ስርሆተ ገፅ

“ኢትዮጵያ ትቅደም!” የጎምቱው ጋዜጠኛ ትዝታ

ስለ ኢትዮጵያ ጋዜጠኝነትና ጋዜጠኞች ታሪክ ሲወሳ፤ ስማቸው አብሮ ከሚጠቀሰው የቀደሙ ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ ናቸው‐ አቶ ከበደ አኒሳ፡ ፡ በእንግሊዝኛዎቹ ቮይስ ኦፍ ኢትዮዽያና የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጦች ላይ ሰርተዋል፡፡ በአማርኛዎቹ የኢትዮጵያ ድምጽ እና የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች በዋና አዘጋጅነት ለበርካታ ዓመታት ሲሰሩ፤ በጋዜጦጠቹ አጀንዳዎችን እየፈጠሩ ተነባቢ እንዲሆኑ አድርገዋል። በእርሳቸው ማበረታታት በጋዜጦቹ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ለከፍተኛ ዕውቅና የበቁ፣ ደራሲያንና ጋዜጠኞች ጥቂት አይደሉም። በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተጠባባቂ መምሪያ ኃላፊ፣ በየዘመቻ መምሪያ ውስጥም ተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ነበራቸው፡ ፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት የወሎ ክፍለ ሀገር ምክትል እንደራሴም ነበሩ። ጡረታ ከወጡ በኋላ የግል ጋዜጦችን በማማከር ሙያዊ አስተዋጽኦ ሲያደርጉም ቆይተዋል። ከበደ አኒሳ ዛሬ የ85 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። ጋዜጣ፣ መጽሔትና መጽሐፍ ከእጃቸውና ከኪሳቸው አይጠፋም፡፡ ሁሌም መነጽራቸውን ሰክተው የድጋፍ ብትራቸውን ከጎናቸው አድርገው በመረጧቸው ካፌዎች በረንዳ ላይ ሲያነቡ ይስተዋላሉ። በተለያዩ ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ጉዳዮች ከሌሎች ጋር ሃሳብ ሲለዋወጡ ደስ ይላቸዋል። ዛሬ መጽሔታችን እኚህን ጎምቱ ጋዜጠኛ እንግዳ አድርጋለች። ከሰፊው ወጋችን ለገጻችን ምጣኔ በተስማማ መልኩ እጅግ ጥቂቱን እነሆ ብለናል።

ታዛ፡- ስላገኘዎት ደስ ብሎኛል ? እንዴት ነው ጤናዎ? 

አቶ ከበደ አኒሳ፡- ደህና ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገን። ትንሽ ሪህ እግሬን ያዝ እያደረገኝ መራመድ ቢከለክለኝም፤ እንደምንም እየበረታሁ እንቀሳቀስበታለሁ። አንድ ጊዜ ወድቄ ወደ ህክምና ስሄድ ነው ሪህ መሆኑን ያወኩት። በተረፈ በጣም ሰላም ነኝ፣ ልቤ፣ ጉበቴ፣ ሳምባዬ፣ ዓይኔ፣ ጆሮዬ፣ አዕምሮዬ ፍፁም ጤና ናቸው። እንደልቤ እንዳነብ፣ እንደልቤ እንዳስብ ረድቶኛል። 

ታዛ፦ የዕርስዎ መዝናኛ ንባብ መሆኑን ወዳጆችዎ ሲናገሩ እሰማለሁ በእርግጥ ንባብ ነው የሚያዝናናዎት?

