አድባራተ ጥበብ

ቤተ-መዘክር ቅርስ እና ትዝታ

አብዛኛውን የህይወት ዘመኔን በቤተ- መዘክር ሥራ ነው። ቤተ-መዘክር የትዝታ፣ የማስታወሻ ሙያ ቤት ቦታ በመሆኑ ነው፤ ጥሬውን ትርጉም ስናጤነው። መዘክር የሚለው ቃል “ማሰብ እና መቆጠር በልብ ማኖር ባፍ ማውሳት” ተብሎ ነው በኪዳነወልድ መዝገበ ቃላት የተተረጎመው። የደስታ ተክለወልድ መዝገበ-ቃላትም “ዘከረ፣ ዐሰበ፣ አስታወሰ፣ አወሣ; የሚለውን ትርጉም ያቀብለናል። የቀደምቶቹ መዝገበ-ቃላት ቤተ- መዘክር የሚለውን ጽንሰ-ሀሳብ አላካተቱም። ቤተ-መጽሐፍ ወ-መዘክር ተብሎ ሲቋቋም፤ በይዘቱ ቤተ-መዘክርን ያሰበ ይመስላል። ይህ ድርጅትና መዝገበ-ቃላቱ የታተመበት ዘመን ይቀራረባል።

 በቅርቡ የታተመው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማዕከል መዝገበ-ቃላት ለቤተ-መዘክር መነሻ የሚሆን ትርጉም አካፍሎናል። ትርጉሙንም “ጥንታዊ የሆኑ ቅርሶች ተጠብቀው የሚቀመጡበትና በሕዝብ የሚጎበኙበት ቤት” ነው ይለናል። ይህም ማለት ቀደምቶቹ የመዝገበ-ቃላት አዘጋጆች ዛሬ ሙዚየም ተብሎ ከሚጠራው ቃል ጋር ብዙም ዝምድና እንደሌላቸው እንረዳለን። የቅርቡ መዝገበ-ቃላትም ቤተ-መዘክር የጥንቱን ብቻ የሚያመለክት ሆኖ እናገኘዋለን።

 የዓለም-አቀፉ የቤተ-መዘክር ማህበር ከ1946 ጀምሮ የቤተ-መዘክርን ትንታኔ በየጊዜው ሲያሻሽለው እና አንዳድ ጭብጦችንም ሲጨምር እንደነበር ታውቋል። በቅርቡ በብራዚል በተደረገ ስብሰባ /memory/ ትውስታ፣ የሚለውን ጭብጥ መጨመሩን ስለ ቤተ-መዘክር ከተሳተፍኩበት ዓለም- አቀፍ ስብሰባ ተሳታፊ ሰምቻለሁ። ይህም የሚያመለክተው ቤተ-መዘክር ዓለም-አቀፋዊ ይዘቱ እየሰፋ መምጣቱን እንገነዘባለን።

 በጽሑፍ ያገኘሁት የ2007 በቬና፣ አውስትሪያ በተደረገው ጠቅላላ ስብሰባ ውሳኔ ይህን ይመስል ነበር፡- A museum is a non-profit, permanent institution in the service of society and its development, open to the public, which acquires, conserves, researches, communicates and exhibits the tangibles and intangibles of humanity and its environment for purposes of education, study and enjoyment.

ይህ የቤተ-መዘክር ትንታኔ መነሻነት የሚያስረዳን ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ቋሚ ለሕብረተ-ሰብ አገልግሎት እና እድገት ሲሆን፤ እንደ ጥንቶቹ ለፈለጉት ብቻ ክፍት የሆነ ሳይሆን፤ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ተጨባጭ እና የማይጨበጥ የሆኑትን ቅርሶች የሚሰበስብ፣ የሚያጠና፣ የሚያገናኝ እና ለእይታ የሚያቀርብ ለስብእና እና ተፈጥሮ የሚውል የትምህርት፣ የጥናት እና የመዝናናት ማዕከል መሆኑን ነው።

