ታሪክ እና ባሕል

ባህል- ዋና ዋና ባህርያቱና ማህበረሰባዊ ፋይዳው

‹‹አከልቸሬሽን›› በባህል መስክ ከሚከሰት የለውጥ ሂደት እንደ አንድ አብነት የሚቆጠረው ዘይቤ ‹‹አከልቸሬሽን›› ተብሎ ይታወቃል:: ይህን ቃል አዘውትረው የሚጠቀሙት አሜሪካውያን አንትሮፖሎጂስቶች ሲሆኑ እንግሊዛውያን አቻዎቻቸው የባህል ግንኙነት (cultural contact) የሚለውን ይመርጣሉ:: ያም ሆነ ይህ በሁለት የተለያየ ባህል ባላቸው ማህበረሰቦች ወይንም የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ዘለግ ላሉ ተከታታይ ዓመታት በግንባር በሚደረግ ግንኙነት (first-hand contact) ሳቢያ በአንዱ ወይንም በሁለቱም ማህበረሰቦች ባህላዊ ዘርፎች ውስጥ ለውጦች መከሰታቸው አይቀርም::

 በባህል መወራረስ የተነሳ የሚከሰቱ የባህል ለውጦችን የማጥናቱ ጉዳይ ገንኖ የነበረው በ1930ዎቹ ነበር:: የጥናቱ መሪዎች ሜልቪል ኸርስኮቪትዝ፣ ራልፍ ሊንተን፣ ሮበርት ሬድፊልድ የተባሉት አሜሪካውያን አንትሮፖሎጂስቶችና የእነርሱ ደቀመዛሙርት የነበሩ ሌሎች ተመራማሪዎች ነበሩ:: እነኚህ ምሁራን ባካሄዷቸው ጥናቶች ውስጥ በሂደት የታዩ አንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹አከልቸሬሽን›› በሁለት የተለያዩ ህዝቦች መካከል በተፈጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ሳቢያ የሚከሰት የባህል ለውጥ ነው በማለት በአጭሩ ገልጸውታል:: በተለይ የዚህ ትርጓሜ መሪ አቀንቃኝ ኸርስኮቪትዝ ነበር:: እንደ እርሱ አስተሳሰብ የሁለቱ ህዝቦች የግንኙነት ባህርይና አግባብ፣ የባህላዊ መወራረሱ ስፋትና ውሱንነት እንዲሁም በባህላዊ እሴቶች ላይ የሚያስከትሉት ውጤት በ‹‹አከልቸሬሽን›› ሂደት ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አይደሉም::

በ‹‹አከልቸሬሽን›› መስክ የሚደረጉ ጥናቶች በሚከተሉት ሦስት የባህል ለውጥ ሂደት ውጤቶች ላይ የሚያተኩሩ ይሆናሉ::

አንደኛው በአሮጌውና በአዲሱ ባህል ውህደትና ይህን ተከትሎ በሚፈጠረው አዲስ ውሁድ ባህል ላይ ሲሆን፣

 ሁለተኛው ከአዲሱ የባህል ክፍሎች ውስጥ ከቀድሞው ባህል ጋር ተጣጥመው ሳይዋሃዱ በመቅረታቸው ገለል በተደረጉ የባህል ክፍሎች ላይ ነው::

 ሦስተኛው የአዲሱንና የአሮጌውን ባህል ግጭት ተከትለው በመጡት ለውጦች ሳቢያ በተከሰቱ እንግዳ ባህርያትና ራስን ከተለወጠው ሁኔታ ጋር ለማስተካከል በሚወሰዱ እርምጃዎች ሂደትና ውጤት ላይ ነው::

 በማህበረሰቦች ግንኙነት ወቅት የግንኙነቱን አግባቦች አስቀድሞ ለይቶ መተንበይ ቢያስቸግርም በለውጥ ሂደት አራት ዓይነት የግንኙነት ውጤቶች እንደሚስተዋሉ ይታመናል:: እነዚህም፡-

ከአዲሱ ባህል የተወሰኑትን መቀበል፣ ከአዲሱ ባህል የተወሰኑትን መጣል (ያለመቀበል)፣ ከቀድሞው ባህል የተወሰኑትን አጥብቆ መያዝ፣ ከቀድሞው ባህል የተወሰኑትን መጣል ናቸው:: ከፍ ሲል ከተጠቀሱት አራት ነጥቦች የምንረዳው በማህበረሰቦች ግንኙነት የ‹‹አከልቸሬሽን›› ሂደት ምርጫ፣ ውህደትና ለውጦችን ከነባርና ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የማጣጣም/የማዛመድ ክህሎት የሚስተዋልበት መሆኑን ነው:: በመሆኑም ከ‹‹አከልቸሬሽን›› ውጤቶች አንዷን ሰበዝ መዝዞ ምንጯ የት እንደነበር ለማወቅ መሞከር አንድም አሳሳች፤ አሊያም የማይቻል ነው::

 ግኝት፣ ፈጠራና ፈጠራን ማዳበር (Discovery, Invention & Innovation)

ግኝት፣ ፈጠራና ፈጠራን የማዳበር ክንዋኔዎች የባህል ለውጥ ሂደት አበይት ምሳሌዎችና ውስጣዊ ነፀብራቆች ናቸው:: በሦስቱ ክንዋኔዎች መካከል ቴክኒካዊ የትርጉም ልዩነት አለ:: ለምሳሌ ግኝት ቀደም ሲል በውል ያልታወቀን ወይንም ያልተስተዋለን ነገር ድንገት ወይንም ሆን ብሎ አስቦ የማግኘት፣ የማወቅና የመገንዘብ ጉዳይ ነው:: ፈጠራ ደግሞ ፍጹም አዲስ የሆነን ነገር ስራዬ ብሎ የመፍጠር ወይንም የመፈልሰፍ ተግባር ነው:: የግኝትም ይሁን የፈጠራ ውጤቶች በድንገትና በዋዛ-ፈዛዛ መሃል የሚከሰቱ ሊሆኑ ይችላሉ:: አንዳንድ ጊዜ ግን የብዙ ዘመን ተሞክሮዎች (antecedents) ድምር ውጤቶች ሆነው ይገኛሉ::

በሌላ በኩል ደግሞ ፈጠራን የማዳበር ተግባርን የወሰድን እንደሆነ ከፍ ሲል ከጠቀስናቸው ሁለት ክንዋኔዎች የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን:: በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተፈለሰፈን አዲስ ነገር ለሌላ ህብረተሰብ በሚጠቅም መልኩ የማዛመድ ተግባር ፈጠራን ማዳበር ተብሎ ሊወሰድ ይቻላል:: በዚህ ባህርይው ፈጠራን የማዳበር ተግባር ጥንቃቄ የተሞላበት ምርጫ የሚስተዋልበት ባህላዊ-ስነልቦናዊ እርምጃ ነው:: ስለዚህ ፈጠራን የሚያሻሽል ወይንም የሚያዳብር ሰው የሚከውነው ተግባር የማዛመድ ስራ ነው ማለት ነው:: ባለሙያው ችግሮችን ተረድቶና ለይቶ፣ ለመፍትሄ የሚረዱ አማራጮችን ከመዘነ በኋላ ከሚኖርበት ነባራዊና ባህላዊ ሁኔታ አፈንግጦ ሳይወጣ ለራሱ በገባው መንገድ እርምጃዎችን ይወስዳል:: ስለዚህ ፈጠራን የሚያዳብር ባለሙያ ከአንድ ማህበረሰብ የተወሰዱ ግኝቶችን ለሌላ ማህበረሰብ ይጠቅሙ ዘንድ ትርጉምና ተቀባይነት ባለው መንገድ እያለዘበ በማዋሃድ የለውጥ ሂደትን እንደሚያፋጥን ሞተር ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው::

