የታዛ ድምፆች

ቢትኮይን (BIT COIN) አዲሱ ገንዘብ ምንድነው

የፕላኔታችን የወደፊት የመገበያያ ጠንካራና አስተማማኝ ገንዘብ ይሆናል ተብሎ የሚታመነው ቢትኮይን (BitCoin) ነው። ቢትኮይን እ.አ.አ. በ2008 ዓ.ም. በዓለም ላይ ደርሶ በነበረው አስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ በአብነትነት የተፈጠረ ገንዘብ ነው። ፈጣሪው ጃፓናዊው ሳቶሺ ናካሞቶ ይባላል። ሳቶሺ፣ የኢኮኖሚና የሂሳብ ሊቅ ከመሆኑም በላይ ተመራማሪ ነው። ‹‹ይሄንን የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከተለው ምንድነው? የሚል ምርምር አካሂዶ፤ እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም. የቢትኮይንን ቀመር ሠርቶ ለዓለም አበረከተ። በእሱ ቀመር መሠረት በዓለም ላይ ቢትኮይን የሚመረተው እስከ 2140 ዓ.ም. ድረስ ብቻ ነው። ይህም 21 ሚሊዮን ቢትኮይን ብቻ ነው – የሚመረተው። ከዚህ ውስጥ እስካሁን ደረስ 17 ሚሊዮን ቢትኮይኖች በሰዎች እጅ እንደገቡ ይነገራል። ለመጪዎቹ ዘመናት ስርጭት የቀሩት ወደ 4 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ ናቸው። ከተሰራጩት ውስጥ ፈጣሪው ሳቶሺ ናካሞቶ አንድ ሚሊዮን ቢትኮይኖችን ለራሱ አስቀርቶ እንደተሰወረ ይነገራል።

በዓለማችን ካሉት ሐብታሞች መካከል ቢትኮይን በብዛት ያላቸው የሚከተሉት ናቸው።

 1. ባሪ ሲልበርት (Barry Silbert)፣ 48 ሺህ

2. ቲም ደራፐር (Tim Draper)፣ 30 ሺህ

3. ቻርሊ ሽረም (Charie Shrem)፣ ይፋ ያላወጣቸው ብዙ ሺዎች

 4. ቶኒ ጋሊፒ (Tony Gallippi)፣ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ቢትኮይኖች

 5. ሳቶሺ ናካሞቶ ( Satosh Nakamoto)፣ 6.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ፣ አንድ ሚሊዮን ቢትኮይኖች

 6. አጎት ሳም፣ FBI የወረሰበትና ለሕዝብ በግልጽ ጨረታ በ48 ሚሊዮን ዶላር የሸጠበት 144 ሺ ቢትኮይኖች የሚጠቀሱ ናቸው።

 የማይክሮሶፍቱ ባለቤት ሚስተር ቢል ጌት፣ የጸረ ቫይረሱ ኩባንያ ባለቤት ሚስተር ማካፌ፣ የቪርጂን ግሩፑ ባለቤት፣ ኦፕራ ዊንፍሬና የመሳሰሉት ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን በቢትኮይን ቢዝነስ ላይ ኢነቨስት ያደረጉ ቱጃሮችም ናቸው። ኦፕራ በቅርቡ የ100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጋለች።

