ጥበብ በታሪክ ገፅ

ሳም ኩክ፣ የገና ሰሞን የጠፋው ኮከብ

በህይወት ጉዟችን በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ። ገናን ሳስብ ከግማሽ ዘመን በላይ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ታሰበኝ። ዛሬም ድረስ እንቆቅልሹ ያልተፈታልኝ የዳሊ መጨረሻ! በሙዚቃው ዓለም በድንገት የተከሰተውና ዝናው በዓለም ላይ በአጭር ጊዜ የናኘው ዳሊ ቀኑ የእሱ አልነበረም። ሁሉም የገና በአልን (Christmas) ለመቀበል ተፍ ተፍ የሚልበት ወቅት ነበርና፤ ዳሊ ለቤተሰቡና ለወዳጆቹ የገና ስጦታ መግዣ ገንዘብ ለማውጣት በአካባቢው ካለ የሎስአንጀለስ ባንክ በመዝለቅ 2,500 ዶላር ወጪ ያደርጋል። ይህን ገንዘብ ይዞ ትንሽ ዘና ለማለት ያህል አመሻሹ ላይ ካሊፎርኒያ ጋለንዳሌ ወደሚገኘውና ሀብታሞች ወደሚዝናኑበት የማርቶኒ (Martoni’s) የተባለ የጣሊያኖች ሬስቶራንት ያመራል። እዚያም ሬስቶራንቱ ውስጥ ከምታስተናግደው የ22 ዓመት ቆንጂዬ፣ ከኤሊሳ ቦየር ጋር ድንገት ይገናኛል። ኤሊሳ በተለመደው የመቅለስለስ ባህሪዋ ዳሊን ቀርባው ጨዋታ ይጀምራሉ። በሬስቶራንቱ ጥሩ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ በጊዜው ዘመናዊና ቅንጡ በሆነችው ቀይ “Ferrari” መኪናው ተያይዘው ከሎስአንጀለስ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው “PJ’s” የተባለ ናይት ክለብ ያቀናሉ። በናይት ክለቡ ከተዝናኑ በኋላ ከሌሊቱ 8፡30 አካባቢ ዳሊ መኪናውን በፍጥነት እያሽከረከረ በሎስአንጀለስ ደቡብ አቅጣጫ ወደሚገኘው ሀሺንዳ የእንግዳ ማረፊያ (motel) ያመራሉ። በምን ጉዳይ ላይ እንደሆነ ባይታወቅም ከውቧ አስተናጋጅ ኤሊሳ ጋር እየተጨቃጨቁ ነበር። ከተወሰነ ጉዞ በኋላ ከእንግዳ ማረፊያው ይደርሱና አረፍ ብለው ጨዋታቸውን ይቀጥላሉ። ዳሊ አገር አማን፣ ቀዬው ሰላም ብሎ የጀመሩትን ጨዋታ በፍስሀ ለማሳረግ ውቢቷን ልጅ ይዞ ወደ መኝታ ክፍል ያመራል።

