አድባራተ ጥበብ

ነባሩና አዲሱ፡- የባሕል ፍልሚያ (በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥራዎች)

ለዚህ ሀተታ የተመረጠው፣ሌላኛው የብላቴን ኅሩይ ወልደሥላሴ ልቦለድ ‹የልብ አሳብ› ነው። ደራሲው ‹የልብ አሳብ›ን ከመጻፋቸው ቀደም ብሎ ሴት ልጆቻቸውን ዘመናዊ ትምህርት አስተምረዋል። እንደሚታወቀው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጭ ሀገር ደርሰው ተምረው የተመለሱ ሴት ተማሪዎች መሃል፣ ቀዳሚነቱን የሚይዙት፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ የራስ እምሩ ኃይለሥላሴ እና የብላቴን ኅሩይ ልጆች ናቸው። ከዚህ ዘመን ቀደም ብሎ ለትምህርት ባህር ማዶ የተላከች ሴት አልነበረችም።

የ‹ልብ አሳብ› መጽሐፍ በር ከፋች፣ ዓይን ገላጭ፣ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ፋና ወጊ ጽዮን ሞገሳ ናት። ተራኪው፣ ነባሩን ባሕል የሚሞግቱት በጽዮን ሞገሳ በኩል ነው። አባቷ ዘመናዊ ትምህርት እንድትማር ይፈልጋሉ፤ እናቷ ደግሞ በዘመኑ ሴቷ ‹ሴት› የሚያሰኛትን፣ በኋላም በባሏ ቤተሰብም ተከባሪ የሚያደርጋትን ፈትል የመፍተሉን፣ እንጀራ የመጋገሩን፣ ወጥ የመሥራቱን፣ ጠጅ የመጣሉን፣ ጠላ የመጥመቁን ነገር ትሰልጥንበት እንጂ፤ አባቷ እንደሚሉት ጽሕፈት መጻፍ፣ ስፌት መስፋት፣ ልብስ መጥለፍ፣ ይህን የመሰለውን ሁሉ ትማር የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉ አልነበሩም።

በባልና ሚስት መካከል ንትርክ ሲፈጠር፣ ገላጋይ ሸምጋይ ሆነው የገቡት መምሬ፣ ከነባሩ ባሕላዊ ትምህርትና ከዘመናዊው ትምህርት የተሻላትን እንድትመርጥ እድሉን ለጽዮን ሞገሳ ይሰጧታል።

 ጽዮን ሞገሳ፣ በእናቷ በኩል የቀረበላትን ምርጫ አልተቀበለችም። እነዚህ ሙያዎችና የሴትነት መገለጫዎች ድካም የሚጠይቁ፣ ገንዘብ እስካለ ድረስ ደግሞ በቀላሉ የሚገዙ መሆናቸውን በዝርዝር ማስረዳቷን ቀጠለች። ይልቁንስ፣ መጽሐፍ ማንበብ ብትማር፣ ‹የቀድሞውን ዘመን ያባቶቻችንንና የአገራችን ታሪክ፤ የዛሬውን ዘመን በእውቀትና በጥበብ የተሠራውን ሥራ ሁሉ› ለማወቅ እንደምትችል፤ ‹ጽሕፈት ብማር ያሰብሁትን እንዳልረሳው፤ አስቤ የሠራሁትን እንዳልዘነጋው እየጻፍሁ አስቀምጣለሁ› ማለቷን፤ የእጅ ሥራ ብትማር፣ ‹ቀኑን ሙሉ ያለ ሥራ ተቀምጬ ብውል በሽተኛ መሆኔ አይቀርምና እጄን በማንቀሳቀስ ሥራ በመሥራት ሕዋሳቶቼ ሁሉ የተፈጥሮ ሥራቸውን እየሰሩ ጤናዬን አገኛለሁ› ማለቷን በድርሰቱ ውስጥ እናነባለን።

 እንደተመኘችውም ሆነላት። ተማረች። ሰውነቷ እያማረ፣ ዕውቀቷ እየበሰለ ሄደ። ብርሃኔም አየና ተመኛት። እርስዋን ለማግባትም ቁርጥ ሃሳብ አደረገ። እርስዋ ግን፣ በወቅቱ 13 ዓመቷ ነበርና፣ ‹15 ዓመት ሳይሞላኝ አላገባም› አለች።