በመሰረቱ በባህል መስክ የሚከሰት የለውጥ ሂደት ስኬት የሚኖረው የማህበረሰቡን ስርዓታዊ ወይንም ተዋረዳዊ መዋቅር (hierarchical order) ክፉኛ የማያዛባና መሰረታዊ ከሆኑ

ማህበራዊ እሴቶች ጋር የማይጣረስ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው:: ሆኒግማን በዚህ መሰረታዊ ነጥብ ላይ ‹‹ሰርቶ የማሳየትን ስልት›› (demonstration) ያክልበታል:: ሰርቶ የማሳየት ስልት አዳዲስ ግኝቶችን፣ ፈጠራዎችንና የተሻሻሉ የፈጠራ ውጤቶችን የማቀበልና የመቀበል ወይንም የመቀባበል ተግባራዊ ሂደት በመሆኑ በአዲሱ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ምን ማድረግ እንደሚቻልና እንደማይቻል ፍንትው አድርጐ ለማሳየት ይረዳል:: ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በመምህራንና በግብርና የኤክስቴንሽን ሰራተኞች እለታዊ ስራ ውስጥ ሰርክ የሚስተዋል ክስተት ነው::

ይሁን እንጂ ግኝቶችም ሆኑ የፈጠራ ውጤቶች ሁኔታዎች ሲፈቅዱ እንጂ እንደተገኙ ወዲያውኑ ለአገልግሎት ላይበቁ ይችላሉ:: በዚህ ረገድ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል:: ለምሳሌ የዘረመልን ጥናትን (genetics) መሰረታዊ መርሆዎች በመልካም ሁኔታ አቀናብሮ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳቀረበ የሚነገርለት ኦስትሪያዊው መነኩሴ ግሪጐር ሜንድል፣ የድካሙ ውጤት በስፋት ተቀባይነትን ከማግኘቱ በፊት በአንድ እጅግም በማይታወቅ የምርምር መጽሄት ላይ ከታተመ በኋላ ማንም ከጉዳይ ሳይቆጥረው ለበርካታ ዓመታት ቆይቷል:: ዲዲቲ የተቀመመው በ1890 አካባቢ ሲሆን ለተባይ ማጥፊያነት አገልግሎት ላይ የዋለው ግን ከ65 ዓመታት በኋላ ነበር:: የጥንት ግሪኮች በእንፋሎት ስለሚሰራ ሞተር እውቀቱ ነበራቸው፤ ነገር ግን የግሪክ ባህል ትኩረቱ ለማሽን ሳይሆን ለሰው ልጅ ስለነበር የተጠቀሙበት ለአሻንጉሊት ስራ ብቻ ነበር:: በሌላ በኩል ግን ጃምስ ዋት የተባለው እንግሊዛዊ በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የእንፋሎት ሞተርን ለፋብሪካና ለመጓጓዣ በሚውል መልኩ አስተካክሎ ባቀረበ ጊዜ በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች 17 ዓይነት ሌሎች ተመሳሳይ የፈጠራ ውጤቶች ለገበያ ቀርበው ነበር:: ሁኔታው ለባለሃብቶችም፣ ለፈጠራ ባለሙያዎችም እጅግ ምቹ እንደነበር ለመረዳት ይቻላል::

የባህል መዋዋጥ (Cultural Assimilation)

የተለያየ ባህል ያላቸው የተለያዩ ግለሰቦች ወይንም የግለሰቦች ስብስቦች በረዥም ዘመን መስተጋብር አንድ ላይ በመዋሃድ አዲስና የጋራ የሆነ የባህል ውሁድ የሚፈጥሩበት ሂደት መዋዋጥ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል:: በተመሳሳይ መልኩ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ‹‹ካልቸሮሎጂስትስ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቁና በባህል ጥናት ላይ በይበልጥ የሚያተኩሩ አንትሮፖሎጂስቶች የአንድ ባህል ልዩ ልዩ ክፍሎች በሌላ ባህል ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሰርጸው የሚገኙበት፣ ወይንም አንድ ማህበረሰብ ከሌላ ማህበረሰብ ጋር ባህላዊም ማህበራዊም በሆነ መልኩ ተዋህዶ የሚገኝበት ሁኔታ ባህላዊ መዋዋጥ ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ይስማሙበታል:: በተለይ የኋለኛው ዓይነት ሁኔታ ጦረኝነትና ወረራ የህብረተሰቡ ዋና የኑሮ ዘይቤ በነበረበት የሰው ልጅ ማህበራዊ የእድገት ደረጃ ወቅት ተደጋጋሚ ክስተት ነበር:: በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ አንትሮፖሎጂስቶች ‹‹አሲሚሌሽን›› አንድዮሽና ሁለትዮሽ ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ሁለት ባህርያት ሊኖሩት እንደሚችሉ ይናገራሉ:: የመጀመሪያው ባህርይ አንድ ግለሰብ ወይንም የግለሰቦች ስብስብ የሌላ ማህበረሰብን ባህል ወርሶና ማንነቱን ተላብሶ ፍፁም የዚያ ማህበረሰብ አባል የሚሆንበት ሂደት ሲሆን የሁለትዮሽ ባህርይው በሁለት የተለያዩ ማህበረሰቦች ባህላዊ ውህደት የሚገለጽ ነው:: በዚህ ምክንያት አንዳንድ ሊቃውንት ‹‹አሲሚሌሽን›› የግድ ሙሉ ለሙሉ መዋዋጥን የማይጠይቅና በባህላዊ ግንኙነት ምክንያት የተወራረሱት አዳዲስ የባህል እሴቶች ከነባሩ የባህል መዋቅርና ክንዋኔ ጋር ተጣጥመው የሚቀጥሉበት ክስተት ነው በማለት ይከራከራሉ:: ከዚህ አንፃር ሲታይ ከጥቂት ቴክኒካዊ ልዩነቶች በስተቀር ‹‹አሲሚሌሽን›› ከ ‹‹አከልቸሬሽን›› ብዙም የተለየ ሆኖ አናገኘውም:: በአጠቃላይ የ‹‹አሲሚሌሽንን›› ሂደት በሚቀጥለው ስዕላዊ ሞዴል ማስቀመጥ ይቻላል::

የባህል ስርጸት (Cultural Diffusion)