 አቶ ከበደ አኒሳ፡- አዎ! እንደ እህልና ውሃ ሁሉ፤ ንባብን ውስጤ ይፈልጋል። መነበብ አለባቸው ብዬ ያመንኩባቸውን መጽሐፍ፣ ጋዜጦችም ሆነ መጽሔት አነባለሁ። በምክንያትም ቢሆን ሳላነብ የዋልኩ ዕለት ምቾት አይሰማኝም። በጣም ቅር ይለኛል። ይህ እንግዲህ ተፈጥሮዬ ነው። የአገራችንን እና የዓለምን ሁኔታን መከታተል ያጓጓኛል። ይህ ደግሞ የማንኛውም የጋዜጠኛ ባህሪ ይመስለኛል። ሊሆንም ይገባል።

 ታዛ፦ ለማንበብ የሚመርጧቸው የጽሑፍ ስራዎች የትኞቹ ናቸው?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ ሁሉንም የአገር ውስጥና የውጪ ጋዜጦችና መጽሔቶችን፣ መጽሐፎችንም አነባለሁ። ቀልቤን የሚስቡ ርዕሶችንና ጉዳዮችን እመርጣለሁ። ለምሳሌ ታይም፣ ኒውስ ዊክ፣ ኢኮኖሚክስ መጽሔቶችን ከውጪ፣ ሪፖርተርን፣ አዲስ አድማስን፣ ፎርቹን፣ ካፒታልና ሌሎች በእንግሊዝኛና አማርኛ የሚዘጋጁ መጽሔትና ጋዜጦችን አነባለሁ። በተቻለኝ መጠን እንደታተሙ ሳላነባቸው እንዳያልፉኝ እፈልጋለሁ። የሚገርምህ ታይም መጽሔት 75 ሳንቲም ይሸጥ ከበነበረበት ጊዜ ጀምሮ ነው የንባብ ደንበኝነቴ። ዛሬ ቡክ ወርልድ ብትሄድ ዋጋው መቶ ብር ነው። እኔ ግን ኢትዮጵያ ሆቴል ጀርባ በ10 ብር፣ በ20 ብር እገዛለሁ። ገንዘብ በእጄ ካለ መጀመሪያ የማውለው ለጋዜጦችና፣ መጽሔቶች ነው። ከዚያ በተረፈው ነው ቢራ የምጠጣው። ቤቴ የውጪ ጋዜጦችና መጽሔቶች ክምር ታገኛለህ። እንደሌሎቹ ጋዜጦች ሲበዙብኝ በኪሎ ልሸጣቸው አልችልም። ስለማይፈለጉ።

 ታዛ፦ መጠጥ አንዱ መዝናኛዎ ነው ልበል?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ በፍጹም! ቅድም እንዳልኩህ ንባብ ነው መዝናኛዬ። ዛሬ ከሁለት ሦስት ቢራ የበለጠ አልወስድም። አቅሙም የለኝም። በደንብበ የሚጠጣበት ጊዜ አልፏል። በጊዚያችን ጠጥተናል፣ ጨፍረናል፣ ተዝናንተናል። ግን ስራችንን ሳንበድል ነው። ጋዜጣዬ ተጠናቃ ወደ ማተሚያ ቤት ሳትላክ አንዲት ቢራ አልቀምስም ነበር። ጋዜጠኝነት ከፍተኛው የህዝብ ኃላፊነትን የመሸከገም ግዴታ ያለበት ሙያ ነው።

