ማዕደ ስንኝ

ነግሬህ ነበር ማሬ…

አላልኩም ነበረ!!

ያቺ ፀሐይ ግባት

ፀሐይ መውጫ ተብላ

ሳትጠልቅ የጠለቀች

በግድ ተገልላ

የገባቸው ፀሐይ

ግድ የተሸፈነች

ፀሐይ መውጫ ተብላ

ዳግም ትወጣለች

አላልኩህም ነበር

ደምቃ ታበራለች፡፡

እኮ!!

ብዬህም አልነበር

በዛች ፀሐይ ግባት

ፍፃሜ የራቀው

አስቀኚው ፍቅራችን

የተልኮሰኮሰው

ዳግም ፍንትው ይላል

ደህና ሁኚ አትበለኝ

በጅምር አይቀርም

ፍቅሬ ሆይ እመነኝ

ፀሐይ አልገባችም

ግርዶሽ ከልሏት ነው

ብዬ የወተወትኩህ

ያው ዘንድሮ አየኸው፡፡

ምን ብዬህ ነበረ?

ፀሐይ ትግባ ተብላ

በእኛ ላይ ብትጠልቅም

ፀዳሏ ቢከለል

ጨለማ ቢመስልም

ተፈጥሮ ነውና፤ ደም ስጋ ነውና

መውጣቷ አይቀርም፡፡

ከመዳፍ የቀሩ

ቀለበቶቻችን

ቃል ኪዳን ማሰሪያ

ተምሳሌቶቻችን

ከጣት ይጠልቃሉ

እመነኝ ፍቅርዬ

እያልኩ አልሞገትኩም?

ተስፋ አትቁረጥ ብዬ፡፡

እህ!

አውቄው ነበረ

የተዘጋው መንገድ

ግጥሙ ጎዳና

የከፈሉት ሰማይ

በስሜት ዳመና

ሁሉ ነፃ ሆኖ

እንደምንገናኝ

አንተን ውዴን ፍቅሬን

ከጎኔ እንደማገኝ

አንዳች ድብቅ መንፈስ

ለውስጤ ነግሮኛል

ዳግም አንድነትን

ማግኘቴ ታውቆኛል፡፡

ለዛ እኮ ነው ፍቅሬ

ሁለቱን አስርታት

ስገባ ስወጣ

ዘመድም ጎረቤት

ከንፈር ሲመጡልኝ/ከንፈር ሲመጡብኝ

ስለ ፍቅሬ አዝነው

²ምናለ `ማትተይው

ልክ እንደሞተ ሰው

በቃ እሱን እርሺ

አልቅሰሽ ቅበሪው

በይ ኑሮ ጀምሪ

ከልብሽ ላይ ፋቂው²

ብለው ተቆጥተው

ጧት ማታ ሲመክሩኝ

ሁሉን አሸንፎ

ዛሬን ያሳየኝ

ያቺ ፀሐይ ግባት

ሳትጠልቅ የጠለቀች

እጅግ ፈክታ አምራ

ዳግም ትወጣለች

የሚለው ተስፋዬ

የልቤ ብርታት ነው

ፍቅርህ ሀኔ ቀርቶ

ሌሎችን የገፋው፡፡

ያው እንደነገርኩህ

ግርዶሹም ተነሳ

ፀሐይዳግም ወጣች

እኔም አላፈርኩም

እሷም አላሳጣች፡፡

ይኸው መጠበቄ

ትርጉሙን ሳያጣ

አንተን ውዱ ፍቅሬን

ህልሜንም ሳላጣ

ቆመው ታሪክ አዩ

ያሽሟጠጡኝ ሁሉ

ያእኔ የዘበቱብኝ

ቆሞቀር እያሉ፡፡

ነግሬህ ነበር ማሬ…

ግጥም

ግጥም

ግጥም

ፍሬዘር ዘውዴ (ቬና)

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top