ጥበብ በታሪክ ገፅ

ኢትዮጵያና ኤርትራ – አኵስምና መጠራ

ደዐማት

በእኛ ሀገር ሊቃውንት “ቀለም ሳይዘጋጅ፣ ብራና ሳይዳመጥ፣ ብርዕ ሳይቀረጽ” የተጻፈ ታሪክ የሚለው አባባል አንድ ረጅም ዘመን የቆየ ታሪክን ያመለክታል። ለማለት የተፈለገው የሰው ልጅ በጥንታዊ ሥልጣኔ ሥነ ጽሑፍን ብራና፣ በደንገል/ ፓፒረስ/papyrus፣ ወይም በቅጠል፣ በእንጨትና በቅርፊት ላይ ከመጻፉ፣ ሥዕልን ከመሣሉ በፊት ድንጋይ ቀርጾ ሰሌዳ ዕብን አዘጋጅቶ ጽሑፍ የጻፈበትን ዘመን ለማመልከት ነው። የሰው ልጅ በጋራ መኖር፣ በቋንቋ መግባባት፣ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን አዘጋጃቶ መተዳደር ከቻለ በኋላ ቀጣዩ የሥልጣኔ ጉዞ የየዕለቱ የማኅበራዊ ኑሮ ሥርዓቱን፣ የዘመን ክንውኑን፣ የተፈጥሮ መስተጋብሩን፣ የግልና የቡድን ስሜቱን በቃል፣ በምሳሌ/በምልክት፣ በፊደል በሥነ ጽሑፍ ከዚያም በረቂቅ ሥነ ሥዕል መዘገብ ነበር።

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ታሪካቸውን፣ ጥበባቸውን፣ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ዘግበው ማቆየታቸው ልዩ መታወቂያቸው ነው። በአንፃሩ በሀገራችን ለቅድመ ታሪክ ቅርሶች የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች አለመሰጠቱ፣ የተገኙትም የታሪካዊ ቅርሶች ጥናት በአብዛኛው ማለት ይቻላል ለምዕራባውያን ትንተና አሳልፎ መስጠቱ ስለራሳችን ታሪክና ማንነት የሆነውንም ያልሆነውንም ሌሎች እንዲነግሩን አድርጎናል።

 በዓለም ዙሪያ ባሉ ጥንታዊ የሥልጣኔ ታሪኮች ውስጥ በአንድ ወቅት አብበው ጥቂት ቆይተው የከሰሙ በርካታ ሥልጣኔዎች አሉ። ከዘመን ብዛት የደበዘዙ፤ ግን ያልከሰሙ የሥልጣኔ አሻራዎች እንዳሉ በኢትዮጵያም ልብ ይላል።

በእኛ ሀገር ቀዳሚ ከሚባሉት “ቀለም ሳይዘጋጅ፣ ብራና ሳይዳመጥ፣ ብርዕ ሳይቀርጽ” ዓለም ደረስኩብት ካለው ሥልጣኔ ሁሉ በላይ በሥነ ጥበብ፣ በአስተሳሰብ፣ በሕዝብ ሥብጥር፣ በንግድ፣ በእርሻ ምርትና በከብት ርባታ፣ በውትድርና በዜጎቻቸው የኑሮ ዋስትና፣ በኑሮ ደረጃ፣ በቋሚ ሀብት፣ በግዛት ስፋት በመሳሰሉት አስደናቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ታላላቅ ሥልጣኔዎች ተመዝግበው ይገኛሉ።

ደዓማት (ደዐመተ) እጅግ ጥንታዊ ከሚባሉት የዓለም ሥልጣኔዎች አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በየሃ፣ በአኵስም አካባቢና በሐውልተ መላዞ፣ በኤርትራ በሰነዓፈ-መጠራና ሌሎች አካባቢዎች ከተገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ለመረዳት እንደሚቻለው ደዓማት በጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ ኢተነባቢ ቅርጸ ፊደል (unvocalized) ደዐመተ [ ] የሚል ተገኝቷል። ይህም በስድስት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ላይ ከዐሥር ጊዜ በላይ ተደጋግሟል። በነገሥታቱ ስም ላይ የደዓማቱ ሙካሪብ (ሙካሪብ ዘደዓማት) እንዲሁም የነገሥታቱ የንግሥና ስማቸውን አሟልተው በሚጠሩበት ጊዜ አብሮ ይጠራል። ከዚህ በመነሣት ፍራንሲስ እንፍሬ ሥያሜው የሕዝብ ወይም የአካባቢ መጠሪያ ሊሆን ይችላል ሲል፤ ለማስረጃነት የደዓማት ነገሥታት ራሳቸውን “መለከነ ደዐመተ” መለከነ ማለት መለከ-ገዛ/ነገሠ የሚለውን ግሥ የሚወክል ሲሆን (ንጉሠ ደዐማት) ለማለት ስለሆነ ምስክር አድረጎታል (ፍ/ አንፈሬ)።

