በላ ልበልሃ

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጸጋዎችና ሳንካዎች በኢትዮጵያ

ባለፉት ተከታታይ እትሞች ስለ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጸጋዎችና ሳንካዎች ብዙ ተነጋግረናል። ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ከሰው ልጆች የተግባቦት ባህርይ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ላይ የታዩትን ዝንፈቶችና መልካም ገጽታዎች እንዲሁም አሁን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ለሚስተዋሉት እንከኖች መንስኤ የሆኑትን ገፋኤ ኃይላት በሰፊው አይተናል። የቴክኖሎጂ ገዥ መንፈስ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚውን ምን ያክል እንደጠቆጣጠረው፣ ስሜት በተጫናቸው ጸሐፊዎችና ለህዝብ ነጻነት በሚዋጉት መካከል ያለውን ልዩነት መለየት እጅግ በጣም አዳጋች ከመሆኑም በላይ እንደ አገር ለመቀጠል የሚያስችለንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በጎ ገጽታ እንዳይኖረው አድርጎታል። ከዚህ ሁሉ ችግር መውጫው ቀዳዳ በየት በኩል ነው? የዘመናችን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ምን ትሩፋቶችን ሊያስገኝ ይችላል? የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የአገር ሰላም፣ የዜጎችን አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ደህንነት የሚጎዱ ተጠቃሚዎችን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? ይህንን ማድረግስ የማን ኃላፊነትና ድርሻ ነው? ይህ የማጠቃለያው ክፍል እነዚህን ጥያቄዎች ማዕከል ያደረገ ነው።

፰. ማጠቃለያ:- ምን ይሻላል?

አሁን እያስተዋልናቸው ካለነው ጥፋቶች ተላቆ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ለመልካም ዓላማ ማዋል ይቻላል። ባለፉት ዓመታት ምን ምን መልካም ሚናዎች እንደተጫወተ በባለፉት እትሞች አይተናል። ከነዚያ በተጨማሪ ሌሎችም ጥቅሞች ይኖሩታል። ለምሳሌ:- በቦታ ተራርቀው የሚገኙ የኢትዮጵያውያንን ባህሎች በማስተዋወቅ አንዱ ከአንዱ የሚማራቸውን መልካም ልምዶች ማካፈል የሚያስችል ምቹ የተግባቦት መንገድ ነው። የአንዱ ባህል ባለቤት ስለ ባህሉ መልካም ልምዶች ለሌላኛው በማስነበብ በአገራዊ ህጎች፣ የትምህርት ፖሊሲዎች፣ እንዲሁም ማንኛውም ማኅበረ- ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄነት ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ትውፊቶችን መወራረስ ይቻላል። ይህም ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ አገር በቀል እውቀቶችንም ጭምር ማጋራትን ያጠቃልላል።

 ከዚህ በተጨማሪ በዘመን ተራርቀው የሚገኙ ትውልዶችን ማነጋገር የሚቻለበትን መንገድም ማመቻቸት ይቻላል። የታሪክ፣ የባህልና የቅርስ ጥናት ባለሙያዎች ለማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በሚመጥን መንገድና በቀላል አቀራረብ የምርምራቸውን ግኝቶች፣ እንዲሁም የግል ልምዶቻቸውን በማካፈል ለአሁኑ ትውልድ የአስተሳሰብ አድማስ መስፋት የራሳቸውን ሚና መጫወት ይችላሉ። ሁሉም ከሃሜትና ከ “በሬ ወለደ” ተራ ወሬ፣ ከመሰዳደብና የጽያፍ ንግግር ነጻ በመውጣት ለሌሎች የእውቀት እና የአስተሳሰብ እድገት ይጠቅማል ያለውን ቢጽፍ አንባቢውንም ከወሬ ሱስ ወደ እውቀት ጉጉት፣ አዲስ ነገርን ወደ መስማት ፍላጎት መቀየር ይቻላል።

