ፍልስፍና

ለመሆኑ “የአፍሪካ ፍልስፍና” ከወዴት ነው?

(ወደ አፍሪካ ፍልስፍና የሚወስዱ መንገዶች)

ባለፉት ክፍሎች ስለ አፍሪካ ፍልስፍና ታሪካዊ ዳራና የአፍሪካን ፍልስፍና ለማጥናት ስለምንከተላቸው መንገዶች ተነጋግረናል። በዚህ ክፍል ደግሞ በአፍሪካ ፍልስፍና ውስጥ ስለሚገኙ ተምሳሌታዊ አስተሳሰቦች ትንሽ ነጥቦችን እናነሳለን። የአንድን ማኅበረሰብ አገር በቀል አስተሳሰብ ለመረዳት የዚያን ማኅበረሰብ ባህልና እሴት በራሱ ቋንቋ ማጥናት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸናል። የባህል ጥናት ራሱን የቻለ ገለጻዊ ዲስኩር ስለሚሆን ያንድን ማኅበረሰብ የአስተሳሰብ መሠረት ለማግኘት ከባህልና ቋንቋ ጥናት በተጨማሪ ፍልስፍናዊ አቀራረብ ያንን ማኅበረሰብ በተሻለ መልኩ ለመረዳት ያግዛል። እንዲያውም የባህል ጥናት የሚሸፍናቸው አስተሳሰባዊ ብልቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ በተች አቀራረብ የሚደረግ ጥልቅ ፍልስፍናዊ ዳሰሳ እውነተኛውን የማኅበረሰብ አስተሳሰባዊ ኅሊና ያሳየናል። ለዚህ ነው ልሂቃን ሁለት ባህሎችን በአንድ ዓይነት መመዘኛ መገምገምና ለማወዳደር መሞከር ቢያንስ ያንደኛውን ባህል መሠረታዊ ይዘት ይሸፍነዋል የሚሉት። ባለፈው የጠቀስነው ዊረዱ ለዚህ ሙግት ተጠቃሽ ነው።

 በባንቱ ማኅበረሰብ ፍልፍፍና ሰፊና ጥልቅ ምርምር ያደረገ ፕላሲድ ቴምፕልስ የተሰኘ ሚሲዮን ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይለናል። “Folklore alone and superficial descriptions of strange customs cannot enable us to discover and understand primitive man. Ethnology, linguistics, psycho-analysis, jurisprudence, sociology and the study of religions are able to yield definitive results only after the philosophy and the ontology of a primitive people have been thoroughly studied and written up.”

ከሚታየውና ዘፈቀዳዊ ከሚመስለው የየለት እንቅስቃሴና ባህላዊ ክዋኔዎች በስተጀርባ የዚያን ማኅበረሰብ ሕይወትና ተፈጥሮ የተረዳበት የአስተሳሰብ አስኳል አለ። እንደ ሌቪንና ሳምነር ያሉት አጥኝዎች በኢትዮጵያ ቃላዊ ጽሑፍና ባህላዊ ሕይወት ውስጥ ፍልስፍናን ፈልፍሎ ማውጣት እንደሚቻል ሲያሳስቡ ያንን የአስተሳሰብ አስኳል የማግኘት ጥረት ሲያበረታቱ ነው። በርግጥ ራሳቸውም በተግባር አሳይተውናል። ይህን መርህ በመከተል ነው የማኅበረሰቡን ፍልስፍና ማግኘት የሚቻለው። በርግጥም ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ የራሱ የሆኑ ተግባራዊ መገለጫዎች ሊኖሩት ግድ ይላል። ያንን ፍልስፍናዊ መሠረት፣ አስኳል ወይም የአስተሳሰብ ደም ሥር ሳያገኙ እንዲሁ በባህል ጥናት ወይም በሃይማኖታዊ እምነት ብቻ ለመገምገም መሞከር ሁለት ስህተቶችን ያስከትላል። የመጀመሪያው የዚያን ማኅበረሰብ ባህል በተሳሳተ መንገድ መረዳትና መተርጎም። ሁለተኛው ደግሞ ያንን ማኅበረሰብ ፍልስፍና የለውም ብሎ መፈረጅ። በአፍሪካ ፍልስፍና ታሪክ እንደተስተዋለው እንደዚህ ዓይነቶቹ ስህተቶች መዳረሻቸው ያ ማኅበረሰብ አያስብም ወይም ምክንያታዊ አይደለም የሚል ድምዳሜ ይሆናል። ብዙ ጊዜ የአፍሪካውያን ፍልስፍና የሚተችበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ባህላዊ ክዋኔዎቹን ከጥንቆላ ጋር በማያያዝ አስተሳሰብንና የሕይወትን ትርጉም ከዘመናዊ የሥነ አመክንዮና የሳይንስ መንገድ አንጻር ብቻ መመዘን ነው። ይህም ሕይወትን በምልዓት አለመመልከት ይሆናል።

