ታሪክ እና ባሕል

ባህል-ዋና ዋና ባህርያቱና ማህበረሰባዊ ፋይዳው

ባህል የሚለው ቃል በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ጊዜ፣ ለተለያየ ጉዳይ፣ በተለያየ መልክ ሲነገር ይሰማል:: የቃሉ ትርጉምና የያዘው ፍሬ ሃሳብ ሰፊ የመሆኑን ያህልም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሉ ምሁራን ብዙ ብዙ ጽፈውበታል፤ እየጻፉበትም ነው። በማህበራዊ ሳይንስ ያበቃለትና ያለቀለት ጉዳይ ስለማይኖር ወደፊትም ይተነተንበታል። የታሪክ፣ የሶሲዮሎጁ፣ የአንትሮፖሎጂ፣ ወዘተ ምሁራን የባህል ጥናት ቀዳሚ ተመራማሪዎች ናቸው።

 ይሁን እንጂ እነኚህ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ጥልቅ ዕውቀትን ያካበቱና ምርምሮችን ያካሄዱ፣ ባህልን በአንድ ወይንም በሌላ ምክንያት የሚያጠኑ ምሁራን በቃሉ ብያኔ ላይ የጋራ ስምምነት የላቸውም። የሚያስቀምጧቸው የትርጉም ትንታኔዎች ግልጽ፣ የተመጠኑና ዘላቂነት ያሏቸው አይደሉም። አንዳንዶቹ ባህል ጠንከር ያለ ጽንሰ-ሃሳብ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ባህል እንደ ጽንሰ-ሃሳብ የሚፈረጅ ሳይሆን የሰውን ቀልብ በቀላሉ ሊስብ የሚችል የእለት ተለት ተራ ቃል ነው፤ ምክንያቱም ለጽንሰ- ሃሳብነት የሚያበቁ በግልጽ የተቀመጡና የተፈተኑ መረጃ መለኪያዎች ስለሌሉት ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ቁጥራቸው በቀላሉ የማይገመት ምሁራን እንዲህ ያለውን ማቆሚያ የሌለው ክርክር ከተራ ጉዳይ በመቁጠር በቃሉ ብያኔ ላይ ሳይሆን ፋይዳ ባለው ገቢራዊ ትንታኔው ላይ ማተኮርን ይመርጣሉ። ይህም ሆኖ ባህል የሰው ልጅ የኑሮው ውጤት መሆኑን፣ በአያት በቅድመ አያት ተካብቶ፣ ዳብሮና ጐልብቶ ሲወርድ- ሲዋረድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የጋራ ሃብት መሆኑን፣ የሚያድግና የሚለወጥ እንዲሁም የሚጠፋ መሆኑን፣ ከበርካታ የልማት ትልሞች ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው መሆኑን፣ ወዘተ ሁሉም ይስማሙበታል። ለመሆኑ ባህል ምንድነው? ከቃሉ ትርጉም እንነሳ።

 የቃሉ ትርጉም

 ባህል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት በምሁራን የሚደረጉ ጥረቶች የሰው ልጅ ዝንተ-ዓለም ‹‹ለምን?›› እያለ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ከሚደረጉ መሰል ጥረቶች እንደ አንዱ የሚቆጠሩ ናቸው። ለምሳሌ በስነ-ሰብ የትምህርት ዘርፍ የባህልን ምንነት ለመግለጽ የሚደረጉ ጥረቶች በስነህይወት ስለ አዝጋሚ ለውጥ፣ በፊዚክስ ስለ መሬት ስበት፣ በህክምና ሳይንስ ስለ በሽታ ከሚደረጉ ምርምሮች ጋር ሊነጻጸሩ እንደሚችሉ አንዳንድ ጽሁፎች ይጠቁማሉ።

 በመላምት መልክ የሚቀርቡ ሃሳቦች ሳይንሳዊ ትርጉም የሚኖራቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚከናወን ምልከታ ሊረጋገጥ የሚችል ውጤት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ይህንን ሁኔታ ለማሟላት የሚረዱ የትርጉም ዘርፎች ‹‹ለስራ የሚረዱ ትርጉሞች››

(operational definitions) ተብለው ይታወቃሉ። እንዲህ ዓይነት ባህርይ ያላቸው ትርጉሞች የመላምቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ ከሚውለው ሳይንሳዊ የምልከታ ዘዴ ጋር የሚያገናኙ ሃሳቦች ናቸው። አንድ ቃል ከስራ አንፃር ተተርጉሟል የሚባለው በመረጃ የተገኙና ሊለኩ የሚችሉ ባህርያትን ሊያሳይ በሚችል መልኩ የተቀመጠ እንደሆነ ነው። ለምሳሌ በዲግሪ ሴልሺየስ ወይንም በፋኸረንሃይት ስኬል የሚገለጸው የሙቀት መጠን ትርጉም ‹‹ኦኘሬሽናል›› ወይንም ለስራ የሚረዳ ትርጉም ነው።

ስለ ሳይንሳዊ ትርጉሞች በምናወሳ ጊዜ በቅድሚያ ልንገነዘበው የሚገባን ነጥብ የትርጉሞች ርዕሰ ጉዳይ ቃላት እንጂ ቁስ ወይንም ክስተት አለመሆኑን ነው። ለምሳሌ ባህል ስለሚባለው ቃል ትርጉም

“የአንድ ማህበርን ወይንም ማህበረሰብን የስነምግባር ደንቦች (rules of etiquette) ጠንቅቆ ማወቅና መተግበር፣ ፈጻሚው የማህበሩ ወይንም የማህበረሰቡ አባል መሆኑ የሚረጋገጥበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ክዋኔው የማህበሩ ወይንም የማህበረሰቡ አባል ባልሆኑ ባዕዳን ላይ የሚፈጥረው ስሜትና ባህርይ የሚስተዋልበት ጭምር ነው ”

