ጥበብ እና ባህል

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሳንካዎችና ጸጋዎች – በኢትዮጵያ

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ እያደረግን ያለውን ሐተታ ቀጥለናል። ባለፉት ክፍሎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ሁለት ገጽታዎች አይተናል: ጸጋዎቹንም ሳንካዎቹን። በተለይ በአገራችን ማኅበረ ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ እያስከተለብን ያለው ተግዳሮት ምን ያክል ግዙፍ እንደሆነ ለማየት ሞክረናል። ግን እንዲህ በመገናኛ ብዙኃን ጋጋታ በስሜት የሚመራ ወጣት ከየት መጣ? እርስ በርሳችን እንድንናቆር መንስኤ የሆነው የአስተሳሰብ ሕጸጽና የታሪክ ስብራት የቱ ጋ ነው? የሚሉ መጠይቆችን ማንሳታችን አይቀርም። የዚህ ክፍል ጽሑፍ ማጠንጠኛ ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው።

 ፯. ለመሆኑ “ክብራችን” ወዴት ጠፋ?

 እንግዲህ እድሜ ለማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የት ላይ እንደምንገኝ የቤታቻንን ጓዳ ጎድጓዳ ገልጦ እርቃናችንን እያሳየን ይገኛል። የመገናኛ ብዙኃኑን መልካም አስተዋጽኦዎች አድንቀን ሳንጨርስ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልሱበት ተቃርኖዎችን አይተናል። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ ጥያቄ መጠየቅ አይኖርብንም? “ለመሆኑ ይኸ ሁሉ ማኅበራዊ ተቃርኖ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን ከምንመለከትበት ማንነት ጋር እንዴት መታረቅ ይችላል?” የሚል ጥያቄ ኅሊናችንን በርግዶ ካልገባ በርግጥም ያለንበትን ሁኔታ ሳንዘነጋ አልቀረንም ማለት ነው። የጥያቄው መንፈስ “ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ያክል ልጓሙን በጥሶ እንዲጋልብ የተደላደለ እርካብ እና ከምርምርና ምክንያት ይቅ ስሜት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ እንዲፋፋ ለም አፈር ሆኖ ያገለገለው ምን ዓይነት ማኅበራዊ ክፍተት ቢያገኝ ነው?” የሚል ነው። “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ እኛ ስለራሳችን ያለን ግንዛቤ ለማንም የተደበቀ አይደለም።

 ራሳቸውን እንደጻድቅ፣ ለሰዎች ክብር የሚሰጡ እንግዳ ተቀባዮች፣ ራሳቸውን ጨዋ ነን ብለው የሚያምኑ፣ በአያሌ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ መልካም እሴቶች ተኮትኩተናል ብለው በዓለም መድረክ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ፣ አገራችንን በዓለም መድረክ አስከብረን በነጻነትና በአንድነት ለዘመናት ኖረናል ከሚሉት ወገኖች ነን የሚሉቱ ናቸው በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የጥላቻ ጭንብል አድርገው የሚተውኑት። ይህ ተቃርኖ በውኑ እኛ ስለኛ ባለን ክብርና አመለካከት ልክ ነውን? ብለን ጓዳችንን እንድንፈትሽ ያስገድደናል።

 ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አገር በቀል ባህል፣ ትውፊትና እውቀቶች የበለጸጉ፣ የታላላቅ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ሃይማኖቶች ተከታዮች እንደሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን እዚህ ላይ እነዚህ የባህል አስተምህሮዎችና የሃይማኖት ስብከቶች ምን ሲሰሩ እንደኖሩ ግራ ይገባል። እንደ ዜጋ ሁሉም የእምነቱ ተከታይ እናቶች በመቀነታቸው፣ አባቶች በኪሳቸው የቋጠሯትን አዋጥተው የገነቧቸው አብያተ እምነቶችና ደመወዝ እየከፈሉ የሚያኖሯቸው ሰባክያን ራሳቸውንና ልጆቻቸውን ለሰማያዊ ገነት እንዲሁም ለምድራዊ ቀናነት የሚሆን ትምህርት እንዲሰጧቸው ነው። ነገር ግን እነዚህ ተቋማት የተፈለገውን ያክል ማኅበራዊ ሰናይነትን በኢትዮጵያ ምድር ማምጣት አልቻሉም። እንዲያውም አንዳንድ አማንያን ነን ባዮች ሌሎቹን የሚሳደቡበት የጥላቻ ንግግር ሲያደርጉ፣ ክፍፍልና አስተዳደራዊ እብለቶች መስተዋላቸው ተቋማቱ ምን ዓይነት ተከታዮች እንዳሏቸው በራሱ አመላካች ነው። በየሃይማኖት ተቋማቱ የሚደረገው የርስ በርስ ክፍፍል በራሱ የአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ ጠቋሚ ምልክት ነው።

