በላ ልበልሃ

ቴሌቪዥንና ፋይዳው አሉታዊ ወይስ አዎንታዊ

ቴሌቪዥን በመላው ዓለም ባሉ ተጠቃሚዎች ዘንድ እንደ አንዱ የቤተሰብ አባል እየተቆጠረ ከመጣ ቆይቷል። አሁን አሁን እቤት ውስጥ የሚያየው በሌለበት ሰዓት እንኳ ድምጹ ስለተለመደ ፀጥ ብለን እንከፍተዋለን። ቤቱ ጨልሞ ብርሃን ሲያስፈልገን መስኮት መጋረጃውን እንደምንገልጥ ሁሉ፤ ቤት ስንገባ ጭርታን የምናስወግደው በቴሌቪዥናችን ድምጽ እየሆነ መጥቷል። ይህ ዘመናዊው አኗኗር በሰዎች ላይ ያመጣውን መገለል እና አስገዳጅ የሆኑ ለብቻ የመኖር የኑሮ ዘይቤዎችንም ለመቋቋም ጭምር አገልግሏል።

 በብዙ ሀገራት የቴሌቪዥን ይዘቶች የሚያመጧቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች በምሁራን ለብዙ ዓመታት ሲጠኑ ቆይተዋል። በተለይም ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ መገናኛ ብዙሃን በተደራሹ (audience) ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ በሰፊው እየተጠና ይገኛል። ስለ እነዚህ ጥናቶች ቀደምት የሆኑት በ1920 ዎቹና 1930ዎቹ የተካሄዱት ሲሆኑ፤ የመገናኛ ብዙሃን ይዘቶች በተደራሹ ላይ በጣም ከባድ እና ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ ነበር። እነዚህ ተመራማሪዎች ካካሄዷቸው ምርምሮች በተጨማሪ ሦስት ክስተቶች ምሁራኑን ስለግኝታቸው ትክክለኛነት እርግጠኛ እንዲሆኑ አድርገዋቸው ነበር። የመጀመሪያው በወቅቱ የነበሩት በአዉሮፓ በሬዲዮ የሚተላለፉ የጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች ወጣቱን ወደ ጦርነት ለማነሳሳት የነበራቸው ውጤታማነት ነው። ሁለተኛው በወቅቱ የነበሩት ፊልሞች በህጻናት ላይ ያመጡ የነበሩት የባህሪ ለውጦች ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ በወቅቱ የነበሩ የተሳሳቱ የኮሙኒኬሽን ሞዴሎች ናቸው። እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ተመራማሪዎቹ የመገናኛ ብዙሃን በተደራሹ ላይ ከፍተኛና ቀጥተኛ ተፅዕኖ አላቸው ብለው እንዲያስቡ ምክንያት ሆነው እንደነበር ይታመናል።

ከዚህም ቀጥሎ በ1940ዎቹ እስከ በ1960ዎቹ የመጡት የምርምር ውጤቶች ግን የመገናኛ ብዙሃንን ተፅዕኖ በእጅጉ ዝቅ አድርገው (Minimal effect) ያቀረቡ ነበሩ። ለምሳሌ በአሜሪካ በተደረጉ ጥናቶች እነ ፖል ላዛርስፊልድ እና ኤሊሁ ካዝ በ1940ዎቹ የአሜሪካ ፕሮዚዳንት ምርጫዎች ወቅት ሚዲያ የነበረውን ተጽዕኖ ለማወቅ ሲሞክሩ ያገኙት ውጤት በወቅቱ አስገራሚ ሆኖ ነበር። የምርምሩ ውጤት እንዳሳየው ከሆነ በፕሬዚዳንት ምርጫ ወቅት እጅግ እልህ አስጨራሽ የሆነ የሚዲያ የምረጡኝ ቅስቀሳ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ ሰዎች ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ግን የሚዲያ ጥረት እዚህ ግባ የሚባል ሚና አልነበረውም። ይልቁንም ከጓደኞች፤ ከቤተሰብና ከስራ ባልደረቦች ጋር የተደረጉ የእርስ በርስ ውይይቶች መራጮችን ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል ወሳኝ እንደነበሩ ተደርሶበታል። ይህም ቀደም ብሎ ሲታሰብ የነበረውን ከባድ የመገናኛ ብዙሃን ተፅዕኖ በጥርጣሬ ስር ከማስገባትም አልፎ ጊዜ ያለፈበት ግኝት ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል።