 ታዛ፦ ዛሬም ጋዜጠኛ ሲባል በህብረተሰቡ ዘንድ ጠጪ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ አለ። ይህ ደግሞ ከእናንተ ዘመን ጀምሮ የመጣ አመለካከት ነው፤ ለምን ይመስልዎታል?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ ምን መሰለህ፤ እርግጥ በእኛ ዘመን ብዙዎች ጠጪዎች ነበርን። ኮክቴል እና በየኤምባሲው የሚደረግ ግብዣ ላይ እንድንገኝ እንጋበዛለን። ኤምባሲዎች የየራሳቸውን አቅምና ዲፕሎማሲያዊ ንቃታቸውን የሚያሳዩበትን ግብዣ ነው የሚያደርጉት። መጠጡ በገፍ ይወርዳል። ይበላል፣ ይጨፈራል። በዚህ ምክንያት መጠጠጥ ተለመደ። ልምዱ እንደሙያው እየተወራረሰ መጣ። በዚያውም እርስ በእርስ መገባበዙና ኪስን ማራቆቱም መጣ። ያ ሁኔታ ይመስለኛል ጋዜጠኛ ጠጪ ነው የሚል ስም ያሰጠን። ብዙዎቻችን የሬዲዮም ሆነ የቴሌቪቭዥን ጋዜጠኞሦች፤ በተለይም ዋና ኤዲተሮች አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል አለፍ ብሎ ያለው አነስተኛ ህንጻ ላይ ነበር የምንዝናናው። ቦታውን «ሰከንድ ቪዥን» እንለዋለን። ያዕቆብ ወልደማርያም ነው እንዲያ ብሎ ያወጣለት። ፈርስት ቪዥን ቢሯችን ነው። እና ከስራ መልስ መገናኛችን ነበር። ነገር ግን ጋዜጠኛ ሆነው የማይጠጡም እንደነበሩ ልብ ሊባል ይገባል። የስራ ትጋትና ኃላፊነትን ሳንዘነጋ ነው ያንን የምናደርገው። በሌላ ንጽጽር ግን በዛሬውና በዚያን ዘመን ጋዜጠኞች ከፍተኛ ልዩነት አለ።

ታዛ፦ ለምሳሌ?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ በእኛ ዘመን የነበረው ጋዜጠኛ አብዛኛው በልምድና በፍላጎት ሙያውን የተካነው ቢሆንም፤ አንባቢ ነበረ። በጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ትንታኔ መስጠት የሚያስችለውን ዕውቀት ከንባብ ያካብታል። ዛሬ ጋዜጠኛው ተግቶ ለማንበብ የሚታክተው ይመስለኛል። በእኛ ዘመን መረጃ ለማግኘት፣ የመረጃ ምንጮችን ለማግኘት ፈተና ነው። ብዙ መቧጠጥ ነበረ። የዛሬው ጋዜጠኛ ቴክኖሎጂው አግዞታል። የሞባይል ስልኩ፣ ኢንተርኔቱ መኳተንን ቀንሶለታል። ስለዚህ እድለኛ ነው። በእኛ ጊዜ ጋዜጣው መንግስታዊ ብቻ ቢሆንም አንድም ቀን ከህትመት ተስተጓጉሎ አያውቅም። ዛሬ ግን በተለይ የግሎቹን ጋዜጦች በቀናቸው አታገኛቸውም። የተለያዩሉ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ ማተሚያ ቤቶቹ አለመተባበራቸው ነው። ታተመ አልታተመ መንግስትም አይጨነቅበትም። ደንበኛ አንባቢ ደግሞ ይጠብቃል። የፈለገውን ሲያጣ እሱም ይተወዋል። ጥቂት ጊዜ ብቅ ብለው የጠፉ ምርጥ ምርጥ ጋዜጦች እንደነበሩም ታዝቢያለሁ። ይህ የፕሬስ ህጉ ቀና አለመሆን ነው። መስተካከል ያለበት ይመስለኛል። በእኛ ጊዜ ዋናው የመረጃ ምንጭ የመንግስት ጋዜጦችና መጽሔቶች አንድ ቴሌቪዥንና አንድ ሬዲዮ ነበሩ፤ ዛሬ የቴሌቭዥን ቻናሎች በዝተዋል ለዚያውምመ በጥራት። የኤፍ ኤም ሬዲዮኖች መበራከት ትልቅ የለውጥ ምልክት ነው። ያሉት ኤፍ ኤሞች ሙያውን ተከትለው በደንብ ከሰሩ ሕዝባችን በመረጃ ይበለፅጋል። የሌሎች ዘርፎችም ማደግ የሚመጣው መረጃ ሲኖር ነው። የጋዜጠኝነት ስራ ዘርፍ በዝቶ እየታየ እንዳለ ሁሉ፤ ጥራትና ብቃት ላይ አትኩሮ ውድድሩን ማለፍ ይገባል ባይ ነኝ። በዕድሜዬ ይህንን ማየቴ ዕድለኛ ነኝ።

