ጣዕሞት

ዝክር ገብረክርስቶስ ደስታ

ለጥበብ ሰዎች ሁሌም ክብርና ሞገስ ከጎናቸው ነው። በስጋ ሞት ቢለዩም፤ ትተውት የሚያልፉት የጥበብ አሻራ ሁሌም ስማቸውን ያስጠራል። ገብረክርስቶስ ደስታ እንዲህ አይነቱን ክብር ከታደሉት ጥቂቶች አንዱ ነው። በሰዓሊነቱና በገጣሚነቱ የሚታወቀው ገብረክርስቶስ፤ በስራዎቹ ከአገር ያለፈ ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን ተቀዳጅቷል። በሃገረ ጀርመን በስደት ላይ እያለ ህልፈቱ የተሰማው ይህ የጥበብ ሰው፤ አገሩን አጥብቆ ከመውደዱ የተነሳ፤ ቢሞት እንኳ አጽሙ ለአገሩ አፈር እንዲበቃ አጥብቆ ይመኝ እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ። እስካሁን ምኞቱን የሚያሳካ ጥረት ባለመታየቱ የጥበባዊ ስራዎቹ አድናቂዎች፣ አክባሪዎቹ እንዲሁም ደቀ መዝሙሮቹ ስለምን ይህንን አላደረጉም የሚል ጥያቄ እንዲጫርባቸው ሆኗል።

 ሰሞኑን የገብረክርስቶስን ማንነትና ስራዎቹን ለማስታወስ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የጥበብ ማዕከል በተካሄደው የውይይት መርሐግብር ላይ የተደመጠው አስተያየትም ይኸው ነው። «ስለምን አጽሙን ለአገሩ አፈር አናበቃም?» ለሚለው የተሳታፊዎች ብርቱ ጥያቄ ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ ለመስጠት የሚችል አካል አልተገኘም። ይሁንና አንድ ቀን እንደሚሳካ የሁሉም ምኞትና ተስፋ ሆኗል።

ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚሁ መርሐግብር፤ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ስለ ገብረክርስቶስ ማንነትና ስራዎች ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል። ገብረክርስቶስ የኢትዮጵያ የስዕል ጥበብ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ የጣረ፣ ብዙዎችን ያስተማረ፣ በስዕሎቹ ፍቅርን ሲገልጽ የኖረ መሆኑንም በምሳሌ አሳይተዋል። በፍልስፍና የተቃኙ ረቂቅ ግጥሞቹም ሃሳበ ምጡቅነቱን የሚያሳዩ መሆናቸውን በጥናታቸው አመላክተዋል። ስለ ገብረክርስቶስ ያዘጋጁትን መጽሐፍ በማተምም ሆነ በማከፋፈል ረገድ ከፍተኛ ፈተና እንዳጋጠማቸው፤ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማትም ሚናቸውን በአግባቡ እንዳልተወጡ፤ በዚህም መጽሐፉ አንባቢ እጅ ለመድረስ እንዳልቻለ አምርረው የተናገሩት ሰዓሊ እሸቱ፤ የቀደሙ የጥበብ ሰዎችን ማንነትና ስራዎች ለትውልድ ማስተማሪያነት ማዋል ካልተቻለ ሌሎች ጠቢባንን ማፍራት አዳጋች እንደሚሆን አበክረው ተናግረዋል።

የገብረክርስቶስ ማንነትና ስራዎች ገና መጠናት እንዳለባቸው፣ ስራዎቹም ተበታትነው እንደባከኑ፣ ለዝርፊያና ለቃጠሎ እንደተዳረጉ የጠቀሱት ሰዓሊ እሸቱ፤ ቢያንስ ስራዎቹን አሰባስቦ ለማስተማሪያነትና ለቅርስነት ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዚህም የጥበብ አፍቃሪዎች፣ ቤተሰቦቹ እና የሚመለከታቸው ተቋማት ኃላፊነቱን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ነው ያስገነዘቡት። ገብረክርስቶስን በአንድ ቃል እንዴት እንደሚገልጹት ከታዳሚዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ « ልሂቅ፣ ጠቢብ፣ ምሉዕ ኢትዮጵያዊ» ሲሉ ገልጸውታል።

 በዚሁ ወቅት ሃሳባቸውን የሰጡት ሰዓሊ ደስታ ሐጎስ፤ ከስራዎቹና ማንነቱ አንጻር ገብረክርስቶስን በፍቅር እንደሚመስሉት ተናግረዋል። ለታሪክና ምርምር ሊውሉ የሚችሉ በራሱ ድምጽ የተቀዱ ግጥሞቹን እንደሰጣቸውና በክብር እንዳኖሩት የጠቆሙት ሰዓሊ ደስታ፤ ኃላፊነቱን የሚወጣና አደራ የሚቀበል ተቋም ካለ ለማስረከብ ፈቃደኛ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

