አድባራተ ጥበብ

አሹራ

መንፈሳዊ፣ ማህበረ ባህላዊና ታሪካዊ ትርጓሜው

‹‹አሹራ›› የሚለው ቃል መሰረቱ አረብኛ ሲሆን፤ ቃላዊ ትርጉሙም ‹‹አስር›› አስር ማለት ነው። በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ፣ በእስልምና የሒጅራ አቆጣጠር የመጀመሪያው ሙሐረም ወር አስረኛው ቀን ማለት ነው። ‹‹አሹራ›› ከቀን መገለጫነቱ ያለፈ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ገጽታም አለው። በእነዚህ የተዘረዘሩ የመገለጫ ምክንያቶችና መሰረቶች በአሹራ ልዩ ልዩ ከበራዎች ይፈጸማሉ። በዚህ አጭር ጽሑፍ ስለ አሹራ ከበራ ምንነት፣ ታሪካዊ ዳራ፣ ስለከበራው ይዘት፣ እንዲሁም በአገራችን የአሹራ ከበራ በተለይ ምን አይነት ታሪካዊና ማህበረ ባህላዊ ይዘት እንዳለው ለማስተዋወቅ ይሞከራል። በሙስሊሙ አለም አሹራና የአሹራ ከበራ ይዘትና ቅርጽ ሁለት መልክ አለው። አንደኛው ሹዓዊ ሲሆን፤ ሁለተኛው ሱኒያዊ በመባል ይታወቃል። ንባባችንን የሁለቱ መልኮች ምንነትን በማንበብ እንጀምራለን።

 1. ሺዓና ሲኒ ሙስሊሞች

 አሹራና የአሹራ ከበራ በሺኣና በሱኒ ሙስሊም መካከል የተለየ ትርጉም፣ ታሪካዊ ዳራና የከበራ ሂደት አለው። የእነዚህ ሁለት ቡድኖች ልዩነት ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ በኋላ እሳቸውን በሚተካ መሪ ወይም ኸሊፋ ዙሪያ ለሁለት የተከፈለ ልዩነትና ቡድን ተፈጥሮ ነበር። አንደኛው ቡድን ምንጊዜም ቢሆን የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ኸሊፋ ከእሳቸው የዘር ሀረግ መሆን አለበት የሚል አቋም ያዘ። የዚህ ቡድን ተከታዮች ‹‹ሺዓ›› ተባሉ። የሺዓ ተከታዮች በኢራን፣ በኢራቅ፣ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ በአጠቃላይ በተወሰኑ አገሮች ይገኛሉ። ከአጠቃላዩ የአለም ህዝበ ሙስሊም ከ15 – 20 በመቶ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።

ሁለተኛው ቡድን ደግሞ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ኸሊፋ በእሳቸው መምሪያና ፈለግ፣ በአራቱ ኸሊፋዎቻቸው ልምድ፣ እንዲሁም በሊቃውንቶችና በቀጥተኛ ዑለሞች አማካኝነት የሚመረጥ መሆን አለበት የሚል አቋም ያዘ፤ አሸናፊም ሆነ። የዚህ ቡድን ተከታዮች፣ በአጠቃላይም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ሱንና ተከታየች ‹‹ሱኒ›› ተባሉ። ሱኒ ሙስሊሞች በመላው የአለም ክፍል የሚገኙ ሲሆኑ፤ ከ80- 85 በመቶ የሚሆነውን የአለም ህዝብ ሙስሊም ይሸፍናሉ።

 2. የአሹራ ከበራ በሽዓ ተከታዮች

 የአሹራና የአሹራ ከበራ በሺዓዎች ዘንድ ከነብዩ ሙሐመድ የልጅ ልጅ ከነበረው፣ ከሁሴን ሞት ታሪካዊ ዳራ ጋር የተያያዘ ነው። በእስልምና ታሪክ የዑማያድ ስርወ መንግስት ኸሊፋ ሙዓውያ እ.ኤ.አ በ680 እንደ ሞተ፣ ሙዓውያን በሚተካው ላይ ውዝግብ ይፈጠራል። ገና ከመነሻው ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) እንደሞቱ የሳቸው ኸሊፋ አልይ መሆን አለባቸው ሲሉ የነበሩ የሺዓ ወገኖች የሙዓውያ ኸሊፋ የአልይ ልጅ (የነብዩ የሴት ልጃቸው ልጅ) ሁሴን መሆን አለበት ይላሉ። ነገር ግን የሺዓዎቹ ሀሳብ ወድቆ የሙዓውያ ልጅ የነበረው ዛይድ ኸኪፋ ይደረጋል። በዚህም በሁሴንና በዛይድ መካከል ቅራኔ ይፈጠራል።