 ታዛ፦ በወቅቱ የነበሩት የሙያ አጋሮችዎ እነማን ነበሩ?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ ኦዎ! ስንቱን ልጥቀስልህ? ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ፀጋዬ ታደሰ ( ዘ‐ ሮይተርስ) ፣ ያዕቆብ ወልደማሪያም፣ ተስፋዬ ሀብትህይመር፣ ተሾመ አደራ፣ መስፍን ብርሃኔ፣ በዓሉ ግርማ፣ ነጋሽ ገብረማርሪያም፣ የሸዋረን ፣ጊዮን ሀጎስ… ብዙ ናቸው። ሁሉም ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ጽፈው የሚያጽፉ የሚዲያ መሪዎች ነበሩ። በሙያቸውም የተካኑ ለኢትዮዽያ ጋዜጠኝነት ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ናቸው። የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ዛሬ የሉም። እኔ ያዕቆብ እና ፀጋዬ ብቻ ቀረን…።

ታዛ፦ ዘፈን ይወዳሉ?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ አዎ። የብዙነሽ በቀለ፣ የጥላሁን ገሠሠ፣ የመሐሙድ አህመድ ዘፈኖች ይመስጡኛል።

ታዛ፦ ከዘመኑ ዘፋኞች የሚካኤል በላይነህን ዘፈንንም እንደሚወዱት አንድ ጊዜ አጫውተውኛል።

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ ትክክል! ፊሎሶፊካል ነው ዘፈኑ። ያለምክንያት አልወደድኩትም። የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥሞችንኮ ነው የዘፈነው። ገብረክርስቶስ ወደ ዕውቅና ከመምጣቱ በፊት ወዳጄ ነበረ። ጋዜጣዬ ላይ ግጥሞቹን አወጣለት ነበር። አንድ ጊዜ እየተዝናናን ስናመሽ በወጋችን መሃል «ነገ አንድ ግጥም ይዤልህ እመጣለሁ» አለኝ። እንዳለውም በማግስቱ አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስቴር ፊት ለፊት ያለው የድምጽ ጋዜጣ ቢሮዬ ይዞልኝ መጣ። ግጥሙን ሳነበው ወደድኩት። «ስወድሽ…. ስወድሽ …» ይላል። ሃሳቡ ምጡቅ፣ ብስል ያለና ወደ ውስጥ የሚሰርጽ መልዕክት ያለው ነው። አተምኩለት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተወዳጅ ግጥም እንደሆነች ዘለቀች። ይኸ የዛሬው ትውልድም እንዲህ አሽሞንሙኖ ይዘፍናታል። ጥሩ ሰዓሊ ብቻ ሳይሆን፤ ጥሩ ገጣሚም እንደሆነ ይየታወቅለታል። ምን ያደርጋል…።

