ስርሆተ ገፅ

“አንብብ፣ አንብቢ፣ አንብቡ፣ እናንብብ…”

በንባብ ማንነትን መለወጥ እንደሚቻል ከራሱ የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ሌሎችን ሲመክር አይታክትም። የመርከበኝነት ህይወት የሥራው ጅማሬ ይሁን እንጂ፤ በጋዜጠኝነት ሙያ ብዙ ሰርቷል። የአራት መጻሕፍት አዘጋጅም ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ስለ ባህር ውስጥ ህይወት እና ስለ መርከበኝነት የሚያቀርባቸው ትረካዎች አስደማሚ ነበሩ። በእነዚህ ስራዎቹ ብዙዎች ያስታውሱታል፤ ዛሬ በጄ.ቲቪ «ከፀሐይ በታች» የተሰኘ ፕሮግራም ከፍቶ ትውልዱን ለንባብ እያተጋ ይገኛል ‐ ሊዲንግ ሲማን ዘነበ ወላ። ከንባብ ጋር ስለተቆራኘው ሕይወቱ ብዙ አውግቶናል። ጥቂቱን እነሆ።

ታዛ፦ አዲስ አበባ ውስጥ ጨርቆስ ተወለድክ፣ እዚያው አደግክ፣ እዚያው ስራ ያዝክ፤

ዘነበ፦ ልክ ነው።

 ታዛ፦ አንባቢያን ስለ ልጅነትህ፣ አስተዳደግህ ማወቅ ቢፈልጉስ?

 ዘነበ፦ እሱን «ልጅነት» የተሰኘ መጽሐፌ ውስጥ ቢያገኙት አይሻልም? ሁለንተናዬ ተጽፎበታል። ማንነቴ ሲገለፅ ከቀይ ባህር እና ከቂርቆስ ልጅነት ጋር ቢያያዝ ደስ ይለኛል።

ታዛ፦ ባህር ኃይል ምን ያህል ዓመት ሰራህ? ወደዚያ ለመግባት የተነሳሳህበት ምክንያት ካለህ?

ዘነበ፦ ከሰባት ዓመት በላይ አገለገልኩ። መርከበኝነት የምወደው ሙያ ነው። እንጀራ ነው ወደ ጋዜጠኝነቱ ይዞኝ የመጣው። ባህር ኃይል ስገባ 24 ዓመቴ ነበር። ውትድርና ትልቅ ሙያ እንደሆነ ባውቅም መቀጠር አልፈልግም ነበር። ግን በወቅቱ የነበረው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አስገድዶ ወታደር አደረገኝ። ብሔራዊ ውትድርና ሲታወጅ የደሃው እንጂ የሀብታም እና የባለስልጣን ልጅ አይዘምትም ነበር። የግዳጁን ከመቀበል የውዴታ ይሻላል ብዬ በ1975 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ባህር ኃይል ተቀጠርኩ፤ እስከ ግንቦት 19/ 1983 ጠዋት ድረስ የባህር ኃይል ባልደረባ ነበርኩ። ከሰዓት በኋላ ቀፎኝ ቀረሁ፤ ደመወዜን ሳልቀበል በማግስቱ ለውጥ ሆነ። ያንን ደመወዝ ባለመቀበሌ ግን ሰብዕናዬን ድህነት አደቀቀው። ሌሎች ባልደረቦቼ የሁለት ወር ተቀብለው ነበር፤ እኔ ግን ያቺን ቀን ባለመቀበሌ በጣም ተጎዳሁ። በሁለት እግሬ እስከምቆም ድረስ ረጅም ጊዜ ተሰቃየሁኝ።

ታዛ፦ እንዴት አገገምክ ታዲያ?

