በላ ልበልሃ

በኢትዮጵያ፤ ጥላቻን በጥላቻ ህግ ማቆም ይቻል ይሆን?

በኢትዮጵያ አንድ ህግ ሊወጣ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ በቅርቡ በሰጡት ማብራሪያ አመልክተዋል። ይህ የጥላቻ ንግግር ህግ (Hate Speech Law) በመባል የሚታወቀው ህግ ነው። ይህ ህግ በበርካታ ሀገራት የተለመደ በመሆኑ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዘግይቷል ሊባል የሚያስችል ነው። በህንድ ከጉዳዩ አሳሳቢነት ጋር በተያያዘ ከተራው ህግ ከፍ ብሎ በህገ መንግስቱም ጭምር እንዲካተት ተደርጓል።

 የጥላቻ ንግግር ሲባል አገላለፁ በቀጥታ ከአንደበት ወይም ከንግግር ጋር የተያያዘ ይምሰል እንጂ፤ በውስጡ በርካታ ጥቅል ሀሳቦችን የያዘ መሆኑ መታወቅ አለበት። የጥላቻ ንግግር በአንደበት አማካኝነት በመድረክ ከሚነገረው ንግግር ጀምሮ በጽሑፍ እንደዚሁም በኤሌክትሮኒክስና በምስል ጭምር እስከሚገለፀው የጥላቻ ድርጊት ድረስ አካቶ የሚይዝ ነው።

 አገላለፁ በፈረንጆቹም ጭምር “Hate Speech” በሚለው አጠራር ስለሚታወቅ ጉዳዩ ከአንደበት ንግግር ጋር ብቻ የሚያያዝ ይመስላል። ሆኖም ትንታኔው በጥልቀት ሲመረመር የጥላቻ ንግግር መገለጫው አንድን ማህበረሰብ ወይንም ግለሰብ ለማጥቃት ለማሸማቀቅና ለማግለል በማሰብ በንግግር፣ በምስል፣ በጽሑፍ፣ በካርቱን፣ በቅርፃ ቅርፅና በልዩ ልዩ ምልክቶች ተደግፎ ጥላቻን ማሰራጨት ማለት ነው። ጥላቻው የሚሰራጨው ከግለሰቡ ወይንም ከማህበረሰቡ ዘር፣ ማንነት፣ የቆዳ ቀለም፣ ሀይማኖት፣ ዜግነት፣ ፆታና የጤንነት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል።

ስሙ እንደሚያመለክተው የጥላቻ ንግግር መነሻውና ምንጩ ጥላቻ ነው። ማንኛውም ነገር ምክንያትና ውጤት (Cause and Effect) ያለው በመሆኑ፤ ጥላቻም ቢሆን የራሱ የሆነ መነሻ ምክንያት አለው። ጥላቻ መነሻው ምንም ይሁን ምን፤ በአንድ ሀገር ወይንም ማህበረሰብ ውስጥ ማህበራዊ መደላድል ካገኘ ጉዳዩ በጊዜ መፍትሄ ካላገኘ በስተቀር ሊያስከትለው የሚችለው ጥፋት ከ-እስከ ተብሎ ሊገለፅ የሚችል አይደለም።

 አንድ ግለሰብ ሌላውን ግለሰብ በአንድ አጋጣሚና ጉዳይ በደል ሲያደርስበት ሊጠላው ይችላል። ይህ መነሻና ምክንያት ያለው ጥላቻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ባጭሩ የጥላቻው መነሻ የደረሰው በደል ነው ማለት ነው። ይህ አይነቱ ጥላቻ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ሶስተኛ ወገን ገብቶ፤ ሁለቱም ወገኖች ችግሮቻቸውን አስረድተውና ተነጋግረው ወይንም የሌላ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ሳያስፈልግ መፍታት ከቻሉና ቂማቸውን ካወረዱ ጉዳዩ እዚያው ላይ ያከትማል።