 አቻ ከሆኑ የግእዝ ነባር ሥያሜዎች በመነሣት ደዓመተ (ደዓማት) ማለትን ሲያመለክት ትርጉሙን በተለያየ መንገድ ልንረዳው እንችላለን። በዘመኑ የመረጃ ምንጭ ስለ ስሙ የተሰጡ ትርጉሞች በቀጥታ ባይኖሩም ለምሳሌ ስቱወርት ሞንሮ-ሂይ (2002) Ethiopia: The Unknown Land ላይ “ድኢምት” ከሚለው ነባር የአረብኛ ቃል ጋር በማገናኘት ደዓማት ማለት “ችካል”፣ ወይም “አምድ” ነው በማለት ተርጉሟል። በግእዝ ቋንቋ “ድዒም ወይም ድዒሞት” የሚለው አንቀጽ፣ ዘሩ ባይገኝም “ደዐመ” ከሚለው ግሥ ሊገኝ የሚችል ሲሆን መትከል፣ ማቆም፣ ድጋፍ ማድረግ፣ አንድን ነገር እንዳይወድቅ እንዳይንሸራተት ማጥበቅ፣ መመሥረት ጸንቶ እንዲቆይ ማድረግ ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “ድዒም”ን እይ) ቃሉን የመሠረቱትን የፊደላት ዘመዶች በቅደም ተከተል ሲጠኑ “ደዐመተ” የተመሠረተው በሦስት ፊደላት ነው። የመጨረሻው “ተ” ምእላድ (suffix) ነው። ምእላዱ ከሚያገለግልባቸው ሙያዎች አንዱ ለብዙ አንቀጽ (plural formation) ሲሆን ለምሳሌ ዓመት ብሎ ዓመታት፣ ነፋስ ብሎ ነፋሳት እንደሚለው “ደዓመ” በነጠላ ሲበዛ “ደዐማት” ሊሆን ይችላል። ከዚህ ትርጉም ስንነሣ ደዐማት ማለት ጠንካራና ጽኑ፣ የተተከለ የማይነቀል፣ የማይወድቅ “ደዒማ” በሚል ስም የሚጠሩ በርካታ የኢሮብ አካባቢ ሴት ነዋሪዎች አሁንም አሉ። (ሕሉፍ በቃል)

ወደ ፊት የሚመጣው ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ4500 ዓመት በፊት “ጤፍን”ና “እንሰት”ን የመሰሉ ከእኛ ውጭ የትኛውም ዓለም ያልተመረቱ የግብርና ምርቶች በአሁኗ ኢትዮጵያ ደቡባዊና ደቡብ ምዕራባዊ፣ እንዲሁም ማእከላዊና ሰሜን ምዕራባዊ ክፍል ዐባይን ጨምሮ ባሉ ወንዞች ዳርቻ ማምረታችን የታመነ ነው። በተለይ በዐባይ ሸለቆና መጋቢዎቹ ዝቅተኛ ተፋሰስ ባለባቸው የመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍል በርከት ያሉ የጋማና ቀንድ ክብቶችንም ማርባት በዚሁ ዘመን መጀመሩን የሚገልጹ ማስረጃዎች በብዛት ይገኛሉ። (ሔንዝ ገጽ፡11)

በዘመናት ጅረት ሳይፈታ እየጠነከረ የመጣው ሰብዓዊ የማኅበራዊ ኑሮ ትሥሥርና እያደገ የመጣው ሀብታቸው፣ እየረቀቀ የመጣው ጥበባቸው ጠንካራ መንግሥትና አስደናቂ ሥልጣኔን መሥርቷል። ሥልጣኔውም ራሱን እየተካ በጎረቤትና ሩቅ ባለው ታዛቢ ሳይቀር ተጽእኖና ተደሞ መፍጠሩ አልቀረም። በተለይ በዐባይ ወንዝ ዳርቻ የተጀመረው ከምንጩ ጀምሮ እስከ ማብቂያው የሜዲትራንያን ባህር ድረስ የመርዌ፣ የኑብያ፣ የፑንት፣ የግብጽ፣ ሥልጣኔዎችና ሌሎች አስደናቂ ሥልጣኔዎች መነሻውን በኢትዮጵያ ያደረገው እድገትና ማኅበራዊ አሰፋፈር ነው። ከእነዚህም አንዱ ደዓማት (ደዐመተ) ነው።

 የደዓማት ሥልጣኔና ሥርወ መንግሥት የተስፋፋው በመላው የምሥራቅ አፍሪካ፣ ሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ፣ ደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ እና የአፍሪካ ቀንድ አልፎ በአሁኑ አጠራር እስከ ደቡብ ዐረቢያ ድረስ ነው። የዚህ መጠነ ሰፊ የሆነ ግዛት ማዕከል ደግሞ እስከ አሁን የተገኙት በአፍሪካ በሰሜናዊው ኢትዮጵያና በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኤርትራ፣ በደቡብ ዐረቢያ ደግሞ

በአሁኗ የየመን ግዛት ሒምያር አካባቢ ለመሆኑ በቂ መረጃዎች አሉ። ስለ ደዓማት ብዙ አልተባለም፣ ጥቂት ምሁራን የራሳቸውን መላ ምት አስቀምጠዋል። ከዚያ ያንኑ ስናስተጋባ ቆይተናል። ስቱወርት ሞንሮ-ሂይ፣ ኤድዋርድ ኡሌንዶርፍና ሩዶልፍ ፋቶቪች ይኽ ሥልጣኔ መጠነኛ የሆነ የውጭ ተጽእኖ ቢኖረውም ሙሉ በሙሉ ሀገር በቀል ሥልጣኔ ነው በሚለው ይስማማሉ።

ፊሊፕሰን ደዓማት ግዛቱ ሰፊ ቢሆንም ማእከሉ ኢትዮጵያ ነው በዓረብ ግዛት ውስጥ ፈጽሞ አልነበረም ይላሉ። ኢትዮጵያዊው ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያና ስታንሌይ ብረስቲን ደዓማት ቅይጥ ሥልጣኔ ነው ባይ ሲሆኑ፣ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ምሁራን ደግሞ የኢትዮጵያውያን ብቻ ዕድገት ውጤት ነው የሚለው አቋም አላቸው።

