ጥበብ በታሪክ ገፅ

የኦሮሞና አማራ ድመራ በአባይ (ግዮን)-ትውፊት

በአባይ -ግዮን ትውፊት፣ ኦሮሞና አማራ እንዴት እንደሚደማመር ለማውሳት በቅድምያ ስለ አባይና ትውፊቱ ጥቂት ማለቱ ያግዛል። ነገረ አባይ ከሚገመተው በላይ ጥልቅ፣ ረቂቅና ውስብስብ ሆኖ፤ በብሉያን ግሪኮች አምነት ውስጥ የገዘፈ ስፍራ ይዞ፣ ከአራት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንደድንቅና ብርቅ አስከብሮ ያስፈቀረ ነው። ቢሉያን ግሪኮች ክርስትና ከመፈጠሩ በፊት አምልኳቸውን የመሰረቱት በአስራ ሁለት አማላክት አመራራር ( አንደ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አይነት ነገር) ሲሆን ሊቀ-አማልክቱም ዚዩስ ነበር።

 ሊቀ አማልክት ዚዩስ ጥሎበት ከዚያ ሁሉ፤ የአለም ሀገሮችና ህዝቦች በላይ፤እንዲያውም ከሚገዛው ግሪክና ህዝቡ ይበልጥ የሚያፈቅረውና የሚያከብረው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እንደነበረ ጥንታዊ ጽሑፎች ያመለክታሉ። በአለም የስልጣኔ አንደኛ እርከን ላይ ይገኙ የነበሩት እነዚያ ግሪኮች ኢትዮጵያ ሲሉ የትኛውን ስፍራ እንደሆነም አጥርተው የጠቆሙ ናቸዉ። ዩሮፒዲስና አናክሳጎረስ የተባሉ ሊቃውንቶቻቸው ኢትዮጵያ የምትባል አገር የአባይ ግዮን ወንዝ የሚመነጭባት፤ መንጭቶም ወደ ግብጽ የሚጓዝበት የጥቁር ህዝቦች ሀገር አንደሆነች ጽፈዋል። ሊቁ ሆሜር ከዛሬ 2 ሺህ 800 አመት በፊት እንዳመለከተው ደግሞ፤ ኢትዮጵያ የሊቀ አማልክቱ የዜዩስ ልዩና ቅዱስ ምድር አንደሆነች፣ አማልክቱም (በተለይ የሊቀ አማልክቱ የዜዩስ ወንድም እና የባህር አምላክ ፖሲደን /ኔፕቱን ) ከማንኛውም ስፍራና ህዝብ በላይ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባላቸው ፍቅር እራሳቸውን ወደተራ ምድራዊ ሰውነት ዝቅ አድርገው፣ በዚህች ምድር ዘወትር በሚጣለው ግብር እየታደሙ ‹ተሀድሶ› ያደርጉ ነበር። ከዚያም አልፎ፣ግሪኮች አማልክቶቻቸውን እጅግ ውብ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ንግስታትና ልእልቶች ጋር (አንደ እቴጌ ካሲዮጵያና ልእልት አንድሮሜዳ ካሉ፣ የውበት አማልክት ከሆነችው አፍሮዳይት እንኳ በቁንጅና ከሚበልጡ ጋር) በግብረ ስጋ እያገናኙ ጀግኖቻቸውን፣ መሪዎቻቸውን፣ ሊቃውንቶቻቸውን ፈጥረውባቸዋል። አባይ ስለሚፈልቅባት ስለዚህች አገረ ኢትዮጵያ ክብርና ሞገስ ከዛሬ 2 ሺህ10 አመት በፊት በብሉይ ኪዳን፣ ከዚያም በኋላ በነብዩ መሀመድ አንደበት ብዙ ብዙ የተባለ ቢኖርም ለስፍራና ጊዜ ቁጠባ እዚህ ላይ ልታቀብ።