እያንዳንዱ የፌስቡክ አክቲቪስት “ነጻ አወጣዋለሁ” ከሚለው ማኅበረሰብ ባህል መልካም ተሞክሮዎች ለሌላው ማካፈል፣ ሁሉም በጋራ የሚጠቀሙበትን አገር ለመገንባት እንቅፋት የሆነውንና ጠፍሮ የያዘውን ገዥ መንፈስ ለማስወገድ በመትጋት ጠንካራ የጋራ ማኅበረ-ፖለቲካዊ መስተጋብር መዘርጋት ይቻላል። የመጣበትን ማኅበረሰብ የባህል፣ የሃይማኖትና የታሪክ መልካም እሴቶችን ሳይጋፋ፣ ለሙያው ክብር ታማኝና ቀና በመሆን ለሰው ልጆች ሁሉ ደህንነትና መልካም መጻኢ እድል የሚበጀውን ሐሳብ ሊያንጸባርቅ ይገባል። ይህንን ለማድረግ ሁሉም ከብሔር ወይም ነገድ ጠባብ ጓዳው ወጥቶ ዓለምን በከፊል አጮልቆ ከሚያይበት ጠንጋራ መነጽር ተላቆ፣ ለሁሉም የሰው ልጆች ደኅንነትና ውብ ተፈጥሮን (Ecosystem Welbeing) እውን ለማድረግ ቢታትር ከሚያናቁሩን፣ ከሚያደናቁሩን የፈጠራ ወሬዎች ተላቆ በዓለም መድረክ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነ ዜጋን እውን ማድረግ ይቻላል።

 በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመዋጋት ሰዎችን በማሰባሰብ ረገድ እንደ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሁነኛ መሳሪያ ያለ አይመስለኝም። መረጃ በሽርፍራፊ ሰከንዶች በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በሚደርስበት በዚህ ወቅት፤ የሕይወት ፈተና የተጋረጣባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት የሚያስችል መንገድ ለማመቻቸት ቀላል ነው። በተለያዩ ዓለማት እንደምናየው እንደ “Go Fund Me” ዓይነቶቹ መርሃ ግብሮች በቀላሉ የተሳካ ውጤት የሚያስገኙት በማኅበራዊ መገናኛ የክተት አዋጅ ጥሪ ነው።

መረጃን በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው በማስተላለፍ ረገድ በእጅጉ ፈጣን በመሆኑ በቀላል ወጪ አያሌ ጥቅሞችን ማግኘት ይቻላል። በየደቂቃው የሰቆቃ ወሬዎችን ብቻ ሳይሆን አስደናቂና ጠቃሚ መረጃዎችን ለተጠቃሚው በማቅረብ ሕይወትን ምቹ፣ አገልግሎችን ቀልጣፋ የሚያደርጉ መንገዶችን መቀየስ የሚያስችል መልካም ገጽታውን ማስፋት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በወረቅትና በግድግዳዎች ላይ ብቻ የተወሰኑትን ማስታወቂያዎች፣ በአብያተ መጻሕፍት መደርደሪያዎች የተገደቡትን የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወዘተ ለማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በሚመጥን መልኩ ማቅረብና ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ ይቻላል። የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶች ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ ህጎችና ደንቦች፣ የዕለት ተዕለት አሰራር ጠቋሚዎች ወዘተ በቀላሉ ለህዝቡ እንዲደርሱ በማድረግ ተገልጋዮቻቸው መብትና ግዴታዎቻቸውን አውቀው ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉና ከአላስፈላጊ የቢሮክራሲ እንግልት እንዲላቀቁ ማድረግ ይቻላል።