 ደዓማት የሀገር ውስጥ ዕድገት ነው፣ የውጭ ሀገር ሥልጣኔ ቅጅ ወይም ቅጥያ ነው፣ ወይም የተቀየጠ ነው የሚለውን ለይቶ ማየቱ ተገቢ ነው። ለምሁራኑ አስተሳሰብና የጥናት ውጤት እንደመነሻ የተወሰደው ጭብጥ ምንድነው የሚሉትና ለሥልጣኔው መለኪያ የተወሰደው መረጃ ቋንቋንና ሥነ ጽሑፍን መሠረት ሲያደርግ፣ የመንግሥት አስተዳደርን የማኅበረሰብ አደረጃጀት መሠረት ሲያደርግ፣ ሃይማኖትንና የአምልኮ ሥርዓትን መሠረት ሲያደርግ፣ ኪነ ጥበብንና ሥነ ጥበብን መሠረት ሲያደርግ በየራሱ ሚዛን ስለሚበይን መላምቶቹን ከመቀበላችን በፊት የመላምቱን መነሣ በጥንቃቄ ማጤኑም ገንቢ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋ ያለቸው በባህል የሚለያዩ፣ ወይም አንድ ባህል ያላቸው በቋንቋ የሚለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ያሏት ከመሆኗ አንፃር የታሪክ ውሳኔዎች ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረጉ ከስሕተት ያድናል። በተጨማሪ ሥልጣኔው በዘመኑ የነበረው የውጭ ግንኙነት፣ የሀገር ውስጥ ፖሊሲ፣ የሥልጣኔዎችን ቅደም ተከተል አብሮ በማየትን ይጠይቃል። ዋናው ግን ደዓማት ገናና ሥርወ መንግሥትን መሠረት ያደረገ ተከታታይነት የነበረው አስደናቂ ሥልጣኔ የነበረ መሆኑ ነው።

በየሃ( )ና አካባቢው የአርኬዎሎጅ ጥናት ያደረጉት ፍራንሲስ አንፈሬይ፣ 1963፣ በ1972-73፣ ሩዶልፍ ፋቶቪች በ1971 በሕንፃዎች ፍርስራሽና ከሸክላ፣ ከብረትና ከድንጋይ የተሠሩ ልዩ ልዩ ሥነ ጥበባዊ ቁሳቁሶች በመነሣት አሁን የሚታመነው የደዓማት ሥልጣኔ ሥርወ መንግሥት በ1000-800 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እንደተጀመረ ይናገራሉ።

መሪዎቹ በቀይ ባህርና በሕንድ ውቅያኖስ የንግድ ዝውውር በምሥራቅ በኩል በምዕራብ ደግሞ በዓባይ ሸለቆ ለም መሬት፣ በተከዜ (አጥባራ) ና ሌሎች ወንዞች በሚተገበር የእርሻ ልማት የአራዊት አደን፣ የከበሩ ማዕድናት ቁፈራ ላይ የተመሠረተ የንግድና የሸቀጣ ሸቀጥ ልውውጥ በማድረግና ጠንካራ ማኅበራዊ ትሥሥርን በመፍጠር አንድ ሥርወ መንገሥት የመሠረቱ ገዥዎች ነበሩ። በንግድ ልውውጦቻቸው ወርቅ፣ ብር፣ ዝሆን፣ የኤሌ ሸል፣ የከርከሮ ቀንድና አራዊትን በመሸጥ ወይም በመለወጥ ይታወቁ ነበር። በድንጋይ ላይ ተጽፈው የተገኙት በጥንታዊው የግእዝ ፊደል ወይም በተለምዶው ሳቢያን(ሳባዊ) የተጻፉ ሥነ ጽሑፎች እንደሚገለጹት በርከት ያሉ የአካባቢውን ገዥዎች ስም ይዘዋል። የደዓማት ሥልጣኔ ምናልባትም እጅግ አስደናቂ ከሚያሰኙት ሥራዎች አንዱ የብርት መዓድን አጠቃቀማቸው ሲሆን ከልደተ ክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ብረትን አቅለጠው በርካታ ቁሳቁሶችን ለመምረታቸው የሚያረጋግጡ መረጃዎች ተገኝተዋል። በ1955-56 እኤአ ጅየን ለክላንት በአርኬዎሎጅ አማካኝነት በሐውለተ መላዞ አካባቢ የተገኘው የጥጃ ምስልና የእጣን ማጨሻ ከዚሁ ሥልጣኔ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጠዋል።

የደዓማት ሥልጣኔ አሁን በተለመደው ግን ገና ብዙ ሥራ በሚጠብቀው መላምት የቅድመ አኵስም ሥልጣኔ ነው። ደዓማት ማእከሉን “የሃ” በማድረግ በኋላ ለቅድመ አኵስም ሥልጣኔ መነሻ ሆኗል የሚለው አባባል በሰፊው ሲነገር ይሰማል። ደዓማት መጠነ ሰፊ በነበረው ግዛቱ አዶሊስን የንግድ፣ የፖለቲካና፣ የሥልጣኔው የባህር በር አድርጎ ዐርበ ሰፊ የመንግሥት ሥርዓት የመሠረተ ሥልጣኔ ሆኖ ቆይቷል። የፖለቲካ አስተሳሰቡ ውስጥ ወንዶችም ሴቶችም ጠንካራ ተሳትፎ ነበራቸው፤ በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ብዙ ሕዝቦችን ያቀፈ፣ ጠንካራ የወታደራዊ ኃይል ያለው፣ በሰሜን ከሜዲትራንያን፣ በደቡብ ምሥራቅ ከደቡብ አረብ ጋር ጥብቅ የኢኮኖሚና የሥነ ጥበብ ትሥሥር የፈጠረ፣ እግጅ ውብ የሆነ የሥነ ጥበብ ክንውንን ይዞ የቆየ አደረጃጀት ነበረው።