ዛይድ ሁሴንን ለማንበርከክና ስልጣኑን ለማደላደል እንቅስቃሴ ይጀምራል። ሁሴንም ስልጣኑን ለመያዝ በማሰብ ቤተሰቦቹንና የተወሰኑ ተከታዮቹን ይዞ ድጋፍ ለማግኘት ከመካ ተነስቶ ወደ ኢራቅ ጉዞ ያደርጋል። ዛይድ የሁሴንን ወደ ኢራቅ መሄድ ይሰማና ጦር ይልካል። የዛይድ ጦርም ካራባ የተባለ ቦታ ሁሴንን፣ ቤተሰቦቹንና ተከታዮቹን ይከባል። በዚሁ ቦታ በተለይ በሙሐረም አስር በተደረገ ጦርነት ሁሴን ይገደላል። የዛይድ ጦር የሁሴንን ጭንቅላት ቆርጠው የኢራቅ ከተማ በሆነችው ኩፋ አውራ ጎዳና እንዲጎተት፣ በዚህም ለሌሎች ተቃዋሚዎች መቀጣጫ እንዲሆን ያደርጋሉ። ለሺዓዎች አሹራ የዚህ የሁሴን ሞት መታሰቢያ የሀዘን ወቅት ተደርጎ ይወሰዳል።

ሺዓዎች ሁሴን በተገደለበት ካርባላ የመቃብር ሃውልት አቁመዋል። ይህ የሁሴን የመቃብር ሀውልት ለሺዓዎች ቅዱስ ቦታ ተደርጎ ይታመንበታል። በመላው አለም የሚገኙ ሺዓዎችም በየአመቱ ወደ እዚህ ቦታ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ። በልዩ ልዩ ክዋኔዎችም ለሁሴን ያላቸውን አክብሮትና ሀዘን ይገልጻሉ። የሁሴንን አሟሟት የሚገልጹ ባነሮች ለትእይንት ይቀርባሉ። አንዳንዶች በብረት ሰንሰለት ፊታቸውን ይገርፋሉ። ሌሎች ሰውነታቸውን በስለት ይዘለዝላሉ። ከዚህም በተጨማሪ መድረክ ተዘጋጅቶ የሁሴን ታሪኮች በግጥምና በትረካ ይቀርባል። በድራማ ይተወናል። ተሳታፊውም በልቅሶ ሀዘኑን ይገልጻል። በዚህ አይነት ሁኔታ ከበራው እስከ አርባ ቀን የሚዘልቅ ይሆናል።

3. የአሹራ ከበራ በሱኒ ሙስሊሞች

የሱኒ ሙስሊሞች የአሹራ ቀንን በዋናነት ምንዳ ፍለጋ፣ በተጨማሪ አላህን ለማመስገን ሲሉ በጾም፣ ለተቸገሩ ሶደቃ በማብላትና በመስጠት አክብረውት ይውላሉ። የጾም ጊዜውም የሙሐመረም ወር ዘጠነኛውና አስረኛው ወይም አስረኛውና አስራ አንደኛው ሊሆን ይችላል። በጣም የሚወደደውና ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.አ.ወ) አመላክተዋል የሚባለው ዘጠነኛውንና አስረኛውን ቀን እንደሆነ ይታመናል። አሹራን በጾም ማሳለፍ በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) የተፈጸመና ሙስሊሞችም እንዲጾሙ ማዘዛቸው እንደሆነ ይታመናል።

 ለዚህም የሚከተለውን ነብያዊ ሀዲስ ይጠቅሳሉ። ‹‹ኢብኑ አባስ እንዳስተላለፉት፣ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.አ.ወ.) የአሹራ ቀን ጾመዋል። ይህን ቀን መጾምንም አዘዋል›› ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ተከታዮቻቸው የአሹራን እንዲጾሙ ዚያዙ፣ የአሹራ ጾም ‹‹ያለፈውን አመት ወንጀል ያስምራል›› ሲሉ መንፈሳዊ ፋይዳውን ወይም ትሩፋቱን እንደገለጹ ይታመናል።