አልማዝ ወንድሙ የተባሉ የገብረክርስቶስ የቅርብ ቤተሰብ በመርሐግብሩ ላይ ተገኝተው በሰጡት ሃሳብ ገብረክርስቶስ በህይወት እያለ በእጅ ጽሑፉ ያስቀረው ኑዛዜ በእጃቸው እንደሚገኝ ገልጸው፤ በኑዛዜው ውስጥ ከስዕሎቹ የሚገኘው ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ስራ ላይ እንዲውልለት መፍቀዱን ተናግረዋል። በየቦታው ተበታትነው የሚገኙ ስዕሎቹንና ግጥሞቹን በማሰባሰብ ረገድም የጥበብ ወዳጆች እንዲበረቱ ጠይቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ በቅርቡ በማዕከሉ አዘጋጅነት የዕውቁ የክላሲካል ሙዚቃ ቀማሪ የዶ/ር አሸናፊ ከበደን ህይወትና ስራዎች የሚመለከት የመነሻ ጽሑፍ በአርቲስት ሰርፀ ፍሬስብሐት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ለማወቅ ተችሏል። ማዕከሉ በእንዲህ መልኩ ለአገርና ለወገን በጎ ስራ የሰሩ የጥበብ ሰዎችን በየአሥራ አምስት ቀኑ የሚዘክር ሲሆን፤ ይህ መርሐግብሩ ለ40ኛ ጊዜ መከናወኑን ለማወቅ ተችላል።

የቤቲ-ጂ አልበም የአፍሪካ ምርጥ

አልበም ተባለ

ኦል አፍሪካ ሙዚክ ወይም ደግሞ አፍሪማ በመባል የሚጠራው የመላው አፍሪካዊያን የሙዚቃ ፌስቲቫል በጋና ዋና ከተማ አክራ ለ5ኛ ጊዜ ተካሂዷል። በዚህ ዝግጅት ላይ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ አርቲስቶች ተካፍለዋል። ሀገራችን ኢትዮጵያን ወክላ የተሳተፈችው ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ-ጂ) በስድስት ካታጎሪዎች ዕጩ ሆና የቀረበች ስትሆን፤ ወገግታ የተሰኘው አዲሱ አልበሟ የአፍሪካ ምርጥ አልበም በመባል ተሸላሚ እንድትሆን አስችሏታል። እንዲሁም፤ የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ሴት አርቲስት በሚለው ዘርፍ የአሸናፊነትን ድል ተቀዳጅታለች።

 ቤቲ-ጂ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን በሊሴ ገብረማርያም የተማረች ሲሆን፤ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የመናገር ችሎታ አላት። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። ለአስር ዓመታት እንግሊዝኛ ዘፈን በተለያዩ መድረኮች ከተለያዩ ባንዶች ጋር በምሽት ክለቦች በእንገሊዝኛ ስትዘፍን ቆይታለች። በአሁን ሰዓት ፊቷን ወደ አማርኛ በማድረግ የመጀመሪያው አልበሟ ማነው ፍፁም; የተሰኘ ሲሆን፤ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች በተናጠል እና በህብረት ሥራዎቿን ለአድናቂዎቿ አቅርባለች። ቤቲ-ጂ በተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎችም ላይ ለሃገሯ እና ለህዝቧ ትሰራለች።

