ጥበብ በታሪክ ገፅ

ማርከስ ጋርቬይ፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ፊታውራሪ!

አውሮፓውያን የጻፏቸውን የታሪክ መጻሕፍት ስንመረምር ብዙ የጎደሉ ነገሮች እንዳሉባቸው መረዳት እንችላለን። የአፍሪካ እና የህዝቦቿ ታሪክ በጽሑፎቻቸው ሊሰጣቸው የሚገባውን ቦታ አላገኙም። በተለይም ታላላቅ መሪዎቻቸው በህብረተሰባቸው ታሪክ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ መሆናቸው እየታወቀ አልተጠቀሱም። የመጠቀስ ዕድል ያገኙት እንኳን፤ በአውሮፓውያን ቅኝ ላለመገዛት ያመፁ በመሆናቸው እንደ ተራ ዕብድ ተቆጥረዋል።

ይህ በአውሮፓውያን የታሪክ ጸሐፊዎች የተደረገው ሴራ አንድም የዘረኝነታቸውን፤ አለበለዚያም ደግሞ አውሮፓዊ ባልሆነው ህዝብ ላይ የፈፀሙትን ወንጀል ለመደበቅ ሲሉ ያደረጉት እንደሆነ ማወቅ አዳጋች አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ስለ አፍሪካ፣ ስለ ህዝቦቿና ስለ ታላላቅ መሪዎቻቸው ተጽፈው የሚገኙት የታሪክ ሰነዶችም የዚህ ከፍተኛ ምሁራዊ ደባ ህያው ምስክር ናቸው።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የጥቁርን ህዝብ ታሪክ በጥቁር ዓይናቸው ማየት የቻሉ፤ የጥቁር ህዝብ ታሪክ ጸሐፊዎች ብቅ ብቅ በማለታቸው፤ ተድበስብው ታልፈው የነበሩ የጥቁር ህዝብ ታሪኮች መስተካከል ጀምረዋል። ለዚሁም የማርከስ ሙሴ ጋርቬይ ታሪክ ምሳሌ ይሆናል።

 ስለ ጋርቬይ ሲነገር የጃማይካውያን የፀረ- ባርነት ትግል ታሪክ አብሮ ይነሳል። ጃማይካውያን ከባርነት ቀንበር ለመላቀቅ ያደረጉት የሚያኮራ የትግል ታሪክ እንዳላቸው ይነገራል። በ1937 የተደረገውን ንቅናቄ ለማፈን ይሯሯጡ የነበሩት ስፓኒሾችና እነሱን የተኩት የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ሳይወዱ ያምናሉ። በጊዜው አመፁን ለማክሸፍ በቅኝ ገዢዎች ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም። በስፔን ቅኝ ግዛት ሥር እስከነበሩበት እስከ 1655 ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ የጦርነት ዘመቻ ተካሂዶባቸዋል። በእንግሊዞች መገዛት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶም ኮሎኒያሊስቶቹ በዲፕሎማሲና በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲያቸው ትግላቸውን ለማፈን ሞክረው ነበር። ሆኖም ጃማይካውያን የቅኝ ገዥዎቹን ሴራ በትግላቸው ለማክሸፍ ችለዋል።

 የጃማይካ ህዝብ በአመጽ እና በአልገዛ ባይነት ትግል ውስጥ እያለፈ እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ድረስ ቢዘልቅም የኑሮ ሁኔታው እየከፋ መሄዱ ግን አልቀረም። የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎችም የመሣሪያ ኃይላቸውን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን፤ በሥነ-ጽሑፍ ደረጃ በዘረኛ የታሪክ ጸሐፊዎቻቸው አማካይነት የመርዝ ብዕራቸውን በሰፊው የዓለም ጥቁር ህዝብ ላይ አዞሩ። “አንድ የ30 ዓመት ጥቁር ሰው ጭንቅላት ከ5 ዓመት አውሮፓዊ ህፃን የተሻለ አያስብም” የሚል መሰረት የሌለው ፕሮፖጋንዳ ይነዙ ጀመር። ለምሳሌም በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ የኖረው “ዴቪድ ሂውም” እየተባለ ይጠራ የነበረው እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ “ብሔራዊ ጠባይ” በሚለው ጽሑፉ እንዲህ ይላል።

“እኔ አሁንም ቢሆን የኔግሮ ህዝብ በተፈጥሮው ከነጮች ዝቅ ለማለቱ ጥርጥር የለኝም። በጊዜያችንም … አንዳችም የሰለጠነ የጥቁር ህዝብ መንግሥት በዓለማችን ላይ አናይም። ለዚህ ሀቅ በሳይንስና በኪነት የተሰማራ የጥቁር ዘር በአሁኑ ጊዜ አለመኖሩ ራሱ ምስክር ነው።”

ዴቪድ ሂውምና መሰል አውሮፓውያን ፀሐፊዎች ስለ ጥቁር ህዝብ ጠንቅቀው ያላወቁት ነገር ሁሉ ህልውና አልነበረውም። ለመጀመሪያ ጊዜም ጃማይካውያን ብቻ ሳይሆኑ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በሌሎች የካሪቢያን አገሮች የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ድርጊቱን በይፋ ማውገዝ ጀመሩ። ክርክሩና ውዝግቡ ብሔራዊነቱን አልፎ አለማቀፋዊ መልኩን ያዘ።

ይህንን ጠንካራና ዘረኛ የሆነ የአውሮፓውያን ትምክህት ማርከሻ የሚሆን የጥቁር ህዝብ ተጠሪ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊ እየሆነ መጣ። በዚህን ጊዜ ነበር የጥቁር መሪ በሻማ መብራት በሚፈለግበት ወቅት ወጣቱ ማርከስ ሙሴ ጋርቬይ በጃማይካና በጥቁር ህዝብ ታሪክ ተከስቶ ታላቅ ሚና ሊጫወት የበቃው።

 ማርከስ ሙሴ ጋርቬይ “አይል ኦፍ ስፕሪንግ” እየተባለች በምትጠራ መንደር ተወለደ። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በጊዜው ለጃማይካውያን ተብሎ በተከፈተው ትምህርት ቤት ገባ። በ14 ዓመቱ 1ኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ በወላጆቹ ድህነት ምክንያት ትምህርቱን መቀጠል ባለመቻሉ፤ ሥራ መፈለግ ግድ ሆነበት። አጎቱ ይሰራ በነበረበት የማተሚያ ቤት ጊዚያዊ ሥራ ስላገኘም የተወለደበትን መንደር እና ወላጆቹን ትቶ ወደ ጃማይካ ዋና ከተማ ኪንግስተን ሄደ።