እንዲህ ያለውን የአባይ ዝና የሰሙ፣ግብጽን በመስከረም የድርቅ ወቅቷ በታላቅ ፍሰትና ነፍስ አድን ደለል የሚያለመልማትን ወንዝ የተመለከቱ የአለም ታላለቅ ሰዎች የወንዙን ምንጭ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት እያደረባቸው ብዙ ምእተ አመታት ባዝነዋል። ግሪካዊው ታላቁ የታሪክ ሊቅ ሄሮዶተስ ከክርስቶስ ልደት 453 አመት አስቀድሞ፣ ለረጅም ጊዜ በአሰቸጋሪ ባህር ላይ ተጉዞ አስዋን ደርሶ ሲታክተው ተመልሷል። የፐርሺያ ንጉስ ዳግማዊ ካምቢስስ ሙሉ ሰራዊቱን እየመራ ገስግሶ አብዛኛውን ሰራዊቱን በረሀ አስበልቶ የጓጓለትን የአባይ ምንጭ ሳያይ ተመልሷል። ክርስቶስ ከመወለዱ ከ60 ዓመት በፊት ሮማን ይገዛ የነበረው ንጉስ ኔሮ ከፍተኛ ጦር እየመራ ነጭ አባይ ከደረሰ በኋላ በረግረግ ተከትሮ ተመልሷል። ታላቁ የስነ ምድርና ስነ ፈለግ ተመራማሪ በጦሎሜዎ እንዲሁ ሞክሮት፣ አባይ ከጨረቃ ተራራዎች መሀል የሚፈልቅ እንደሆነ መላምት ሰንዝሯል።ታዲያ በዚያን ዘመን አንድ ከባድና የማይታለም ነገርን ለመግለጽ ሲፈለግ ‹የአባይ ምንጭን እንደመፈለግ ከንቱ ልፋት› ይባል ነበር።

 ከምእተ አመታት በፊት፣ ‹በድብቅ የኢትዮጵን ድንበር ሾልኮ ወደሀረር ከተማ የዘለቀ የመጀርያው አውሮፓዊ› ተብሎ ከፍተኛ ዝናን ያተረፈውሪቻርድ በርተን የተባለ ወታደር በእንግልጣሩ የብሪቴይን ሮያል ጂኦግራፊካል ሶሳይቲ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ፣ ሰፔክ ከተባለው አሳሽ ጋር በመሆን ነጭ አባይ ደረሰ። ‹ቀዳሚው ነጭ አባይ አግኚ እኔ ነኝ› በሚል ተጋጩና፣ አገራቸው ላይ ህዝብ ፊት ሊሟገቱ ቀጠሮ ይዘው ግዮን ሳይደርሱ ተመለሱ። ሪቻርድ በርተን ከስፔክ ይልቅ አንደበተ ርቱእ ስለነበረ የሙግቱ አሸናፊ ማን ሊሆን እንደሚችል ለመተንበይ አዳጋች አልነበረም። በሙግቱ ግጥሚያ እለት ግን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጠረ። ስፔክ ሞተ። ዘመዶቹ፣ ስፔክ የሞተዉ ጠመንጃዉ ባርቆበት ነው ይላሉ። ሌሎች ደግም ሰፔክ ሪቻርድ በርተንን በሙግት የማሸነፉ ጉዳይ አጠራጥሮት፣ ህዝብ ፊት ከምዋረድ ብሎ ጥይቱን እንደጠጣዉ ይጽፋሉ።

 የአባይ ግዮንን ምንጭ ለማግኘት የተሳካለት ስፓኒሻዊው የካቶሊክ ቄስ አባ ፔድሮ ፓኤዝ ነው። በ1610 ዓ.ም። (ፈረንጅ እንዲህ ብሎ የጻፈውን እንዳለ በማስፈሬ እኔው ራሴ ውጉዝ ከመአርዮስ! ከእልፍ አእላፍ ዘመናት በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ያወቀውን እንዳላወቀና፣ፈረንጅ የበላይነቱን ሊያረጋግጥብን የአባይ ምንጭ ለመጀመርያ ጊዜ በአውሮፓዊ እንደተገኘ ያስተማሩንን እንዳለ በመገልበጤ)። እንዲያውም ጥንት ጥንት ምንጩን አይተው ‹ግሽ አባይ› ሲሉ የሰየሙት ቅዱስ ዘራብሩክ እንደሆኑ ይታመናል። ቅዱስ ዘራብሩክ ማየት የተሳናቸው ሆነው ተወለዱ። በሰባት አመታቸው ከመሬት እንቁ አገኙና ዋጡ። ወዲያው አይናቸው በራ። ቅዱስ መንፈስ ሰርጾበቸው በአካልም በመንፈስም አጸናቸው። ሰውነታቸው በብርሀን አብረቀረቀ። በጾም በጸሎት እና በበጎ ምግባር ብዛት ቅድስናን ተጎናጸፉ። መላእክት በሁለቱ ትከሻዎቻቸው ላይ ስድስት ስድስት ክንፎችን አበቀሉላቸው። በሚፈጽሙት ኦርቶዶክሳዊ ተአምራት የቀናው ካቶሊካዊው ንጉስ እንዲታሰሩ አዘዘ። ይህ ሲታያቸው የጸሎት መጻህፍታቸውን በግሽ አባይ ምንጮች ውስጥ ጣሉ። እሳቸውም ለብዙ አመታት በጨለማ ውስጥ ታሰሩ። ከእለታት አንድ ቀን ግን ሀይለኛ ቀስተደመና እስር ቤቱ ላይ አረፈ። የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ይህን እንዳዩ ተደናግጠው ፈቷቸው። ቅዱስነታቸውም ወደምንጮቹ ደርሰው ፣‹ግሽ አባይ..አባይ መጻህፍቴን ወደላይ ትፋቸው› አሉ። እንዳሉትም ሆነ። በአምስት አመት የእስራታቸው ጊዜ በውሃ ተዘፍዝፎ የቆየው መጽሐፍ ምንም ሳይርስ፣ ከነአዋራው ነበር ከእጃቸው ያረፈው። ይህን ተአምር ሰከላ ደርሶ ከግሽ አባይ ጠበል አጠገብ የቆመ ምእመን ዛሬም ከካህናቱ ያዳምጣል።