ጽዮን ሞገሣ የተማረች ናት። ተራኪው እንደሚለው – ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረባት ናት። ቃሏን ትጠብቃለች፤ ጤናዋን ትጠብቃለች፤ እምነቷን በፈጣሪዋና በምትወደው ባሏ ላይ ታሳድራለች።ደራሲው፣ አንዲት ሴት በዚያን ዘመን እንዴት መኖርና ማሰብ እንዳለባት ምሳሌ አድርገው የቀረጿት ናት። ሰውነቷን አትበድልም፤ ትምህርቷን አታስተጓጉልም፤ ዕውቀቷን አትደብቅም።

 ከነባሩ ይልቅ ለአዲሱ ባሕል እጅ የሰጠች ናት። ወላጆቿን ጥየቃ ልጇን ይዛ ወደ ቡልጋ በወረደች ጊዜ፤ ልጅዋ ሲታመምባት የወሰነችው አንዱ ውሳኔ ለዚህ ጥሩ አስረጅ ነው። ልጅዋን ጤነኛ ለማድረግ፣ የአካባቢው ሰው መላ ሲመታ፣ የእሷ ሃሳብ የተለየ መሆን፤ አዋቂነቷን የአዲሱ ባሕል ተከታይነቷን የሚያጎላ ነው።

ጽዮን ሞገሳ፣ ክታብ ልጇ አንገት ላይ ከማሰር፣ ባህላዊ በሆነ መንገድ ከማከም ይልቅ ቀዳሚ ምርጫ ያደረገችው ስጋና ደሙን መቀበልን ነበር። ሥጋና ደሙን ቢቀበል የዘላለም ሃይማኖት ሊወርስ እንደሚችል ታምናለች። ‹ጥቂትም በጎ የሆነልኝ እንደ ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ የልጆች ሀኪም መኖሩን ሰምቻለሁና ወስጄ አሳክመዋለሁ› ብላም ትመልስላቸዋለች። ወደ አዲስ አበባም ሄዳ ታሳክመዋለች፤ ይድናልም።

 4. ድል አድራጊው አዲሱ ባሕል

 ‹ሴት ልጅ ከማጀት ወጣች፣ አደባባይ ዋለች ማለት በጊዜው ለነበረው ስርዓተ ማኅበር የወንጀል ያህል ነው፤ ትልቅ ድፍረት! አባዊው ሥርዓት የቆመበትን አንድ ትልቅ መሠረት መናድ ማለት ነው! በምን ዳኑ? በስልት፣ በለዘብታ፣ የሐሳብ ማራቸውን ሲቆርጡ አውራው እንዳይነካ በመጻፋቸው። በዛሬው ቋንቋ ስለ ሴቶች እኩልነት፣ የሴት ልጅ አካለ መጠን ሳትደርስ እንዳታገባ፣ ለማታውቀውም ሰው መዳር የሌለባት መሆኑንም የጻፉ የመጀመርያው ‹‹ፌሚኒስት›› ጸሐፊ እንበላቸው ይሆን?›

ከላይ የተቀመጠው አገላለጽ፣ ‘በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት’ እንዲሉ፤ ብዙ የታመቁ ሀሳቦችን ጸንሷል፤ ወልዷል፤ አሳድጓልም። ሃሳቡ የሚያወያይ ነው። የሃሳቡ ባለቤት ዕውቁ የሥነ- ጽሑፍ ምሁር ዶክተር ዮናስ አድማሱ ናቸው። እኔ በበኩሌ፣ የኅሩይ ድርሰቶች የዘመመውን ለማቃናት፣ የደበዘዘውን ለማፍካትና የጨለመውን ለማብራት የሚጥሩ፣ የሚጣጣሩ ለመሆናቸው እማኝ እሆናለሁ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ፣ ከነበሩበት ዘመን አንጻር ሲታይ እንደ ስማቸው ኅሩያን የሆኑ ድርሰቶችን ደርሰዋል፤ ትውልዱን ሞግተዋል፤ ተፋልመዋል፤ በፍልሚያውም አሸንፈዋል፤ በማሸነፋቸውም ወዳጆቻቸው ቅኔ ተቀኝተውላቸዋል።

 ዶክተር ዮናስ፣ ‹ኅሩይ ቀፎው እንዳለ ሳይረበሽ በብልሃት እየተቀነሰ የሚለወጠው እንዲለወጥ በስልት፣ በለዘብታ የሃሳብ ማገራቸውን እንደቆረጡ፣‹መድበለ ጉባዔ› በተሰኘው፣የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ባሳተመው መጽሐፍ ላይ ዕይታቸውን አስፍረዋል። እንደ እኔ ፍተሻ፣ ይህ አገላለጽ ‹የልብ ሃሳብ› የተሰኘውን ድርሰታቸውን እንጂ ‹አዲስ አለም›ን አይወክልም። የኅሩይ የመጀመርያ የፈጠራ ሥራ የሆነው ‹የልብ አሳብ› ተለሳልሶ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ይዞ ነው የተነሳው። ድምጹ የለዘብታ ነው። አያስጮህም፤ አያነታርክም።

