነው። በዚህም መሠረት እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ሀገሮች አንበሳ፣ ጦር፣ ጋሻ፣ ዘውድ የመሳሰሉትን ሲያዘወትሩ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ብርቅዬ የሆኑ አእዋፍን፣ ላባዎቻቸውን፣ ነብር፣ ተኩላ፣ ግመል፣ ጎራዴ፣ ዶሮ የመሳሰሉትን ያዘወትራሉ። የሆኖ ሆኖ የጌጣጌጥን አሠራር ታሪክ ሰፋ አድርገን የተመለከትን እንደሆነ ወደ ኤፍራጥስና ጤግሮስ፣ ወደ አባይ፣ ወደ ያንግ ቲዝና ወደመሳሰሉት የሥልጣኔ ምንጭ የሆኑ ወንዞች ማተኮራችን አይቀርም። እነዚህም በወንዞች ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች በደለበው መሬት የእርሻ ሥራቸውን እያገኙ ኑሯቸውን እያሻሻሉ፣ ሥልጣኔን እያስፋፉ ሲሄዱ የማዕድናትም ጥቅም እየተከሰተላቸው፣ የጌጣጌጥ ባለቤት የመሆን ፍላጎታቸው እየዳበረ መጣ። ለጌጣ ጌጥ ከተጠቀሙባቸው ማዕድናት መካከልም ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች ይገኙባቸዋል።

 ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ ይደረግ የነበረው ጌጥ በመላው አካል እስኪደረግ ድረስ ቀጠለ። በዚህም መሠረት ለራስ ዘውድ፣ አክሊል፣ ወለባ፤ ለጆሮ፣ ለአፍንጫና ለከንፈር ጉትቻ፤ ለአንገትና ለደረት ሐብል፣ ድሪ፣ ጠልሰም፤ ለወገብ ቀበቶና ዝናር፤ ለጣቶች ቀለበት፤ ለእጅ አንባር፤ ለእግር አልቦ … እያለ የመላ አካላቱን ልዩ ልዩ ክፍሎች በጌጣጌጥ ማስዋብ ባህል ሆነ።

 በጣም ጥንታውያን የሚባሉት ጌጦች የተገኙት ዛሬ ቶል አልሙቋያር ተብሎ በሚጠራው ያኔ ኡር ተብሎ በሚታወቀው የሱማሊያ ግዛት ንግሥት ከነበረችው ከፖ- አቢ መቃብር ውስጥ ሲሆን፤ ይህ ጌጣጌጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት 3ኛ ምዕተ ዓመት እንደተሠራ ይገመታል። የዚችም ንግሥት አካል የላይኛው ክፍል ደረቷ፣ አንገቷ፣ ራሷ፣ እጇና ጣቶቿ በተገመደ ወርቅ፣ በብር እና በመሳሰሉት ጌጣጌጦች አሸብርቆ እንደነበረ ያመለክታል። ይህም የጌጣጌጥ ሥራ በወቅቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበረ የሚያመለክት ነው።

 እ.አ.አ 1567-1320 ቅድመ ክርስቶስ በነበረው ጊዜም የግብጽ ፈርኦኖች ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስና ከመሳሰሉት ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ያደርጉ እንደነበረ ሲታወቅ፤ የዛኔው ዘመን ወርቅ አንጣሪዎችም እንደነበሩ የሚያመለክት ነው። በተለይም በንግሥት አሸወቴፕና ቱታንካሜን በተባለው ፈርኦን መቃብር ውስጥ በተለያዩ የወርቅ ማስቀመጫ ሣጥኖች የተገኘው ጌጣጌጥ ጥራት ያለው ብቻ ሳይሆን የአንጥረኞቹንም መራቀቅ የሚያመለክት ነው።

 በሜዲትራንያን ባሕር ውስጥ በሚገኙት በተለይም ለግሪክ፣ ለአፍሪካ፣ ለኤስያ ቅርብ የሆኑት ደሴቶች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይታይባቸው ስለነበረ ከ2 ሺ ዓመት ቅድመ ክርስቶስ አካባቢ የታወቁ የወርቅ አንጣሪዎች ነበሩባቸው። ሜቄዶንያም እንደሌሎቹ ጥንታውያን ግዛቶች በንግድ ሥራ ብቻ ሳይሆን በዕደ ጥበብ ሙያም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር። ከስፔንና ከጣሊያን ጋር በነበራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በ8ኛውና

“በአሁኑ ጊዜ በበለፀጉ አገራት ጥራት ያላቸው ጌጣጌጦች የሚመረቱ ሲሆን፤ በጌጣጌጥ ገበያ አሜሪካ ከፍተኛውን ድርሻ ይዛ ትገኛለች። በዚህም መሠረት ይህችው በኢኮኖሚ የገዘፈች አገር በዓለም 30% ያህል ድረሻ ሲኖራት፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ቻይና ከ8-15%፣ ኢጣሊያ 5%፣ መካከለኛው ምሥራቅ 9% ድርሻ እንደሚኖራቸው ይገመታል።”