መንስኤው ይኸ ብቻ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም ፍቅረ ነዋይ በሃይማኖት ሰዎች ልቡና ተደላድሎ፣ ፍቅረ ቢጽንና ፈሪሃ እግዚአብሔርን ከልባቸው ነቅሎ፣ ፍርሃት ሸብቦ ይዟቸው የዘመኑ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መንፈስ ተገዥ በመሆን ለምዕመናኑ አርአያ መሆን እንዳልቻሉ ያሳያል። ይህም ብቻ አይደለም። ፖሊስ ወይም ግለሰቦች ሰዎችን ሲገድሉ፣ መንግሥት ጥፋት ሲያጠፋ ራሳቸውን መስዋዕት እስከ ማድረግ በሚደርስ ግሳጼ “በቃ” አለማለታቸውና አለማውገዛቸው ከሃይማኖቶቹ ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል። የአብያተ እምነቶቹ መሪዎች በተደላደለ ኑሮ ለዘመኑ ተገዥ እየሆኑ ምዕመኑ ሃይማኖታዊ ሕይወት እንዲኖረው መጠበቅ እንዲሁ ቀልድ ይመስላል።

 ሽማግሌዎቻችንም የሚኮሩበትን ኢትዮጵያዊ ባህል (በየትኛውም አካባቢ ያለ አገር በቀል እውቀት) የልጆቻቸውን ስብዕና ለመገንባት ምን ያክል አስተዋጽኦ እንዳደረገ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል። የታሪክ፣ የቋንቋ፣ የማኅበረሰብና የባህል ጥናቶች እንደሚያሳዩት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ኅብረተሰቦች ባህላዊ እሴቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለሥነ ምግባራዊ ቀናነት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ከነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች የወጡ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች የሌሎችን ሰብአዊ ክብር የሚጋፋ እንቅስቃሴ ላይ ተሰልፈው ነው የምናገኛቸው። ይህ ተቃርኖ ራሳችንን ከመመልከት ይልቅ በተግባር የማንገልጻቸውን የአውሮፓ የዲሞክራሲና የመብት

“በአገር ውስጥ የሚኖረው ወጣት በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ተስፋው ጨልሞ የቻለው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት ሲሰደድ፣ ግማሹ መንገድ ላይ ወድቆ ሲቀር፣ “የተሳካለት” ደግሞ በየሔደበት አገር ሆኖ በመንግሥት ላይ ያቄማል”

እሳቤዎች እያቀነቀንን እነርሱን ለመተግበር ደግሞ በእጅጉ ወደ ኋላ ቀርተናል። ወይ ራሳችንን ሆነን “በቲኦሪ” የምናውቃቸውን የራሳችንን ባህላዊ እሴቶች በተግባር አላሳየናቸውም፤ አልያም እንደ ስልጡኖቹ የዓለም ህዝቦች በዘመናዊ ሳይንስና ፍልስፍና መርሆዎች ሰብዓዊነትና ዲሞክራሲ ባህል በምድራችን ላይ አልሰፈነው። ከዚህ ባሻገር ከህዝብ ግብር እና ከሌሎች የልማት በጀቶች ተቀንሶ እየተገነቡ ያሉ የህዝብ የትምህርት ተቋማት ሥራዎቻቸውን እየሰሩ ለመሆኑ አጠራጣሪ ነው። የትምህርትና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ትልቁ ድርሻ ሰዎችን በምክንያታዊነትና በታማኝነት ኮትኩቶ ባኅርየ ሰናይነት ያላቸው፣ ሙያዊ ብቃትና ተጠያቂነት የሚሰማቸው ምክንያታዊ ዜጎችን እውን ማድረግ ነው። የጥላቻ ንግግሮቹ፣ በስሜት የሚነዱ ጽሑፎችንና የርስ በርስ መካሰሱን በፊታውራሪነት ከሚመሩት አካላት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እንደሚገኙ መገመት አያዳግትም። ሁለት ሦስተኛውን ዜጋ (ከ30 ሚልዮን በላይ ህዝብ) በትምህርት አሳትፊያለሁ የምትል አገር በየዓመቱ የሚመረቁ ባለ ዲግሪዎች ፌስ ቡክን መቋቋም የሚያስችል የምክንያታዊነት ማጣፊያ ሲያጥራቸው ማስተዋል ትምህርቱም ምኑንም ያክል እንዳልተራመደ ያሳያል። ባጭሩ ፌስቡክ ያሌቃቸውን መካነ አእምሮዎች ሊቋቋሟቸው አልቻሉም። ይህም የትምህርት ሥርዓታችን በታሪክ ፊት ከተጠያቂነት አያመልጥም።

