ከቀንዱም ከሸሆናውም

ኩዴታው ያስገኘው ሽልማት

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የመቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሰሞኑን በመንበረ-ጽባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስርዓተ- ቀብራቸው ተፈፅሟል:: ነፍስ ይማር:: ፕሬዝዳንቱ “ ድሮና ዘንድሮ ” በሚል ርዕስ በተፃፈው የህይወት ታሪካቸውና ሥራዎቻቸው መጽሐፍ ላይ ከገጽ 129-31 በ1953 ዓ.ም በተደረገው መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ (ኩዴታ)ን አስመልክተው ትዝታቸውን እንደሚከተለው አውግተው ነበር::

 ሁሉም የመሰለውን አስተያየት መስጠቱን ቀጠለ:: እኔም የጦር ሰራዊቱ አባል ሁኜ በሚካሄደው ነገር ላይ ምንም ዓይነት ፍንጭ ስላልነበረኝ እንደማንኛውም የከተማው ነዋሪ ከይሆናል ወሬ ማምለጥ አልቻልኩም:: በህዝቡ ላይ የሚታየው ያለመረጋጋት መንፈስ እኔንም ስላሳሰበኝ ከቢሮ ወጥቼ በቀጥታ ወደ ቤቴ እየሄድኩ እያለሁ የኢትዮጵያ ሬድዮ ያልተለመደ የሬድዮ ፕሮግራም አስደመጠን… ሙዚቃው ይስተጋባል… በመሃል ደግሞ ልዑል አልጋ ወራሽ ህዝቡን የሚያረጋጋ ንግግር ያደርጋሉ…


የመቶ አለቃ ወ/ጊዮርጊስ (የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩ)

“ንጉሡን ተክቼ ህዝብን በሰላም አስተዳድራለሁ፣… በደሞዜ እተዳደራለሁ…ህዝብን በቅንነት አገለግላለሁ… የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ይሆናሉ፣… የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥ ደግሞ ሙሉጌታ ቡሊ ናቸው” ይላሉ:: ሙዚቃ… ደግሞ የአልጋ ወራሽ ንግግር … ብቻ ነገሩ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም ሆነብኝ:: ይህ ሁሉ ሆኖ ማን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እንዳደረገ የሚታወቅ ነገር የለም::

 ነገሩ ገርሞኝ ሁኔታው ማወቅ አለብኝ ብዬ መኪናየን አስነስቼ ጎረቤቴ የነበሩትን አቶ ዘውዴ ወልደሚካኤልን ይዤ ወደ ስድስት ኪሎ በረርኩኝ:: ሽማግሌዎች አረጋዊያን ከስድስት ኪሎ ወደ መሽዋለኪያ፣ ከመሽዋለኪያ ደግሞ ወደ ስድስት ኪሎ ይመላለሳሉ:: ነገሩን ለመጠየቅም ስለማይመች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጠሁበት የጦር ሰራዊቱ ክፍል የመንግሥት ግልበጣ አድርጎ ይሆናል ብዬ አሰብኩ:: እንዴት ወሬውን እንኳ አልነገሩኝም? በማለት ወደ መሽዋለኪያ በረርኩኝ:: የተወሰኑ የጦር የበላይ ኃላፊዎች ያለወትሯቸው በየቦታው ተሰባስበው አገኘኋቸው:: ተራ ወታደሩም መሳሪያውን አንግቦ በንቃት የሚጠባበቅ ይመስላል::

በእራሴ ሙሉ ግምት እና እምነት ጦር ሰራዊቱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ አድርጓል፤ ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ:: በመሻሎኪያው የጦር ሠፈር ያሉት የጦር አዛዦች ያለውን ሁኔታ ስጠይቃቸው “ትንሽ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ተደርጎ ነው:: … ሆኖም ነገሩ በተረጋጋ መልኩ እየተጠናቀቀ ነው… አንተም ተረጋግተህ ቤትህ ሆነህ እራስህን ጠብቅ” ብለው አንድ ዑዚ ጠመንጃ ሰጥተውኝ ሸኙኝ:: ማን ሙከራውን አደረገ?… ምን እርምጃዎች ተወሰዱ? የሚለውን ጥያቄ ለማቅረብ አልሞከርኩም:: ይህንን ዝርዝር ለመጠየቅም ሆነ ለማውራት ሁኔታዎች አያመቹም:: ብቻ የጦር ሰራዊቱ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ አድርጓል የሚል ሙሉ እምነት በውስጤ ስላደረ የተሰጠኝን ዑዚ ይዤ ወደ ቤቴ አመራሁ::

 የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉት የክቡር ዘበኛ አዛዥ የነበሩት ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይና አቶ ግርማሜ ንዋይ የተባሉ ወንድማማቾችና የክቡር ዘበኛ አባል የሆኑ ግብረ አበሮቻቸው መሆናቸው ዘግይቶ ታወቀ:: የመንግሥት ግልበጣ ሙከራው ከሸፈ:: ያከሸፈው ደግሞ የጦር ሰራዊቱ አባል መሆኑን ስሰማም በእጅጉ ገረመኝ:: …

ንጉሡ ከውጪ ጉብኝታቸው ከተመለሱ በኋላ የመንግሥት ግልበጣውን ላከሸፉ ወገኖች ፌሽታ ሆነ፣ ሽልማቱ የማዕርግ ለውጡ፣ ሹመቱ ወዘተ… ተዥጎደጎደ:: በወታደሩም በስቪሉም ሠፈር ያሉት በሙሉ ቀማመሱ:: እኔም ብሆን ለወሬ ፍለጋና የጦር ሰራዊቱ መንግሥት ግልበጣ ሙከራ ማድረጉን ለማረጋገጥ ወደ መሽዋለኪያ ለሄድኩበትና አንድ ዑዚ ለተሰጠኝ፣ “ከቤትህና ከአከባቢህ አትራቅ” ተብዬ ለተመከርኩበት የመንግሥት ወገን ተብዬ ለሽልማት ተጠራሁኝ:: ነገሮች በተጋጋሉበት ሁኔታ ውስጥ አልነበርኩም ማለቱ አደጋ ስለነበረው ወደ መከላከያ ቢሮ ተጠርቼ የተዘጋጀልኝን የዳግማዊ ምኒልክ ፈረሰኛ እና ልዩ ሜዳሊያ ከጄኔራል ከበደ ገብሬ እጅ ፀጥ ብዬ ተቀበልኩኝ::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top