 በ7ኛው ክፍለ ዘመን (ቅ.ክ) ይህንኑ የጥበብ ሙያዋን አስተዋውቃለች። በ7ኛውና በ6ኛው ክፍለ ዘመን (ቅ.ክ) የነበረችው ግሪክም ወደ ታናሿ ኤስያ ወደ ደቡባዊ ጣሊያንና በባልካን ወሽመጥ ሥልጣኔዋን ስታስፋፋ የዕደ ጥበቡንም ሥራ አስተዋውቃለች። በ3ኛውና በ2ኛው ክፍለ ዘመንም (ቅ.ክ) የሄለኒስቲክ የወርቅ ሥራ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እንደነበረ ለመረዳት ይቻላል።

 እንደ ግሪክ፣ ግብጽ፣ ሉሜሪያና ፊንቃውያን ሁሉ፤ ሮማውያን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ግሩም ድንቅ የዕደ ጥበብ ሥራ ይሠሩ እንደነበረ ይታወቃል። በዘመነ ሬናሴንስ ደግሞ በጣሊያን፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ ለራስ፣ ለደረት፣ ለእጅና ለእግር (እስከጣቶቻቸው) ይደረግ የነበረው ጌጥም ልብስ ላይ እየተለጠፈ ይለበስ ጀመር። በዚህ ዘመን ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ ከልዩ ልዩ ማዕድናት የሚሠሩ ጌጣጌጦች በጣሊያን እንደ ቬንቬኒቶ ሴሊኒ እና ሊዮናርዶ ዳቪንቺ፣ በፈረንሳይ ዱቬ፣ ኢቴን ደሊዮን እና ፍሌሚንግ አብርሃም የመሳሰሉት ንድፍ አውጭዎችን በመጠቀም ይሠሩ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።

 የጌጣጌጥ ሥራ በልዩ ልዩ ሀገሮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ቢሆንም፤ ይጠቀሙበት የነበሩት የቤተ መንግሥት ሰዎችና የመንግሥቱን ሕልውና አጠናክረው ይዘው የነበሩ ባለሥልጣኖች ነበሩ። በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሔድ ግን ተራው ሕዝብ ሁሉ በወርቅ፣ በብር፣ በአልማዝና በመሳሰሉት የከበሩ ድንጋዮች ባይሆንም በሚመስሉ ጌጣጌጦች መጠቀም ጀመረ። ሥራው ከእጅ ወደ ማሽን ሥራ ሲሸጋገርም ጥንት እጅግ በጣም ውድ የነበረው ዋጋ እያዘቀዘቀ መጣ። ጥቂት ግለሰቦች ያካሂዱት የነበረው ሥራም ወደ ኢንዱስትሪ በመለወጡ የሠራተኛው ቁጥር ከተጠቃሚው ብዛት ጋር ማደግ ጀመረ። የሥራ ክፍፍሉም መልክ በመያዝ እንደማንኛውም የሚገጣጠም ዕቃ ሁሉ ነዳፊ፣ አቅላጭ፣ ቅርፅ አውጭ፣ ፈርጥ ጨማሪ ወዘተ ተብሎ ተመደበ። ከአንዱ ባለጌጥ ፋብሪካ ሌላው እየተወዳደረ አንድ ሁለት ተብሎ የሚጠቀሰው ሥራ ቁጥር ስፍር የሌለው ሆነ። ወርቅን፣ ብርን፣ ፓላቲኒየምን፣ ከልዩ ልዩ ማዕድናት ጋር በመቀላቀል ብቻ ሳይወሰን ብረት እንኳን እራሱ ከሌሎች የብረታ ብረት ዓይነቶች ጋር እየተቀላቀለ መሠራት ጀመረ። የዘመኑ አርቲፊሻሎች ሁሉ የኢንዱስትሪው አብዮት ውጤቶች ናቸው።

 በአሁኑ ጊዜ በበለፀጉ አገራት ጥራት ያላቸው ጌጣጌጦች የሚመረቱ ሲሆን፤ በጌጣጌጥ ገበያ አሜሪካ ከፍተኛውን ድርሻ ይዛ ትገኛለች። በዚህም መሠረት ይህችው በኢኮኖሚ የገዘፈች አገር በዓለም 30% ያህል ድርሻ ሲኖራት፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ቻይና ከ8- 15%፣ ጣሊያን 5%፣ መካከለኛው ምሥራቅ 9% ድርሻ እንደሚኖራቸው ይገመታል።

 ምንም እንኳን አገራችን ከጥንታዊ ጌጣጌጥ አምራች አገሮች ተርታ የምትመደብ ቢሆንም እንደ ዕድሜዋ በዚህ ኢንዱስትሪ ያላት ጉዞ አዝጋሚ ነው። ዛሬም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የተመረቱ ጌጣጌጦችን ለገበያ ታቀርባለች። ይሁንና ጌጣጌጦቻችን የሀገራችንን የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት የስልጣኔ አሻራ የሚያንጸባርቁ ሆነው እንዲገኙ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top