አድባራተ ጥበብ

በጣይቱ የደመቀች የመድረክ ፈርጥ!

ኪነ-ጥበብ መክሊቷ መሆኑን ገና በልጅነቷ ነው ያወቀችው። አያያዟን ያዩ ሁሉ አደነቋት፤ መንገዱን አሳዩዋት፤ አበረታቷትም። ይህም ምርጥ የሚባሉ የዜማ ግጥሞችን እንድትደርስ፣ በታላላቅ መድረኮች እንድትነግስ፣ በሂደትም በብዙዎች ልብ ውስጥ እንድትሰርፅ አደረጋት። እሷም ብትሆን ይህን ውለታ አልረሳችም። የጥበብ አባቶቿንና እናቶቿን ሁሌም በአድናቆት ታነሳቸዋለች፣ ታወድሳቸዋለች። በፋንታዋም ተከታዮቿን ትደግፋለች፣ ታተጋለች፣ ያላትን ሁሉ ሳትሰስት ትሰጣለች፤ የዛሬዋ እንግዳችን ዓለምፀሐይ ወዳጆ!

ተወዳጇ ተዋናይት ዓለምፀሐይ በበርካታ የመድረክ፣ የቴሌቪዥን፣ የራዲዮና የፊልም ሥራዎች ላይ በመሪነት ተጫውታለች። “የቬኒሱ ነጋዴ”ን፣ “አንድ ጡት”ን፣ “ዋናው ተቆጣጣሪ”ን፣ “ጣይቱ”ን፣ “ማክቤዝ”ን፣ “ሐምሌት”ን፣ “ያልተከፈለ ዕዳ”ን፣ “የደመወዝ ሰሞን”ን ለአብነት ያህል መጥቀስ እንችላለን። “በር”ን፣“ደማችንን፣ጥሩ ናፋቂ ከተውኔት ድርሰቶቿ፤አማቾቹን፣የፌዝ ዶክተርን፣ማክቤዝ ከዝግጅቶቿ ልናነሳ እንችላለን። ሁለት የግጥም መድበሎቿንማረፊያ ያጣች ሕይወትእናየማታ እንጀራ ለህትመት አብቅታለች። ጥላሁን ገሠሠን፣ ማህሙድ አህመድንና ሙሉቀን መለሰን ጨምሮ በበርካታ ድምጻውያን የተዜሙ ግጥሞችን አበርክታለች። ዓለምፀሐይ የኢትዮጵያ የተውኔት ሙያተኞች ማኅበርንም በሊቀመንበርነት መርታለች።

 ዓለምፀሐይ ላለፉት 27 ዓመታት ኑሮዋን በሀገረ አሜሪካ ብታደርግም ከሀገሯና ከሙያዋ ግን አልራቀችም። በህልሟም በእውኗም ከሀገሯ እና ከህዝቧ ጋር ነች። በስደት ዓለም ሊታሰብ የማይቻለውን ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከልን በማቋቋም የጥበብ ሰዎች መሰባሰቢያ ታዛ ሆናለች። ማዕከሉ ምን ሰራ? የሚለውንና ከሱ ጋራ ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎችን በሚቀጥለው ዕትም የምናቀርብ ሆኖ፤ ለዛሬው በሀገሯ ስለተደረገላት አቀባበልና ስለ ሥራዎቿ ጥቂት ታወጋናለች።

ታዛ፡- ዓለም እንኳን በደህና መጣሽ! በአካል ወደ ሀገርሽ ስትመጭ ምን ተሰማሽ? ማለት ቀላል ጥያቄ ይሆን? የጥበብ ቤተሰቦችሽን አቀባበልስ እንዴት አየሽው?

 ዓለምፀሐይ፡- ቀላል አይደለም። ስገባ ከአውሮፕላን ጣቢያው ጀምሮ የነበረው አቀባበል እጅግ በጣም ስሜቴን የነካ ነበር። ምክንያቱም ያስተማሩኝ፣ ያሳደጉኝ፣ በሙያ ህይወቴ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በብሔራዊ ቴያትር ቅጥር ግቢና ከዚያም በፊት በነበረው ህይወቴ ውስጥ የነበሩ የጥበብ አባቶቼን አግኝቻለሁ። እንደነ ጋሽ ተስፋዬ አበበ፣ ጋሽ ጌታቸው ደባልቄ፣ ጋሽ መርዓዊ ስጦት፣ ደቤም (ከያኒ ደበበ እሸቱ) ሌሎችም ተቀብለውኛል። ወዲህ ደግሞ መለስ ብዬ ሳየው እኔ የፈጠርኩት ወይም እኔ ባዘጋጀሁት ወይም በኔ ድርሰት ውስጥ የተሳተፈ ወጣት አካል የምለው በአቀባበሉ ውስጥ ነበረበት። እንደነ ሙሉዓለም ታደሰና ቴዎድሮስ ተስፋዬ ያሉ ባለሙያዎች ነበሩበት። ሌላው ደግሞ ጭራሽ በመድረክም ላይ ገጥመውኝ የማያውቁ በስምና በሥራዬ ብቻ አድንቀውኝ የመጡ እንደነ ግሩም ኤርምያስ አይነት ተዋንያን፣ ሌሎችም በ”ሰው ለሰው” የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሲጫወቱ የማውቃቸው ተዋንያን ነበሩበት። ከዚያ ውጪ እንደዜግነቴ ኢትዮጵያዊው ወጣትና ተሰባስቦ የነበረው ሌላው ህዝብ የፈጠረብኝ ስሜት ለእኔ መቼም ቀላል አይደለም። በጣም ርቦህ የምትወደውን ምግብ አግኝተህ መብላትና መጥገብ አይነት ስሜትም አለበት። የመርካትና የደስታዬን መጠን ማጣት፤ ለእንባ ዳርጎኛል። በህይወቴ ውስጥ በርካታ የሀዘንም የስደትም እንባ አንብቻለሁ። ይህኛው ግን የደስታ እንባዬን በጣም ያገነነው ሆኗል። ከቤቴም ስገባ (ብሔራዊ ቴያትር) የተጫወትኩት፣ ያዘጋጀሁትና የጻፍኩትን ቴያትር ነው መድረኩ ላይ ያየሁት። ከአራት ዓመት ጀምሮ ያሳደግኳቸው የህጻናት አምባ ልጆች ራሳቸውን ችለው፣ ስራ ይዘው፣ አግብተው፣ ወልደው ያገኘሁበት ግቢ ነው ብሔራዊ ቴያትር። ይህን ሁሉ ላቀነባበሩልኝ የኮሚቴ አባላትና ባለሙያዎች መቼም የምስጋና ቃል የለኝም። አንተ፣ ተክሌ ደስታና አዩብርሃን ትዕዛዙ ከአሜሪካ፣ ተስፋዬ ገብረሃና ከአውስትራሊያ አብራችሁኝ መምጣታችሁ የፈጠረብኝን ስሜት እኔ ነኝ የማውቀው። መወለዳቸውን የማላቅ ዘመዶቼ ከጅማ፣ ከናዝሬት፣ ከደብረዘይት መጥተው አይቻቸዋለሁ። በአያቶቼም በሌሎችም የተዋለዱ ናቸው። እንግዲህ ይህን ሁሉ አይቼ ነው ትልቅ ደስታ የተሰማኝ። ነገር ግን ያጣኋቸው ነገሮችም እንደነበሩ ተሰምቶኛል። እንደከያኒ እውቀቴን ልሰጥና ልወስድም ላድግም የምችልበት ዕድል አምልጦኛል። አገር ውስጥ ስትሆን የምታየው፤ ቀጥታ የሚሰማህ ስሜት ትኩሳቱ፣ ደስታም ሆነ ሀዘን፣ ያሳድገኝ ነበር በጥበብ። የበለጠ ያሰሩኝ ነበር ብዬ የማስባቸውን ነገሮችም አጥቼበታለሁ። እኔም ላካፍል እችል የነበረውን ጥበባዊ አቅሜን ሳላካፍል ወይም ሳላስተላልፈው ቀርቼ በስደት ዓለም ለሌሎች ወጣቶች፣ ለሌሎች ሰዎች ሳውለው ወይም በሌላ ባልረባ ክርክር ውስጥ ያፈሰስኩት ጉልበት ሳያስቆጨኝ አልቀረም። እንደሰው ደግሞ የጎደለብኝ ነገር ብዬ የማስበው የቤተሰቦቼን ሀዘን አልተካፈልኩም፣ ቤተሰቦችን በወግ አስታምሜ አልቀበርኩም። የልጅ ልጅም ሲወለድ አብሬያቸው አልነበርኩም። ሰርጋቸውን አልበላሁም። ልደታቸውን አልተካፈልኩም። ከዚያ ሌላ ወደዚህ ልመጣ ስል አንድ በጣም የገረመኝ ሁኔታ አለ።