ለወጣቱ ሠራተኛ ጋርቬይ ይህ የሥራ አጋጣሚ ብዙ ልምዶችን እንዲቀስም ረድቶታል። የከተማ ኑሮ፤ ፀጥታ፣ መልካም ጉርብትና የነሳውን ያልነሳውን፤ ከብዙ ሰዎች ጋር የመገናኘትን፣ ኃሳብ የመለዋወጥን፣ ተከራክሮ የማሸነፍንና የመሸነፍን አዲስ ልምድና ባህል እንዲቀስም አድርጎታል። የጥቁር ህዝብ ጉልበት መበዝበዝ እና መመዝበር በገጠሩ ብቻ ተወስኖ ሳይቀር በከተሞችም በተቋቋሙት ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎችም አስከፊ መልክ እንደነበረው የዓይን ምስክር ለመሆን በቅቷል።

ለመጀመሪያ ጊዜም በ1907 ዓ.ም ጋርቬይ የማተሚያ ሠራተኞች ማህበር መሪ በመሆን፤ በኑሮ መወደድና በዋጋ መናር ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ ባካሄዱበት ወቅት ትልቅ ሚና ተጫወተ። የጋርቬይ ትግል በሥራ ቦታው ብቻ አልተወሰነም። ለመጀመሪያ ጊዜ በህቡዕ የፖለቲካ ክበብ አቋቋመ። “ትግላችን” የሚሰኘው የክበቡ ልሳን ኤዲተር በመሆንም የጥቁር ህዝብ ለመብቱ እና ለነፃነቱ ሲል መከተል የሚገባውን የትግል አቅጣጫ መተለም ጀመረ። ልሳኑንም እንደ ማደራጃ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ያዘ። ቆይቶም ይህንን የፖለቲካ ሥራ፤ የትርፍ ሰዓቱን በመሰዋት ብቻ ሊገፋው እንደማይችል ሲረዳው የዕለት ዳቦ የሚያገኝበትን የማተሚያ ቤት ሥራውን ተወ።

 ይሄም ቢሆን የሚያዋጣው አልነበረም። ጋዜጣውን ማሳተም ቀርቶ ከዕለት ዕለት የሚያደርሰውን ምግብ ለማግኘት ባለመቻሉ፤ ለሥራ ፍለጋ ከሃገር ርቆ ለመሰደድ ተገደደ። በ1909 ዓ.ም የጃማይካን አፈር ለቆ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ወደምትገኘው ሃገር ኮስታሪካ ተሰደደ። እዚያም በአንድ የፍራፍሬ አምራች ኩባንያ ተቀጥሮ በጊዜ ተቆጣጣሪነት መሥራት ጀመረ።

 በኩባንያው ተቀጥረው ጉልበታቸውን የሚሸጡ ጥቁር ሠራተኞች እና ህንዶች በሥራ ቦታቸው ላይ የሚደርስባቸውን ግፍ ሁሉ ተመለከተ። ግማሾች በእርሻ ቦታው ላይ እንዳሉ በመርዘኛ እባብ ተነድፈው ህክምና ባለማግኝታቸው ሲሞቱ፤ ከፊሎቹ እንደ ነብር በመሳሰሉ የዱር አራዊት እየተበሉ በዋሉበት ሲቀሩ አየ። ይህንን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መሰናክል አልፈው ለዕለት ኑሯቸው የምትሆናቸውን ገንዘብ ማግኘት የቻሉትንም ሠራተኞች በአከባቢው የሚገኙ ስፓኒሽ ሽፍቶች በቆንጨራቸው እየቆራረጡ፣ እየገደሉ፣ ገንዘባቸውን ሲዘርፉ የዓይን ምስክር ለመሆን በቃ።

ይህን ግፍ ለማጋለጥ እና ጥቁር ህዝብን ለማደራጀት ሲል፤ ሰርቶ ባጠራቀማት ገንዘብ “La Natanace” የሚል አዲስ ጋዜጣ ማውጣት ጀመረ። የፈለገውን ያህል ዕርዳታና ድጋፍ ባለማግኘቱ ግን ሁሉንም ነገር ትቶና ኮስታሪካን ለቆ ወደ ፓናማ ሄደ። ነገር ግን እዚያም ያጋጠመው ከኮስታሪካ እምብዛም የተለየ አልነበረም። በአንድ ማተሚያ ቤት ተቀጥሮ ለጥቂት ወራት ከሰራ በኋላ መደበኛ ስራውን ትቶ “La Prenza” እየተባለ የሚጠራ ጋዜጣ ማተም ጀመረ። ሆኖም በጋዜጣው ላይ የሚወጡት ጽሑፎች ከፓናማ መንግስት ባለ ሥልጣኖች ጋር እንዲጋጭ አደረገው። የጀመረው ዕቅድም ከሸፈ። ፓናማን ለቆ መጀመሪያ ወደ ኢኳዶር ከዚያም ወደ ኒካራጉዋ፣ ሆንዱራስ፣ ኮሎምቢያና ቬኒዚዌላ ወደተባሉት የደቡብ አሜሪካ ሃገሮች ተዘዋወረ።

 በሄደባቸው ሀገሮች ሁሉ የጥቁር ህዝቦችን ስቃይ፣ በደልና የነጮችን ዘረኝነት በተጨባጭ ተመለከተ። ጥቁር እስከሆኑ ድረስ ጃማይካውያን፣ በሆንዱራስ፣ በአሜሪካ ሆነ በአውሮፓ የኑሮና የሥራ ሁኔታቸው ልዩነት የሌለው መሆኑን ተገነዘበ። ለመጀመሪያ ጊዜም ከእንግዲህ ወዲያ የሚነሳ የጥቁር ህዝብ እንቅስቃሴ በተለያዩ አህጉራት ያሉትን ጥቁሮች እስካላቀፈ ድረስ የትም መድረስ እንደማይችል ተረዳ። በተዘዋወረባቸው አገሮች የሚኖሩት ጥቁር ህዝቦች ተመሳሳይ በደልና ጭቆና ስለሚደርስባቸው፤ እነሱን በማህበር ማደራጀቱ አስቸጋሪ አይሆንም ብሎ ራሱን አሳመነ።

 ምክንያቱም ይሄንን ዓላማ መሰረት በማድረግ በጊዜው በሃገሩ የሚኖሩት ዜጎች የእሱን እርዳታ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሚፈልጉት መሆናቸውን በደብዳቤ ስለገለጹለት ነበር። ለዚህም ነው ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በ1911 ዓ.ም ወደ ጃማይካ ሊመለስ የበቃው።

 እንደደረሰም በዕቅዱ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ “The Univesal Negro Improvement Association” የሚባል ማህበር አቋቋመ። ዓላማውም ጥቁር ህዝቦችን ለማንቃት እና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዲወስኑ ለማዘጋጀት፤ መብቱንና ግዴታውን ለማሳወቅ ሲሆን፤ በመጨረሻም ወደ አፍሪካ እንዲመለሱ ለመርዳት ሆነ። ለዚሁ ተግባር እንዲረዳም “Negro World” የሚል ልሳን እየታተመ መውጣት ጀመረ።