 ይኸው የላይ የላይ ጥናት በራሱ ሌላም እንከን አለው። ይኸውም የአገር በቀል እውቀት ባለቤቶቹን “ይህ ለምን ሆነ ሲሏቸው አባቶቻችን ነገሩን” በማለት ያለ ምክንያት የተቀበሉት እምነት ነው የሚል ፍረጃ ነው። እርግጥ ነው አብዛኛዎቹ የአገር በቀል እውቀቶች (በተለይ ከመድሃኒት ጋር በተያያዘ) ባለቤቶቹ ለማንኛውም ሰው እንዲሁ አይገልጡም። ይህ ማለት ግን ፍጹም እውቀት የላቸውም ማለት አይደለም። ያ ለግለሰቦቹ የራሳቸው ንብረት ስለሆነ ማንም እንደፈለገ ሊያገኘው አይችልም። የራሳቸውን እውቀት ለኛ ስላልገለጡልን እነርሱም በግምት ነው የሚኖሩት ማለት አይደለም። ያ መድኃኒት ወይም ባህላዊ እውቀት አካላዊና ሥነ-ልቡናዊ ችግሮችን በዘላቂነት ሲፈውስ ተስተውሏልና። ውስብስብና ዘመናዊ ቴክኖሎጅን ተጠቅሞ መፈወስ የማይቻልን ህመም ባለ ባህል መድኃኒቱ በቀላሉ ሲያክመው እያየን ነው። በዚህ ረገድ መድኃኒት ቀማሚዎች፣ የስነ ልቡና ባለሙያዎች፣ የተሰበረ የሚጠግኑ ወጌሻዎች ከዶክተሮቹ በላይ ስኬታማ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው።

 ሳይንሳዊ ማብራሪያ፣ ሥነ አመክኖያዊ ሂደት ወይም የሂሳብ ቀመርን ስላልተከተለ አንድ እውቀት ለአቅመ እውቀት አልደረሰም ብሎ መፈረጅ ባንድ በኩል የዚያን ማኅበረሰብ ለዘመናት የተከማቸ ማኅበራዊ የጥበብ መካዘን እንዲሁ ችላ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ለዘመናችን ችግሮች አማራጭ መፍትሔ እንዳይገኝ በሩን ከርችሞ ከመዝጋት አይተናነስም። እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ በማድረግ ነው በአፍሪካ ፍልስፍና ጓዳዎች ውስጥ ለማኅበራዊ መስተጋብር፣ አካባቢያዊ ደኅንነት፣ ሥነ-ልቡናዊ ችግሮች፣ የእውቀትና ምርምር፣ የፖለቲካ ፍልስፍና፣ ሐተታ ተፈጥሮ፣ የሕይወት ምሥጢር፣ ሥነ መለኮት ወዘተ ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ የአስተሳሰብ ቁልፎችን የምንዳስሰው።

