የጉዞ ማስታወሻ

ቤጂንግ – ሰሜናዊቷ መዲና

ወደ ቻይና ሄድኩ። ቻይና የሄድኩት ‹‹ፑሽ አፕ›› ሰርቼ አይደለም። ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ፑሽ አፕ ሰርተው የሄዱ ነበሩ። የእኔ ለየት ይላል። ከቻይና ኮሙኒኬሽን ዩኒቨርሲቲ በተደረገልኝ ጥሪ መሠረት ነው ወደዚያ ያቀናሁት። እንደ ዕድል ሆኖ የተለያዩ ሃገራትን ጐብኝቼያለሁ። ቻይና ግን ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በውስጤ ቀርታለች። ታሪኳ፣ ትንታግ አብዮታዊነቷ በውስጤ ሲነድ ኖሯል።

 አስታውሳለሁ፣ ያኔ የማኦዚም ድባብ በኢትዮጵያ ያረበበበት ጊዜ ነበር። የግለት፣ የሙቀት፣ የአብዮታዊ እመርታ ጊዜ። ማኦን፣ የማኦን ‹‹ቀይ መጽሐፍ›› የማንበብ ጅማሬ። በአብዮት ቋያ የመንደድ የወጣትነት ኃይል። ጂማ፣ በተለይ ሚያዝያ 27 አጠቃላይ ት/ ቤት የዚያ ፖለቲካ ግለት አንቀሳቃሽ ሞተር ነበር። በጂማ ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት ይታይ የነበረው ‹‹በድል ላይ ድል!›› የሚለው የቻይና ፊልም ዛሬም እንደ ህልም በውስጤ ትርዒቱን ያሳያል – ቻይናን ሳስብ።

ቻይናውያን አብዮተኞች ተራራ እየናዱ ሀገሩን ሲያለሙ፣ ከድል ወደ ድል ሲሸጋገሩ ማዬት በዚያን ወቅት ቀልብ ይስባል። ያኔ በነበረው አብዮታዊ ግለት አብዮታዊ ወጣቶች (በአብዛኛው የሚያዝያ 27 ተማሪዎች) ወደ ጅማ ቤተ-መንግሥት አቅንተው ደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቁስላሴን ለማባረር ተመሙ። ‹‹ና-ሰው›› አዳራሽ ድብልቅልቁ ወጣ። ከመንቲና፣ ከሰጦ ሜዳ፣ ከቦሳ፣ ከኩሎ በር፣ ከመንደራ ልባቸው የሚነድ ወጣቶች ደጃዝማች ፀሐዩን አንቀው ለማስወጣት ቆርጠው ተደንደረደሩ። ግን አልሆነም።

መትረየስ የደገነ የፈጥኖ ደራሽ የጥበቃ ጦር ጥይቶቹን ማዝነብ ጀመረ። ያ የነደደ ወጣት ቅስሙ በመሳሪያ ኃይል ተፍረከረከ። አስታውሳለሁ በነጋታው በየቦታው የወደቀው የጫማ ክምር ከ‹‹ና-ሰው›› አዳራሽ ፊት ለፊትና በፈረንጅ አራዳ አውራ ጐዳና ላይ ሲታይ ለተቃውሞ የወጣውን የህዝብ ብዛት የሚያሳይ ነበር። ደጃዝማች ፀሐዩ አምልጠው በሄሊኮፕተር አዲስ አበባ ገቡ። ከዚያም ከደርግ ጋር ሲዋጉ ተገደሉ። ከቻይና ጋር የነበረው ፖለቲካዊ ግንኙነትም ከዚያ በኋላ እንዳከተመ አስታውሳለሁ።