ከዚህ ውጪም ከአንድ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ሀይማኖት ወይንም ብሔረሰብ የወጣ ግለሰብ ወይንም ቡድን፤ በአንድ አጋጣሚ ሌላው ላይ ጥፋት ሲያደርስ የሚችልበት አጋጣሚም አለ። ሂትለር እንደግለሰብ ወይንም ናዚ እንደ ፓርቲ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ከጀርመኖች መካከል ወጥቶ ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ጥፋትን አድርሷል። እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ተበዳዩ ክፍል፤ በደል ላደረሰበት አካል ማህበረሰባዊ ውክልና በመስጠት፤ ይወክለዋል ብሎ ያሰበውን የህብረተሰብ ክፍል በአጠቃላይ ጠቅልሎ በጅምላ የሚጠላባቸው አጋጣሚዎችም አሉ።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተጠናቀቀ ማግስት ዓለም ጀርመኖችን በምን መልኩ ሲመለከታቸው እንደነበር ማንም የሚያውቀው እውነታ ነው። ዓለም በጀርመኖች ላይ የነበረው አመለካከት አሉታዊነትን እንዲላበስ ያደረገው የመላ ጀርመኖች ድርጊት ሳይሆን ጀርመኖችን ይወክላል ተብሎ የታሰበው የናዚ ፓርቲና ሂትለር ባደረሱት ጥፋት ነው። ይህ የጉዳዩ ቀጥተኛ ተዋናይ ከሆነው ግለሰብ ወይንም ቡድን ባለፈ የጥላቻውን አድማስ ማስፋቱ የጅምላ ጥላቻ ወይንም ጭፍን ጥላቻ ተብሎ የሚወሰድ ነው። እንደዚህ አይነቱ የጅምላ ጥላቻ፤ ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንደሚያቦካ ሁሉ፤ በጥቂት ሰዎች ጥፋት በርካቶችን የገፈቱ ቀማሽ የሚያደርግበትን አደገኛ ሁኔታ ይፈጥራል።

በዚህ መልኩ ማህበረሰባዊ የጥላቻ አድማስ እየሰፋ በሚሄድበት ወቅት ደግሞ ቀስ በቀስ ህብረተሰቡ የተጋመደበትን ጥብቅ ማህበረሰባዊ ትስስር (Social Fabric) ሳይቀር ክፉኛ እየበላው ስለሚሄድ በመጨረሻ ሀገራዊ አንድነትን ሳይቀር አደጋ ላይ የሚጥል ይሆናል። በእርግጥ ማህበረሰባዊ ትስስሮች በአንድ ምሽት የጥላቻ ንግግር ሊላሉ ወይንም ሊበጣጠሱ አይችሉም። የጥላቻ ንግግር ማህበረሰባዊ መሰረትን ለማናጋት የራሱ የሆነ በቂ ጊዜ ይወስዳል። ጉዳዩን ወደ ሀገራችን ስንመልሰው በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት እየታዩ ላሉት መሰል ማህበረሰባዊ ቀውሶች በርካታ መነሻ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ አንዱ የጥፋቱ ዱላ አቀባይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ግን የጥላቻ ንግግር ነው።

 የጥላቻ ንግግሮች በቀጥታ ለአንድ የተወሰነ የታዳሚ ክፍል በአካል ከሚደረግ የመድረክ ንግግር ጀምሮ እስከ ተቀናጀ ውስብስብ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ድረስ የሚዘልቅ ነው። በኢትዮጵያ በዚህ ደረጃ ከጋዜጣ እስከ መጻሕፍት ብሎም ከማህበራዊ ሚዲያዎች እስከ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች በብዙ መልኩ በጥላቻ የተበከሉ መረጃዎች ሲተላለፉ የቆዩ መሆናቸው እሙን ነው። እንደው ለትዝብት ያህል የዓለም አቀፍ የጥላቻ ንግግር መስፈርቶችን እንደ መለኪያ በማስቀጥ እስከዛሬ በየሚዲያዎቻችን ለህዝብ የደረሱ መረጃዎች ቢፈተሹ ምን ያህሉ በስንት ንፁኃን ልብ ውስጥ ጥላቻን እንደዘሩ ፈጣሪ ይወቀው።

