ማዕደ ስንኝ

ይወለዳል

ይወለዳል አዲሱ ሰው…

ባዲስ ዘመን

ባዲስ ፍኖት እየተጓዝን

አብረን ሁነን

አብረን ኑረን፤

ይወለዳል ኢትዮጵያዊው…

የኩሽ ሞገስ

የሴም ጥንስስ

ያገር ጋሻ ያለም ተስፋ

እውቀት ጥበብ የሚያሰፋ፤

ይወለዳል አዲሱ ሰው…

ባዲስ ምእት

ባዲስ ሥርዓት

ባዲስ ብሥራት

ይወለዳል ኦሞቲኩ፤ ይወለዳል ኒሎቲኩ

አጋር ጌጡ፥ ለሴም ኩሹ፣

በየፊናው በየመስኩ፤

ይወለዳል ኢትዮጵያዊው…

ያ ሣባዊው ያ ጥንታዊው

ባዲስ ዘመን ባዲስ ምዕት

ባዲስ ንጋት ባዲስ ጥባት

ይወለዳል መመኪያችን

ኢልማ ቢያ፥ አባቢያ የጦቢያችን

የካም አበው ወራሻችን… አሻራችን፤

ይወለዳል አዲሱ ሰው…

በክልዔቱ ሚሊኒዬም ምትካችን

ባለታሪክ፥ ባለእምነት ቀዬ ጠባቂያችን

ይወለዳል ሳይንቲስቱ

ሃኪም መንዲስ ላገሪቱ…

ይወለዳል ጥበበኛው

ባለመቃ ባለሸራ አዚመኛው…

ይወለዳል ብእረኛው ጋዜጠኛው

ቆላ ደጋ ተወርዋሪው፤

ይወለዳል ያ ጀግና ሰው

አገር ድንበር የሚሰዋው

ባርበኝነት የምንጠቅሰው

በቁርጡ ቀን የምንጠራው፤

ይወለዳል ባዲስ ዘመን

ባዲስ ሥራት አዲስ ወገን

ይወለዳል አዲሱ ሰው፣ ባዲስ ንጋት

ባዲስ ጀምበር፣ ባዲስ መዓልት፤

ይወለዳል በክልዔቱ

ባሥር መቶው ዓመታቱ

ፍቅር አንጋሽ ሰማእቱ

ያንድነት አውድ መሠረቱ

የቃል ኪዳን ቀለበቱ

የናት አገር ’ርስተ ጉልቱ፤

ይወለዳል ኢትዮጵያዊው…

ስምን ተግባር የሚያወጣው

ረሃብ በሽታን የሚረታው፤

ይወለዳል አዲሱ ሰው

ባዲስ ንጋት ባዲስ ጀምበር

ባለታሪክ ባለማ’ረግ ባለአገር፤

ይወለዳል አዲሱ ሰው

ይወለዳል…

ሐምሌ 18 ቀን 1999 ዓ.ም.

ሂዩስተን – ቴክሳስ፣ ሰሜን አሜሪካ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top