 ምንም እንኳ የአጠቃሏዊነት ባህርይ ቢኖረውም እንደ ዛኪያ አገላለጽ የአፍሪካውያን የጋራ አስተሳሰባዊ ስነ ልቡና መገለጫዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ:- [በተፈጥሮ፣] በፈጣሪና በሰው ልጆች ቅድስና ማመን፣ በማህበረሰብና በግለሰቦች መካከል የማይነጣጠል አንድነት እንዳለ ማሰብና ለባህርያዊ ቀናነትና ሥነ ምግባራዊ በጎነት ቅድሚያ መስጠት የሚሉት ይገኙባቸዋል። እነዚህ አፍሪካዊ የአስተሳሰብ ዓምዶች በማኅበራዊና ግላዊ ሕይወት የራሳቸው መገለጫ ይኖራቸዋል። እንደ ሶቅራጥስ አስተሳሰብ የግል ሕይወት የተመረመረ መሆን አለበት። ይህም የግል ቀና ባህርይን የሚያሳይ ነው። በግለሰብና በማኅበረሰብ ሕይወት የማይነጣጠል ህብረት መኖሩ ደግሞ የማኅበራዊ መስተጋብርን ሰናይነት የሚያጠቃልል ይሆናል። ይህም ለተፈጥሯዊ ቅድስና ትልቅ ግምት ከመስጠት የሚመነጭ ይሆናል። ከነዚህ የአስተሳሰብ መሠረቶች በመነሳት ነው ያንድን ማኅበረሰብ ባህላዊ፣ ማኅበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን የምንገመግመው።ባለፈው ክፍል ያየናቸውን አምስት ያክል መንገዶች ተከትለን መሠረታዊ የአፍሪካውያንን “ባህላዊና ዘፈቀዳዊ” ሕይወት ስንፈትሽ በርካታ ዘመንና ቦታ ተሻጋሪ የፍልስፍና አስተሳሰቦችን ማግኘት እንችላለን። የሰው ልጆች በረጅም ጊዜ የታሪክ ጉዟቸው ያካበቷቸው ጥበቦች ውስጥ የአፍሪካውያን ድርሻ ምን ነበር? የሚለው ጥያቄ የተወሰነ ምላሽ የሚያገኘውም ይህንን ሐሰሳ በቁርጠኝነት ለሚያከናውኑቱ ነው። እንደነ ሄግል ዓይነቶቹ አውሮፓውያን ለዚህ ጥያቄ ፍጹም አሉታዊ መልስ ሲሰጡ ይስተዋላል። እጓለ ገብረ ዮሐንስ የተሰኙ ኢትዮጵያዊ ምሁር በአፍሪካ ሰማይ ላይ የሥልጣኔን አየር ለሚፈልግ ሰው ጥረቱ ብርቱ ትዕግስትን ይጠይቃል ይላሉ። ምስራቃዊ አፍሪካን እንደ ናሙና በመውሰድ ለዘመናት የኖሩ አባቶቻችን በመንፈሳዊ ርዕዮተ ዓለም እየታገዙ ያስገኟቸውን የአስተሳሰብ ርቀቶች፣ ጽርየቶች (Insights) ለመረዳት ብርቱ ክንፍ፣ አጉሊ መነጽር (የንስር ዓይንና ክንፍ) ያስፈልጋል ባይ ናቸው። ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ግን የተሸፈነውን አየር፣ የቸልተኝነትን አቧራ ሲገፉት አንድን ነገር ማረጋገጥ ይቻላል “ሰማዩ ባዶ እንዳልነበረ” ይገለጥልናል ይላሉ እጓለ። የራሳቸው ፍለጋ ምን እንዳስገኘ እንዲህ ይላሉ “በአፍሪካ ምስራቃዊ ዳርቻ የታወቀውን ሥልጣኔ ለማስገኘት ብዙ ሊቃውንት ጥረዋል። ሰማዩ ወይም ጠፈሩ ልሙጥ ነበር። የነዚህ ሰዎች ጥረት የሚያበሩ ከዋክብት በዚህ ጠፈር ላይ አስገኝቷል። ምን ይሆናል። ብዙ ደመና ሸፍኗቸዋል። እነሱን ለመረዳት ክንፍ [-] ብርቱ የሕሊና ክንፍ ያሻል። እንዳቅማችን እንሞክራለን። ስለዚህ ማኅበረ ሊቃውንት በመላ ለመናገር በጠቀስነው ምክንያት [በርካታ ስለሆኑ ሁሉንም ከመተንተን ይልቅ ሊወክላቸው የሚችለውን አንድ መምረጥ እንደሚሻል] አይቻልም። አብነት ወይም ምስለኔነት ያለውን እንመርጣለን። ይህም […] ያሬድ [-] ቅዱስ ያሬድ ነው። ቅዱስ ያሬድ በዘመናት መካከል ለነበሩት ሁሉ የሀገራችን ሊቃውንት እንደራሴነት ያለው ጥልቅ መንፈስ ነው ብለን እናምናለን።” (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 63)