ታዛ፦ «ኢትዮጵያ ትቅደም!» የምትለዋን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ መልዕክት እንዲኖራት ያደረጉት እርስዎ መሆንዎ ይሰማል፤ ለምን?፣ እንዴትና መቼ ነው ያ የሆነው?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ በ1957 ዓ.ም ነው። የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበርኩ ጊዜ ነው ይህን ጥምር ቃል ርዕስ አድርጌ ርዕሰ አንቀፅ የጻፍኩበት። በወቅቱ ብዙ አነጋግሯል። «ንጉሡን ለመንካት ነው። አገር ከእርሳቸው ትበልጣለች ማለቱ ነው» እያሉ እኔን የወነጀሉኝ ነበሩ። በዚያን ወቅት ጃንሆይ ቤተ‐ መንግስት ጠርተውኝ ‘ምን ለማለት ፈልገህ ነው ይህን የጻፈከው?’ ብለው ጠየቁኝ። እኔም ‘ግርማዊ ሆይ ከግለሰብ ጥቅም የአገር ጥቅም ይበልጣል። ሁሉም በየሙያው ዘርፉ አገሩን እያሰበ ከሰራ አገር ትለማለች። ትበለጽጋለች። ስለዚህ ከግለኝነት ወጥተን አገርን እያሰብን እንስራ፤ በሰላም እንኑር ማለቴ ነው’ አልኳቸው። ተደሰቱ። ‘እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ ያለው ሰው ነው ይህች አገር የሚያስፈልጋት፤ በል በርታ!’ ብለውኝ አሰናበቱኝ። በኋላም የምክትል እንደራሴነት ሹመት ሁሉ ሰጡኝ። የሆነው ሆኖ ይህች ጥምር ቃል በጋዜጣዋ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ልዩ መታወቂያዋ ሆኖ ለበርካታ ዘመናት ኖራለች። የሚገርመው ደርግ ሲመጣ ከፊት «ያለ ምንም ደም» የሚል ቃል ጨምሮበት የፖለቲካው መመሪያና ማራመጃ አድርጓት ቀጠለ። ዛሬም ይህች ቃል ጽኑ ነች። ከማናችንም በላይ ኢትዮጵያ ትቀድማለች። ልብ በል «ኢትዮጵያ ትቅደም!» ስል እንደ አሜሪካኖች ከሀገራት ሁሉ የበላይ እንሁን አይደለም። አገራችንን ከራሳችን እናስቀድማት ነው።

ታዛ፦ የወሎ ክፍለ ሀገር ምክትል እንደራሴ በነበሩ ጊዜ በአገሪቱ የከፋ ድርቅ ተከስቶ ነበር። ያኔ እንግሊዛዊው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጆናታን ድምቢልቢ ስለ ድርቁ ሲዘግብ እርስዎ ሁኔታውን እንዳመቻቹለት ይነገራል፤

አቶ ከበደ አኒሳ፦ ልክ ነው። በፍቃድ ሊዘግብ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ጋዜጠኛ ተፈሪ ወሰን እና አንድ ለጊዜው የማላስታውሰው ጋዜጠኛ ወደኔ ይዘውት መጡ። በሚገባ ተቀብዬው በክፍለሀገሩ እያዟዟርኩ ያለውን የድርቅና የርሀብ ሁኔታ በደንብ አሳየሁት። አንድ ቲም ይዞ ነበር የመጣው። እሱ ዘጋቢ ነው። ሌሎች የካሜራ ባለሙያዎችም አሉ። እያዘነም እየተገረመም ነበረ ያንን አሰቃቂ የረሃብ ዜና እና ፕሮግራም ለቢቢሲ የሰራው። ጆናታን ግሩም ሰው ነበር። በደንብ ነው የተግባባነው። ታዋቂና ጎበዝ ነው። በዚያ ዜናም ዝናው ገኗል። አባቱም ታዋቂ ጋዜጠኛ ነበሩ።

