ቀዳሚ ቃል

ጥበብ የሚቀዳው ከምንጩ ነው

ጥበብ በተግባሯ ከማዝናናት፣ ከማሳወቅና ማስተማር ባለፈ፤ ለስኬታማ ማህበራዊ መስተጋብር ትልቅ ዋጋ አላት። ማንነት በጥበባዊ ስራ ውስጥ ይገለፃል። በጥልቁ ሲታሰብ በማናቸውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥበብ የሚኖራት ፋይዳ የላቀ ነው። የጎበጠው እንዲቃና፣ የተበላሸው አንዲስተካከል፣ የደበዘዘው እንዲፈካ፣ የላላው እንዲጠብቅ፣ የደከመው እንዲበረታ የማድረግ ኃይል አላት።

 ጥበብን የሚጠበቡ ተዋንያን፣ በማህበረሰባችን ዘንድ ክብር አላቸው። የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ማንነት እንደመስታወት ሆነው በስራዎቻቸው ሲያንፀባርቁ፤ እኩዩ ከሰናይ የሚለይበትን አግባብ ይፈጥራሉ፤ ያሳያሉ። የማህበረሰቡ ማንነት መታያ አብነት ወይም ሞዴል ናቸውና ማህበረሰቡ ሊያጣቸውና ሊርቃቸው አይፈልግም።

 በተለያዩ ወቅቶች በጥበብ ስራዎቻቸው የገነኑ፤ የሚደነቁና የሚከበሩ አርቲስቶች ከሀገር ወጥተው ሲቀሩ ተስተውሏል። ያለመመለሳቸው ምክንያት በአገራዊ ሁኔታ ያለመመቸት፣ የተሻለ ኤኮኖሚ አቅም የመፍጠር ፍላጎት ወዘተ ምክንያቶች ሊሰጡ ቢችልም፤ የጥበብን ዋጋ ከፍ ለማድረግ ግን የጥበብ ሰዎች ከአገራቸው፣ ከቀያቸው፣ ከቋንቋቸው፣ ከባህላቸው፣ ከታዳሚዎቻቸው ልርቁ አይገባም። የጥበብ ምንጩ ያለው የተወለዱበት፣ ያደጉበት ከመሆኑ አንጻር የፍላጎታቸው ተሟልቶ በአገራቸው ቢኖሩ ይመረጣል።

 ለበርካታ ዓመታት በውጪ ሲኖሩ የነበሩ አርቲስቶቻቸን በአገሪቱ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ አገራቸው በመመለስ ከአድናቂዎቻቸውና አክባሪዎቻቸው ጋር እየተቀላቀሉ ነው። ሕዝቡ ባሳየው አቀባበል ምን ያህል ለዚህች አገር እንደሚጠቅሙ የተገነዘቡት አጋጣሚ ይመስለናል። አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆና ሌሎችም አርቲስቶችቻችን በተደረገላቸው አቀባበል የተስተዋለው ይኸው ነው።

 ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሌሎችም ወደ አገራቸው በመመለስ፤ ባመቻቸው ሁሉ የጥበቡን ዘርፍ ቢያሳድጉ መልካም እንደሆነ ይሰማናል። በሕዝብ ይሁንታና ጭብጨባ ያደጉ አርቲስቶቻችን ከተሰደዱ ጥበብ ይነጥፋል፤ መድረክ ይራቆታል፤ ተደራሲም ይራባል። ይህ እንዳይሆን ደግሞ በሙያው ሊያገኙት የሚገባው ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሙያዊ ኃላፊነትና አገራዊ ስሜት ግን ሊገዛቸው ይገባል።

 ውድ አንባቢዎቻችን በዚህ ዕትማችን አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆ እንግዳችን ነች። ስለጥበባዊ ሕይወቷ፣ ስለ ሕዝቡ አቀባበልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ታወጋናለች። ሌሎች በምሁራን የሚቀርቡ የታሪክ፣ የባህልና የጥበብ ጉዳዮችንም ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top