ለዘመናት የተሰራው ዲስኮርስ ከአንድነትና የጋራ እሴትን ከመገንባት ይልቅ የራስን ማንነት መገንባቱ ላይና ያንን የማሳየት ፋሽን ሾው ውድድር ላይ የተሰማራ ይመስላል። ለዘመናት በአንድ አገር ጥላ ሥር የኖሩ ህዝቦች በክፉም በበጎም አብረው ያሳለፏቸው መዋዕሎች የጋራ ማንነት እንደገነቡ አይካድም። ይህም በባህል ጥናቶችና በታሪክ ትርክቶች የሚረጋገጥ ነው። ነገር ግን ታሪኩም ለፖለቲካ ፍጆታ በሚስማማ መልኩ አንዱን ጥፋተኛ ሌላውን ባላደራ፣ አንዱን በዳይ፣ ሌላኛውን ተበዳይ አድርጎ በማቅረብ የመከፋፈልና የመጠላላት ፖለቲካዊ ዲስኩር የዘመናችን መገለጫ ሊሆን ቻለ።

ያለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ቡድኖች የተፈጠሩበት ዘመን ነው። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ለዘመናት አይነኬ የነበሩ ጨቋኝ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችን ለማጋለጥና ለመገርሰስ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አይካድም። ነገር ግን በሌላ በኩል ሲታይ ከአንድነት ይልቅ የብሔር ነጻነትና መብት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶች በልዩነት ላይ ያለን አንድነት ለመስበክ ብዙ ተደክሟል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ታሪክ እንደ አንባቢዎቹ ትርጓሜና እንደተራኪዎቹ ዓላማ እንደፈለገ ሲተነተን አይተናል። በዚህም ከታሪክ መማርን ሳይሆን ቁርሾን የሚፈጥሩ ዲስኩሮች ትልቁን ቦታ ይዘዋል። ይህ የታሪክ አረዳድና አጠቃቀም በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ብቻ የተወሰነ አልነበረም። እውነትና እውቀት የምሁራን ሳይሆን የባለ ጉልበትና የባለ ጊዜ ናት እንዳለ ሚሼል ፉኮ በኛም የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃኖቻችን ሳይቀሩ ልዩነትን እንጅ አንድነትን ሲሰብኩ፣ ሲያስተምሩ አልተስተዋሉም። በዚህም የመልስ ምት ፖለቲካ ከባለፈው የጋራ እሴት እንዳንማር ጋርዶብን ታሪካችን አንዱ ወገን በዳይ ሌላው ወገን ተበዳይ አድርጎ አቀረበልን። በዚህም ቂም በቀል፣ ጥርጣሬና በጥላቻ መተያየት የዘመናችን ባህል ሆኖ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንም ያንን ቂም በቀል የሚያንጸባርቁበት የቃላት ጦርነት ቀጠና ሊሆን ቻለ። ቀድሞ “ለብሔር ብሔረሰቦች መብት አትመችም” የተባለችው ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ የብሔሮች መነታረክ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለጋራ ብልጽግና የማይበጅ እንደሆነ ምልክቶቹ እየታዩ ነው (አብዲሳ ዘርዓይ፣ 2017)። የዚሁ የመጠላላት አዙሪት ብሔር ተኮር ጥቃት እየተበራከተ ያሁኒቷ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊነትም፣ ለብሔረሰቦች እኩልነትም የማትመች ሆናለች።

 ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ አሻጥርና የርስ በርስ መጠፋፋት ሌላው የቅርብ ዘመን ትውስታችን ነው። በ1960ዎቹ የነበሩት የፖለቲካ ቡድኖች ታሪካቸውን እንደሚያሳየን ባንድም በሌላም የርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ አረዳድ ልዩነት፣ ያንን የሚያስፈጽሙበት መንገድ መለያየት በመካከላቸው ቁርሾ ፈጥሮ እርስ በርሳቸው ሲገዳደሉ ኖሩ። የሞቱት ሞተው የተረፉት ግማሾቹ ስልጣን ሲይዙ ግማሾቹ አኩርፈው ኮበለሉ። በመካከላቸው እርቅ ሳይፈጸም ይኸው ይዘውት የነበረው መንፈስ ግጭትና ቁርሾ አሁንም የፖለቲካ ምኅዳራችን ላይ ናኝቶ ይገኛል። “ የ ‘ያ ትውልድ’ መንፈስ አሁንም አገሪቱን እያስተዳደራት ነው” ብለው በድፍረት የሚናገሩ አሉ። ይኽም በህዝቦች መካከል ለሚፈጠረው ቁርሾ የራሱን ትልቅ ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ረገድ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኃይሉን ተጠቅሞ ሲያሳድድ፣ በውጭ አገር የሚኖረው ተባራሪና አኩራፊ ደግሞ “የመናገር ነጻነቱን” ተጠቅሞ ትግሉን ቀጠለ። በዚህ መሐል ብዙኃኑ የማኃበራዊ መገናኛ ብዙኃን ቤተሰብ ውዥንብር ውስጥ እንዲገባና የጥላቻ ንግግር፣ የመከፋፈል ሰለባ እንዲሆን ተዳረገ።

በአገር ውስጥ የሚኖረው ወጣት በኑሮ ውድነትና በሥራ አጥነት ተስፋው ጨልሞ የቻለው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት ሲሰደድ፣ ግማሹ መንገድ ላይ ወድቆ ሲቀር፣ “የተሳካለት” ደግሞ በየሔደበት አገር ሆኖ በመንግሥት ላይ ያቄማል። ሌላው ግን በአገሩ ውስጥ ሆኖ የችጋር ኑሮን እየመራ በመገናኛ ብዙኃን የሚለፈፈውን ልማት እየሰማ፣ የቱጃሮችና ባለጊዜዎች የበይ ተመልካች ሆነ። በዚህም ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር ድንጋይ መወርወር እንደ መፍትሔ ይቆጥረው ጀመር። ኢፍትሐዊ የሃብት ክፍፍልና ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ እጦት ወጣቱን በአገሩ ላይ አኩራፊ እንዲሆን አደረገው። ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን የሚዘዉሩት ደግሞ ይህንን ቀዳዳ

“ቁጥራቸው ይብዛም ይነስም በፌስ ቡክ መንደር በእኩይ ዓላማ ንጹሐንን የሚያጫርሱት የፌስቡክ አክቲቪስቶችና የነርሱ ተከታይ መንጋዎቻቸው ግን በዚህች አገር የባህል፣ የሃይማኖት፣ የትምህርት ተቋማትና የሁሉም አገልግሎት ተቋማት ጓዳዎች ያለፉ ናቸው። ስለዚህ ሃገር እንደ ሃገር በዘመን ሂደቷ ውስጥ በዜጎቿ ዘንድ ኢምክንያታዊነትን፣ መጥፎ ጠባይንና ድንቁርናን የምትቀርፍበት ሂደት ይኖራታል”

ተጠቅመው ወጣቱን ቀሰቀሱ። መንግሥትም በእስራት፣ በማሰቃየትና ተኩሶ በመግደል ሊያስቆም ሞከረ። መጠላላት፣ መገዳደል፣ መካሰስና መሰዳደብ የማኅበራዊ መስተጋብራችን መገለጫዎች ሆኑ።