ከዚህም ተነስተው ተመራማሪዎቹ የሰዎችን ባህሪም ሆነ ተግባር ለመወሰን ከሚዲያ ይልቅ የእርስ በርስ ተግባቦት (Interpersonal communication) የተሻለ እንደሆነና ሚዲያ የተጠበቀውን ያህል ተፅእኖ እንደሌለው መስክረዋል። ምርምሮቹ በቀጠሉ ቁጥርና የመጠቁ የምርምር ዘዴዎች በተግባር ላይ እየዋሉ መምጣት ሲጀምሩ በሚዲያ ተፅእኖ ላይ የተለያዩ አዳዲስ የምርምር ግኝቶች ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምረው ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ግኝቶች ሚዲያ በጣም የሚጋነን ተፅዕኖ እንደሌለው ነገር ግን ያን የህልም ተፅዕኖው ተቃሎ የሚታይ እንዳልሆነ (Moderate Effect) ማሳየት ችለዋል።

 ከነዚህ መልከ ብዙ ምርምሮች በጣም አነጋጋሪና የብዙዎችን ቀልብ የሳቡት ቴሌቪዥን በህጻናትና በታዳጊዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅእኖ የሚያሳዩቱ ናቸው። በነዚህ ምርምሮች ግንዛቤ እና ብዙዎቹ ተመራማሪዎች እንደሚየምኑት ከሆነ ቴሌቪዥን በሁሉም ህብረተሰብ ላይ ተመሳሳይ የሆነ ተፅእኖ ማሳደር አይችልም። ለምሳሌ በተማረውና ባልተማረው፤ በወንድና በሴት፤ በህፃናትና በአዋቂዎች፤ በገጠር ነዋሪና በከተሜ ላይ የተለያየ መጠን ያለው ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል ማለት ነው።

ከነዚህ የቴሌቪዥንን አሉታዊ ተፅእኖ ከሚተነትኑት ንድፈ-ሃሳቦች ውስጥ በጣም ገናና የነበረውና እስካሁን ተመራማሪዎችን እየሳበ የሚገኘው ካልቲቬሽን ቲዎሪ (Cultivation Theory) የሚባለው ነው:: የዚህ ቲዎሪ ግንባር ቀደም ባለቤት የሆነው ጆርጅ ጋብርነር በ1970ዎቹ የጀመረው ጥናቱ ላይ ተመርኩዞ እንደሚያስረዳው ከሆነ፤ አንዳንድ የቴሌቪዥን ይዘቶች በተለይም ፀብና ወንጀል (violence) የሚበዛባቸው ፊልሞች በተመልካቾች ላይ ምንም እንኳ በረጅም ጊዜ የሚከሰት ቢሆንም፤ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው ያስረዳል። ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በህፃናት ላይ የጠና እንደሆነ ይናገራል። በዚህ ቲዮሪ እንደሚገለፀው፤ አንድ ሰው በቀን 4 ሰዓት እና ከዚያ በላይ እንደዚህ ያሉ የቴሌቪዥን ይዘቶችን የሚመለከት ከሆነ ከባድ የቴሌቪዥን ተመልካች (Heavy Television Viewer) በሚለው ዘርፍ ይመደባል። እነዚህ ረዥም ሰዓት የመመልከት አመል ያለባቸው ሰዎች ናቸው እንግዲህ ለተፅዕኖው ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚወሰዱት።

