በላ ልበልሃ

መቋጫ ያጣው የሰንደቅ ዓላማችን ውዝግብና ቀጣዩ ፈተና

“አፄ ኃይለሥላሴ በኦፊሴል ጉብኝቶቻቸውና በተለያዩ ዝግጅቶች ሳይቀር ሁለቱን ባንዲራዎች እየቀያየሩ ሲጠቀሙ በጊዜው በነበሩ ቪዲዮና ፎቶግራፎች ያሳያሉ። እነዚህን እውነታዎች በማስረጃነት ለማረጋገጥ በዩቲዩብ እና ሌሎች ድኅረ-ገፆችም የተጫኑ ምስክር ይሆናሉ።”

 ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) የአንድ አገር ሁለንተናዊ መገለጫ ነው። የክብር እና የሉአላዊነት ምልክት እንዲሁም የቃል ኪዳን አርማም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የየትኛውም ሀገር ህዝብ በሀገሩ ባንዲራ ጥላ ሥር ተመክቶ ይኖራል። እንደሚታወቀው፤ ሰንደቅ ዓላማ በቀጥታ ከቀለማት፣ ከዲዛይን እና ከዓርማ ጋር የተያያዙ ውክልናዎች አሉት። በሰንደቅ ዓላማ ላይ ያሉ ቀለማት ወይንም ዓርማዎች ለውበት ወይንም ለጌጥ የሚደረጉ ሳይሆኑ በሚገባ ታስቦባቸው የሰንደቅ ዓላማውን ባለቤት ፍላጎት ሊገልፁ በሚችሉ መልኩ የሚቀመጡ ናቸው። ከሰንደቅ ዓላማው ቀለማትና አርማ ጀርባ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነትና የመሳሰሉት መገለጫዎችና እሴቶች ያሉ በመሆናቸው የቀለማቱ ወይንም የዓርማው ውክልና እነዚህን ፅንሰ ሀሳቦች በሚገባ አሰናስሎ የያዘ መሆን አለበት።

የዓርማ ጉዳይ

የባንዲራ የቀለማት አጠቃቀምን በተመለከተ አንዳንድ ሀገራት መደበኛ ቀለማትን ብቻ ሲጠቀሙ፤ ሌሎች ደግሞ ከመደበኛ ቀለማቱ ባሻገር የተለያዩ አርማዎችን በባንዲራዎቻቸው ላይ ሲያደርጉ እንመለከታለን። በባንዲራ መደበኛ ቀለማት ላይ ከሚደረጉ ዓርማዎች መካከል በብዛት የሚስተዋሉት ኮከብ፣ ጨረቃ፣ መስቀል፣ ጋሻና ጦር እንደዚሁም የተለያዩ እንስሳትና ዕፅዋት ምስሎች ይገኙበታል።

 በባንዲራቸው ላይ ኮኮብ ወይንም ከዋክብትን ከሚጠቀሙት ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ዚምባቡዌ፣ ጋና፣ ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ ቺሊ፣ኢትዮጵያ፣ እስራኤል ሌሎች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ያሉባቸው አንዳንድ ሀገራት ደግሞ ኮከብን ከግማሽ ጨረቃ ጋር አጣምረው በባንዲራቸው ላይ ሲጠቀሙ ይታያል።

በዚህ በኩል ፓኪስታን፣ ቱርክ፣ አልጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ኡዚቤኪስታንና ሌሎች ሀገራት ሊጠቀሱ ይችላሉ። በባንዲራቸው ላይ መስቀልን ከሚጠቀሙት ሀገራት መካከል ደግሞ ፊንላንድን፣ ዴንማርክን፣ ኖሮዌን፣ ዩናይትድ ኪንግደምን እና ፊጂን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።

ሀገራት በባንዲራቸው መደበኛ ቀለም ላይ የተለያዩ አይነት አርማዎችን የመጠቀማቸውን ያህል፤ ምንም አይነት አርማን የማይጠቀሙ ሀገራትም አሉ። ኮሎምቢያ፣ ቻድ፣ ኮትዲቩዋር፣ ጣሊያን፣ ኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ቤኒን፣ ፈረንሳይ፣ ጊኒ እና ሀንጋሪን፤ የመሳሰሉ ደግሞ አርማ አልባ ልሙጥ ባንዲራን ከሚጠቀሙ ሀገራት ተርታ ይመደባሉ።