የእስልምና ሊቃውንት የአሹራ ጾም ሲጀመር ግደታ ነበር ይላሉ። ከጊዜ በኋላ አላህ ሙስሊሞች የረመዳን ወርን እንዲጾሙ ወህይ ወይም ራዕይ ሲወርድላቸው የአሹራ ጾም የሱና ወይም በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ። ጾሙ ሱናም ቢሆን ከላይ የተገለጸውን ምንዳ የሚያስገኝ በመሆኑ፣ ይህን ምንዳ ፈላጊዎች የተጠቀሱትን ሁለት ቀኖች ይጾማሉ።

በሱኒ ሙስሊሞች የአሹራ ጾም ታሪካዊ ዳራ አለው። ታሪካዊ ዳራውም ከሙሐመረም ወር ጋር የተያያዘ ነው። የሙሐመረም ወር አላህ የተከበሩ ካላቸው አራት ወሮች አንደኛው ነው። በእነዚህ ወሮች የሚፈጸሙ ሰናይ ሀሳቦች፣ ፍላጎቶችና ድርጊቶች ሁሉ ከሌሎቹ ወሮች የበለጠ ምንዳ እንደሚያስገኙ ይታመናል። ሌላናው ምክንያት በዚህ የሙሐረም ወር ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ከመካ ወደ መድና ሂጅራ ያደረጉበት ወር ከመሆኑ ጋር ያያይዙታል። አለም እንደሚያውቀውና እንደሚጠቀምበት የሙስሊሞች የዘመን አቆጣጠር አንድ ብሎ የሚጀምረው በዚህ የሙሐመረም ወር ነው። ከዚህ የሙሐረም ወር ጋር የተያያዙ ሌሎች ተረኮችም አሉ። አደም ከሐዋ ጋር የተዋወቁበት፣

ነብዩ ኢብራሂም ከእሳት ፈተና ያመለጡበት፣ የነብዩ ኖህ መርከብ መሬት የረገጠበት፣ ነብዩ ሙሳ እስራኤላውያንን ከግብጹ ፈርኦን በአላህ ተአምር ነጻ ያወጡበት ወር (ወርና እለት) ተደርጎም ይታመናል። ሁሉም የክስተት ተረኮች ሰፋፊ ገጽ የሚወጣቸው ስለሆኑ ሁሉንም መተረኩ አያመችም። ይሁንና አሹራ በተነሳ ቁጥር በሱኒ ሙስሊሞች ተዘውትሮ የሚነሳውና የአሹራ ከበራ እንደመነሻ ተደርጎ የሚወሰደው ከነብዩ ሙሳ ጋር የተያያዘው ታሪካዊ ተረክ ነው።

ነብዩ ሙሳ በግብጹ የፈርኦን የጭቆና አገዛዝ ስር ከነበሩ እስራኤላውያን ይወለዳሉ። ነብዩ ሙሳ በተወለዱበት ወቅት፣ የፈርኦን ንጉስ ስልጣኑን የሚፈታተን ሰው ከእስራኤላውያን እንደሚወለድ ህልም አይቶ ነበር። በዚህም የተነሳ ከእስራኤላውያን የተወለዱ ወንድ ህጻናት ባሉበት እንዲገደሉ አውጆ ነበር። የነብዩ ሙሳ እናት ልጇ አደጋ ውስጥ እንዳለ በተረዳችና ጭንቅ በገባት ጊዜ፣ አላህ ህጻኑን ሙሳ በጨርቅ ተቅልላ በሳጥን አድርጋ ባህር ላይ እንድትጥለው አሳወቃት። የነብዩ ሙሳም እናት የታዘዘችውን ፈጸመች። በቅዱስ ቁርአን እንደተገለጸው ነብዩ ሙሳን የያዘው ሳጥን እፈርኦን እጅ ገባ። ፈርኦንና ሚስቱ ህጻኑን እንዳዩ በፍቅር ተማረኩ፤ በእህቱ አማካኝነት የእናቱን ጡት እየጠባ እቤተ መንግስታቸው በእንክብካቤ እንዲያድግ አደረጉ። ‹‹ወደ ሙሳም እናት አጥቢው፣ በሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባህሩ ውስጥ ጣይው፤ አትፍሪም፤ አትዘኝም፤ እኛ ወደ አንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና ማለትን አመለከትን። የፈርዖን ቤተሰቦችም (መጨረሻው) ለነርሱ ጠላት ሀዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት። … የፈርዖንም ሚስት ለኔ የዓይኔ መርጊያ ነው፤ ለአንተም (የዓይን መርጊያ ይሆናል)፤ አትግደሉት፤ ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና አለች፤ እነርሱም አነሱት። (28፡7-9)።