አሁን ወደ ቤጂንግ ልመልሳችሁ። ቤጂንግ ማለት ‹‹ሰሜናዊት መዲና›› ማለት ነው። የቤጂንግ ልዩና ታዋቂ ምግብ የሚባለው – ‹‹የቤጂንግ ዳክዬ›› ነው። የአራዳ የስም ላጲሶች ስለ ቻይና ምግብ የሚሉት አላቸው። ‹‹በቻይና ከሰማይ- አይሮፕላን፣ ከምድር- መኪና፣ ከባህር- መርከብ ብቻ ነው የማይበላው›› የሚል። አባባላቸው እውነት ሊመስል ይችላል። ግን ቤጂንግ የራሷ ምርጫ አላት። ዕውነት ነው፣ የቅንቡርስ ጥብስ፣ የጉንዳን ድርቆሽ፣ ወይም የቀርከሃ ቀንበጥ ሾርባ፣ የውሻ ሥጋ ቅቅል፣ (እንዳይዘገንናችሁ ቆጠብ አድርጌዋለሁ) ይበላል ሲባል ከመስማት በስተቀር እኔን አላጋጠመኝም። እንዲያውም ቤጂንጋዊያን በቤጂንግ ጐዳና ውሻዎቻቸውን ሲያናፍሱ መመልከት ይቻላል። እርግጥ ነው የቀርከሃ ቀንበጥ ቅጠሎች በሾርባ መልክ ሲቀርቡ እጅ ያስቆረጥማሉ።

 በተረፈ በቻይና ሆቴሎች በመስታወት በተሠራውና በሚሽከረከር ጠረጴዛ ላይ ለዓይን የሚታክት ምግብ መመገብ ይቻላል። ብቻ ከፈለጉት እያማረጡ ወንበሩን እያሽከረከሩ መጠቀም ሰፊ ምርጫ አለው። አስቸጋሪው ነገር የቻይናን መመገቢያ ሁለት ቀጫጭን ዘንጐች ይዞ መጠቀም ነው። ቢያስቸግርም በዘንጐቹ መመገብ የግድ ነው። ሹካ፣ ማንኪያ አቅርቡልኝ ለማለት በቋንቋና በምልክት መግባባት አይቻልም። ካልቻሉበት ተርቦ መዋል ነውና በግድ ይለምዱታል። በቻይና ምን የማይለመድ አለ?

በቤጂንግ ካስገረሙኝ ነገሮች ቤጂንጐች ፎቶ-መነሳት መውደዳቸው ነው። የውጭ ዜጋ ከመሰላቸው ማናቸውም ሰው ጋር ፎቶግራፍ መነሳት ያስደስታቸዋል። ነፍስ የላቸውም። ይዤው የሄድኩት ካሜራ ቻይናዎችንና አስደናቂ ቦታዎችን ከማንሳታቸው ይልቅ ተመልሰው የእራሴ ፎቶ-ማንሻ መሆናቸው አስገረመኝ። በመጀመሪያ ቀን ሆቴላችን አካባቢ አብረውኝ ፎቶ ተነሱ። እንዲያው አንዳንድ አመለኞች የፈፀሙት መስሎኝ ነበር። በነጋታው፣ በሦስተኛው ቀን፣ ብቻ እስከምመለስ ድረስ ፎቶ መነሳት ብቻ ነበር።

 በጠዋት ተነስቼ ከሆቴል ሞንጐሊያ መስኮት ወደ ውጭ ስመለከት ያጋጠመኝ ሰማያዊ ሰማይ አልነበረም። ሰማዩ አመዳይ ነው። ታፍኗል። ቻይናዎች ያመጡት ስልጣኔ ሰማያዊ ሰማይ እንዳያዩ አድርጓቸዋል። ሥልጣኔ መልሶ ጠላት ሲሆን መመልከት በቻይና ብርቅ አይደለም። ብርቅ የሚሆነው ሁሉም ቻይናዊ በፓርኮች መሃል ሆኖ ‹‹ታይ ቺ›› (Tai chi) የተሰኘውን ቀላል ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲሰራ መመልከት ነው። ቻይናዎቹ በጋራ አካላቸውን ያሰራሉ። የጋራ ሥራ ያስደስታቸዋል። ጐንበስ፣ ቀና፣ ዞር-ዞር ሲሉ የሲንፎኒ ሙዚቃ የሚመሩ የሙዚቃ መሪዎች ይመስላሉ ስፖርተኞቹ። ቻይናውያን በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ሳይሆኑ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ናቸው። ነጋ-ጠባ ይጣደፋሉ፣ ይሠራሉ። ቅዳሜ፣ እሁድ አይታወቅም። የወደፊቱ ዓለም የእነሱ ስለመሆኑ ያልማሉ ይመስለኛል – በያንዳንዱ ቻይናዊ ልብ ውስጥ ‹‹የወደፊቱ ዓለም የእኔ ነው!›› የሚል እሳቤ የሚደልቅ ይመስለኛል። ይህ ሁኔታ የአፍሪካውያንን የሚዳቋና የአንበሳ ሩጫ አባባል ያስታውሰኛል። ከቶማስ ፍሬድማን ነው መጀመሪያ ያነበብኩት፤ እንዲህ ይላል፡-