ቢትኮይን ክሪፕቶከረንሲ (Cryptocurrency) ሲሆን፤ በማናቸውም ማእከላዊ ተቋም፣ መንግሥትና ኩባንያ ቁጥጥር ስር ያልወደቀ በአሃዛዊ ቀመር የተሠራ ገንዘብ ነው። ይልቅስ በተጠቃሚዎች ለተጠቃሚዎች የቆመ ነጻ የኤሌክተሮኒክ ጥሬ ገንዘብ ነው ይሉታል። ሳቶሺ ይህን የመረጠበትን ምክንያት ሲገልጽ፤ ‹‹ሰዎች በመንግሥት፣ በባንኮች፣ በትላልቅ ድርጅቶች አይተማመኑም። ምክንያቱም የግል ምስጢራቸው አፈትልኮ የሚወጣበት ቀዳዳ ብዙ ስለሆነ፤ አቻ ላቻ (Peer-to-Peer) ብቻ የገንዘብ ዝውውርን ማድረግ ይመቻቸዋል ይላል። ይህም ማለት፣ ቢትኮይን ያለባንክና የመሳሰሉት ተቋማት ጣልቃ ገብነት፣ በሁለት ሰዎች መካከል ብቻ የሚደረግ የገንዘብ ልውውጥ ነው። ሳቶሺ ቢትኮይንን፤ ‘’አቻ ላቻ የሚገበያዩበት የኤሌክትሮኒክ ጥሬ ገንዘብ ሥርዓት ነው›› ይለዋል። “Bitcoin: A Peer-to-Peer Electronic Cash System” ቢትኮይን ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመገበያያ ገንዘብ በዓለም ላይ በሥራ ላይ የዋለው እ.አ.አ. በግንቦት 2010 ዓ.ም. ነው። የኸውም አንዱ ቢትኮይን በ0.0025 የአሜሪካን ዶላር ሽርፍራፊ ሳንቲም ይመነዘር በነበረበት ወቅት ነው። በዚያን ዓመተ ምህረት የፍሎሪዳው የ ኮ ም ፒ ው ተ ር ፕርግራመር ላዝሎ ሃንቼዝ አንድ ፒሳ በ10 ሺህ ቢትኮይን እንዲሸጡለት አዘዘ። እንግሊዛዊው የፒሳ ቤቱ ባለቤት ሽያጩን አጽደቆ ለላዝሎ ሁለት ፒሳዎች እቤቱ ድረስ ላከለት። እነዚያ 10 ሺህ ቢትኮይኖች ከዚያ ወዲህ በነበረው ምንዛሬ (ባንድ ወቅት አንድ ቢትኮይን በ10 ሺህ ዶላር በተመነዘረበት ስናሰላው) የ100 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም ከዚያ ወዲህ አንድ ቢትኮይን እስከ 20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድረስ መመንዘር ስለቻለ ነው። ከዚያን የላዝሎ የፒሳ ግዢ ቀን ጀምሮ፤ በቢትኮይን ቤተኞች ዘንድ በየአመቱ ግንቦት 22 ‹‹የፒሳ ቀን‹‹ እየተባለ ይከበራል።

 በሁኑ ጊዜ አሜሪካንን ጭምሮ በርካታ አገሮች ቢተኮይንን መደበኛ የመገበያያ ገንዘብ አድርገው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ። የቢትኮይን ኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖች በየአገሩ ተተክለው ሕዝቡ በመጠቀም ላይ ነው። ጎረቤቶቻችን ኬንያ፣ ዩጋንዳና ጅቡቲ ባፍሪካ ውስጥ የቢትኮይን ኤ.ቲ.ኤም. ማሽኖች አገልግሎት ላይ ካዋሏቸው አገሮች መካከል ናቸው።

ቢትኮይን አጅግ ምስጢራዊና አስተማማኝ በሆነው ‹‹ብሎክ ቼይን – BLOCK CHAIN‹‹ በሚባለው አንዱ ሰው ካንዱ ሌላ አቻው ጋር ብቻ ገንዘብን በሚለዋወጥበት የሂሳብ ቀመር ሥርዓት ላይ የተመሰረተ ነው። ብሎክ ቼይን ማናቸውንም በቢትኮይን ታሪክ ውስጥ የተደረጉትን የቢትኮይን ገንዘቦች ዝውውሮች መረጃዎችን በቋሚነት መዝግቦ የሚያኖር ነው። ይህን መረጃ ማንም ምንም ቢሆን ሊደመስሰው ወይም ሊያጠፋው አይችልም።

 ማንም የቢትኮይን ተጠቃሚ እውነተኛ ስሙን፣ አድራሻውንና እሱነቱን የሚገልጹ መረጃዎችን መጠቀም አይጠበቅበትም። ቢትኮይን የተጠቃሚውን የግል እሱነቱን ገላጭ መረጃዎቹን ይሸሽግለታል። እናም በመገልገያ ስምና (user name) እሱ ለብቻው በምስጢር መርጦ እንዲገለገልበት በመረጠው ምስጢራዊ ቁልፍ በነጻነት እንዲጠቀም ያደርገዋል።