በባለፉት ክፍሎች ያየናቸውን ጥፋቶች ለማስቆምና ከጸጋዎቹ ተጠቃሚ ለመሆን የመጀመሪያው መንገድ ማኅበራዊ ፍትሕን ማስፈን ነው። በሃብታሙና በድሃው፣ በፖለቲካ መሪውና በዜጋው መካከል ያለውን የሰማይና የምድር ያክል የተራራቀ ሕይወት ማጥበብ፣ ማቀራረብ አለብን። በዚህም ተስፋ የቆረጡትን፣ አኩራፊ ወጣቶችና የጉስቁልና ሕይወት የሚመሩትን ድሀ ዜጎች ልብ ስብራት መጠገን ያስፈልጋል። በድሃው ሕይወት ላይ ዳንኪራ የሚመቱትን ሐብታሞች፣ ልበ ደንዳና ጨካኝ የፖለቲካ መሪዎች ደግሞ በዲሞክራሲና በሥነ-ምግባር መርሆዎች፣ በሕጋዊ እርምጃዎች ልጓም መግራት ያስፈልጋል። የጋራ አገር ሲባል ጸጋዋም ፍዳዋም ለሁሉ እኩል የሚዳረስባት እንጅ አንዱ ኗሪ፣ ሌላው የበይ ተመልካች አኗኗሪ ሆነው የጎሪጥ የሚተያዩባት መሆን የለባትም።

አሉን የምንላቸው ባህላዊና ዘመናዊ የሰውን ልጅ ባኅርይ የሚገሩና አስተሳሰቡን የሚያርቁ፣ የሚያበለጽጉ ተቋሞቻችንም የጋራ ችግራችንን መፍታት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል። ምንም እንኳ የሃይማኖትና የፖለቲካ

“በየደቂቃው የሰቆቃ ወሬዎችን ብቻ ሳይሆን አስደናቂና ጠቃሚ መረጃዎችን ለተጠቃሚው በማቅረብ ሕይወትን ምቹ፣ አገልግሎችን ቀልጣፋ የሚያደርጉ መንገዶችን መቀየስ የሚያስችል መልካም ገጽታውን ማስፋት ያስፈልጋል”

መለያየት ሕገ መንግሥታዊ መርህ ቢሆንም፤ ሃይማኖተኞች የሃይማኖታቸውን መልካም እሴት በማኅበረ-ፖለቲካዊ ሕይወታችው ውስጥ በማንጸባረቅ ተምሳሌታዊ ሚናን ሊጫወቱ ይገባል። የትምህርት ተቋሞቻችንም የጥንት ግሪክ ፈላስፎች እንዳሉት በሰዎች ዘንድ ባኅርየ “አራዊትነትን” ሊቀርፉና ሥነ- ምግባራዊ በጎነትን ሊያመጡ ይገባቸዋል። የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ቁጥጥር እንደዚህ ባለው ተዘዋዋሪ መንገድ እንጅ ፌስቡክን በመዝጋት ወይም ግለሰቦችን በማሰርና በማንገላታት ዘላቂም ጊዜያዊም መፍትሔ እንደማያመጣ አይተናል። የዚህ ማኅበረ- ፖለቲካዊ በጎ ተግባቦት እንደ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ያሉትን የዘመኑ ጸጋዎች ተጠቅሞ ለቀጣዩ ትውልድ ያደገች አገርን ለማውረስ በጋራ የሚሰራ የመንፈስ ትስስርን መፍጠር ይቻላል።

 ስለዚህ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ መልካም አገር በቀል እውቀቶችን የምንጋራበት፣ ወንዝ ተሻጋሪ (ብሔር ተሻጋሪ) ኅብረቶችን በመፍጠር ለሰብአዊነት ዓላማ የሚውሉ የሐሳብና የገንዘብ መዋጮ እድርተኞችን የሚያሰባስብ፣ በአገራዊ ፖለቲካ ኢ-ዲሞክራሲያዊና ጨቋኝ አገዛዞችን በጋራ የምንዋጋበት የህዝብ ዓይንና ጆሮ፣ የተጨቆኑ ድምጾች የሚስተጋቡበት ነጻና ገለልተኛ ልሳን መሆን ይችላል።