ከህብረተሰብ ታሪክ እንደምንማረው በጊዜው ከህብረተሰቡ የቀደመ መሪ ወይም ግለሰብ ብዙ ውግዘት እና ለፈፋ ከተለያየ አቅጣጫ እንደሚደርስበት ሁሉ፤ ጋርቬይም ከዚህ ዓይነት ወቀሳና ውግዘት ማምለጥ አልቻለም። በጃማይካ ህብረተሰብ ውስጥ የተሻለ ኑሮ መኖር የጀመሩት ጥቁር ጃማይካዊ ንዑስ ከበርቴዎች በድርጅቱ መመሥረት ብቻ ሳይሆን Negro የሚለውን ቃል በመጠቀሙ ዝቅተኛ አስመስሎ የጠራቸው ስለመሰላቸው ይቃወሙት ጀመር። ንግግር እንዲያደርግ በተጋበዘባቸው የስብሰባ አዳራሾች እየተገኙ ጋርቬይን አላናግር አሉ። እሱን ለመጣል ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ከነጮችም በኩል ከዚህ ያላነሰ ተቃውሞ ደረሰበት። ያለ አንድ ሃሳብ የሚበዘብዙትን ህዝብ የሚያስተባብር እና ለአመፅ የሚያዘጋጅን ማህበር በአንክሮ መመልከት ስላላዋጣቸው በቻሉት መንገድ ማህበሩን ለማፍረስ ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። የጋርቬይን ስም ለማጥፋትም የቻሉትን ሁሉ አደረጉ።

 በዚህ ወቅት (በመጋቢት 1912 ዓ.ም) ነበር ጋርቬይ ወደ እንግሊዝ አገር የሄደው። እንግሊዝ አገር በመሄዱም ከብዙ አፍሪካውያን ጋር ለመተዋወቅና በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ ለመወያየት ዕድል አገኘ። ስለ አፍሪካ ጥንታዊ ታሪክ እና ሥልጣኔ፣ ስለ መልክዓ ምድሯ፣ ስለ ማዕድኗና ስለአፍሪካ ህዝቦች በቅኝ መገዛት ሰፋ ያለ ልምድ ማግኘት ቻለ። የጥቁር ህዝቦችን በተለይም የአፍሪካን ታሪክ እንደፈለጉ ሲጠመዝዙ የነበሩትን ታሪክ ፀሐፊዎች ለማጋለጥ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ምርምር አደረገ። የአውሮፓ ታሪክ ፀሐፊዎች ሊያወሱት ስለማይፈልጉት ስለ ኢትዮጵያ መዋዕል፣ ስለ ግብፅ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ፣ ከፍተኛ ደረጃ ስለደረሰው የቲምቡክቱ ጥንታዊ ሥልጣኔ እያነሳሳ መጻፍ ጀመረ።

የአውሮፓ የሃይማኖት ሰዎች እና ምሁራን የራሳቸውን ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት መጽሐፍ ቅዱስን ሲጠቀሙበት፤ ጋርቬይና ጓደኞቹ ግን እንደ ኢትዮጵያና ግብፅ ያሉት ሃገሮች ታሪካቸውና ጥንታዊነታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፋ ያለ ቦታ የተሰጠው መሆኑን መስበክ ቀጠሉ። በመዝሙር ምዕራፍ 68 ቁጥር 31 “ልዑካን ከግብፅ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያም ወደ አምላክ እጆቿን ትዘረጋለች” የሚለው ጥቅስ ለጋርቬይ ብዙ መልዕክት ነበረው። በተለይም ኢትዮጵያ ከአውሮፓውያን ቀድማ የክርስትና ሃይማኖትን መቀበሏንና አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ይከፋፈሉ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች ሃገር መሆኗ በጋርቬይ ትምህርት ተሰጥቶበታል። ለዚህ ነበር ጋርቬይ በፃፋቸው ግጥሞችና ባደረጋቸው ንግግሮች የኢትዮጵያን ስም ጠቅሶ ማጠቃለል የቻለበት አንዱ ምክንያት። ለጋርቬይ አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ የጥቁሮች ሠንደቅ ነበረች።

 ስለ አፍሪካና ስለ ጥቁር ህዝብ ያካበተው አዲስ ልምድና ዕውቀትም የአፍሪካን ህዝብና ታሪኳን በመደገፍ እንዲጽፍ አደረገው። ይህም የአውሮፓ ታሪክ ጸሐፊዎች ስለ አፍሪካና ስለ ህዝቦቿ የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያጋልጥ አስቻለው። ከእነርሱ የተለየ የታሪክ አቀራረብ እንዳለም ጠቆመ። ለምሳሌም “African

“በተረፈ ግን “አምላክ” ጥቁሩን ሰው ሲፈጥር በጨለማ ጊዜ ስለነበር ነጭ መቀባቱን ስለረሳው ነው ጥቁር ሆኖ የቀረው የሚሉትን የነጭ ዘረኞች አባባል አትስሙ” ብሏል”

Times & Oriental Review” በሚል ጋዜጣ ላይ በ1913 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ የጻፈው እንዲህ ይላል። “እስኪ የሰውን ልጅ ታሪክ እንደገና እንገምግመው። ለመሆኑ ጥቁር ህዝብ ታላቅ ታሪክ የለውምን? የሚያኮራ የሰው ልጅ ታሪክ አልነበረውም? ዕውነተኛ የታሪክ ተማሪዎች፣ የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የቲምቡክቱ ሥልጣኔ ከአውሮፓና ከኤስያ ስልጣኔ ልቆ ይታይ እንደነበረ ያወሳሉ። አውሮፓ የሰው በላዎች፣ የአረመኔዎችና የሃይማኖት የለሾች መኖሪያ በነበረበት ወቅት፤ አፍሪካ የራሳቸው የሆነ የበለፀገ ባህል ያላቸው የጥቁር ህዝቦች መኖሪያ ምድር ነበረች” ይላል።

ጋርቬይ የፈለገውን ያህል በእንግሊዝ አገር መቆየት አልቻለም። አገር ቤት ያቋቋመው ማኅበር ከተለያዩ አቅጣጫ ተቃውሞ ስለደረሰበት፤ ማህበሩን ከመፍረስ ለማዳንና የትግል ጓዶቹን ለማበረታታት በቶሎ መመለስ ነበረበት። በ1914 ዓ.ም ወደ ጃማይካ ተመለሰ። እንደፈራውም ማህበሩን ለማፍረስ ያልተደረገ ሙከራ አልነበረም። ጋርቬይ እንደደረሰ አዲስ ስትራቴጂ አወጣ። ጥቁር ጃማይካውያንን እንደገና ማስተማር ማንቃትና ማደራጀት፣ በማህበራቸው እምነት እንዲኖራቸው ማድረግን ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ወሰደ። ለዚህም እንዲረዳ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የአፍሪቃ ብሔራዊ ሠንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር አወጣ። የባንዴራው ቀለም ጥቁር ቀይና አረንጓዴ ሲሆን፤ ጥቁሩ ቀለም የዓለምን ጥቁር ህዝቦች፣ አረንጓዴው የአፍሪካን ለምለም ሜዳና ሸንተረር፣ ቀዩ ደግሞ አፍሪካን ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትንቅንቅ የሚፈሰውን የአፍሪካውያን ደም እንዲወክል ተደረገ። የብሔራዊው መዝሙር ስም The Universal African Anthem እየተባለ ሲጠራ፤ የመዝሙሩ ግጥም በጥቂቱ ሲቀነጨብ እንዲህ ይላል።

 ኦ! ኢትዮጵያ!