በስነሰብ የትምህርት መስክ አንድ ግኝት ወይንም የፈጠራ ውጤት የግኝቱ ወይንም የፈጠራ ውጤት ባለቤት ከሆነው ህብረተሰብ አልፎ ወደ ሌላ ህብረተሰብ የመዳረሱ ሂደት ስርጸት ተብሎ ይታወቃል:: የባህል ስርጸት በተደራጀ ዘይቤ መጠናት የጀመረው ባህልን በሚመለከት አዝጋሚ የለውጥ ሂደት ንድፈ ሃሳብ (evolutionary theory) ጠቀሜታ እየቀነሰ ከመጣበት የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ወዲህ ነው::

 የስርጸት ሂደት መልኩ ብዙ ነው:: ለምሳሌ ዊስለር የተባለ አንትሮፖሎጂስት ‹‹ተፈጥሮአዊ›› (natural) እና ‹‹የተደራጀ›› (organized) የሚባሉ ሁለት የባህል ስርጸት ዓይነቶች እንዳሉ ይገልጻል:: ተፈጥሮአዊ የሚባለው የባህል ስርጸት በአጋጣሚ ግንኙነትና በበጐ ፈቃድ ምርጫ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የተደራጀ የባህል ስርጸት ግን ሆን ተብሎ ታስቦበትና ተዘክሮበት እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የአስገዳጅ ሁኔታዎች ግፊት ታክሎበት የሚከናወን ነው:: አሜሪካዊው አንትሮፖሎጂስት ኘ/ር ክሮበር ደግሞ የባህል ስርጸት በማህበረሰቦች የቀጥታ ግንኙነትና ይህም በማይሆን ጊዜ በሃሳብ ስርገት በሚፈጠር አንድን ነገር የመፈልሰፍ ግፊት ሊከሰት እንደሚችል ይገልጽና እንዲህ ዓይነቶቹን የባህል ስርጸት ክንዋኔዎች እንደየ ቅደምተከተላቸው የግንኙነት ስርጸት (contact diffusion) የግፊት ወይንም የሃሳብ ስርጸት (stimulus or idea diffusion) ብሎ ይጠራቸዋል:: ኪሲንግ የተባለው ሌላው አሜሪካዊ የስነሰብ ሊቅ ደግሞ ተቃርኗዊ ስርጸት (antagonistic diffusion) እና የተገታ/ግት ስርጸት (controlled diffusion) የተሰኙ ሁለት የስርጸት ዓይነቶችን ይለይና ባላንጣ በሆኑ ሁለት ማህበረሰቦች መካከል የሚከናወነውን የባህል እሴቶች ልውውጥ ተቃርኖአዊ ስርጸት ይለዋል:: የባህል ውጤቶችን ተቀባይ በሆነው ህብረተሰብ ዘንድ ለአቀባበሉ የምርጫ መርሆ ሲኖርና ሁኔታውም በዚሁ መልክ ሲከናወን ክንውኑን ግት ስርጸት በማለት ይጠራዋል::

ከጊዜ አንፃር የባህል እሴቶች ስርጸት ተመሳሳይ ፍጥነት የለውም:: አንዳንዶቹ ከሌሎቹ ፈጥነው ሊሰራጩና ሊሰርጹ ይችላሉ:: ለምሳሌ ከሃሳብ ወይንም ከአስተሳሰብ ይልቅ የቁሳቁስ ወይንም የማቴሪያል ውጤቶች ፈጥነው ይሰርጻሉ:: ለፈጣን የሃሳብ ስርጸት ዋናው እንቅፋት የቋንቋ ጉዳይ ነው::

 አዳዲስ አስተሳሰቦች ጸንተው የነበሩ የእሴት ስርዓቶችን ክፉኛ ስለሚፈታተኑ የባህል እሴት ስርገትንና ተከትሎ የሚመጣውን ለውጥ አዝጋሚ እንዲሆን ያደርጉታል:: ይሁን እንጂ በባህል ላይ የሚደረግ ድንገተኛ ለውጥ (spurt) በማህበረሰብ የኑሮ ዘይቤ ላይ የዛኑ ያህል ድንገተኛ ለውጥን ያስከትላል:: በሰው ልጅ የእድገት ታሪክ ውስጥ በዚህ አግባብ ሊጠቀስ ከሚችለው ድንገተኛና ግዙፍ የባህል ለውጥ አንዱ የእርሻ ስራ መጀመር ነው:: የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልገውን ምግብ ማምረት በመጀመሩ በመንደር ተሰባስቦና ተረጋግቶ የመኖር ባህልና ጉልህ የሆነ ማህበራዊ የስራ ክፍፍል ከመከሰቱ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቁጥር መጨመርም ታይቷል:: ለዚህም ይመስላል ክሉኮን የተባለው አንትሮፖሎጂስት ንጽጽራዊ በሆነ አገላለጽ ‹‹ተፈጥሮአዊና ድንገተኛ የሆነ የዘረመን ለውጥ (mutation) ለስነ ህይወት ተመራማሪው ሰፊ የምርምር መስክ እንደሆነ ሁሉ የእርሻ ስራ መጀመርና ተከትለው የታዩት ለውጦችም ለአንትሮፖሎጂስቱ የዛኑ ያህል ሰፊ የጥናት መስኮች ናቸው›› ያለው::

 የስርጸት ፍጥነት የተለያየ እንደሆነ ሁሉ የስርጭቱ መንገድም ተመሳሳይ አይደለም:: ዲክሰን የባህል ስርጸት ሂደትን ከሰደድ እሳት ጋር ያነጻጽረዋል:: እንደሚታወቀው የሰደድ እሳት ከመነሻው ጀምሮ በእኩል ሁኔታ አይሰራጭም:: የነፋሱ አቅጣጫ፣ የአካባቢው እርጥበት ወይንም ድርቀት፣ የውሃ መኖር ወይንም አለመኖርና ሌሎች ነገሮች የእሳቱን መዛመት ወይ ሊያፋጥኑ አሊያም ሊያዳክሙ ይችላሉ:: በመሆኑም የሰደድ እሳት በሚዛመት ጊዜ አንድን አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ውድም አድርጐ፣ የተወሰነ አካባቢን ይዘልና ደግሞ የሚቀጥለውን አካባቢ ሊያወድም ይችላል:: በተመሳሳይ መልኩ የባህል እሴቶች ስርጸትም በሁሉም ስፍራ የተስተካከለ ሊሆን አይችልም:: ለምሳሌ የባህር መስመርን ተከትሎ የሚከሰት የባህል እሴት ስርገት አብዛኛውን ጊዜ ተከታታይነት የሚጐድለው ወይንም የተቆራረጠ እንደሚሆን ይገመታል:: በሌላ በኩል ደግሞ የሁለት ባህሎች ግንኙነት በግለሰብ ወይንም በመጽሃፍ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የሚተላለፉት የባህል ክፍሎች (cultural elements) ተጠይቃዊ ትስስር (logical relations) ያላቸው ስብስቦች (ለምሳሌ ፈረስ፣ ኮርቻ፣ ልጓም፣ እርካብ፣ መኮርኮሪያ፣ ወዘተ) ይሆናሉ::