የደንበኞቿን ኪስ በማውለቅ ከምትታወቀው ኤሊሳ ጋር ወደ መኝታ ክፍል ያመራው ዳሊ ፈፅሞ ያላሰበውና ያልጠበቀው ነገር ይገጥመዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት ዳሊና ኤሊሳ መኝታ ክፍል ከገቡም በኋላ ጭቅጭቃቸው ያይላል። በዚህ መሀል ዳሊ ልብሱን መኝታ ክፍል አውልቆ ወደ ሻወር እንደገባ አመለኛዋ ኤሊሳ ለገና ስጦታ መግዣ ከባንክ ያወጣውን 2,500 ዶላር ጨምሮ ሁሉንም ልብሱን ይዛ ትሮጣለች። የሄደችውም ከስድስት ወር በፊት አንዱን ደንበኛ በጥይት ተኩሳ ወደገደለችው የእንግዳ ማረፊያው ስራ አስኪያጅ ቤሪታ ፍራንክሊን ቢሮ ነበር። በአጋጣሚ ወይም ልቡ ጠርጥሮ ሊሆን ይችላል ዳሊ ከሻወር ወደ መኝታ ክፍሉ ሲያመራ ልብሱንም ኤሊሳንም ያጣቸዋል። በሁኔታው የተደናገጠው ዳሊ እርቃኑን እንደሆነ ቁልቁል ሲመለከት ኤሊሳ ወደ ቤሪታ ቢሮ ስትገባ ያያታል። በዚህን ጊዜ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ቁልቁለቱን በሩጫ ወርዶ ቤሪታ ቢሮ ውስጥ ይገባል። እንደገባ ከ55 ዓመት የእድሜ ባለፀጋዋ ቤሪታ ጋር ይፋጠጣሉ። “አምጫት እዚህ ስትገባ አይቻታለሁ” ብሎ ቤሪታን በኃይለ ቃል ይጠይቃል። ቤሪታ ከእንግዳ ማረፊያው ባለቤት ጋር በስልክ እያወራች ስለነበር ዳሊ የሚያወራውን ጉዳይ ልብ አላለችውም። በዚህ የተናደደው ዳሊ ወደ መኪናው በማምራት ኤሊሳን መፈለግ ይጀምራል። ሲያጣት ወደቤሪታ ቢሮ ይመለሳል። እንደገና “ኤሊሳን አምጪ” ይላታል። አሁንም የስልክ ወሬዋን ያልጨረሰችው ቤሪታ ስልኩን አቋርጣ “አላየኋትም” የሚል ምላሽ ትሰጠዋለች። ሁኔታው እየከረረ ይሄድና ወደ ግብግብ ይገባሉ። በስተመጨረሻ ቤሪታ ከመሳቢያዋ ሽጉጥ አውጥታ ዳሊን ደረቱ ላይ ሶስት ጊዜ በመምታት ወለሉ ላይ ትጥለዋለች።

ሌሎች ደግሞ “አይደለም፣ ወደ መኝታ ክፍል ከገቡ በኋላ ኤሊሳ ወይም የሆነ ሰው ዳሊን ጭንቅላቱን በሆነ ነገር መቶት እራሱን ስቶ እንዲወድቅ ከተደረገ በኋላ ኤሊሳ ልብሱንና ዋሌቱን ይዛ ቤሪታ ፍራንክሊን ቢሮ ትገባለች። ከዚያም ዳሊ ሲነቃ በሁኔታው ግራ ይጋባና ራቁቱን ቤሪታ ቢሮ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ጓደኛሞች ከእሱ የተወሰደውን ገንዘብ ሲቆጥሩ በበሩ መስታወት ውስጥ ይመለከታል። ልብሱንና ገንዘቡን እንዲመልሱለት ይጠይቃቸዋል። በሩን ቆልፈው “አንከፍትም” ይሉታል። በዚህ የተናደደው ሳም ዳሊ በሩን በሀይል ለመክፈት ይታገላል። ከዚያም በሩን ሰብሮ ሲገባ ልማደኛዋ ቤሪታ በሽጉጥ ሦስት ጊዜ ተኩሳ ደረቱ ላይ ትመታዋለች። ከዚያ ኤሊሳ ወጥታ ፖሊስ እንድትጠራ ትነግራታለች። ኤሊሳ እንደተባለችው ሮጣ ትወጣና መንገድ ላይ ላገኘቻቸው ፖሊሶች አንድ ሰው በስራ አስኪያጇ ቢሮ ውስጥ ራቁቱን መጥቶ ሊደፍራቸው ሲል በሽጉጥ እንደተመታ ትናገርና በዚያው ትጠፋለች። በቦታው የደረሱት የፖሊስ አባላት ዳሊ መሞቱን ያረጋግጣሉ። ሆኖም በወቅቱ ኤሊሳ ዋሌቱንና ገንዘቡን ይዛ ስለሄደች ሟች ማን እንደሆነ ፖሊሶቹ አላወቁም ነበር።