 ከላይ የጠነሱትን መንደርደሪያ የትርጉም ጽንሰ-ሀሳቦች ይዘን የቅርስ እና የትዝታ ግንኙነቶችን ለመዳሰስ እንሞክር። ቅርስ ስንል ለብዙዎቻችን የሚመጣልን ሀሳብ የጥንት፣ የሩቅ ዘመን ቅሪት ሆኖ ነው። በተጨባጭም ከእኛ ዘመን እና ዕይታ ውጭ የሚሆን ይመስለኛል። በአገራችንም ስለ ቅርስ በወጡ ድንጋጌዎች መሠረት፤ የመጀመሪያው ደንብ ቅርስን ሲተሮጎም ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ያለውን ብቻ የሚያካትት አድርጎ ነበር። በሂደትም የተሻሻለው ትርጉም ይዘቱ ለየት ያለ እና ለሕብረተ-ሰቡ ጥቅም የሚውል ከሆነ፤ የዛሬውም ምርት ቅርስ ሊሆን ይችላል በሚል ይደነግገዋል። ለዚህ ቅርስ የጥንቱንም የዛሬውንም የሚያካትት ነው ካልን ዘንድየ ቅርስ ዓይነቶችንም በጨረፍታ ለማጤን እንሞክር። በእኔ ዕይታ ቅርስ የግለሰብ፣ የማህበረ-ሰብ፣ የአገር እና የዓለም አቀፍ ደረጃ ይኖረዋል። አሁን ወደ ትዝታ ልንሸጋገር ነው። የግለ-ሰቡን ቅርስ ስናወሳ የአያት፣ የእናት፣ የአባት ውርስን ይመለከታል። እንዲሁም ደግሞ በህይወት ዘመናችን ባሳለፍነው ጉዞ ላይ የማንረሳቸው ትውስታዎች እና ንብረቶች ቅርሶቻን ናቸው። የጋብቻ ቀለበቴ ከነጠላነት ወደ ቤተ-ሰብነት ያሸጋገረችን ከፍተኛ ዋጋ ያላት ቅርሴ ናት።

 ይህንኑ ጭብጥ ይዘን ወደ ማህበረ-ሰቡ ስንሸጋገር፤ በአንድ አከባቢ የሚኖሩ ማበረ-ሰቦች በወል ካከናወኑዋቸው ክንዋኔዎች መካከል በውል ከሚያስታውሷቸው ድርጊቶች መካከል የተወሰኑቱ የውል ቅርስ ሆነው ይሸጋገራሉ። በአገር ደረጃ የጥንቱንም ሆነ የአሁኑን ቅርሶች በመለየት ለሕብረተ-ሰቡም የተለየ እውቀት እና ጥቅም የሚሰጠውን የአገር ቅርስ ተብሎ ይመዘገባል። በሂደትም ለዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመጥኑትን በመለየት በዩኒስኮ መሠረት አስፈላጊው ምዝገባ ከተከናወነ በኋላ በዓለም አቀፉ የቅርሶች መዝገብ ይመዘገባል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የመሪውን ደረጃ በመያዝ ዘጠኝ የዓለም ቅርሶች ባለቤት ለመሆን በቅታለች። እስቲ ለትዝብት ያህል ዘጠኙንም የዓለም ቅርሶች በምናባሁ ለመጎብኘት ሞክሩ?… ስንቱን አዳረሳችሁ? ዘጠኙን መጎብኘት ለቻላችሁ ከፍተኛ አድናቆቴ ይድረሳችሁ። ምንም ላልተሳካላችሁ ግን በትዝብት መልክ ከእኔ ጋር እንድትንሸራሸሩ ፈቅጄላችኋለሁ።