 ፔድሮ በመጀመርያ የሰርጸ ድንግል ወንድም ልጅ የሆነውን ወጣቱን ንጉስ ዘ ድንግልን (አጤ አጥናፍ ሰገድን) እና እቴጌ አናቱን አባብሎ አስኮተለካቸው። ቀጥሎም ሱስንዮስን አስኮተለከው። ፈላጭ ቆራጭ ባለሟል ሆኖ ቀሳውስቱንና ካህናቱን አሳደደ። በንጉሱ መሪነት ሚያዝያ 1610 ዓ.ም ግሽ አባይ ደርሶ የአባይን ምንጭ ሁለት ጉድጓዶች ተመለከተ። በደስታ ሰክሮ ፎከረ። ‹የፐርሺያ ነገስታት ቆጵሮስ እና ካምቢስስ፣ታላቁ አለክሳንደር፣ዝነኛው ጁሊየስ ቄሳር ሊያገኙት ያልቻሉትን እኔ ፔድሮ ፓአዝ አሳካሁት› እያለ እንደ እብድ ፈነደቀ። እውነትም ሊፈነድቅ ይገባዋል። ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ አመት በላይ ታስሶ ሊገኝ ያልቻለውን፣ ከፈረንጅ ተደብቆ የነበርን የአባይ ምንጭ አገኘሁ ብሎ ለአውሮፓ ማውረት ታላቅ ውጤት ነው። ንጉሱም ጎረጎራ ላይ ሰፊ መሬት መራው። ሃይማኖቱን ሲያስፋፋ ኖረና እዚያው ጎርጎራ በ1614 ዓም ሞቶ ተቀበረ።

ምንጩ ከተገኘ ከ11 አመት በኋላ በ 1621 ዓም ሌላው ፖርቱጋላዊ የካቶሊክ ቄስ አባ ጀሮሜ ሎቦ አስደናቂውን ምንጭ ለማየት ወደሰከላ አቀና። ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ ግሽ ተራራ ስር ተሰብስቦ የሚያደርገው በእጅጉኑ አስገረመው። የቤተስኪያኑ ሊቀ-ካህናት ፍሪዳ ይሰዋና ጭንቅላቱን ከሁለቱ የአባይ ምንጮች ያስነካል። ያ ሁሉ እልፍ አእላፍ ሕዝብ እሱን ተከትሎት እያንዳንዱ ፍሪዳውን ይጥላል። ተበልቶ ከተጠጣ በኋላ የዚያ ሁሉ እርድ አጥንት ተቆልሎ ተራራን ያክላል። ሊቀ ካህኑ ካጥንቱ ተራራ ላይ ይወጣና ከጫፉ ይቆማል። አባ ጀሮሜ በጥሞና ያየዋል። ከዚያም የአጥንት ተራራዉ ይለኮሳል። እንደ መስቀል ደመራ እሳቱ ሰማይ ይደርሳል። ያ ሁሉ አጥንት ተቃጥሎ አልቆ የአመድ ቁልል ሲሆን ሊቀ- ካህኑ አመዱን አራግፎ ብቅ ይላል። እልልታ ይነግሳል። ይሄኔ አባ ጀሮሜ ወደ ሊቀ ካህኑ ሮጦ ‹ አንተ ጠንቋይ!› ብሎ ያምባርቅበታል። ወደ ህዝቡ ዞሮ ‹ ይህንን መተታም እንዳታምኑ! በምትሀት ነው ያደነዘዘን› ሲል ደጋግሞ ይጮሀል። የሰማው ሰው አልነበረም። ጮሆ ጮሆ ሲደክመው በቅሎው ላይ እመር ብሎ ለብቻው እንደ እብድ እየለፈለፈ ከአካባቢው ተሰወረ። ያስለፈለፈው ያው የግዮን- የኢትዮጵያ አምላክ ሳይሆን አይቀርም ይባላል። አመታት ቆይቶ የካቶሊክ መንግስት ወድቆ አጤ ፋሲል ሲነግስ ካቶሊኮችን ሰብስቦ አጋዘ። ከዚያም ወደ አገራቸው ሲያባርራቸው አባ ጄሮሜም አብሮ ተባረረ።