 እንግዲህ የአፍሪካውያንን የጥበብ፣ የፍልስፍና ምስለኔ ለሚያስስ ሰው እጁ ባዶውን እንደማይመለስ እጓለ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎቹም በየራሳቸው የደረሱበት እውነታ ነው። ጥቂቶቹን እንመልከት:-

1. ኡቡንቱ (Ubuntu):-

ይህ ፍልስፍና ግለሰብ ከማኅበረሰብ የተነጠለ ማንነት የለውም፣ ማኅበረሰብም ያለ ግለሰቦች ምንም አይደለም የሚል አስተሳሰብ ነው። ኡቡንቱ በበርካታ የአፍሪካውያን አስተሳሰብ ሰርጾ ያለ ፍልስፍና ነው። በማኅበራዊ ፋይዳው ሲታይ “I am because we are” ወይም እኔ ያለሁት እኛነት ስላለ ነው የሚል ነው። አንድ ግለሰብ የሚኖርበት ማኅበረሰብ ባህልና እሴት ውህድ ውጤት፣ የዚያ ግለሰብ የሕይወት ገመድ የተፈተለው ከማኅበረሰቡ የሕይወት ፈትል እንደሆነ፣ እንዲሁም ግለሰቡ የሚኖረው ማኅበረሰቡ ደኅና ሲሆን እንደሆነ ያሳያል። ስለዚህ ሰውን ሰው የሚያሰኘው በተፈጥሮው የተሰጠው አካላዊ ወይም ተፈጥሯዊ ተክለ ሰብእና ብቻ አይደለም። ይልቁን በማኅበረሰቡ የአስተሳሰብና የማንነት፣ የባህልና የሥነ ልቡና፣ የጥበብና የፍልስፍና ውህዶች ተቀይጦ የተሰራና በመሰራት ላይ ያለ የአካባቢው ውጤት ነው ወደሚል “የሰውነት” ትርጓሜ ያመራል።

ሙሉ እኔነት የሚረጋገጠው የሌሎቹን እኔነት በለበስኩት ልክ ነው፣ ሰውን ሰው ያሰኘው ሌሎቹን በውስጡ በተረዳበት፣ የሌሎችን ሰዎች ማንነት ባንጸባረቀበት ልክ ነው። ዴዝሞንድ ቱቱ እንዲህ ይላሉ:- “[…] Ubuntu is the essence of being a person. It means that we are people through other people. We cannot be fully human alone. We are made for interdependence, we are made for family. When you have ubuntu you embrace others. You are generous, compassionate.” ከፖለቲካዊ ፍልስፍና አንጻር ካየነው የአንድ ማኅበረሰብ በጎ ህልውና የሚረጋገጠው በሌሎች ማኅበረሰቦች በጎነት ልክ ነው። ይህንን የአፍሪካን የየለት ኑሮ መገለጫ ከጥንት እስከ ዘመናችን ፈላስፎች በተለያየ መንገድ ሲገልጹት የኖሩት ነው። ለምሳሌ አርስቶትል ከመንጋው የተለየ ግለሰብ እንደ አውሬ ይቆጠራል ይላል። ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነውና የዚህ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ አባልነት የሰውነት መገለጫ ነው። በተመሳሳይ የቅርብ ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንትም የአንድ ማህበረሰብ ደህንነት የሚረጋገጠው እኔነትና እኛነት ሲዋሃዱ ነው። እንዲያውም ፍትህ ማለት በሰዎች መካከል የፍላጎቶች መዋሃድ እንደሆነ ይነግረናል። ወደ ሄግል ፍልስፍና ስንመጣም ያው ነው። የሰው ልጆች የታሪክ ጉዞ መዳረሻው እኔነትን በእኛነት ውስጥ፣ እኛነትን በእኔነት ውስጥ ማግኘት ነው።

