ታሪክ እና ባሕል

የትምህርት መሰረታዊ ይዘት በጥንታዊት ግሪክና በኋለኛው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት – ግርድፍ ሀተታ

‹‹ትምህርት ቤቶች የሰብዓዊነት መቅረጫ ማዕከላት ናቸው። ሰው በእርግጥም ሰው የሚሆነው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተኮትኩቶና በልጽጐ የወጣ እንደሆነ ነው።››

ጆን አሞስ ኮሜኒየስ

 እንደ መግቢያ

 የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ትምህርት ምንነትና ባህርያት በጥልቀት መዘርዘር አይደለም። በጽሑፉ ለማንሳት የፈለግሁት በአጠቃላይ ስለ ትምህርት፤ በተለይ ደግሞ ስለሀገራችን የትምህርት ስርዓት (ስለ ባህላዊውም፣ ዘመናዊውም፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ስለነበረውም፣ አሁን ስላለውም፣ ወዘተ) አንዳንድ ሃሳቦችን እያነሳን እንድንወያይ ነው። ተምረናል የምንለው ዜጎች በአንድ ወቅት ተማሪዎች፣ ከዚያም በሙያ ምርጫም ይሁን ምደባ በመምህርነት የስራ መስክ ተሰማርተን የነበርን ወይንም የተሰማራን፣ ቤተሰብ መስርተን ልጆች አፍርተንም ከሆነ ልጆቻችንን የምናስተምር በመሆናችን ለትምህርት ጉዳይ በጣም ቅርብ ነን። ስለዚህ ለመነሻ ያህል በዚህ ጽሑፍ ትምህርት በጥንቱ የግሪክ ስልጣኔ ምን መልክ እንደነበረው፣ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገሮች የትምህርት ባህርያት ምን እንደሆኑ በአጭሩ ለማመልከት እሞክራለሁ። ሌሎች ዓምደኞች ወይንም ጸሐፊዎች ከዚህ በመነሳት ሰፋ ያሉና የላቁ ሃሳቦችን የያዘ መጣጥፍ እንደሚያስነብቡን አምናለሁ።

 ትርጓሜና ጥቅል ሃሳብ

 በዚህ ጽሑፍ ትምህርት የሚለውን ቃል በእንግሊዝኛው ‹‹ኤጁኬሽን›› ለሚለው ቃል አቻ አድርገን እንጠቀምበታለን። በትርጉም ደረጃ ትምህርት ሰፊ ጽንሰ-ሃሳብን የያዘ ቃል ቢሆንም፤ ቀለል ባለ አገላለጽ ትምህርት አንድ ህፃን ወይንም ሰው ስርዓት በተመላበት መንገድ እውቀትን፣ ልምድን፣ ክሂሎትንና መልካም አስተሳሰብን የሚቀስምበት ሂደት ነው። ትምህርት ሰውን የሰለጠነ፣ የተማረ፣ የላቀና የዘመነ እንዲሆን ያስችለዋል። በትምህርት የሰው ልጅ አካላዊ፣ አዕምሮአዊ፣ ሞራላዊና ማህበራዊ ችሎታዎች ተጣጥመው ይበለጽጋሉ፤ በልጽገውም በኑሮ ሂደት ዓላማ ላለው አገልግሎት ይውላሉ። በመሆኑም ማህበረሰብ እንዲሰለጥንና ይበልጥም ማህበራዊ እንዲሆን ትምህርት በጣም አስፈላጊ ነው። የትምህርት ግቡ ሰውን የተሟላ ማድረግ ነው። ማንኛውም ህብረተሰብ ለትምህርት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው በህይወት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጋፈጥና ለማስወገድ ሁነኛ መሳሪያ በመሆኑ ነው። በአጭሩ ትምህርት ለህይወት ፈተና ነቅቶ የመገኘት ሂደት ነው። በዚህ የተነሳ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ትምህርት ለማህበራዊ መሻሻልና ብልጽግና ትክክለኛው ጐዳና እንደሆነ ይታመንበታል።

ትምህርት የስልጣኔን ያህል ረዥም ዕድሜ አለው። ከህብረተሰብ እድገት ታሪክ አንፃር በጥንታዊ የጋርዮሽ ስርዓት የነበረው ትምህርት ያልተቀናበረ፣ በተግባር ላይ ያተኮረና በግለሰብ ላይ የተመሰረተ ነበር። ትምህርት ቤት ብሎ ነገር አልነበረም። ልጆች ትምህርት የሚያገኙት በወላጆቻቸው አማካይነት ሲሆን፣ የሚማሩትም ጠና ያሉት ወይንም አዋቂዎቹ የቤተሰብ ወይንም የጎሳው አባላት ለመኖር ሲሉ ያከናውኗቸው የነበሩትን መሰረታዊ ስራዎች ነበር። ይህ ዓይነቱ ትምህርትና የትምህርት አሰጣጥ ህብረተሰቡ በመደብ እስከተከፋፈለበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ቆይቷል።

