ጣዕሞት

አንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ የምስጋናና የአክብሮት ካባ ደረበ

በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ የመጣው አንጋፋ የጥበብ ሰዎችን ማክበር፣ ስራዎቻቸውንና ማንነታቸውን ዛሬ ላለው ትውልድ ማስተዋወቅ ነው። ለዚህ ቅዱስ ዓላማ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። ስንዱ ቢሰነብት የተባለች የጥበብ አፍቃሪ ለዚህ አንዷ አብነት ሆናለች። ስንዱ በቅርቡ «እንዳታነቡ» የሚል ርዕስ ያለው የግጥምና የሕይወት መዘክር መጽሐፍ አዘጋጅታ ለንባብ አብቅታለች።

 ለኪነጥበብ ሰዎች ካላት ከበሬታ የተነሳ በግሏ በምታዘጋጃቸው የምስጋና መርሃግብርም የጥበብ ሰዎችን ታመሰግናለች። ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው መርሐግብር የአንጋፋው ከያኒ ደበበ እሸቱ ስራዎችና ማንነት ከፍ እንዲል አድርጋለች። ታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር በተዘጋጀው በዚሁ መርሃግብር ላይ የከያኒውን ማንነትና ስራዎች የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ቀርቧል። የግጥም፣ የሙዚቃ፣ የዲስኩር እና የሽልማት ስነ ስርአቶች ዝግጅቱን አድምቀውት ነበር።

የመርሐግብሩ አዘጋጅ ስንዱ ቢሰነብት ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጸችው፤ የመርሐግብሩ ዋና አላማ ለሃገርና ለወገን መልካም ስራ የሰሩ የጥበብ ሰዎችን በሕይወት እያሉ ማመስገን፣ የሌሉትንም መዘከር ሲሆን፤ ወጣቱን የጥበብ ሰውና የጥበብ አፍቃሪ ከአንጋፋዎቹ ጋር ማገናኘትና መልካም አርአያነታቸውን እንዲቀስሙ ማድረግ ነው። በተጨማሪም የበጎ አድራጎት ስራ አንዱ የመርሐግብሩ አካል ነው። ወደፊትም መርሐግብሩን በተሻለ ሁኔታ ለማስቀጠል ጥረት እያደረገች መሆኑን የጠቀሰችው ስንዱ፤ ለዚህም ድጋፍ የሚያደርግላት አካል ቢኖር ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች። በምታዘጋጀው መርሐግብርም በሕይወት ያሉና የሌሉት በተናጠል የሚመሰገኑና የሚዘከሩ መሆኑንም ገልጻለች።

በመርሐግብሩ በርካታ የጥበብ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ በመድረኩ ከባለቤቱ ከወይዘሮ አልማዝ ደጀኔ ጋር የምስጋና ካባ ደርቦ ክብሩን የተቀዳጀው ከያኒ ደበበ፤ ላከበሩት ሁሉ ምስጋናው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግሯል። አንጋፋው ከያኒ ተክሌ ደስታ በመድረኩ ተገኝቶ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን የተዘጋጀውን ሽልማትም ለእለቱ ባለታሪክ ከያኒ ደበበ እሸቱ ሰጥቷል።

ከአሁን ቀደም በተደረጉ ተመሳሳይ የምስጋናና የመዘከር መርሐግብሮች ታዋቂው ከያኒ ጌትነት እንየው፣ አንጋፋው ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ ገጣሚ ይልማ ገብረአብና ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ይህን ክብር ተቀብለዋል።

ትርጉም የሩሲያ ልቦለዶች መጽሐፍ ለንባብ በቃ

“የሩሲያ ልብ-ወለዶችና ሌሎች ታሪኮች” የተሰኘው አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ በቅቷል:: መጽሐፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ነው የተዘጋጀው። ከሩሲያ ወደ አማርኛ የተተረጎመው ይህ መጽሐፍ፤ በተለይ ከኢትዮጵያውያን አንባቢያን ስነ-ልቦና ቁርኝት ያላቸው የሩሲያ ጸሐፊያን ስራዎች ካተተ ነው:: በውስጡም በአመዛኙ የቼኾቭ ድርሰቶች የአምበሳውን ድርሻ ሲይዝ፤ የቶልስተይ፣ የጎርኪይ፣ የቡኒንና ሌሎች አጫጭር ልብ-ወለዶችን አካትቷል:: በተጨማሪም ደራሲው በተለያዩ አገራት ባደረጉት ምልከታ የጉዞ ማስታወሻና ልሎች መጣጥፎችን አካተዋል።

 የመጽሐፉ ተርጓሚ በመቅድማቸው “ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀሁበት ዋና ምክንያት የስነ- ጽሑፍና የጋዜጠኝነት ተማሪዎች ትምህርት ያገኙበታል፣ የአጻጻፍ ስልቱን ይማሩበታል በሚል ነው:: በሰለጠነው ዓለም ወጣቱ ትውልድ በአእምሮው እንዲበለፅግ ለማድረግ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍት በእጅጉ የሚታተሙና የሚሰራጩ ቢሆንም፤ እንደ አለመታደል ሆኖ በሀገራችን ተገቢው ስፍራ አይሰጣቸውም::

ወደፊት ግን በዕውቀት የበሰሉና የሰሉ ወጣቶች ስፍራውን ሲይዙ ይህ አመለካከት የሚለወጥ ይመስለኛል:: የዚህ መጽሐፍ ዝግጅትም ዋና ዓላማ ይኸው ነው” ብለዋል።

 መጽሐፉ 291 ገጾች ሲኖሩት ፤ሰላሣ ስድስት ንዑስ ርዕሶችና ሦስት ክፍሎችም አሉት:: በተለያዩ መጽሐፍ መደብሮች በ90 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

“የኤርትራ ጉዳይ” ኦድዮ ሲዲ ተመረቀ

ሰሞኑን በኦድዮ ሲዲ የተሰናዳው ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› የተሰኘ የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተመርቋል። በተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተዘጋጅቶ የቀረበው ይኸው ኦዲዮ ሲዲ በታዋቂው ከያኒ ተፈሪ አለሙ ለ26 ሰዓታት የተተረከ ነው።

በዚሁ የምረቃ ሥነሥርዓት ወቅት ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› በሚል ርእስ 14 ደቂቃ የፈጀ ምጥን ዶኪመንታሪ ፊልም ለታዳሚው የቀረበ ሲሆን፤ ፊልሙም ከዚህ ቀደም ብዙም ያልታዩ ምስሎችንና ቪድዮዎችን ያካተተ ነበር። በኢሳያስ አስራት ተደርሶ በሚሊዮን ጸጋዬ የተተወነው ‹‹ የብርቱ ሰው ወግ›› የተሰኘ ባለ አንድ ሰው ተውኔትም የታዳሚውን ትኩረት የሳበ ነበር። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አክሊሉ ሀብተወልድ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ ያተኮረው ይህ ተውኔት አክሊሉ ለእናት ሀገራቸው የነበራቸውን ልዩ ፍቅር አሳይቷል።

 ይህን በአይነቱ ለየት ያለ አቀራረብ ያለው ሥራ ይዞ የመጣው ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን፤ ከአሁን ቀደምም የጸሐፌ-ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን፤ የልጅ እንዳልካቸው መኮንንን፤ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትንና የተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠን ማንነትና ስራዎች የሚያስቃኙ ሥራዎችንም ለህትመት ካበቃቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። በመርሀግብሩ የታሪክ ሰዎች፣ ምሁራን፣ ደራሲያን፣ እንዲሁም ሌሎች የጥበብ ሰዎች ተገኝተዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top