በምንነጋገርበት ጊዜ የምናወራው ስለ ቃሉ እንጂ ባህል የተባለውን ክስተት ስለሚገልጹና በመረጃ ስለተደገፉ ባህርያት አይደለም። በሌላ አነጋገር ትርጉም አንድ ቃል ምን ወክሎ እንደቆመ ወይንም ጥቅም ላይ እንደዋለ የሚገልጽ ማብራሪያ ነው። የሚያብራራው ቃሉን ለመጠቀም የሚያስፈልጉና ብቁ የሆኑ ሁኔታዎችን (necessary and sufficient conditions) በመጥቀስ ነው።

ምሁራን እንደሚተነትኑት፤ የአስተሳሰብ፣ የእምነት፣ የደስታ፣ የእፎይታና ሌሎች የተለያዩ ስሜቶች የሚገለጹባቸው ዘይቤዎች በባህል ውስጥ የተካተቱ ናቸው። አብዛኞቹ የባህል መገለጫ ዘይቤዎች በጉልህ የሚስተዋሉ ቢሆኑም ጥቂቶቹ ደግሞ ከዚህ የተለዩ ናቸው። ክሉኮን እንደሚለው ባህል አንድ ማህበረሰብ ለመጪዎቹ ዘመናት ይጠቅመው ዘንድ ለረዥም ጊዜ ያካበተው የተከማቸ እውቀት ነው። ክምችቱ በየሰዉ አዕምሮ፣ በመጻህፍት ወይንም ደግሞ በልዩ ልዩ ቁሳቁስ መልክ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በባህል መስክ የሚደረጉት ጥናቶች የተሟሉ እንዲሆኑ ከተፈለገ የባህል ግልጽና ድብቅ የመገለጫ ባህርያት በሚገባ ሊዳሰሱ ይገባል።

 የሆነው ሆኖ ሁሉም ማህበራዊ ክንዋኔዎች በባህላዊ ዘይቤ የተቃኙ አይደሉም። በጊዜ ሂደት በባህሉ መሰረት መፍትሄ ሊያገኙ የማይችሉ አዳዲስ ክስተቶች መፈጠራቸው አይቀርም። የችግሮቹ መከሰትና የመፍትሄዎቹ መገኘት ለባህል መዳበር መንስዔ ይሆናል። ነገር ግን የተከሰቱትን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት አዲስ የተገኙት የመፍትሄ እርምጃዎች እንደ ማህበረሰቡ የባህል እሴት ሊወሰዱ ከተፈለገ አባላቱ ሊያውቋቸውና ሊገለገሉባቸው ይገባል። በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች በሙሉ በሁሉም የህብረተሰብ አባላት ዘንድ በሚገባ ይታወቃሉ ማለት እንዳልሆነም ልብ ሊባል ይገባል።

በህብረተሰቡ እምነት ውስጥ ሰርጸው የሚገኙት ማህበራዊ ዕሴቶች መሰረታዊ የባህል ገጽታ መገለጫዎች ናቸው። ማህበረሰቡ የተለያዩ ቁሳዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመከወን በተደጋጋሚ የሚጠቀምባቸው ስልቶችና ድርጊቶቹ የክዋኔውን ቅደም ተከተል ስርዓታዊ ደንብ ያመለክታሉ። ባህል እንደ ውርስ ወይንም ቅርስ ተወስዶ የሚበየን ከሆነ የሚያመለክተው ትልቅ ቁምነገር የሰዎችን ክንዋኔ ወይንም ስራ ሳይሆን ስራውን ለማከናወን ይረዷቸው ዘንድ የቀሰሙትን ትምህርት ነው። የቀሰሙት ትምህርት ለማህበረሰቡ አባላት አንድ የሆነ ጉዳይ በሆነ ወቅት የተከሰተ እንሆነ ምን መደረግ እንዳለበትና እንዴት መደረግ እንደሚኖርበት ሳይደናበሩ በቀላሉ እንዲወስኑ ያስችላቸዋል። በዚህ ረገድ ባህል የሰውን ልጅ የእለት ተለት ህይወት በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ትልም ነው የሚለው የ1945ቱ የእነክሉኮንና ኬሊ ብያኔ ከዚህ ጋር ይጣጣማል።

የትርጉምን ምንነት ከተነተንበትና እርሱን ተከትለው ከቀረቡት ማብራሪያዎች ስንነሳ ባህልን ለመግለጽ የተደረጉት ሙከራዎች በአመዛኙ ማህበራዊ ውርስን፣ ከተሞክሮ ወይንም ከትምህርት የተገኙ ባህርያትን፣ ሃሳብንና አስተሳሰብን እንዲሁም የጋራ ባህርያትን አጉልተው የሚጠቅሱ ሆነው እናገኛቸዋለን። በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ ባህል ከሰው ልጅ ህይወት ጋር የተሳሰረ፣ መጪውን የኑሮ ዘይቤ ለመተለም የሚረዳና ያለፈውን ዘመን የአስተሳሰብ ዘይቤዎችና ክንዋኔዎች የያዘ ማህበራዊ እሴት ነው። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ውስጥ የባህል ጉዳይ ረዳት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ሎርዴዝ አሪዝቴ በአንድ ወቅት ባህል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ አጠር ባለ ንጽጽራዊ መንገድ ሲመልሱ ‹‹ሰውነታችንን እንደ ኮምፒዩተር ‹ሀርድዌር› ብንወስድ፣ ባህልን እንደ ‹ሶፍትዌር› ልንቆጥረው እንችላለን ብለዋል››።

ትዕምርቶች (Symbols)፣ ማህበራዊ እሴቶች (Social Values) እና ስነ-ምግባር (Norms)