 መቼም የአባይ ምንጭ ጉዳይ ፈረንጁን ሁላ አሳብዷል፣ በ1762 ዓ.ም ደግሞ ጀምስ ብሩስ የሚባል እስኮታዊ ከግሪካዊ ጓደኛው ጋር ሆኖ በአጤ አድማስ- ሰገድ እየተመራ ከምንጩ ደረሰ። እሱም ‹የአባይን ምንጭ ያገኘሁ የመጀመሪያው ሰው!› ብሎ ዘለለ። ከጓደኛው ጋር ዋንጫቸውን በጠበሉ ሞሉና ‹ለውቢቷ ልእልት ካተሪና ረጅም እድሜ!› ብለው አጋጭተው ጨለጡ። ከ150 አመት

“በተለይ ጳጉሜ ሶስት የሩፋኤል እለት ታቦት ከድልድዩ መሀል ሲደርስ ኦሮሞውም፣ አማራውም ክርስትያኑም፣ ሙስሊሙም፣ ዋቄፋታውም፣ ወደዚያው ሄዶ ከበአሉ ይታደማል”

በፊት ከእሱ ቀድሞ ሌላ ፈረንጅ እንዳየው ሳያውቅ ቀርቶ ነው ወይስ ሊያጭበረብር? ብቻ ተክለፈለፈ። ቀበጣጠረ። ይባስ ብሎ ከምንጩ አጠገብ ይንከባለላል። አጤው ግራ ተጋብተው ሲያዩት ቆዩና የግዮን መንፈስ የተጠናወተው መስሏቸው ‹ ልጅ ያቆብ (ለጀምስ ብሩስ ያወጡለት ስም)፤ በጤና ነው አንዲህ የምትሆነው? ምንድነው እሱ ለአንድ ምንጭ እንዲህ የሚያንሰፈስፍህ? እንዲህ ብርቁ ከሆነ…ንሳ ፋሲል፤ ከምንጩ አንስተህ ፣ሰከላን ከልለህ በርስትነት ለልጅ ያቆብ ምራው። መዝገብ ላይ ጣፍለት።› ጀምስ ብሩስ ማመን አቃተው። ኋላ ላይ ይሄ ፈረንጅ የኢትዮጵያን አንድ አካል እንደ አገሩ ግዛት አስመዝግቦ የቅኝ ግዛት ጥያቄን የተዳፈነ እሳት እንደሚያራግብ ንጉሱ ልብ አላሉም ነበር። ብሩስ እንዲህ ያለ ውለታ ተደርጎለት እንኳን ለኢትዮጵያ ፍቅር አላሳየም። ስለ ኢትዮጵያ የጻፈው ህዝቡን የሚያንቋሽሽና የሚያጥላላ፣ የአውሮፓን አንባቢ ጉድ ያስባለ ነበር። የአንዱ ጎሳ ጭንቅላት የውሻ፣ ያንዱ የእባብ፣ የአንዱ የዝንጀሮ፣..ደግሞ ሰው ሰውን የሚመገብ…። የአባይን ምንጭ ለማግኘት እሱ የመጀመርያው እንደሆነም እውነትን ሸምጥጦ ባገሩ ተረከ። ዝናው እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጠለ። ያቺን የሚመኛትን ልእልት በእጁ አስገብቶ ኋላ ለመንገስ እየተዘጋጀ ሳለ ያላሰበው አደጋ ብቅ አለ። ስለኢትዮጵያ ትክክለኛ ግንዛቤ ያላቸው ጎብኚዎች እየተረባረቡ ቀጣፊነቱን አጋለጡት። ተፍጨረጨረ፤ ተንጨረጨረ። አፈረ። ከሰው አይን ለመሸሸግ ቤቱን ዘግቶ ተደበቀ። በመጨረሻ የኢትዮጵያ፣ የግዮን አምላክ ቀስፎት ከበረንዳው ላይ አሽቀንጥሮት ተፈጥፍጦ ሞተ።