 መጽሐፍቻችን ብቻ እንኳ ስንወስድ ባለፉት ዓመታት በልብወለድ፣ በታሪክና በመሳሰሉት መልኩ ለህዝብ ሲቀርቡ ከነበሩት የጽሑፍ ውጤቶች መካከል ቀላል የማይባሉት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ጥላቻን ያዘሉና በቀልን የሚሰብኩ ናቸው። የአንዱን ታሪክ ለማጉላት የሌላውን ታሪክ ማንኳሰስ፣ አንድ የህብረተሰብ ክፍል ባልነበረበት ዘመን ለተፈጸመ ድርጊት ታሪክን እያጣቀሱ መክሰስ፣ ማሳጣትና የመሳሰሉት እውነታዎች በኢትዮጵያ በሰፊው ሲሰራባቸው የቆዩ ልምዶች ናቸው። መሰል መጻሕፍት በመቶ ሺዎች ቅጂ እየታተሙ ወደህብረተሰቡ ሲደርሱ የህዝቡ ህሊና ምን አይነት የጥላቻ ሥነ ልቦናን እያዳበረ እንደነበር መገመት አያስቸግርም።

እናም አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ በየብሔረሰቡ ለንባብ የበቁ በርካታ መጻሕፍት ታሪክን እያጣቀሱ፣ ቂምን አቀንቅነው የትውልዱን አስተሳሰብ በጥላቻ ሥነልቦና ሲቀርፁና ሲያፋፉ ቆይተዋል። በጥላቻ ስብከት ውስጥ ቂም ተረግዞ በቀል ተወልዷል። ቂም ቋጥሮ የበቀልን ፍሬ እንዲያፈራ የተደረገው ትውልድም ዛሬ የሀገር ፈተና ሆኗል። የጥላቻ መልዕክት በእያንዳንዳችን ተዘርቶ በቅሎ፣ ፍሬ አፍርቶና ታጭዶ ወደጎተራችን ከገባ በኋላ በየቤታችንና በየሥራ ቦታችን በደንብ አላምጠን ተመግበነዋል። ከሰውነታችንም ጋር አዋህደነዋል። እናም ዛሬ አንድን ሰው ስናሳድድ፣ ስንገድልና ስናፈናቅል ቅጣት ታህል የርህራሄ ስሜት የማይሰማን በዚህ የተነሳ ነው።

 እናም ዛሬ ወገን በወገኑ ላይ ጨክኖ የጥላቻ ሰይፉን ከቂም ሀፎቱ እየመዘዘ ጥፋት እያደረሰ ይገኛል። ይህም በመሆኑ ዛሬ በርካቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ለመሰደድና ለመፈናቀል ብሎም ለእንግልትና ለሞት ተዳርገዋል። ዩኒሴፍ በነሀሴ ወር 2018 ባወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ምድር ከገዛ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 2.8 ሚሊዮን ደርሷል። ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከተከሰቱት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ዜጎች ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እና ዓለም አቀፉ የስደተኞች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በጋራ ባወጡት መግለጫ በሁለቱ አዋሳኝ ክልሎች በተከሰተ ዘርን ያማከለ ግጭት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ከዚያ በኋላም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞንና በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን በተቀሰቀሱ ተደጋጋሚ ግጭቶች ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህ መልኩ በጂግጂጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በቡራዩ፣ እያልን ዜጎች ከማንነታቸው ጋር ብቻ በተያያዘ የተፈናቀሉባቸውን እንደዚሁም የዘር ጥቃት ሰለባ የሆኑባቸውን አጋጣሚዎች መዘርዘር ይቻላል። እንደ ዩ ኤን ሲ ኤች አር (UNCHR) መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ወደ ግዛቷ የሚገቡ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስጠለል በዓለም አቀፍ ደረጃ መልካም ስምና ዝናን ያተረፈች ሀገር ናት። በዚህም እስከ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ድረስ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ የተሰደዱ ወደ ዘጠኝ መቶ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን በተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች በማስተናገድ ላይ ናት። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭት የሚያስከትለው የዜጎች መፈናቀል ሃገሪቱ የምታስተናግዳቸውን የውጭ ስደተኞች ሶስት እጥፍ ያህል እየሆነ ነው።