 ራሱን ከፍ ወዳለ ሥልጣኔ በማሳደግና ሌሎች ለውጦችን በማስተናገድ ደረጃ የደዓማት ሥርወ መንግሥት አሁን ከተገኙት ልዩ ልዩ ሕብርና ውበት ካላቸው ቁሳቁሶች፣ ከቤት አሠራሩ፣ ከአምልኮ አፈጻጸሙ፣ አንፃር በየጊዜው በውስጥ ያደጉም ይሁን በውጭ የተፈጠሩ የአስተሳሰብ ለውጦችን በጊዜያቸው እንዳስተናገደ ያረጋግጣሉ። ይህንንም በዘመናት ተከታታይነቱን በኪናዊ ለውጦቹ ለመገንዘብ ተችሏል። አንዳንዶቹ ለውጦች የሥርወ መንግሥቱን መናኸሪያ ቦታና ከፍ ያለ የሥነ ጥበብ ደረጃንም እስከ መቀየር የደረሱ ነበሩ። ስለዚህ የሥልጣኔውን አሻራ በተለያዩ ማእከሎች ለማየት ተችሏል።

 ለአንድ ሥልጣኔ በተከታታይ ጸንቶ ለመቆምና በየጊዜው የሚነሣ ትውልድን የማገልገል አቅም የሚኖረው ከወቅታዊ አስተሳሰቦችና ከለውጦች ጋር ያለው አብሮ የማደግ፣ የማዛመድና የመለወጥ ጠባይ ሲኖረው ነው። ሥልጣኔ የሚያድገው ከኅብረተሰብ አስተሳሰብ ጋር ነው።

“አኵስም ለሥልጣኔው ያስፈለጉትን ጠንካራና እጅግ ብዙ የሰው ኃይል፣ መጠነ ሰፊ የጥሬ ሀብት ክምችት፣ የንግድ ልውውጥ፣ ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥት፣ በመንግሥት ሥራ እርስ በርሱ የተሣሣረ የግዛት መተማመንና አንድነት፣ ከቅድመ አኵስም የደዓማት ሥልጣኔ እንዳለ ለመውረሱ ብዙዎች ይስማማሉ”

የተነሣበትን አስተሳሰብ፣ የዕውቀት ደረጃ፣ ሁለንተናዊ የሀብት አቅም፣ አደረጃጀት፣ ዳራና ራዕይ ይዞ ከቆየ ሌላው ሲለወጥና ሲያድግ ባለበት ከቆመ ያለምንም ጥርጥር ይዋጣል ወይም ይጠፋል። ለምሳሌ በደዓማት ዘመን አካባቢ ከነበሩ ሥልጣኔዎች “አማሌቅ”ን በሳዖል ዘመን ወይም “ኢያሪኮን” በኢያሱ ዘመን ብንወስድ ራሳቸውን አጥረው በመቆየታቸው ሲፈርሱና ሲጣሱ ሕልውናቸውም ሥልጣኔአቸውም ሊረሳ ችሏል። የደዓማት ሥርወ መንግሥት ቢያንስ አሁን ባሉን መረጃዎች በተከታታይ ከአምስት እስከ ስድስት መቶ ዘመን የቆየ ሥልጣኔ ነበር። ከዚያም አልጠፋም እየተዳከመ ሲመጣ በዚያው አካባቢ ለተነሡ ሥልጣኔዎች መሠረት ወይም ማጠናከሪያ በመሆን ቀጥሏል። ከእነዚህም የአኵስም ሥልጣኔ አንዱ ነው።

 ለደዓማት ሥርወ መንግሥትና ሥልጣኔ መዳከም እንደ ዋና ምክንያት የሚወሰዱት እጅግ ሰፊ በሆነ ግዛቱ በመካከል የተፈጠረው መለያየት ነው። በሂደት የተነሡ ትናንሽ መሳፍንት ለጥቂት ጊዜ ራሳቸውን ከገዙ በኋላ ከማእከላዊው አሐዳዊ መንግሥት (monarchy) ጋር የነበራቸው ግንኙነት መላላት እነሱም በራሳቸው እንዳይቆሙ አደረጋቸው። በተለይ መለያየቱ ካመጣው ሁለንተናዊ መዳከም በተጨማሪ ምናልባትም ለግጭት መንሥኤም ሊሆን ይችላል፣ እያደር የንግድ ልውውጥ፣ የማኅበራዊ አስተዳደር ትሥሥር መዳከም፣ የፖለቲካ መራራቅ የመሳሰሉት ሲፈጠሩ በሚወለዱ ሌሎች የመለያየት ጣጣዎች ደዓማት ቀስ በቀስ ተዳከመ። ይሁን እንጅ በወቅቱ በደዓማት ሥርወ መንግሥት መዳከም ወዲያውኑ የውጭ ጠላት ባለመግባቱ ደዓማት ከነአካቴው ሳይጠፋና ሕልውናው ሳይረሳ ለአኵስም ሥልጣኔና ሥርወ መንግሥት መጠናከር እንደ መነሻ ሆኖ አገልግሏል። ለዚህም በቅርበት የነበረው ማኅበራዊ ትሥሥር እገዛ አድርጓል። ስለዚህ በሳይንሳዊ ምርምር ግኝት እስከ አሁን ባለው መረጃ በይበልጥ የሚታመነው ደዓማት የቅድመ አኵስም ሥልጣኔ በመሆን ለአኵስም መነሻ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ ነው። በትውፊት የሚታመነውም ከዚሁ የራቀ አይደለም።