ቢትኮይንን በኢኮኖሚ አቅሙ እዝቅተኛው ደረጃ ላይ ላለው የሕብረተ-ሰብ ክፍል መጠቀሚያ የሚያደርገውን መርሃ ግብር የነደፈው ደሞ፤ አሜሪካዊው ረስ መድሊን (Russ Medlin) ነው። ይህ ሰው እ.አ.አ. በ2014 ዓ.ም. ከጓደኖቹ ጋር ሁኖ ቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) የሚባል ክለብን አቋቋመ። ዓላማው አቅማቸው በገንዘብ ረገድ አነስ ያሉ ሰዎች የቢትኮይን ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። ረስ መደሊን ከ1000 በላይ መስራቾች ወይም ፋውንደሮች በስሩ ያሉት የቢትኮይን ከበርቴ ነው። የክለቡን አባልነት መመዝገቢያ 99 የአሜሪካን ዶላርና 500 ዶላር ወይም 1 ሺህ ዶላር ወይም 2 ሺህ ዶላር ያለዚያም ‹‹መስራች‹‹ ወይም ‹‹ፋውንድር‹‹ የተባለውን ሌሎቹን ሁሉ የሚያጠቃልለውን የ3 ሺ 500 ዶላር የቢትኮይን ማውጫ መሣሪያ የሆነውን (BitCoin Antmining) የገዛ ሰው የክለቡ አባል መሆን ይችላል። አንድ ሰው አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ የቢትኮይን ማውጫ መሣሪያ በብዛት መግዛትም ይቻለዋል።

በዋና መሥራችነት ደረጃ (FOUNDER) የሚገኙ ወደ አንድ ሚሊዮን ተኩል የዓለም ሕዝቦች የቢትክለብ አባላት ናቸው። አንዱ ሰው ሌላውን ወዳጁን ወይም የቤተስብ አባሉን እያሳተፈ፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ የሚያድግበትና የሚበለጽግበት በነጻነት የሚካሄድ ቢዝነስ ነው።

 በአሁኑ ጊዜ የቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) በ110 አገሮች ተሰራጭቶ ይገኛል። በአገራችንም የቢትኮይን ክበብ ተቋቁሞ እውቅና እያገኘ ከመጣ፣ ወደ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ይህንን አዲስ ቴክኖሎጂ በአገራችን እንዲስፋፋና ብዙሃን እንዲጠቀሙበት በብዙ እየረዳች ያለችው፣ በደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነችው፣ ኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ሃና ተክሌ

“ቢትኮይንን በኢኮኖሚ አቅሙ እዝቅተኛው ደረጃ ላይ ላለው የሕብረተ-ሰብ ክፍል መጠቀሚያ የሚያደርገውን መርሃ ግብር የነደፈው ደሞ፤ አሜሪካዊው ረስ መድሊን (Russ Medlin) ነው። ይህ ሰው እ.አ.አ. በ2014 ዓ.ም. ከጓደኖቹ ጋር ሁኖ ቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) የሚባል ክለብን አቋቋመ”

(ወይም በባለቤቷ ቤተሰብ መጠሪያ ስም ሃና ፒንድዛ) ነች። ወይዘሮ ሃና ባርባዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ክለቡን የተቀላቀለችው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ነው። የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ የማቲማቲክስ ፕሮፌሰር ከሆነው፣ ጋቦናዊው ባለቤቷ ከዶ/ር ኤድሰን ጋር ሁና ያኔ የጀመረችው የቢትክለብ ኔትወርክ አክቲቪቲዋ ዛሬ በአፍሪካ ውስጥ ቁንጮ የቢትኮይን ቱጃሮች (Tycoon) አድርጓቸዋል፡፡

ወይዘሮ ሃና በየወሩ ከ300 – 350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ከቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) እና ከቢትኮይን ማውጫ መሣሪያ (BitCoin Antmining) ገቢ ታገኛለች። በክለቡ የመጨረሻ የማእረግ ደረጃም እሷና ባለቤትዋ ይገኛሉ። ሁለቱም በአፍሪካ ውስጥ ብቸኞቹ ሜጋ ሞንስተር ቢልደሮች (Mega Monster Builders) ናቸው። አንድ ሰው በክለቡ ውስጥ የመጨረሻውን የሜጋ ሞንስተርነት ደረጃ ሲይዝ፤ ከክለቡ የ100 ሺህ ዶላር ሽልማትን ያገኛል። እናም ሃናና ባለቤትዋ ይህን ሽልማት ያገኙ ያፍሪካ ብቸኛ ልጆች ናቸው። በዓለም ላይ ያሉት ሜጋ ሞንስተሮች ቁጥራቸው 40 ያህል ብቻ ነው።