ትዕምርት ምልክት ነው። ምልክቶችን መፍጠርና መጠቀም የሚችለው ሰው ብቻ ነው። ሁሉም የሰው ተግባራትና ባህርያት የሚመነጩት ከዚህ ልዩ ችሎታ ነው። ይህ በምልክቶች የመጠቀም ልዩ ሰብዓዊ ችሎታ የሰው ልጅ ባህል እንዲኖረው አስችሎታል። ሰው ያለባህል ማህበራዊ ኑሮ ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ማህበራዊ ኑሮ ጉንዳንና ንብን በመሰሉ ነፍሳት መካከል የሚታየውን ዓይነት የደመነፍስ የህብረት ኑሮ የሚመስል ይሆናል።

 በአንትሮፖሎጂስቶች አመለካከት ትርጉሙ በተጠቃሚዎች ዘንድ በወል የታወቀና ለአንድ ሌላ ነገር በውክልና የቆመ ማንኛውም ነገር ምልክት ይባላል። ምልክት የትኛውም ዓይነት ፊዚካላዊ ባህርይ ሊኖረው ይችላል- – የማቴሪያል፣ የቀለም፣ የድምፅ፣ የጣዕም፣ የመዓዛ፣ የቁሳዊ እንቅስቃሴ፣ ወዘተ። የያዘው ትርጉም ከሚወክለው ነገር ውስጣዊ ባህርይ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ምልክት በሰው የሚፈጠር እስከሆነ ድረስ የትርጉሙ ምንጭ ማህበራዊ ነው ማለት ነው። ስለዚህ የምልክቶች ትርጉም ሰዎች በዘፈቀደ ያወጡት ሲሆን ከምልክትና ከትርጉሙ አንፃር ሲታይ ባህል የምልክት ስርዓት (symbol system) ነው ማለት ይቻላል።

ከባህል ትንታኔ ጋር በተያያዘ ሁለት ዓይነት የምልክት ዓይነቶች ተለይተው ይታወቃሉ። እነኚህም አመልካች (referential) እና ገላጭ (expressive) የሚባሉት ናቸው። አመልካች ምልክቶች ውሱን (specific) ትርጉም ያላቸውና አገልግሎታቸውም የእጅ/የዕደጥበብ መሳሪያን ያህል ግልጽ የሆነ ነው። የገላጭ ምልክቶች ትርጉም ግን ሰፊና ቀጥተኛ ያልሆነ ነው። ከባህል ጽንሰ-ሃሳብ ጋር የተዛመዱትና ሁነኛ ድርሻ ያላቸው ገላጭ ምልክቶች ናቸው። የግለሰብንም ሆነ የቡድን ማንነትን በማረጋገጥ ረገድ ገላጭ ምልክቶች ወሳኝ ድርሻ አላቸው። በመሆኑም ማህበራዊ ትስስርን እውን በማድረግ አገልግሎት ላይ ሲውሉ የሚስተዋሉት ምልክቶች ገላጭ በሚለው ፈርጅ የተፈረጁት ሆነው እናገኛቸዋለን። ገላጭ ምልክቶች የሰንደቅ ዓላማን ወይንም የበዓል አከባበርን ያህል ቁልጭ ብለው የሚታዩ መሆን አይጠበቅባቸውም። ለምሳሌ የአንድ ማህበርን ወይንም ማህበረሰብን የስነምግባር ደንቦች (rules of etiquette) ጠንቅቆ ማወቅና መተግበር፣ ፈጻሚው የማህበሩ ወይንም የማህበረሰቡ አባል መሆኑ የሚረጋገጥበት መንገድ ብቻ ሳይሆን ክዋኔው የማህበሩ ወይንም የማህበረሰቡ አባል ባልሆኑ ባዕዳን ላይ የሚፈጥረው ስሜትና ባህርይ የሚስተዋልበት ጭምር ነው።

 የጋራ ባህል ያላቸው ህዝቦች እጅግ ጉልህ በሆነ መንገድ በወል ከሚገለገሉባቸው ምልክቶች አንዱና ዋነኛው ቋንቋ ነው። ቋንቋ የምልክት መግባቢያ ነው። መግባባቱ በቃል ወይንም በጽሁፍ ሊሆን ይችላል። ቋንቋ ከባህል ጋር በሦስት ዋና ዋና መንገዶች የተቆራኘ እንደሆነ የስነልሳን ሊቃውንት ይናገራሉ። ቋንቋ የባህል ግምጃ ቤት፣ የባህል ማዕቀፍና የባህል ተምሳሌት ነው። እንደ ባህል ግምጃ ቤትነት ቋንቋ የማህበረሰቡን በዓላትና የአከባበራቸውን ስርዓት፣ ትውፊቱን፣ ጸሎቱን፣ እርግማንና ምርቃቱን፣ በአጠቃላይ የነገሮችን ትርጉም ሁሉ አካትቶ ይዟል። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ ለመሆን የማህበረሰቡን ቋንቋ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። የቋንቋው መበልጸግ የባህሉን መስፋፋት፣ የቋንቋው መጥፋት ደግሞ የባህሉን መክሰም ሊያመለክት ይችላል።

ቋንቋ የተለያዩ ችሎታዎችን ለማዳበር፣ የአስተሳሰብ ዘይቤን መስመር ለማስያዝና አድማስን ለማስፋት እጅግ ወሳኝ የሆነ ማህበራዊ መሳሪያ ነው። ይህ የቋንቋ ባህርይ በሚገባ የሚገለጸው በጽሁፍ ጥበብ ነው። ጽሁፍን የሚያነብ ሰው በአካል ከማያውቀው ሌላ ሰው ጋር በሃሳብ ይገናኛል። ይህም በመሆኑ የተማረው ሰው ከአካባቢው ርቆ ስለሚገኘው ዓለም ያለው ግንዛቤ ካልተማረው ሰው እጅግ የተለየ ነው። በተጨማሪም ከቃል መግባባት በተለየና በላቀ ሁኔታ ቃላትን በጥንቃቄ እያጠኑ በመተንተን ልዩ የአስተሳሰብ ዘይቤን ማዳበር የሚቻለው በጽሑፍ ጥበብ ነው። ሳይንስ፣ ዘመናዊ ቢሮክራሲና የአስተዳደር መዋቅር፣ ዐውደ-ጥናት፣ ወዘተ የጽሑፍ ቋንቋ በመኖሩ እውን የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ለዚህም ነው ቋንቋ የባህል ማዕቀፍ ነው የሚባለው።

ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው ቋንቋ ትዕምርተ ባህል ነው። የማህበረሰብ አባላት ከሚጋሯቸው የባህል እሴቶች ጉልህ በሆነ መልክ የሚስተዋል ነው። ቋንቋ በአንድነት መካከል ልዩነትንም ሊያመለክት ይችላል። የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ቋንቋውን በመናገሩ ከሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተለየ መሆኑን እንደሚያሳይ ሁሉ በዚሁም አንድነቱን ወይንም ተመሳሳይነቱን ያረጋግጣል።

 ከቋንቋ ቀጥሎ ሌሎች የባህል መገለጫዎች ማህበራዊ እሴቶችና ስነ-ምግባር ናቸው። ማህበራዊ እሴቶች ህብረተሰቡ ለአንድ አስፈላጊ የወል ግብ ያስቀመጣቸው የጋራ አስተሳሰቦች ናቸው። ማህበራዊ እሴቶች ሰናይ ወይንም እኩይ፣ በጐ ወይንም ክፉ፣ አስፈላጊ ወይንም የማያስፈልግ ተብለው ተፈርጀው የሚቀመጡና በማህበሩ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ማህበራዊ እሴቶች ከህብረተሰብ ህብረተሰብ ሊለያዩ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ማህበረሰብ ትህትናንና ይሉኝታን፣ ሌላው ደግሞ ድፍረትና መጋፈጥን፣ አንዱ መተባበርንና መረዳዳትን፣ ሌላው ውድድርን እንደ ማህበራዊ እሴት ሊቀበላቸው ይችላል። ነገር ግን የሰው ልጅ በባህልና በሌሎች አግባቦች የተለያየ ቢሆንም ሰው በመሆኑ የሚጋፈጣቸው የወል ጉዳዮች በመኖራቸው የተነሳ ማህበራዊ እሴቶች አጠቃላይ ባህርይ ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ የትኛውም ማህበረሰብ ቢሆን ምስቅልቅልንና ዋስትና ወይንም ተስፋ ማጣትን፣ ደካማ የቤተሰብ አደረጃጀትንና ጤና ማጣትን እንደ ማህበራዊ እሴቶች ተቀብሎ አያጐለብትም። ሆኖም እያንዳንዱ ማህበረሰብ መረጋጋትንና ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ጠንካራ የቤተሰብ አቋምንና ጤናን ለመንከባከብ የሚያስችሉት የተለያዩ መርሆዎችና እርምጃዎች ይኖሩታል። በልማት በገፉ ሀገሮች የዋስትና መሰረቱ ትምህርት ወይንም በባንክ የተቀመጠ ወረት ሊሆን ይችላል። በኢንዱስትሪ ልማት ወደኋላ በቀሩ ሀገሮች ግን የዋስትና ማረጋገጫው ወገን ወይንም የዘመድ ብዛት ሊሆን ይችላል። በደምሳሳው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውንና እንደ ግብ የተቀመጡ እሴቶችን እውን ለማድረግ የተቀረጹ ዘይቤዎች ወይንም መመሪያዎች ስነምግባር ይባላሉ።

ስነ-ምግባር የማህበረሰብ አባላት ሊያደርጉ የሚገባቸውንና የማይገባቸውን የሚወስኑ የድርጊት መርሆዎችን በሙሉ ያጠቃልላል። ስነ-ምግባርና ማህበራዊ እሴቶች እጅግ ውስብስብ ግንኙነት አላቸው። የማህበረሰብ አባላትን ባህርይ በማረቅና ማህበራዊ ቁጥጥርን በማረጋገጥ ረገድ ሁነኛ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ከስነምግባር ዘርፎች አንዳንዶቹ በህግ መልክ ተቀርጸው ይደነገጋሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም የስነምግበር ዘርፍ ለግለሰብም ይሁን ለማህበረሰብ እኩል ጠቀሜታ አላቸው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ፋሽንን የመሰሉ ማህበራዊ ክስተቶች በጊዜአቸው በማህበረሰብ አባላት ዘንድ ጠንከር ያለ ተቀባይነትን ያገኙና በማህበራዊ ስነምግባር (social norms) መልክ ዘለግ ላለ ጊዜ ሊቆዩ ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን የማህበራዊ እሴት እምብርት ተደርገው አይወሰዱም። በአፍራሹ ዴሞክራሲ በሰፈነበት ህብረተሰብ የዴሞክራሲ መርሆዎችን የመንከባከብና የማጐልበት ምግባር ማህበራዊ እሴቶችን እውን የማድረግ መሰረታዊ ተግባር ነው።

