ጥበብ እና ባህል

“አጌም” ‹ንጉሥ ይገረፋል፤ ሰማይ ይታረሳል!›

ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዕትሞች “አጌም” የሚለው ፅንሰ- ሀሳብ፡-

“ከባህላዊ ፍችው አንፃር ሲታይ በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈው የመጡና በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ትልቅ እሴት ተቆጥረውና ተከብረው የኖሩ ጥንታወዊ አባቶች የመሠረቷቸው ሕጎች በባህላዊ የአስተዳር ተቋማት መሪዎች መጣሳቸው ሲታወቅ ሰላምን ለመመለስ የሚከናወን ‘ህዝባዊ ዐመፅ’ ማለት ነው። አጌም በባህል የተፈጠሩ፣ በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ፣ አኙዋዎች ከጥንታዊ አባቶቻቸው ከተረከቧቸው ድንቅ የሰላም ጥበቃ መንገዶች አንዱና ዋነኛው ትውፊታዊ እሴት ነው።”

 በሚል ለመግለፅ ሞክሬያለሁ።

በባህላዊ መሪዎች፣ ማለትም በኜያው (በንጉሡ) ወይም በኜያው ሥር ባሉ ኳሮዎች (የአካባቢ መሪዎች) ጥሰት ምክንያት ህዝባዊ ዐመፁን የሚያስነሱ በርካታ ባህላዊ ሕጎችና ደንቦች መካከልም፡-

ሀ) በህብረተሰቡ አባላት መካከል አድልኦ መፈፀም፣ ፍትኅ ማጓደል፣

ለ) በየዓመቱ ከተቻለ ሦስት ጊዜ (በአራት በአራት ወራት)፣ ካልተቻለ ሁለት ጊዜ (በመንፈቅ፣ በመንፈቅ)፣ አጉዋጉዋ (ግብር እንደማለት ነው) አዘጋጅቶ ህዝቡን አለማብላትና አለማገናኘት፣

ሐ) ስስታም፣ ስግብግብ፣ ሆኖ መገኘት፣

መ) በጦርነት ጊዜ ከፍርሀት ወይም ከቸልተኝነት የተነሳ የንግሥና እና የበትረ-መንግሥት (የህብረተሰቡ ኅልውናና ሉዐላዊነት ትእምርታዊ መገለጫዎችን (symbols, emblems of power) ጥሎ በመሸሽ ለጠላት አሳልፎ መስጠት፣

ሠ) ከሌሊቱ ስድስት ስዓት በፊት ከሚስቱ (ከሚስቶቹ) ጋር የግብረ- ሥጋ ግንኙነት ማድረግ እና የመሳሰሉት የሕግ ጥሰቶች መፈፀሙ ሲታወቅ፣

 (ረ) “ኦቶችንግ”ን (የነፍስ ግድያን) ጉዳይ በጊዜውና በአግባቡ ወደ ጆዶንጎ (ወደ ሀገር ሽማግሌ) በቸልታ ካለመምራት የተነሳ በገዳይና በሟች ቤተሰቦች መሀል ተጨማሪ የሰው ሕይወትና ንብረት መጥፋቱ ሲታወቅ፣ ወዘተ፣ መሆናቸውን ማስታዎስ ያስፈልጋል።

ይህን ካልኩ በዚህ ክፍል አጌሙ (ህዝባዊ ዐመፁ) የሚያልፍባቸው ደረጃዎች፣ የሚከተላቸው ደንቦችና የሚወስዳቸው እርምጃዎች ምን እንደሆኑ፣ ዐመፁ በየደረጃው በማን እንደሚመራና እንዴት እንደሚከናወን፣ እንዲሁም፣ የአጌም አማራጭ መፍትሔዎች፣ ወዘተ፣ ምን እንደሆኑ በአጭሩ እንመለከት።

የአጌም ደረጃዎች፡- ከላይ ከተጠቀሱት የሕግ ጥሰቶች በአንደኛው ወይም ከዚህ በላይ በሆኑ ጥፋቶች የተቀሰቀሰ አጌም አራት ደረጃዎችን ማለፍ ግዴታ ይሆናል። አንደኛው ደረጃ ጥሬ (ለጋ) አጌም ይባላል። ይህም በቁሙ “ገና ሥር ያልሰደደ፣ ያልበሰለ”፣ “ገና እየተብላለ የሚገኝ” እንደማለት ነው። ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ በሳል አጌም ይባላል። ይህም በቁሙ “ሥር የሰደደ”፣ “ያፈራ”፣ “የበሰለ”፣ “የጎመራ” እንደማለት ነው። ከትርጉሙ መገንዘብ እንደምንችለው ጥሬ (ለጋ) አጌም እጅግ በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈልገው የዐመፁ ደረጃ ነው። ሦስተኛው ይፋ-አጌም ሲሆን፤ አራተኛው የአጌም እርምጃ ተብለው ይከፈላሉ።