እንደ ምሁራኑ አባባል ከባድ የቴሌቪዥን ተመልካቾች እነዚህን ወንጀልና ግጭት የሚበዛባቸው ፊልሞች ከነባራዊው አለም ጋር በማመሳሰላቸው የሚመጣ የመጨነቅ ምልክት ይታይባቸዋል። ይህም በሳይንሳዊ አጠራሩ ሚን ወርልድ ሲንድረም (Mean World Syndrome) ይሉታል። በተከታታይ የተደረጉ ጥናቶች እንዳሳዩት እነዚህ ከባድ ተመልካቾች ነባራዊውን ዓለም ልክ ፊልም ላይ እንደሚያዩት አስፈሪ ወንጀልና ጸብ የበዛበት አድርገው ይቆጥራሉ። በምርምሩ ውስጥ የተካተቱት ስለ ነባራዊው ዓለም የተጠየቁ ተመሳሳይ የምርምር ጥያቄዎች ቴሌቪዥንን ለረዥም ጊዜ እና ለአጭር ጊዜ ለሚመለከቱ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ቀርበው ነበር ። አሰገራሚ የሆነው ውጤት ቴሌቪዥንን ለረዥም ጊዜ የሚመለከቱ ሰዎች ስለነባራዊው ዓለም ተጠይቀው የሰጡዋቸው ምላሾች በቲቪ ላይ ከሚታዩት ክስተቶች ጋር በጣም ተቀራራቢ መሆናቸው ነበር።

ለምሳሌ ጥናቱ በተደረገበት በአሜሪካ ከህዝቡ ስንት በመቶው ፖሊስ ይመስላችኋል? በሳምንት ውስጥ ከቤትህ ብትወጣ ምን ያህል ጸብና ወንጀል ሊያጋጥምህ ይችላል? በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖሊስና የጦር ኃይል መጨመር ወይስ መቀነስ ያስፈልጋል? ወንጀል ላይ የተሰማሩ ሰዎች እነማን ናቸው? በወንጀለኛ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ምን ያህል ጠንካራ መሆን አለበት? ጥቁሮችና የሂስፓኒክ ሰዎች ምን አይነት ሰዎች ናቸው? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ያዘለ መጠይቅ ቴሌቪዥን በሚመለከቱ ሰዎች ካስሞሉ በኋላ ውጤቱ ሲታይ ቴሌቪዥን ለረዥም ጊዜ የሚያዩ ሰዎች እና ቴሌቪዥን ለአጭር ጊዜ የሚያዩ ሰዎች በሰጡት ምላሽ መካከል ተመራማሪዎቹን ያስገረመ ውጤት ነው የተገኘው። አስገራሚው ነገር ቴሌቪዥን ለረዥም ጊዜ የሚያዩ ሰዎች ከተጠበቀው በላይ ከቴሌቪዥን ይዘት ጋር የተመሳሰሉ ምላሾችን ሰጥተዋል። ለምሳሌ በአሜሪካ ስንት በመቶው ፖሊስ ነው ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛው መልስ በወቅቱ አንድ በመቶ ሲሆን ቴሌቪዥን ለረዥም ጊዜ የሚያዩ ሰዎች በጣም ከፍ ያለ ቁጥር ገምተዋል። እንደ ተመራማሪዎቹ ይህ የሆነው በፊልሞች ላይ የሚታዩ የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎች እሰከ 20 በመቶ ስለሚደርሱ ይህ ተጽእኖ አሳድሮባቸው ነው ብለው ያምናሉ።