 ታዛ፡- ምንድነው እሱ?

 ዓለምፀሐይ፡- አንዳንዴ ከልጆቼ ጋር ለእረፍት ወደ አውሮፓ ወይም እዚያው አሜሪካ ውስጥ ስሄድ ጭንቅ ብሎኝ ለልብሴም ዝግጅት ሦስት ቀን ነው የምንቆየው፣ ይሄም ያስፈልገናል፣ ምግባችን ይሄ መሆን አለበት፣ የምናርፍበት ሆቴል እዚህ ነው የሚል ጭንቀት አለ። ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ልመጣ ስል ጭንቀቴን ለሌላው ወረወርኩት መሰለኝ ውስጤ ምንም ጭንቀት አልነበረም። ይህ ስሜት ራሴን ነው የገረመኝ። የሚቀበለኝ ላይ ልጣለው፣ ደስታዬ አይሎ ያ ችግር ይጥፋ አላውቅም። ከልብሴ፣ ከመኝታዬ፣ ከአመጋገቤ ጋር ተያይዞ ምንም ሀሳብ የለብኝም። የደከሙ እነማን አሉ፣ እነማንን አያለሁ የሚል ማስታወሻ ከመያዜ በስተቀር። ከሙያተኞች ያጣናቸውንና በህይወት ካሉት ደግሞ እነማንን ማየት እችላለሁ ከማለት፣ ከቤተሰቦቼ ለእነማን ቅድሚያ መስጠት አለብኝ ከማለት በቀር፣ ጭንቀቱ ውስጤ አልነበረም። ሌላው ስለኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ የምስጋና ቃል ያጥረኛል። ለተደረገልኝ ነገር፣ ለተሰጠኝ ፍቅር፣ የተሰማኝን ለመግለፅ አልችልም። እግዚአብሔር ያክብርልኝ ከማለት በቀር።

ታዛ፡- ከአዲስ አበባ ውጪስ የጥበብ ታዳሚዎችን አግኝተሻል?

 ዓለምፀሐይ፡- አዎ! በመሰረቱ ስመጣም ከመንግስት ጋር የነበረኝ ውይይትና ንግግር ወደ መድረኩና ወደ ጥበብ ሰዎች እንደማተኩር፣ የእኔ ፍላጎቴ ያን አይነት ስለነበረ ያደረግኩትም ያሳለፍኩትም አብዛኛውን ነገር በጉብኝቴም ቢሆን ትኩረቴ በዚያው አካባቢ ነው። ጎጃምም፣ ጎንደርም የባህልና የጥበብ ሰዎችን ሰብስቦ በማነጋገር ነው የጀመርኩት። በሙሉ ዓለም የባህል ማዕከልና በጎንደር የባህል አዳራሽ በጥበቡ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ከአርቲስቶቹ ጋር በነበረው ውይይት ተረድቻለሁ። ወደፊት በምን ሁኔታ ችግሮቹ እንደሚቀረፉ ተወያይተናል። ሌላው በበርካታ ቦታዎች የተደረገልኝ የጥበብ መስተንግዶ ነው። በራስ ሆቴል ግጥም በጃዝ፣ በሰምና ወርቅ የግጥም ምሽትና ግጥም በመሰንቆ ፕሮግራም ታድሜያለሁ። ጎጃም ውስጥ በቅኔ ትምህርት ቤቶች ተገኝቻለሁ። ገዳማትን ጎብኝቻለሁ። በመሳፍንት ቤት ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅት ተደርጎልኝ ነበረ። በፈንድቃ የጃዝ ሙዚቃ ቡድንና በነ አበጋዝ ክብረወርቅ የሙዚቃ ቡድን ፕሮግራሞች ተገኝቼ ነፍሴን አስደስቻለሁ። በእግረመንገድም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጥበብ ደረጃ የት ላይ ነች የሚለውን ለመገንዘብ ችያለሁ። ጎበዝ፣ አንበሳ አንበሳ የሆኑ ወጣት ጸሐፊያን፣ ወጣት ተዋንያን፣ ወጣት አዘጋጆች፣ ወጣት ሰዓሊያን፣ ወጣት ፕሮዲዩሰሮችን ተዋውቄያለሁ። ይህንን ከሀገሬ ውጭም ሆኜ እከታተለው፣ አየው ስለነበር በስም በዝናም ቢሆን አውቃቸው ስለነበር የተገነዘብኩት ነገር አለ። ሆኖም በተሰሩት ህንጻዎች፣ በተደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ፣ በተደረገው የመንገድ ግንባታና የመኪና የውበት መጠን ሰዎች ላይ ያልሰራናቸው ስራዎች አሉ ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ችግር እየፈጠሩ ነው ያለው። እና ዝቅተኛ ግንዛቤዎች የማይባቸው ሁኔታዎች አሳዝነውኛል። በጥበቡ ዘርፍ የምደሰትበትና የማደንቅበት ደረጃን ሳስብ የነ ፈንድቃንና የነ አበጋዝን የሙዚቃ ሥራዎች ሳይ ልዩ አይነት ደስታ ነው የተሰማኝ።