 በአጠቃላይ በስነሰብ የትምህርት መስክ ሁለት ዓይነት ማህበራዊ ስነምግባራት ተለይተው ይታወቃሉ። እነኚህም ፎክዌይስ (folkways) እና ሞሬስ (mores) ይባላሉ። ፎክዌይስ የተባለውን ቃል በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ግድም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው አሜሪካዊው የማህበረሰብ ስነልቦና ተመራማሪ ኘ/ር ዊሊያም ግራሃም ሳምነር ነው። እንደ ኘ/ር ሳምነር አስተያየት ፎክዌይስ አንድ ማህበረሰብ የተለያዩ ክዋኔዎችን በዘልማድ፣ በወጉና ትክክለኛ ነው ተብሎ በሚታመንበት መንገድ የሚከውንበት ማህበራዊ እሴት አካል ነው። ፎክዌይስ እጅግ ሰፊና ጽኑ የማህበረሰብ ልማዳዊ ድርጊቶችን አካትተው ሊይዙ ይችላሉ። ሆኖም ከፎክዌይስ ጋር የተዛመደው ትክክል የመሆንና ያለመሆን ሃሳብ ያን ያህል የገረረ አይደለም። ለምሳሌ በነጮች የገና በዓል አከባበር ስርዓት የገና ዛፍ ማዘጋጀት በእኛም ሀገር በበዓል ቀን ቄጤማ ወይንም እርጥብ ሳር የመጐዝጐዝ ልማዳዊ ድርጊት እንደ ፎክዌይስ ሊወሰድ ይችላል። የገና ዛፍ አለማዘጋጀትም ሆነ ቄጤማ ወይንም እርጥብ ሳር አለመጐዝጐዝ የማህበረሰብ ስነምግባርን ክፉኛ የሚጻረሩ ነውር ተግባራት ተደርገው አይወሰዱም። ይህን ያላደረገ ሰው ወይንም ቤተሰብ ምናልባት እንደ ግድየለሽ ወይንም ለየት ብሎ መታየትን የሚሻ ተደርጐ ይወሰድ እንደሆን እንጂ እንደ ምግባረ ብልሹና ወንጀለኛ የሚቆጠር አይሆንም።

ሞሬስ ግን ከዚህ ለየት ያሉ ናቸው። እንዲያውም ስርወቃሉ ራሱ ‘’moreays’’ የሚባለው የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን ‹‹ሊቀበሉትና ሊያከብሩት እንጂ ሊቃወሙትና ሊጥሉት የማይቻል ደንብ›› እንደማለት ነው። ስለሆነም ሞሬስ ትክክል የመሆንንና ያለመሆንን ሃሳብ በአጽንዖት የያዙ ናቸው። ከማህበራዊ ስነምግባር በሞሬስ መልክ የተፈረጁትን መጣስ ከህብረተሰቡ ቁጣን፣ መገለልን፣ ከፍ ሲልም ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ በእኛና ምናልባትም በሌሎች በርካታ ማህበረሰቦች ዘንድ ውሻን አርዶ መብላት ማህበራዊ ስነምግባርን በጽኑ የተጻረረ ድርጊት በመሆኑ ይህን ያዩ ጐረቤቶች ሁኔታውን በንቀት ከማለፍ ይልቅ በቅርብ ለሚገኝ የህግ አካል ማሳወቃቸው የማይቀር ነው። ከዚህ የምንረዳው በዚህ ድርጊት የተጣሰው የማህበራዊ ስነምግባር ዘርፍ ሞሬስ የተሰኘው መሆኑን ነው።

ባህልና የወል ባህርያቱ

ባህል በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ የጋራ ሃብት ነው። እያንዳንዱ ህብረተሰብ የራሱ የሆኑ የተለዩ ባህላዊ ገጽታዎች አሉት። ለጥናት ያመች ዘንድ እነኚህን የባህል

“አንዳንድ የስነ-ሰብ ምሁራን ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› አደገኛና አደገኛ ያልሆነ ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ሁለት ባህርያት እንዳሉት ይናገራሉ። የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› አደገኛ ያልሆነ ባህርይ ከባህል አንፃር ሰፋ አድርጐ መመልከት ባለመቻል ይገለጻል። ቢድኒ የተባለ ጸሐፊ እንደሚለው ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› በተወሰነ ደረጃ በሁሉም ህብረተሰብና ባህል ውስጥ አለ።”

ገጽታዎች በተለያየ ዘይቤ ከፋፍሎ መመልከት ይቻላል። ለምሳሌ ማንኛውም ህብረተሰብ ተፈጥሮን የሚያስገብርበት ቴክኖሎጂ፣ ውሱን ሃብቶችን በአግባቡና በቁጠባ የሚጠቀምበት የኢኮኖሚ ስርዓትና ምርትን የሚያከፋፍልበት ስልት፣ የቤተሰብ፣ የጐሳና የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካና የፍትህ ስርዓቶች፣ ውበትን የማድነቅና የመግለጫ ዘዴ እንዲሁም የመግባቢያ ቋንቋ ይኖሩታል። ሁሉም ባህል ችግርን የሚጋፈጥበትና መፍትሄ የሚያስቀምጥበት መንገድ አለው። ስለዚህ ሁሉም ባህል በራሱ ምሉዕ ነው። ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ባህል ለራሱ፣ በራሱ ልዩ ነው። አሌክሳንደር ክሮበር እንደሚለው ለአንድ ህብረተሰብ ራሱን የቻለ አንድ ባህል አለ።

ባህላዊ እውነታ ሁልጊዜም ቢሆን ታሪካዊ እውነታ ነው። ንጽጽራዊም ይሁን አርኪኦሎጂካዊ በሆነ መንገድ ወደኋላ መለስ ብለው ታሪክን መመርመርና መረዳት ካልቻሉ በስተቀር ባህልን በውል ለመገንዘብ አይቻልም። ማንኛውም ባህል የጥንቱን ታሪካዊ ተሞክሮ፣ የዘንድሮውን ነባራዊ ሁኔታና የመጪውን ዘመን ትልም ያካተተ ነው። ስለዚህ ባህል የታሪካዊ እውነታነት ባህርይ ካለው ባልተቆራረጠ ረዥምና ተከታታይ ሂደት የተከማቸና የተቀናበረ የህብረተሰብ የጋራ ሃብት ነው ማለት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ ደግሞ ባህል የመወራረስን፣ የመዋሃድን፣ የመለያየትን፣ የመክሰምን፣ የማበብን፣ ወዘተ ክስተቶች የያዘ ነው።