 ኦ! ኢትዮጵያ!

የአማልዕክት ምርጫ ሰገነት

የዝናቡ ደመና ሲሰበሰብ በማታ

ሰራዊታችን በአሸናፊነት ሲገባ በዕልልታ

 ኦ! ኢትዮጵያ… ተዋጊው ጦሩን እየሰበቀ ሲመጣ

በቀይ ጥቁር አረንጓዴ ባንዴራ ሲመራ

አውቀነዋል

ድል የእኛ መሆኑን

የጠላት ኃይል

 ብትንትኑ መውጣቱን።

ኦ! ኢትዮጵያ…

ጋርቬይ የማስተማሩን ሙያ በደንብ ተያያዘው። ትምህርቱም ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የተጠናከረ የፍልስፍና መሠረት እየያዘ መጣ። የጥቁር ህዝብ ጥያቄ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአካባቢው ወጥቶ አፍሪካዊ መልክና አፍሪካዊ መልስ ማግኘት ጀመረ። ጋርቬይ “ጃማይካውያን ራሳቸውን አፍሪካውያን ነን ብለው መጥራት እስካልቻሉ ድረስ የበታችነታቸውን አምነው ተቀብለዋል ማለት ነው” ብሎ አስተማረ። ለምሳሌም ሚያዚያ 22 ቀን 1914 ዓ.ም በአንድ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ ባደረገው ንግግር፣

“ጃማይካውያንና ባርባዷውያን ራሳቸውን ዌስት ኢንዲያን ነን ብለው ይጠራሉ። አሜሪካ የተወለዱ ጥቁር ህዝቦች አሜሪካውያን ነን ማለት ይቀናቸዋል። የጥቁር ህዝብ የትም ይኑር የት፤ ራሱን አፍሪካዊ ነኝ ማለት እስካልደፈረ፣ በአፍሪካዊነቱ እስካልኮራ ድረስ ዝቅተኛነቱን አምኖ ተቀብሏል ማለት ነው። ይህ የተዛባ አቋማችን ነው የአውሮፓውያን መሳቂያና መሳለቂያ የሚያደርገን” ይላል። ጋርቬይ የህዝቡን ሞራል ለማነሳሳት እና የባህልና የኪነት ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የጥቁር ህዝብ የባህል ተቋም ለመክፈት አቀደ። ሆኖም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ተቋሙ በሥራ ላይ ሳይውል ቀረ። እየቆየም ከአባላት እና ከተከታዮቹ የሚያገኘው ትብብር እየቀነሰ መጣ። ምንም እንኳ ተቃዋሚዎቹ ለዚህ ማህበር መዳከም ተጠያቂዎች ቢሆኑም፤ የጋርቬይ ትምህርት ከህዝቡ ብሶት እና አጣዳፊ ከሆኑ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ጋር በቀጥታ አለመገናኘቱ ሌላው ምክንያት እንደነበር በጊዜው የነበሩ ተከታዮች ይናገራሉ። ይህ ሁኔታ ግን ጋርቬይን ጨርሶ ተስፋ አላስቆረጠውም። ገንዘብ ማግኘት እስከቻለ ድረስ ያሰበውን ተቋም ሊከፍት እንደሚችል አመነ።

በጊዜው አሜሪካ ውስጥ የራሱን የንግድ ሥራ አቋቁሞ መሰል ጥቁሮችን ስለሚረዳው ብሩከር ዋሽንግተን የሚባል ሰው ሰምቶ ስለነበር ከእሱ ጋር ደብዳቤ መጻጻፍ ጀመረ። ተስፋ የሚሰጥ መልስም አገኘ። ጋርቬይ ወደ አሜሪካ ሄዶ አብሮት ቢሰራና የሚፈልገውን ማህበር ቢያቋቁም ሊረዳው ዝግጁ መሆኑን አሳወቀው። ጋርቬይ አሜሪካ ለመቀመጥ ባይፈልግም፤ ለተወሰነ ጊዜ ሄዶ፤ የጃማይካውን ማህበር ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመመለስና በሚያጠራቅመው ገንዘብ ያቀደውን የባህል ማሰልጠኛ ተቋም ለማቋቋም ወሰነ። በዕቅዱ መሰረትም በመጋቢት ወር 1916 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ሄደ። ጃማይካን ከመልቀቁ በፊትም እንዲህ ሲል ተናገረ። “ጥቁር ህዝቦች ሆይ! ፊታችሁን ወደ አፍሪካ አዙሩ እና ተመልከቱ። አንድ የጥቁር ህዝብ ዘውድ ይጭናል፤ አዳኛችሁም ይሆናል” አለ።

 ጋርቬይ አሜሪካ ሲደርስ አገሪቱንና ህዝቧን እንዳሰበው ሆነው አላገኛቸውም። መጀመሪያ ሊያገኘውና አብረው ሊሰሩ የተስማሙት ብሩከር ዋሽንግተን፤ ጋርቬይ የአሜሪካንን አፈር ከመርገጡ ሁለት ወራት በፊት መሞቱን ሰማ። በዚህ ተስፋ ሳይቆርጥ፤ ማህበሩን በአስቸኳይ አቋቁሞ የድርሻውን ለማበርከት ተዘጋጀ። ለዚህ እንዲረዳውም ስለ ጥቁር አሜሪካውያን የኑሮ ሁኔታ ለማወቅ አሜሪካንን እየተዘዋወረ አየ። ብዙዎችንም በየቤታቸውና በመንገድ አነጋገረ። ስለ ማህበር ማቋቋም ጉዳይ፣ ስለ አፍሪካና ህዝቦቿ፣ እንዲሁም ስለ ራሳቸው እያነሳ አስተያየታቸውን መሰብሰብ ጀመረ።

ይሁን እንጂ የጥቁር አሜሪካውያንን የንቃት ደረጃ ሲገመግም ሙሉ በሙሉ ተስፋ ባያስቆርጠውም፤ ስለ አፍሪካና ስለ ቅድመ- አያቶቻቸው ምንም አለማወቃቸው፤ ከአሜሪካ ወጥተው እንደ ነጮች ወደ ሌሎች ሃገሮች አለመዘዋወራቸው፤ ስለ ሌላው ህዝብ የአኗኗር ሁኔታ ምንም ሀሳብ የሌላቸው መሆናቸውና፤ የራሳቸው የሆኑትን አፍሪካውያን እንኳ ዕርቃናቸውን ሆነው የሚዘዋወሩ አረመኔዎችና ከዛፍ ዛፍ እየተንጠለጠሉ ዝንጀሮ ሲነዱ የሚውሉ ሰው መሰል ፍጡሮች እንደሆኑ አድርገው መቁጠራቸው፤ ጋርቬይን ምን ያህል ከባድ ሥራ ከፊቱ እንደሚጠብቀው አስገንዝቦታል።