 ‹‹ሲነጋ አፍሪካ ውስጥ ሚዳቋ ቀድማ ትነቃለች፣ ከፈጣኑ አንበሳ በላይ ፈጥና ካልሮጠች እንደምትበላ ታውቃለችና፤ ሲነጋ አንበሳ ከእንቅልፉ ይነቃል። አንበሳው የምትንቀረፈፍ ሚዳቋ ጠልፎ መያዝ እንዳለበት ያውቃል፤ ያለበለዚያ በጠኔ ይሞታል። አንበሳም ሆንክ፣ ሚዳቋ ምንም አይደለም። ፀሐይዋ ሞቅ ስትል ሩጫህን ግን መጀመር አለብህ›› ይላል አባባሉ።

አንበሳው ማን ነው? ሚዳቋዋስ?

ዛሬ ትራምፕ የንግድ ማዕቀብ እያደረግን ነው ብለው በቻይና ላይ እየፎከሩ ነው። እዚያ በነበርኩ ጊዜ ቻይናዎቹን ስለ ትራምፕ ማዕቀብ ጠየቅናቸው። ቻይና ጉራ አያውቅም! አሁንም ቢሆን እኛ እንደ አፍሪካውያን ታዳጊ ነን። የትራምፕ ትራምፔት ግን አያስደነግጠንም ይላሉ። አሜሪካ ትራንፔቷን ትንፋ እንደማለት። አሜሪካኖች የቻይና 1.3 ትሪሊዩን ዶላር ባለዕዳ እንደሆኑም ያወሳሉ። ግን እኛ በማንም ላይ ጉራ አንነዛም። ማንንም ለመድፈቅ አንፈልግም። ከዓለም ጋር መንገድ ነው ትልማችን ይላሉ። ቻይናዎች አንድ አባባል አላቸው። ‹‹ወፊቷን ለማጥመድ ቀድመህ ጐጆዋን ሥራላት›› (To attract the phoenix, build the nest first) የሚል። ይሄውና ለዚህ ብለን እኮ ነው ‹‹One Belt, one Road›› የሚል ቀደምተኝነት የወሰድነው ይላሉ። ምዕራቡ አለም በተራው ‹‹አዲሱ የቻይና ማርሻል ፕላን›› እያለ ያጣጥለዋል። አምስት ትሪሊዮን ዶላር ለዓለም መድበናል ይላሉ ቻይናዎች። ለአፍሪካ ወንድሞቻችን ደግሞ የ6ዐ ቢሊዮን ዶላር ቀደምተኝነት ወስደናልና ቶሎ የተጠቀመበት ሀገሩን ያሳድጋል ሲሉ ይመክራሉ። በርቱና ተጠቀሙበት ይሉናል።

“ዓይናቸው፣ ስሜታቸው ሁሉ ሥራና ዕውቀትን መገብየት ነው። ሲጓዙ ከሞባይላቸው ዓይናቸውን አይነቅሉም። ለሥራ፣ ለእውቀት ያላቸው ጉጉት ያስደምማል። ሩቅ አስበው የሚጓዙ ፍጡሮች ናቸው”