 ለደዓማት ሥርወ መንግሥትና ሥልጣኔ ማሳያ የሆኑ በጥቅል ስማቸው የቅድመ አኵስም ሥልጣኔ ቅርሶች ዛሬ በኢትዮጵያና በኤርትራ በሰፊው ይገኛሉ። በኢትዮጵያ አኵስም በኤርትራ መጠራ በዋናነት ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ የሃ የደዓማት ዋና መናኽሪያ፣ ዋና ከተማ፣ ዋና ቤተ መቅደስ፣ ዋና የገበያ ማዕከል፣ ዋና የውጭ ግንኙነት ማእከል፣ ዋና የኢኮኖሚ መድረክ ሲደረግ በኤርትራ መጠራና አዶሊስ የደዓማት ዋና የገበያ ማእከል፣ በአዶሊስ በኩል ዋና የኢኮኖሚ ልውውጥ ወደብ፣ በመጠራም የታላላቅ አብያተ መቃድስ፣ የንግድ ማእከሎች፣ የታላላቅ ሰዎች መኖሪያና መገኛ ተደርጎ ይወሰዳል። በአኵስም፣ በየሃ፣ በመጠራና በቆሐይቶ፣ በሐውልተ መላዞ፣ በሐውልቲ፣ በአዶሊስ፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች በማይፋቅ፣ በማይደበዝዝ፣ በማይለወጥ የጥንታዊ ግእዝ ፊደላት ታሪኩ ተመዝግቧል። አኵስምና መጠራ በአጠቃላይ ግንዛቤ የሁለቱም ተከታታይ ሥልጣኔዎች (የቅድመ አኵስምና የአክስም) የዘለዓለም ምስክሮች ናቸው። ቆይቶም ይኽ ምስክርነት በድኅረ አኵስም እና በቀጣይ ዘመናት እንዴት እንደቀጠለ መጠቆሜ አይቀርም።

በሳይንሳዊ መላምት አኵስም ሥልጣኔ የተጀመረው ከ100 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው የሚለው አስተሳሰብ ቀስ በቀስ ወደ 1000 ዓመት መጠጋቱ እየታየ ነው። ይሁን እንጅ ከላይ በመጠኑ ለማየት እንደተሞከረው አኵስም ከ1000 ዓመት እስከ 500 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ድረስ የነበራትን ተጽእኖዎች የሚያሳዩ ቁልፍ መረጃዎች እስከ አሁን አልተተነተኑም። (Αδουλίς አዱዎሊስ) ከአሁኑ ምጽዋ ወደብ በስተደቡብ 30 ማይል ያህል ርቃ የምትገኝ የአክሱማውያን የባሕር በር ነበረች። ግሪካዊው ነጋዴ ኮስማስ ኢንዲኮፕለዩሰተስ (Cosmas Indicopleustes/ቶማስ አዳዌ ውቅያኖስ) በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአዶሊስ በኩል ሲያልፍ ሁለት የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን መዝግቧል። የመጀመሪያው ከ247-222 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበረው ፕቶሎሚ ዩርጌትስ የአክሱማውያን ዝሆኖችን ተጠቅሞ ጠላቶቹን እንዴት እንደወጋ የሚገለጽ ሲሆን፤ ሁለተኛው 27ኛው የአኵስም ንጉሥ በሰሜናዊ ግዛቱና በደቡብ ዐረብ ያገኘውን ድል የሚዘክር ነበር። ሁለቱም የአክሱማውያን ገናናነት የሚያሳዩ ነበሩ። ከስከስ ሌላው የዘመነ አኵስም መዘክር ነው፣ ከመጠራ ስምንት ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቀው ይኽ የቅድመ አኵስምና የዘመነ አክኵስም ታሪከዊ መካነ ቅርስ ሌላው አስገራሚ ቦታ ነው። ቁመታቸው እስከ 14 ሜትር ድረስ የሚደርሱ የግእዝ ጽሑፍ ያለባች ሐውልታት የተገኙበት ልዩ ቦታ ነው።

 አኵስም ለሥልጣኔው ያስፈለጉትን ጠንካራና እጅግ ብዙ የሰው ኃይል፣ መጠነ ሰፊ የጥሬ ሀብት ክምችት፣ የንግድ ልውውጥ፣ ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥት፣ በመንግሥት ሥራ እርስ በርሱ የተሣሣረ የግዛት መተማመንና አንድነት፣ ከቅድመ አኵስም የደዓማት ሥልጣኔ እንዳለ ለመውረሱ ብዙዎች ይስማማሉ። በቀይ ባህርና በሕንድ ውቅያኖስ ያሉት የባህር በሮቹ፣ ዐባይን ጨምሮ ዓመቱን ሙሉ ሳይጎድሉ የሚፈሱት ታላላቅ ወንዞቹ በሰፊው ግዛቱ ያለው የእርሻ ምርት፣ በአሁኑ ኢትዮጵያ ማእከላዊ ሜዳማ ግዛቶች ያለው እንስሳት ሀብት፣ በደጋማውም በቆላማውም አካባቢ ያሉ የዱር እንስሳት አደን፣ በሰፊው ግዛቱና በብዙ የሰው ኃይሉ መሠረት የሚከናወነው የማዕድን ሀብት አኵስም ጠንካራ የጥሬ ሀብት ክምችት ባለቤትና ከዚህ ለሚመነጨው የንግድ ሀብት ባለቤት እንዲሆን ረድቶታል። ይኽ እንደተጠበቀ ሁኖ በኤርትራም ያለው የዘመነ አኵስም ቅርስ በጥልቀት የሚስረዳው የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ማእከሎቹን ሰፊነት፣ በዚያም ያለው መጠነ ሰፊ የጥሬ ሀብት ምርት፣ የንግድ ልውውጥ፣ ወርቅና ብርን የመሰሉ የማዕድናት ሀብት የባሕር በሮቹ በተለይም የአዶሊስ ወደብ የነበራትን ቁልፍ የኢኮኖሚ ሚና ነው። በኢትዮጵያ ካሉት የአኵስም ከተማ፣ ሀውልተ መላዞ፣ ሽሬ፣ ውቅሮ፣ ተምቤን፣ ገረዓልታ፣ እንዲሁም ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ አሁንም በርከት ያለ የምርምር ሥራ ያልተሠራባቸው ማእከላዊ የኢትዮጵያ ግዛቶች፣ (በተለይ በእርሻ፣ በከብት ርባታና የአደን ሥራ፣ የማዕድን ቁፋሮ የተከናወነባቸው) ለአኵስም ሥልጣኔና ሥርወ መንግሥት ዋና ምሥክሮች ናቸው።

 የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ለጥንታዌ ሥልጣኔ ትልቁ ግብዓት ነው። የሰው ቁጥር ካነሠ ጥሬ ሀብት በውሱን ቦታዎች ብቻ ከሆነ ሥልጣኔ አይታሰብም፣ ለአክሱማውያን (ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን) የተፈጥሮ ጥሬ ሀብትን በተለይ ግብርና ዋና የኢኮኖሚ ምንጫቸው አድረገው ስለሚወስዱ በወንዞች አካባቢ እጅግ ሰፊ ሀገር መሬት ይቆጣጠራሉ። ይኽ ምናልባት እንደ ዓባይ ያለ ወንዝን ከምንጩ እስከ ሱዳን፣ ግብጽ እስዋን ድረስ ጥቅም ላይ ያዋለ ሊሆን ይችላል። ለእንስሳት ሰፊ የግጦሽ መሬት፣ ለዱር አራዊት አደን በተለይም የኢኮኖሚና የውትድርና ጠቀሜታ ያላቸው እንደ ዝሆን፣ ጎሽ፣ አጋዝን፣ ከርከሮ የመሳሰሉትን ለማግኝት ሰፊ ግዛትና የሕዝቦች ትሥሥር ያስፈልጋቸው ነበር። በዚህ

“የላስታው ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ሚስት ቅድስት ንግሥት መስቀል ክብራም ከዚሁ አካባቢ ገዥዎች በተለይም በኢትዮጵያ መደባይ ታብር አካባቢ የሥጋ ዝምድና ነበራት። ስለሆነም በላስታ-ላሊበላ ያሠራችው ቤተ ክርስቲያንም “ቤተ አባ ሊባኖስ” ይባላል”

መሠረት የበርካታ ቋንቋና ባህል ያላቸው ሕዝቦች ትሥሥር ውጤት በመሆን አኵስም እጅግ ጠንካራና ገናና መንግሥት ሆኖ ተመሥርቷል። ይኽ የአኵስም ብዝኅነት (Multi-cultured, Multi-nation and Multilingual) መገለጫ ሲሆን፤ በምሥራቅ አፍሪካ አኵስምን የመሰለ ጠንካራ መንግሥት አልታየም። ማኔ የተባለ የፋርስ ሃይማኖታዊና ሕዝባዊ መሪ (216-274 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ) በዓለም ላይ ከቀድሞ ጀምሮ አራት ኃያላን መንግሥታት አሉ፤ ሮም፣ ፋርስ፣ ቻይናና አኵስም ናቸው ብሏል። በተመሳሳይ ዘመን የታላቁ እስክንድር (Alexander the Great) መኰንንኖች በጢሊሞስ (ፕቶሎሚ) ካልዕና ሣልስ ከአኵስም ጋር የተሳካ የንግድ ግንኙነት እንደነበራቸው ይልቁንም ጠላታቸው ሴሉሲይን ለመግጠም የሚያስችላቸውን የዝሆን ላይ ውጊያ የጦርነት ስልት ከአኵስም እንደቀሰሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 ደሀርት አውሮፓውያንና የአረብ ጸሐፊዎች ስለ አኵስም እጅግ ብዙ ነገሮችን ጽፈዋል፣ የባሕር በሮቻቸው፣ ታላላቅ ከተሞቻቸው፣ የተስፋፉባቸው ግዛቶች፣ የእምነት ጥንካሬአቸው፣ የማኅበራዊ ትሥሥራቸውንና የውትድርና ብቃታቸውን ጭምር በአክብሮት ዘግበዋል። የአኵስም ቅርጸ መንግሥት በብዝኅነት ላይ የተመሠረተ አሐዳዊ (monarchy) መሆኑ፣ ግዛቱም የአንድ ወጥ ሕዝብ አለመሆን፣ በብዙ መልኩ በአኵስምና በመጠራ፣ በኢትዮጵያም በኤርትራም በተገኙ የድንጋይ ጽሑፎች ተገልጧል። ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ4ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ኢዛና ዘመነ መንግሥት አኵስም ንጉሥ ራሱን የገለጸበት አገላለጽ ንጉሥ ኢዛና “የሳባ፣ የሳለሄን፣ ሂምያርና ደሁ- ራይዳን” ንጉሥ ብቻ ሳይሆን የሐበሻት (ቅይጥ ሕዝቦች) ንጉሥ የሆነ ንጉሠ ነገሥት እንደነበር በግእዝና በግሪክ ቋንቋ የተጻፉ የማይጠፉት፣ የማይደበዝዙ፣ የማይፋቁ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ይመሰክራሉ። በቋንቋ ረገድ በጽሑፍ ያልተገለጹት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ቢያንስ በጽሑፍ  የተገኙ ሁለት ቋንቋዎች በአንድ አይነት ፊደል ሲገለጹ፣ አኵስም ከተፈጠረች ብዙ ዓመት በኋላ በአውሮፓ የተነሣው የዮናንያን መንግሥት ቋንቋ “ግሪክ” ወይም “ጽርዕ” ሳይቀር በአኵስም እና በመጠራ በአዶሊስ ወደብ ተጽፎ ተገኝቷል። ተመሳሳይ ሁኔታን በብዙዎቹ የአኵስም ነገሥታት ሳንቲሞች ላይ ታይቷል።