በርከት ባሉ የስነሰብ ድርሳናት ውስጥ ሰፍረው የምናገኛቸው የባህል ጥናት ውጤቶች አብዛኛውን ጊዜ ባህልን የሚተነትኑት ባህርይን፣ ድርጊትን፣ ሃሳብንና ቁሳዊ የዕደጥበብ ውጤቶችን በሚገልጹ ጥቅል ሀረጐች ነው። ሊቃውንቱ እንደሚሉት ለባህል ጥናትና ትንታኔ የመጀመሪያውና መሰረታዊው ተግባር ደቂቅ የሆኑትን የአንድ ባህል ንዑስ ክፍሎች (traits) መለየት ነው። የእነኚህ ንዑስ ክፍሎች ስብስብ ነው ተቋም (institution) ወይንም (traits complex) ተብሎ የሚታወቀው።

በማናቸውም ህብረተሰብ ሰፊ የባህል ማዕቀፍ ውስጥ የምናገኛቸው ንዑስ ክፍሎች ፋይዳ የሌላቸው ከንቱ ነገሮች አይደሉም። አንድ የሆነ ተግባርን ለመከወን የሚረዱና ለህብረተሰቡ ትርጉም ያላቸው ናቸው። በስርዓት የታጀበው ድግግሞሻዊ ክንዋኔአቸው (configuration) ለባህሉ መልክ፣ ትርጉምና ልዕልና ያጎናጽፈዋል። ስለዚህ ባህል በውስጡ የተዛመዱና የተቀናጁ ንዑሳን ክፍሎችን አካትቶ የያዘ በመሆኑ አንዳንድ የስነሰብ ተመራማሪዎች ባህልን ራሱን እንደቻለ ስርዓት (system) ይመለከቱታል።

 አብዛኞቹ የባህል ገጽታዎች በግልጽ የሚታዩ ቢሆንም ድብቅ ወይንም ‹‹አብስትራክት›› የሆኑ ገጽታዎችም አሉ። ግልጽ የባህል ገጽታዎች ልክ እንደ በረዶ ጋራ ወይንም እንደ ማንኛውም ገዘፍ ያለ አካል ለሁሉም ጐልተው የሚታዩ ናቸው። ጋብቻ፣ ውልደት፣ ቀብር፣ ንቅሳት፣ ሰላምታ አሰጣጥ፣ ጨዋታ፣ ጌጣጌጥ፣ ወዘተ በዚህ አግባብ እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ ሲሆኑ ለሰዎች ድርጊት ምክንያት የሚሆኑ አስተሳሰቦች፣ ለአካላዊ እንቅስቃሴ (gestures) እና ለቁሳቁስ እንዲሁም ለህይወት ፍልስፍና የሚሰጡ ትርጉሞች፣ ወዘተ ድብቅ ባህላዊ ገጽታዎች ናቸው። ሆኒግማን የተባለው የስነሰብ ሊቅ እነኚህ መንታ የባህል ገጽታዎች ዘወትር በቅራኔ የተሞሉ እንደሆኑ ይገልጻል። በተለይ ህብረተሰብ በሽግግር ወቅት በሚገኝበት ጊዜ የማህበራዊ እሴቶች ቅራኔ ጐልቶና ሰልቶ ይስተዋላል። ምስቅልቅል በበዛበት የለውጥ ማዕበል ውስጥ የሚገኝ ባህል ውስጣዊ ሰላም፣ መረጋጋትና ማህበራዊ ደስታ ስለሚጐድሉት መደናበርና ቀቢፀ-ተስፋ ገንነው ይታያሉ። ምንጊዜም ቢሆን ባልዳበረ ባህል ውስጥ የማህበራዊ እሴቶች ግጭት በስፋት ይኖራል። የእርስ በርስ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ዋና ዋና ብሄራዊ ችግሮችን ለመፍታት አለመቻል አበይት መገለጫዎች ናቸው። ኤድዋርድ ሻፒር እንዲህ ያለውን ባህላዊ ሁኔታ ትክክለኛው ወይንም መሰረታዊው ባህላዊ ገጽታ ባለመሆኑ “spurious culture” ይለዋል።

 በአጠቃላይ ባህልን በተመለከተ ፍርድ-መሰል የምዘና አስተያየት መስጠት ቀላል አይደለም፤ ተመራጭም አይደለም። የስነ-ሰብ ምሁራን ብዙ ጊዜ ይህን ከማድረግ የተቆጠቡ ናቸው። በአጋጣሚ አንዳንድ አስተያየቶች በሚሰነዝሩ ጊዜ እንኳ ገለልተኛ መሆንና ተገቢውን አክብሮት መስጠት ይመረጣል ይላሉ።

ከባህል አንፃር የጠባብነትና የአንፃራዊነት ፍልስፍና (Cultural Ethnocentrism & Cultural Relativism)

በስነሰብ የትምህርት ዘርፍ አንድን ባህል በሁሉም መመዘኛ ከሌሎች እጅግ የተሻለ፣ ትክክለኛና የበላይ አድርጐ የመመልከትና ሌሎች ባህሎች ከእርሱ ያነሱ፣ ሰንካሎችና መናኛ እንደሆኑ የመቀበል አስተሳሰብ “ኤትኖሴንትሪዝም” ወይንም ጠባብነት ተብሎ ይታወቃል። ይህ አስተሳሰብ ሰዎች ራሳቸውን በውል ከሚያውቁት ጉዳይ ጋር የማዛመድ፣ ለማያውቁትና ምናልባትም በጥርጣሬ ለሚመለከቱት ጀርባን የመስጠት ዓይነት ተደርጐ ሊወሰድ ይችል ይሆናል።

በሌላ አነጋገር “ኤትኖሴንትሪዝም” የራስን ባህላዊ እምነት፣ እሴትና ስነምግባር በጭፍኑ የመቀበልና የሌሎችን አዛብቶና አጥላልቶ መመልከት ማለት ነው።