 በቢትኮይን ክለብ ውስጥ የተለያዩ የአባላት ደረጃዎች አሉ። ማይነር፣ ቢልደር፣ ፐሮ ቢልድር፣ ማስተር ቢልደር፣ሞንስተር ቢልደርና ሜጋ ሞንስተር ቢልደር የሚባሉት ናቸው። እነዚህን ደረጃዎች አንድ ባንድ ጨርሶ ሃና የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ብዙ ሰዎችን የክበቡ አባላት የማድረግ ሥራን መስራት ይጠይቃል። በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ 2 ሜጋ ሞንስተር ቢልደሮች (Mega Monster Builders) ፣ 6 ሞንስተር ቢልደሮች (Monster Builders)፣ 44 ማስተር ቢልደሮች (Master Builders)፣ 81 ፕሮ ቢልደሮች (Pro Builders) ይገኛሉ። የማይነሮችና የቢልደሮች (Miners and Builders) ቁጥር ብዛት ያለው ነው።

በአገራችን በኢትዮጵያ ይህ መጣጥፍ እስከተዘጋጀበት እለት ድረስ ሦስት ፕሮ ቢልደሮች በሁለት የስኬታማዎች ክበቦች (ACHIEVERSKLUB) ውስጥ ይገኛሉ። ከእነሱም መካከል የአንደኛው ክበብ መሪ ከሆኑት መካከል ታታሪዎቹ አቶ ሰለሞን ብርሃኑና አቶ ዘውዱ ተሾመ ናቸው። አቶ ሰለሞን የክበቡ መሥራችና የደም ስር ነው። አቶ ዘውዱ ታትሮ በመሥራቱና ብዙ ሰዎችን ባጭር ጊዜ ውስጥ የክበቡ አባላት በማድረጉ፤ በስድስት ወር እዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል። በሌላው ክበብ ውስጥ ደግሞ መስራቹ አቶ ቴዎድሮስ በፕሮ ቢልደርነት ደረጃ ላይ ይገኛል። በዚህ ክበብ ውስጥ አባል ከሆኑት መካከል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የቀድሞው ባልደረባ የነበሩት አርቲስት አድማሱ ግዛው አንጋፋው የእድሜ ባለጸጋ ናቸው። አርቲስት አድማሱ የ83 ዓመት አዛውንትና በክበቡ ውስጥ በታታሪነት ከሚጠቀሱት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

 ወደ ሃና ልመለስ… የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ወጣቷ ሃና ሙሉ ጊዜዋን፣ ቀንና ሌሊት ሳትመርጥ፣ በቢትኮይን ክለብ ሥራ ላይ ታሳልፋለች። እ.አ.አ. መስከረም 1-3 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ያፍሪካ የቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) ጉባኤ ላይ ተጋብዤ ተካፋይ በነበርኩበት ጊዜ፤ የሃናን የክለብ መሪዎች ማሰልጠኛ ማእከልና የግሏን መኖሪያ ቤት (አርፌበት ጭምር) ጎብኝቼዋለሁ። ይህ አቺቨርስ ክለብ (ACHIEVERSKLUB) በመባል የሚታወቀው የስኬታማዎች ክበብ እሷና ባለቤቷ ያቋቋሙት ነው። ክበቡ የቢትክለብ ኔትወርክ አባላትን ያመራር ብቃት ለማሻሻል በየቀኑ ሥልጠና ይሰጣል። ዋናዪቱ አሰልጣኝ እራስዋ ሃና ስትሆን፤ ሌሎችም ተጋባዥ ምሁራን አልፎ አልፎ በማሰልጠኑ ተግባር ላይ ይሳተፋሉ። ባፍሪካ ውስጥ በየአገራቱ የተቋቋሙት የቢትክለብ ኔትወርክ (BitClub Network) የስኬታማዎች ክበቦች (ACHIEVERSKLUB) ሁሉ በእሷ ስር የተደራጁ ናቸው። ምክንያቱም የቢትኮይን ሃብታም የሆነ ሌላ ሰው አፍሪካ ውስጥ ባለመኖሩ፤ እሷና ባለቤትዋ ብቻ ናቸው በዚህ ቢዝነስ ውስጥ ለመግባት ለሚፈልግ ሰው አስቀድመው ደራሽ የሆኑት። ለ20 ሺህ አፍሪካውያን መሥራች አባልነትም ቅን እርዳታዋን ያበረከተችውም ሃና ነች።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለተቋቋሙት ሁለት ክበቦችም ደራሽ የሆነችው እሷ ነች።