 በአጠቃለይ ስርጸት (ዲፊዩዥን) የመዋዋስ ባህርይ ጐልቶ የሚታይበት የባህል ለውጥ ሂደት አንድ ፈርጅ ነው:: እንዲያውም አንዳንዱ ባህል ከራሱ አንጡራ የባህል ውጤቶች ይልቅ ከውጭ ያገኛቸው በርከት ብለው የሚታዩበት ሁኔታ የተለመደ ከሆነ ቆይቷል:: ራልፍ ሊንተን እንደሚለው ከአንድ ማህበረሰብ የማቴሪያል ንብረቶች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ አንጡራ ባህላዊ ሃብቱ ናቸው:: የሰው ልጅ በተፈጥሮው ጊዜ ወስዶ፣ አውጥቶና አውርዶ አዲስ ነገርን ከመፍጠር ይልቅ ሌላው የፈለሰፈውን ለቀም አድርጐ ጥቅም ላይ ማዋል ቀላል መሆኑን የሚረዳ ነውና ጊዜ እያለፈ፣ አለምም እየዘመነ በሚመጣ ጊዜ የመቶኛው ስሌት በእጅጉ እያነሰ እንደሚሄድ እሙን ነው::

 ልማት

የልማት ጽንሰ ሃሳብ ፈርጀ ብዙ ገጽታዎችን ያካተተና መገለጫዎቹም የዚያኑ ያህል በርካታ የሆኑ ናቸው:: ኢኮኖሚያዊ በሆነው ትንታኔ ከልማት መለኪያዎች አንዱ የነፍስ ወከፍ ገቢ የሚባለው ነው:: የአንድ ሀገር ጠቅላላ ምርት ለሀገሩ ህዝብ ተካፍሎ የሚገኘው አሃዝ የነፍስ ወከፍ ገቢ ይባላል:: የነፍስ ወከፍ ገቢ የሀገር ኢኮኖሚ ምርታማነት ነፀብራቅ ነው:: የኢኮኖሚ ብልጽግናን ከሚያመለክቱ ሌሎች ተጨማሪ መለኪያዎች መካከል የዜጐች አማካይ የህይወት ዘመን፣ የሞት፣ የወሊድና የህዝብ ቁጥር እድገት መጠን ዋና ዋናዎቹ ናቸው:: በአንድ ሀገር የሚከናወኑት የተለያዩ የምርት እንቅስቃሴዎች ምርታማነት፣ የተማረ የሰው ሃይል ስርጭትና የትምህርት ደረጃ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የውሃና የሌሎች መሰረተ ልማቶች አቅርቦት፣ የአካባቢ ንጽህና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸውን የኢኮኖሚ ልማት መለኪያዎች እውን ለማድረግ የሚረዱ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው:: የእነኚህ ድምር ውጤት በልማት ደረጃ አንድ የሆነ እርከን ላይ ሊቀመጥ የሚችል የኑሮ ዘይቤን (pattern of life) መፍጠር ነው::

 ከአንድ ሀገር ህዝብ ውስጥ በአብዛኛው ዘንድ የተሻሻለ የኑሮ ደረጃ፣ የተሻለ ምግብና የአመጋገብ ስርዓት፣ ጤናማ አካል፣ የጸዳ መኖሪያና አካባቢ እንዲኖርና ከበሽታ ነጻ የሆነ ህይወት ለመምራት ከፍተኛ ፍላጐት ሲኖር ብልጽግናን እውን ለማድረግ የሚያስፈልጉ ህሊናዊ ሁኔታዎች ተሟልተዋል ተብሎ ይታመናል:: ይሁን እንጂ የህሊናዊ ሁኔታዎች መሟላት ብቻ በቂ አይደለም:: በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚፈለገውን ዓይነት የተሻሻለ የኑሮ ዘይቤ ለመምራት የሚያስችል እውቀትና ሃብት መኖር አለበት::

አሌክስ ኢንክልስ እና ዴቪድ ስሚዝ የተባሉ ተመራማሪዎች በመልማት ላይ ያሉ ስድስት ሀገሮችን በናሙና ወስደው ባደረጉት ጥናት በሰው ዘንድ ዘመናዊ አስተሳሰብን ብሎም የኢኮኖሚ ልማትን እውን በማድረግ ረገድ ትምህርት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በአጽንዖት ገልጸዋል:: እንደነርሱ አስተያየት ፈጣን፣ ውጤታማና ዘላቂነት ያለው ልማት የሚረጋገጠው በአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የዘመናዊ ሰው አስተሳሰብ በስፋት ሲሰርጽ ነው:: የተስተካከለ የግል ህይወትና ሰብዕና (personal efficiency)፣ ለወቅታዊ መረጃዎች ባዕድ ያልሆነ፣ ከተለምዷዊ ተጽዕኖዎች ነፃ የሆነ፣ ነገሮችን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ክፍት አዕምሮ ያለውና ግትር ያልሆነ፣ ንቁ፣ ተሳታፊ ዜጋ ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው::

“የኢኮኖሚ ብልጽግናንከሚያመለክቱ ሌሎችተጨማሪ መለኪያዎችመካከል የዜጐች አማካይየህይወት ዘመን፣ የሞት፣የወሊድና የህዝብ ቁጥርእድገት መጠን ዋና ዋናዎቹናቸው”

በሌላ አነጋገር የልማት ዋናው ትርጉምና መለኪያ በአመለካከትና በልማድ ለውጥ የታጀበ ሰብዓዊ ልማት ነው:: ከአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ያልተዛመደ የነገሮች ወይንም የሁኔታዎች ለውጥ ልማት ሊሰኝ አይችልም:: ልማት የእውቀት፣ የአመለካከትና የአፈጻጸም ለውጥ የማያቋርጥ ሂደት ነው:: ይህን እውን የማያደርግ ልማት ትርጉም የለውም::

 ከፍ ሲል የጠቀስነው ዓይነት ሰብዓዊ ልማት የሚረጋገጠው በሰዎች በራሳቸው ነው:: ታዋቂው የታንዛኒያ ኘሬዝዳንት፣ ጁልየስ ኔሬሬ፣ እንዳሉት አንድ ሰው ለሌሎች ሰዎች ቤት ወይንም ሌላ ነገር ገንብቶ ሊሰጥ ይችላል፤ ነገር ግን ያ ሰው በእነኛ ሰዎች ውስጥ ክብርን፣ ኩራትንና በራስ የመተማመን ስሜትን ሊፈጥር አይችልም:: እነኚህ ባህርያት በሰዎቹ በራሳቸው ብቻ እውን የሚሆኑ ናቸው:: ሰው ራሱን ማልማት የሚችለው ባለው እውቀትና ችሎታ በማህበረሰብ ህይወት ውስጥ እኩል ተሳታፊ ሲሆን ነው::

 በጥቅሉ ልማት የአንድን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና ያንን የተሻሻለ የኑሮ ሁኔታ መልሶ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚኖር ዘላቂ ችሎታ ነው:: ይህን በመሰለ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ህይወቱን ለመምራት የቻለና ከድህነት የተላቀቀ ነው:: ስለዚህ ልማት የህዝብን ሁለንተናዊ ህይወትና የሚገኝበትን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ከባቢ ሁሉ የሚመለከት ጉዳይ ነው::