ታዛ፦ ያንን የርሃብ ሁኔታ ሲያይ ስሰሜቱ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ የስሜት መጎዳት አይበት ነበር። ከዚያን በፊት እንደዚያ አይነት ርሃብና እልቂት አይቶ አያውቅም። በምግብ እጦትና በበሽታ በየመንደሩ የሚረግፈው ህዝብ ቀላል አልነበረም። በአጥንቱ የሚንቀሳቀስ፣ በየጎጆውና በየመንደሩ ተጠቅልሎ በመተኛት ሞቱን የሚጠብቅ ብዙ ነበር። የሚያጣጥር። የእርዳታ እህል ለማድረስ ብንጥርም፤ የመኪና መግቢያ መንገድ ችግር በመኖሩ በፈለግነው ደረጃ ህዝቡን ልንታደገው አልቻልንም። ያ ጊዜ፣ ያ ዘመን ከሚነግሩት በላይ አስከፊ ነበር። ታዲያ ለጆናታን ወሎ ውስጥ ልዩ ስሙ ውርጌሳ የሚባል ቦታ ወስጄው ሁኔታውን ሳሳየው በርሃቡ ራሷም ልታልፍ የደረሰች አጥንቷ ያገጠጠ እናት ልጇን ታቅፋ ጡት ታጠባለች። በሕይወት ያለ መስሏት። ልጁ ግን ክንዷ ስር ለዘለአለሙ አሸልቧል። ድንብልቢ ይህን በፊልም አስደግፎ ሰርቶታል። ይህ እልቂት እንዲታይ ሁኔታውን ሳመቻች፤ ዓለም ይታደገናል ከሚል ቀናኢነት ነበር። ደርግ ግን ለራሱ የስልጣን መቆናጠጫ ምክንያት አደረገው። ርሃቡ እንዳይነገር ታፍኖ የነበረውን ሁኔታ መስከረም 1/ 1967 ዓ.ም ገላለጠው። ሕዝባዊ ቁጣን የሚያስነሳ ነበር ዘገባው። በማግስቱ ዘውዳዊው ስርአት መገርሰሱን አወጀ። እና እኔ በዚህ ስራዬ አልፀፀትም። ድንብልቢም ህሊናውን የሚያፋፋ እንጂ የሚያኮስስ ስራ አልሰራም።

 ታዛ፦ ከዚያን በኋላ ጆናታ ድምቢልቢን አግኝተውታል፡፡ ያውቃሉ?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ አግኝቼዋለሁ። ከአመታት በፊት በደርግ ዘመን መጥቶ ሂልተን ባረፈ ጊዜ አግኝቶኛል። ተገባብዘን ብዙ አውርተናል። የሰራነው ስራ ተገቢ እንደነበረም ነው የተማመነው። እንዲያውም የተወሰነ ብር ሰጥቶኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ። እንደኔው አርጅቷል። ግን ታሪክ የሰራ የማከብረው ሰው ነው።

ታዛ፦ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በኃላፊነት ሲሰሩ፤ በርካታ ፈተናዎችን እንዳሳለፉ፣ ስኬቶችንም እንደተጎናጸፉ ይሰማኛል። ዛሬ በአገራችን ስላለው የሙያው ሁኔታ ምን ታዝበዋል?

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ አሜሪካን አገር ሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትን ስማር የመጨረሻ ወረቀቴን የጻፍኩት በአሜሪካ ማስሚዲያ ላይ ነው። ለማንኛውም ህዝብ አመቺና ተስማሚ የሆነ መገናኛ ብዙሀን አላቸው ። የሆነውን፣ ያለውን፣ ሊሆን የታሰበውን ሁሉ በሚዲያዎቹ ታገኛለህ። የተደራጀ ነው። በአገራችን ግን ይህ የተሟላ አይደለም። ከላይ ለመጠቃቀስ እንደሞከርኩት ችግሮች አሉ። ለዚያ ችግር መፍትሄ መፈለግ ያለበት መንግስት ብቻ አይደለም። ጋዜጠኛ ተባብሮ መታገል አለበት። ለፕሬስ ነጻነትና ለመረጃ ተደራሽነት መሟገት አለበት። እርግጥ የሚዲያ ኢንደስትሪ ዝም ብሎ የሚገባበት አይደለም። ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም ገንዘብ ያስፈልገዋል። ባለሃብቱ በገንዘብ ቢያግዝ ጋዜጠኛ ሞልቷል። በተለያዩ ሚዲያዎች ድንቅ ችሎታ ያላቸው ጋዜጠኞችን አይቻለሁ። ዛሬ ሳንሱር የለም፤ በእኛ ዘመን የአንዲት ቃል እንዲያውም ፊደል ግድፈት የምታመጣው የትርጉም ስህተት አበሳ ታስቆጥራለች። እርግጥ በንጉሱ ዘመን ጃንሆይን በመጥፎ የሚያነሳ ወይም የሚተች ጽሑፍ አይጻፍም ነበር። ሌሎች ሚኒስትሮችንና የስራ ዘርፋቸውን ግን ተችተን እንጽፍ ነበር። በሙያው የማይቆጨኝን ሰራ ሰርቼ፣ አሰርቼ ለሌሎች አስተላልፌፊያለሁ ብዬ አስባለሁ።