ከመፈናቀሉ ባሻገር ደግሞ ግድያ፣ መደፈር፣ የአካል መጉደል፣ የንብረት መጥፋትና በአንድ ጀንበር ወደ ድህነት አዘቅት ውስጥ መግባትም ከባዱ ፈተና ሆኖ ታይቷል። ችግሩ በዚህም የሚያበቃ አይደለም። ዜጎች በተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች ያለው ጥላቻ የከፋ በመሆኑ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞው ቦታቸው ከመመለስ ይልቅ ከዚያ ውጪ ባለ ቦታ መስፈር የመፈለጋቸው ፈተናም አጋጥሟል። እንደዚህ አይነት አካሄዶች እየሰፉ ከሄዱ የህዝቡ ማህበረሰባዊ ትስስር ይበልጥ እየተበጣጠሰ የሚሄድ በመሆኑ በቀጣይ የሚኖረው ሃገራዊ አደጋ የከፋ ይሆናል። በኢትዮጵያ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት የሚያስተላልፈው ወሳኝ መልዕክት ቢኖር ጥላቻ ሰፊ ማህበራዊ መደላድል እያገኘ መሆኑን ነው።

ከዚህ ውጪ ዋነኛው የጥላቻ ንግግር መዝሪያ መንገድ ማህበራዊ ሚዲያው ነው። ዛሬ አንድ ሰው ፎቶግራፍ ያነሳል፣ ድምፅ ይቀርፃል፣ የተንቀሳቃሽ ምስልን ይወስዳል። ከዚህም በተጨማሪ በስልኩ አማካኝነት ሀሳብን በፅሁፍ ማስፈር የድምፅና የቪድዮ ምስሎችን በዚያው በስልኩ የአርትኦት ሥራን ጭምር በመስራት የፈለጉትን መረጃ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት በጥቂት ሰኮንዶችና ደቂቃዎች ውስጥ ማሰራጨት ይቻላል። በፈለጉት ጉዳይ ላይ አስተያየትን (Comment) ማስፈር፤ እንደዚሁም መረጃን ለሌሎች ማጋራት (Share ማድረግ) አንዱ የሚዲያው ባህሪ በመሆኑ ሥራውን በእጅጉ አቅልሎታል። ዛሬ መረጃን ማሰራጨት በዚህ መልኩ የቀለለውን ያህል ጥላቻን መንዛትም በዚያው ፍጥነት እየቀለለ ሄዷል። ኑክሌር ለኤሌክትሪክ ኃይልና ለህክምና ጭምር የማገልገሉን ያህል፤ የሰውን ልጅ ከምድረ ገፅ ለማጥፋትም ጭምር ይውላል። እናም ኑክሌር የሚጠቅመውም ሆነ የሚጎዳው እንደ አጠቃቀሙ ነው ማለት ነው። በተመሳሳይ መልኩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ጥቅምና ጉዳትም በተገልጋዩ የአጠቃቀም ሁኔታ ይወሰናል።

 ከማህበራዊ ሚዲያዎች መካከል ሰፊ ዓለም አቀፍ ማህበራዊ ትስስርን መፍጠር የቻለው ፌስቡክ ዛሬ በሁለት መሰረታዊ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ይገኛል። እነዚህም ተግዳሮቶች የጥላቻ ንግግሮችን ያዘሉ መልዕክቶችና ልቅ የወሲብ ፊልሞች ስርጭት ነው። ድርጊቱ ያሳሰበው ኩባንያው ለመሰል መልዕክቶች ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች፤ የተሰራጨውን መረጃ በመጥቀስ መልዕክት ቢልኩለት እርምጃ የሚወስድ መሆኑን በመግለፅ፤ በሚቀርቡለት ማስረጃዎች መሰረት ጉዳዩን አጣርቶ በርካታ የፌስቡክ ገፆችን በየቀኑ እየዘጋ ይገኛል። ሆኖም ከማህበራዊው ሚዲያ ተጠቃሚ ብዛትና ከቴክኖሎጂው ውስብስብ ባህሪ ጋር በተያያዘ ይህንን ክፍተት ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት አልተቻለም።…

