ቀዳሚ ቃል

ግጥም እና ዜማ ለማን?

የተሳሳተን መስመር መጠቆም፣ የህዝብን ህመም፣ የፍትህ እጦት፣ በደልን መናገር ማዜም፣ እንደሚባለው ድሮ በአዝማሪዎች ይነገራል። ይከወናል።

 የአዝማሪዎቹ ተቃውሞ፣ የድፍረታቸው ምክንያት፣ ተነግሮ፣ ከሚተላለፈው በተጨማሪ በዘመኑ ደራሲያን፣ ሥርዓቱን ለመተቸት፣ የሹማምንቱን ያልተገባ ባህርይ ለማሳየት፣ በልቦለድ እና በታሪክ መጽሐፎች ላይ ሠፍሯል። ስለዘፈኖቹ ሲነሳ፣ ነፃነትን በአፈነ፣ ፍትህን በነፈገ፣ ሥርዓትን ውስጥ በኃይለኛነቱ የታወቀ፣ ሕዝብን የናቀ መሪ ፊት ተገኝተው፣ በግጥምና ዜማ ያለፍርሃት ጥፋቱን የተናገሩ አዝማሪዎች እንደነበሩ ተነግሯል።

 ከንጉሳዊያን ቤተ-ሰብ ዘመን ወዲህም ቢሆን ከዘፈኑ ይልቅ መዝሙሩ ልቆ ብቻ ከማዜም ይበልጥ ህብረ-ዝማሬው በልጦ፣ ለርዕዮተ-ዓለም ማራመጃ ታስቦ ከ “ደም ማፍሰስ”፣ ከ “መደምሰስ”፣ ከ “ማስወገድ”፣ ጋር “ቃል መግባት” ለ “ነፍስ አለመሳሳት” ተደባልቀው የተገጠሙ ዜማ ወጥቶላቸው ተደምጠዋል።

 በእርግጥ ለ “አብዮት ድል ማድመቂያ” በሚል ከተቀናበረው ለ “አብዮት ቀን መታሰቢያ” ተብሎ ከተዘጋጀው ወጣ ብለው ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ በዜማቸው የተወደዱ በግጥማቸው ይዘት የተሞገሱ ድምፃውያን ባይበዙም ታይተዋል። ዘፈን በሀገራችን በተለምዶ ከሌሎች የኪነ-ጥበብ ውጤቶች ይበልጥ ፈጥኖ፣ ተሰናድቶ፣ ስሜትን የመለወጥ አቅም ያለው ሙያ እንደመሆኑ ሹመኞች በህገ-ወጥ መንገድ ከብረው ሲታዩ፣ ህዝብ ንቀው እንዳሻቸው መኖር ሲጀምሩ፣ ቃላቸውን አጥፈው ሀገር ሲጎዱ የተመለከቱ ከያኒያን በቀጥታም ባይሆን ግጥም ፅፈው ፣ ዜማ አውጥተው ዘፍነዋል። ወይም ለድምፃዊያን ሰጥተዋል።

 አድማጩ ይረዳናል ወይም ፍችውን ይነግረናል ባሉት ስልት፣ መልዕክታችን ይደርስልናል ብለው በመረጡት መንገድ፣ ተቃውሟቸውን አስተላልፈዋል።

 ይሁን እንጂ የአብዛኞቹ ድምፃውያን ዘፈኖች ለምን እንደተፃፉ የሚነገረው ምን ሊያስተላልፉ እንደፈለጉ የሚታወቀው መንግስት ሲለወጥ ይመስላል። ምንም እንኳን የአንዳንዶቹ ግጥም ከጅምሩም ይዘቱ ሌላ ቢሆንም ፤

 ዛሬም ስለ ህዝቦች ፍቅር፣ መውደድ እና መደጋገፍ፣ ስለ ሀገር ፍቅር ዕድገትና ብልፅግና አስታዋሽ ሳይጠብቁ፣ በሰቦካ ጎኑ ሳይሆን በኪነ- ጥበብ ለዛው፣ ግጥም ፅፈው ወይም ተቀብለው፣ አዜመው ወይም ለሌሎች ድምፃውያ ሰጥተው፣ አሁን ያለን ስሜት፣ የሚያዩትን እውነት ሠርተው ቢያሳዩን የተሻለ ይሆናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top