 ‹አዲስ ዓለም› ግን እንግዳ ነው፤የአዲስ ዓለም ፈጣሪው አወቀ ባይተዋር ነው፤ የሚያደርገው የሚናገረው ሁሉ፤ በተጉለት ነዋሪዎች ዘንድ እንደ እብድ የሚያስቆጥረው ነው።

ሀኖ ሴና አስፋው ዳምጤ እንደሚሉት ‹… የሚገጥመውን ፈርጀ ብዙ የባሕል ግጭት በማንፀባረቅ ረገድ የመጀመርያው የአማርኛ አቢዮት መሆኑ ነው። እንዲያውም በአፍሪካ ቋንቋዎች የመጀመርያው ነው የሚሉም አሉ›

በነገራችን ላይ፣ የሥነጽሑፍ ተመራማሪዎች፣ የኅሩይን ሥራዎች ሲዳስሱ፤ የመጀመሪያው የሚለውን ቃል ያበዛሉ። ዶክተር ዮናስ አድማሱ፣ ‹የመጀመርያው ፌሚኒስት ጸሐፊ እንበላቸው ይሆን?› ሲሉ፣ አስፋው፣ ‹የባህል ግጭት በማንፀባረቅ ረገድ የመጀመርያው የአማርኛ የፈጠራ ሥራ ባለቤት› ይሏቸዋል። ቴዎድሮስ ገብሬ፣ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመርያው አሊጎሪያዊ ልቦለድ ጸሐፊ ናቸው› ይሏቸዋል። ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ደግሞ፣ ከወረራው በፊት አምራች ደራሲ በመሆን የቀዳሚነቱን ቦታ ሲሰጣቸው፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው፤ ከጣልያን ወረራ በፊት አራት ታሪካዊ መጽሐፍ በመጻፍ ጀማሪ ያደርጓቸዋል። እኔ ደግሞ፣ ‹የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካን አውሮፓ› (1803) እና ‹ደስታና ክብር›ን ጠቅሼ የመጀመርያው በአማርና ቋንቋ የተጻፈ የጉዞ ማስታወሻ ደራሲ አደርጋቸዋለሁ፤ በኢትዮጵያ የታተሙ መጻሕፍትን ዘርዝሮ በማስቀመጥም ከሌላው አስቀድማቸዋለሁ። ለእሳቸው የቀረቡ፣ በአማርኛና በግዕዝ ቋንቋ የተደረሱ ቅኔዎችን ሰብስበው በማሳተምም ቀዳሚ አደርጋቸዋለሁ።

 ብላቴን ጌታ ኅሩይ ‹አዲስ ዓለም›ን ከማሳተማቸው ሰባት ዓመት ቀደም ብሎ ‹ዐወቀ ሰባት ዓመት ቆይቶ ተመለሰባት› ያሏትን ፓሪስን አይተዋል። አልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ተከትለው አውሮፓን ከጎበኙ ሰዎች መካከል አንድ ነበሩ። የጉዟቸው አኳኋንም፣ ‹ደስታና ክብር› በሚለው በብላቴን ጌታ ኅሩይ መጽሐፍ ተገልጿል። ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ሥር የሰደደ፣ በንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘመን የጀመረ መሆኑን (ገጽ 34) በወቅቱ የነበሩ የፓሪስ ከንቲባ አስረድተዋል። አፍሪካን የማልማት፣ መንገዷን የማቅናት ምኞት በውስጣቸው እንዳለም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

 ‹ደስታና ክብር› (ገጽ 35) የፓሪስ ከንቲባን ንግግር ጠቅሶ ከጻፈው አንድ አንቀጽ ስንመዝ የሚከተለውን እናገኛለን።

 ‹ይህንን ለኢትዮጵያ ሥልጣኔና ትምህርት የሚሆነውን ነገርና ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እንደ ደንቡ የሚገባትን ማዕረግ እንድታገኝ የሚጣጣረውን ለመፈፀም እንዲቻላት እንዲህ ያለ የታላቁን ንጉሥ የአፄ ምኒልክን መንገድ የተከተለ እውቀትን የተገለፀለት አልጋወራሽ በማግኘቷ እጅግ ደስ ብሏታል›