 ባህልና ልማት

ባህል የረዥም ዘመን ማህበራዊ ተሞክሮ በመሆኑ መገለጫዎቹ የሆኑት እሴቶችና የስነምግባር መርሆዎች የማህበረሰቡ አባላት ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ያላቸውን አመለካከት የሚወስኑ እንደሆኑ ቀደም ሲል ለመግለጽ ሞክረናል:: አንዳንድ ሰዎች ከዚህ መሰረታዊ ነጥብ በመነሳት፣ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው፣ በተለያዩ ሀገሮች የሚካሄዱት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጦች መሰረት ውስጥ አንዱ ባህል እንደሆነ የላቲን አሜሪካን ማህበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የጃፓንን፣ የታይዋንንና የቻይናን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በአብነት በመጥቀስ የባህልን ሚና አጉልተው ይናገራሉ:: ጠንካራ ባህላዊ እሴቶችና አመለካከቶች አኩሪ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያፋጥኑ እሙን ነው::

 የኢኮኖሚ ልማት ምርታማነትን፣ ገቢን፣ ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚያካትት በመሆኑ ከሰዎች አመለካከት፣ ማህበራዊ እሴቶችና ሌሎች ነገሮች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው:: ሰዎች በራስ የመተማመን፣ የፈጠራና የተነሳሽነት ስሜት ኖሯቸው ራዕይ ያለው ህይወት እንዲመሩ የዳበረ ባህልና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል::

በአንድ ሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ብልጽግናን ሊያመጡ ስለሚችሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘት የሚረዱ ጠቃሚና ጠቋሚ ሃሳቦችን በግልጽ ለመጨበጥ ባህል እጅግ ከፍ ያለ ድርሻ አለው:: ጠንክሮ የመስራትን፣ በርትቶ የመቆጠብን፣ ደፍሮ ኢንቨስት የማድረግን፣ ለወል ግብ በቅንነት የመተባበርን ስሜት ለማስረጽ የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ባህልና ባህላዊ አስተሳሰብ (tradition) ያላቸው ሚና የሚናቅ አይደለም:: በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ተግባራትንና ውጤቶቻቸውን በመወሰን ረገድ ባህል ያለው ተጽዕኖ ይህን ያህል ገዝፎ ሊታይ የሚችል አይደለም የሚሉ ምሁራን አሉ::

ለልማት አጋዥ የሆኑ አንዳንድ ባህላዊ እሴቶቻችንና ጉድለቶቻቸው

 ለአካባቢያዊና ሌሎች ልዩነቶች ግምት የማይሰጥ ደምሳሳ ድምዳሜ ይሁን እንጂ፣ እንደ አንዳንድ ተመራማሪዎች አስተያየት የኢትዮጵያውያን ባህል ለጦርነትና ጦረኛነት ላቅ ያለ ግምት የሚሰጥና አንዱ አሸናፊ፣ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበትን ሁኔታ የሚቀበል ነው:: እነርሱ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን ተጠራጣሪዎች፣ ምክንያታዊ ላልሆነ አስተሳሰብና አምልኮ ተገዢ የሆኑ፣ ድብቆች፣ የተለየ አስተሳሰብን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁነቱ የሚጐድላቸው፣ ፈታኝ በሆኑ መልካም አጋጣሚዎች ከመጠቀም ይልቅ የነበረው እንደነበረ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ናቸው:: እነኚህ ባህርያት በአመዛኙ ፍፁም ታዛዥነትን በሚሰብኩ የሃይማኖት ተቋማትም ድጋፍ የሚሰጣቸው ናቸው:: የልጆች አስተደደግና የሴቶች ቤተሰባዊ አስተዳደር በፍፁም ትዕዛዝ ተቀባይነት ላይ የተመሰረተና በቤተሰብ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ውሳኔን ለማሳለፍ ዕድል የሚነፍግ ነው:: የማህበረሰቡ አደረጃጀት ለዕደ ጥበብ ክህሎት ተገቢውን ክብርና ማበረታታት ከሚሰጥ ይልቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ትላልቅ ግብዣዎችን በማድረግ ሃብት ለሚያባክኑ ተግባራትና ግለሰቦች ልዩ ግምት የሚሰጥ ሆኖ ይገኛል:: በአጠቃላይ እነኚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያውያን ባህል ውድድርና ፈጠራን የማያበረታታ፣ ለተሳካ የግል ኑሮ የሚረዱ ጥረቶችን፣ አስተሳሰቦችንና ራዕይን የሚያንኳስስ፣ ብሎም ለተሻለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያልተመቸ ነው:: (በአሁኑ ጊዜ ይህ አስተሳሰብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችት የሚሰነዘርበትና ተቀባይነቱም እንደ ቀድሞው እንዳልሆነ ማብራሪያ አያስፈልገውም::)

ይሁን እንጂ ከፍ ሲል ከቀረቡት አስተያየቶች የምንረዳው በባህልና በኢኮኖሚ ልማት መካከል ያለው መስተጋብር ውስብስብና የተለያዩ አስተያየቶችን የሚያጭር መሆኑን ነው:: ለተመጠነ የሃሳብ ልውውጥ ግን የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስቶ መወያያት ይቻላል::

1. አዎንታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ እርምጃዎችን ለማስመዝገብ የሚረዱ ጠቃሚ የባህላችን ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው? እነኚህ ጠቃሚ የባህል ገጽታዎች ምን ያህል በተግባር ውለዋል? ያስገኙትስ ውጤት ምንድን ነው?

2. ጠንካራ ሰራተኝነትን፣ ቅድሚያ ተነሳሽነትን፣ ፈጠራንና ውድድርን የሚያበረታቱት ባህላዊ ተግባራት የትኞቹ ናቸው? እነኚህ ተግባራት እንዲሻሻሉ የሚያደርገው ማን ነው? እንዴትስ ይሻሻላሉ?

3. ከህብረተሰቡ አብዛኛው ክፍል ባህል በኢኮኖሚ ልማት ላይ ስላለው አንድምታ ምን ያህል ተረድቷል? ይህንን ነጥብ አጉልቶ በማስረዳት ረገድ መስራት የሚገባቸው ተቋማት የትኞቹ ናቸው? ለልማት አጋዥ የሆኑ ባህላዊ ተግባራትን በመደገፍና በማስፋፋት በኩል የመንግስት በተለይም የሚዲያው ሚና ምን መሆን ይኖርበታል?