 ዳሊ የሳም ኩክ የቅፅል ስሙ ነው። እስካሁን በቅፅል ስሙ ያስተዋወቅኩዎት ያለጊዜው በአጭሩ የቀረው ድንቅ የጥበብ ሰው ሳም ኩክ የተወለደው እ.አ.አ. በ1931 ሚሲሲፒ ክላርክስዳሌ በተባለች መንደር ነው። ሳም ከወንጌል ሰባኪ አባቱ ቻርልስ ኩክ እና ከእናቱ አና ሜ ኩክ የተወለደ ሲሆን፤ ስምንት ልጆችን ላፈሩት ወላጆቹ አምስተኛ ልጅ ነበር። ሳም ገና በለጋ እድሜው ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲዘምር የሰሙት ሁሉ ልጁ የተለየ የድምፅ ቅላጼ እንዳለውና ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ መገምት አላዳገታቸውም። ሳም በእድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ የተለያዩ የቤተክርስቲያን ኳየሮች አብሯቸው እንዲዘምር ጥያቄ ያቀርቡለት ጀመር። በዚህም “የእውነተኛው መንገድ” (Highway Q.C) ኳየር መዘምራን አባላትን ተቀላቀለ። እጅግ የተለየ የድምፅ ስጦታ የተቸረው ሳም የሀያ አመት ወጣት ሲሆን በዝማሬ እየታወቀና እየገነነ መጣ። በአማኞች ዘንድ በወቅቱ ዝነኛና ታዋቂ የነበረውን ዘማሪ ሀሪስን (R.H. Harris) “የሚተካ ነው” እስከመባል ደረሰ። በወቅቱ

“ሁኔታው እየከረረ ይሄድና ወደ ግብግብ ይገባሉ። በስተመጨረሻ ቤሪታ ከመሳቢያዋ ሽጉጥ አውጥታ ዳሊን ደረቱ ላይ ሶስት ጊዜ በመምታት ወለሉ ላይ ትጥለዋለች”

እጅግ ታዋቂ የነበረው “የነብስ አዳኞች” (The Soul Stirrers) የተሰኘ ኳየር አባላትን ተቀላቅሎ ዝማሬውን ቀጠለ።

 በዚህ ጊዜ በአሜሪካ የተለያዩ ቤተክርስቲያናት እየተዘዋወረ ዘምሯል። በነዚህ ጊዜያትም ሳም አንድ ነገር ተገንዝቧል። ጥቁሮች በቀለማቸው ምክንያት እየተገፉ ነው። በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው መገለልና መድሎ ያስቆጨውና ያስቆጣውም ጀምሯል። በዚህም የተነሳ ነጮች በሚገለገሉበት የቤተክርስቲያን ኮንፍረንሶችና ዝግጅቶች ላይ እንዲዘምር ሲጋበዝ ግብዣውን “አልቀበልም” በማለት በወቅቱ የጥቁሮች ሰብአዊ መብት ተሟጋችነቱን በተግባር አሳይቷል። ይህ ወቅት ሳም ወደ ዝናና መታወቅ ማማ የመጣበት፣ ስሙ መናኘት የጀመረበት ነበር። ከዚህ ኳየር አባላት ጋር ለስድስት ዓመታት ከዘመረና በርካታ መንፈሳዊ መዝሙሮችን አሳትሞ ለአድማጭ ካደረሰ በኋላ የህይወት አቅጣጫው ይለወጥ ዘንድ ግድ ሆነ። በብዙዎች ጉትጎታና ውትወታ ፊቱን ከመንፈሳዊ ዘማሪነት ወደ አለማዊ ዘፋኝነት አዞረ። በለስላሳ፣ ተስረቅራቂና ማራኪ ድምጹ ከብዙዎች ልብ ውስጥ በመግባት እጅግ ዝነኛ ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም።

እ.አ.አ. በ1957 ያሳተመው “ላኪልኝ” (“You Send Me”) የተሰኘው አልበሙ በሚሊዮኖች ኮፒ የተሸጠ ሲሆን፤ በአጭር ጊዜም ውስጥ ወደ ቢዝነሱ አለም ለመቀላቀል ችሏል። የጥቁር አሜሪካዊያን አርቲስቶች ኮከብ እስከመባልም ደረሰ። ይሁንና ሳም ከአንዳንድ የክፍያ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያዎች ጋር አይግባባም ነበረና በኋላ ላይ SAR/Derby የተሰኘ የራሱን የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ በማቋቋም ወደ ስራ ገባ።