 ከከንቲባውም ሆነ ከሌሎቹ ንግግር እንደምንረዳው ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ዓይን ለመግለጥ፣ መንገድ ለመምራት፣ ሕይወቷን ለማብራት፣ ዓለም ከደረሰበት ስልጣኔ ተካፋይ እንድትሆንና ከተዘጋ ጭለማ ክፍል እንድትወጣ (ገጽ 38) ለማገዝ ፍላጎት አሳይተዋል።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በፓሪስ የቤተመንግሥት ስርዓት ተደንቀዋል። የወይን ጠጅ አሳላፊዎች ስልጣኔና ፍጥነት እጅግ መስጧቸዋል። በቤተመንግሥቱም፣ በቤተክርስቲያኑም፣ በቤተሙዚየሙም ኪነ-ህንፃ ተደምመዋል። ይህ መደመምና የአውሮፓን ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ መመሰጥን የፈጠረው በአልጋ ወራሹም ዘንድ ነው።

5.ማጠቃለያ

የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሁለቱ ልብ- ወለዶች  ‹የልብ አሳብ›ና ‹አዲስ ዓለም› – በተቀራራቢ ጊዜ የታተሙ ድርሰቶች ናቸው። ቀዳሚው ተከታዩን በኅትመት የሚበልጠው በሁለት ዓመት ብቻ ነው። ሁለቱም አዲሱን ባሕል ለመትከል የሚደረግን ትግል ያሳያሉ። እርግጥ ነው ‹የልብ አሳብ›፣ የ‹አዲስ ዓለም›ን ያህል ፍልሚያ የለውም። አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ሙግት የለውም። ቀዝቀዛ ነው- ዝግ ያለ። ጽዮን ሞገሳ አዲሱን ባሕል ስትኖረው ይታያል እንጂ በምታነሳቸው ሃሳቦች ነቀፌታ ሲሰነዘርባትና ከፍ ያለ ሙግት ሲገጥማት አይታይም። ውሳኔዎቿ የሌላውን ሕይወት አያውኩም፤ መሰረቱን አይነቀንቁም፤ እንደ ዐወቀ ጉባዔ አዘርግተው ሊቃውንቱን አያነታርኩም።

ሁለቱም ልብወለዶች የአዲሱ ባሕል አቀንቃኞች መሆናቸው ግን አይካድም። ዐይናቸው የሚገለጠው፣ የዕይታ አድማሳቸው የሚሰፋው በትምህርት ሰበብ ነው። የጽዮን ሞገሳ ዕውቀቷ በሀገር ውስጥ ነባር ዕውቀት የተወሰነ ሲሆን፤ የአወቀ ግን ከባሕር ማዶ የተቀዳ ነው። አለባበሱም አስተሳሰቡም ‹የባዕዳን› ነው። ከነባሩ ባሕል ሙሉ ለሙሉ የተገነጠለ ነው። እያንዳንዱ ምዕራፍ፣ እያንዳንዱ ሁነትና እያንዳንዱ ተረክ በፍልሚያ የተሞላ ነው።

በሁለቱ ድርሰቶቻቸው አቀራረብ በኩል መጠነኛ የማይባል ለውጥ አለ። ‹የልብ አሳብ› የአንዲት ሴትን ሕይወት ተከትሎ የተደረሰ ነው – አንዲት ሴት ተምራ ቤተሰቦቿን እንደምን ማስተዳደር እንዳለባት የሚያስረዳ። ‹አዲስ ዓለም› ግን፣ የልቡን አሳብ ስለተከተለ አንድ ወጣት ሳይሆን፣ አውሮፓ ዘልቆ፣ ፓሪስ ደርሶ፣ አኗኗሩም አስተሳሰቡም ፈረንጂኛ ስላደረገ፣ አዲስ ዓለም ይዞ ስለመጣ ወጣት ነው የሚተርከው። ውሳኔዎቹ፣ እርምጃዎቹ የሌላውን ሕይወት የሚነኩ፣ የሚነቀንቅ፣ የሚበጠብጡ ናቸው።

‹የልብ አሳብ›ም ሆነ ‹አዲስ ዓለም› የወላጆቻቸውን ሕይወት ከማስተዋወቅ ይጀምራሉ። የት ከማን እንደተወለዱ ይነገራል። እንደ ገድላት – ገድላት ውስጥ እንደሚነበቡ ባለታሪኮች – የወላጆቻቸው ስምና ሕይወት በመጠኑ ይነገራል። የሁለቱም ልቦለድ መሪ ገፀባህርያት መሠረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንድም ቦታ ገድላት፣ ድርሳናትና አዋልድ መጻሕፍት በአንደበታቸው አይጠቀስም። የሚጠቅሱትም ሀዲስ ኪዳንን ነው። ወንጌልን። ብሉይ ኪዳን አይተነትንም፤ ምሳሌም አይጠቀስበትም።