 የኡቡንቱ አስተሳሰብ እንዲሁ የተለመደና በዘመናችን መጤ ባህሎች እየተዋጠ መጣ እንጂ በልጆች አስተዳደግ፣ በማኅበራዊ ችግር አፈታት፣ በርስ በርስ ግንኙነት ከፍተኛ ፋይዳዎችን እየተጫወተ የኖረና አሁንም ከዘመናዊ የፖለቲካ ማኅበራዊ አስተሳሰቦች ጋር ቢቀየጥ ለማኅበራዊ ፍትህ፣ ለደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል። በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ አሁንም በገጠሩ ማኅበረሰብ የሚስተዋለው ማኅበራዊ ትስስር ከዚህ እኔነትና እኛነትን አንድ አድርጎ ከመረዳት ነው። ልጆች በጋራ ያድጋሉ፣ ማኅበራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ይበጅላቸዋል፣ ሥራዎች በጋራ ይሰራሉ:: አንዱ እየተራበ ጎረቤቱ አይጠግብም (ቢያንስ ያበድረዋል)፤ ኧረ እንደ አፋር ባሉ ማኅበረሰቦችስ ምግብን ተካፍሎ መብላት፣ ያንዱን ችግር ተካፍሎ መፍትሄ ማበጀት የማኅበረሰቡ ግዴታም ጭምር ናቸው።

 2. ኡጃማ (Ujamaa) (የአፍሪካ “ሶሻሊዝም” መሠረት):-

 እንደ ኔሬሬ ያሉ የፖለቲካ ፈላስፎች የአፍሪካውያንን አንድነት ሲቀይሱ እንደ መነሻ ያደረጉት የማርክስን ሕብረተሰባዊነት ወይም የፈረንሳይ አብዮት ያስተጋባቸውን ሰው ሰራሽ ወንድማማችነት አይደለም። ይልቁን ለረጅም ዘመናት አፍሪካውያን የኖሩባቸውን “በተፈጥሮ” የአፍሪካውያን የሕይወት መገለጫ የሆነውን ኡጃማ ነው። ትርጉሙ ወንድማማችነት፣ ቤተሰባዊነት ወይም ባጭሩ አንድነት፣ ማኅበራዊ ውሕደት ነው። እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል ራሱን የዚያ ማኅበረሰብ ቤተሰብ እንደሆነ በመቁጠር ለማኅበረሰቡ ደህንነት እንደያቅሙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ለኔሬሬ ኅብረተሰባዊነት (Socialism and communism) ያለ ሥራ አስተዋጽኦ ትርጉም እንደሌላቸው ሁሉ አፍሪካዊ ኡጃማም እያንዳንዱ በሰራው ልክ ማኅበራዊ አባልነቱን ያረጋግጣል ይለናል። የዚህ ፍልስፍና ማኅበረ ፖለቲካዊ ፋይዳው ዝቅ ሲል ያንድን ማኅበረሰብ ሰላማዊ ቤተሰባዊነት ለማረጋገጥ ሲረዳ ከፍ ሲል ደግሞ የአፍሪካውያንን ህብረት ለማረጋገጥ ሩቅ መሔድ ሳይጠበቅብን በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሚገኘውን የኡጃማ አስተሳሰብ ለዘመኑ በሚመጥን መንገድ ብንጠቀምበት ስኬታማ መሆን ይቻላል። የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኞች ይህንን ይሁንታ ማቅረባቸውም ከአስተሳሰቡ ፍልስፍናዊ ጥልቀት የተነሳ ነው።