 እናም ዛሬ በኢትዮጵያ እየታየ ካለው አደገኛ የዘር ጥላቻ አኳያ ይህ ህግ በኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው። አንድ ነገር በመጨረሻ ከሚታየው ውጤት በፊት እንደየሁኔታው የሚያልፍባቸው ደረጃዎች አሉት። በርካታ የማህበራዊ ጥናት ባለሙያዎች እንደሚያመለክቱት ከዘር ማጥፋት፣ ዜጎችን ከማፈናቀል፣ የጅምላ ጥቃትን ከማድረስ በፊት ወይንም ጀርባ የጥላቻ ንግግሮች አሉ። የጥላቻ ንግግሮች አንድን አካል ሰይጣናዊ መልክ ሰጥተው በመፈረጅ በታዳሚዎቹ አዕምሮ ውስጥ ጥልቅ ጥላቻ እንዲኖር የማድረግ ኃይል አላቸው። ይህ ጥላቻ አንድ ጊዜ በታዳሚው አዕምሮ ውስጥ ከሰረፀ በኋላ ደግሞ ማህበራዊ መደላድልን በሚያገኝበት መልኩ በደንብ ይብላላል። ተብላልቶም አያበቃም። በጥላቻ አይን እንዲታይ የጥላቻው ስብከት ሰለባ የሆነው ማህበረሰብ ክፍል በሂደት ሥርዓት ባለው መልኩ ቅርፅና ይዘት ተሰጥቶት ከተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲገለል ይደረጋል።

የጥላቻው ንግግር ሰለባ የሆነው ማህበረሰብ በሌላው አዕምሮ የተሳለበት (Portray የተደረገበት) መንገድ አደገኛ በመሆኑ ነገሮች በሂደት ከማህበራዊ ትስስር ከመነጠልና ከማግለል ባለፈ የተፈረጀውን የህብረተሰብ ክፍል ወደ ማጥቃትና ለማጥፋት ወደመነሳት ተግባር የሚገባበት ሁኔታ አለ።

እናም ይህንን ሁኔታ ስንመለከት የጥላቻ ንግግር የዘር ማጥፋት ዋነኛ መሰረት መሆኑን እንረዳለን። የጥላቻ ንግግር ከጀርባው ያላስተናገደ አንዳች አይነት የዘር ማጥፋት በዓለማችን አልተፈፀመም። ናዚ በአይሁዳውያን ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት መፈፀም ከመጀመሩ በፊት ጀርመናውያን በአይሁዶች ላይ የከፋ ጥላቻን እንዲያዳብሩ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ መደላድል ሰርቷል። ይህ ጥልቅ የሆነ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ በእያንዳንዱ ጀርመናዊ አዕምሮ ውስጥ በመስረፁ የአይሁዳውያን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በመርዝ ጭስ መገደል፣ ቆዳቸው እንደ እርድ እንስሳ በህይወት እያሉ መገፈፍና እንደ ዝንጀሮ የመድሀኒት መሞከሪያና መማሪያ መደረጉ እንደ ድል ብስራት ተደርጎ የሚነገርበት ሁኔታ ነበር። ይህም የናዚ ፀረ ሴማዊ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል የጀርመናውያንን ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር መሰረት ንዶት እንደነበር ግልፅ ማሳያ ነው።