ታዛ፦ ከአሜሪካ የክብር ዜግነት አግኝተዋል?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ ትክክል ሰጥታኛለች። የኔንብራስካ ስቴት ነው የሰጠኝ። ዱካኪስና ጆርጅ ቡሽ ሲወዳደሩ ለምርጫ ታዛቢነት ሄጄ በነበረ ጊዜ እግረመንገዴን ይህችን ስቴት ስጎበኝ ነው የተሰጠኝ። አሁን አሜሪካን ልሂድ ብል ያለምንም ችግር መሄድ እችላለሁ። በነገራችን ላይ ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በተያያዘ በጉብኝትና በስራ በርካታ አገሮች ሄጃለሁ። አሜሪካን አገር ደግሞ ተመላልሻለሁ። ልክ ጆን ኤፍ ኬኔዲ እንደሞተ ቢን ጆንሰን እና ጎልድ ዎተር ሲፎካከሩ የምርጫው ታዛቢነት እኔና ብርሃኑ ዘሪሁን ነበርን የሄድነው።

ታዛ፦ እዚያው የመኖር ሃሳብ አልመጣብዎትም?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ ለምን? ምን አጥቼ? ክብሬ የሚጠበቀው በአገሬ ስኖር ነው። በሰው አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታየሁ ስለምን እሸማቀቃለሁ? እኔ ብቻ ሳልሆን በዚያ ዘመን የነበርን ጋዜጠኞች መዋዕለ ነዋይ አታሎን መቅረትን አልፈለግንም። እዚህ በኑሮ ባይደላንም ነጻነታችንን የሚነፍገን የለም ስለዚህ…

ታዛ፦ ዛሬ ላይ ሆነው ስለ ትናንት የሚቆጩበት ነገር አለ?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ የለም። በአቅሜ መስራት ያለብኝን፣ መሆን ያለብኝን ሆኜ አልፌያለሁ። አንድ ዛሬ ዛሬ እየገባኝ የመጣው ነገር፤ እያረጁ በሄዱ ቁጥር ሕይወት እየጣፈጠችህ መምጣቷን ነው። ረጅም ዕድሜ የመኖር ስሜትና ፍላጎት ይመጣል። አሁንም ዕድሜ ኖሮኝ መልካም የሆኑ የአገሬንና የዓለምን የለውጥ ሂደቶች ብመለከት ደስ ይለኝ ነበረ። ነገር ግን አሁን ጊግዜው እያጠረ፣ እየመሸ ነው የሄደው። ግን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። ብዙ አሳይቶኛል። ክብርና ሞገሱን እየሰጠ አኑሮኛል። በቀሪ ዕድሜዬ የተሻለ ማንበብን እፈልጋለሁ። እርሱ እስከፈቀደ…።

ታዛ፦ ስለ አገራችን ወቅታዊ ሁኔታስ የሚሉን አለ?

አቶ ከበደ አኒሳ፦ ጥሩ ተስፋም ስጋትም አለ። ኢትዮዽያዊነት እየተዘመረ ነው። አሁንም «ኢትዮዽያ ትቅደም! »ን መርሀችን ማድረግ ብንችል ደስ ይለኛል። ዕድገትና ብልጽግናን ስንሻ ሰላምን ማስቀደም እንዳለብንም መዘንጋት የለብንም። ሚዲያዎች ለዚህ ቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸውና ኢትዮዽያን እንዲያስቀድሙ እመክራለሁ።

 ታዛ፦ በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ።

 አቶ ከበደ አኒሳ፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ። በርቱ። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top