አባ ጀሮሜ እንዲያ ያራከሰው፣ ግን ዛሬም ቢሆን ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው የአባይ-ግዮን ትውፊት ተሸርሽሮም ቢሆን፣ ከ30 ሚሊዮን አመታት በፊት በተፈጠረው የጣና ሀይቅ ዳርቻና ለሚሊዮኖች አመታት ጥልቅ ሸለቆ እየቦረቦረ፣ በግብጽና በሱዳን ምድረ በዳ ያለውን የሰው ልጅ ለመታደግ በሚፈሰው ቅዱስ ወንዝ ዳርቻ እየተዘከረ ይገኛል። ክብረ በአሉ መንፈሳዊና ባህላዊ እሴት ባዘለ መልኩ ይከበራል። ዘር፣ ቋንቋ ፣ሃይማኖት ሳይለይበት። አንዱ ምሳሌ በኦሮምያ እና በአማራ ክልል አዋሳኝ ላይ ባለው የድሮው ድልድይ ላይ የሚካሄደው ትውፊት ነው።

አባይ በክረምት ተሞልቶ ደንገላሳ ሲል፣ ከአሮጌ ወደ አዲስ ዘመን፣ ከጨለማ ወደ ብርሀን መሸጋገርን ባመላከተበት ጳጉሜ ቀናት፣ ኦሮሞውና አማራው ወደ መኖርያው ወገን ባለው የአባይ ጠርዝ እየተሰባሰበ አምላኩ ጤንነትን፣ ብልጽግና እንዲያጎናጽፈው፣ ትዳርና ልጅ እንዲሰጠው በቅዱስ ውሀው እየተጠመቀ፣ ጠበሉን እየጠጣ፣ ስለት የያዘለት ደግሞ እርዱን እየሰዋ ይቋደሳል (ልክ የግብጽና የሱዳን ወንድሞቹና እህቶቹ እንደሚያደርጉት)። በተለይ ጳጉሜ ሶስት የሩፋኤል እለት ታቦት ከድልድዩ መሀል ሲደርስ ኦሮሞውም፣ አማራውም ክርስትያኑም፣ ሙስሊሙም፣ ዋቄፋታውም፣ ወደዚያው ሄዶ ከበአሉ ይታደማል። አንዱ ወገን በድልድዩ አድርጎ ወደሌላው አንቀጽ ይሻገራል። በመኖርያው ክልል የነበረውን የአሮጌ አመት እርኩሰት ከወንዙ ማዶ አራግፎ በንጻት ሊመለስ ሲል ወደ ‹ሌላው ድንበር› ይዘልቃል። ይሄኔ ‹እርኩሰትህን ወደኔ ክልል ለማራገፍ እንዴት ወደ ክልሌ ትሻገራለህ! ብሎ አተካራ የሚያነሳ ከቶ አይኖርም። ሁለቱም ወገን ስነስርአቱን በጋራ አክብረው፣ ለሚቀጥለው አመት ተስለው፣ ከወንዙ ጠበል ቀድተው፣ ጠጠር ለቅመው፣ በመንፈሳዊ እርካታ ወደመኖሪያቸው ይመለሳሉ። ጠበሉንና ጠጠሩን ከቤት፣ ከበረትና ከጎተራ በክብር ያስቀምጣሉ። ለመንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ለቁሳዊ ግልጋሎት ዋስትና ኦሮሞውና አማራው በአባይ ትውፊት እንዲህ ተዳምረው እልፍ አእላፍ ዘመን ዘልቀዋል – አስከ አሁን ድረስ። የሰይጣን ጆሮ አይስማውና መደመር ብቻ ሳይሆን ተባዝተው፣ የአባይን ትውፊት በእንዱስትሪ እያበለጸጉና እያዘመኑ፣ እንደ ግብጽ በቱሪዚም የአለም መናሀርያ እያደረጉን ይዘልቃሉ። ልሂቃን ተብየዎች ደግ ደጉን ከህዝብ እንማር!

እነሆ ‹በኔ ክልል ጉዳይ ምን አገባህ? በማይመለከት ጥልቅ አትበል! ዋ!!!› መባል በተጀመረበት ወቅት፣ እየሰጋንና እየፈራን፣ በአባይ ትውፊት አሰናስለን ስለኦሮሞና ስለአማራ እንዲህ ዘገብነ። ገና ስለ ዓለም የምንጥፍ አይደለምን?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top