 የናዚን ትዕዛዝ የሚያስፈፅሙ አካላትም በዚህ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ስርፀት ውስጥ ያለፉ ስለነበሩ ሲፈፅሟቸው በነበሩት እኩይ ተግባራት ሁሉ ሊያመዛዝን የሚችለው ሰብዓዊ የህሊና ክፍላቸው ሙሉ በሙሉ የታወረ ስለነበር፤ ድርጊታቸውን እንደ ፅድቅ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ነበር። በሩዋንዳ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከደረሰው የዘር ማጥፋት ጀርባ በሬዲዮ ፕሮፖጋንዳ ጭምር የታገዘ የጥላቻ ንግግር ዘመቻ ነበር። በተለይ በቱትሲዎች ላይ የጅምላ ግድያው ሲፈፀም፤ የቱትሲዎችን ነፍስ ለማሳነስ “በረሮዎች” ወይንም “cockroaches” የሚል የጥላቻ ስያሜ ተሰጥቷቸው ነበር። በመሆኑም አንድ ሁቱ፤ አንድን ቱትሲ ሲገድል የሚሰማው በረሮ የገደለ ያህል ነበር ማለት ነው። በዚህ መልኩ በሀገረ ሩዋንዳ በቱትሲና ሁቱ መካከል የተሰራጨው የዘር ጥላቻ ከአንድ ሚሊዮን ላላነሱ ሰዎች የዘር ጭፍጨፋ ምክንያት ሆኗል። ሀገሪቱ ከተረጋጋች በኋላ በርካታ በድርጊቱ የተሳተፉ ሩዋንዳውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ሲጠየቁ በጊዜው በነበረው የጥላቻ ንግግር በከባድ የበቀል ስካር ስሜት ጥቃቱን የፈፀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። እናም እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ የጥላቻ ንግግር ለጥፋት ምን ያህል አቀጣጣይ ነዳጅ እንደሆነ ግልፅ ማሳያ ነው።

 በጥላቻ ንግግር የተመረዙ ሰዎች በዚያ በተመረዙበት ጉዳይ ሊያመዛዝኑ የሚችሉበት የአዕምሮ ክፍል (Reasoning Faculty) ሙሉ በሙሉ ዝግ ነው። እናም በውስጣቸው ከሚነደው የጥላቻ እሳት የተነሳ የጠሉትን ሰው ሲያርዱ፣ ሲደበድቡ፣ ሲገሉና አካሉን ሲቆራርጡ የሚሰማቸው ውስጣዊ ስሜት፤ ፍርሀትና ፀፀት ሳይሆን፤ ደስታ ነው። ከዚህ አሰቃቂ ድርጊት ጀርባ ያለው ነዳጅ ደግሞ ጥላቻ ነው። እናም የጥላቻ ንግግር ለጥፋት ያለው እምቅ አቅም ከ-እስከ ተብሎ የሚገለፅ አይደለም።

 የጥላቻ ንግግርን በህግ መገደብ ይቻላል። ሆኖም ህግ በማውጣት ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ህግ አንድን ድርጊት በወንጀልነት ለይቶ ቅጣትን በመደንገግ በዚያ ድንጋጌ መሰረት አጥፊው ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ ይችላል እንጂ የችግሩን ምንጭ የማድረቅ አቅም የለውም። እናም የጥላቻ ንግግር የራሱ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት ያለው በመሆኑ፤ ከሁሉም በፊት ሊሰራ የሚገባው በነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ ነው። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በማንነት ላይ የተመሰረተ የዘር ፖለቲካ በዜጎች መካከል “እኛ እና እነሱ” የሚል የቡድንተኝት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። ጉዳዩ “በእኛ እና በእነሱ” ሳያበቃ የጥላቻ መፈራረጁም ይሄንኑ “እኛ እና እነሱን” መሰረት ያደረገ ነው። እናም ባለፉት አመታት በነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ አውድ ጥላቻ፣ እርስ በእርስ መጠራጠር፣ መፈራረጅ፣ ታሪክን ለመናቆሪያነት መጠቀምና ዘርን መሰረት አድርጎ መጠቃቃት በእጅጉ ነግሶ ታይቷል።

 ይህን ችግር ከመሰረቱ ማጥናት ምናልባትም የችግሩን ምንጭ ለመለየት በእጅጉ ይጠቅማል። በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል የሚያደርግ ህግ ማውጣት ብዙም ከባድ አይሆንም። ሆኖም ህጉ ጥላቻን ለመከላከል ድጋፍ ሰጪ ይሆናል እንጂ ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አይችልም። መንግስት ይህንን ህግ ከማውጣት ጎን ለጎን ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ሊወስዳቸው የሚገቡ በርካታ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ማስተካከያዎች እንዳሉ ግን መታወቅ አለበት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top