በዚህ ረገድ ከአፍሪካ ሀገራት በብዛት ተጠቃማዎቹ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። በተለይ በኬንያ ‹‹የሞምባሳ- ናይሮቢን የባቡር መንገድ›› በጋራ ሠርተናል ሲሉ እንደማሳያ ነገሩን። ይህ ሲነገር ኬንያዊው ዶክተር እዝቅኤል ሙቱዋ ፊቱ በደስታ ፈካ ሲል ይታየኛል። ሰውየው ቡፋ – ብጤ ነው። እርግጥ በሀገሩ ትልቅ ኃላፊነት አለበት-የኬንያ የፊልምና የብሮድካስት ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው። ብዙም ደረት የሚያስነፋ ስልጣን ባይሆንም በሰዎች መሀል ቁጢውን የሚነሰንስ ሰው ነው። ስለ ራሱ ሲያስተዋውቅ እንዲህ አለ፡- ‹‹የአሁኑ የኬንያ ፕሬዚደንት እንዲመረጥ ያመቻቸሁት እኔ ነኝ። እንዴት ማሸነፍ እንደሚችል ያዘጋጀሁት እኔ ነኝ። በሚቀጥለው ምርጫ ደግሞ እኔ ለፕሬዚደንትነት ስለምወዳደር ያን ጊዜ ጠብቁ!›› ሲል መልሶ በወፍራም ምላሱ፣ አፍሪካዊ ሳቁን ሳቀ። እኛም እየተያየን ዶ/ር ሙቱዋ ላይ ሳቅን። ናይጄሪያዊው አብዱልዋሂድ ብቻ ነው ያልሳቀው። ለምን ቢሉ – ዕንቅልፉን ይለጥጥ ነበርና ነው። እንዲያው ብቻ ሌሎቻችን ተሳሳቅን ማለት ይቻላል። አንዱ ቻይናዊ በመሃል ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቻይና!›› እንደምትባል ታውቃላችሁ? ሲል ቤቱን ኩም አደረገው። ሙቱዋ ደስ ያለው አይመስልም። አጅሬው ቻይና ይህን ያልኩት እኔ አይደለሁም ‹‹ኒው ዮርክ ታይምስ›› ጋዜጣ ነው፣ ሲል የበለጠ እሳት ለኮሰበት። ልጥልጥ ኑግ የመሰለው ፊቱ ላይ ላቡ ችፍ ሲል ይታየኛል።

ቻይና ዛሬ መሸጥ፣ መለወጥ የቻለች ሀገር ናት። የቻይና ዕቃ፣ የቻይና ዋጋ፣ ሌላው ቀርቶ የቻይና ዲቃላዎች በየሀገሩ እየተፈጠሩ ስለመሆናቸው ማን ይክዳል? በእኛ ሠፈር እንኳ፣ በዚያ በኮብል ስቶኑ መግቢያ አንድ ቻይናዊ ህጻን ልጁን ይዞ ሲወጣ ፊት ለፊት ተገጣጥመናል። ‹‹ኒ ሓው!›› አልኩት በቻይንኛ። ‹‹እንዴት ነህ?›› እንደ ማለት።

 ቻይና በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ እጅና እግሯን ካስገባች በኋላ ‹‹አውትሶርሲንግና ኦፍሾሪንግ›› የተሰኙ የኢኮኖሚና የትብብር ቃላትን በመዝገበ – ቃላቷ ውስጥ አስፍራለች። ደግሞም ተጠቅማበታለች። በተለይ ‹‹ኦፍሾሪንግ›› ቻይናን ጠቅሟታል። ቶኪዮ ወይም ኦሃዮ ያለ ፋብሪካ ተነቅሎ ቻይና ሲገባ ነው ‹‹ኦፍሾሪንግ››፤ ተመሳሳይ ምርት ያቀርባል ለደንበኞቹ። ትርፉ ግን ቻይና በመግባቱ የትየለሌ ነው። ምክንያት አለው። ርካሽ ጉልበት፣ ዝቅተኛ ታክስ፣ ድጋፍ ያለው የኃይል አቅርቦትና ዝቅተኛ የጤና ኢንሹራንስ ተጠቃሾች ናቸው። ይህን በማድረጓ ቻይና ዛሬ ሁለተኛዋ የኢኮኖሚ ታላቅ ሀገር ሁናለች። የምትባንን ሚዳቋ ሳትሆን የምታስፈራ አንበሳ ሁናለች። ከ One Belt, one Road ቀደምተኝነትም ፈጣን ሚዳቋ የሆነች አፍሪካዊ ሀገር ትጠቀማለች። እሷም ኬንያ ሳትሆን አትቀርም። እኛስ? እኛማ እየተበላላን ስለሆንና በጐጆ ደረጃ ወርደን ስለምናስብ ለዚያ አልታደልንም።ያሳዝናል።