በተለይ የፈንድቃው ለመጀመሪያ ጊዜ ስላየሁት እንደሆነ አላውቅም፣ ቴክኖሎጂውን ከባህል እድገት ጋር አብሮ አያይዞ ዋሽንትና መሰንቆው፣ ውዝዋዜው ያስደስታል። ይህም ይሰራል ወይ? እስክል ድረስ ተደምሜያለሁ።

 ታዛ፡-ሌላስ የታዘብሽው ነገር አለ?

 ዓለምፀሐይ፡- አለ! በአንዳንዶቹ በኩል ከተዋንያኑ የግል ችግሮች ጀምሮ በጥበብ ላይ የደረሱ በደሎችን ተገንዝቤያለሁ። በሴት ተዋንያት የሰውነት ቅርጽና ውበት ላይ ተመስርቶ የሚደረገው ካስቲንግ (የሚና ድልድል)፣ ሴቶች ሲወልዱ ከመድረክ የሚወገዱበትና ከትርኢት የሚገለሉበት ሁኔታ፣ በግል ፍቅርና ግንኙነት የመስራት ነገር ጥሩ አይደለም፤ ይህ በገንዘብ ከሚደረገው ሙስና አያንስም። ያንን አይነት የባህል ዝቅጠት ማየቴ አሳፍሮኛል። ጥበቡም ቢሆን መንገዱን ይዞ በሚገባው ደረጃ ለማደግ ያልቻለው በሀያሲያን አለመኖር ነው። እኔ ባደግኩበት ጊዜ ከነጋሽ ጸጋዬ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ሳህሉ አሰፋ ጀምሮ የምንፈራቸው የሙያ አጋዦቻችን፣ ቆንጣጮቻችን ነበሩ። “አሁን ይህን ሰራሁ ብላ ነው?” በማለት ይገስጹናል። ጥሩም ብንሰራ እንዳንኮፈስ ይነግሩናል። በጋዜጠኝነትም የሄድክ እንደሆነ የሚፈሩ፣ ያለ ይሉኝታ በመጽሔትና በጋዜጣ ይወቅሱን የነበሩ እነ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ማዕረጉ በዛብህ፣ ጳውሎስ ኞኞ ነበሩ። የሃያሲው ጉልበት ከጥበቡ የበለጠ እንጂ ያላነሰ ስለነበረ ደራሲው ተጠንቅቆ ነበር የሚጽፈው። አዘጋጁም እንደዚያው። ያኔ ጥሩ ደረጃ የነበረው ለዚያ ይመስለኛል። ዛሬ ሃያሲው አብረኸው ስላመሸህና ስለጠጣህ ጥሩ ነገር የሚጽፍልህ ከሆነ፣ ጋዜጠኛው ስለ ጠላህና ስላኮረፈህ የሚያወግዝህ ከሆነ፣ የጥበብ መንገድ በዚያ ደረጃ ነው የሚቀረው። እሱን ነገር አይቻለሁ፣ አስተውያለሁ። ለሀገር ለወገን የሚውሉ ጥበቦችን ለማሳደግ፣ የሰው አስተሳሰብ ላይ ለመስራት ዋናው ሚዲያ ነው ሀላፊነት ያለው። ያ አስተሳሰብ ለምን አልተቀረጸም ስትል በትርጉም ላይ ማተኮር፣ የሳንሱር ወይ የመንግስት ችግር ይኖራል። በየዘመኑ። በእኛም ጊዜ ነበር። ግን በዚያም ችግር ስር ጋሽ ጸጋዬ እንደሚለው “ከያኒና የጥበብ ሰው ጪስ ነው፤ መውጫ አያጣም” ነው። ቀዳዳዎችን ፈልጎም ቢሆን ቢያንስ ፖለቲካውን ባይነካ በማህበራዊ አስተሳሰቦች ላይ ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮች እንደነበሩ እገምታለሁ። አንድ ሃኪም ተጠያቂነት ሳይኖረው በሽተኞች ከሞቱ እዚያ ላይ መስራት ከፖለቲካ ጋር ላይገናኝ ይችላል። ያን የኃላፊነትን የተጠያቂነትን ስራ እንኳን የሚቀርጽ ነገር አለመኖሩ ትንሽ ያሳስባል፣ ያሳዝናል። እሱ ተሰምቶኛል። ሌላው በቴያትርና በሲኒማ ጥበብ ውስጥ ያለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ግንዛቤው በበቂ ታውቋል ወይ? የሚል ስጋት አድሮብኛል። ለምን ቴያትር ቤቶች ወድቀው ደክመው አግኝቻቸዋለሁ።

–>
ዓለም ከአንጋፋዋ ተዋናይት አስካለ አመነሸዋ ጋር

“በዕድሜና በጤና ችግር ቤት የዋሉ እንደነ አርቲስት እትዬ አስካለ አመነሸዋና ከያኒ ጀምበሬ በላይ ያሉ ባለሙያዎችንም ጠይቄያለሁ። በሞት የተለዩ የሙያ ባልደረቦቼን የሲራክ ታደሰ፣ የዓለሙ ገ/አብና የፈቃዱ ተ/ማርያም ቤተሰቦች ዘንድ ሄጃለሁ። አልጋ ላይ የዋሉ ዘመዶቼንም እንዲሁ ተዘዋውሬ አይቻለሁ”

ታዛ፡- ምክንያቱ ምን ይመስልሻል?