የአድዋው አርበኛ

በርካታዎች የተሰዉበት፣ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በዘመናዊ ጦር መሳሪያ የተደራጀውን የጣሊያን ወታደር በጋሻ እየመከቱ፣ በጦር፣ በጎራዴ፣ በድንጋይና በዱላ እያራወጡ ኢትዮጵያን ነጻ ያወጡበት ድል ነው‐ የአድዋ ድል። ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት ተብላ የምትጠራውም ያለ ምክንያት አይደለም። ሴት ወንዱ፣ ሕጻን አዛውንቱ በዘመቻው ታድመዋል። በአጼ ምኒልክ ፊታውራሪነት፣ በእቴጌ ጣይቱ አበረታችነት ዘመቻውን ያልተቀላቀለ የለም። ሌላው ቀርቶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትም ዘምቷል። በአድዋ ዘመቻ የሆነውን አንድ ታሪክ የሚያስታውስ መርሐግብር ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (በአራዳ ጊዮርጊስ) ተከናውኖ ነበር። መምሬ ካሳሁን እንግዳ በአድዋ ዘመቻ የቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት አንግሰው ከዘመቱ ሦስት ካህናት አንዱ ናቸው። እኚህ መንፈሳዊ አርበኛ ታሪካቸው ብዙ ነው። የእርሳቸውን ፈለግ የተከተሉት ልጃቸው መምሬ ዘውዴም ይህንኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ለበርካታ ዘመናት አገልግለው አልፈዋል። የሁለቱም ታሪክ የተዘከረበት ይህ እለት በአባት አርበኞች ምስጋናና በካህናት ጸሎት ታስቦ ውላል። የመምሬ ካሳሁን የልጅ ልጅ አቶ ኤፍሬም ዘውዴ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት አጭር መልዕክት «የመምሬ ካሳሁንን ገድል ለመዘከር የፈለግነው ስማቸው ከሌሎች ሰዎች በላይ እንዲቀመጥ ፈልገን ሳይሆን፤ ወራሪው ጦር እብሪትና ነፍጥ ይዞ ለጦርነት ቢነሳም፤ ለአገርና ለንጉሥ ፍቅር፣ ለቅዱስ አምላኩ ያለውን እምነት ሰንቆ የተነሳውን ሰራዊት ማንበርከክ እንደማይችል፤ እንዲያውም አፍሮ እንዲመለስ የሆነበትን ትልቅ ትምህርት ለትውልድ ለመተው ነው» ብለዋል። በዚህ ጊዜ መምሬ ካሳሁን ይጸልዩበት የነበረው የብራና ዳዊት፣ ጽላቱን አንግሰው ወደ አድዋ ሲዘምቱ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ የጦር ዘመቻውን እቅድ የሚያሳይ ንድፍ፣ ልጃቸው አጋፋሪ ዘውዴ ካሳሁን ያዜሙት ከመስከረም 1 እስከ ደብረዘይት ድረስ የተቀረጸ የተክሌ ዝማሜ ቅጂ እና ሌሎች ቅርሶች ለትምህርት እና ለታሪክ ይቀመጥ ዘንድ በልጅ ልጆቻቸው ለሙዚየሙ ተበርክቷል። ለዚሁ በተዘጋጀው ልዩ መስኮትም ሲታይ ይኖራል። አገሪቱን ሊወር የመጣውን ባዕድ ሰራዊት ለመመከት በተደረገው ተጋድሎ ውስጥ ስማቸውና ግብራቸው ሲጠቀስ የሚኖረው መምሬ ካሳሁን ህይወታቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አመሰራረትና አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው። በንባብ ከተሰማው አጭር የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ የሚከተለው

“መምሬ ካሳሁን ይጸልዩበት የነበረው የብራና ዳዊት፣ ጽላቱን አንግሰው ወደ

አድዋ ሲዘምቱ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ የጦር ዘመቻውን እቅድ የሚያሳይ ንድፍ፣

ልጃቸው አጋፋሪ ዘውዴ ካሳሁን ያዜሙት ከመስከረም 1 እስከ ደብረዘይት

ድረስ የተቀረጸ የተክሌ ዝማሜ ቅጂ እና ሌሎች ቅርሶች ለትምህረት እና ለታሪክ

ይቀመጥ ዘንድ በልጅ ልጆቻቸው ለሙዚየሙ ተበርክቷል።”

ይገኝበታል። «መምሬ ካሳሁን እንግዳ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጽላት አድዋ አንግሰው (ተሸክመው)፣ አዝምተው፣ ፋሽስት ጣሊያን ድል ሆኖ ከተመለሱ በኋላ ከአምላካቸው የተቀዳጁት በረከት ነፍስ እንዳገኙ ሁሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጣሊያን ቂም እንደያዘባቸው ብዙ አመላካች ነገሮች ተከስተው ነበር። በዚህ መሰረት ጣሊያን ከ40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ዳግም በወረረ ጊዜና በአምስቱ ዓመታት የትግል ዓመታት ውስጥ ብዙ ጊዜ እርሳቸውንና ሦስት ወንድ ልጆቻቸውን ለማሰርና ለመግደል ሙከራ አድርጎባቸው ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ አምልጠው ሕይወታቸውን አትርፈዋል። ዘውዴ ካሳሁን እና ጽጌ ካሳሁን የተባሉ ልጆቻቸው ከጣሊያን እስር ሲያመልጡ፤ ትልቁ ልጃቸው ተክለማርያም ካሳሁን የብላቴን ጌታ ሕሩይ አማች በመሆናቸው ብዙ ክትትል ተደርጎባቸው አዚናራ በሚባል የጣሊያን ደሴት ወስጥ ከነባለቤታቸው ታስረው ስቃይን ተቀብለዋል»