እጅግ የተደነቅኩት ዋነኛው – በቻይና ወጣቶች ነው። በሜትሮ ባቡር ውስጥ፣ መንገድ ላይ ፣ አሳንሰር ውስጥ ሳይቀር ወጣቶቹ ይቸኩላሉ። ፋታ የላቸውም። ዓይናቸው፣ ስሜታቸው ሁሉ ሥራና ዕውቀትን መገብየት ነው። ሲጓዙ ከሞባይላቸው ዓይናቸውን አይነቅሉም። ለሥራ፣ ለእውቀት ያላቸው ጉጉት ያስደምማል። ሩቅ አስበው የሚጓዙ ፍጡሮች ናቸው። የተለየ የሱስ ምርኮኝነት አይታይባቸውም። ሲቀመጡ ኮምፕዮተራቸው ላይ ዓይናቸውን ከተከሉ ሌላ ነገር አያስቡም። ተንኮል የለባቸውም። የሩቅ ሀገር ሰው ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዴ አንድ የገበያ ሥፍራ ፈልገን ጠየቅናቸው። አቅጣጫውን ነገሩን፣ እኛም በተባልነው መሠረት ወደዚያ እያመራን ነበር። ብዙ ተጉዘናል፣ የመሩን ቦታ ትክክለኛ ያለመሆኑን የተረዱት ወጣቶች እያለከለኩ ይከተሉን ነበር። ደረሱብን። በማሳሳታቸው ታላቅ ይቅርታ ጠይቀው ትክክለኛውን ቦታ ለማሳየት አብረውን ተጓዙ። ይህ አስደናቂ ነው። የእኛ ወጣት፣ የእኛ ተማሪ ግን፣ በደም፣ በጐሣ፣ በጐጆ ልዩነት ዱላ ይማዘዛል፣ ገጀራውን በሌላው ወንድሙ ላይ ይስላል። የዓይኑ ቀለም ካስጠላውም ዘቅዝቆ ይሰቅለዋል። ዘቅዝቆ መስቀል ካልጠቀመው ወይም ካላረካው በመኪና አስከሬኑን ይጐትታል። ያስጐትታል። ፌስቡኪስት፣ፌክቡኪስት፣ አክቲቪስት፣ አጭቤይስት… ተብዬዎች በኩራት ሲዘባነኑ ማዬት ያስደምማል። መንግሥት ሆነናል የሚሉ ተመፃዳቂ መሆናቸው ያስተዛዝባል። አንዳንዱማ ወጣት ጨካኝነቱ ከየት እንደመጣ ማወቅ ያዳግታል። የወንድሙን አስከሬን ጐትቶ ማሰቃየት ካላረካው ቤንዚን ያርከፈክፍበታል። ከዚያም እሳት ለኩሶ አስከሬን እየዞረ ጮቤ ይረግጣል። ይህ ዛሬ የደረስንበት አሳዛኝ ትርዒት ነው። ሀገር፣ ትውልድ፣ ወላጅ፣ ተወላጅ፣ መሪ፣ ተመሪ፣ ሊያፍርበት የሚገባ የርኩሰት መንገድ። የጠበበ የሙታኖች ጉድጓድ! ከዚህ ሠይጣናዊ ጐዳና ወጥቶ እንደ ቻይናዎች መሠልጠን ለኢትዮጵያችን የማይታለም ህልም መስሎ ይታየኛል። ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ጉድ ያየች ሀገር ስለሆነች አትወድቅም፣ ኢትዮጵያ አትጠፋም። ‹‹ከሞተ አንበሳ ማር ይወጣል›› የሚለው አባባል የሚሠራው ለኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ተስፋ አላት!