ዘነበ፦ የሚወደኝ ወልደገብሬል አባተ የሚባል ሰው ነበር፤ ያለሁበትን ሁኔታ አጠናና «ዝም ብለህ ጻፍ፤ እኔ አሳትምልሃለሁ፤ ባህር ኃይል የሚከፍልህንም ወርሃዊ ደመወዝ እከፍልሃለሁ» አለኝ። መታደል ነው። ያለ ሃሳብ “ሕይወት በባህር ውስጥ” የሚለውን መጽሐፍ ጻፍኩ፤ አሳተመልኝ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጋዜጠኛ የመሆን ዕድል ገጠመኝ። በ347 ብር ደመዎዝ። ጌትነት አይደል? ወደ 13 ዓመት አገለገልኩ። ወልደገብርኤልንም አመስግኜ ከእሱ ደመወዝ መቀበሌን አቆምኩ። “ሕይወት በባህር ወስጥ”ን 12,336 ብር አውጥቶ አምስት ሺ ኮፒ አሳትሞልኛል።

 ታዛ፦ የገንዘብ አቅም ፈጠርክበት?

 ዘነበ፦ በፍፁም። ስም ብቻ፤ ግን ግዙፍ ስም። የሚወደኝ ሰው መኖሩን አወቅኩ፣ ያንን የችጋርና የችግር ጊዜ አለፍኩበት። በወቅቱ በአዲስ አበባ መስተዳድር የአማርኛ መማሪያ ውስጥ አንዱ የመጽሐፌ ውስጥ ታሪክ ተካቶ መውጣቱ ትልቅ ነገር ነበር ‐ ለእኔ። ትልቅ የሞራል መነቃቃትን ነው የፈጠረልኝ። እንደነ ከበደ ሚካኤል፣ እንደነ ሐዲስ ዓለማየሁ እንዲህ አይነት ሞገስ የሚገባኝ ሰው ነኝ እንዴ? እስከማለት አስቤም ነበር።

ታዛ፦ ከቀይ ባህር ትልካቸው የነበሩ የባህር ላይ ሕይወት መጣጥፎችህ በሬዲዮ ተወደው ይደመጡ ነበር፤ ያንን ለመጻፍ ጊዜ ነበረህ ማለት ነው?

 ዘነበ፦ አልነበረኝም። የመጻፍ ፍቅር ግን በብዙ ነበረኝ። ተያያዥ ታሪክ ልንገርህ። ምጽዋ ቃኚ የጦር 204 መርከብ ላይ ተመድቤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር፣ ከስድስት ቀን ስሰራ 1,852 ኪሎ ሜትር ቅኝት እናደርጋለን። ድካም አለው፤ ግን የሥነ ጽሑፍ ስሜቴ ውስጤ ይቀጣጠል ነበር። እዚያው ሆኜ ስለ ድርቅ ሁኔታ የካቲት መጽሔት ላይ ጻፍኩ። ግዛቸው መስቀሉ የሚባል ዕልቅና ያለው የባህር ኃይል ባልደረባ ሞስኮ ሆኖ አነበበልኝ። ወዶት ኖሮ ምጽዋ ሲመጣ ከመርከቤ አስጠርቶ አገኘኝ። ያኔ በመርከቧ የመድፍ ክፍል ኃላፊ ነበርኩ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ «ጽሑፍህን ወድጃታለሁ፤ ታነባለህ?» አለኝ። «አዎ አነባለሁ» አልኩት። እውነትም አነብ ነበር። ምጽዋ ሲኒማ ካሌብ ፊት ለፊት አንዲት ትንሽዬ የመጽሐፍ መደብር ነበረች። ምን አይነት አስተዋይ ሰው እንደሆነ አላውቅም፤ ከአዲስ አበባ መጻሕፍት እያመጣ ይሸጥ ነበር። ፍራንክ በጣም ቢያጥረኝም ከዚያ እየገዛሁ አነብ ነበር። ከማገኛት ደመወዜ ለእናቴ እቆርጥና በሌላ ነገር ሳልዝናና መጽሐፍ ሸመታ ላይ እተጋለሁ። በጥንቃቄና በብልሃት የኖርኩበት ዘመን ነው። ታዲያ ግዛቸው ያን ዕለት «የበለጠ እንድታነብ መሬት ብትወርድ ይሻልሃል» አለኝ። «አይ አልወርድም» አልኩት። ምክንያቱም መርከቧ ላይ ጥሩ ስለምሰራ አብሬያት ካልሰመጥኩ በስተቀር የምትለቀኝ አይመስለኝም። ግን ግዛቸው ቦታን የመቀየር አቅም ያለው ሰው ስለነበር አግባብቶ አስወረደኝ። ቀጥታ የባህር ኃይል ቤተ መጻሕፍት ኃላፊነትን ነው የተረከብኩት። መጻሕፍትን ዋኘሁባቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ኢንሳይክሎፒዲያ የሚባል መጽሐፍ የዓለምን ታሪክ እንደያዘ ያወቅኩት ያኔ ነው። በቃ ከመጻሕፍት ጋር ይበልጥ ተቆራኘሁ። እዚያ ውስጥ ሆኜ ነው እንግዲህ እነዚያን መጣጥፎች በሬዲዮ እንዲቀርቡልኝ አደርግ የነበረው። ኋላ ላይ ተሰባስበው፤ ተጨማምሮባቸው ታተሙ። ሕይወትን በተለያየ አቅጣጫ ለመመልከት አግዞኛል። ያ ለእኔ መልካም ጊዜ ነበር።