 በመሆኑም አጌም በለጋ ደረጃው እንዳይቀጭ በሚስጢር ተይዞ እንዲጠነክርና እንዲስፋፋ ማድረግ የጨዋታው ሕግ ይሆናል። በዚህ ደረጃ ላይ ዐመፁን የሚመሩት ሚስጢር የማያባክኑ፣ በነዋሪው ዘንድ አክብሮት የተቸራቸው፣ ተሰሚነትና ተደማጭነት ያላቸው በየቀበሌው የሚገኙ መሪዎች (headmen)፣ በየመንደሩ የሚገኙ ልበኛ ሰዎች ናቸው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፣ ምስጢሩ ባክኖ፣ በመውጣት ከኜያው ወይም ደግሞ ከኳሮው ጆሮ የደረሰ እንደሆነ ሰዎቹ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሳያስቡት ሊታፈኑና ያለ ምህረት ሊገደሉ ይችላሉ። ስለዚህ ምስጢሩን በመጠበቅ ሰዎቹ በየመንደሩ ከሚገኙ ጠንካራ ሰዎች ጋር መገናኜት፣ መወያየት፣ ዕቅድና ስልት በመንደፍ ዐመፁን እንደ ሰደድ እሳት ከመንደር መንደር፣ ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከወረዳ ወረዳ ማዛመት፣ ማስፋፋት፣ ማጎልበትና በየጊዜው እድገቱንና ደረጃውን መመዘንና መለካት ይኖርባቸዋል።

 አጌመኞቹ ይህን በማድረግ ላይ ሳሉ በተለይም የዐመፁ ዒላማ ከሆነው ኜያ (ንጉሥ) ወይም ኳሮ ቲያንጊ (የዕድሜ እኩዮች) እና አጎቶች፣ በተጨማሪም፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ከቡራው (ከቤተ- መንግሥት) ጀቡራዎች (ዘቦች) እጅግ በጣም መጠንቀቅ አለባቸው። ምክንያቱም በባህሉ መሠረት ቲያንጊ (የዕድሜ እኩዮች) “ፍቅር እስከመቃብር” እንደሚባለው ከእናት ልጅ፣ ከወንድም፣ በላይ ከሞት በስተቀር ጥቅምና የዝምድና ጣጣ የማይሽረው ቃልኪዳን ስላላቸው ምስጢሩን ካወቁ ፈጥነው የማያዳግም በቀል መውሰዳቸው የማይቀር ጉዳይ በመሆኑ ነው። የኜያው (ንጉሡ) ወይም የኳሮው አጎቶችም የዚያኑ ያህል አደገኛነት አላቸው። ስለዚህ በጥሬ (በለጋ) አጌም ደረጃ አጌመኞች ከእነዚህ ክፍሎችና ከእነዚህ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ካላቸው የህብረተሰቡ አባላት እውቀት ውጭ አጌሙ እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።

በሳል አጌም፡- አጌም “በሰለ”፣ “ጎመራ”፣ የሚባለው ከላይ ከተጠቀሱት የህብረተሰቡ ክፍሎች በስተቀር ቀስ በቀስ በሁሉም ቀበሌዎች በሚገኙ ሁሉም መንደሮች ነዋሪዎች፡- ወንድ፣ ሴት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አዋቂዎች፣ ሽማግሌዎች፣ ወዘተ፣ በምስጢር ተዳርሶ ለእርምጃ ዝግጁ መሆኑ በአጌም መሪዎች የግንኙነት መረብ (ህዝባዊ ወይም ‹ፎክ› ኔትወርክ) አማካኝነት ሲረጋገጥ ነው። ዐመፁ ከዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በታመነበትና በተረጋገጠ ጊዜ የአጌም መሪዎቹ በሀገሩ የተከበሩና ተሰሚነት ያላቸውና እምነት የተጣለባቸው የተወሰኑ ጄዶንጎዎች (የሀገር ሽማግሌዎች) መርጠው ከሀገሩ ኝቡር (መንፈሳዊ አባት ወይም መሪ) ጋር ሆነው ተጠያቂ ወደ ሆነው ኜያ (ወደ ንጉሥ) ወይም ወደ ኳሮው ይልካሉ።