 በወቅቱ የአሜሪካ ሚዲያዎች “የምንጊዜም የሮክና ሮል ሙዚቀኛ” ሲሉ አወድሰውታል። ከእሱ በኋላ ወደ ሙዚቃው አለም የመጡ አዳዲስ ዘፋኞች የእሱ ተፅእኖ እንዳረፈባቸውና እንደሚያደንቁት ተናግረዋል። ካሳተማቸው ሥራዎቹ “ለውጥ ይመጣል”( A Change is Gonna Come) የተሰኘው አልበሙ የተለየ እንደነበር ይነገራል። ይህ አልበሙ ለለውጥና ለጥቁሮች ነፃነት መከበር የነበረውን ተቆርቋሪነት ያሳያል የሚሉ አሉ። ሳም “ተፈቃሪ” (Lovable) የተሰኘውን የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሙን ሲያሳትም ከቤተክርስቲያን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። እሱም ይህ እንደሚገጥመው አውቆ ነበርና አልበሙን ያወጣው “ዳሊ ኩክ” በሚል የቅፅል ስሙ ነበር። በማስከተል ተደማጭና መሳጭ ሙዚቃዎቹን ለአድናቂዎቹ እነሆ ብሏል። “ሁሉም ቻቻን ይወዳል” ( Everybody Loves to Cha Cha Cha) “አስራ ስድስት ብቻ” (Only Sixteen) “ምን አይነት ድንቅ አለም ነው” (What a Wonderful World) የተሰኙ ሙዚቃዎቹን በጣፋጭና መሳጭ ድምፁ አንቆርቁሮ ተደንቆበታል። Twistin’ the Night Away, Sad Mood, Bring It on Home to Me, “ሌላ ቅዳሜ ምሽት” (Another Saturday Night), “ሮም በአንድ ጀንበር አልተገነባችም”, Rome (Wasn’t Built in a Day) የተሰኙት ሙዚቃዎቹ በየዘመኑ ብዙዎችን ያዝናኑ ሲሆን፤ ዛሬም ድረስ አይረሴ ሆነው ዘልቀዋል። ሳም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ድንገት ብልጭ ብሎ የጠፋ ተፅእኖ ፈጣሪ የብሉዝና የሪትም አባት ነውም ይሉታል። የሶል ንጉስ እስከመባልም ደርሷል። ትንፋሹን ለረጅም ጊዜ ማቆየትና በአንዱ ትንፋሽ ስልቶችን እየቀያየረ መዝፈን የሚችል ባለ ልዩ ተሰጥኦ ባለቤት እንደነበረ የሚመሰክሩም አሉ።

 ሳም በዚች ምድር ላይ በቆየባቸው እጅግ ጥቂት ጊዜያት በነዚህ ውብ ሙዚቃዎቹ በተለይም የዓለማችንን ነጭ ወጣቶችና መላውን የጥቁር ህዝብ ቀልብ ለመግዛት ችሏል። ሳም ሙዚቀኛ ብቻም ሳይሆን በጊዜው “ነቅነቅ” (Shake) የተሰኘው አዲስ የዳንስ ስልት ባለቤትም ነበር። እነዚህ ስራዎቹ በሳም ህይወት ውስጥ አዲስ ምእራፍን የከፈቱና ዓለም በመላ በዚህ ሰው ላይ ዓይኑን እንዲጥልበት ምክንያት ሆነዋል። ዝናው በዓለም ላይ በናኘበትና ጥሩ የህይወት መስመር ላይ በነበረበት ወቅት ልክ የዛሬ 54 ዓመት በእለተ ሐሙስ ሳይታሰብ ወዳጆቹን፣ አድናቂዎቹንና መላውን ጥቁር አሜሪካዊ ባስደነገጠ ሁኔታ በ33 አመቱ ከላይ በተገለፀው አሳዛኝ ሁኔታ ለሞት በቅቷል።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት አድናቂዎቹን በሞት የተለየው ሳም ኩክ፤ ድምፃዊ፣ የግጥምና የዜማ ደራሲ፣ የሙዚቃ አዘጋጅ፣ አቀናባሪና አሳታሚ ነበር። ብዙ የጥበብ ስራዎቹን ለዓለም ማበርከት በሚችልበት እድሜው እንዲሁ እንደዋዛ ከቤቱ ወጥቶ የመቅረቱ ነገር ዛሬም እንቆቅልሽ ነው። የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ዳኞችና ባለስልጣናት ሳም የሞተው በአስገድዶ መድፈር ሙከራ እንደሆነና ገዳዩ ቤሪታ ፍራንክሊን በሰጠችው የእምነት ክህደት ቃልና ምስክርነት ይህን አረጋግጠናል ቢሉም፤ ዛሬም ድረስ ብዙዎች ከግድያው ጀርባ ሚስጥር እንዳለና ግድያው በታቀደና በተቀነባበረ ሁኔታ እንደተፈፀመ ይስማማሉ። ይህም እውነት ተዳፍኖ የመቅረቱ ጉዳይ ዛሬም ድረስ በርካቶችን በቁጭት እያንገበገበ ይገኛል።