 ስለ ቢትኮይን ማውጫ መሣሪያ ወይም በሠራተኛ ጉንዳን የተመሰለውን መሣሪያ (BitCoin Antmining) ምንነት ትንሽ ላብራራ… ይህ የቢትኮይን ማውጫ መሣሪያ የዴስክቶፕ ኮምፒዩተር ቅርጽና ተግባር ዓይነት ሥራ ያለው ነው። እያንዳንዱ የክለብ አባል ከተመዘገበበት እለት ጀምሮ ባንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህ መሣሪያ በመገልገያ ስሙ (User name) ተዘጋጅቶ፣ ካንድ ማእከላዊ የቢትኮይን ማውጫ ማእከል ወይም ሁዳድ (Mining Farm) ይቀመጥለታል። ግለሰቡ ልክ በተመዘገበ በወሩ ማሽኑን በገዛበት የገንዘብ መጠን ዲጂታል ገንዘብ ወይም ቢትኮይን እያመረተ ድርሻውን ማታ ማታ ይከፍለዋል። ዋናው መታወቅ ያለበት ይህ ቢዝነስ የኢንተርኔት አገልግሎትን በእጅጉ የሚጠቀም መሆኑን ነው። በዓለም ላይ 21 የቢትኮይን ማምረቻ መውጫዎች ማእከላት ወይም ሁዳዶች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ እጅግ ግዙፎቹ የሚባሉት ማውጫዎች የሚገኙት በሞንጎሊያ፣ በዋሽንግተን፣ በካናዳ፣ በጆርጂያ፣ በቪርጂኒያና በአይስላንድ ነው። ቻይና፣ ኖርዌይ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያና ሌሎች አገሮችም አሏቸው። በአንዳንድ አገሮችም በድብቅ የተቋቋሙ ማምረቻዎች እንዳሉም ሹከሹክታ አለ።

እነዚህን የቢትኮይን ማምረቻ መሣሪያዎች ማእከላት ያላቸው አገሮች በጸጥታቸውና በደህንነት ዋስትናቸው አንቱ የተሰኙ በመሆናቸው፣ ብዙ ቡድኖች ማምረቻዎቹን ይገዟቸዋል። በሃና ስር የተደራጁት የአፍሪካዎቹ ቡድኖችም የአይስላንዱን ማምረቻ መሣሪያዎች የገዙ ናቸው። የኢትዮጵያዎቹ ሁለት የስኬታማዎች ክበቦች (ACHIEVERSKLUB) በአይስላንድ ማእከል ወይም ሁዳድ አማካኝነት ቢትኮይኖቻቸውን የሚያስወጡ ናቸው። አይስላንድ አስተማማኛ ደህንነት ያለባት አገር ከመሆኗም በላይ፣ ማውጫዎቹን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ኃይለኛ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይል ያላት አገር ነች። በዚህም ላይ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ በእንቅስቃሴ ላይ የሚሆኑት ማሽኖች ማቀዝቀዣ እንዲኖራቸው የግድ ይላል። እናም አይስላንድ በበረዶ የተከበበች አገር በመሆንዋ፣ የተፈጥሮ ማቀዝቀዣ ሆኖ በረዶው ለማሽኖቹ እያገለገላት ነው። በየአሥር ደቂቃው 12.5 ቢትኮይኖች ይመረታሉ። የሲ.ኤን.ኤኑን ጋዜጠኛ ሪቻርድ ኩዌስት የአይስላንዱን የቢትኮይን ማውጫ ማእከል አስመልክቶ የሠራውን ግሩም ፕሮግራም ከዩቲዩብ ላይ መመልከት ለተጨማሪ ግንዛቤ ይረዳል። https://www.youtube.com/ watch?v=PgICVbsoR-w

 በነገራችን ላይ ስለ ኤሌክትሪክ ፍጆታው ጥቂት ማለቱ ላንባቢያን ተጨማሪ መረጃን ይሰጣል። አይስላንድ የሚገኘው የቢትኮይን ማውጫ ማእከል ከ60-70 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም ነው። በትልቅነቱም ከሚጠቀሱት ሁዳዶች መካከል አንዱ ነው። በአሜሪካን አገር በሞንታና ውስጥ በመገንባት ላይ ያለው የቢትኮይን ማውጫ ማእከል ሥራው ሲጠናቀቅ፤ ወደ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም ይሆናል። ይህም ወደ 20 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባትን አንዲት ታላቅ ከተማ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ያህል ሆነ ማለት ነው። ከዚህ እውነታ የምንረዳው፣ ያለ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ቢትኮይንን ማውጣት አይቻልም ማለት ነው።