ዓለምፀሐይ፡– በእኛ ጊዜ ቴያትሮች ክብር ነበራቸው። በሌሎች ሀገሮች ደግሞ ክብራቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ አንዲት የፊልም ተዋናይት ለትወና ስትመለመል በጣም ትጨነቃለች፤ ብቃቷን ሳትተማመን ወደ ውድድር አትመጣም፤ ያም ሆኖ ያስጨንቃታል። “በበቂ እጫወተዋለሁ ወይ? በሼክስፒር ቴያትር ላይ ልቀርብ ነው! ብሮድዌይ ልሄድ ነው!” በማለት ክብር አድርጋው ነው የምታወራው። ምክንያቱም ከትንፋሽህ ጀምሮ ከህዝብ ጋር የምትገናኝበት ፈተና ነው። አሜሪካኖች በቴክኖሎጂ የሚታገዘው የሲኒማ ጥበባቸው የገንዘብ አቅም ደረጃ ኃይለኛ ነው። ሀብታም ድርጅቶች አሉ። ለምሳሌ ሆሊውድ ሀብታም ነው። በስራ ደረጃው ግን ከቴያትር ጋር አይወዳደርም። ያ ደግሞ በአሜሪካ ስለታወቀ በደንብ በእርዳታና በድጋፍ እንዲኖር፣ እንዲከበርና እንዲቆይ ነው የሚደረገው። ሀብታሞችም ሆነ መንግስት ገንዘብ የሚሰጡበት ምክንያት የቴያትር ጥበብ ትልቅነቱ፣ ክብደቱና ወደህዝቡ የሚያስተላልፈው መልዕክት ጉልበቱም ስለታወቀ ነው። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ከሲኒማው ጥበብ የሚገኘው ብር ተፈለገና ቴያትር ጉልበት እንዳይኖረው ሆነ። ስለዚህ ተዋናዩም አይሰራበትም፣ አዘጋጆችም ወደዚያ አያደሉም። የገንዘብ አቅም እንደሌለውም ታወቀ። በዚህ ምክንያት የጥበብ ጉልበቱ ተረሳ ማለት ነው። ይኸ ነገር መታረም አለበት። መንግስትም፣ ቴአትር ቤቶቹን በኃላፊነት የሚመሩት ሰዎችም፣ የቴአትር ባለሙያዎችም አበክረው ሊመክሩበት ይገባል።


 ዓለምና ተስፋዬ ገ/ሃና በብሔራዊ ቴያትር እንደ እቴጌ ጣይቱና አጼ ምኒልክ ሲተውኑ

 ታዛ፡– በቆይታሽ ሌላ ያከናወንሽው ነገር አለ?

ዓለምፀሐይ፡- የበዓታን ቤተክርስቲያን፣ የአጼ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱን የእንጦጦ ቤተመንግስት፣ የልብ ህሙማንን ማዕከል፣ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማእከልን ጎብኝቻለሁ። ብቻ ምን ልበልህ በነበረችኝ የአንድ ወር ገደማ የተቻለኝን ያህል ለመንቀሳቀስ ሞክሪያለሁ። በዕድሜና በጤና ችግር ቤት የዋሉ እንደነ አርቲስት እትዬ አስካለ አመነሸዋና ከያኒ ጀምበሬ በላይ ያሉ ባለሙያዎችንም ጠይቄያለሁ። በሞት የተለዩ የሙያ ባልደረቦቼን የሲራክ ታደሰ፣ የዓለሙ ገ/አብና የፈቃዱ ተ/ማርያም ቤተሰቦች ዘንድ ሄጃለሁ። አልጋ ላይ የዋሉ ዘመዶቼንም እንዲሁ ተዘዋውሬ አይቻለሁ።

ታዛ፡- በሕይወቴ ውስጥ አሉ ከምትያቸው ፀሐፊያነ-ተውኔት፣ አዘጋጆችና ተዋንያን ሶስት ሶስት ጥቀሽ ብልሽ እነማንን ታነሺልኛለሽ?

 ዓለምፀሐይ፡– እጅግ ብዙ ናቸው። ብቻ ሶስት ሶስቱን ለምሳሌ ያህል ብትጠቅሽልኝ ስላልከኝ፣ ከላይ የማስቀምጣቸው ወይም እንደምሳሌ ሁልጊዜ የማነሳቸው በፀሐፌ ተውኔቶች በኩል እኔ ከጀመርኩበት ከመላኩ አሻግሬ ነው መነሳት የምፈልገው። ብዙ ሰው ያላወራለት ግን ድንቅ የሆነ የቴያትርን ባህሪያት በማወቅና በመገንዘብ፣ ጥበብን ሲጠበብ ኖሮ ያለፈ ሰው ነው። ሀገርንም በሚመለከት እንደነ “ማሪኝ”፣ “ሽፍንፍን”፣ “ዓለም ጊዜና ገንዘብ”ን የመሳሰሉ ቴያትሮችን የደረሰ ነው። እውነት ለመናገር በዚያን ጊዜ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ጉቦኞችን ይጋፋ ይታገልበት የነበረው የባህሪ አወጣጥና አቀራረጹ ድንቅ ነበረ። ከአስራ አምስት በላይ የሆኑ ድርሰቶችን የጻፈ ጎበዝ ሰው ስለነበር ከእርሱ መጀመር እፈልጋለሁ። ከዚያ ሌላ ጋሽ ጸጋዬ ገብረመድህን ነው። ጋሽ ጸጋዬ አጻጻፉ ለደካማ ተዋንያን ጉልበት የሚሰጥ፤ አንበሳ የሚያደርግ ነው። ከዚያ ውጪ በየደረጃው ያሉ ጉቦኞችን፣ የመንግስት አሰራርን ድክመቶች ይተቻል። በማህበራዊም ይሁን በፖለቲካ ያሉትን እየነቀሰ ሲሟገት የነበረ፣ ቋንቋችንን ያበለጸገ፣ ያሰፋ፣ ሲመቸው በአማርኛ፣ ሲመቸው በግዕዙ፣ ሲመቸው በኦሮምኛ ጭምር ቃላትን እያመሰጠረ ተደራሲ እንዲዝናና ያደርግም ነበር። ለምሳሌ “ማክቤዝ” ላይ ያሉትን የመናፍስት ባህሪያት በኢትዮጵያ ድቤ መቺዎችና ቃልቻዎች አጨዋወት አይነት ሼክስፒርን ኢትዮጵያዊ አድርጎ ያቀረበበት ትልቅ ጉልበት ስለነበረው ነው። ስለዚህ የማከብረው ሰው ነው። ከዚያ ሌላ ጋሽ መንግስቱ ለማ ናቸው። መንግስቱ ለማ ለእኔ በጣም በቀለለ፣ በጣም የራሳችን በሆነ ቋንቋ፣ የራሳችን በሆኑ ሰዎች ባህሪያት አጠገባችን ባሉ ጎረቤቶችና አያቶች የራሳችንን እናቶችና አባቶች በቀለለ ባህሪ፤ ግን ደግሞ በሚጣፍጥ ቋንቋ አድርገው ብዙ ቴያትሮችንና ጽሑፎችን የሰሩ ሰው ነበሩ። እንግዲህ ሶስቱ ለእኔ በመጀመሪያ በህይወቴ ውስጥ ዕድልም አግኝቼ ያየኋቸውና ያወቅኋቸው ናቸው።