 3. የግብጻውያን ማት (Maat):-

ይህ ጽንሰ ሐሳብ የሕልውና፣ የተፈጥሯዊ ውበት፣ የምሉዕነት መገለጫ ነው። ማት የነገሮችን ሕልውና፣ የርስ በርስ ግንኙነት በጎነት የሚወስን ውስጣዊ ሕግ ነው ልንለው እንችላለን። የነፍስና የስጋን ውህደት፣ በተፈጥሮና በፈጣሪ መካከል ስላለው የውህደት ሰንሰለት ድርና ማግ አድርጎ የሚያስተሳስር የሕላዌ ንጥር ነው። የአጠቃላይ የተፈጥሮ ሥርዓታዊነትና ዘፈቀዳዊ አለመሆን መገለጫ ነው። በተፈጥሯዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ ውበትን የሚያጎናጽፍ ነፍስ ነው።

ጽንሰ ሐሳቡ ሰፊና የተለያዩ መገለጫዎች ሲኖሩት ኦቤንጋ የተሰኘ ተመራማሪ ስለ ማት ያስቀመጠውን ማጠቃለያ እዚህ ላይ የነገራችን ማሰሪያ ብናደርገው ይሻላል።

“Maat is reality as a whole, that is, the totality of all things possessing actuality, existence, or essence. Maat is that which exists objectively. In fact, Maat is that which has necessary and not just contingent existence. This is why Maat is everywhere and pervades all creation (er-djer). It means also that Maat is pertinent to all the spheres of reality, the divine or sacred, the cosmic, the physical, the political, and the familial. In short, Maat is an exhaustive and comprehensive concept.

This inclusiveness makes it an orderly and aesthetically coherent whole; which is why Maat also means the orderliness of the totality of existence. Accordingly, everything in the universe that is real and orderly is the expression or manifestation of Maat.”

 ለግብጻውያን የግለሰቦችን ጠባይ ወይም የማኅበረሰብን መዋቅር የሚገመግሙበት መስፈርት ይህንን የማትን ጠማሪነት ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ማለት እንችላለን። የምናደርገው ነገር ከዚህ የተፈጥሮ ሕግ ጋር የማይጋጭ እንደሆነ ማረጋገጥ ይኖርብናል። ለሃይማኖተኛ ሰው ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ይመሳሰላል። ሲሴሮ የተባለ የጥንት ሮማ ፈላስፋ የአንድ ነገር በጎነት የሚለካው ከተፈጥሮ ሕግ ጋር ባለው ቅንጅት ወይም ስምምነት ነው ይላል። ይህ ማት እንግዲህ የሚዛንነትን ሚና የሚጫወት ይሆናል። ከማት መሰረታዊ የጠማሪነት፣ የዳኝነት፣ የስምሙነት ባህርይ ውጭ የሆነ ነገር በህግ ወንጀል፣ በማኅበረሰብ ውጉዝ፣ በሃይማኖት ሃጢአት እንደምንለው ነው ማለት ነው። ይህ አስተሳሰብ እንደ ኦቤንጋ የግብጻውያን ብቻ ሳይሆን የአብዛኛዎቹ አፍሪካውያን አስተሳሰብም ነው ይለናል። እርግጥ ነው እያንዳንዱ ባህል ቢፈተሽ መሰል አስተሳሰብ አይጠፋም።

 4. የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት:-

 በኢትዮጵያና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ የሚገኘው የኦሮሞ ማኅበረሰብ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ህዝቦች የራሱ የሆነ አገር በቀል እውቀት ክምችት እንዳለው ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። በዋናነት የገዳ ሥርዓት በመባል የሚታወቅ ሲሆን የፖለቲካ፣ የሥነ-ተፈጥሮ፣ የሥነ-መለኮት እንዲሁም የሥነ-ምግባርና ማኅበራዊ መስተጋብር ፍልስፍናዎችን ያቀፈ ነው። በፖለቲካው ረገድ የገዳ ዲሞክራሲ በመባል የሚታወቀው ፍጹም ግልጽና

