ጣዕሞት

ልደትን ያደመቀ ምርቃት

“ታላቁ የጥበብ ባለሟል» በሚል ቅጽል የሚታወቀቁት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ የተወለዱት የመስቀል በዓል ዕለት መስከረም 17 ነው። ዘንድሮ 82ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በደመቀ ሁኔታ ሲያከብሩ፤ እንደ ያለፉት ሁለት ዓመታት የልደት በዓላቸው አከባበር ሁሉ፤ አዲስ መጽሐፋቸውን በማስመረቅ ነው።

 ደራሲያን፣ የተውኔት ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ ሌሎች የኪነጥበብ ሰዎችና አድናቂዎቻቸው በተገኙበትና በላፍቶ ሞል በተከበረው የልደት በዓላቸው ላይ ነው «አስብና ክበር» በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን መጽሐፍ ያሰመረቁት።

«Think and grow rich» በሚል ርዕስ አሜሪካዊው ደራሲ ናፖሊዮን ሂል በእንግሊዝኛ የተዘጋጀውን መጽሐፍ «አስብና ክበር» በሚል ርዕስ ወደ አማሪኛ በመተርጎም፤ ለንባብ ያበቁትን ይህን መጽሐፍ አንብበው የተረዱ፣ ሰርተው በሀብት ለመለወጥ ለሚተጉ ሁሉ የስኬታማነት ምስጢርን ያገኙበታል የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሮፌሰር ተስፋዬ ተናግረዋል።

መጽሐፉን ደጉ ዮሴፍ የተባሉ ወዳጃቸው ካዋሷቸው ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመት በውስጣቸው ሲያውጠነጥኑ እንደነበር፤ ተርጉመው ለቀጣዩ ትውልድ ሳያስተላልፉ ቢቀሩ ህሊናቸውን ሲቆረቁራቸው ሊኖር እንደሚችልም ነው የገለፁት። ታዳሚውን በማመስገን አዝናኝ በሆነ ቀልድ አዘል ንግግራቸውም ልደታቸውንና የመጽሐፋቸውን ምርቃት አድምቀውታል።

 ኬክ ባስቆረሰው፣ ሻምፓኝ ባስከፈተው በዚህ የልደት በዓል ላይ ከታደሙት አስተያየት ሰጪዎች መካከል ወዳጃቸው አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ «ተስፋዬን በስራዎቹ ለአገሪቱ ላበረከተው ሙያዊ አስተዋጽኦ ባወድሰው፣ ባወድሰው…አይበቃውም። በዚህ ትጋቱ ገና ብዙ ይሰራል። ዕድሜና ጤና ይስጠው…» ሲሉ ተደምጠዋል። ባለቤታቸው ወይዘሮ መንበረ ግርማ በበኩላቸው፤ «በሰላምና በጤና መኖርህ ያስደስተኛል። በርታልኝ! …» ብለዋል።

በመድረክ ትወና፣ በቴአትር አዘጋጅነት፣ በጸሐፊ ተውኔት፣ በግጥም፣ በልቦለድ፣ በፊልም ስራ በቴአትር ቤቶች ስራ አስኪያጅነት፣ በመምህርነት፣ በተርጓሚነትና በሌሎች የጥበብ ስራዎች የሚታወቁት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ፤ በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ከአሥራ ሁለት በላይ መጽሐፎችን ለንባብ አብቅተዋል።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ መጽሐፍ ለንባብ በቃ

ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን ከመመስረታቸው ባለፈ፤ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበብን በማሳደግና በርካታ የሙዚቃ ሙያተኞችን በማፍራት የሚታወቁት ተስፋዬ ለማ፤ በአሜሪካን አገር በስደት ላይ እየሮሩ ባለበት ነው ከአመታት በፊት ህልፈታቸው የተሰማው። በዚህም በርካታ የጥበብ አፍቃሪዎች አዝነዋል፤ ስለ ታላቅ ውለታቸው በብሔራዊ ክብር ምስጋና ሳይቸራቸው መቅረቱ አስቆጭቷል።

 አርቲስት ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ለ40 ዓመታት ሲኖሩበት፤ ለሙዚቃ ጠበብቱ ጥላሁን ገሠሠ፣ ለመሐሙድ አህመድ ፣ ለሂሩት በቀለ እና ለሌሎች ታዋቂ ድምጻዊያን ግጥሞችና ዜማዎችን በመስጠት ይታወቃሉ።