 በዓለም የተለያዩ ሀገራት ባንዲራ የረዥም ዘመን ታሪክ አለው። ከመቶ ዓመት በላይ ታሪክ ያለው የሀገራችን ባንዲራም በዘመናት ሂደት ቅርፅ እና ቀለሙን እየቀያየረ ዛሬ ያለበትን ደረጃ ላይ ደርሷል። ከታሪክ እንደምንረዳው አንድ አንድ ሀገራ እንደ ርእዮተ-ዓለማቸው መለዋወጥ ሁሉ፤ ባንዲራቸውንም ሲቀያይሩ ተስተውለዋል። በዚህ ረገድ አሜሪካ ተጠቃሽ ስትሆን፤ የሶሻሊስት ስርዓት አራማጇ ኩባ ግን ሥርዓተ- መንግሥት ቢለዋወጥባትም አንድም ጊዜ ባንዲራዋን ሳትቀይር ፀንታ ኖራለች። ወደ እኛ ሀገር ስንመለስ፤ አነጋጋሪ ሁኔታዎች አሉ።

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን በተመለከተ፤ ባንዲራው አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ በተለያዩ ለውጦች ውስጥ አልፏል። በለውጥ ሂደቶቹ ውስጥ እንደ አሁኑ የከረረ አወዛጋቢ ጉዳዮች መኖራቸውን በታሪክ የተዘገበበት ሁኔታ የለም።

በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የሰንደቅ ዓላማ ዥዋዥዌ

የኢትዮጵያን ባንዲራ አመጣጥ በተመለከተ ሰፊ ትንታኔ ያለው በመሆኑ ጉዳዩን በአጭሩ ለመመልከት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት መጀመሩ ነገሩን ቀለል ያደርገዋል። በዚህ ዘመነ-መንግሥት የሀገሪቱ ባንዲራ አንዳንድ ጊዜ የንጉሠ ነገስቱ የሞዓ አንበሳ ዓርማ ያለበት ሲሆን፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ልሙጡ አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ ብቻ ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። የአፄ ኃይለሥላሴን ዘመነ መንግስት የባንዲራ ታሪክ ለማወቅ ዛሬም ድረስ የታሪክ መዘክር ሆነው የተቀመጡ ፎቶግራፎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማየት ይቻላል።

 አፄ ኃይለሥላሴ በኦፊሴል ጉብኝቶቻቸውና በተለያዩ ዝግጅቶች ሳይቀር ሁለቱን ባንዲራዎች እየቀያየሩ ሲጠቀሙ በጊዜው በነበሩ ቪዲዮና ፎቶግራፎች ያሳያሉ። እነዚህን እውነታዎች በማስረጃነት ለማረጋገጥ በዩቲዩብ እና ሌሎች ድኅረ-ገፆችም የተጫኑ ምስክር ይሆናሉ።

 ለምሳሌ ያህል ንጉሠ-ነገሥቱ እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም በእንግሊዝ በነበራቸው ጉብኝት ከተጓዙበት መርከብ ሲወርዱ በግዙፉ መርከብ ላይ ተሰቅሎ የሚታየው አምስት የዳዊት ኮከቦችንና የሞዓ አንበሳ ምልክትን የያዘ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ነበር። ሁለቱ ኮከቦች በላይኛው የአረንጓዴ መደብ ላይ፤ እንደዚሁም ቀሪዎቹ ሦስቱ ኮከቦች ደግሞ ከታች ባለው በቀዩ መደብ ላይ ተቀምጠው ይታያሉ። በቀዩ መደብ ላይ ከተቀመጡት ኮከቦች መሀል ሦስተኛው ኮከብ ከሞዓ አንበሳው ምልከት በታች ባለው የቀዩ ቀለም አግድም መሀል ለመሀል (Midpoint) ላይ የተቀመጠ ነው። በዚህ ሰንደቅ ዓላማ ላይ በክብ ቀለበት ውስጥ ባለመስቀል ልሙጥ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያለበትን ባንዲራ የያዘ ባለዘውድ አንበሳ ይታያል። ይህም የሞዓ አንበሳ አርማ ነው። በዙሪያውም “ሞዓ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ” የሚል ጽሑፍን አካቶ ይዟል። ይህ ሰንደቅ ዓላማ በንጉሱ የተለያዩ ሀገራት ኦፊሴላዊ ጉብኝቶቻቸው ወቅት ጥቅም ላይ መዋሉ የሀገሪቱ ዋነኛ ሰንደቅ ዓላማ እንደነበር ግልፅ ማሳያ ነው።