“ልጆች በጋራ ያድጋሉ፣ ማኅበራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሄ ይበጅላቸዋል፣ ሥራዎች በጋራ ይሰራሉ:: አንዱ እየተራበ ጎረቤቱ አይጠግብም (ቢያንስ ያበድረዋል)፤ ኧረ እንደ አፋር ባሉ ማኅበረሰቦችስ ምግብን ተካፍሎ መብላት፣ ያንዱን ችግር ተካፍሎ መፍትሄ ማበጀት የማኅበረሰቡ ግዴታም ጭምር ናቸው።”

ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የመሪዎች ምርጫ ይካሄዳል። ምርጫውና አመራሩ ብቻ ሳይሆን አባ ገዳዎቹን ወይም መሪዎቹን የመሪነት ጥበብ የሚያስተምሩበት የእድሜን እርከን መሠረት ያደረገው ሥርዓት ትልቅ ፍልስፍናዊ መሠረት ያለው ነው። ከሥነ- ተፈጥሮ ጋር በተያያዘም ሁሉም ነገር ከፈጣሪ የመጣ ቅዱስና ወንድማማች ነው ብለው ስለሚያምኑ ተፈጥሮን የመንከባከብ ባህላቸው ተምሳሌታዊ ነው። እንደ ፕሮፌሰር ወርቅነህ ቀልቤሳ አገላለጽ ይህ ፍልስፍና Ecotheology በመባል የሚታወቅ ሲሆን የተፈጥሮን ቅድስናና የሰው ልጅ የተፈጥሮ አካል እንጅ ውጭ ሆኖ የሚበዘብዝ አምባገነን እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። ከሰላም ጋር በተያያዘም ነጋ (Peace) የተሰኘ ጽንሰ ሐሳብ የማኅበረሰባዊ ሰላምን የማኅበረሰቡ መገለጫ እንደሆነ ያሳያል። እንደ ጠና ደዎ አገላለጽ በኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎች ዘንድ ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮ በሙሉ የተሰጠ ጸጋ እንደሆነ ይታሰባል። “The Oromo of Ethiopia maintain that “peace,” translated as nagaa, is the essential key to all cosmic and human order, possessing the highest and most central value for humanity to pursue.”

 5. የቅኔ ባህል:-

የኢትዮጵያውያን የቅኔ ባህል የተለያዩ መገለጫዎች አሉት። ከነዚህ ውስጥ የሰምና ወርቅ ቅኔና የግእዝ ቅኔ ይገኙበታል። የሰምና ወርቅ ቅኔ በአጫጭር ሰም ለበስ ግጥሞች አማካኝነት ማኅበራዊ ትችት፣ አድናቆትና ሙገሳ፣ ፖለቲካዊ ትችትና አመጽ፣ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ወዘተ የሚገለጹበት ዘይቤ ነው። ከላይ ሲታይ የዋዛ ፈዛዛ የሚመስለው አገላለጽ በውስጡ እምቅ ሐሳብን የያዘ ነው። ይህም ሁለት ዓይነት አቀራረብ ያለው ነው። ባንድ በኩል ህዝቡ በተለያየ አጋጣሚ የሚቀኘው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አዝማሪ ከዜማና ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር አዋዝቶ የሚያቀርበው ነው። “እረኛ ምን አለ?” “አዝማሪዎች ምን ይላሉ?” “የህዝቡ እንጉርጉሮ ምን ይመስላል?” ወዘተ

ዓይነት ጥያቄዎች የፖለቲካ ሰዎች የህዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ የሰምና ወርቅን ቅኔ ማፍታትንና መተንተንን እንደ አንዱ አማራጭ መጠቀማቸው የቅኔው ፍልስፍናዊ እምቅ ጥበብ ምን ያክል ማኅበረ-ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው ያሳያል።