 የዚህ ሁሉ መደምደሚያ እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ ቴሌቪዥን ለረዥም ጊዜ የሚያዩ ሰዎች ሳይታወቃቸው አለምን ወይንም አካባቢያቸውን ወንጀል የበዛበት አስፈሪ ቦታ አርገው ይወስዳሉ። በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች አጠራጣሪና የማይታመኑ በማንኛውም ጊዜ አደጋ ሊያደርሱባቸው የሚችሉ እና ሁልጊዜ ጥንቃቄ መጓዝ እንደሚያስፈልግ ይሰማቸዋል። ለዚህም ብዙዎች ከቤት አለመውጣትን አማራጭ እስከማድረግ ይደርሳሉ። ይህንን ነው ተመራማሪዎቹ [Mean World Syndrome] የሚሉት። ትርጉሙም አለምን እንደ መጥፎ ሥፍራ የማየት አባዜ ማለት ነው።

 በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች በውጭው አለም ላይ ያላቸው እምነት ይቀንሳል፤ ከሰዎች ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት ጥርጣሬ የተሞላበት ይሆናል፤ የተወሰኑ የማህበረሰብ አካላት ወንጀለኛ እንደሆኑ አድርገው ይወስዳሉ፤ በሀገሪቱ ወንጀል በጣም በዝቷል ብለው ስለሚያስቡ ጥብቅ የሆነ የመንግስት አደረጃጀትና አወቃቀር እንዲኖር ይጠይቃሉ፤ ብዙ የህግ አስፈጻሚ ኃይል በሀገሪቱ እንዲኖር ድምፅ ይሰጣሉ፤ በአጠቃላይ ህይወታቸው በፍርሃት የተሞላ ይሆንና የተለየ አመል ይዘው ይወጣሉ።

እንደዚህ ከሆነ እንግዲህ ስንቶቻችን ልጆቻችን የሚመለከቱትን የቴሌቪዥን ይዘት እንከታተላለን የሚለው ጥያቄ በጣም አንገብጋቢ ይሆናል። የልጆቻችን የወደፊት ህይወት እንዳይዛባ መውሰድ ያለብንን ጥንቃቄ እነዚህ ተመራማሪዎች ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲመክሩ ቆይተዋል። ብዙዎቻችን ባለማወቅ ባንጠቀማቸውም፤ ልጆቻችን መጥፎ የቴሌቪዥን ይዘቶችን እንዳያዩ በሪሞት ኮንትሮል የማገጃ ጥበብ በዲሽ መቀበያዎች ውሰጥ ተካቷል።

ምሁራን እንደዚህ አይነት ፀብ የበዛባቸዉ ፊልሞች መሸት ባሉ ሰዓታት ብቻ እንዲቀርቡ ማለትም ህፃናት በተኙበት ሰአት እንዲተላለፉ በህግ ጭምር እንዲደነገግ እስከማድረግ ደርሰዋል። እኛ ሀገር ይህን የመሰለ ቁጥጥር ይኑር አይኑር ባላውቅም ብዙዎቹ ቻናሎች አሁን አሁን ከውጪ በቀጥታ የሚመጡ መሆናቸው ህግ የማስከበሩን ስራ አዳጋች ያደረገው ይመስላል። ስለዚህ ቀሪው መፍትሔ የራስን ቤት መቆጣጠር ይሆናል ማለት ነው።

በተቃራኒው ህፃናት ብዙ ከቴሌቪዥን የሚማሩት ነገር አለ። በተለይ ስለ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስለ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለ ስነ ተፈጥሮና ስነ ምድር ብዙ ነገር ይማራሉ። ለምሳሌ አልበርት ባንዱራ ቴሌቪዥን ሰዎችን በተለይም ህፃናትን ክፉም ሆነ ደግ ነገሮችን የማስተማር አቅም እንዳላቸው በምርምር አስደግፎ ይናገራል። ችግሩ የህፃናት የመገንዘብ አቅም በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለፊልም ተብሎ በገጸ-ባህርያት የተሰራን ድርጊት በእውነት ከተደረገው ነገር ለይቶ ማየትና ማገናዘብ በጣም ይከብዳቸዋል። በፊልሞች ላይ የሚያዩት ነገር በእውን የተደረገ ስለሚመስላቸው በነሱ ላይ ጫናው የበረታ ይሆናል።