አፄ ኃይለሥላሴ በግብፅ በነበራቸው ጉብኝት በቀድሞው የግብፅ ፕሬዝዳንት ገማል አብዱል ናስር አማካኝነት በካይሮ ኤርፖርት አቀባበል ሲደረግላቸው ከግብፅ ባንዲራ ጎን ሲውለበለብ የሚታየው ይሄው ባለ አምስት ኮከብ የሞዓ አንበሳ ባንዲራ ነው።

 በተመሳሳይ መልኩ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እ.ኤ.አ በ1963 ዓ.ም በአሜሪካ በነበራቸው ሁለተኛው ኦፊሴላዊ ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ኬነዲ ጋር ሆነው በግልፅ ሊሙዚን መኪና በቀኝና በግራ አውራ ጎዳናዎች ላይ የተኮለኮለውን ህዝብ እጃቸውን እያውለበለቡ ሰላምታ እየሰጡ ሲያልፉ በሊሙዚን መኪናዋ ግራና ቀኝ ላይ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ስንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለው ይታያሉ። በዚህ ወቅት በመኪናው ላይ ሲውለበለብ የነበረው ሰንደቅ ዓላማ፤ ቀደም ሲል የተገለፀው ሞአ አንበሳውና ባለ ዓምስት ኮከቡን አረንጓንዴ ፣ቢጫ ፣ቀይ ቀለማትን አጣምሮ የያዘው ባንዲራ መሆኑን ቪዲዮው በግልፅ ያሳያል።

 እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም ዳግማዊ ንግስት ኤልሳቤጥ(Queen Elizabeth II) በኢትዮጵያ የመልስ ጉብኝት ሲያደርጉ ከቀደመው ባንዲራ በተለየ መልኩ በመላ አዲስ አበባ መንገዶች ግራና ቀኝ ተሰቅሎ የሚታየው የሰንደቅ ዓላማ አይነት ደግሞ ዓርማ የሌለበት የአርንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ሆኖ ይታያል።

 በእርግጥ በ1948ዓ.ም በራሳቸው በንጉሱ ዘመነ መንግስት የወጣው የ1948ቱ ሕገ መንግስት አንቀፅ 124 የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓንዴ ቢጫ ቀይ ባለሦስት ቀለማት ባንዲራ ብቻ እንደሆነ እንጂ፤ ሌላ ተጨማሪ አርማን የሚያካትት አለመሆኑን በሚከተለው መልኩ በግልፅ አስቀምጦ እንመለከተዋለን፡- “በህግ ተዘርዝሮ እንደተወሰነው የንጉሠ-ነገሥቱ መንግስት ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ከላይ ከመጀመሪያው አረንጓዴ፣ መካከለኛው ቢጫ፣ ከታች መጨረሻው ቀይ ሆኖ በአግድም የሚደረግ የሦስት ቀለማት ጨርቅ ነው”

ሆኖም ከተቀመጠው ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ አንፃር ሲታይ ንጉሠ- ነገሥቱ በኦፊሴል ሲጠቀሙበት የነበረው ባንዲራ አረንጓዴ ቢጫው ቀዩን ልሙጥ ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆን፤ ባለ አምስት ኮከብና የሞአ አንበሳ አርማን በተጨማሪ ምስልነት የያዘን ባንዲራ ነበር። ይህም በጊዜው በህገ መንግስቱ የተደነገገውና በተግባር የሚታየው እውነታ ፈፅሞ የተለያየ መሆኑን ያስገነዝበናል።

በእርግጥ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚታየው መስቀል እንደዚሁም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህበረ ቀለማትም ቢሆኑ ከቀስተ ደመና እና “እግዚአብሔር ለኖህ ልጆች የሰጠው ቃል ኪዳን ነው” በሚል ይሰጥ የነበረው የተለምዶ ክርስቲያናዊና መንፈሳዊ ትንታኔ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያንን የማይወክል በመሆኑ ቅሬታ ሲሰማበት የቆየ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።