 ጋርቬይ አሜሪካ በሄደ በሁለተኛው ወር ቅርንጫፍ ማህበሩን በኒውዮርክና በተለያዩ ከተሞች ከፈተ። “Negro World” የሚል ልሳን እያተመ ማውጣትም ጀመረ። በስብሰባ አዳራሾችና የንግግር ቦታዎች እየተገኘ፤ ስለ ጥቁር ህዝብ አንድነት፣ ስለ አፍሪካና ታሪኳ፣ ስለ ጥቁር ህዝብ ብሶት እና ችግር እያነሳ ማስተማሩን ተያያዘው። የጋርቬይ ድምፅ ከጠረፍ ጠረፍ መሰማት ጀመረ። የተከታዮቹና የአባላቱ ቁጥርም እየጨመረ መጣ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የአባላት ቁጥር 4.5 ሚሊዮን ደረሰ። በጋዜጣው ላይ ጋርቬይ የጥቁር ህዝብ ዓላማ ምን መሆን እንዳለበት፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ፕሮግራሙ ምን መሆን እንደሚገባው መጻፍ ጀመረ።

ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ የአፍሪካውያን መሆኗንና የአፍሪካን ህዝብና ባህልም ከፍ ለማድረግ ራሳቸው አፍሪካውያንና፤ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሰበ።

 በጊዜው “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” ብሎ በፃፈው አጭር ግጥም ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።

አፍሪካ ለአፍሪካውያን፤

አባቶቻችን ያለሟት፣

 በእንባ በደማቸው ያቀኗት፣

 ዘሩ ሲዘራ በወራቱ፣

 እሸቱን ስናይ በወቅቱ፤

የተናፈቀው የአዝመራ ወራት ይመጣል፤

ጊዜውን ጠብቆ ከተፍ ይላል።

አፍሪካ ለአፍሪካውያን ….

ጨለማው ተገፏል

 ጎህ መቅዳጃ ሰዓቱ ደርሷል፤

 የከበደው ዳመና ያንዣብባል፤

አሁን ልውረድ፣

 አሁን ልዝነብ ይላል።

በተስፋ…..

ጋርቬይ ይሄንን ድል ያገኘው ያለምንም ተቀውሞ አልነበረም። በትግሉ ሂደት በጋርቬይ እና በማህበሩ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዷል። ተቃውሞውም ከተራ ስድብ እስከ ግድያ ሙከራ ድረስ ዘልቋል። ለአንዳንድ ወዳጅና ጠላታቸውን ላለዩ ጥቁር አሜሪካውያን ጋርቬይ ህይወቱን በከንቱ የሚያሳልፍ ቂል ሰው መስሎ ይታያቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች ጋርቬይን የመሰለ ጥሩ ጸሐፊ፣ ተናጋሪ እና ጎበዝ አደራጅ በዚህ ዕውቀቱ ትልቅ ደሞዝ እያገኘ ጥሩ በልቶ፣ ጥሩ ለብሶ መኖር የሚችል ሰው ሆኖ ሳለ፤ መድረክ ላይ ወጥቶ ስለ አፍሪካ ሲናገር በመዋሉና ራሱን በማስራቡ ከማዘን አልፎ እንባ እስኪወጣቸው ድረስ ይስቁ ነበር።

 አንዳንድ ግብዝ ጥቁር አሜሪካውያን ባለሙያዎችና ጠበቆችም የነበረውን የቀለም ልዩነት ጥቁሮችንና ነጮችን በማጋባት ማጥፋት ይቻላል ብለው ይከራከሩ ነበር። ለዚህም መፍትሔው የጋርቬይ ትምህርት ሳይሆን የነጮችና የጥቁሮች ጋብቻ በህገ መንግስቱ ውስጥ እንዲገባ መለስተኛ ትግል ማካሔድ ነው ብለው ያምኑ ነበር።

በዚህ እምነታቸውና ለነጮች ባላቸው ታማኝነት ምክንያትም ከነጮች የበለጠ የጋርቬይ ጠላት ሆኑ። ከነሱ አስተሳሰብ ብዙ ያልራቀና በጥቁሩ ምሁር በዶክተር ደቡዋ የሚመራ The National Association for the Advancement of Colored People (NAACP) የተባለው ማህበርም ተመሳሳይ ፕሮግራም ይዞ ቀረበ። ማህበሩ ጥቁርና ነጭ አባሎች ሲኖሩት ዶክተር ደቡዋ ጥቁር አሜሪካኖች ለሃገራቸው ማለትም ለአሜሪካ ታማኝና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንጂ የነጮችን የበላይነት ለመቋቋም ብቻ ሲሉ የህዝብን ሰላም ለመበጥበጥ የሚነሱ ዕብዶች አይደሉም እያለ መስበክ ጀመረ።

ጋርቬይንም ጥቁር ህዝብን ለማሳሳትና ለማጥፋት የተላከ ሰይጣን አድርጎ ያየው ነበር። አልተሳካለትም እንጂ ጋርቬይን የሆነና ያልሆነ ሰበብ እየፈለገ ከነጮች ጋር ሴራ እየጠነሰሰ ከአገር ተገዶ እንዲወጣ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። የአሜሪካ መንግስትም ቢሆን ይህ የጋርቬይና የማህበሩ እንቅስቃሴ ከመቼዉም የበለጠ እያሳሰበው መጣ። የመንግሥት ባለሥልጣኖች በጊዜው የነበሩትን አሥር ሚሊዮን ጥቁር አሜሪካውያን የሚሰበስብና አንድ የሆነ የወል አላማ የሚሰጣቸውን እንቅስቃሴ ማስቆም እንደተቀዳሚ ተግባራቸው አድርገው ወሰዱ። ማህበሩን በቀጥታ እንዲፈርስ ማድረግ በጊዜው የነበረውን ህገ መንግሥት መፃረር ስለሆነባቸው መጀመሪያ የማህበሩን የአመራር ቦታዎች በእነሱ ጥቅም አስጠባቂዎች የማስያዝ አዲስ ስትራቴጂ አወጡ። እነዚህ አድርባዮች ለጊዜው በማህበሩ አመራር ሰርገው መግባት ቢችሉም፤ ማህበሩ ቆይቶ ባካሄደው የአመራር ብወዛ ግን እንዲወጡ ተደርጓል።

ጋርቬይ ግን ዶክተር ደቡዋንና እሱን መሰል አድርባዮች ከማጋለጥ ወደኋላ አላለም። በአንድ በኩል እነዚህን የመንፈስ ደካሞችና ራስ ወዳዶች ሲተች፤ በሌላ በኩል ጥቁሮች በራሳቸው ዕምነት እንዲኖራቸው ማስተማሩን ቀጠለ። ጥቁር ሆኖ ከከርዳዳ ፀጉር ጋር መፈጠር ከሌላው ዘር እንደማያሳንስ፤ ጥቁር ህዝብ ራሱን በራሱ እስካላስከበረ ድረስ ማንም የማያከብረው መሆኑን አስገነዘበ።

