ስርሆተ ገፅ

የውዝዋዜ ማሠልጠኛ ቢኖር እመርጣለሁ

ኪዳኔ ምስጋና ይባላል። ተወልዶ የአደገው አዲስ አበባ መርካቶ አማኑኤል አጂፕ ማደያ አከባቢ ነው። በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባህል አዳራሽ በውዝዋዜ ሞያ ተቀጥሮ ከአገለገለ በኋላ በአሁኑ ሰዓት አሰልጣኝ ሆኖ እየሠራ ይገኛል። ኪዳኔ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እና በተለያዩ መድረኮች ከሌሎች ባለሞያዎች ጋር በመሆን ውዝዋዜ በማቅረብ ይታወቃል። በአዲስ አበባ እና በክልሎች በተለያዩ መድረኮች በዝግጅት ተሳትፏል።

ሞያው ምን ያህል አድጓል ብለህ ታስባለህ?

 አብዛኛውን ጊዜ ውዝዋዜ ከተለያዩ የሀገረሰብ ዘፈኖች ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት ድምፃውያን ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ እንደመለያየቱ የእኛም ሞያ እንደየዘፈኖቹ ዓይነት እና የአጨዋወት ስልት በየጊዜው አዳዲስ አቀራረቦችን በመሞከር እየተለወጠ እና እያደገ ያለ ይመሥለኛል።

. ጥረቶች ካሉ ብትነግረኝ?

በእረፍት ሰዓት በተለይም ክረምት ክረምት ላይ ለታዳጊዎች ሥልጠና እንሰጣለን። ችግሩ በሀገራችን በቂ የውዝዋዜ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የለም። በእርግጥ ወደፊት አቅም ያላቸው እና ሞያውን ለማሳደግ የሚፈልጉ ይህን ተግባር እንደሚፈፅሙ አምናለሁ። በሀገራችን የውዝዋዜ ማሰልጠኛ ቢኖር እመርጣለሁ።

 . ሞያውን በተመለከተ የሌሎችን አስተያየቶች ምን ያህል ትቀበላላችሁ?

 ከተለያዩ ባለሞያዎች ጋር እንገናኛለን። ከሀገር ውጭ ካሉትም ጋር እንነጋገራለን። በዘፈን ክሊፖች ላይ በሚቀርበው ውዝዋዜ በአለባበስም ይሁን በሌሎች አቀራረቦች ላይ ትክክል ካልሆኑ ይጠቁማሉ። በዙን ጊዜ በቴአትር ቤቶች በተለይ አልባሳት የሚመርጡ ባለሞያዎች በመኖራቸው ችግሮች ላይከሰቱ ይችላሉ እንደተባለው ስህተቱ የሚጎላው በክሊፖች ላይ ነው። ያንንም ቢሆን እንዲያስተካክሉ እንናገራለን። እኛም ጋ ትክክል ያልሆነ ሥራ ካለ እናርማለን።

. ከሰራሃቸው መድረኮች የትኞቹ የተሻሉናቸው?

ለእኔ ሁሉም የተሻሉ ናቸው። ይበልጥ የማስታውሳቸው በሚሊኒየም በዓል ያቀረብነው የተለያዩ ክልሎች የባህል ውዝዋዜ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር በሙዚቃዊ ድራማ ሥልት የአዘጋጀነው እንዲሁም በአማራ፣ በኢትዮጵያ ሱማሌ እና በደቡብ ክልሎች እየተዘዋወርን የሠራናቸው ያስደስቱኛል።

.ወደፊት በአቀራረብ በኩል ቢለወጥ የምትለው ካለ?

 በዓሎች ላይ ለምሳሌ አዲስ ዓመት ሊሆን ይችላል ከቴአትር ቤቶች ውጭ ቢዘጋጅ ጥሩ ይመስለኛል። አንዴ የኤርትራ ቴሌቪዥን ስከታተል በአዲስ ዓመታቸው ይሁን በአብዮት በዓላቸው ትዝ አይለኝም ብቻ እስቴድዮም ውስጥ በርካታ ተመልካቾች ባሉበት እና በሚሳተፉበት ዝግጅታቸውን ሲያቀርቡ ተመልክቻለሁ። እንደ እነዚያ ዓይነት አቀራረቦች በሀገራችን ቢለመዱ እመኛለሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top