በቻይና ሞባይል ትልቅ ሥራ ይሠራል። ካፌ ገብቶ ለመክፈል ኪስ መፈተሽ አያስፈልግም፣ ኤቲኤም ማሽን ፊት ለፊት መላፋት አያስፈልግም። ብቻ ሞባይልዎን አውጥተው ለክፍያ ማቅረብ በቂ ነው። በሞባይል ምግብ ይገዛሉ፣ ሆቴል ይጠቀማሉ፣ የታክሲ ወይም የሜትሮ ክፍያ ይፈጽማሉ። ማናቸውንም ነገር በሞባይል መክፈል ይቻላል። እኛ ሞባይል እንሸከማለን እንጂ አንጠቀምበትም፣ ቻይናውያን ግን በትክክል ይጠቀሙበታል። እዚህ ቅርብ ኡጋንዳ እንኳ ውሃና መብራት በሞባይል ስልክ መክፈል ከተጀመረ ብዙ ቆየ። እኛ ሞባይል እንሸከማለን፣ ያውም ከአንድም ሁለት፤ ቻይናውያን ግን ይጠቀሙበታል።

 በነገራችን ላይ በቻይና አሁንም ብስክሌቶችና ስኩተሮች ከፍተኛ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሠጣሉ። ለቤጂንግ 25 ሚሊዮን ነዋሪ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። በሞባይላቸው ተከራይተው ወደፈለጉበት ከደረሱ በኋላ አቁመው ይሄዳሉ። ካምፓኒው አሰባስቦ ለአገልግሎት ያውለዋል። እኛስ ለአዲስ አበባ የመሬት አቀማመጥና መንገድ የሚሆን የትራንስፖርት ዘዴ እንዴት መዘየድ አቃተን?

መቼም ቻይና በኢኮኖሚ የፈረጠመች ብቻ ሳትሆን በከተሞቿ ዘመናዊነትም ታላቅ ሁናለች። ከ16ዐ በላይ በሚሆኑ ከተሞች፣ በያንዳንዳቸው ከሚሊዮን በላይ ህዝቦች ይኖሩባታል። በአንዱ ከተማ ለዓለም የሚቀርብ የዓይን መነጽር ፍሬም ሲሠራ፣ ሌላኛው ፓንትና ካናቴራ ያመርታል። ሌላው ከተማ ደግሞ የኮምፒዩተር ስክሪኖች ለዴል ኩባንያ ሠርቶ ለአሜሪካኖቹ ያስረክባል። ስለዚህ ቻይና አደጋም፣ ሸማችም፣ መልካም አጋጣሚም ሆና ትታያለች። ሽሮ ወይም ሽንኩርት ከጓዳችን ሲጠፋ አደጋ ናት።

 ልብሶችና ጫማዎቿ በርካሽ ሲቀርቡልን፣ ሠራተኞቿ መንገድና ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ሲገነቡልን መልካም አጋጣሚያችን ናት። ዛሬ ቻይና እንደ ማኦ ዘመን አይደለችም። ኮካንና ማክዶናልድን እንዳልተጠየፈች፣ ከተሞቿ በእነዚህ የኮካና የማክዶናልድ ባህል ተቀይደው ሲታዩ ያ የማኦ ዝግ ዘመን ሲያስደንቀን ይኖራል። ዕድሜ ለዴን ዥያኦፒንግ ቻይናን ለዓለም በረገዱ። በፍሬድማን አባባል የዓለምን ክብነት ሳይሆን ዝርግነቷን አጣጣሙ። ዛሬ በቻይና የተመረተ፣ የቻይናን ቅናሽ ዋጋና በየጉራንጉሩ ‹‹ከቻይኖች የተወለዱ!›› ልጆችን ማየት ጀምረናል። ነገ ምን ጉድ እንደምታመጣ ከወቅቱ የቻይና ዕድገት መገመት ይቻላል።