ለምሳሌ ይሄንኑ በሚመለከት በ1919 ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በነፃነት አዳራሽ ተገኝቶ በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ተከታዮቹ ባደረገው ንግግር “ወንዶች ሆይ! ግድግዳ ላይ ያንጠለጠላችኋቸውን የነጭ ጌቶች ፎቶግራፎች በአስቸኳይ አንሱ። በምትካቸውም የጥቁር ሴቶችን ፎቶ አስቀምጡበት። እናቶች ሆይ! ለህፃኖቻችሁ ነጭ አሻንጉሊቶችን ወርውራችሁ እነሱን የሚመስሉ አሻንጉሊቶች ስጧቸው። ወንዶችና ሴቶች ሁሉ! አምላክ በአምሳሉ ፈጥሮናል። እኛን ጥቁር አድርጎ ከከርዳዳ ፀጉር ጋር ሲፈጥረን አንዳችም ስህተት አልሰራም። ሲፈጥረንም የአፍሪካን መልክዓ ምድር፣ ተፈጥሮ ሀብቷንና የአየር ጠባይዋን ለራሳችን ጥቅም እንድናውል ኃይልና ዕውቀት ሰጥቶናል።

 የእኛ አፍሪካን ለቆ መውጣትና በባርነት ቀንበር ሥር መኖር ያለፍላጎታችን ቢሆንም፤ የታሪክን ሂደት ጠንቅቀን ስንመለከት ኃይለኛው በደካማው ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ ይሄንን መሰል ኢሰብአዊ ድርጊት መፈፀሙ አዲስ አይደለም። በተረፈ ግን “አምላክ” ጥቁሩን ሰው ሲፈጥር በጨለማ ጊዜ ስለነበር ነጭ መቀባቱን ስለረሳው ነው ጥቁር ሆኖ የቀረው የሚሉትን የነጭ ዘረኞች አባባል አትስሙ” ብሏል። ይሄንን ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ ነበር፤ ከአንድ ጥቁር አሜሪካዊ በተተኮሱ ሦስት ጥይቶች እግሩ ላይ ቆስሎ ሐርለም ወደሚገኘው ሆስፒታል የተወሰደው። ተኳሹ ተይዞ ወደ እስር ቤት በተወሰደ በሁለተኛው ቀን “ራሱን ገደለ” ቢባልም፤ ከማን እንደተላከ ማወቅ ግን የሚያዳግት አልነበረም። ይህ የጠላት ድርጊትም ጋርቬይን የበለጠ እንዲቆርጥ እንጂ ከጀመረው ትግል እንዲሸሽ አላደረገውም።

ጋርቬይ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ማህበር ራሱን ከኢኮኖሚ ጥገኛነት ነፃ ካላደረገ በስተቀር የሌሎች መሳሪያ ሆኖ ይቀራል፤ የሚል ዕምነት ስለነበረው ጥቁር ህዝቦች በተቻላቸው መጠን እርስበርሳቸው እንዲረዳዱና ችግራቸውን በራሳቸው እንዲወጡ ማስተማሩን ቀጠለ። ሥራ ያላቸው ጥቁር አሜሪካውያን የሚያገኙትን ገንዘብ በጥንቃቄ እንዲይዙ፤ ሥራ የሌላቸው ደግሞ ሥራ እንዲፈልጉ መከረ። በጊዜው የነጭን ሆነ የጥቁር ሰራተኛ መብት እናስጠብቃለን በሚሉ የአሜሪካ ሶሻሊስት እና ኮሚኒስት ድርጅቶች እንዳይደለሉ አሳሰበ። ይህ አቋሙ ግን ከኮሚኒስቶች ከፍተኛ ተቃውሞ አስከተለ።

ድርጅቶች ጋርቬይን ፀረ-ኮሚኒስትና የጥቁር ሰራተኞችን ሊበዘብዝ ከከበርቴዎች ጋር ውል የተፈራረመ አድሃሪ ነው፤ ብለው አወገዙት። ጋርቬይ ግን ፀረ-ኮሚኒስት አለመሆኑን አስረዳ። ይሁንና የትግል ቅድሚያ አሰጣጥ ልዩነት በእሱ ማህበር እና በኮሚኒስቶች መካከል እንዳለም ነገራችው። በጊዜው የነጭ ሰራተኞች አንገብጋቢ ጥያቄ ከከበርቴው ጋር ተደራድሮ ኑሯቸውን ማሻሻል ሲሆን፤ የጥቁር ሰራተኞች ጥያቄ ግን በቀላሉ ይወገዳል የማይሉት የዘረኝነት ጥያቄ መሆኑን አብራራ።

ጋርቬይ ማህበሩ የምጣኔ ሀብት መሰረት ያለው ህብረተሰብ ከፍተኛ የፖለቲካ ተደማጭነት ይኖረዋል ብሎ ያምን ስለነበረ በአሜሪካም ሆነ በአፍሪካ ያሉ ጥቁር ህዝቦች በኢኮኖሚ ራስን የመቻሉን ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጡት ማበረታታት ቀጠለ። ማህበሩም አንዳንድ ተጨባጭ ሥራዎችን መሥራት ጀመረ። ለምሳሌ ለዚሁ ዓላማ እንዲረዳና በተለያዩ አህጉራት የሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች እንዲገለገሉበት ከአባላቱ ባሰባሰበው ገንዘብ አንድ የመርከብ አገልግሎት አቋቋመ። የጥቁር ኮኮብ የባህር አገልግሎት የተባለው ድርጅት ከአፍሪካና ከዌስት ኢንዲስ ሙዝ፣ ብርቱካንና ሌሎች ጥቁር ነጋዴዎች የሚያስጭኗቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ክፍያ እንዲጭን ማድረግ ነበር። በተጨማሪም ወደ አፍሪካ ለመመለስ የሚፈልጉ ጥቁሮችን ቢቻል በነፃ አለዚያም በመጠነኛ ገንዘብ እንዲያጓጉዝ ማህበሩ ወሰነ።

