ከቀንዱም ከሸሆናውም

ሞገደኛው ጋዜጠኛ

ለየት ባለ ባህሪው የሚታወቀው ጋዜጠኛና ደራሲ መንግስቱ ገዳሙ (ሞገደኛውጋዜጠኛ) በመንግሥት እና በባለሥልጣናት ላይ የሚሰነዝረው ትችት እና የነቀፋ ጽሑፉ የበረታ ነው። በመራራ ቀልዱ እና ተንኮሉ ሰውን ማስደንገጥ እና ማሳጣትም ባህሪው ነበር። ስለሱ ሲነገር አብሮ የሚነገሩ ጥቂት ተንኮሎቹን እነሆ ብለናል። ምንጫችን «ያልተዘመረላቸው» የተሰኘው የፍፁም ወልደማሪያም መጽሐፍ ነው።

 አንድ ጊዜ ሞሞቱን በስልክ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ጸሐፊ አስነግሮው በቢሮው ውስጥ ከባድ ሀዘን ሆነ። ወሬውን የሰማ ሁሉ ቀብሩ ወደ ሚከናወንበት ወደ ቀጨኔ መድኃኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን ቅጥር ግቢ በመሄድ የሟች አስከሬኑን ይጠባበቅ ጀምሯል። ነገርግን የተጠበቀው አስከሬን በሳጥን ሳይሆን ነጭ ባርኔጣና ጥቁር ሱፍ ግጥም አድርጎ ለብሶ ከቀብርተኞች ጋር ተቀላቀለ። ለቀብር የተሰበሰበውም ሰው ሁሉ በሁኔታው ተገርሞ ወደ ሥራው ተመለሰ። በሌላው ቀን ወዳጆቹ ተሰብስበው “ለምንድነው እንዲህ ያደረግከው?” ብለው ቢጠይቁት “ስሞት የሚኖረኝን የቀብርሥነ-ሥርዓት አይነት ሳልሞት ለማወቅ ብዬ ነዋ!” ማለቱ ይነገራል።

በንግድ ባንክ ሲሰራ የሰራው ተንኮልም በሃላፊዎች ዘንድ ቁጣን አጭሮ ነበር። ንጉሱ የባኩን አገልግሎት ሊጎበኙ በቦታው ሲገኙ “አጅሬ” ተጣጣፊ አልጋ በድብቅ አስገብቶ ክፍሉ ሲጎበኝ እሱ ተኝቶ ተገኘ። ንጉሡ ስለምን እንደዛ እንዳደረገ ሲጠይቁት “አለቆቼ ስራ ስለማይሰጡኝ የምሰራው ስራ ሳይኖር በከንቱ ደሞዝ እንደሚከፈለኝ ለማሳወቅ ነው” ብሎ ተናገረ። በዚህ ድርጊቱ የተበሳጩት አለቆቹ በማግስቱ የስንብት ደብዳቤ ፃፉበት። እሱ ግን ፍርድ ቤት ከሶ መስሪያ ቤቱን ረታ። ነገር ግን ጉዳዩን ተከታትሎ ሳያስፈፅም በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በጋዜጠኝነት ተቀጠረ።

መንግስቱ ገዳሙ ከሃያ ያላነሱ መጻሕፍትን ጽፎ ለአንባቢያን ቢያቀርብም የማተሚያ ቤት ዕዳ መክፈል አቅቶት ሲሰቃይ ከማተሚያ ቤቱ ዕዳ በላይ ሊሸጡ የሚችሉ መጻሕፍቱን ለድርጅቱ በነፃ ያድል ነበር። በወቅቱ የነበረበትን ችግር ለመቅረፍም መጽሐፍቱን ለአዟሪዎች በዱቤ እና በነፃ ይሰጥ ነበር።

አንድ ጊዜ ደግሞ አንድ ሚስኪን ፈረንጅን በሰባት መቶ ብር ደሞዝ ቀጥሮ ካፖርት እያሸከመ በፒያሳ ያዞር ነበር። ይህም “ፈረንጅ የአበሻ አሽከር አይሆንም” የሚለውን አመለካከት ለማፍረስ ነበር።

ፀባዩ ለየት ያለነበር፤ ሳይኮሎጂስቶች “ዲቪየንት” አፈንጋጭ የሚሉት አይነት። አንድ ጊዜ ለስራ ጉዳይ ወደ አስመራ ይላካል። ታዲያ መንግሥቱ በአስመራ ስላሉ እስር ቤቶች ጽሑፍ ለማቅረብ ይፈልጋል። ነገር ግን ባለሥልጣኖቹን እንዲገባ ቢያስፈቅድም መልሳቸው እምቢ ሆነበት። በዚህ የተናደደው ሞገደኛው ጋዜጠኛ መንግስቱ ገዳሙ ምሽት ላይ አንድ መላ ይገለፅለታል። ወንጀል ሰርቶ ፖሊስ ጣቢያ መታሰር። ስለዚህ አንድ መጠጥ ቤት ይገባና ባዶ ጠርሙሶች እየመረጠ ስብርብራቸውን ያወጣል። ኡኡታው ይቀልጣል። ፖሊስም ደርሶ እያዳፋ ወደ ጣቢያ መንግስቱን ይወስደዋል። ከሦስት ቀናት እስር በኋላ በዋስ ተለቆ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ስለ አስመራ ማረሚያ ቤቶች በርከት ያሉ መጣጥፎችን በመፃፍ ለማጋለጥ ቻለ። ይኸው

ትረፊ ያላት

ነፍስ …

መቼም ሰው ያለቀኑ አያልፍም። መጋቢት 6 ቀን 1963 ዓ/ም ግርማዊ ንጉሠ-ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ይዞ ወደ አባያ ሲነሳ በአውሎ ንፋስ ምክንያት መሰናክል አጋጥሞት የወደቀው ሄሊኮፕተር ከጥቅም ውጪ ሆኗል።

 መጋቢት 7 ቀን 1963 ዓ/ም ዕትም የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ በፎቶግራፍ አስደግፎ እንደዘገበው፤ ሄሊኮፕተሩ በአውሎ ንፋስ ምክንያት መሰናክል ደርሶበት የወደቀው፤ ከሃዋሳ ከተማ 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በብላቴ የእርሻ ልማት የተደረገው ንጉሳዊ ጉብኝት ከተፈጸመ በኋላ ፤ ወደ አባያ ለመሔድ በተነሳ ጊዜ ነው።

ይኸው 28 ሰዎች ሊይዝ የሚችለው በሶቪየት ኅብረት የተሰራው ሄሊኮፕተር ተሰናክሎ ቢወድቅም፤ ግርማዊ ንጉሠ-ነገሥት አንዳችም ጉዳት ሳያገኛቸው ከሄሊኮፕተሩ በደህና በመውጣት ጉዟቸውን በአውቶሞቢል ቀጥለው በሌሎች ሥፍራዎች የተዘጋጀውን የጉብኝት ፕሮግራም ሲያከናውኑ ውለዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top