 ሆኖም በሂደት ሁሉንም አካታች(All Inclusive) የሆነ ሰንደቅ ዓላማን እውን ለማድረግ በነበረው ሂደት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ህብረ ቀለማቱ፤ የልምላሜ፣የተስፋና የመስዋዕትነት መገለጫዎች መሆናቸው በግልፅ ተቀምጦ፤ አንበሳው የያዘው መስቀል ደግሞ አንበሳው ብቻ ሲቀር ሙሉ በሙሉ ከባንዲራው ላይ እንዲነሳ ተደርጓል።

 የደርግ ዘመን ሰንደቅ ዓላማ

 ደርግ ወደ ሥልጣን እየተንደረደረባቸው በነበሩት የመጀመሪያዎቹ የለውጥ ዓመታት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በቀጥታ ከዙፋናቸው ከማስወገድ ይልቅ ፖለቲካውን የማስታምም ሥራን ሲሰራ ስለነበር፤ ያንኑ የቀድሞውን መስቀል አልባ ባለ አንበሳ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጎ ቆይቷል። ሆኖም ወታደራዊው መንግስት ዙፋኑን ሙሉ በሙሉ አስወግዶ ስልጣኑን እያጠበቀ ሲሄድ ለሁለት ጊዜያት ያህል የተለያዩ ዓርማዎችን በአርንጓዴ፣ቢጫ ቀዩ ህብረ ቀለማት ባንዲራ ላይ አስቀምጧል።

 ሆኖም በጊዜ ሂደት የመንግስቱን አርማና የሀገሪቱን ባንዲራ በመለያየት ምንም አይነት አርማ የሌለው ባንዲራ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል። ይህንንም ባንዲራ ደርግ ራሱ በ1979 ዓ.ም ባወጣው የኢሕድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 113 ላይ በግልፅ እንዲቀመጥ አድርጓል። በዚሁ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (የኢሕዲሪ) ሕገ መንግስት ተብሎ በሚታወቀው ምዕራፍ አስራ ስድስት ላይ ባሉት ተከታታይ አንቀፆች ሰንደቅ ዓላማን፣ብሄራዊ አርማን፣ብሔራዊ መዝሙርን እና የመንግስትን የሥራ ቋንቋን በተመለከተ በተቀመጠው ድንጋጌ፤ በተለይ ባንዲራን በተመለከተ በዚሁ ምዕራፍ አንቀፅ 113 ላይ የሚከተለውን አስቀምጦ እናገኘዋለን፡-

 “የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓንዴ፣ከመሀሉ ቢጫና ከታች ቀይ ቀለም ያለው ባለ አግድም ቅርፅ ነው። ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል።” ይላል።

“የማህበራዊ ሚዲያዎችም የባንዲራ ፖለቲካውን ጦርነት ይበልጥ አፋፋሞታል። የባለኮከቡን ባንዲራ በተመለከተ የኮከቡን ምስል ከሰይጣናዊ አምልኮ ምልክት ጋር በማያያዝ ሃይማኖታዊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ።”

አወዛጋቢው የኢህአዴግ ዘመን ሰንደቅ ዓላማ

የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ በነበሩት የኢህአዴግ የሽግግር መንግስት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ቀደም ሲል የነበረው ምንም አይነት ምልክት የሌለው ልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ጥቅም ላይ ውሏል።

 ከዚያ በኋላ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ብሔራዊ አርማ እንደሚኖረው በሦስተኛው አንቀፅ ላይ እንደዚህ ሲል ደንግጓል።

 “የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ከመሀል ቢጫ፣ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሄራዊ አርማ”

ይህን ካስቀመጠ በኋላ የአርማውን ዓላማ እንጂ ዓይነቱን በተመለከተ በራሱ በህገ መንግስቱ ዝርዝር አንቀፆች ተንትኖ ያስቀመጠበት ወይንም በሌላ ዝርዝር ህግ እንደሚቀመጥ የጠቆመው ምንም ነገር የለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ የዓርማውን ዓይነት በተመለከተ “ህገ-መንግስቱ አንድም መዘርዘር አለበለዚያም በሌላ ህግ እንደሚወሰን በግልፅ ማስቀመጥ ነበረበት”በማለት የሚከራከሩ ወገኖች አሉ።