 ነብዩ ሙሳ አቅማቸው ሲደርስ አላህ እውቀትንና ጥበብን ሰጣቸው። በዘመኑ የነበረውን ገናን የምትሀትና የድግምት ችሎታ የሚያፈርስ የተአምር ባለቤት አደረጋቸው። (አላህ ለሙሳ ከሰጣቸው ዘጠኝ የተአምር ትእምርቶች መካከል በትር ይገኛል) ነብዩ ሙሳ እድሜያቸው ሲደርስ ለህዝቡ ወደ እስልምና ጥሪ ማድረስ ጀመሩ። ይህ የነብዩ ሙሳ ወደ እስልምና ጥሪ ከፈርዖን ጋር አጣላቸው። ተአምር በማሳየትም ተፈታተናቸው። ፈርዖን ከነብዩ ሙሳ ተአምር እንደሚበልጥ ለማሳመን ብዙ ጊዜ ተፎካክሮ በሁሉም ተሸነፈ። ሆኖም ፈርዖን በብዩ ሙሳ መበለጥንና መሸነፍን መቀበል ከበደውና ነብዩ ሙሳንና እስራኤላውያኑን ለማጥፋት ወሰነ።

ፈርዖን ነብዩ ሙሳንና እስራኤላውያኑን ለማጥፋት እንደተዘጋጀ፤ አላህ ነብዩ ሙሳን ‹‹ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ፤ እናንተን የሚከተሉዋችሁ ናቸውና›› ሲል በራእይ አዘዛቸው። ነብዩ ሙሳም በዚህ መለኮታዊ ትእዛዝ መሰረት ሰዎቻቸውን ይዘው ሌሊቱን ወደ ቀይ ባህር ጉዞ ጀመሩ። ፈርዖን ይህን በተረዳ ጊዜ ጦሩን ይዞ ተከተላቸው። አባይ ዳርቻም ደረሱባቸው። የፈርዖን ጦር የደረሰባቸው መሆኑን ባዩ ጊዜ የሙሳ ሰዎች ተረበሹ፤ ተጨነቁ። ጭንቀታቸውንና ፍርሃታቸውንም ለነብዩ ሙሳ ገለጹ። ነብዩ ሙሳም ‹‹አይዟችሁ አትፍሩ፤ ጌታዬ ከኔ ጋር ነው፣ ቀናውን መንገድ ይመራናል›› በማለት አበሸራቸው። የአላህ ቃልም ተፈጸመ። ‹‹ወደ ሙሳም ባህሩን በበትርህ ምታው ስንል ላክንበት፤ (መታውና) ተከፈለም፤ ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ›› (26፡62)። ነብዩ ሙሳና ጓደኞቻቸውም በደረቁ መሬት ተሻገሩ። ባህሩ እንደተከፈለ ፈርዖንና የፈርኦን ጦርም ተከተላቸው። ሁሉም ተከትተው እበሀሩ አጸድ ውስጥ እንደገቡ እንደ ታላቅ ጋራ ቆሞ የነበረው ውሃ በፈርዖንና በጦሩ ላይ ወደቀባቸው። ሁሉም ጭዳ ሆኑ።

 ነብዩ ሙሐመድ ከመካ ወደ መዲና ሂጅራ ባደረጉበት ወቅት ይሁዶች ፈጣሪ ለነብዩ ሙሳ የሰጣቸውን ጸጋ ለመዘከር የአሹራን ቀን በጾም እንደሚያሳልፉ ይረዳሉ። ነብዩም (ሰ.አ.ወ) ለሙሳ እኛ እንቀርባለን ብለው እሳቸውም ጾመው ሙስሊሞችን የአሹራ ጾም እንዲጾሙ ያዛሉ። ከላይ እንደተገለጸው የአሹራ ጾም ሲጀመር በሙስሊሞች ላይ ግደታ ነበር። አላህ የረመዳንን ወር ግዴታ ካደረገ በኋላ የአሹራ ጾም በነብዩ ጥብቅ ሱና ተደርጓል። አሹራ በሙሐረም ወር የሚገኝ በመሆኑ፣ ነብዩ (ሰ.አ.ወ) ‹‹ከረመዳን ወር ቀጥሎ በላጩ ጾም የአላህ ወር የሆነው የሙሐረም ወር ጾም ነው›› በማለታቸው ብዙዎች የአሹራን ጾም አጥብቀው በጾም ያሳልፉታል።