ታዛ፦ ባህር ኃይል ዳግም ሊመሰረት እንደሆነ እየተሰማ ነው፤ እዚያ ላይ ሚና ይኖርህ ይሆን?

ዘነበ፦ አዎ ሰምቻለሁ። በሙያዬ የሚፈለግብኝን አገራዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ። ብዙውን ጊዜ እንደሚስተዋለው ነባር ዕውቀቶችን አንጠቀምባቸውም። ቀድመው እዚያው ውስጥ የነበሩ ምሁራንን አገሪቱ ልትጠቀምባቸው ይገባል። የሚያሳዝነው ጣና ላይ እንቦጭ አረም መከራችንን እያሳየን ነው፤ ያንን አረም አጭደው ድራሹን የማጥፋት አቅም ያላቸው ባህረኞች ግን አዲስ አበባ ውስጥ ታክሲ እየነዱ ነው። ቺካጎ በርካታ የባህር ኃይል ባልደረቦች እንዳሉ አውቃለሁ፤ የአገራችን ሁኔታዎች ቀና ከሆኑ እነሱ በቀናነት አገራቸውን ያገለግላሉ ብዬ አስባለሁ። በሌላም ሙያዎች እውቀትን ለትውልድ ለማስተላለፍ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ሳንጠቀምባቸው አልፈዋል፤ ይህ ያሳዝነኛል። ለምሳሌ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ስንመጣ የሚዘገንንህን ነገር ልንገርህ… ታዋቂው የሬዲዮ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ከ30 በላይ አገሮች እየተዟዟረ ተምሯል። «አንድም ቀን ልምዴን ለወጣት የጋዜጠኝነት ተማሪዎች ሳላካፍል ልሞት ነው» አለኝ። እንዳለውም ሁኔታዎች ሳይፈቅዱለት፤ ያሰበውን ሳያሳካ ሞተ። ትልቅ ጥፋት አይደለም?! አገሪቱን ማንም ይምራ ማን ዕውቀት መሸጋገር አለበት። ያ ባለመሆኑ ግን ዛሬ ተማርን የሚሉ አንዳንድ ጋዜጠኞች ውጤታማ ሳይሆኑ እየቀሩ ነው። ያሳዘናል። እኔ በግሌ ግን ቢያንስ እንዴት ማሰብ እንደሚኖርባቸው ልነግራቸው እያሰብኩ ነው።

 ታዛ፦ በሕይወት ልምድ ያለፍክባቸውን፣ ያነበብካቸውን፣ የሆንካቸውን፣ ያየኸውንና የሰማኸውን ተመርኩዘህ ያዘጋጀሃቸው መጻሕፍት፤ “ሕይወት በባህር ውስጥ”፣ “ማስታወሻ” (የስብሐት ገብረእግዚአብሔር የሕይወት ታሪክ) “ልጅነት” እና “መልህቅ” ናቸው። እስካሁን ወደ ፈጠራ ስራ አልመጣህም ልበል?