 እነኚህ ጥያቄዎች በባህልና በልማት መካከል ያለውን ግንኙነት ለመመርመር የሚበቁ አይሆኑ ይሆናል፤ ነገር ግን በጉዳዩ ዙሪያ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ውይይትን ለማነሳሳት በቂ ናቸው:: ተካልኝ ገዳሙ የተባሉ ፀሀፊ በአንድ ወቅት ባወጡት ጽሁፍ ለልማት አመቺ ከሆኑት የሀገራችን ባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦችን ለይተው ይጠቅሳሉ:: እነኚህም የረዥም ጊዜ ሀገርንና ህዝብን የማስተደደር ልምድ፣ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ የህብረተሰቡን አመለካከትና ባህርይ የሚያንጹ እምነቶች ወይንም ማህበራዊ እሴቶችና የህዝቡ ዓይነተኛ ባህርይ ናቸው::

 ሀገርን የማስተደደር የረዥም ጊዜ ልምድ ለኢኮኖሚ ልማት አመቺ የሆኑ ገጽታዎች አሉት:: በሰላምም ሆነ በዘመቻ ጊዜ አንድን ህብረተሰብ አሰባስቦ ለጋራ ዓላማ ማንቀሳቀስና ውጤት ማግኘት ማስቻል በኢኮኖሚው መስክም ተፈላጊነት ያለው ተግባር ወይንም ችሎታ ነው:: ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ሆነው ህዝብ አርሶ፣ ነግዶና ሌሎች ልዩ ልዩ ስራዎችን ሰርቶ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ ከሚወስኑት ነገሮች ውስጥ የአስተዳደርና የፍትህ ተቋማት ዋነኞቹ ናቸው:: ‹‹በዚህ ረገድ ሀገራችን የማይናቅ የታሪክ ቅርስ አላት:: አባቶቻችን ሀገራችንን ለረዥም ዘመን በነጻነት ያቆይዋት አደጋ ባጋጠመ ጊዜ ህዝቡን የማሰባሰብና የመምራት ስርዓት ዘርግተው፣ በሰላምም ጊዜ የዕለት ተግባሩና ኑሮው ለአደጋ ዝግጁ በሚያደርገው ተመሳሳይ ስርዓት እንዲደራጅ በማድረጋቸው ነው››:: መሪዎችን ለመቀበልና ዳኞችን ለመሰየም ከመስፈርቶቹ አንዱ ይህን የመሰለው ብቃት ነበር::

ይሁን እንጂ በዚህ የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ ህዝቡ የነበረው ተሳትፎ እምብዛም የሚያኩራራ አልነበረም:: በእርግጥ አዝማሪው በዘፈን ሽፋን፣ ባህታዊው ሃይማኖትን ተገን በማድረግ፣ ድሃው እስከ ንጉሱ ድረስ አቤቱታውን በማቅረብ፣ ምህረት ፈላጊው ከቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገብቶ በመደወል፣ የፖለቲካ አስተያየቱን፣ ማስጠንቀቂያውንንና ሌሎች ጥያቄዎችን በማቅረብ ህዝብ ድምጹንና ብሶቱን ሊያሰማ የሚችልበት እድል ነበረው:: ‹‹ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ የሚናገሩለትን ሰዎች ለመምረጥ ህዝቡ በየጊዜው በሸንጐ ይገናኝ ነበር››:: ይህ ጥንታዊ ልምድ ለአዲሱ ዘመን የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ልማት ሂደት በመጠኑም ቢሆን ጠቃሚ ገጽታዎች ቢኖሩትም የፖለቲካ ስርዓቱን መሰረታዊ ባህርይ የሚያንጸባርቅ አልነበረም፤ አይደለምም:: ሲወርድ ሲዋረድ የመጣልን የአስተዳደር ልምድ መሰረታዊ ባህርይው የመግዛት እንጂ የማስተደደር አይደለም:: ህዝብ ብሶቱን የሚያሰማበት አንዳንድ መንገድ ቢኖርም የመንግስትን የመግዛት ጠባይ ሊለውጥ የሚችል አልነበረም:: በመሰረቱ ህዝቡም ቢሆን መንግስትን የመቋቋም ዝንባሌው በጣም ውሱን ነበር:: የገዥዎች በትዕዛዝ የማስተዳደር ስልት፣ የህዝብም የታዛዥነት መንፈስ ለልማት ሂደት መፋጠን የሚያግዙ አይደሉም::

ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ የህብረተሰቡን አመለካከትና ባህርይ የሚያንጹ እምነቶች ‹‹የሰው ልጅ ቀና ቀና ወደሆነው ጐዳና እንዲያመራ የሚገፋፉ›› ሞራላዊ እሴቶች በመሆናቸው የልማት ሂደትን የሚያበረታቱ ሆነው እናገኛቸዋለን:: በገንዘብም ሆነ በሌላ ጉዳይ ታማኝ መሆን፣ ቃልን አክብሮ ባሉበት ቦታ መገኘት፣ ፍትህና ርትዕን ማወቅ፣ ሃላፊነትን

“ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ የህብረተሰቡን አመለካከትና ባህርይ የሚያንጹ እምነቶች ወይንም ማህበራዊ እሴቶችና የህዝቡ ዓይነተኛ ባህርይ ናቸው”

ተቀብሎ መወጣት፣ አስተዋይነትና ታታሪነት በዚህ አግባብ ሊጠቀሱ የሚችሉ አብነቶች ናቸው:: እነኚህን ሞራላዊ እሴቶች ተላብሰውና አክብረው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ በአርአያነት የሚታዩ፣ የሚከበሩና የሚፈለጉ ሰዎች ናቸው:: የልማት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ በሆኑባቸው ቦታዎችና ጊዜያት ተፈላጊነት ያላቸውም እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ናቸው::

 ቀደም ሲል የአንድ ህዝብ አይነተኛ ባህርይ በሚል ጥቅል ሀረግ ያስቀመጥነው ነጥብ ከፍ ሲል ከጠቀስናቸው ጉዳዮች ጋር በቅርብ የተያያዘና ለልማት ዋና መሰረት የሆነው የሰው ሃይል ብቃት (the quality of human resources) የሚገኝበትን ደረጃ የሚያመለክት ነው:: የህዝብን ጥራት ለመለካት መሞከር አስቸጋሪና ችግር ላይ የሚጥል ቢሆንም፣ እዚህ ላይ ለማለት የተፈለገው ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን ለልማት አስፈላጊ የሆኑ ባህላዊ እሴቶችን ተግባራዊ የሚያደርግ ህዝብ በቁጥር እየበረከተ ሲሄድ፣ በዚያው መጠን የህዝብ ጥራት የምንለው ነገር እውን እየሆነ ይመጣል ነው::

ልማትንና መሻሻልን ወደኋላ ከሚጐትቱት የባህላችን ቅሪቶች ሳይጠቀስ የማይታለፈው ምቀኝነት ነው:: ‹‹ምቀኝነት ከቅናት ባሻገር የሚገኝ ነው››:: በሌሎች ስኬትና መሻሻል ተነሳስቶ ራስንም ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ለልማት ጠቃሚ መሆኑ አያጠራጥርም:: ይህ በተለምዶ አነጋገር መንፈሳዊ ቅናት የምንለው ነው:: ምቀኝነት ግን አንድ ግለሰብ፣ ቡድን ወይንም ድርጅት የመሻሻል እድል ሲያጋጥመው ወይንም ሊያጋጥመው ሲል ምንም ጥቅም ላይገኝ ያንን እድል ማስተጓጐልና መተናኮል ነው:: ምናልባት ምቀኝነትን ጥሩ አድርጐ ሊገልጸው የሚችለው በእግዚአብሄርና በአንድ ኢትዮጵያዊ መካከል ተደረገ የተባለው ቃለምልልስ ነው:: እግዚአብሄር ኢትዮጵያዊውን ‹‹የምትጠይቀኝን ማንኛውንም ነገር እፈጽምልሃለሁ:: ለወዳጅህ ግን እጥፍ አደርግለታለሁ:: ምን ባደርግልህ ትወዳለህ?›› ቢለው፤ ‹‹አንድ ዓይኔን አጥፋልኝ አለው›› ይባላል::