4. አሹራና የአሹራ ከበራ በኢትዮጵያ

አሹራና የአሹራ ከበራ በአገራችን የነበረውና አሁንም ያለው ግንዛቤ፣ እንዲሁም የከበራው ባህሪ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ገጽታ ያለው ነው። በመንፈሳዊ ባህሪው የአሹራ ጾም ያስገኛል ተብሎ ከሚታመነው የፈጣሪ ጸጋ ጋር የተሳሰረ ነው። ይህን የፈጣሪ ጸጋ የሚፈልጉ እለቱን በጾም ዘክረውት ይውላሉ። በታሪካዊ ገጽታው ባብዛው ከነብዩ ሙሳ የፈርዖን ክስተት ጋር ያገናኙታል። በባህላዊ ገጽታው ደግሞ የአሹራን መንፈሳዊና ታሪካዊ ገጽታ መሰረት በማድረግ እለቱን በልዩ ልዩ ከበራዎች ያሳልፉታል። በዚህ ቀጥሎ የምንዳስሰው ይኸንን አገራዊ ገጽታውን ይሆናል።

በአገራችን የአሹራ ከበራ የተለመደ አመታዊ ክዋኔ ነው። በተለይም በሐረርና በትግራይ በተለይም በነጃሺ በተለየ ሁኔታ በድምቀት ተከብሮ ይውላል። ከበራው ከታሪካዊና ከመንፈሳዊው በላይ ባህላዊና አካባቢያዊ ገጽታው ጎልቶ የሚታይበት ነው። እዚህ ላይ በአሹራ ከበራ ሁሉን አካታች ስለሆነው በነጃሺ የአሹራ ከበራ ባህላዊና ማህበራዊ ገጽታ የሚከተለውን ይመስላል።

ነጃሺ በእስልምና ታሪክ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ቤተሰቦችና ተከታዮች ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰደዱበትና ጥገኝነት የተሰጡበት ንጉስ መጠሪያ ስም፣ እንዲሁም የእኒህ ንጉስ የመቃብር ቦታ የሚገኝበት ቦታ መጠሪያ ነው። በዚህ ቦታ ለዘመናት የአሹራ ከበራ እየተፈጸመ እስካሁን ዘልቋል። በነጃሺ የሚከበረው የአሹራ ከበራ ከላይ ከተጠቀሱ አጠቃላይ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ መሰረቶች በተጨማሪ የራሱ የሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ይዘቶች አሉት።

በጥንት ጊዜ የአገራችን ሁጃጆች የሀጅ መንፈሳዊ ጉዞ በአብዛኛው በእግር ከዚያም በኤርትራ የባህር መስመር ላይ ነበር። የእግሩም ሆነ የባህሩ ጉዞ አስቸጋሪና በተበታተነ መንገድ የሚፈጸም ነበር። በዚህ የተነሳ ማን መንገድ ላይ እንደቀረ፣ ማን ሀጁን ፈጽሞ እንደተመለሰ ለማወቅ ነጃሺ ለደርሶ መልስ መገናኛ ተመረጠ። ነጃሺ በአንድ በኩል የንጉሱ የመቃብር ቦታ የሚገኝበት መሆኑ ከአካባቢው ተጽእኖ መከላከያ፣ በሌላ በኩል አሹራ የሀጅ መንፈሳዊ ጉዞ ካለፈ ከሁለት ወር በኋላ የሚውል መሆኑ ለሁጃጆቹ መገናኛ በቦታም ሆነ በመንፈሳዊ ከበራው አመቺ ነበረ። እናም ነጃሺ ለዘመናት ከሀጅ ጉዞ መልስ የመገናኛ ማእከል ሆኖ ተቋቋመ። ይህ ልማድ ከመላው አገሪቱ ወደ ሀጅ የሄዱ ሙስሊሞች የሀጅ ደርሶ መልስ የመገናኛ ማእከል ከመሆን በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘቱን በማስፋት ሀጅ ያልሄዱ ሙስሊሞችም በነጃሺ ተገኝተው በአሹራ ከበራ እንዲሳተፉ እድል ሰጠ። በዘንድሮም የአሹራ ከበራ የኤርትራ ሙስሊሞች መሳተፍ የዚሁ የነጃሺ የአሹራ ከበራ መገለጫ የቅርብ ማስረጃ ነው።