 ዘነበ፦ አዎ አልመጣሁም። እሱ ሂደት አለው። በቀጣይ ወደዚያው መምጣቴ አይቀርም።ሌሎች እያዘጋጀኋቸው ያሉ መጽሐፎች ግን አሉ። ጄ.ቲቪ ላይ መስራት ከጀመርኩ በኋላ ለታዳጊዎች መጽሐፍ መጋበዝ ስፈልግ አጣለሁ። ያሉት መጻሕፍት ታች ላሉት ሕጻናት ወይ ደግሞ ከ18 ዓመት በላይ ላሉ ልጆች ነው። አቅሜ በፈቀደ መጠን ለእነዚህ ልጆችና ታዳጊዎች የሚሆን ነገር ስፈትሽ እኖራለሁ። ከዚህ በኋላም ፍተሻዬ ይቀጥላል። አቅምም እየፈጠርኩ ስለመጣሁ እራሴ አዘጋጅቼ ወይም ቀድሞ የተጻፉና ለታዳጊዎች የሚመጥኑ መጻሕፍትን እያሰስኩ ለማሳተም ተነስቻለሁ። ደራሲዎቻችንም ይህንን ቢያስቡበት ጥሩ ነው። ከ12 አስከ 18 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች የሚያነቡት መጽሐፍ የላቸውም። ከዚህ በኋላ ኰምጠጥ ያለ ዕድሜ ላይ እየገባሁ ነው። በተለያዩ ጉዳዮች መጻፌን እቀጥላለሁ። በየአመቱ አንድ አንድ መጽሐፍ አስነብባለሁ ብዬ አስባለሁ።

ታዛ፦ የበርካታ ደራሲያን ምሬት የማሳተምና የማከፋፈል ጣጣ ነው፤ ይህን እንዴት ነው የምታልፈው?

ዘነበ፦ አለ ምሬቱ። ተስፋ የሚያስቆርጥ ብዙ ነገር አለ። እድለኛ ሆኜ ሊሆን ይችላል፤ አንድም የሚሸፍጠኝና ነውረኛ የሆነ አከፋፋይ አልገጠመኝም። ከድህነት ክፋት የተነሳ አንዳንድ ልጆች የደራሲያንን ገንዘብ ቶሎ መስጠት የማይፈልጉ አሉ። እዚህ ላይ ራሱን የቻለ ትልቅ ስራ ሊሰራ እንደሚገባው አምናለሁ። የብዙ ወዳጆቻችን ምሬት አለ።

ታዛ፦ የደራሲያን ማህበር አባል ነህ?

ዘነበ፦ አይደለሁም። የጋዜጠኞች ማህበር፣ የአብሮ አደጎች ማህበር፣ የምንም ነገር አባል አይደለሁም። ሆኜም አላውቅም። ይህ የእኔ የውስጥ እምነት ነው። በፖለቲካ ድርጅትም ሆነ በሌላ የለሁበትም።

ታዛ፦ እንዴ! እድር፣ ዕቁብ በመሳሰሉ ማህበራዊ…?

ዘነበ፦ እሱን በባለቤቴ በኩል አለሁበት። ምን መሰለህ… ነጻነትን አጥብቄ እፈልጋለሁ። እራሴን ሆኜ፣ 41 ቁጥር ጫማ ውስጥ ቆሜ መኖርን ነው የምፈልገው። በማንም ተጽዕኖ ስር መውደቅን አልፈልግም። ወደድኩም ጠላሁም ማህበረሰቡ እንደሚከታተለኝ አውቃለሁ፤ ከምሰራው ስራ ጋር በተገናኘ በስነ ምግባር መታረም እንዳለብኝም መቶ በመቶ የምቀበለው ነው። ነገር ግን፤ በሕግ፣ በመመሪያ፣ በደንብ መመራት ከጀመርኩ ማፈንገጥ፣ መመርመር፣ ነጻ ሆኜ ሃሳቤን በምፈልገው መልኩ ማራመድ አልችልም ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ በአባልነት ውስጥ መታጠርን አምርሬ እርቃለሁ። ማንም ጥላውን እንዲያጠላብኝ አልፈልግም። በእኔ እምነት በምድር ላይ ደራሲ ሆነህ ስትፈጠር፤ ቢቻል ዘርም ባይኖርህ ይመረጣል። በነጻነትህ፣ በእምነትህ እንድትሄድ። ግን ያ ሊሆን አይችልም።

ታዛ፦ ሂስ ለሥነ ጽሑፍ ዕድገታችን ትልቅ ዋጋ እንዳለው ይታመናል፤ ዛሬ ዛሬ በሂስ እየነቃ ወይም እየተጋ የሚመጣ ደራሲ አይስተዋልም። በዚህ ላይ ምን ሃሳብ አለህ?