ይህ የማህበሩ አዲስ ስትራቴጂ ከግለሰቦች አንስቶ እስከ መንግሥት ድረስ ያለውን የጠላት ኃይል እንደገና ቀሰቀሰው። ነጭ ገበሬዎች ጥቁሮቹ ሰራተኞች ወደ አፍሪካ ቢመለሱ የጀመሩትን እርሻ ዳዋ እንደሚበላው ታያቸው። የፋብሪካ ባለቤቶች በርካሽ ዋጋ የሚገዙት የጥቁሮች ጉልበት ተነቅሎ ወደ አፍሪካ ቢሄድ፤ ፋብሪካቸው ወና ሆኖ የሚቀር መሰላቸው። ነጯ የቤት እመቤትም እየደበደበች የምታሰራትን ጥቁር ሴት ከፊቷ ማጣት የማትችለው ሆኖባት ጭንቅ ገባት። ጥቁር አድርባዮችና ራስ ወዳዶችም የመምራት ዕድል እናገኝ ይሆናል ያሉትም የጥቁሮች ወደ አፍሪካ መጓዝ ባዶ ሜዳ ላይ ያስቀራቸው ስለመሰላቸው የሚይዙ የሚጨብጡትን አጡ። በአጭሩ ይህ የማህበሩ ውሳኔ የነጮችንም የአድርባዮችንም ቤት አንኳኳ። የመርከብ ባለቤት የነበሩ ነጮችም በአነስተኛ ዋጋ ለመጫንና ለማጓጓዝ የተቋቋመው የጥቁሮች መርከብ ተቀናቃኝና ተጫራች ሆኖ መቅረቡ በጣም አስደነገጣቸው። ይህን የማህበሩ ፖሊሲ ለማክሸፍም ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም። የማህበሩ ዕቅድ በሥራ ላይ በዋለ በ6 ወራት ውስጥ ብዙ ለውጥ ታየ። ጥቁር አሜሪካውያን ከፍተኛ የሆነ የለውጥ እንቅስቃሴ አካሄዱ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ የተሰማሩት ስድስት መርከቦች ቀንና ማታ መስራት ጀመሩ። ወደ አፍሪካ ለመመለስ የተመዘገበው ሰው ቁጥር ብዛት ነጮችን ብቻ ሳይሆን ጋርቬይንና ማህበሩን በጣም አስገረማቸው።

 በዚህ ፕሮግራም ምክንያት አሜሪካ ውስጥ ከፍተኛ ሽብርና ድንጋጤ ተፈጠረ። የአሜሪካ ኮንግሬስ ጋርቬይንና ማህበሩን ከዚህ ተግባር ለማስቆም ወሰነ። የማህበሩ ጽ/ቤቶች ለጊዜው እንዲዘጉም አደረገ። ጋርቬይን በህዝብ መካከል ጥላቻ ፈጥረሃል፤ ጥቁር አሜሪካውያንን ለአመጽ አደራጅተሃል፣ መሳሪያ ደብቀሃል፣ የመርከቡን ኩባንያ ስታቋቁም ለመንግሥት መክፈል የሚገባህን ታክስ አልከፈልክም ብለው ከሰው፤ ያለዋስ እንዲታሰር አደረጉ። ከሳሽ የአሜሪካ መንግሥት ሲሆን፤ ምስክሮች ደግሞ እንደነ ዶ/ር ደቡዋ ያሉ ጠላቶቹ ነበሩ። በመጨረሻም ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ፤ ግንቦት 16 ቀን 1925 ዓ.ም በጋርቬይ ላይ 5 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወደ ቶምብ እስር ቤት ተላከ። ጋርቬይ “ጥፋተኛ አይደለሁም” ብሎ ከአንዴም ሁለቴ ይግባኝ በማለት ያልተሳካ ሙከራ አደረገ።

በጋርቬይ መታሰር ምክንያት ብዙ ትርምስ ተፈጠረ። ማህበሩም እንደፈለገ መሥራት አልቻለም። ይሁን እንጂ የማህበሩ አባላት በመሪያቸው መታሰር ከፍተኛ ተቀውሟቸውን አሰሙ። ሰብአዊ ድርጅቶችም የተቃውሞ ድምፃቸውን አስተጋቡ። የአሜሪካ ኮሚኒስት ፓርቲም ከጋርቬይ ጋር በጊዜው የነበረውን ልዩነት ትቶ፤ የእሱን በአስቸኳይ መፈታት ጠየቀ። እነ ዶ/ር ደቡዋ ግን ጋርቬይን ቢቻል በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ካልተቻለ ደግሞ የአምስት ዓመት እስራቱን እንዲጨርስ ከዚያም ወደመጣበት ሃገር ወደ ጃማይካ እንዲባረር የአሜሪካን መንግሥት መወትወት ቀጠሉ።

 በመጨረሻም ጋርቬይ ቶምብ እስር ቤት ውስጥ ሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት ካሳለፈ በኋላ ተፈትቶ የአሜሪካንን አፈር ለቆ እንዲወጣ ተደረገ። ጋርቬይ በህዳር ወር 1927 ዓ.ም የአሜሪካንን ኒው ኦርሊያንስ ወደብ ለቆ ወደ ጃማይካ ተመለሰ። ወደቡን ለቅቆ ሲሄድ ባደረገው ንግግርም እንዲህ አለ።

 “የአፍሪካ ልጆች ሆይ! አይዟችሁ! በዚህ ጊዜያዊ በሆነ ጥቃት ተስፋ አትቁረጡ። በአፍሪካ የምትታየን የጠዋት ፀሐይ ዓለምን ሁሉ ታለብሳለች። የብርሃኗ ፍንጣቂ አዲስ ህይወት ታመጣልናለች። በህይወት እስካለሁ ድረስ ለህዝቤ የገባሁትን ቃል ኪዳን ለመፈፀም ወደኋላ አልልም። አይዟችሁ! ታገሉ ለመብታችሁ ቁሙ።”

በወደቡ ተሰብስበው ሊሰናበቱት የመጡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተከታዮቹ በሀዘንና በብስጭት ስሜት (ብዙዎችንም እንባ እየተናነቃቸው) እንዲህ ሲሉ ዘመሩ።

 የፍጡራን ሁሉ አባት፣

የኃያላን ኃይል ኩራት፣

የሁሉም ሰው የበላይ ነው፣

 አምላክ መሪያችንን ባርከው

 ማርከስ ጋርቬይን

ወደ ድል ጎዳና ምራው

 ሁሌ ከአደጋ ጠብቀው፣

 የሚመኘውን ሁሉ ስጠው

 ፈጣሪ መሪያችንን ባርከው

ማርከስ ጋርቬይ

 የአፍሪካ ልጅ ነው ከልቡ፣

 ጥርጣሬ የለም በሆዱ፣

 እንደሰዎች እንኳ ክፋት የለው

 አምላካችን መሪያችንን ባርከው

 ማርከስ ጋርቬይ።

ጋርቬይ በተወለደባት ደሴት ጃማይካ ከደረሰ በኋላም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ ታከተኝ ብሎ ትግሉን አላቆመም። አሜሪካ ትቶት ከመጣው ማህበር ጋር መጻጻፉን ቀጠለ። ከጥቂት ወራት በኋላም ወደ ላቲን አሜሪካ ሀገራት ለመሄድና ዜጎቹን ለማበረታታት ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ የመግቢያ ቪዛ በመከልከሉ ፕሮግራሙን መሰረዝ ግድ ሆነበት። ከአንድ ዓመት በኋላም በሚያዚያ 1929 ዓ.ም ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄደ። ከአፍሪካውያን ጋር የጥናት ክበብ አቋቁሞ ለአፍሪካ የነበረውን ዕውቀት ማስፋፋት ጀመረ። ለጥቁር ህዝብ ምን መደረግ አለበት? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ሰፋ ያሉ ውይይቶች አካሄደ። በተለያዩ አዳራሾች እየተገኘ ንግግር አደረገ። ከዚያ ወደ ፈረንሳይ ሄደ። በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ውስጥ ስለሚገኙ አፍሪካውያን በመጠኑም ቢሆን (የቋንቋ ችግር ይግጠመው እንጂ) ማንበብ ቻለ።