አንዳንድ የስነ-ሰብ ምሁራን ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› አደገኛና አደገኛ ያልሆነ ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ሁለት ባህርያት እንዳሉት ይናገራሉ። የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› አደገኛ ያልሆነ ባህርይ ከባህል አንፃር ሰፋ አድርጐ መመልከት ባለመቻል ይገለጻል። ቢድኒ የተባለ ጸሐፊ እንደሚለው ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› በተወሰነ ደረጃ በሁሉም ህብረተሰብና ባህል ውስጥ አለ። ይህንን አባባል ኸርስኮቪትዝ ተቀብሎ የበለጠ ሲያብራራው ‹‹የጽሑፍ ባህል በሌላቸው ማህበረሰቦች ዘንድ ‹ኤትኖሴንትሪዝም› በተረቱ፣ በትውፊቱ፣ በተረትና ምሳሌው፣ በስነቃሉ፣ በስም አወጣጡ ውስጥ ሁሉ ይስተዋላል›› ይላል። አንዳንድ ጊዜ በእነኚህ ማህበረሰቦች ዘንድ የማህበረሰቡ የወል መጠሪያ ራሱ ‹‹ሰው›› (human being) የሚል ስያሜ ይኖረዋል። ይህም ማለት ከማህበረሰቡ ውጭ የሆነ ሌላ ሰው ሁሉ ከሰብዕና ዝቅ/ወጣ ያለ ነው እንደማለት ይሆናል። ለምሳሌ በብሪቲሽ ኰሎምቢያ ግዛት የሚኖሩት የካስካ ህንዶች ራሳቸውን ‹‹ዲኔ›› ብለው ይጠራሉ። ትርጉሙ ‹‹ሰዎች›› እንደማለት ነው። ካስካዎች በቅርብ የማያውቋቸውን ጐረቤቶቻቸውን ከሰብዓዊ ፍጡር ዝቅ ያሉ አውሬዎችና አደገኞች አድርገው ይቆጥሯቸዋል። በአሪዞና ግዛት የሚኖሩት ሆፒ የተባሉት ህንዶችም ስማቸው ‹‹እንከን-የለሾቹ›› (good in every respect) የሚል ትርጉም ያለው ነው። ስለዚህ በዚህ መልክ የሚገለጸው ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› ማህበራዊ ትውውቅን የሚጋብዝ አይደለም። ጠቅለል ባለ አነጋገር አደገኛ ያልሆነው የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› ባህርይ የአንድን ህብረተሰብ ባህላዊ እሴት በሌላ ህብረተሰብ ላይ ከመጫን የታቀበ፣ ለራስ ባህል የሚኖር ጽኑ እምነት ተደርጐ ሊወሰድ ይቻላል።

 አደገኛ የሆነው የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› ገጽታ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ነፃና እኩል ነው የሚለውን መሰረታዊ ሀቅ የሚጨፈልቅ ነው። ይህ አስተሳሰብ ለአንድ ህብረተሰብ የተለያዩ ግቦች ስኬት ሊረዱ የሚችሉ የሌላ ህብረተሰብ የካበቱ ልምዶችንና እውቀቶችን ከመንቀፍና ካለመቀበል አልፎ የሃሳብ ልውውጥን ሁሉ በግልጽ ይገድባል። መናቆርና የከረረ ጥላቻ መገለጫዎቹ ሲሆኑ የዘር መድልዖ፣ ፋሺዝም፣ ናትሲዝም፣ አፓርታይድ፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በዘመናችን የተከሰቱ አደገኛ የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› ምሳሌዎች ናቸው።

 የ‹‹ኤትኖሴንትሪዝም›› ተቃራኒ ‹‹ሪሌቲቪዝም›› ወይንም አንፃራዊነት ነው። በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አሰርት ሰፊ ተቀባይነትን አግኝቶ የነበረ አከራካራ አስተሳሰብ (doctrine) ሲሆን እስከ 1930ዎቹ እና 40ዎቹ ድረስ ብዙም ሳይዳብር ቆይቷል። በባህል ረገድ አንፃራዊ አስተሳሰብን ዳግም አንቀሳቅሰው ጉልህ አስተዎጽዖ ያበረከቱት አሜሪካዊው የስነሰብ ተመራማሪ ሜልቪል ኸርስኮቪትዝ እና ደቀመዝሙሩ ኤርንስት ካሲረር ናቸው። ይህ አስተሳሰብ ‹‹ባህልን በተመለከተ የማህበራዊ እሴቶች ባህርይና ሚና ምንድነው?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚረዳ እንደሆነ ኸርስኮቪትዝ አበክሮ ያስገነዝባል። የአስተሳሰቡ መሰረታዊ መርህ ባህልን በሚመለከት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች መነሻቸው ባህላዊ ልምድ ሲሆን፣ ባህላዊ ልምድ ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ባለው የባህል ግንዛቤ (enculturation) መሰረት በሚያቀርበው ትንታኔ የሚገለጽ ይሆናል የሚል ነው። ለምሳሌ ለተፈጥሮ አካባቢ፣ ለጊዜ፣ ለርቀት፣ ለክብደት፣ ለመጠን፣ ወዘተ ያለ ግንዛቤ እንደየባህሉና እንደየግለሰቡ ባህላዊ እውቀት የተለያየ ነው።