በሌላ በኩል የህዝባችን የገንዘብና የሃብት አያያዝ ልማድ ከቁጠባ ጋር በአዎንታ የተሳሰረ አይደለም ለማለት ያስደፍራል:: ቁጠባ ከፍጆታ ገለል የተደረገ ሃብትን ያመለክታል:: ‹‹ልማት በተስፋፋባቸው ሀገሮች ገንዘብን ለመቆጠብ ያለው ጠንካራ ስሜት ጐልቶ ይታያል››:: ቁጠባና የልማት ሂደት በሁለት አበይት መንገዶች ሊያያዙ ይችላሉ:: አንደኛው መጠን ሲሆን ሌላው ቅርጽ ነው:: በአንድ ሀገር ውስጥ ያለው የቁጠባ መጠን አነስተኛ ከሆነ ለኢኮኖሚ ልማት መልካም መሰረት ሊሆን አይችልም:: በቁጠባ የተያዘው ሃብትም ወደ ልማት ስራ ሊውል በማይችልበት፣ ለምሳሌ በከበሩ ጌጣጌጦች፣ መልክ ከሆነ ትርጉም አይኖረውም::

 ራግናን ነርክስ የተባለ የምጣኔ ሃብት ሊቅ ‹‹የካፒታል ክምችት ችግር ባልበለጸጉት ሀገሮች›› በሚል ርዕስ በ1970 ባሳተመው መጽሃፍ ድሃ ሀገሮች በሁለት የተዛቡ ዑደቶች (vicious circle) ሊገለጽ የሚችል አነስተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ገጽታ ይስተዋልባቸዋል ይላል:: እነኚህ የተዛቡ ዑደቶች የምርት ሂደትን ከሚወስኑ ጉዳዮች አቅርቦት (supply of factors of production) እና ከምርት ፍላጐት (demand for products) ጋር የተያያዙ ናቸው:: ከአቅርቦት አንፃር ያየን እንደሆነ በድሃ ሀገሮች ዘንድ ከፍተኛ የካፒታል እጥረት አለ:: ይህም የሚሆነው የድሃ ሀገር ዜጎች የመቆጠብ አቅም አነስተኛ በመሆኑ ነው:: አነስተኛ የቁጠባ አቅም የአነስተኛ ገቢ ነፀብራቅ ነው:: አነስተኛ ገቢ ደግሞ ዝቅተኛ ምርታማነት ያለው ምጣኔ ሃብት ውጤት ነው:: ዝቅተኛ ምርታማነትም ከካፒታል እጥረትና ከአነስተኛ ቁጠባ ጋር ይያያዛል:: የነርክስን ሃሳቦች በሚቀጥለው ምስል መግለጽ ይቻላል::

ነርክስ አበክሮ እንደሚገልጸው እነኚህ ተያያዥ ጉዳዮች አንዱ ሌላውን በሚወስን መልኩ እርስ በርሳቸው በጥብቅ የተሳሰሩና የጋራ ባህርያቸው አንዱ የሌላውን ዋጋ ማቀጨጭ ነው::

 ከምርት ፍላጐት አንፃር ደግሞ ነርክስ አምስት እርስ በርሳቸው አሉታዊ በሆነ መንገድ የተሳሰሩ ተለዋጮች ያስቀምጣል:: እርሱ እንደሚለው በልማት ወደኋላ በቀሩ ሀገሮች ሰዎች ያላቸውን ሃብት ስራ ላይ ለማዋል ወይንም ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጐት/ ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው:: የዚህ ምክንያቱ የህዝቡ የመግዛት አቅም ደካማ ሆኖ መገኘቱ ሲሆን፣ ደካማ የመግዛት አቅም ደግሞ ከአነስተኛ ገቢ ጋር በቀጥታ ይያያዛል:: ገቢ አናሳ የሚሆነው ምርታማነት ዝቅተኛ በመሆኑ ነው:: የምርታማነት ዝቅተኛ መሆን በምርት ሂደት ውስጥ የሚዟዟረው ካፒታል አነስተኛ መሆኑን ያመለክታል:: አናሳ ካፒታል ገንዘብን ለልማት ከማዋል ፍላጐት ጋር የተያያዘ ነው:: ከፍ ሲል በተቀመጠው መልክ ይህን ሃሳብ በሚከተለው ምስል መግለጽ ይቻላል::

 እነኚህ ከአቅርቦትና ከፍላጐት ጋር ተያይዘው በአሉታዊ መልክ የቀረቡ ጉዳዮችን ስዕል በአዎንታዊ መልክ ለመቀየር መወሰድ የሚገባውን እርምጃ በተመለከተ ነርክስ የሚሰጠው አስተያየት ከመካከላቸው የአንደኛውን ዋጋ ከፍ ማድረግን ነው:: ይህ ሲሆን የተዛባው ዑደት ይስተካከልና ልማታዊ ገጽታ ይኖረዋል:: በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ንግድን ማስፋፋት፣ የህዝብ ቁጥር እድገትን መመጠን፣ በእርሻ ስራ ላይ የተሰማራውን ትርፍ የሰው ሃይል መቀነስ፣ ቁጠባን በግዴታ ተግባራዊ ማድረግና ዓለም አቀፍ ብድር ማግኘት የታሰበውን ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳ ነርክስ ያሰምርበታል:: ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ባለሃብቶች በድፍረትና በቁርጠኝነት በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተሰማርተው ስርነቀል መዋቅራዊ ለውጥ እውን ሲሆን ብቻ ነው::

 ራግናር ነርክስ ያቀረባቸው ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎች የሚመልሷቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ሁሉ የሚያነሷቸው ጥያቄዎችም ሊኖሩ ይችላሉ::

እዚህ ላይ ማተኮር ያለብን በአስተያየቱ ምሉእነት ወይንም ጉድለት ላይ አይደለም:: የቀረቡት ጥቅል ሃሳቦች ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ምን ያህል የተያያዙ እንደሆነ ነው:: የሚያነሳቸው ጉዳዮች መሰረታዊና መዋቅራዊ ናቸው:: በመሆኑም የሚፈለገው ለውጥ ስርዓታዊና ከብዙ ነገሮች ጋር የተሳሰረ እንደሆነ እንገነዘባለን:: ብዙ ነገሮች ከተባሉት ውስጥ ደግሞ ባህል በተሰኘ አንድ ቃል ተካትቶ የምናገኘው የህብረተሰብ አስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ አንዱ ነው::

ቀደም ባሉት ዘመናት የሀገራችንን የኋላ ቀርነት ምክንያት ለመተንተን በውጭ ሀገር ዜጎችና በሀገር ተወላጆች አማካይነት የተደረጉ ሙከራዎች ጉልህ ልዩነቶች ይስተዋልባቸዋል:: ለምሳሌ ከ18ኛው ምዕተ ዓመት ወዲህ በብዛት ወደ ሀገራችን ይመጡ የነበሩ የውጭ ዜጎች (በአመዛኙ ሚሲዮናውያን) የሀገሪቱ ኋላቀርነት መሰረታዊ ምክንያት የህዝቡ እምነት፣ ወግና ልማድ እንደሆነ በጻፏቸው መጻህፍት በስፋት አትተዋል::