የቢትኮይን ክለብ አባላት አንድ አባባል አላቸው። ‹‹በሂሣብ እናምናለን፣ በቢትኮይን እናምናለን – We trust in maths, We trust in BitCoin” ቢትኮይን የሂሳብ ቀመር ወጤት ነው ማለታቸው ነው። እውነቱም ይሄው ነው። በቅርቡ በጆሃንስበርግ ተሰብስበው የነበሩት የቢትክለብ አባላት ቁጥራቸው ከ3000 ባላይ የሆነ ነበር። ከኢትዮጵያው ክበብ የተሳተፍኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። አ.አ. የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያን የክለቡን አባላት ቪዛ በመከልከሉ ነበር የቀሩት። ለጸረ አፓርታይድ ትግሉ የአገሬ ሕዝብ ያደረገውን አሰተዋጽኦ የዘመኑ ደቡብ አፍሪካውያን የዘነጉት ይመስለኛል። በቢትኮይኑ ጉባዔ ላይ ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ወንዶችና ሴቶች ስለቢዝነሱ ጠቃሚ የልምድ ልውውጦችን አግኝተውበታል። ኬንያ ከመቶ በላይ የክበብ አባላትን አሳትፋለች። በነሞንስተር ቢልደሩ ሬይሞንድ የሚመራው ጠንካራው የኬንያ ቡድን ብዙ ባለሚሊዮን ዶላር ቱጃሮችን ጭምር ያቀፈ ነበር።

የክለቡ መሥራች ረስ መድሊን በግል አውሮፕላኑ ካሜሪካ ሲበር መጥቶ፤ በጉባኤው ላይ ጠቃሚ ትምህርቶችን በአባላት ሰጥቷል። ‹‹እኔ የምፈልገው 10 ሺህ ሚሊዮኖሮችን ቢሊዮኖሮች ማድረግ ነው‹‹ ብሏል። ይህ ቢዝነስ መተማመንን እንደ ብርቱ ምርኩዝ ይዞ፣ ተቃቅፎ መጓዝን እንደሚሻ በብርቱ አስምሮበታል። ማምሻው ላይ ከቢልደር ጀምሮ ደረጃ ካለን የየክለቡ መሪዎች ጋር እራት ከበላ በኋላ፤ በቢትኮይን ዙሪያ ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሾችን ሰጥቷል። ይህ ቱጃር ሰው፣ በግል የጸጥታ ጠባቂዎቹ እንደታጀበ፤ ሌሊቱን ወደ አሜሪካን ተመልሷል።

 በሁለተኛው ቀን በተካሄደው የክለብ መሪዎች ስልጠና ላይ ሃና የተናገረችው የሚጠቀስ ነው። የእሷ ፍላጎት 1000 የክበብ መሪዎችን በስሯ ማፍራትና፤ በመጨረሻም ሞልቶ በተረፈው ገንዘብዋ አንድ ደሴት ለመግዛት የምትሻ መሆንዋ ነው። ሀና በደቡብ አፍረካ ውስጥ በሁለት ዓመት ተኩል የቢትኮይን ቢዝነሷ ባገኘቻቸው ሚሊዮኖች፣ ብዙ ቤቶችን፣ መኪናዎችንና ንብረቶችን በደቡብ አፍሪካ፣ በዱባይና በአዲስ አበባ ማፍራት የቻለች ጠንካራ ወጣት ሴት ነች።

“የክለቡ መሥራች ረስ መድሊን በግል አውሮፕላኑ ካሜሪካ ሲበር መጥቶ፤ በጉባኤው ላይ ጠቃሚ ትምህርቶችን በአባላት ሰጥቷል። ‹‹እኔ የምፈልገው 10 ሺህ ሚሊዮኖሮችን ቢሊዮኖሮች ማድረግ ነው‹‹ ብሏል። ይህ ቢዝነስ መተማመንን እንደ ብርቱ ምርኩዝ ይዞ፣ ተቃቅፎ መጓዝን እንደሚሻ በብርቱ አስምሮበታል”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top