ዘነበ፦ እሱ ነው ትልቁና አሳሳቢው ነገር። ምንም ሂስ የለም። ለምሳሌ “መልህቅ” ላይ ምንም ነገር አልተጻፈም፤ ሰው አልወደደውም እንዳልል 25ሺ ኮፒ ተሽጧል። ሌሎች መጽሐፎች ላይም ተመሳሳይ ነገር ይታያል። ከአንድ ወዳጄ ጋር በስነ ጽሑፍ ዙሪያ ስናወራ «በአገራችን በርካታ ደራሲያን እየተፈጠሩ ነው፤ ይህ እድገታችንን አያሳይም ወይ?» ብዬ ጠየኩት፤ ያባነነኝ ምላሹ «አያሳይም፤ ጥሩ አይደለም፤ ይህ የሆነው ሃያሲ ስለሌለን ነው» ማለቱ ነው። እውነቱን ነው። አንዳንድ የሚወጡ መጽሐፎች በእጄም የማልነካቸው አይነት ናቸው። በአንጻሩ ጥሩ ጥሩ መጽሐፎች ታሽጎባቸው፤ ገለባ የበዛባቸው መጽሐፎች በቲፎዞ እና በተለያዩ የማሻሻጫ ጥበቦች እንዲሸጡ ሲደረግ ይስተዋላል። የሆድ ጥያቄ፣ ከድህነት የመውጪያ ጥያቄ ነው አገራችንን እየናጣት ያለው። ይህ ሥነ ጽሑፋችንን እንደሚገድለው ማወቅ አለብን። የሥነ ጽሑፍ ምሁራን እንዳሉን ይታወቃል፤ ሃያሲዎች። ብዕራቸውን በመጽሐፎች ላይ 

“የሚገርምህ ዘመንን መልቀቄ ግን ጠቅሞኛል። የመጀመሪያውን ሦስት ሳምንታት በመኝታ ነው ያሳለፍኩት። በጊዜ እጥረት እየገዛሁ ቤቴ የከመርኳቸውን መጻሕፍት ቁጭ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ። አገራዊ ታሪኮችን፤ በተለይም ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ደርግ ምን እንደነበሩ፣ ምን እንዳደረጉ ማወቅ ቻልኩ።”

ጨክነው መወደር አለባቸው። ያ ነው የሥነ ጽሑፍ እድገታችንን የሚያመጣው። ወደፊት ይመጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

 ታዛ፦ ጋዜጠኝነትን በአግባቡ ከተጠቀሙበት የዕውቀት ጎተራ የመሆንን ያህል ያፋፋል የሚል እምነት አለኝ፤ አንተስ?

 ዘነበ፦ ምን ጥርጥር አለው? ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል።

ታዛ፦ ከዚህ አንጻር አዲስ ዘመን በሰራህባቸው 13 ዓመታት ምን ተጠቀምክ፤ ምንስ ጠቀመክ?