ሌሎች (የአገልግሎት፣ የፍትህ፣ የፖሊስ ሌሎቹም የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ የአገልግሎት) ተቋማት እና የተቋማቱ መሪዎች ተገልጋዮቻቸውን እንዴት ቢያገለግሉ ነው ዜጎቹ በአገራቸው ላይ እንዲህ ሊነሱና ሊቀየሙ የቻሉት? ይህ በርግጥ ሰፊ ነገር ነው። ህዝብን የሚያስቆጣው፣ የሚያስኮርፈውና የሚያስቀይመው የመንግሥት አካላት ጨቋኝነት፣ ኢዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንዲሁም ከበርቴውና ባለጊዜው ብዙኃኑን ባያንገላቷቸው ኖሮ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጥሪና በስሜት ወለድ ጋጋታ ሆ ብሎ ወጥቶ ድንጋይ የሚወረውር፣ ሰዎችን በማንነታቸው ለይቶ የሚደበድብ፣ ሰው የሚገድልና ንብረት የሚያቃጥል ወጣት ባላየን ነበር። ይህም በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲለፈፍለት የነበረው ዲሞክራሲና ሁሉን አሳታፊ ልማት ተዓማኒነቱ አጠያያቂ ይሆናል ማለት ነው። የተፈጥሮ ሃብትን (መሬትን ጨምሮ) እኩል እንዳንጠቀም በማድረግ በዜጎች መካከል ቅሬታን የፈጠረ ቢሮክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምህዳር ነበረን።

 የአንድ ማኅበረሰብ በጎ ተግባቦት የሚረጋገጠው በባህል፣ በሃይማኖትና በዘመናዊ ትምህርት በሚያገኘው የመልካም እሴቶች አስተዋጽኦነት በሚበለጽግ የአስተሳሰብ ልኅቀትና የበጎ ምግባር ባኅርያት እውናዊነት ነው። ምንም እንኳ አያሌ የእምነት ተቋሞች ቢኖሩም በህዝቡ ልብ ፈሪሐ እግዚአብሔር ሊያቆጠቁጥ አልቻለም። እንዲያውም የሃይማኖት ተቋማት ራሳቸው የምዝበራ፣ የመጠላላትና የኃጢአት ተቋማት ወደ መሆን ተቀየሩ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን የምክንያታዊነትና የጥበብ መፍለቂያዎች ከመሆን ይልቅ በተቃራኒው የጥላቻ ፋብሪካዎች፣ አንዳንድ ምምህራኖቻቸውና ተማሪዎቻቸውም የጥላቻ ዘመቻው ፊታውራሪዎች ለመሆን በቁ። የተሻለ ምክንያታዊነትን ከማረጋገጥይልቅ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ መሃይምናንን እያየን ነው። በውኑ ትምህርቱ “አደድቦ መጣል” (ጸሐይ ጀንበሩ 2008) ላይ የተሰማራ እስኪመስለን ድረስ የመገናኛ ብዙኃንን ጋጋታ መቋቋም የማይችል የመካነ አእምሮ (University) ማህበረሰብ እያየን ነው። ትህትናና ምክንያታዊነት ከማኅበረሰባችን ልቡናና አእምሮ ኮበለሉ።

የነዚህ መሰል ነባራዊ ሁኔታዎች ድምር ውጤት አሁን ለምናያቸው ስሜት የተጫናቸው ጸሐፍትና ተከታዮቻቸው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የተደላደለ ቦታ እንዲያገኙ ምክንያት ሆኑ። በፌስቡክ ወለድ ውዥንብርና ሽብር ኢትዮጵያም እንደ አገር፣ ኢትዮጵያውያን እንደዜጋ ሕይወታቸው አደጋ ላይ እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ ቀፍሪካና ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለዓለም ሰላም አስጊ ይሆናል። ኢትዮጵያ በቀጠናው ካላትና ሊኖራት ከሚገባው ሚና አንጻር ሲታይ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል።