ፕሮፌሰር ቻን ዕንቁላል በመሰለው ሀይገር አውቶቡስ (የአዲስ አበባው ሀይገር ከየት እንደመጣ እግዜር ይወቀው) ውስጥ ሆነን በነገው ዕለት ጉብኝት እንዳለን አበሰረች። ‹‹ነገ የምትጐበኙት የቻይናን ታላቁን ግንብ ነው›› ስትለን ሁላችንም እንደ ህፃን ፈነደቅን። እውነትም የሚያጓጓና ሁላችንም የተደሰትንበት ነው። ግንቡ ጥንታዊ ቢሆንም እንደገና የተገነባው በሚንግ ዳይናስቲ 1368 ነበር። በወቅቱ ተዋጊዎቹንና ፈረሰኞቹን ሞንጎሎች ለመመከት የተዘጋጀ ነበር። እኔም እንደ ማርኮ ፖሎና እንደ ጆቫኒ ዳ ፒያን ዴል ካርፒኔ ይህን ግንብ የመመልከትና የመተረክ ዕድል ስለገጠመኝ ደስተኛ ነኝ። ለእንደኛ አይነቱ የተራራ ሰው ብዙም አስደናቂ ባይባልም በዚያን ወቅት መሠራቱ ያስገርማል። የመጨረሻው መዳረሻ ላብ በጀርባ እስከሚወርድ ድረስ ያስጨንቃል። ትንፋሽ ይፈልጋል። እንዲያም ሆኖ የመጨረሻው ‹‹የገነት በር›› ድረስ መዝለቅ ያስፈልግ ነበርና ደረስኩበት። ማን ከገነት በር ይቀራል? በሚል። የዚያን ዕለት ብዙዎቻችን እግራችን ተሳስሮ ነበርና ጠጅ ቤት ውስጥ እንደሚከራከሩ ሰዎች ይንጫጩ የነበሩት ናይጄሪያውያን ፀጥ ብለዋል። ተንጋለው ዕንቅልፋቸውን ይለጥጣሉ። በተለይ ናይጄሪያዊው አብዱልዋሂድ ለማንኮራፋት የሚቀድመው አልነበረም። እኔም የሩሲያ ኮስሞናቶች ሳይቀሩ ከጨረቃ ላይ የሚታይ ‹‹የምድር ብርቅዬ ›› ብለው ያደነቁትን የግንብ አሰራር እያሰላሰልኩ ዕንቅልፍ ይዞኝ ዥው አለ። ስለ ነገው የቲያንሜን አደባባይ ጉብኝት እንኳ ሳላስብ ጭልጥ አልኩኝ – በሚደላው የኢነር ሞንጐሊያ ሆቴል። ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው።

