ቀዳሚ ቃል

ዘመን ተሻጋሪ ለመሆን…

የጥበብ ሰዎች ሙዚቃን እንደየስሜታቸው ይገልጿታል። ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ፣ ሙዚቃ የነፍስ ምግብ፣ ሙዚቃ የሕይወት ቅመም ወዘተ እያሉ። ስለ ሙዚቃ ስናነሳ ሙዚቀኞቻችንን እንድናስብ እንገደዳለን። ዘመን ተሻጋሪ የሚባሉ ስራዎቻቸውን የለገሱን እንደ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ካሳ ተሰማ፣ ሂሩት በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ… ለአገራችን ሙዚቃ እድገት አስተዋጽዋቸው ከፍተኛ እንደሆነ እናስባለን። ሙሉቀን መለሰ፣ አስቴር አወቀ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ እያልን ብነቀጥል ደግሞ ማቆሚያ ያጥረናል። ከእነዚህ ድምጻዊያን ጀርባ ያሉ የሙዚቃ ጠበብትን እናንሳ ብንል ማቆሚያ ማጠሩ አይቀሬ ነው። ሳህሌ ደጋጎ፣ አበበ መለሰ፣ ይልማ ገብርአብ፣ ፀጋዬ ደቦጭን ግን አለመጥቀስ አይቻልም።

ከ1940ዎቹ አጋማሽ እስከ 70 ዎቹ መጨረሻ የነበሩ ዘፈኖች ዘመን ተሻጋሪነታቸው የሚጎላው ያለምክንያት አይደለም። መዋዕለ ነዋይ ላይ ከማተኮር ይልቅ የጥበብ ፍቅሩ ላይ በመውደቃቸው፣ ሙያዊ ብቃት ላይ በማተኮራቸው ነው። ለጥበቡ ዕድገት አጋዝነት የነበራቸው ተቋማትም በዚያው ልክ ትኩረታቸውና የነበራቸው «እኔ እበልጥ… እኔ እበልጥ» ፉክክር አበርትቷቸዋል። ከክቡር ዘበኛ፣ ከፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ከሐገር ፍቅር፣ ከራስ ቴአትር እና ከብሔራዊ ቴአትር የሙዚቃ ክፍሎች ባሻገር፤ በየ ምሽት ክበቡ ሕዝቡን ያዝናኑ የነበሩት ዳህላስ፣ ዋሊያ፣ ሸበሌ፣ አይቤክስ፣ ሮሃ እና ሌሎች ባንዶች ዘመን ተሻጋሪ ስራን ሰርተውልን አልፈዋል። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ የራሱን ዘመን ተሻጋሪ ስራ የሰራው ዓለማየሁ እሸቴ፤ ዛሬም እዚያው ስሜት ውስጥ እንዳለ ነው። በፖሊስ ኦርኬስትራ እና በተለያዩ ባንዶች ውስጥ ሲዘፍን የኖረው ዓለማየሁ፤ አድማጭና ተመልካችን የመሳብ የራሱ የሆነ የመድረክ ጥበብ አለው። ዘፈንን ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር በጥሩ እያዋሃደ ህዝብን ሲያዝናና ያልዳሰሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች የሉም። በሕይወት ጉዞ ወስጥ ማንም ሰው ሊገጥመው እንደሚችለው ሁሉ፤ በገጠመው የጤና እክል ለዓመታት ከመድረክ ቢርቅም፤ ዛሬ ግን «ተሽሎኛል» እያለን ነው። በዚህች ዕትማችን እንግዳ ስናደርገውም ይህ አሁን ያለበትን የጤንነት ሁኔታ፣ ያለፉት ዘመን ትውስታዎቹ እንዲሁም በቀጣይ የሙዚቃ ሕይወቱ እንዲያወጋን ነው። ጥሩ አውግቶናል።

 «በንባብ የሕይወትን ጉዞ ወደ መልካም አቅጣጫ መለወጥ ይቻላል» እያለ የሚመክረው ዘነበ ወላም ሌላው እንግዳችን ነው። እዚያም፤ እዚህም እያልን ያወጋነውን እነሆ ብለናል። እንደ ተለምዷችን በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና የቅርስ ሃብቶቻችን ዙሪያ የሰነቅነውን ይዘን ቀርበናል። አስተያየቶቻችሁ ያተጋናልና፤ ደውሉ፣ ጻፉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top