በባህልና በኢኮኖሚ እድገት መካከል መደጋገፍ መኖሩ ሃቅ ነው:: ለኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊ የሆኑ ሁኔታዎች ተሟልተው ልማት እውን ከሆነ አቻ የሆነ የባህል ለውጥ ያስከትላል:: ከኢኮኖሚ እድገት የግድ የሚወለደው የባህል ለውጥ በራሱ አዝጋሚ ሂደት ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው:: ይሁን እንጂ አጥብቀን የምንመኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት ደግሞ ዜጎች ያለአንዳች ማዕቀብና መቋረጥ በተሰማሩበት የስራ መስክ ከሚገኝ ውጤት ቋሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን፣ በየደረጃው የተቀመጡ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ስራዎቻቸውን በግልጽና በፍፁም የሃላፊነት ስሜት የሚያከናውኑበትን፣ ለሚወስዷቸው እርምጃዎችም ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሁኔታ ያረጋግጣል:: የዚህ ሁኔታ መረጋገጥ የህግ የበላይነት በህብረተሰቡ ዘንድ አንዲሰርጽ ይረዳል:: ይህ ደግሞ በተራው ሰዎች እርስ በርሳቸውና ከመንግስት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትና መስተጋብር አስተማማኝ እንዲሆን ያግዛል:: በመጨረሻም ‹‹ይህን በቅርብ በመከተል ሰዎች ስለ ስራና ስለ ንብረት ያላቸው አመለካከት አዎንታዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይሄዳል››:: እውን እንዲሆን የምንፈልገው የባህል ለውጥ ከዚህ ሁኔታ ጋር የተጣጣመና ይህ ዓይነት ሁኔታም እንዲከሰት የሚያግዝ መሆን ይኖርበታል::

 ቀደም ሲል በዋናው ጽሑፍ የአንድ ሀገር ባህል ከሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር የተሳሰረና አንዱ የሌላው ነጸብራቅ እንደሆነ ለመግለጽ ተሞክሯል:: ይህ ማለት ባህልም የምርት ስርዓቱ አንድ አካል ነው ማለት ነው:: የምርት ስርዓቱ በባህሉ ላይ፣ ባህልም በምርት ስርዓቱ ላይ የየራሳቸው ተጽዕኖ አላቸው:: ባህላዊ ያልሆኑ ጉዳዮች የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የሚያፋጥኑ መሆናቸው አሌ የሚባል ባይሆንም፣ የእነርሱ ስኬት የሚረጋገጠውና የብልጽግናው ሂደት ፈጣንና የተደላደለ የሚሆነው ባህላዊ የሆኑ ጉዳዮችም ከአጠቃላይ የልማት ትልም ጋር ተሳስረው የተገኙ እንደሆነ ነው:: ይህ ጉዳይ በልማት ወደኋላ በቀሩ ብዙ ሀገሮች ዘንድ ሲያመች ከግምት የሚገባ ብዙ ጊዜ ግን የሚዘነጋ ጉዳይ ነው:: የልማት ውጥኖች ሁሉ ቀዳሚ ትኩረታቸው ቁሳዊና አሃዛዊ (ስታቲስቲካዊ) ጉዳዮች ላይ ወይንም ‹‹በአሃዛዊ ስሌት በሚተመኑና በሚለኩ የልማት ገጾች ላይ›› ይመስላል:: ምናልባት ይህ ሁኔታ ከጉዳዩ ውስብስብነት የሚመነጭ ሊሆን ይችላል:: ቁምነገሩ ልማት ሲታሰብ፣ የልማት እቅድ ሲወጣና በስራ ላይ የሚውልበት መንገድ ሲታለም እውቀቱና አቀራረቡ ‹‹ከህዝቡ ግንዛቤ›› ጋር የተገናዘበ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ነው::

በእኛ ግምት አሉታዊ የሆኑት የልማድ ወይንም የባህል ገጽታዎች እንደ አዎንታዊዎቹ ሁሉ የብዙ ዘመን የኑሮ ዘይቤ ውጤቶች ናቸው:: አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እነኚህ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በመባል የሚፈረጁት የባህል ገጽታዎችም ከስሌት ውስጥ መግባት አለባቸው:: ህዝቡ ለብዙ ዘመናት የኖረበት ነባር እምነትና አመለካከት በቁሳዊ ኑሮው ላይ ተጽዕኖ አለው:: ለባይተዋር ታዛቢ ተመሳሳይ ትርጉም ይኑረው አይኑረው ሌላ ጉዳይ ነው እንጂ፣ ህዝቡ ለያዘው እምነትና አመለካከት የራሱ የሆነ ምክንያት አለው:: ባህልን ለልማት ጥረት በሚያግዝ መልኩ ለማስተሳሰር በምናደርገው እንቅስቃሴ ማተኮር ያለብን ጐጂ የሆኑትን የባህል ገጸታዎች ነቅሶ በመለየትና የሚወገዱበትን ዘዴ በመሻት ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ለልማት አስተዎጽኦ ያላቸውን በርካታ አዎንታዊ እምነቶችንና አመለካከቶችን በሚገባ ተረድቶ በማጐልበትና ‹‹የእውቀታችን ገንዘብ በማድረግ ጭምር ነው:: የእነኚህ እምነቶችና አመለካከቶች ትልቁ ፀጋ ወይንም ፋይዳ ከልምድ ጋር ተቆራኝተው ከግብር ጋር የተሳሰሩ መሆናቸው ነው››::

ለተራው ዜጋ፣ ባህል ለስሜት ቅርብ የሆነ ተራ ቃል ነው:: ለመስኩ ባለሙያ ግን ውስብስብና ሰፊ የጥናትና ምርምር መስክ ነው:: ስፋቱና ውስብስብነቱ የሚመነጨው ባህል ከማንም ይልቅ የሰው ልጅና የሰው ልጅ ብቻ ማህበራዊ ሃብት በመሆኑ ነው:: ባህልን ያለሰው፣ ሰውንም ያለባህል ማሰብ አይቻልም::

 ሰው ማህበራዊ ፍጡር በመሆኑ ዝንተ ዓለም ተገልሎ ሊኖር አይቻለውም:: ሰው በማህበር ሲኖር መስተጋብር ዋና ባህርይው ነው:: በመስተጋብር ውስጥ ልውውጥ፣ መወራረስ፣ መዋዋጥ፣ መናቆር፣ መተባበር፣ ወዘተ የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ክስተቶች ናቸው:: እነኚህም በባህል (ማለትም በኑሮ ዘይቤ) ይገለጻሉ:: ሰዎች አንዳቸው ከሌላቸው የሚቆራኙት በዘፈቀደ ሳይሆን በባህላቸው መሰረት ነው:: ባህል ያለፈው ዘመን የሚዳሰስበት፣ የአሁኑ ዘመን ህይወት የሚገፋበት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱም የሚተለምበት ነው:: ያለፈው ዘመን አስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ የወደፊቱ ህይወት መሰረት ነው:: ይህን በውል ያላገናዘበ ህብረተሰብ መጪው ዘመኑ ጨለማ ነው:: መልካም የባህል ጥናት ይህን ክፍተት ያስወግዳል::

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top