 ታዛ፡-በአዘጋጅነት ደረጃ ስሜትሽን የሚገዙት?

 ዓለምፀሐይ፡- ጋሽ ሳህሉ አሰፋ በጣም ልዩ ሰው ነበር። የተማረው ግሪክ አገር ነው። ማስተርሱን የያዘው። በአዘጋጅነት “የቬነሱ ነጋዴ” ላይ አብሬው ለመስራት እድሉን አግኝቻለሁ። እሱም እንደዚሁ ዕይታው ሰፋ ያለ ነው። ከፍ ያለ ደረጃ የነበረው አዘጋጅ ነበር። ከዚያ በተረፈ ስብሃት ተሰማ ወጣት አዘጋጅ ነበር። ከራሺያ ነው ተምሮ የመጣው። በዝግጅት ዓለም ውስጥ ቴያትሮችን ስጫወት የተለየ ልምድ ያጋጠመኝ ከስብሃት ነው። እኔ መቼም በዚያን ዘመን አብሬው ያልሰራሁት አዘጋጅ አልነበረም። ጋሽ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ጋሽ አባተ መኩሪያ፣ ደበበ እሸቱ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ሃይማኖት ዓለሙ፣ ጸጋዬ ገብረመድህን…።

ታዛ፡- ስብሀትን በልዩነት ያስቀመጥሽው እንዴት ነው?

 ዓለምፀሐይ፡- የስብሃትን ምንድነው ልዩ የሚያደርግብኝ፤ ስብሃት ጠጅ ቤት ይወስደንና እዚያ ያሉ ባህሪያትን ያስጠናናል። ጠላ ቤት፣ አረቄ ቤት አይቀረውም፤ መንገድ ላይ ያሉ የአእምሮ ህሙማንን ጭምር በደምብ እንድናስተውላቸው ያደርገናል። እሱ ባሳየኝ “ሐምሌት” ላይ የወፌይላን ባህሪይ ለመጫወት እንድችል ረድቶኛል። ባህሪያትን እንድዳስስ እንድጨብጥ ያደረገኝ ሰው ነበር። ሌላው “ዋና ተቆጣጣሪን”ና አንድ የቼኾብን ድርሰት ሲያዘጋጅ አብሬው ሰርቻለሁ። ያኔ ራሺያን ይጽፍ እንደሆነ እሱ ደግሞ አግንኖ እስከ መቶ ተዋንያን ሊሳተፉ የቻሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል። መድረክ ላይ። ዜማን፣ ስዕልን፣ የመድረክ ቅርጽንና ትወናን አንድ ላይ አዋህዶ ጉልበት የመስጠት ችሎታ አለው። አሁን “ሀሁ”ን ሰው እንደዚያ የሚንጫጫበት ኮረሱ አለ፣ የመድረክ እነጻው ሌላ ነው። መቆሸሹንም እንዳለ መድረኩ ላይ ያቀርበዋል። እና ይሄ ይሄ የጋሽ አባተ የአዘገጃጀት ጥበብና ስልት ነው። “ቴዎድሮስ”ንም “እናት አለም ጠኑ”ንም “ሊስትሮ ኦፔራ”ንም ሌሎቹም ላይ ሳየው ያ ጉልበት አለው ጋሽ አባተ። ስለዚህ ለእነዚህ ለሶስቱ የጥበብ ባለውለታዎች ቅድሚያውን እሰጣለሁ።

 ታዛ፡- በትወናው በኩልስ?

ዓለምፀሐይ፡- እንደተዋናይ በትወና ደረጃ እድለኛ ሆኜ ሀገር ፍቅርም፣ ብሔራዊ ቴያትርም፣ ማዘጋጃ ቤት ከነበሩትም ተዋንያን ጋር ገና ከልጅነቴ ጀምሮ አብሬ ስለሰራሁ ከብዙዎቹ ጋር ቅርበት አለኝ። ብዙዎቹ ይህንን ሙያ በትንሽ ክፍያና በብዙ ስቃይ በዚያ ላይ ለቡድን ስራ የተመቸች ነበረች።

በትወና የቡድን ስራ ወሳኝነት አለው። እትዬ አስናቀች ከወጣቶች ጋር የመግባባት፣ ከአንጋፋዎቹ ጋር አብሮ የመስራት፣ አዲስ የመጣን አዘጋጅ የመቀበል፣ አዳዲስ ጸሐፌ ተውኔቶችን አክብሮ የመስማት ተፈጥሮዋ የሚደነቅ ነው። ከዚያ ሌላ የእኔ አባቴም፣ አስተማሪዬም፣ ወንድሜም፣ በትከሻው ደግሞ ይዞ መድረክ ላይ ያነገሰኝ ወጋየሁ ንጋቱ ነው። ወጋየሁ ብቻውን የሚነግስ ሳይሆን፤ በአካባቢው ያሉትን ተዋንያን ጭምር ይዞ የሚነሳ ሰው ነው። ደግሞ እሱ ብቻ ሊገዝፍ የማይፈልግ ልዩ ሰው ነው ወጋየሁ። እና አንተ እርግጠኛውን ባህሪ እስክትይዝ ድረስ አብሮህ ይቀጠቅጣል፤ ላንተም ባህሪ ያስባል። ተሸክሞህ ነው የሚያነግስህ።

ታዛ፡- እንደዜማ ግጥም ደራሲነትሽ የሰጠሻቸውን ግጥም አሳምረው የተጫወቱልሽን ዋና ዋና ድምጻውያን ብትጠቀሽልን?