የግእዝ ቅኔ በበኩሉ እንዲሁ ሰም ለበስ ቢሆንም በዋናነት ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን የሚመለከት ሲሆን ፈጣሪን እስከ መተቸት የሚደርስ የጥልቅ ምርምር ውጤት ነው። አእምሮንና ከፍተኛ የግእዝ ቋንቋ ችሎታን የሚጠይቀው የግእዝ ቅኔ የሰው ልጅ በጥልቅ ተመስጦ የሚገለጥለትን እውነት በአጭር ቃላትና በቀላል አገላለጽ የሚያስቀምጥበት መንገድ ነው። የቅኔ ባህል የቋንቋን የገላጭነት ኃይል ያሳያል። ከላይ የጠቀስናቸው ሊቅ እጓለ ስለ ቅኔ እንዲህ ብለዋል። “ኢትዮጵያውያን በክርስትና ክንፍ ላይ ሆነው አየረ አየራት ወጥተው እመቀ እመቃት ወርደው የነገሮችን ባህርይ ለመመርመርና ለመረዳት የህሊና ጥረት አድርገው ከብዙ የሃሳብ ትክክለኝነትና ጽርየት ደርሰዋል። … እዚህ ላይ በመጀመሪያ ሊወሳለት የሚገባው ከማናቸውም ሃገር ስነ ጽሁፍ ጋር ሊወዳደር የሚችለው የቅኔ ትምህርት ነው። እንዲያውም አቻም የሌለው ነው ለማለትም ይቻላል። ቅኔ ወይም ግጥም በፈረንጆች ቀላል ነገር ነው። ሁሉም የሚረዳው ለተራ ህዝብ የሚሆን ነው። … እነርሱ እንደሚሉት የፍልስፍና ህዝባዊ አቀራረብ ግጥም ይባላል ማለት ነው። ቅኔ ስንል ግን ጨርሶ ሌላ ነገር ነው። ከባድ ነው። ምስጢር የተሞላ የረቀቀ ፍልስፍና የተከማቸበት ማለት ነው። ባለቅኔውም ሰሚውም በህሊና ርቀት [ረቂቅነት] የተራመዱ ናቸው። ሁለቱ ሲገናኙ አንደኛው ከመጀመሩ ሁለተኛው ይበል! ይበል! እያለ በአንክሮ ይፈነዳል። በምስጢሩ ገፈት ብቻ ሰክሮ ወይም በኃይለ ቃሉ ተማርኮ ነው። የኅሊና ርቀትና የቃል የአንደበት ጉልበት በቅኔ ትምህርት በጣም ተስፋፍቶ ይታያል።” (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 73)

 ታላቁ ባለቅኔ ጸጋዬ ገብረ መድህን በበኩሉ “ ‘ሥነ-ግጥም ወይም ቅኔ የሥነ-ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበባት ሁሉ፣ የፈጠራ ሁሉ የደም ጠብታ ነው’ ይላሉ አበው።” ይለናል። የሁለቱም ምሁራን አገላለጽ የገዘፈ እውነትን ይዟል። በቋንቋ ላይ ተራቅቆ፣ ቃላትን አሰካክቶ ጥልቅ ስሜትን፣ የኑባሬን ምሥጢር መግለጽ መቻል የጠቢባንን ልዕለ ኅሊና ሲጠይቅ ለጥበብ ደግሞ የደም ጠብታዋ፣ የነፍሷ እስትንፋስ ነው ማለት ነው። በሁለቱም የቅኔ ባህሎች (በሰምና ወርቅ እና የግእዝ ቅኔ) የምናገኘው ይህንን የጥበብ የደም ጠብታ ነው።

 እነዚህን እንደ ማሳያ ናሙናነት አቀረብሁ እንጅ እጅግ በርካታ ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸው ብርቅዬ አስተሳሰቦችን ማግኘት ቀላል ነው። በቀጣዩ ክፍል ተጨማሪ ፍልስፍናዎችን በመዳሰስ ለዘመናችን ችግሮች መፍትሔነት የሚኖራቸውን ፋይዳ ለመተንተን እሞክራለሁ። (ይቀጥላል) 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top