ኢትዮጵያዊነት፡ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ ወደ አገር ቤት ሊገባ ነው

ይህ መብት ተኮር የሆነ የሥነ ዜጋ ማኅበር የተቋቋመበት ዓላማ የሕዝቡ የሆኑትን የኢትዮጵያዊነት እሴቶች፣ ትሩፋት፣ ታሪክና ባህል በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰርፁ ለማድረግ ነው። እነዚህ እሴቶች እንዲዳከሙ፤ እንዲኮሰምኑና እንዲጠፉ፣ ወጣቱ ትውልድም የሚወርሰው እንዲያጣ በመደረጉ የሚያስከትለውን የአብሮነት ዕጦት አደጋ በመገንዘብ፤ ለዘመናት በአብሮነት፣ በመከባበር የገነባውን ኢትዮጵያዊነት መልሶ ለማምጣት፤ ብሎም ውህደትን፣ አንድነትን ለመፍጠር፤ የጋራ የሆኑ እሴቶች እንዳሉን ለማሳወቅና ለማስተማርም ነው።

 መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ይህ የሥነ ዜጋ ማኅበር ከተቋቋመ ስድስት አመታትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ አገር ቤት ገብቶ ተግባሩን ለማከናወን መወሰኑን የጉባኤው ሊቀመንበር ዶ/ር እርቁ ይመር ለታዛ ተናግረዋል። ሊቀመንበሩ ስለ ማህበሩ ተግባራት ሲናገሩ፣ “ድርጅታችን የኢትዮጵያዊነትን እሴቶች የሚያጠናክሩና በተለያዩ ዋና ዋና የሀገራችን ጉዳዮች ላይ በታወቁ ምሁራን አቅራቢነት አራት ሲምፖዚየሞች አካሂዷል:: በሁለቱ ሲምፖዚየሞች የቀረቡትን ጽሁፎች ለህትመት አብቅቷል። የተቀሩትንም ለማሳተም እየተዘጋጀ ይገኛል። በተጨማሪም ከአስር በላይ የሆኑ የታወቁ ምሁራን ያዘጋጁትን ‘የዜጎች ቃል ኪዳን ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ’ የተባለውን ሰነድ በምስረታው ጉባኤ ላይ ተቀብሎት ሌሎችም የፖለቲካና የማኅበረሰብ ድርጅቶች

“ተቋሙን ለመመሥረትም ሆነ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም የወጣቶችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ፤ ስለ ሥነ ዜጋ፤ ሰብዓዊ መብቶችና ስለዲሞክራሲ መብቶችና ግዴታዎች ጥልቀትና ብቃት ያለው ትምህርት እንዲስፋፋ ማድረግ መሆኑንም ዶ/ር እርቁ አስረድተዋል”

መመሪያ አድርገው እንዲቀበሉት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ብዙዎችም እየተቀበሉት ነው” ብለዋል። “በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያዊነትን ማኅበር ወደሀገር ቤት ይዞ ለመግባት ወስነን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን። ፍላጎታችንና ዓላማችን የኢትዮጵያዊነት ኢንስቲትዩት/ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ለማቋቁም ነው” ያሉት ሊቀመንበሩ ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ዋና ዋና ተግባሮች ሲያብራሩም፤ በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰብ ተቋሞች ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያዊነትን እሴቶችና ታሪክ በሰፊው ማሳወቅ፣ እስካሁን የተመዘገቡትን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝምድና፣ የባሕልና የታሪክ ትሥሥር የሚያጠናቅር አካል በመፍጠር ሰነዶችን ማሰባሰብ መሆኑን  ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምርምርና ትንተና የሚያቀርቡ ምሁራንን ማሰባሰብ፤ ተቋሙን ለመመሥረትም ሆነ ዓላማዎቹን ለማስፈጸም የወጣቶችን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ፤ ስለ ሥነ ዜጋ፤ ሰብዓዊ መብቶችና ስለዲሞክራሲ መብቶችና ግዴታዎች ጥልቀትና ብቃት ያለው ትምህርት እንዲስፋፋ ማድረግ መሆኑንም ዶ/ር እርቁ አስረድተዋል።

 አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያዊነት አባሎች ከ40 ዓመታት በላይ በውጭ ሀገር የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን የተቋሙን ሥራዎች በሚፈለገው ዓይነትና መጠን ለማካሄድ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ማህበሩ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top