ዓለምፀሐይ፡- ሁሌም እንደምለው በአማርኛ ቋንቋ እውቀት፣ የቱ ቃል መነሳት የቱ ቃል መውደቅ እንዳለበት በመገንዘብ፣ በሙዚቃ ቅንብር (አሬንጅመንት) ውስጥ ትልቅ ሚና በመጫወትና ሙዚቃው ቋንቋ ውስጥ ገብቶ በመስራት፣ ዜማዎቻቸውንና ሜሎዲዎቻቸውን በመምረጥ፣ በዚያ ደረጃ ሙሉቀን መለሰ ትልቅ ነገር ስላለው ነው ሙሉቀን ሙሉቀን የምለው። ምክንያቱም እሱ እነዚህን ነገሮች ያደርጋል። የሙዚቃ ቅንብር ውስጥ ይገባል። ሜሎዲዎቹ ላይ ተጠንቅቆ ነው የሚመርጠው። ግጥሞቹም ላይ እንደዛ ነው። ቋንቋ ያውቃል። ሙሉቀን ላይ የማያቸው ጉልበቶች እነዚህ ስለሆኑ ነው። ጥላሁንን ተመልከተው። ጥላሁን ገሰሰ በተጫወታቸው ዘፈኖች ውስጥ ያሉ ግጥሞችን ጽፈን እናንብባቸው ብንል ደካማ የሆኑ ብዙ ግጥሞች አሉ። እሱ ስለዘፈናቸው ብቻ “ፓ” ብለን ተደንቀን የምንወዳቸው አሉ። ለምን? ቅላጼ ያበጅላቸዋል። በዜማዎች መካከል የሚሰራቸው ነገሮች አሉ። ሌላ ዘፋኝ ቢዘፍናቸው ሊወድቁ የሚችሉ ዜማዎች በጥላሁን ጉልበት ሲነሱ ታያለህ። እሱ ስለዘፈናቸው ብቻ። በዚህ ጥላሁን ድንቅ ነው። ማህሙድም ይኸው ጉልበት አለው። ማህሙድም የድምጽ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ የድምጽ ሃይል፣ ጉልበት ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ችሎታም አለው። ለዚህ ነው እነዚህ ዘፋኞች ከሌሎቹ የተሻለ በትውልዶች ውስጥ የሚሸጋገሩ ስራዎችን የሰሩበት ምክንያት።

ታዛ፡- እስኪ ከትራስሽ አጠገብ ከማይጠፉ መጻሕፍት ሶስቱን ንገሪን?

 ዓለምፀሐይ፡- አንደኛው “መጽሐፍ ቅዱስ” ነው። ሁለተኛው “እሳት ወይ አበባ” ነው። ሦስተኛው “Eat Pray Love” የተሰኘ የኤልዛቤት ጊልበርት ስራ ነው። ለነገሩ አጠገ ከ20 በላይ መጻሕፍት አይጠፉም። ሌሎችም አሉ ደጋግሜ እያነሳሁ የማነባቸው። የግጥም መጻሕፍት፣ የተወሰኑ ልብ ወለዶች።

ታዛ፡- እቴጌ ጣይቱን ከመቼ ጀምሮ ነው የወደድሻት?

ዓለምፀሐይ፡- ጆን ባርነስ የሚባል የአሜሪካ ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የክሪስ ፕራውቲን መጽሐፍ ይዞልኝ መጥቶ “አንቺ ይህቺን ባህሪ መድረክ ላይ ስትጫወቺ ማየት እፈልጋለሁ” ብሎ ይሰጠኛል። ይህ ሰው በጣም ወዳጄ ነበር። ስለ እቴጌ ጣይቱ የአጼ ምኒልክ ሚስት ከመሆናቸው ባሻገር የማውቀው ነገር አልነበረኝም። ያን መጽሐፍ እስካነበብኩበት ጊዜ ድረስ። በ1981 ዓ.ም አካባቢ ነው። እና መጽሐፉን ሳነብ የማላውቀውን ብዙ ነገሮች አወኩ። የጣይቱን ጉልበት፣ የጣይቱን ወታደርነት፣ የጣይቱን ገጣሚነት፣ የጣይቱን ዜመኝነት፣ ምን ልበልህ? ደነገጥኩኝ። እቴጌ ጣይቱ ይህን ሁሉ ናቸው እንዴ? እስክል። የሚያሳዝነው “ውጫሌ 17” የተሰኘ ተውኔት ወደ ብሔራዊ ቴያትር መጥቶ እንድጫወታት ተመድቤ ነበር፤ ሆኖም አርብ ዕለት ስክሪፕቱ ተሰጥቶኝ ሰኞ አገሬን ለቀቄ ወጣሁ። የሚገርምህ ክሪስ ፕራውቲን ደግሞ በስደት ዓለም አፈላልጌ አገኘኋት …

 ታዛ፡- ደራሲዋን?

ዓለምፀሐይ፡- አዎ! አገኘኋት ደራሲዋን። “ምን አስበሽ ነው? በምን ፈለግሽው ይህን ነገር” ብየ ጠየቅኳት፤ “ባሌ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ ቤት ይሰራ ስለነበር ወደ ኢትዮጵያ ሲመደብ “የምንሄድበትን አገር ታውቀዋለህ ወይ?” ስለው “ኧረ እኔ ምንም አላውቅም” አለኝ። ስለዚህ ስለ ኢትዮጵያ ማንበብ ጀመርኩ። ስጀምር በመስመርና መስመር ውልብ ብላ የምታልፍ የጣይቱን ታሪክ አያለሁ። ይህቺን ሴትዮ ለምንድነው እንደው ውልብ ብላ እንድትቀር አድርገው የጻፏት? ብዬ ስለ እሷ መመራመር ጀመርኩ” አለችኝ። በዚም የተነሳ “Empress Taytu and Menilek II: Ethiopia, 1883- 1910” የተሰኘ ስራዋን ለማሳተም እንደበቃች ነገረችኝ።

 ታዛ፡- እስኪ ከእቴጌ ጣይቱ ፀጋዎች (Legacies) ሶስቱን አጋሪን?