 የዘንድሮው የነጃሺ አሹራ ከበራ ቢያንስ አራት በሚሆኑ ክፍሎች ተካተውበታል። አንደኛ፤ መስተንግዶ። በዚህ ክፍለ ጊዜ ከመላው አገሪቱና ከኤርትራ የተውጣጡ የከበራው ተሳታፊዎች የተገኙበት፣ በዚህም የእርስ በርስ የመተዋወቂያ፣ የመዘያዬሪያና አብሮ የመብላት፣ በአካባቢው ለሚገኙ የተቸገሩ ወገኖች ሶደቃ የማብላትና ምጽዋት የመስጠት ሂደት ተከናውኗል። ሁለተኛ፤ የሀድራ ክፍለ ጊዜ። የሀድራ ክፍለ ጊዜው ሙሉ ሌሊቱን የሸፈነ ሲሆን፣ የጸሎትና የመንዙማ ክዋኔዎች ተካሂደውበታል። ሶስተኛ፤ ኮንፈረንስ። በኮንፈረንሱ ክፍለ ጊዜ እውቀት ያላቸው ዑለሞች ስለ ሙስሊሙና ስለ አገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ የሚፈጥሩበት፣ እንዲሁም ሀሳብ የተለዋወጡበት ክፍለ ጊዜ ነበር። አራተኛ፤ ትርኢት። በዘንድሮም የአሹራ ከበራ ላይ በተለይ ከኤርትራ የመጡ ሙስሊሞች በአለባበስ፣ በባነር፣ በዜማ፣ በእንቅስቃሴ፣ ወዘተ ታጀበው ልዩ ልዩ ትርኢቶች በማቅረብ የአሹራን ማግስት አድምቀውታል።

 እነዚህ ባጭሩ ተከፍለው የቀረቡ ዝግጅቶች ይዘትና ውበት፣ መሳጭነትና የፈጠሯቸው ስሜቶች፣ ያደሷቸው ተቋርጠው የነበሩ ማህበራዊ ግንኙነቶች፣ የቀሰቀሷቸው ትውስታዎች፣ ወዘተ በእንባ ቀለም ቢጻፉ የሚገለጹ አይደሉም። በሀድራው ላይ በአረብኛ፣ በትግርኛና በአማርኛ የቀረቡ ጸሎቶች፣ በመንዙማ የቀረቡ የምስጋና፣ የፍቅር፣ የናፍቆት፣ የመዘከር ወዘተ ግጥሞች መንፈስን አርክተዋል፤ እምነትን አጽንተዋል። በዚህ ወቅት የፈሰሰው እንባ በድንገት ለተፈጠረ ስሜት ማብረጃ የዋለ አልነበረም። ለምን ቢሉ ከሀያ አመታት በላይ ሳይፈቅዱ እንዲለያዩ የተፈረደባቸው ወገኖች መልሶ መገናኘት የፈጠረው ጥልቅና ረቂቅ ስሜቶች ያፈነዷቸው የእንባ ጅረቶች እንደነበሩ ማሰብ ነው።

ይህ የነጃሺ ማእከል በአካባቢው ተወላጆችና አንዳንድ ግለሰቦች አማካኝነት በየወቅቱ እየታደሰ ለትውልድ ሲተላለፍ የቆዬ ቢሆንም፤ ታሪካዊነቱንና አገልግሎቱን በሚመጥን መልኩ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም። በዘንድሮው የአሹራ ከበራ ግን ቢያንስ ቅርጻዊ ለውጥ ታይቶበታል ማለት ይቻላል። ማእከሉ ባማሩ ህንጻዎችና በቱርክ የህንጻ ድዛይን ዓይነ-ግቡ እንዲሆን ተደርጓል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top