ይህ በሚሆንበት ጊዜም ‹‹አጌም ይፋ ወጣ›› ይባላል። አጌም ይፋ ወጣ ማለትም እስካሁን በጥንቃቄ በሚስጢር ተይዞ ሲብላላ የነበረው ህዝባዊ ዐመፅ ከመብሰሉ የተነሳ ሕግ የጣሰው ኜያ ወይም ኳሮ ሀገር ባከበራቸው፣ ዝናብ ባፈራቸው ጆዶንጎዎች (ሽማግሎች) አማካይነት በይፋ (በግልፅ) እንዲያውቀው ተደረገ ማለት ነው።

 አጌም ይፋ ከሆነ ወዲያ ኜያውም ሆነ ኳሮው ስለ ዐመፁ አወቀም አላወቀ ሊያደርግ የሚችለው የበቀል እርምጃ ‹አጉል መንፈራገጥ፣ መመላለጥ› ከመሆን አያልፍም። በዚህ ደረጃ በቀል ለመውሰድ የሚያደርገው ሙከራ ሊያደርስ የሚችለው መጠነኛ ጉዳት እንጂ ዐመፁን ፈፅሞ ሊገታው አይችልም። ስለዚህ ተመርጠው የሚላኩት ጄዶንጎዎች ተግባር በአንድ በኩል በእርሱ ላይ ህዝባዊ ዐመፅ መነሳቱን በይፋ ነግረው፣ የተነሳበትን ምክንያትም ገልፀው እንደ አባት አደሩ ወይም የአኙዋ ባህል በሚጠይቀው ደንብና ሥነ-ምግባር ተከትሎ እስከዚህ ቀን፣ ወራት፣ ድረስ ችግሩ እንዲፈታ ምክር ለመስጠት፣ በሌላ በኩል ከኜያው ወይም ከኳሮው አንደበት የሚሰጠውን መልስ ተቀብለው ተመልሰው በመምጣት ወክሎ ለላካቸው ህዝብ መልእክቱን ማድረስ ነው። ይህ ሳይደረግ በኜያው ወይም በኳሮው ላይ ርምጃ መውሰድ በባህሉ መሠረት አስነዋሪና ፀያፍ ድርጊት ተደርጎ ይታያል።

 የአጌም ርምጃዎች፡- በእርግጥ ከልምድ እንደታየው ከኜያው ወይም ከኳሮው የሚጠበቀው መልስ ከሁለት አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸውም፣ አንደኛው/ “ራሴን መርምሬና መክሬ በንፁህ ልቡና ደንቡን ተከትየ አከናውናለሁ” የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “አካኪ ዘራፍ! … ሲሆን እናያለን!” ዓይነት ነው። የአጌም ውጤቶችም እንደዚሁ ሁለት ናቸው። አንደኛው ባህላዊ ደንቡን ተከትሎ በሰላማዊ መንገድ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው በኃይል ርምጃ የሚቋጨው ነው። እነዚህ አማራጭ መንገዶችም ኜያው ወይም ኳሮው ለጆዶንጎዎች ከሚሰጧቸው አዎንታዊ ወይም አሉታዊ መልሶች የሚመነጩ ናቸው።

 ጄዶንጎዎች ያመጡት የመጀመሪያው መልስ ከሆነ፣ ማለትም፡- “ራሴን መርምሬና መክሬ በንፁህ ልቡና ደንቡን ተከትየ አከናውናለሁ” ከሆነ ህዝቡ ቀጠሮ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በጉጉት ግን በትእግሥት ይጠብቃል። ቀኑ እየተቃረበ ሲመጣ – ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት ሲቀረው፣ ኜያው ወይም ኳሮው ቃሉን ጠብቆ፣ ደንቡን አክብሮ፣ የተገኜ እንደሆን በግዛቱ ውስጥ በየቀበሌውና በየመንደሩ ለሚገኘው ነዋሪ ህዝብ ሁሉ የስብሰባ

“በመጨረሻም እንደተገመተው ህዝባዊ ተቃውሞው መሠረት በሌለው ምክንያት በተወሰኑ በግብታዊ ስሜት በተመሩ ግለሰቦች የተነሳሳና የተቀጣጠለ ሆኖ ካገኙት የሀገሩ ጆዶንጎዎች (ሽማግሎች) እንዲህ ባሉት ምግባረ-ብልሹ ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት ይወስናሉ”