ጉዞውን በመቀጠልም በጄኔቭ፣ በበርሊንና በሌሎች የአውሮፓ ከተሞች እየተዘዋወረ ተመለከተ። በጃማይካ እያለ “Black Man” የሚል ጋዜጣ እያተመ ማውጣት ጀምሮ ነበር። ሆኖም ከሁለት ወራት በኋላ በጊዜው የነበረው የህዝቡ እርዳታ ስላላበረታታው በ1935 ዓ.ም እንደገና ወደ እንግሊዝ አገር ሄደ። እንግሊዝ አገር በነበረባቸው ዓመታት ውስጥ፤ በጊዜው ሞንትሪያል (ካናዳ) ይደረጉ በነበሩት ከሶስት ያላነሱ የUnivesal Negro Improvement Association ጉባኤዎች ላይ በመገኘት ጉባኤዎችን በሊቀ-መንበርነት መርቷል። ጋርቬይ እንግሊዝ አገር በነበረበት ወቅት ነበር ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የወረረችው።

ጋርቬይ ይሄንን የፋሺሽት ወረራ ተቃወመ። ለመናገር አጋጣሚ ባገኘበት ቦታ ሁሉ ኢጣሊያን አወገዘ። የተወረረችው ሃገርም “የነፃነት ፋናና የአፍሪካ እምብርት ነች” እያለ ሲመካባት የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗም ብስጭቱን እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጎታል። ጋርቬይ ለዚህ ወረራ ሁሉ ተጠያቂ ፋሽስት ጣሊያን ነች ብሎ ቢያምንም፤ በጊዜው የነበሩት የኢትዮጵያ ንጉስም  ከባድ ጥፋት እንደፈፀሙ ይናገራል። ለምሳሌም በለንደን ከተማ አልበርት አዳራሽ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር እንዲህ አለ።

 “እኔ ለንጉሥ ኃይለሥላሴ ክፉ አይደለሁም። የሚያሳዝነው ግን፤ የአውሮፓን ተንኮል ማወቅና መሶሎኒ አመቺ ሰዓቱን ጠብቆ ኢትዮጵያን ለመውረር እንደተዘጋጀ መረዳት ተስኗቸው፤ አስፈላጊውን የጦር ዝግጅት ባለማድረጋቸው ሃገሪቱንና ህዝባቸውን በፋሽስት ጦር ማስጨፍጨፋቸው ነው። በነበረችው አጭር ጊዜ እንኳ ሊደረግ ይገባው የነበረውን የጦርነት መሰናዶ ከማከናወን ይልቅ ኢትዮጵያን በፀሎት ለማዳን አምላክን መማፀንና ታቦታትን ማስቸገር መጀመሩ በአውሮፓውያን ዘንድ መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን አድርጎናል”

በቀድሞው ንጉሥ ቅር የተሰኘ ጋርቬይ ብቻ አልነበረም። ኢትዮጵያ በጣሊያን እንደተወረረች ኒውዮርክ የሚገኙ የጋርቬይ ተከታዮች ሐርለም ውስጥ ገብተው የነጮችን በተለይ የጣሊያን ነጮች ንብረት የነበሩ ሱቆችንና ግሮሰሪዎችን አቃጠሉ።

ጋርቬይ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1940 ዓ.ም በጥር ወር በጠና ታመመ። ለተወሰኑ ወራት ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ከቆየ በኋላ ባደረበት የአእምሮ ህመም ምክንያት፤ በተወለደ በ57 ዓመቱ ይህችን ዓለም በስጋ ሞት ተሰናበተ። ለጥቁር ህዝብ ነፃነት ስትበታተን የኖረች ነብሱ ዕረፍት አገኘች። አፍሪካና ልጆቿም ታላቅ መሪያቸውን በማጣታቸው ደነገጡ፤ ሀዘንም በረታባቸው። በጊዜ ሂደት ትውልድ ይተካካል። ከእሱ ህልፈት በኋላ የመጡት የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች ሆኑ የጥቁር ህዝብ መሪዎች፤ ጋርቬይ ለጥቁር ህዝብ የነፃነት እንቅስቃሴ ያደረገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንና፤ ያካሄደው ትግልም በጥቁር ህዝብ ታሪክ ላይ ህያው ሆኖ እንደሚኖር ይናገራሉ።

 ማርቲን ሎተር ኪንግ በ1960 በጋርቬይ መቃብር አበባ ካስቀመጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤

 “ማርከስ ጋርቬይ የጥቁርን ንቃት ከፍ በማድረግ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሰው ነው። ለመጀመሪያ ጊዜም ጋርቬይ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ አፍሪካውያንና ጥቁር አሜሪካውያን ተዋርዶ የነበረውን ክብራቸውን አድሶ እንደገና እንዲጎናፀፉት አድርጓል፤” ብለዋል። የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ኩዋሜ ንክሩማህም አክራ ላይ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ህዝብ ጉባኤ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ “በዚህ ጉባኤ ከባህር ማዶ የመጡ ወንድሞቻችን በመካከላችን ይገኛሉ። እነዚህ የአፍሪካ ልጆች አፍሪካን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ትግል አፍሪካውያን የማይረሱትን መስዋዕትነት ከፍለዋል። ይህንን ስናገር በሃሳቤ ያለው ታላቁ የነፃነት ታጋይ ማርከስ ጋርቬይ ነው። አንዳችንም እንኳ አፍሪካዊነትና የዘር ልዩነት የሚለው ትርጉም ሳይገባን ጋርቬይ ግን ከሁላችንም ቀድሞ ያወቀውና፤ ለዚሁ ዓላማው ሲታገል የሞተ አንጋፋ መሪያችን ነው” ሲሉ  ታላቅነቱን መስክረዋል።

የዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኬኒት ካውንዳና፤ የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዝዳንት ጀሞ ኬንያታም፤ አፍሪካን ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ለማውጣት ባደረጉት መለስተኛ ትግል ጋርቬይ ትልቅ አርአያቸው እንደነበር ተናግረዋል።

“እነሆ ዛሬ ማርከስ ጋርቬይ የጃማይካ መዲና በሆነችው በኪንግስተን ከተማ ትልቅ ሀውልት ተሰርቶለት በራሱ ስም በተሰየመ አደባባይ ላይ ቆሟል። በመልካም ተግባር “ስም ከመቃብር በላይ ይውላል” ይሏል ይህ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top