ዓለምፀሐይ፡- ከጣይቱ ጸጋዎች ውስጥ የኢትዮጵያን የሉአላዊነት፣ የነጻነት ጥያቄ ማስመዝገቧ አንዱ ነው። ከጠላት ወረራ ያዳነችንና አንገታችን እንዳንደፋ ያደረገችን ጀግናችን ናት። አሁን በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን እንደሌሎቹ የአፍሪካ ወገኖቻችን በጥቁርነታችን የሚሰማን ነገር የለም። በነጮች ስላልተገዛን። ሌላው ዘመናዊ አስተዳደርና ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት ሲጥሩ ስንት ነገስታት አልፈዋል። ጣይቱ ግን በአንኮበር፣ ጎንደር፣ አክሱም ሲዞር የነበረውን መንግስትና አስተዳደር ነው “እስኪ እዚህ ላይ እንከትምና ህዝቡ ወደኛ ይምጣ” ብላ የአዲስ አበባን ከተማ የቆረቆረችው። ከዚያ ሌላ በአነስተኛ ኢንዱስትሪና ሆቴል ማንም ያላሰበውን የልማት መሠረት የጣለች ናት። ሙካሽ ስራው፣ ልብሱ፣ ጌጡ፣ ዕቃው ሁሉ ከውጭ ነበር የሚመጣው። እሷ ግን ዘዴ ፈጠረችና እስኪ አንድ ሰው ላክልኝና የእኔን አገር ሰው ያሰልጥንልኝ አለች። የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መሰረት የተጣለው በእሷ አማካይነት ነው። በትምህርትም እንደዚያው ነው። የኢትዮጵያ መሰረታዊ የባህል ትምህርቶች መነሻ መሆን አለባቸው የሚል አቋም ነበራት። ዛሬ የምንጣላበት “ከምዕራብ ስልጣኔ እንውሰድ እያልን አገራችንን አጠፋነው” የምንለውን ነገር እሷ ዘመናዊውን ከመውሰዳችን በፊት ከዚህ እንጀምርና እናገናኘዋለን የሚል አስተሳሰብ ነበራት። እነዚህ አንኳሮቹ ናቸው።

ታዛ፡- እስኪ ፈተነኝ ስለምትይው ቴያትርና ገፀ-ባህሪ ንገሪን?

ዓለምፀሐይ፡- አንዱ የቬነሱ ነጋዴ ነው። ወንድም ሴትም ሆኖ የመጫወት፣ ድምጽንና መልክን የመቀያየር ነገር ስለነበር ያ ለእኔ በጣም ፈታኝ ነበር። “ሀሁ በስድስት ወር” ራሱ ቀላል ባህሪ አልነበረም። ገኔ አምበርብርን ስጫወት ገና ልጅ ነበርኩ። ሚናው ዜማ አለው። እትዬ ጠለላ ከእኔ በፊት ተጫውታው ነበር። እሷ የድምጽ ቅላጼ አላት። እኔ ግን በዘፈን ረገድ ምንም ስራ አልሰራሁም። እና ባህሪዋ ከበድ የሚል ነበር። “ሐምሌት” ላይ እንዲሁ ወፌይላን ስጫወት፣ እብደቷ፣ ሐምሌትን ማፍቀሯ፣ በሌላ በኩል አለማመኗ፣ ከአባቷ ጋር ያላት ንትርክ ተደራርቦ ባህሪዋ ትንሽ ውስብስብ ብሎብኝ ነበር። በስደት ዓለም የተጫወትኳት እመቤት ሆይ ማክቤዝም እንዲሁ ፈትናኛለች።

ታዛ፡– መጀመሪያ ወደ መድረክ የወጣሽበት ቴያትር ማን ነው? ድርሰቱስ የማነው? ዝግጅቱስ?

 ዓለምፀሐይ፡- ጋሼ መላኩ አሻግሬ የጻፈውና ያዘጋጀው “ዓለም ጊዜና ገንዘብ” የተሰኘ ቴያትር ነው። ዓለም የተባለችውን ገጸ-ባህሪ ነበር ያጫወተኝ። ያኔ አስራ ሦስት ዓመቴ ነበር። ዙፋን ላይ ዘውድ የደፋች ሴት አድርጎኝ ተመልካቹ “እምጵጽ፣ እምጵጽ” ይል ነበር፤ እያዘነልኝ። ቀጫጫ ነበርኩ። ድምጼ ግን ደህና ሳይሆን አልቀረም…።

ታዛ፡- ስላዘጋጀሻቸው ቴያትሮች ብትነግሪን?

ዓለምፀሐይ፡- ከዝግጅት ጋር የተዋወቅኩት በ”እናት ዓለም ጠኑ” ሲሆን፤ የሃይማኖት ዓለሙ ረዳት አድርጎ የመደበኝ ጋሽ ጸጋዬ ገ/መድኀን ነበር። ስለ አልባሳት፣ በመድረክ ስለማለማመድ፣ ስለሜክአፕና ስለትወና አሰራር የተማርኩት ያኔ ነበር። ከዚያ “ትግል ነው መፍትሄው” የተሰኘውን በሴቶች ጥያቄ ላይ የሚያተኩር አጭር ተውኔት ጻፍኩና ለማርች 8 ከታደሰ ወርቁ ጋር አዘጋጅተን አቀረብነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀሁት የሙሉ ጊዜ ተውኔት “አማቾቹ” ሲሆን፤ ድርሰቱ የኤፍሬም በቀለ ነው። በአገራችን የመጀመሪያዋ የሴት አዘጋጅም እንደነበርኩ ቆይቼ ነው የተገነዘብኩት። ከሀገር ከወጣሁ ወዲያ የጣይቱ ማዕከል ካቀረባቸው ቴያትሮች አብዛኞቹን እኔ ነኝ ያዘጋጀኋቸው። ከሃያ አምስት የሚያንሱ አይመስለኝም። ከነዚህ መካከል የጋሽ ጸጋዬ የመጨረሻ ድርሰት “ፐፑ ፊደል ማዶ”፣ “ማክቤዝ”፣ “የፌዝ ዶክተር”፣ “ዴሞቴራፒ”፣ “ታሽጓል”፣ “የሞኝ ፍቅር”፣ “ሬሳው”፣ “ሃሜቶሎጂ”፣ “ያልተያዘ”፣ “ህልመኞች”፣ “ፌስቡክ”ና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ሂደት በጽሑፍም ሆነ በዝግጅት ከረዱኝ ባለሙያዎች ተክሌ ደስታ፣ ተስፋዬ ሲማ፣ ተመስገን አፈወርቅ፣ ቴዎድሮስ ለገሰ፣ አበባየሁ ታደሰ፣ ዓለማየሁ ገ/ሕይወት ይገኙበታል። ከሀገር ቤት ከወሰድኳቸው በ”ዴሞቴራፒ” እና በ”የቴዎድሮስ ራዕይ” ደግሞ ጌትነት እንየውም አለበት። የጣይቱ ማዕከል ፍሬ የሆነው መስከረም በቀለ ራሱ፤ ኮሜዲያን ቢሆንም የጻፋቸውን አጫጭር ድራማዎች አብረን ሰርተናል።