በአሜሪካ ቴሌቪዥን ስርጭትን የሚቆጣጠረው ኤፍሲሲ (የፌዴራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን) ከ1970 ጀምሮ የተለያዩ ድንጋጌዎችን በሚዲያ ተቋማት ላይ አውጥቷል። እነዚህም ጸብ የበዛባቸው ፊልሞች እንዲቀነሱ ካልሆነም በጣም በመሹ ሰአታት እንዲቀርቡ አቅጣጫ ሰጥቷል። የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለህፃናት የሚሆኑ ትምህርታዊ ዝግጅቶችን ያለ ቁጥጥር በሚለቀቁ ጊዜ ህፃናት ከልቅ ወሲብ ቀስቃሽ ይዘቶች ባለፈ በሽጉጥ ግንባር የሚበረቅሰውን፣ በስለት ልብ ላይ የሚወጋውን ከዚህም የባሰ አረመኔያዊ ተግባራትን በፊልሞች ውስጥ ማየታቸው የማይቀር ነው። በሌላም በኩል ወጣቶች ወንጀል መፈጸምን እንደተራ ነገር እንዲያዩ ከማድረግ አልፎ የወንጀል አሰራር ዘዴዎችንም እስከማስተማር ይደርሳል። እንደ አሜሪካ ባሉ የጦር መሳሪያ ግዢ ፈቃድ ባለባቸው ሀገራት በወጣት ልጆች በየትምህርት ቤቱ የሚፈጸሙ በየዜናው የምናያቸው ተደጋጋሚ ግድያዎች መነሻቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፀብና ወንጀል የበዛባቸው ፊልሞች ናቸው የሚሉ ምሁራን እየበረከቱ መጥተዋል። ቴሌቪዥን በርካታ ምሁራን እንደሚስማሙበትም ከሆነ ሰዎችን ወንጀል እንዲሰሩ በቀጥታ ባደርግም በሰዎች ውስጥ በተፈጥሮ ያሉ ወንጀል የመፈፀም ዝንባሌዎችን በተግባር እንዲገለጹ የመገፋፋት (reinforce) አቅም አለው።

በዚህ ዘርፍ የተሰሩት አብዛኛዎቹ ምርምሮች በቴሌቪዥን ላይ ቢያተኩሩም በአንዳንድ ሀገራት የሬዲዮ ድራማዎችን ከመጠን በላይ የሚከታተሉ ሰዎች ላይም ተመሳሳይ የሆነ የመደበላለቅ ምልክት ሊታይ እንደሚችል ይገልፃሉ። በሬዲዮ ድራማ ላይ የምናገኛቸው አብዛኞቹ ገጸ-ባህሪያት በተለይም በፍቅር ግኑኝነት ታሪካቸው ውስጥ ማታለል፣ መክዳት፣ ቅናት፣ መበደል እና ሌሎች የክፋት ተግባራት በሰፊው ታጭቀው በመቅረባቸው የተነሳ ሰዎች ባካባቢያቸው ባሉ ሰዎች ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር፤ የፍቅር ግንኝነታቸው በጥርጣሬ የተሞላ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይታመናል።

 መረሳት የሌለበትና በርካታ ምሁራን የሚመክሩት ግን ይህ አይነት ጫና ለረዥም ጊዜ እንዲህ አይነት የሚዲያ ይዘት ለብዙ ሰዓታት የሚከታተሉትን ብቻ እንደሆነና ሳያዘወትሩ ቴሌቪዥን የሚመለከቱት ላይ ያን ያህል ጫና እንደሌለው ማወቅ ያስፈልጋል። ወላጆች ግን ግንዛቤዉ ኖሯቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ህዝቡም በዚህ ጉዳይ ላይ ተገቢው ግንዛቤ እንዲኖረው መደረግ ይኖርበታል። ለዚህም እንዲረዳ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው በህግ ማዕቀፍ ሊታገዝ ይገባል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top