እንግዲህ የአገሪቱ ባለቤቶች አዛውንቶችና ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሃይማኖተኞች፣ የፖለቲካ ባለ ስልጣናት፣ የኢኮኖሚ ቱጃሮች፣ ሊቃውንት፣ ሲቪል ሰርቫንትና ለእለት ጉርሳቸው የሚሰሩ ምስኪኖች፣ ብዙኃን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች – ባጠቃላይ ሁሉም የኔና ለኔ ናት የሚሏት ሁሉ ናቸው። በፌስ ቡክ የሚታየው ሁኔታ ግን ይህ ሁሉ ዜጋ ከልቡ አንቅሮ እንዳይተፋት የሚያደርግ ወይም ከልቡ እንዲሰራላት የሚያስችለውን የአገር ባለቤትነትን መንፈስ እንዲጎናጸፍ የሚያስችለውን ስንቅ አላስታጠቀችውም ማለት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ በአገር ውስጥ በኖረባቸው ዘመናት የደረሰበት ነገር፣ ከጸጋዋና ከፍዳዋ የተካፈለበትን ፍትሐዊነት መፈተሽ ይኖርበታል። እዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ሊባል ይገባል። የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶቻችን፣ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት በቀናነትና በታማኝነት የሚያገለግሉትን፣ በመልካም ጉርብትናና በመከባበር፣ ለሃገሩ መልካም በማድረግ መሥዋዕትነት እየከፈለ የሚኖረውን አእላፍ ኢትዮጵያዊ መዘንጋቴ አይደለም። ለምሳሌ በዚህ ሳምንት አርባ ምንጭ ላይ በነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ወዳልተገባ ተግባር የተሰማሩትን ወጣቶች ያገር ሽማግሌዎች እንዳካባቢው ወግ ባህል እርጥብ ሳር ይዘው ተንበርክከው በመማጸናቸው ሊከሰት ከነበረው የንብረት ውድመትና የሰው ሕይወት ጥፋት ታድገውናል። ይህም የመልካም ባህላዊ እሴቶቻችን መገለጫ ነው። በየአካባቢው ያሉ አዛውንቶችና የሃይማኖት መሪዎች መሰል ተግባራትን ቢያደርጉ ምናልባትም በምድራችን ላይ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችን ባላየን ነበር።

ቁጥራቸው ይብዛም ይነስም በፌስ ቡክ መንደር በእኩይ ዓላማ ንጹሐንን የሚያጫርሱት የፌስቡክ አክቲቪስቶችና የነርሱ ተከታይ መንጋዎቻቸው ግን በዚህች አገር የባህል፣ የሃይማኖት፣ የትምህርት ተቋማትና የሁሉም አገልግሎት ተቋማት ጓዳዎች ያለፉ ናቸው። ስለዚህ ሃገር እንደ ሃገር በዘመን ሂደቷ ውስጥ በዜጎቿ ዘንድ ኢምክንያታዊነትን፣ መጥፎ ጠባይንና ድንቁርናን የምትቀርፍበት ሂደት ይኖራታል። በዚህም ፖለቲካዊና ፖለቲካዊ ያልሆኑ እሴቶቻችን ምን ያክሉን አስተዋጽኦ ተጫውተዋል? የሚለውን ግን ከመፈተሽ አያግደንም። እንዲያው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ብቻ የሚስተዋለውን ነውር አወሳሁ እንጅ የንግድ ሥነ-ምግባር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የአስተዳደር፣ የርስ በርስ ግንኙነት ባጠቃላይ እንደማኅበረሰብ ለሰብዓዊነት ያለን ክብር ቢፈተሽ የማኅበረ-ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዝንፈት አንገት ቢያስደፋ እንጅ የሚያኮራ አይሆንም። እንግዲህ በተለያዩ መድረኮች ለራሳችን የሰጠነውንና እየሰጠነው ያለውን የታላቅነት ክብር ከግብራችን ጋር በማስተያየት መገምገሙ ወደነገ ለምናደርገው ጉዞ የተሻለውን መንገድ መቀየሱ የየራሳችን ኃላፊነት ይሆናል።

ከዚህ ሁሉ ጥፋት ተላቀን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ለመልካም ዓላማ ለማዋል ምን መደረግ አለበት? በዚህ ዘመን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ከፖለቲካ ተቃውሞ ባሻገር ምን ዓይነት ማኅባራዊ ፋይዳ ይኖረዋል? በማኅበራዊ መገናኝ ብዙኃን ላይ የሚስተዋለውን እኩይ ተግባር እንዴት መቀነስ ይቻላል? ይህንን ማድረግስ የማን ኃላፊነት ነው? ይቀጥላል!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top