 ቤሪታ በሰጠችው ቃል “ሳም እኔንና አብራኝ የነበረችውን ወጣት ሊደፍረን ሙከራ አድርጓል። በዚህም ራሴን ተከላክያለሁ” ነበር ያለችው። ቤሪታ ለፍርድ ቤት በሰጠችው ቃል ሳም ሊሞት ሲል አንድ አሳዛኝ ቃል ተናገረኝ አለች። “አንቺ ሴት መታሽኝ?” “Lady, you shoot me?” የሞቱ ምክንያት የአስገድዶ መድፈር ሙከራ ነው የሚለውን የወቅቱን የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰሙ ከ200, 000 በላይ የሳም አድናቂዎች በሎስአንጀለስና ቺካጎ አደባባዮች ወጥተው ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። ለሞቱ የተሰጠውን ሰበብ እንደማይቀበሉትና ሰብእናው ይህ እንዳልሆነ ይልቁንም ከበስተጀርባው ሚስጥር እንዳለ በመጠቆም ድምፃቸውን አሰምተዋል። ሰሚ አላገኙም እንጂ።

 ኤሊሳ በስተመጨረሻ ተፈልጋ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ጓደኛዋን በማስገደል ወንጀል ተፈርዶባት እስርቤት ገብታለች። ቤሪታም እንዲሁ ቀለል ባለ የሰው መግደል ወንጀል ተፈርዶባት ዘብጥያ የወረደች ቢሆንም፤ አንድ አመት ከስድስት ወር ቆይታ በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ተለይታለች።

 ለሳም ሞት ሁለት ጉዳዮች በዋናነት ይነሳሉ። ሳም በሙዚቃው ዓለም እየገነነና በዚህም ገቢው እያደገ ሲመጣ ለሱ የሚከፈለው ገንዘብ ከስሙና ከሚያስገኘው ገቢ ጋር ባለመጣጣሙ ከሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቷል። በኋላ ላይ የራሱን የሙዚቃ አሳታሚ ኩባንያ ከፍቶ የላቡን ዋጋ ማግኘት ቢችልም ቀደም ብሎ ጥርስ ውስጥ ያስገቡት የሙዚቃው ቢዝነስ ሰዎች በስውርና በተቀነባበረ ሁኔታ እንዳጠፉት የሚናገሩ አሉ።

 ሌላኛው ምክንያት ሳም እየገነነና እየታወቀ ሲመጣ ሀይለኛ ተፅእኖ ፈጣሪ ለመሆን ችሏል። በመጨረሻው የህይወት ዘመኑ ለጥቁሮች መብት የቆመ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሆኖ ብቅ ማለቱ በአክራሪ ነጮች ዘንድ አልተወደደም። እናም ይህም ለሞቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉ አሉ። ሳም ዛሬ በህይወት ቢኖር የ87 ዓመት የልደት በአሉን በዚህ ሰሞን ያከብር ነበር። እውነታው ግን ዛሬም ድረስ ተወዳጅ፣ ተናፋቂና አይረሴ ሙዚቃዎቹን ለአድናቂዎቹ ትቶ ማለፉ ነው። በሀሳብ የሳም ኩክን አንድ ሙዚቃ ጋብዤ መልካም የገና ሳምንት ብላችሁስ?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top