 አኵስም-መጠራ ድኅረ ክርስትና

ጻድቃነ መጠራ በኤርትራ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ከአስመራ ከተማ በስተደቡብ አቅጣጫ 136 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ከሰነዓፈ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ በጥንቱ መጠራ አካባቢ የሚገኙ ጥንታውያንን ገዳማት ይወክላል። እነዚህ ገዳማት በዘመነ አኵስም ክርስትና ወደ አኵስም መግባት ጋር የተያያዙ ለሥርዓተ ምንኵስና ምሥረታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው። ዛሬ ደግሞ በኤርትራ ክርስቲያኖች ዘንድ ለሥርዓተ ምንኵስና ታሪክ እንደ ቅድመ ነገር ይጠቀሳሉ። ጻድቃነ መጠራ ሰባት ናቸው። በገድለ ጻድቃን ዘመጠረ አገላለጽ “ወወጽኡ እሉ ቅዱሳን መንገለ ገዳመ ቡር ወቦ እለ ዔሉ ዘይሰመይ መጠራ፣ ወቦ እለ ዔሉ ገዳመ ባረክናሃ፣ ወቦ እለ ዔሉ ሶርያ ወዳብራ” በማለት ይገልጣል። በሂደት በመጠራ ከ5700 ማኅበረ መነኰሳትን እንደሰበሰቡና ሥርዓተ ገዳምን እንደሠሩ ይነገራል። የተወሰኑት በገዳመ ባረክንሃና ሌሎቹ ደግሞ እምባ ሶይራ ደብረ ሓርሳ፣ ገዳመ ሰፍኦ፣ ገዳመ ማዕዶት፣ ገዳመ ሰራሕቶ መካነ ጊዮርጊስ፣ ማየ ጸዓደ፣ ደብረ ዳሞ፣ በተምቤንና በሌሎችም የኢትዮጵያ አድባራት ጥንታውያን ቦታዎች ገብተው ተቀምጠዋል። በአጠቃላይ በኤርትራ ደቡባዊ ክፍል በሰነዓፈ አካባቢና በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በትግራይ ክልል ውስጥ ቅዱሳት መካናትን መሥርተዋል። ጻድቃነ መጠራ፣ በኢትዮጵያ እንደሚታወቁት ተሰዓቱ ቅዱሳን ናቸው፤ በኢትዮጵያ የፃድቃን አመጣጥ ሀገረ አኵስም (ኢትዮጵያ) ከነበራት ገናና ሥያሜና ፍትሐዊነት፣ ጠንካራ የመንግሥት አቋም ጋር የተያያዘ ነበር። እነሱም አኵስም እንደ ቅድስት ሀገርና መጠለያ (safe haven) ተጠቅመዋታል። በግዛቱ ተፈቅዶላቸው ማኅበረ ደጓዔ፣ ማኅበረ በኵር፣ ማኅበረ ጻድቃን የሚባሉ ገደማትን በአኵስም አካባቢ መሥርተዋል። ቀጥሎም ተሰዓቱ ቅዱሳን እንዳ አባ ጰንጠሌዎን፣ እንዳ አባ ሊቃኖስ፣ እንዳ አባ ጉባ፣ እንዳ አባ ገሪማ፣ እንዳ አባ አፍጼ፣ እንዳ አባ ጽሕማ፣ እንዳ አባ አረጋዊ፣ እንዳ አባ አሌፍና እንዳ አባ ይምዓታ የተባሉ መካናትን መሥርተዋል።

 በኤርትራ ሰንዓፈ አካባቢ ያሉ ከክርስትና በፊት የነበሩ የቅድመ አኵስምና የአኵስም ዘመን ታሪካዊ ቦታዎች በለውከለው (መጠራ) ከስከሰ፣ ቋሓይቶ፣ የመሳሰሉት ቦታዎች የታወቁት ናቸው። አቡነ ዘሊባኖስን ዋናው ናቸው (የኤድዋርድ ኡሌንዶርፍ (1992) An Ethiopic Inscription በሚል ርዕስ (በJournal of the Royal Asiatic Society ገጽ 167-173) እንዳሠፈረው። ደብረ ሊባኖስ ዘሐም በማዕረግ ስሙ ደብረ ወርቅ ከዘመነ አክሱም ጀምሮ የሚታወቅ ጥንታዊ የጻድቃነ መጠራ (በኤርትራ) በኢትዮጵያ ቀደምት (ጻድቃን) ገዳም ነው። አሁን በአካለጉዛይ ሥር በኤርትራ ይገኛል። መሥራቹ አባ መጣዕ በኢትዮጵያም በኤርትራም ትልቅ አባት ናቸው። ገዳማቸው በአክኵም ጽዮን ግብዛና ሥር የነበረበትም ጊዜ ነበር። ለዘመነ አክሱም ነገሥታት እንደ መንፈሳዊ አባት ያገለገሉበት ጊዜም ነበር። የገዳሙ መሪ በፊት ዕጨጌ ዘ-ደብረ ሊባኖስ፤ በኋላም ዐቃቤ ሰዓት በመሆን በአኵስም ቤተ-መንግሥት ከፍተኛ ተሰሚነት ነበራቸው። በኢትዮጵያ የአክኵም ዘመን ያህል አይሁን እንጅ በየዘመኑ የዚህ ገዳም ትልቅነት በሰፊው ተወስቷል፣ በዘመነ አክሱም የታላላቆቹ ነገሥታት መንፈሳዊ አባቶች የሚመረጡት ከዚህ ገዳም ነበር፣ ንጉሥ ገብረ መስቀል ርስት ለገዳሙ እንደሰጠ በገዳሙ ተመዝግቧል። የላስታው ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ሚስት ቅድስት ንግሥት መስቀል ክብራም ከዚሁ አካባቢ ገዥዎች በተለይም በኢትዮጵያ መደባይ ታብር አካባቢ የሥጋ ዝምድና ነበራት። ስለሆነም በላስታ-ላሊበላ ያሠራችው ቤተ ክርስቲያንም “ቤተ አባ ሊባኖስ” ይባላል። በይኩኖ አምላክ፣ አምደ ጽዮን፣ ዳዊትና ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ሁሉ የቦታው ገናናነት እንደተጠበቀ ነበር።