“ጋሼ መላኩ አሻግሬ የጻፈውና ያዘጋጀው “ዓለም ጊዜና ገንዘብ” የተሰኘ ቴያትር ነው። ዓለም የተባለችውን ገጸ-ባህሪ ነበር ያጫወተኝ። ያኔ አስራ ሦስት ዓመቴ ነበር። ዙፋን ላይ ዘውድ የደፋች ሴት አድርጎኝ ተመልካቹ “እምጵጽ፣ እምጵጽ” ይል ነበር፤ እያዘነልኝ። ቀጫጫ ነበርኩ። ድምጼ ግን ደህና ሳይሆን አልቀረም”

ታዛ፡- የጻፍሻቸው ተውኔቶችስ?

ዓለምፀሐይ፡- የሙሉ ጊዜ ተውኔት የጻፍኩት “በር”ን ነው። ከዚያ “ደማችን”ን ከስብሃት ተሰማና ከታደሰ ወርቁ ጋር ሆነን ሰርተናል። የዝግጅቱን ክፍል በሙሉ የሰራው ታዴ ነው። ሙዚቃዊ ዳንስ ያለበት ድራማ ነው። የዜማ ግጥም ሲፈልግ እኔን ይጠይቀኛል። ባህሪያቱን በማውጣት ረገድ ከስብሃት ጋር ይሰራል። ባልሳሳት በደርግ ዘመን ለአራተኛው የአብዮት በዓል የታየ ይመስለኛል። “ያልተያዘ” የተሰኘ ተውኔት (ኮሜዲ) ነው። ውጪ ደጋግመን ሰርተነዋል። በእንግሊዝኛ ተተርጉሞም ፊት በሎስ አንጀለስ ፕሮፌሽናል ተዋንያን እንደገናም ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ ጥሩ ሆኖ ተሰርቷል። ሌሎችም “ህልመኞች”፣ “ሁለገብ”፣ “ኑሮ በየቤቱ”፣ “ጥሩ ናፋቂ”ና የመሳሰሉትን ወደ አስራ ሁለት የሚደርሱ ተውኔቶች ጽፌያለሁ። ታዛ፡- የአንቺን ወደ አገር ቤት መመለስ አስመልክቶ በከያኒ ጌትነት እንየው የተጻፈውና የተነበበው ግጥም ምን ስሜት ጫረብሽ? ዓለምፀሐይ፡- በቃላት ከምገልፀው በላይ ነው። እጅግ በጣም ተደስቻለሁ።

ታዛ፡-ዓለም ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ። በሌላ ጉዳይ ተመልሰን እንደምንገናኝ ተስፋ እያደረግኩ ግጥሙን ለአንባቢያን ቀንጨብ አድርገን በመጋበዝ ብንሰነባበትስ?

 ዓለምፀሐይ፡- በደስታ! እግዚአብሔር ያክብርልኝ።

 ታዛ፡- የጌትነት ግጥም በሼክስፒር “ዓለም የቴያትር መድረክ ነች” ላይ ነው የሚነሳው።

 “ አለም-ተውኔት-መድረክ”

 “ መድረክ – አለም – እና – ተውኔት”……

 አንድ የአንቺ እውነት- የአንቺ እምነት፣

 የአንቺ ጥሪ-የአንቺ ህይወት፤….

 ከመድኃኔዓለም ትምህርት ቤት

 ብሔራዊ ቤተ-ተውኔት፤

 ከብሔራዊ ቴአትር ቤት፤ አሜሪካ ስደት ህይወት፤…

 ከልጅነት እስከ እውቀት፣ በጥበብ ኪዳን የታሰረ፣

በሀገሩ መድረክ ነፍስ አውቆ፤ በሀገሩ መድረክ ላይ አድጎ፣ በሀገሩ መድረክ የኖረ፤…

 ጥበቡንና መድረኩን፣ በፍቅር እንደቋጠረ፣

ከሀገሩ ጋር ተሸክሞ፣ ባህር የተሻገረ፣

 በባዕድ ሀገር መሬት ላይ፤

 ባህሉንና ታሪኩን፤

 በጣይቱ አምሳል አቁሞ፣ እናት ሀገሩን ያስከበረ፤…

27 ዓመታት ሙሉ፣ የጥበብ ስንቅ እየቋጠረ፣

በየአለማቱ ጥግ ሲዋትት፤

ተሰዳጅ የሐገሩን ልጆች ፣ “አይዞን -አይዟችሁ” ሲል የኖረ…

የስደት ህይወት ሰቀቀን፤

ያረገበውን የወገን ልብ፤

 በአንድነት-በእምነት -በፍቅር -በተስፋ ያጠነከረ

 በአንድ የሀገር መውደድ ስሜት፡-

 ወገኑን፡- ከዘመን ዘመን፣ በጥበብ ያሸጋገረ፤

27 ዓመታት ሙሉ ከስደት ሕይወት አቀበት፣ እንግልት እየታገለ፣

መድረኩን እንደመስቀሉ፣ ጫንቃው መሸከም የቻለ፣…..

 እንደአንቺ መንፈሰ- ብረት፤

 እንደአንቺ ልበ -ብርሃን፤

 አለም እንደአንቺ ማን አለ!?

 እኮ የት አለ!?… በመንፈስ ልዕልና ልቆ፣ ነፍሱ በፍቅር የተሞላ፣

 ከቶም፡- እምነቱ እማይረግብ፤

 ከቶም፡- ፅናቱ የማይላላ፤…

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top