የእኚህ ታላቅ የአገር ባለውለታ፤ ለአገር ያበረከቱት ስጦታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አልሆነም። «ህዝብ ለህዝብ»ን ጨምሮ ታላላቅ የሙዚቃ ዝግጀቶችን መርተዋል፣ አስተባብረዋል። ከዚያም ባለፈ በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያን ሙዚቃ ሁለንተናዊ ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ ጥረዋል። « የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ከ1989‐ 1983 ዓ.ም» የሚል ርዕስ ያዘጋጁት መጽሐፍም ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ይህንን መጽሐፍ ሲያዘጋጁ ግን ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አልነበረም፤ በሕመም አልጋ ላይ ውለው ራሳቸውን እያስታመሙ እንጂ።

በሻማ ቡክ አሳታሚነት በዓለማየሁ ገብረሕይወት አርታኢነት ለንባብ የበቃው ይህ መጽሐፍ፤ ቀደም ሲል በአሜሪካን አገር ቢታተምም፤ ሰሞኑን ለአገር ውስጥ አንባቢያን እንዲደርስ በድጋሚ ታትሞ ለንባብ ቀርቧል።

ተስፋዬ፤ የሙዚቃ እድገት ሂደቶችን በዘመን ክፋፍተው ያዘጋጁት ይህ መጽሐፍ፤ ለታሪክ፣ ለጥናትና ምርምር፣ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አፍቃሪዎችና መረጃ ፈላጊዎች እንደ ጥሩ ምንጭ ሊወሰድ እንደሚችል ታምኖበታል።

በአሥር ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ332 ገጾች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ የሚያተኩረው በኢትዮጵያ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ታሪክ ሲሆን፤ የወዝዋዜ ወይንም የዳንስ ክፍልንም ያካትታል። የባለታሪኮቹ ፎቶግራፎችን፣ ስዕሎችን እና የተስፋዬ ለማን ቃለ መጠይቅም አካቷል።

 በመጽሐፋቸው መግቢያ መልዕክታቸው፤ ለመጽሐፋቸው ግብአትነት የተለያዩ መረጃዎችን፣ ላቀበሏቸው ግለሰቦችና ተቋማት አመስግነዋል። የጥንት ተረቶችን እየነገሩ ያሳደጓቸው እናታቸው ወይዘሮ በላይነሽ ካሳ፤ ሲፈጩና ሲፈትሉ

 «ዘፈን ለደስታ ይመስለኝ ነበረ

 ለካስ ለተከፋ ለተቆረቆረ »

 እያሉ በዜማ ያንጎራጉሩት የነበረውን ግጥምም አስፍረዋል።

የደም ትስስርን ያጠበቀ የመታሰቢያ በዓል!


ኩባዊያን እንግዶች ከኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸው ጋር በዓሉን በድምቀት አክብረውታል፡፡

ከዛሬ 40 ዓመት በፊት (በ1969 ዓ.ም) ኢትዮዽያ ከውስጥም ከውጪም ገጥሟት የነበረው ፈተና ቀላል አልነበረም፡፡ ከውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች ፍትጊያ፤ ከውጪ ደግሞ የሶማሊያ ወረራ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ነበረው ውጊያም ለአገሪቱ መሪዎች ጭንቅ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በተለይ ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ዚያድባሬ የኢትዮዽያን ግዛት «እስከ አዋሽ የእኔ ድንበር ነው» በሚል ዘመናዊ ጦሩን አስታጥቆ ጅጅጋን በማለፍ ድሬዳዋን ዘልቆ በመገስገስ ላይ ነበር፡፡

 ኢትዮዽያ ብቻዋን መወጣት ስለማይቻላት ለዚህ ጥቃት ደጋፊ ስታማትር «አለሁ» የሚላት ወዳጅ አላጣችም፡፡ ጽንፈኛው የኮምኒስት ስርአት አራማጁ ፊደል ካስትሮ ቀዳሚ ሆኑ፡ ፡ ከወታደሮች ጋር በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንክ ላኩ፡፡ በተመሳይ ሁኔታም የመን ደጋፏን ስታሳይ ወታደሮቿን አዘመተችልን፡፡ አርፍዳም ቢሆን ሶቪየት ህብረትም አሰልጣኝ መኮንኖችንና የጦር መሳሪያዎችን በመላክ መተባበሯ አልቀረም፡፡