 ይህ እንዲሆን የማን ኃላፊነት ነው? የሁሉም! የእያንዳንዱን የተናጠል ድርሻ ለመተንተን ቦታው ባይበቃም! ሁሉም ከመለያየት መሰባሰብን እያሰበ ቢሰራ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ለዚህ ዓላማ አማራጭ መንገድ እንደሆነ መገንዘብ ከባድ አይደለም። ሁሉም ሙያውና ማኅበራዊ ግዴታው የሚጠይቀውን በጎነት በቀናነት ሊሠራ ይገባል። በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የእኩይ ዓላማ ያላቸውን አካላት ለመቆጣጠር በርካታ አማራጮች አሉን። የመጀመሪያው እያንዳንዱ ጸሐፊ ስለሚጽፈው ጉዳይ ይዘት፣ እውነትነት፣ የቋንቋ አጠቃቀም እና የአንባቢ ሥነ-ልቡና ላይ ሊጨነቅ ይገባል። ሁሉም በሚናገረውና በሚጽፈው ጉዳይ ተጠያቂ እንደሆነ ሊገነዘብ ይገባል። የውሸት ወሬ መንዛት፣ ዘለፋዎችና የጥላቻ ንግግሮች በወንጀል እንደሚያስጠይቁ ማንም አይክደውም። ይህንን እውነታ መዘንጋት በፌስቡክ በርካታ ተከታይ ካላቸው “ከታላላቅና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች” ሳይቀር እያየነው ነው።

 ሁለተኛው የማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ በሚኖርበት አካባቢ ተፈጸሙ ስለሚባሉ የሐሰት ወሬዎች ማስተባበያ መስጠት እና ወንጀለኞችን ማጋለጥ መቻል አለበት። በድሮ ጊዜ ወንጀለኛን አድኖ ለመያዝ ዘመናዊ የፖሊስ ምርመራ ዘዴዎችን መከተል ወይም ቴክኖሎጅን መጠቀም አይቻልም። ይህንን ለማድረግ ህዝባዊ ስብሰባ (አፈርሳታ) በማዘጋጀት ሁሉም አየሁ፣ ሰማሁ፣ አውቀዋለሁ ያለውን መረጃ በታማኝነት በመለገስ ወንጀለኛውን በቀላሉ ማጋለጥና መቅጣት ይቻል ነበር። አሁንም የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚው ማኅበረሰብ አፈርሳታ መውጣት ይኖርበታል። ስህተትን እያዩ አለማጋለጥ፣ ይባስ ብሎ ውሸት እንደሆነ እያወቁ ጸሐፊውን በማድነቅ የልብ ልብ መስጠት፣ እውነት ሲጋለጥ ደግሞ በወገንተኝነት ስሜት ከማናናቅና ጸሐፊውን ከማሸማቀቅ ይልቅ፤ ሁሉም ውሸትን የማስተባበልና እውነትን የማበረታታት ሥነ-ልቡናዊ ድፍረት፣ ምክንያታዊ በራስ መተማመን፣ ቀናነትና ታማኝነት ሲጎናጸፍ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃኑ ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበት መንገድ ይመቻቻል።

መንግሥት የአገር መሪነቱን ኃላፊነት ስለወሰደ የዜጎችን ደኅንነት የሚፈታተኑትን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ተጠቃሚዎችን በንቃት በመከታተል እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። አንዳንድ ታዋቂ የፌስቡክ አክቲቪስቶች የተሳሳተ መረጃ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅር፣ የሚያጋጭ ሐሳብ በሚሰነዝሩበት ጊዜ መረጃውን ማስተባበል፣ ማውገዝ በአካል ጠርቶ ማናገር፣ ለተናገሩት ነገር በህዝብ ፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ (The Burden of Proofe)፣ ወይም ማስተባበያና ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ፤ ከዚያም ባሻገር የማይታረሙ ከሆነ በህጉ መሰረት ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።

 የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ህጎችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን በማውጣት እነሱን ተላልፎ የሚገኘውን አካል ህጋዊ ሂደቱን በተከተለ መንገድ መቅጣት ይኖርበታል። በበርካታ አገራት የመገናኛ ብዙኃን መርሆዎችና የአጠቃቀም ህጎች ተግባራዊ እንደሆኑ ይታወቃል። በእኛም አገር መሰል ህጎች ተግባራዊ ቢሆኑ ኃላፊነት የማይሰማቸውን ተጠቃሚዎች ለተወሰነ ጊዜ ከማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚነት በማገድ እንዲሁም፤ ገጻቸውን እስከ መዝጋት የሚያደርስ እርምጃ መውሰድ ይቻላል። ይህንንም ከሐሳብ ነጻነት፣ ከሰዎች የመናገር መብት እንዲሁም ከሕዝቡ መረጃ የማግኘት መብት ጋር በማይጋጭ መልኩ በመተግበር ማንኛውም ወንጀል የሰራ ሰው እንደሚቀጣው ሁሉ፤ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሩ ወንጀሎችንም የምንቀጣበት ህግ ማውጣት ያስፈልጋል።