 ያም ሆኖ አርማውን በተመለከተ በዝርዝር ህግ ሊወሰን እንደሚገባው ህገ መንግስቱ ራሱ ባይገልፅም፤ ወይንም ደግሞ በራሱ አንቀፆች የአርማውን ምንነት በተመለከተ በግልፅ ትንታኔ ባያስቀምጥም፤ “የሰንደቅ ዓላማና አርማ አዋጅ” በሚል የሚታወቀውና በ1988 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 16 በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ ላይ የሚቀመጠውን የአርማ አይነት በዝርዝርና ገላጭ በሆነ መልኩ እንዲቀመጥ አድርጓል።

 ይህ አዋጅ የወጣው ሕገ መንግስቱ በ1987 ዓ.ም በፀደቀ በዓመቱ አካባቢ መሆኑን ልብ ይሏል። አዋጅ በሕገ መንግስቱ በደፈናው “አርማ” ተብሎ የተቀመጠውን ሀሳብ በማብራራት የአርማው ይዘት ምን አይነት እንደሆነ በሦስተኛው አንቀፅ ላይ በግልፅ ተንትኖ ያስቀምጠዋል።

አንቀፁ በንዑስ አንቀፅ አራት (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ያስቀመጣቸው ግልፅ ድንጋጌዎች የአርማውን አይነት በማብራራት በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል፡-

 የአርማው ቅርፅ ክብ በሆነ ሰማያዊ መደብ ላይ

(ሀ) ከየአቅጣጫው መጥተው የሚገናኙ ቀጥታና እኩል የሆኑ ቢጫ መስመሮች ይኖረዋል።

 (ለ) ቀጥታና እኩል ከሆኑት መስመሮች የተዋቀረ ኮከብ ይኖረዋል።

 (ሐ) ቀጥታና እኩል በሆኑት መስመሮች መጋጠሚያ ላይ የሚፈነጥቅ ቢጫ ጨረር ይኖረዋል። ባለ ዓርማው ባንዲራ ሕገ-መንግስታዊና የዝርዝር ሕግ ድጋፍ አግኝቶ የሀገሪቱ ኦፊሴል ባንዲራ ቢሆንም፤ በዓርማው በኩል የተነሳው አወዛጋቢ ጉዳይ ግን ከፍተኛ የሆነ መነጋገሪያ አጀንዳን የፈጠረ ነበር። የባንዲራ አጠቃቀምን በተመለከተ ከወጣው ጠበቅ ያለ የስደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 ድረስ፤ ቀላል የማይባለው የህብተረሰብ ክፍል አርማ አልባ ሰንደቅ ዓላማውን በሀዘኑ እና በደስታው ወቅት ሲጠቀም ቆይቷል።

መንግስት ባለ አርማው ባንዲራ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝና እንዲሰርፅ ለማድረግ ከ2 ሺህ ሚሊኒየም አከባበር ጀምሮ “ብሔራዊ የባንዲራ ቀን” ብሎ በማወጅ በርካታ ሺህ ባለ ኮከብ ባንዲራዎችን ጭምር በማሰራጨት በመንግስት ተቋማት፣በትምህርት ቤቶችና በመሳሰሉት ተቋማት ሳይቀር ቀላል የማይባሉ የማስረፅ ስራዎችን ሰርቷል። በዚህም በዓውደ ጥናቶች፣ በልዩ ልዩ የጥያቄና መልስ ውድድሮች፣በአደባባይ ክብረ በዓላትና በበርካታ መንግስታዊ መገናኛ ብዙኋን ፕሮግራሞች ሳይቀር የባለ አርማውን ሰንደቅ ዓላማ ለማስረፅ በርካታ ጥረቶች ሲያደረጉም ቆይተዋል።

 የህጉን ጥብቅነት ተከትሎ አርማ አልባው ሰንደቅ ዓላማ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥቅም ላይ መዋሉ ቢቀርም፤ በዲያስፖራው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊው ይያዝ የነበረው ባንዲራ ግንየደጋፊና ተቃዋሚ ጎራንበለየ መልኩ ሁለትና ሦስት አይነት ነበር። እነዚህም ሰንደቅ ዓላማዎች፣ልሙጡ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ፣ባለኮከቡ ባንዲራ እንደዚሁም በተለምዶ የኦነግ ባንዲራ ተብሎ የሚታወቀው ነው።