ኅሩይ ‹ወዳጄ ልቤ› በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ በየአንቀፁ አንድ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ያስቀምጡ ነበር። ጥቅሱ የገባበት ምክንያት ‹የምተርከው ታሪክ፣ የምናገረው ሃሳብ ሃይማኖታዊ መሰረት አለው› ለማለት ነው። ‹ወዳጄ ልቤ›፣ ከታተመ፣ ከስምንት ዓመታት በኋላ፤ የታተመው ‹የልብ አሳብ› ግን ከሁለት ሦስት ጊዜ በላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ አልተጠቀሰም። ‹አዲስ ዓለም› ላይ ደግሞ ፈጽሞ የለም።

‹የልብ አሳብ›ም ሆነ ‹ዐዲስ ዓለም› መቼታቸው ሰሜን ሸዋ ነው – ተጉለትና ቡልጋ። ደራሲውም የዚሁ አካባቢ ተወላጅ ናቸው። ምናልባትም፣ ተጉለትና ቡልጋን የመረጡት፣ በጥንቃቄ ስለሚያውቁት፣ ‹ተሃድሶ ያስፈልገዋል፤ ሊሻሻል ይገባዋል› ብለው ያመኑት ሃሳብ ስላለ ይሆናል። ምናልባትም፣ በወቅቱ ከዚሁ አካባቢ ወጥተው ዘመናዊ ዕውቀት ቀስመው፣ አዲስ ባህል ተዋውቀው ወደ ገጠር የገቡ ልሂቃን የሚደርስባቸውን ፈተና ለማሳየትም ይሆናል። ምናልባትም ተጉለትና ቡልጋ ኢትዮጵያን የሚወክል አንዳች ነገር አግኝተውበት ይሆናል።

 ‹የልብ አሳብ› ታሪኩ ሲጠናቀቅ፣ ከልደት እስከ ሞት ይተርካል። ባለታሪኮቹ የልጅነታቸውን ጨርሰው፣ አግብተው፣ ወልደው፣ የወለዷቸው ወልደው ታሪኩ ይጨረሳል። ‹አዲስ ዓለም› ግን ሙሉው ታሪክ ይህን ያህል ጊዜ አይፈጅም። ጉዞው የተመጠነ ነው። ‹የልብ አሳብ› የተራኪው ጣልቃ ገብነት ሲኖረው፣ ‹ዐዲስ ዓለም› ላይ ግን እንዲህ ያለው ሕፀፅ አይስተዋልበትም። የመጀመርያ ድርሰታቸው፣ በአጻጻፉ ተረት ተጭኖታል፤ ግብረገብ አይሎበታል። ሲጨርስም፣ ‹ይህንንም በመሰለ ጋብቻ ተጋብተው፤ ልጆች ወልደው፤ የልጅ ልጆች አይተው የሚሞቱ ባልና ሚስት እጅግ የታደሉ ናቸው› ይላል።

 ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው ባሕል ላይ ማተኮራቸው ነው። ጽዮን ሞገሣና ዐወቀ ከነባሩ ባሕል የወጡ ናቸው። ከመሰሎቻቸው ይለያሉ። ለመለየታቸው ምክንያት የሆነው ደግሞ ትምህርት ነው። ጽዮን ሞገሳ የሀገር ውስጡን፣ አወቀ የውጪውን የትምህርት ዓለም እንደወደዱት አግኝተውታል። ትምህርቱ ከአዲስ ባህል ጋር አስተዋውቋቸዋል። አዲሱ ባሕል የወደዱትን የመምረጥ፣ የፈለጉትን የመሆን፣ ያሰቡትን የመናገር፣ ነባሩን የመሞገት፣ ነባሩን ባህል ‹አሮጌና ጎታች› ብሎ የመንቀፍ ድፍረት ሰጥቷቸዋል።

 ነባር ከሆነው የሕክምና መንገድ ይልቅ ዘመናዊ የሆነውን የሕክምና ሥርዓት እንዲመረጡ፣ እንዲጠቀሙ፣ ተጠቅመውም እንዲድኑ ያደረጋቸው ደግሞ በትምህርት በኩል ያገኙት አዲስ ዕውቀት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top