 ቲያንሜን አደባባይ ጥሩ ሰዓት ላይ ደረስን። በግራ አቅጣጫ የማኦ አስከሬን ያረፈበት ማዞሊየም (Mausoleum) ይታያል። ሄጄ የ42 ዓመት ዕርሜን ባወጣ ምን አለበት? የሚል ሃሳብ ሰቅዞ ያዘኝ። ‹‹አትቀየመኝ! አትቀየመኝ – ሊቀ- መንበር ማኦ!›› እያልኩ ዘለላ ዕንባ ባፈስለት በወደድኩ። ዳሩ አልሆነም። ወደ ‹‹ተከለከለው ከተማ›› (Forbidden City) ወደሚባለው አመራን። ከፊት ለፊት ማኦ በ1949 በድልና ካለምንም ተኩስ ቀዩን ጦር ይዞ የደሰኮረበት ሰገነት ይታያል። እዚያ ላይ ሆኖ ነው በሁናን ቻይንኛ ሶሻሊስት ቻይና መመሥረቷን ለዓለም ያሳወቀው። እንደተለመደው ፎቶ ተነሳን። ከዚያም አልፈን ወደ ተንቆጠቆጠው ቤተ መንግሥት አመራን። የእነ ሚንግና የእነ ጐንግ ዳይናስቲ የሠሩት ቤተ መንግሥት ነው። ቀልብ ይገዛል። ዕውን የዚህ የተከለከለው ከተማ ግንባታ በ14ዐ7 ዓ.ም ተጀመረ ብሎ ለማመን ይቸግራል። ስድስት የምሥራቅ ቤተ መንግሥቶችና ስድስት የምዕራብ ቤተመንግሥቶች ደምቀው የቤጂንግን ሥፍራ በወርድና በስፋት ይገዛሉ። በመጀመሪያው የ1911 አብዮት ነው ይህ የፊውዳሉ የቤተ መንግሥት ዘመን ያከተመው። ቻይና ግን ያንን የጥንት ሥልጣኔዋን ይዛና አብዮቶቿን ከዘመኑ ጋር አቀናጅታ ተራመደች። እነሆ ዛሬ ታላቅ ሀገር ሆና እንደ ቀድሞዎቹ ዳይናስቲዎች ገዝፋ በዓለም ላይ ትታያለች።

ወደ ሌላው የንጉሣውያኑ የግል መኖሪያ ‹‹The Palace of Heavenly Purity›› እንዳመራን ሙሽሮች አየን። ‹‹ጉሮ ወሸባዬና አቧራው ጨሰ›› የለም! ሙሽሮቹ ተቃቅፈው ፎቶ ይነሳሉ። የጥቁር እንግዶች እዚያ መገኘት ለሙሽሮቹ እንደ ሚልኪ ሳይቆጠር አልቀረም። ሚዜዎቹ አብረን ፎቶ እንድንነሳ ጠየቁን። አቤት ቻይናዎች ፎቶ መነሳት ሲወዱ! ተነሳንላቸው። ሙሽራዋ ተፍለቀለቀች ብቻ ሳይሆን ተፍነከነከች። ቻይናዎች ሲስቁ ያው ጩልጩሌ ዓይናቸው ከቦታው ይጠፋና ይጨፈናሉ። የሚስቁ ሳይሆን ካራቴ ለመስራት ያሰቡ ያስመስላቸዋል።

እኔና መሐመድ ሹማን ምሣ አስፈልጐናል። መሐመድ ግብፃዊ ፕሮፌሰር ነው። መልካም ግብፃዊ። ግብፃውያን እንዲህ ያሉ ቀናና ደጐች አይመስሉኝም ነበር። በህይወቴ የጅምላ ፍረጃ ባላውቅም ግብጾች ግን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ክፉ ይመስሉኝ ነበር። ተሳስቼያለሁ። ለካስ ክፉም፣ ደግም ሰው የትም አለ። የመሐመድ ባህርይ ይህን አስተምሮኛል።

ወደ ፒዛ ቤት አመራን። ፒዛ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓና የጃፓን ምግብ እዚያ መመገብ ይቻላል። የጃፓንን ሱሺ ምግብ የቀመስነው እዚያ ነው። ያን ዕለት ተርቦ እንደከረመ ሰው ምግቡ ላይ ወረድንበት። ለካስ ሆድ የሚፈልገውን ሲያገኝ እንዲያ ይሆናል። በዚያን ቀን ነው ስለ ሆድ አስተሳሰብ ያወቅኩት። ከሱሺው ጋር የሚቀርበው ማባያ የጂማውን ‹‹ደቆ›› (ቆጭቆጫ) አስታወሰኝ። በደንብ አጣጥመን ተነሳን። እንደተለመደው ሰልፊ (ራስ- ገጭ !) ፎቶ ተነሳን። ከዚያም ወደ ፌስቡካችን ለቀቅነው። እኔም፣ መሐመድም ብዙ ላይኮችን አገኘን። ደስም አለን። ቤጂንግን እንዲህ ሆነን ከርመን በላይክ ለቀቅናት። ምንም ይሁን ምን ቤጂንግ በልባችን ታትማ ትኖራለች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top