በኮሪያና በኮንጎ ወታደሮቿን አዝምታ አገራቱን ለመታደግ ላደረገችው መልካም ተግባሯ ሁሉ፤ የዕጇን አላሳጣትም፡፡ በዚህ የድጋፍ ጦርነት ድል መታን፡፡ ካራማራ ተራራ ላይ ድል ስንቀዳጅ፤ ጅግጅጋ ላይ ባንዲራችን ሲውለበለብ ኩባዊያኖች አብረውን ነበሩ፡፡ በዚህ ጦርነት በበለጠ ሁኔታ የልብ ወዳጀነቷን ያጠበቀችው ኩባ ነበረች፡፡ በጦርነቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿ ሕይወታቸውን ሰውተዋል፡ ፡ የቆሰሉና የተማረኩም ቀላል አልነበሩም፡፡ ከድሉ በኋላም በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ የወታደር ልጆችን በአገሯ በማስተማር ቅንነቷን አሳይታለች። የኢኮኖሚ አቅሟ የጠና ባይሆንም «ያለንን እንካፈል» አይነት ነው፤ ይህ ድጋፏ፡፡ ከ6 ሺ በላይ ተማሪዎችን አሰልጥና መላኳ፡፡

«ኢትዮዽያና ኩባዊያን የደም ትስስር አላቸው» የሚባለውም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ኩባዊያን በአገራችን በቆዩበት በዚያን ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ሴቶች ጋር ተዋልደዋል፤ ተዛምደዋል፡፡ በጦር ግንባር ላይ ሲሰዉም ደማቸው አፈር ውስጥ ተቀላቅሏል፡፡ ወደ ኩባ የሄዱ ተማሪዎችም ከኩባዊያን ጋር የመጋባት ፡ የመዋለድና የመዛመድ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡

ከጦርነቱ ድል በኋላ በተለያዩ ዙሮች ስድስት ጊዜ ለነጻ ትምህርት ወደ ኩባ የሄዱት የወቅቱ ታዳጊ ተማሪዎች ዛሬ ጎልምሰዋል፡፡


የኩባው ም/መከላከያ ሚኒስትር ራሞን ኤስቲኖቫ
መታሰቢያ ኃወልቱ ስር የአበባ ጉንጉን ሲያኖሩ

መሀንዲሶች፣ ዶክተሮች፣ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ የቱሪዝም እና የንግድ ስራዎች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ መንግስታዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥም ያገለግላሉ፡፡

እነሆ ይህ የኩባ እና የኢትዮጵያ ወዳጅነት እንዲሁም የካራማራ ድል 40ኛ ዓመት ዘንድሮ አዲስ አበባ ውስጥ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡ በፓናል ውይይት፣ በአውደ ርዕይ፣ በጉብኝት፣ በጦርነቱ የተሰዉ የመታሰቢያ ሃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን በማኖርና በሌሎች የመዝናኛ ዝግጅቶች፡፡ ለአንድ ሳምንት በተካሄደው በዚህ ዝግጅት፤ የኢትዮጵያዊያኖች የከበረ ምስጋና ለኩባዊያኖች እንዲደርስ ሆኗል፡፡

 ከኩባ የመጡ የያኔው የጦር አዛዝ ጀነራሎች፣ ወቅቱ አገሪቱ ምክትል መከላያ ሚንስትር ራሞን እስቲኖባ፣ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር እና የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ የኩባ ተማሪዎች እንዲሁም የኢትዮ ‐ ሶማሊያ ላይ የተሳተፉ የጦር አመራሮችና ጀነራሎች የተገኙበት ክብረ በዓል ዋና አላማ የኩባ መንግስትና ህዝብን ለማመስገን መሆኑን የዝግጅቱ አስተባባሪና የኢትዮ ‐ኩባ ወዳጆች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አበበ አያሌው ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ለህዝብ ወዳጅነቱ ጠንክሮ፤ በመንግስት ደረጃም በተለያዩ መስኮች ትብብር እንዲኖር ማህበሩ እንደሚጥር ገለፀዋል፡፡ ዛሬም በብርቱ የሶሻሊዝም ርዕዮት አራማጅነቷ የምትታወቀው ኩባ፤ ከ11 ሚሊየን ያልበለጠው ሕዝቧን ከኢኮኖሚ አቅሟ ጋር አጣጥማ የምትሮር አገር ነች፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top