ዘነበ፦ የነበረውን ማኔጅመንትና አሰራሩን ልተወው። ግን አዲስ ዘመን የስራ ሰው አድርጎ ነው የቀረጸኝ። ስራህ እለት በእለት ስለሚታይ ለምስጋናም ለወቀሳም ቅርብ ነህ። ካዘጋጀኋቸው ዓምዶች እወደው የነበረው «የዘመን ትውስታ»ን ነው። ምክንያቱም እንዳነብ አድርጎኛል። ለምሳሌ ጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሀኑ ዘሪሁን፣ በዓሉ ግርማ ሌሎች ጸሐፊዎችስ ምን ጻፉ የሚለውንና የመጻፍ አቅማቸውን፣ እንዲሁም ልዩነታቸውን እንዳጠና፣ እንዳውቃቸው ረድቶኛል። የተገነዘብኩት፤ ብርሃኑ ዘሪሁን በአዲስ ዘመን ውስጥ ሲነድ መኖሩን ነው። ያንን የመሰለ ትልቅ የመጻፍ አቅም እዚያ ጋዜጣ ላይ ነው የባከነው። በ50 እና 60 ዎቹ ሲጻፉ የነበሩት ጽሑፎች ዛሬም ያስደምሙኛል። ስላነበብኩ ተጠቅሜያለሁ፤ ስለሰራሁ በእኔ አቅም ሌላው የሚማርበትን ጽሑፍ አበርክቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ሙያውን እጅግ እወደው ነበር።

ታዛ፦ ከወደድከው እንዴት ለቀቅክ?

 ዘነበ፦ አዲስ ዘመንን ስለቅ ተከፍቼ ነው በፈቃዴ የለቀቅኩት። የግለሰቦች ክፋት እንጂ ተቋማዊ አሰራር ሆኖ አይደለም‐ በደሉ። ዛሬም ተቋሙን አልወቅስም፤ ግን የሚሞት ሞተ፣ የሚሰደድ ተሰደደ፣ ዘነበ ወላ ግን ቆሞ አገሩን እያገለገለ ነው። እግዚአብሔር እዚህ ደረጃ ስላደረሰኝ ከልብ ነው የማመሰግነው። ፕሬስ (አዲስ ዘመን) አቅሙ በፈቀደ መጠን በረግረግ ስፍራ ላይ እንደተገኘ ደረቅ መሬት ደቅድቆ ወደ መቃብር መሸኘት ነበር ተግባሩ። ግን አልሞትኩም። በወቅቱ ለነበረው ስራ አስኪያጅ ምን እንዳልኩት ታውቃለህ?… ‘ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ አሥር ደራሲያንን ብትፈጥር አንዱ ዘነበ ወላ ነው’። ደነገጠ። ይህንን ለመሆን ነው እንግዲህ ዛሬ ጥረት ላይ ያለሁት። የሚገርምህ ዘመንን መልቀቄ ግን ጠቅሞኛል። የመጀመሪያውን ሦስት ሳምንታት በመኝታ ነው ያሳለፍኩት። በጊዜ እጥረት እየገዛሁ ቤቴ የከመርኳቸውን መጻሕፍት ቁጭ ብዬ ማንበብ ጀመርኩ። አገራዊ ታሪኮችን፤ በተለይም ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ደርግ ምን እንደነበሩ፣ ምን እንዳደረጉ ማወቅ ቻልኩ። በቃ ዘነበ ወላ በዚህ በኩል መቀጠል ይችላል ብዬ ተነሳሁ።

ታዛ፦ ከዚያስ ጉዞህ ወዴት ሆነ ?

ዘነበ፦ ከዚያ ኤዞፕ ኮሙኒኬሽን ውስጥ ገብቼ በኤፍ.ኤም 97.1 ላይ ከነ ሱራፌል ወንድሙ ጋር መስራት ጀመርኩ። ነጻነቴን ጠብቀውልኝ ስለምሰራ የበርካታ ወጣቶችን ህይወት በጥሩ አቅጣጫ መርቻለሁ ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያዊነትን ሰብኬበታለሁ። ህግን ጠብቄ በድፍረት የምለውን ብያለሁ። ለአምስት አመት ስሰራ ተወዳጅ ፕሮግራም ነበር። ማንበቤን ተጠቀምኩበት። ዛሬ ያለሁበት ላይ ነኝ እንግዲህ…። ታዛ፦ «ከፀሐይ በታች» የተሰኘውን ፕሮግራም በጄ.ቲቪ እያዘጋጀህ ነው፤ … ዘነበ፦ አዎ አሁን እዚያ ላይ ነኝ። ሦስት ዓመቴን ያዝኩኝ። ተወዳጅ ፕሮግራም መሆኑን ከሚደርሰኝ አስተያየት እየተረዳሁ ነው። ዐውዱ መጽሐፍ ይሁን እንጂ፤ ከፀሐይ በታች ባሉ ማናቸውም ነገሮች አወራበታለሁ። ከንባብ ያካበትኩትን ዕውቀት ለሌሎች እያካፈልኩ ጥሩ የመኖሪያ ደመወዝ እያገኘሁ መኖር ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። እዚህ ላይ አንድ መልዕክት ተናግሬ ልለፍ… በጄ.ቲቪ የማስተላልፋቸውን ፕሮግራሞች እየቀዱ ያለ ፈቃዴ በራሳቸው ዌብሳይት የሚለጥፉ ሰዎች አሉ፤ ይህ የሆነው ፕሮግራሜን ከመውደድ የተነሳ አድናቂዎቼ እንዳደረጉት ይገባኛል፤ ነገር ግን በሌላ ጎኑ ጉዳት እንዳለው ታውቆ ይህ ተግባር ቢቆም ደስ ይለኛል።