 የማህበራዊ ሚዲያዎችም የባንዲራ ፖለቲካውን ጦርነት ይበልጥ አፋፋሞታል። የባለኮከቡን ባንዲራ በተመለከተ የኮከቡን ምስል ከሰይጣናዊ አምልኮ ምልክት ጋር በማያያዝ ሃይማኖታዊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ ሰዎችም አሉ። በሌላ መልኩ ልሙጡን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ በተመለከተ “ባንዲራው የሰሜን ተስፋፊዎችን የበላይነት የሚወክል ነው” በማለት ከፍተኛ የሆነ ጥላቻቸውን የሚገልፁ ወገኖችም አሉ።

 ቀጣዩ ፈተና

በቅርቡ የተከሰተው የፖለቲካ የለውጥ ሂደት ደግሞ የሰንደቅ ዓላማውን ጉዳይ የበለጠ እየጦዘ እንዲሄድ አድርጎታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጊዜያት የተነሱት ግጭቶች የሰው ህይወት ሳይቀር እንዲጠፋ አድርገዋል።

 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንዲራ ጋር በተያያዘ እስከዛሬም ድረስ በዜጎች መካከል ያለው ፅንፍ የረገጠ አቋም እንደዚሁ ብቻውን ተነጥሎ የሚቆም ጉዳይ ሳይሆን፤ ከባንዲራው በስተጀርባ ያለው ሰፊ የፖለቲካ ውጥንቅጥ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

ባንዲራን በተመለከተ በበርካታ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ለውጦች ሲደረጉ ነገሮች ያን ያህል በተካረረ አወዛጋቢነት ውስጥ ሲገቡ ያልታዩት፤ የየሀገራቱ የፖለቲካ ባህል በመቻቻልና በለዘብተኝነት አስተሳሰብ ውስጥ የተቃኘ በመሆኑ ነው። ሆኖም በኢትዮጵያ በፍፁማዊ ግዛታዊ አንድነት አምላኪዎችና በአክራሪ ብሄርተኞች የተወጠረው የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ፖለቲካው በብሄራዊ ውይይት የነጠረ ሀገራዊ ወካይ ሀሳብ ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል።

 ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያኖች ያላቸው ደካማ የመወያየትና የመቻቻል ባህል፤ ባንዲራን በመሰሉ ብሄራዊ የማንነት መገለጫዎች ላይ እንኳን እንዳይግባቡ አድርጓቸዋል። አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ ከእልህ ፖለቲካ በመውጣት ነገሮችን “የእኛ ብቻ ካልሆነ” ከሚለው ቅኝት መውጣት ካልተቻለ በስተቀር፤በልዩ መለኮታዊ ኃይል ባንዲራ ከሰማይ ቢወረወር እንኳን ተቀባይነትን የሚያገኝ አይመስልም።

 በመሆኑም አሁን እየታየ ያለው ችግር ከባንዲራ ቀለማት፣ዲዛይን እና አርማ ጋር ብቻ የተያያዘ ሳይሆን በውይይት ካለማመን፣ሀሳብን ማቻቻል ካለመቻል እና የአንዱን እሴት ሌላው መቀበል ካለመፈለግ ጋር ጭምር የተያያዘ ሆኖ ይታያል። ይህ መሆኑ ደግሞ እያንዳንዱ ማህበረሰብ የየራሱን የማንነት መገለጫዎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦች ማንነት መገለጫዎችጋር ማንነት ደምሮና ጨምቆ ሁሉንም ሊያግባቡ የሚችሉ ሀገራዊ መገለጫዎችን እውን የማድረጉን ሥራ ፈታኝ አድርጎታል።

 ያም ሆነ ይህ አሁን ከሚታየው የሰንደቅ ዓላማ ፖለቲካ አንፃር የባንዲራ ጉዳይ የማያዳግም መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ገልፅ ነው። ያለፉትን የሰንደቅ ዓላማ ንትርኮች በሚዘጋ መልኩ ከሥርዓቶች እድሜ ባለፈ ሀገራዊ መገለጫ ሰንደቅ ዓላማን እውን ለማድረግ ግን ገና ብዙ ፈተና ይጠብቀናል። ቸር ያቆየን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top