 እንደ ሉዓላዊት አገር የዜጎቿን ህልውና የሚጋፉትና በብዕር ስም እንዲሁም ማንነታቸውን ደብቀው የሚጽፉትን አካላት ለመቆጣጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስገባት እኩይ ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱትን አካላት መቆጣጠር ይቻላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ፌስቡክን እና መሰል ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ከሚመሩት አካላት ጋር በመነጋገር ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ጠንካራ አገራዊ አቋም ሊኖረን ይገባል።

 በእርግጥ ሰዎችን በኃይል ማስቆም አሰልቺና አድካሚ፣ ፍሬያማነቱም አመርቂ ላይሆን ይችላል። ይህ የመጨረሻው አማራጭ እንጅ ተቀዳሚውና ብቸኛው እንዳልሆነ ከላይ አይተናል። ተቀዳሚው ነገር ከህግና ቁጥጥር ይልቅ ዜጎቹን የሚያስደስቱ እንዲሁም ማንነታቸውን የሚያንጸባርቁበት ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምህዳር ማስፋት፤ በሥነ-ምግባርና በእውቀት ጠንካራ የሆኑ ዜጎቹን የሚያፈሩ ተቋማትን ማጠንከር፣ እንዲሁም የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚው እርስ በእርሱ እንዲተራረም የሚያስችል ባህልን መፍጠር እንደሆነ አጽንኦት ለመስጠት እወዳለሁ። ከዚህ በተጨማሪ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም እንዲሁም የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና የሚያስከትላቸው ፈተናዎች በደንብ ተጠንተውና ተተንትነው በመቅረብ በህዝቡ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ የመንግሥትና የምሁራን ድርሻ ነው።

 ይህ ጽሑፍ በአብዛኛው የግል ትዝብቶች ላይ የተመሠረተ እንጂ የገንዘብ ድጎማ፣ የተመቻቸ ጊዜና ቦታ ተሰጥቶት የተደረገ ጥናት አይደለም። በመጀመሪያው ክፍል ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው፤ የባህል ጥናት፣ የቋንቋ ጥናት፣ የፖለቲካ ሳይንስ ጥናት፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንና የተግባቦት ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ፖሊሲ አውጭዎች እንዲሁም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወዘተ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከማኅበራዊ መገናኛ ሳንካዎች ተላቀን ጸጋዎቹን የምናጣጥምበትን መንገድ ሊያመቻቹ ይገባል። ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ከስሙ እንደምንረዳው ሁሉም የሚጠቀምበት የማኅበረ ሃብት ነውና ችግሩን ለመቅረፍ እንዲሁም ጥቅሙን ለማጣጣም የሚያስችለውን መንገድ መቀየስም ለሁሉም የተተወ ኃላፊነት ነው።

እንዲህ ሲሆን ነው ማኅበራዊ ፍትህ፣ የዜጎች ደህንነት፣ ዘላቂ የጋራ ብልጽግና፣ የተሻለች አገርንና በጎ ተግባቦትን እውን ማድረግ የምንችለው። ሁሉም የቆመበትን ቦታ፣ እየተጓዘበት ያለውን መንገድና ሊደርስበት ያሰበውን ግብ ቆም ብሎ ማየት ይኖርበታል። አገርን በመበተን አገርን መመስረት የሚፈልግ እርሱ ማን ነው? የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ስሜት ወለድ ዲስኩር ሳይመረምር፤ እንዲሁ በመቀበል ከእውቀት ራሱን ነጻ እያደረገ ስሜት የሚነዳውና በስሜት የሚመራ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን “አርበኛ” የሚመሰርታት አገርስ እንዴት ያለች ትሆን?

ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top