 ታዛ፦ የኑሮህ መመሪያ ምን ይመስላል?

 ዘነበ፦ ማንበብና መጻፍ ነው ሱሴ። ሌሊትም ቀንም አልመርጥም። የምተኛው ረጅም እንቅልፍ ከአራት ሰዓት አይበልጥም። ስፖርትን ለጤናዬ እየተገለገልኩበት ነው፤ የእግር ጉዞ አደርጋለሁ፤ በሳምንት አንድ ቀን ዋና እዋኛለሁ፤ ዮጋ እሰራለሁ። በዚያ ዙሪያ ብዙ መጻሕፍትን አንብቤያለሁ። ከዚያ ባለፈ ያገኘሁትን እበላለሁ እጠጣለሁ፤ ማህበራዊ ሕይወት ላይ ጥሩ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ከጓደኞቼ ጋር መጠጥ ሲያምረን እንጠጣለን፤ እንዝናናለን። የምንም ነገር ሱሰኛ አይደለሁም፤ ሁሉንም ግን አልፈራውም። ካነበቡ ሰዎች ጋር እውላለሁ፣ በውይይት አምናለሁ፣ ከታላላቆቼ በደንብ እሰማለሁ። በርካታ ሽማግሌ ጓደኞች አሉኝ። በተለይ ከስነ ጽሑፍ ጋር የተወዳጁ እና ደራሲያን። በእነሱ ተጠቅሜያለሁ።

ታዛ፦ ቤተሰባዊ ሕይወትህስ?

ዘነበ፦ በጥሩ ትዳር ውስጥ ነኝ። ሁለት ልጆች አሉኝ። የመጀመሪያዋ የዩኒቨርሰቲ ተማሪ ነች። በቤታችን ሰላም አለ።

ታዛ፦ ለዛሬው ማንነተህ ብርታት ነበሩኝ የምትላቸው ካሉ?

ዘነበ፦ ቀይ ባህር አስደንግጦ የዓለምን ጽንፍ እንዳሳየኝ ሁሉ፤ ዓይነ ጥላዬን በመግፈፍና ብርሃናማውን መንገድ በመምራት፣ በማስተማር በሕይወቴ ስኬታማነት ላይ ትልቁን ሚና የተጫወተው ጋሽ ስብሐት ለአብ ነው። የወላጆቼም ድጋፍ ቀላል አይደለም። በሕይወቴ ውስጥ ገብቶ መልካምነትን ያስተማረኝ ወልደገብሬልም ለዛሬ ማንነቴ ምክንያት ነው።

ታዛ፦ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ቢኖርህ ምን ታደርጋለህ?

ዘነበ፦ በሁሉም ክልሎች ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት አስገነባለሁ። «አንብብ፣ አንብቢ፣ አንብቡ፣ እናንብብ» በሚል መርህ ትውልዱን ማነጽ ተግባሬ ይሆን ነበር።

ታዛ፦ ያሰብከው እንዲሳካ እየተመኘሁ፤ በዚሁ ብንሰነባበትስ?

 ዘነበ፦ በጣም አመሰግናለሁ፤ ሰላማችን ይብዛ፤ በአገራችን፣ በሕዝባችን ፍቅር ይዝነብ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top