በላስታ ቤተ አባ ሊባኖስ ውቅር ቤተ መቅደስ ከመታነፁ በተጨማሪ በአሁኑ የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ዞን የሚገኘው ደብረ ሊባኖስ የአቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ሥያሜ ከዚሁ ገዳም መሥራች አባ መጣዕ (አቡነ ዘሊባኖስ) ጋር የተያያዘ ነው።

ቡር የሚባለው ቦታ በአሁኑ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በሁለቱም ግዛት መካከል ያለ በኢትዮጵያ የሰሜናዊ ክፍል በተለይም በሽሬ እንዳ ሥላሴና በደቡባዊ ኤርትራ ክፍል የሚገኝ ግዛት ነው። በንጉሥ ካሌብ ጊዜ የመጡ ጻድቃን ተቃውሞ ሲገጥማቸው በንጉሡ ጣልቃ ገብነት እንደተስማሙ (ገድለ አረጋዊን ጠቅሶ ጉይዲ አብራርቶታል (1895)፣ ከአቡነ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን ገድል እንደሚነበብው ደግሞ ቡር ትልቅ ግዛትና የንግድ መተላለፊያ እንደነበር ነው። በመጠራ በርካታ የግእዝ ጽሑፍ ያላቸውና የሌላቸው ሐውልቶች ይገኛሉ። እጅግ ብዙ የቤቶች ፍስራሾችና ከሁለት በላይ የዘመነ አኵሱም አብያተ ክርስያናት መሠረት ይገኛል። እንዳ ሚካኤልንና ታእካ ማርያምን የመሰሉ አብያተ ክርስቲያኖችና የክርስቲያኖች የመቃብር ፍራሾችም ተገኝተዋል። እስከ ዘመነ አርማሐ ድረስ የነበሩ በርካታ የአክሱም ነገሥታት ሳንቲሞች በመጠራ ተገኝተዋል። መጠራ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደጠፋ ባይታወቅም ከ7ኛው መቶ ክፍል ዘመን በኋላ ይኽ ነው የሚባል አሰፋፈር እንደሌለባት አንፈሬ ጽፏል።

 ሌላው በሐማሴን የሚገኘው ጥንታዊው ደብረ ቢዘን ገዳም በኢትዮጵያም በኤርትራም በታሪክ እጅግ ትልቅ ቦታ አለው። ከአስመራ ከተማ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይኽ ገዳም፣ መሥራቹ አቡነ ፊሊጶስ ሁለቱም ሰንበቶች መከበር አለባቸው ብለው ከሚያስተምሩት መምህራን የሚመደቡ ሲሆን፤ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ለዚህ አባት ትልቅ አክብሮት ነበራቸው። ደብረ ድኁኀን፣ ደብረ እንድርያስ ደብረ ኮል (ጎል) የአቡነ ቡሩክ አምላክ ገዳም እየራሳቸው የድኅረ አክስም ዛግዌና ድኅረ ዛግዌ ታሪክን ሥነ ጥበብ መዘክር ናቸው።

 የአክሱም-መጠራ እና አካባቢያቸው መካነ ቅርሶችና በቁፈራ የተገኑ ሥነ ጥበባዊ ቁሳቁሶች የምሥራቅ አፍሪካን የቅድመ አኵስም ደዓማት፣ የአኵስምን የቅድመ ክርስትናንና ክርስትና ዘመንን ጥበብ፣ ባህል፣ ሥርዓትና ቅርጽ መንግሥት፣ የማኅበረሰብ አኗኗር፣ የንግድና ኢኮኖሚ ልውውጥ፣ የውጭ ግንኙነት ፍንትው አድረገው የሚያሳዩ ናቸው። የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈት፣ በአካባቢው ሰላም መስፈን ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ለእነዚህ ታሪካዊ ጥናቶችም ትልቅ ትርጉም አለው። ምናልባትም ከተቻለ የጋራ የሆነ ሥራን ለመሥራት አመች ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል።

 በመጨረሻም የቅድመ አኵስምንና የአኵሱምን ታሪክና ሥልጣኔ ለመረዳት በራሳቸው ፍላጎትና ቅድመ መነሻ የተሰጡትን ትንታኔዎች በመያዝ በመጀመሪያ የደከሙበት ምስጉን ምሁራንን ሥራዎች በጥንቃቀቄ ማጥናቱ እጅግ እጅግ ተገቢ ነው። በመቀጠል አሁን ያሉንን መረጃዎችን በሳይንሳዊና ንጽጻራዊ መንገድ መረዳት በጥንቃቄ መተንተንን ይጠይቃል፣ በተለይ ቀድመው ለተሰጡ መላምቶችና ትንታኔዎች ብቻ እጅ ሳንሰጥ አማራጭ አስተሳሰብን መከተል እንዳለብን ለመጠቆም እወዳለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top