 በአጠቃላይ አንፃራዊነት ባህልን ከተመልካቹ ወይንም ከተመራማሪው አንፃር ሳይሆን ከባህሉ ባለቤት አንፃር ለመረዳት የሚያስችል ዘዴ ነው። በስነሰብ ትምህርት ይህ ዓይነቱ ዘዴ (emic approach) ተብሎ ይታወቃል። ይህ ዘዴ በባህል መስክ የሚደረጉ ጥናቶች በተቻለ መጠን ነባራዊ ወይንም ተአማኒ/‹‹ኦብጀክቲቭ›› እንዲሆኑ ይረዳል። በተጨማሪም ‹‹ሪሌቲቪዝም›› ወይንም አንፃራዊነት ባህላዊ እውነታንና ፍልስፍናውን ለመመርመር የሚረዳ ንድፈ-ሃሳብ፣ የእሴት ስርዓትን ለመገምገም የሚጠቅም መርህ፣ እንዲሁም ለማህበራዊና ባህላዊ ለውጦች የሚሰጥ አመለካከት እንደሆነ በርከት ያሉ ምሁራን ይስማሙበታል።

 ስለ የባህል ለውጥ አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦች

በትውልድ ፖላንዳዊ፣ በዜግነት እንግሊዛዊ የሆነውና ታዋቂው የስ-ነሰብ ሊቅ፣ ብሮኒስካው ማሊኖውስኪ፣ የባህል ለውጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደምሳሳው ሲገልጽ ‹‹አንድ ማህበረሰብ ከአንድ ዓይነት የኑሮ ዘይቤ ወደ ሌላ የሚያደርገው ሽግግር ሂደት ነው›› ይላል። ይህም ሂደት ሁሉ አቀፍ በመሆኑ የህብረተሰቡን ማህበራዊ፣ አዕምሯዊና ቁሳዊ ውጤቶች መዳሰሱ የማይቀር ነው። በመሰረቱ የለውጥ ሂደት ከባህል አበይት ባህርያት አንዱና ሁሉም ቦታ ሁልጊዜ የሚኖር የወል ክስተት ነው። በለውጥ ሂደት ያልታጀበ የሰው ልጅ የስልጣኔ ታሪክ የለም። በመሆኑም ለውጥ የስልጣኔ ቋሚ ባህርይ ነው። ይሁን እንጂ የባህል ለውጥ ጥናት ከተቃራኒው ማለትም ከባህል ወግአጥባቂነት (cultural relativism) ጋር ተነጻጽሮ ካልቀረበ በስተቀር ይህ ነው የሚባል ፋይዳ አይኖረውም።

 የባህል ለውጥን በስፋትና በውስን መልክ (በ‹‹ማክሮ›› እና በ‹‹ማይክሮ›› ደረጃ) ማጥናት እንደሚቻል አንዳንድ የስነ-ሰብ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሁለቱ የጥናት ዘዴዎች መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት የጊዜ ርዝማኔ ነው። በሰፊው ወይንም በ‹‹ማክሮ›› ደረጃ የሚደረገው የባህል ለውጥ ጥናት ረዥም ጊዜን የሚሸፍን ሲሆን በአነስተኛ ወይንም በ‹‹ማይክሮ›› ደረጃ የሚደረገው ጥናት ደግሞ ጥቂት ዓመታትን የሚሸፍን ነው። በማህበራዊና ባህላዊ ስርዓት ውስጥ ወይንም በግለሰብ ባህርይ ላይ ዘለግ ላሉ ዓመታት በተከታታይ የተስተዋሉ ለውጦችን እያነጻጸሩና እያወዳደሩ የማጥናት ዘዴ በግልጽ የሚታወቁ ተጨባጭ ጉዳዮችን ከመለየት ባሻገር በስርዓት የተቀመሩ የቲዮሪ/ የትወራ ሃሳቦችን ለማፍለቅም ይረዳል።

 የባህል ለውጥን የሚያስከትሉ ምክንያቶች ብዙና የተለያዩ ብቻ ሳይሆኑ ውስብስብም ናቸው። ምክንያቶቹን እንደየክብደታቸው በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ያሉት መረጃዎች በቂ ባይሆኑም የተለያዩ ጸሀፊዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያና ግዝፈት እንደሚሰጡ ግን መጥቀስ ይቻላል። በመሰረታዊነት በሦስት አበይት ምክንያቶች የባህል ለውጥ ሊከሰት እንደሚችል ይታመናል። አንደኛው ምክንያት የተፈጥሮ አካባቢ ለውጥ ሲሆን በዚህ ሳቢያ የሚመጣው አዲስ የኑሮ ዘይቤ ያለጥርጥር የባህል ለውጥን ያስከትላል። የተፈጥሮ አካባቢ ለውጥ አዝጋሚ አሊያም ድንገተኛና መጠነ- ሰፊ በሆኑ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች የሚመጣ ነው። የተፋሰሶች መራቆት፣ የደን ውድመት፣ የህዝቦች ፍልሰት፣ ወዘተ በዚህ አግባብ ሊታዩ የሚችሉ ምሳሌዎች ናቸው። ሁለተኛው ዓይነት የባህል ለውጥ በሁለት የተለያዩ ማህበረሰቦች ግንኙነት ሳቢያ የሚፈጠረው ነው። ማሊኖውስኪ እንደሚለው የማህበረሰቦች ግንኙነት ምንጊዜም ቢሆን የባህል ለውጥ መቅድም ነው። በዚህ መልክ የሚከሰት የባህል ለውጥ ፈርጀ ብዙ እንደሆነ በርካታ አብነቶች አሉ። ሦስተኛው ዓይነት የባህል ለውጥ ያለውጪያዊ ተጽእኖ በማህበረሰቡ በራሱ ውስጣዊ መስተጋብር በአዝጋሚ ሂደት የሚከሰት ሲሆን ይህ ዓይነቱ ባህላዊ ለውጥ የዘመናት ክንውን ውጤት በመሆኑ በባህርይው ስርዓታዊ (orderly) እና ተዛማጅ/ ስምሙ (adaptive) ነው። በእንዲህ ዓይነት ሂደት የሚመጣ የባህል ለውጥ የሚመነጨው ከመኖርና ካለመኖር መሰረታዊ ጥያቄ በመሆኑ ለጥያቄው የሚሰጠው መልስ ለውጡን በመቀበልና ባለመቀበል ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top