ጥሪ ያስተላልፋል። መልእክቱም “በዚህ ቀን፣ በዚህ ቦታ፣ ደቂቅ ልሂቅ (ትንሽ ትልቅ ሴት ወንድ) ተገኝታችሁ እውነቱን እንድትረዱት፣ ሰላም እንድናገኝና ከድግሱም እንድትካፈሉ” በሚል መንፈስ የሚተላለፍ ነው። ይህ ማለት ለተነሳበት ዐመፅ መንሥዔ ነገር በስብሰባው ላይ እምነት ክህደቱን ከልብ በመግለፅ፣ ችግሩ በትክክል ከእርሱ ድክመት የመነጨ መሆኑን ካመነበት በሚከተለው ሁኔታ ያስረዳል፡-

“… እውነት ነው። እንደ አባቶቼ ሆኜ አልተገኘሁም። … የአባቶቼን መናፍስት አስቀይሜ አስቆጥቻለሁ። ጥፋቱን የሠራሁት ባለማወቅ ነው፤ አስቤና አውቄ አይደለም። … የአባቶቼ መናፍስት ደስ ብሏቸው ይቅር እንዲሉኝ፣ እናንተም ይህን አውቃችሁ ይቅር በሉኝ። … ለወደፊቱም ፈቃዳችሁ ሆኖ ዕድል ስጡኝ። ከአባቶቼ ምክር እያገኘሁ ድክመቴን እያረምኩ እክሳለሁ። …”

 በማለት ሥነ-ምግባርና ትህትና በተሞላበት አነጋገር በተሰበሰበው ህዝቡ ፊት ይማፀናል። ከዚህ በተቃራኒው በቀረበበት ክስና በተነሳበት ዐመፅ ላይ “ጥፋት የለኝም፤ ንፁህ ሆኜ በሀሰት ተወንጅያለሁ።” ብሎ ይናገራል።

 ከዚህ ሌላም በእርሱ ላይ የተነሳው ዐመፅ መሠረተ-ቢስ ነው ብሎ ካመነበትና ተጨባጭ ማረጋገጫ ካለው ምሎ ተገዝቶ፡- “ገና ከመነሻው እንበለ-ምክንያት ህዝቡን ወደተሳሳተ መንገድ ያነሳሱና በውጤቱም የአባቶቻችንን መናፍስት ያሳዘኑ ሰዎች እነማን እንደሆኑ የሀገር ሽማግሌ በትክክል ተጣርቶ ተገቢውን ቅጣት በመስጠት እንዲታረሙ ይደረግልኝ።” ብሎ ይጠይቃል።

በዚህ መልክ አሳማኝነት ባለው ሁኔታ እንዲታይ ከጠየቀ የሀገር ሽማግሌ ጉዳዩን በጥንቃቄ አጥንቶና መርምሮ የችግሩ መንስዔ ማን እንደሆነ እስከሚደርስበት ድረስ ኜያው ወይም ኳሮው ለተወሰኑ ወራት ስልጣኑን እንደያዘ እንዲቆይ ይደረጋል። በመጨረሻም እንደተገመተው ህዝባዊ ተቃውሞው መሠረት በሌለው ምክንያት በተወሰኑ በግብታዊ ስሜት በተመሩ ግለሰቦች የተነሳሳና የተቀጣጠለ ሆኖ ካገኙት የሀገሩ ጆዶንጎዎች (ሽማግሎች) እንዲህ ባሉት ምግባረ-ብልሹ ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት ይወስናሉ። ቅጣቱም አብዛኛውን ጊዜ የጅራፍ ግርፋት ሲሆን፤ እሱም ህዝብ በተገኘበት ስብሳባ የሚከናወን ነው። በአጠቃላይ አጌሙ በዚህ ሁኔታ ከተከናወነ የአባቶች መናፍስት በጣም ይደሰታሉ። ቁጣቸውን አብርደው ይቅርታ ያደርጋሉ። ሀገሩንም መናፍስቱ በብስጭት ብዛት ያደርሳሉ ተብሎ ከሚፈራው ከባድ አሼኒ (እርግማን) ይታደጉታል። ይህ ሲሆን በህዝቡ ዘንድ በፅኑ ይፈለግ የነበረው ስላም እንደ ዱሮው ተመልሶ ሰፈነ በሚል መረጋጋት ይፈጠራል።