 በወፍ በረር መልክ ከሰሜኑ ጫፍ ብንጀምር የሰሜን ተራራ፣ ጎንደር፣ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ሃዳር፣ ጥያ፣ ሐረር፣ ኦሞ እና ኮንሶ ናቸው። በእያንዳንዱ መካነ-ቅርስ የተለያዩ የዘመን፣ የጥበብ እና የማሕበረሰብ አገልግሎቶችን እናጤናለን። እነዚህ መካነ-ቅርሶች እንደ ቤተ-መዘክር ያገለግላሉ። ለተሻለ ግንዛቤ ግን አጠቃላይ ትምህርት ለመስጠት እንዲያመች ዘንድ አነስተኛ መንደርደሪያ የቤተ-መዘክር ክፍል ሊኖራቸው ይችላል።

 በባህል እና በቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም በየክልሉ ባሉት የዘር ቢሮዎች የቅርብ ምዝገባ፣ እንክብካቤ፣ ጥናት እና ምርምር በማካሔድ ለዕውቀት የማንነት ጥያቄን ለማስፋት፣ ለመዝናናት ቅርሶችን በተደራጀ መልኩ ለዕይታ ይቀርባሉ። ይህም ድርጅት ቋሚ ድርጅትን መጠየቁ አይቀርም። ስለዚህም በመነሻነት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታዩትን ቅርሶች በመጀመሪያ ደረጃ የማሰባሰብ እና የማደራጀት ኃላፊነት የመንግሥት ይሆናል ማለት ነው። ሰሙኑን የተመለሰችውን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበችውን የሉሲን ቅሪት አካል በግለሰብም ሆነ በማህበረ-ሰብ ማስተናገድ እና መንከባከብ አስቸጋሪ ይሆናል። በመሆኑም

“ቤተ-መዘክር በግለ-ሰብም ሆነ በህብረተ-ሰብ ማቋቋምይቻላል፤ ይበረታታልም። የቅርስን ስፋት እና ጥልቀትስንረዳ መንግስት ብቻውን የሚወጣው ኃላፊነትአይደለም። የመሰብሰብ ፍላጎት፣ በእኔ አጠራር፣(በምሳሌነትም እንደነ ስብሃት እና አብደላ ሸሪፍ)የመሳሰሉ ግለ-ሰቦች አማካኝነት ብዙ ስብስቦች ወደቅርስነት ሲለወጡ አይተናል”

የግድ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆን አለበት።

ቤተ-መዘክር በግለ-ሰብም ሆነ በህብረተ-ሰብ ማቋቋም ይቻላል፤ ይበረታታልም። የቅርስን ስፋት እና ጥልቀት ስንረዳ መንግስት ብቻውን የሚወጣው ኃላፊነት አይደለም። የመሰብሰብ ፍላጎት፣ በእኔ አጠራር፣ (በምሳሌነትም እንደነ ስብሃት እና አብደላ ሸሪፍ) የመሳሰሉ ግለ- ሰቦች አማካኝነት ብዙ ስብስቦች ወደ ቅርስነት ሲለወጡ አይተናል። በነጠላ ወይም በሌጣነቱ ትርጉም የማይሰጠውን ዕቃ በዘመን ብዛት ያሳየውን ዕድገት በመመዝገብ ተራውን ዕቃ ጠቃሚ ቅርስ ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ነጠላ አዝራ ብዙ ላትናገር ትችላለች። የዛሬ ሃምሳ ዓመት ከተፈጠረች አዝራር ጀምሮ እስከ ዛሬ ያለውን አዝራር ሂደት ከሰበሰብን ግን የአዝራርን ለውጥ እና ዕድገት እንመዘግለን። ይህም ሂደት የምርት መሳሪያ ዕድገት የጥሬ ዕቃ ለውጥ የህብረተ-ሰቡ ፍጆታ እና ስለ ውበት ግንዛቤ እንረዳለን ማለት ነው። ስለዚህም ቅርስ ስንል ትዝታን ባገናዘበ መልኩ የወል ዕውቀት የምንፈጥርበት ሂደትም ምርትም ነው።

 የቤተ-መዘክር አንዱ ዓላማ ትዝታን በተለያየ መልኩ በማደራጀት ቅርስን ይፈጥራል። በቅርሱም ዕይታ አዲስ ትዝታ በመፍጠር ለመጪው ቅርስ መንገድ ይከፍታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top