 ሁለተኛው ርምጃ ከላይ ከተጠቀሰው በተቃራኒ “ሰላም ያልገዛውን ኃይል ይገዛዋል” እንዲሉ ያለው አማራጭ ኃይልን የመጠቀም ርምጃ ይሆናል። ይህ ግዴታ የሚሆነውም ኜያው ወይም ኳሮው ለጀዶንጎዎች የሰጠውን ቃል ሽሮና ቀነ-ቀጠሮውን ሠርዞ በጉጉትና በትእግሥት ሲጠብቅ የቆየውን ህዝብ ለስብሰባ ጠርቶ የሰላም ሥርዓተ-ክዋኔውን ከማድረግ ይልቅ በማን አለብኝነት ደጋፊዎቹን በማሰባሰብና ጀቡራዎችን ጦርና ዘገር በማስታጠቅ ዐመፁን በኃይል ለመጨፍለቅ የጊዜ መግዣ በማድረግ አዘናግቶ እየተጠቀመበት መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ወይም ደግሞ ህዝቡ ጆበዶንጎዎችን ወክሎ በመላክ ‹‹አጌም በስሏል፤ ስለዚህ በአንተ በኩል ዕቅድና መልስህ ምን ይሆናል?›› ተብሎ በመጀመሪያ ሲጠየቅ፤ “አካኪ ዘራፍ! ያዙኝ ልቀቁኝ! እስቲ እኔ አንበሳው! … ሲሆን እንተያያለን!” በማለት በአቋሙ ገፍቶ ኃይሉን በማጠናከር በየአካባቢው አጌሙን ሲያፋፍሙ በነበሩ ቀንደኛ መሪዎች ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑ ሲታወቅ ነው።

 በዚህ ውጥረት ውስጥ የአጌሙ መሪዎች ደም መፋሰስን በተቻለ መጠን ሊቀንስ በሚችል ሁኔታ በአጸፋው የዐመፁን ፍጥነትና ደረጃ እጅግ በጣም ከፍ ያደርጉታል። ለዚህም፡-

1ኛ/ በሌትም ይሁን በቀን በድንገት ከቡራው ውስጥ ገብተው ወይም ከቡራው ውጭ ባልታሰበ ጊዜ – ባልተጠበቀ ሰዓት – ዐመፀኛውን ኜያ ወይም ኳሮ በቁጥጥር ሥር ለማዋል አጌሙ ይፋ ከመደረጉ በፊት የተመለመሉና የተዘጋጁ የህዝባዊ ጦር ቃፊሮችን ወደ ቡራው (ወደ ቤተ-መንግሥቱ) አካባቢ በማስጠጋት በተጠንቀቅ ማስቀመጥ፤

 2ኛ/ በተለይም የኜያውን ወይም የኳሮን፣ በአንድ ቃል፣ የቡራውን (የቤተ-መንግሥቱን) ጀቡራዎች (ዘቦች) በጭፍን ታዛዥነት የህዝብ ደም ከማፍሰስ ታቅበው ከአባቶች መናፍስት አሸኒ (እርግማን) ራሳቸውን በመጠበቅ ከቅዱስ አጌሙ (ከቅዱስ ዐመፁ) ጎን ቆመው ድጋፋቸውን በተግባር እንዲገልፁ በተለይም በቤተሰቦቻቸው በኩል ምክርና ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው በማድረግ አብዛኘውን ጀቡራ ከአገልግሎት ውጭ መሆኑን ማረጋገጥ።

 3ኛ/ ጀቡራዎችን ጨምሮ ከቡራው ውስጥ በሚገኙ ደጋፊዎች አማካይነት የኜያውን ወይም የኳሮን የልብ ትርተታ በየቅፅበቱ ማዳመጥ (መሰለል) እና እንቅስቃሴውን በዕይታ ውስጥ ማስገባት፣ ወዘተ፣ ግድ ይሆናል።

 በአኙዋዎች ልምድ መሠረት እነዚህንና የመሳሰሉ ርምጃዎችን በጥንቃቄ በመውሰድ ነው እንግዲህ የአጌሙን ዓላማ በማሳካት ከሚጠበቀው ውጤት ላይ መድረስ የሚቻለው። ለዛሬው ከዚህ ላይ እናቁም። በሚቀጥለው ዕትም የአጌም ውጤቶች ምንድን ናቸው? የሚለውን እንመለከታለን። ከላይ እንደተጠቆመው ኜያው ወይም ኳሮው በቁጥጥር ሥር የሚውልበት ሁኔታ መኖሩን ተገንዝበናል። ስለዚህ ቅጣቱ ምን ይሆናል? የትና እንዴት ይከናወናል? የቅጣቱ አንድምታዎች ምንድን ናቸው? እኛስ ከባህላዊ ትውፊቱ ምን እንማራለን? እና በመሳሰሉት ጥያቄዎች ዙሪያ በማተኮር የምናቀርብ ይሆናል። ይከታተሉት። እስከዚያ ደህና ቆዩ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top