 ለትምህርት ቤት መመስረት ወሳኝ ምዕራፍ የከፈተው የጽሁፍ ጥበብ መከሰት ነበር። የጽሁፍ ጥበብ የሰው ልጅ አፈታሪኩን፣ ትውፊቱን፣ ሃይማኖትና የመስተዳድር ጉዳዩን ሁሉ መዝግቦ እንዲይዝ ረዳው። ልጆችም ቀደም ሲል የተጻፉትን መዛግብትና ሰነዶች መረዳት ይችሉ ዘንድ መጻፍና ማንበብ መማራቸው የግድ ሆነ። ይህም በተቀላጠፈ መንገድ ሊከናወን የሚችለው የማስተማሩ ስራ ሲቀናበር በመሆኑ የመምህር መኖር አስፈላጊ ነበር። በዚህ እጅግ ረዘም ባለው የታሪክ ወቅት፣ መምህራኑ የጎሳው ወይንም የማህበረሰቡ የሃይማኖት አባቶችም ነበሩ።

 በዓለማችን ከተነሱት ታላላቅ ጥንታዊ ስልጣኔዎች አንዱና በዘመናችን የትምህርት፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ ወዘተ ታሪክና እድገት ላይ ከቶም የማይደበዝዝ አሻራ ትቶ ያለፈው የጥንታዊት ግሪክ ስልጣኔ ነው። በጥንታዊት ግሪክ የነበሩት ሁለቱ ታላላቅ ከተሞች፣ ስፓርታ እና አቴንስ (አቴንስ)፣ የየራሳቸው የተለያየ የትምህርት ስርዓት ነበሯቸው። የዘመናችን የትምህርት ሊቃውንት፣ ዘመናዊው ዓለም ከስፓርታም ከአቴንስም የትምህርት ስርዓት አንዳንድ ጠቅለል ያሉ መስኮችን እንደወረሰ ያስረዳሉ። ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የሁለቱን ከተሞች የትምህርት ትኩረትና ግቡን ተራ በተራ በአጭሩ ለማየት እንሞክራለን።

 ትምህርት በስፓርታ

 የስፓርታ ትምህርት አምባገነናዊ ነበር። የስፓርታ የከተማ መንግስት (ሲቲ ስቴት) ዋና ትኩረቱ የመንግስትን ደህንነት መጠበቅ እንጂ የእያንዳንዱን ዜጋ እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ አልነበረም። የመንግስትም ደህንነት የሚረጋገጠው ከፍተኛ የጦር ሃይል በማዘጋጀት በመሆኑ የስፓርታ የትምህርት ስርዓት ዋና ትኩረትም የበቁና የነቁ ተዋጊዎችን ማፍራት ላይ ብቻ ነበር። በስፓርታ መንግስት ፍፁም በመሆኑ፣ የዜጎች ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ አይሰጠውም። የስፓርታ ዜጎች እንደ ዜጋ የሚቆጠሩት በመንግስት ገናና ዝና ላይ ሌላ ገናና ዝና ሲያስመዘግቡ ብቻ ነበር። ይህን መሰሉን የትምህርት ስርዓት በቅርቡ ዘመን አዶልፍ ሂትለር በጀርመን ተጠቅሞበታል።

 በስፓርታ ህይወት ዘወትር ከአደጋ ጋር የተቆራኘ ነው። አደጋን መቋቋም ለብቁ የስፓርታ ዜግነት አንድ መስፈርት ነበር። ለዚህም ነበር የስፓርታ ህፃናት ሆን ተብለው ለአደጋ እንዲጋለጡ ይደረግ የነበረው። አደጋውን ተቋቁመው ያልሞቱት ህፃናት እንደ ብቁ ዜጋ፣ በአደጋው የተቀጠፉት ደግሞ እንደ ከንቱ ዜጋ ይቆጠሩ ነበር። የህፃናቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ወታደርነት ብቻ በመሆኑ ገና ከልጅነታቸው መከራና መንገላታት የበዛበትን አስቸጋሪ ኑሮ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ለሀሩርና ለቁር እንዲጋለጡ ይደረጋል። ምቾት የሚሉ ነገር አልነበረም።

በስፓርታ ልጆች ሰባት ዓመት ሲሞላቸው በቡድን በቡድን ይከፈሉና ጠንከር ባለ ወታደራዊ ስነስርዓት ስር እንዲጠበቁ ይደረጋል። ከልጆቹ መካከል ጐበዝና ጠንካራው ይመረጥና የቡድኑ አምበል ይሆናል። ልጆች አስራ ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው በተዘጋጀላቸው ካምፖች ያድጋሉ። በእነኚህ ካምፖች (ፐብሊክ ባራክስ) ውስጥ የሚሰጡት ትምህርቶች ውሃ ዋና፣ ሩጫ፣ አደንና ለአካል ጥንካሬ የሚረዱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ነበሩ።

 በካምፖቹ የሚሰጠው ትምህርት በመንግስት ባለስልጣናት ያላሰለሰ ክትትልና ግምገማ ይደረግበታል። ለእነኚህ ባለስልጣናት ረዳት እንዲሆኑ ሆን ተብለው የተዘጋጁ ገራፊዎች በየካምፑ ይገኛሉ። የአካል ጥንካሬ የትምህርቱ ዋና ግብ በመሆኑ መገረፍ ከትምህርቱ ስነምግባር አንዱ ነበር። አንዲት ትንፋሽ ሳያሰሙ የሚወርደውን የጅራፍ ውርጅብኝ መቋቋም ጥንካሬን የመፈተኛ ዋናው መንገድ ነበር።

 በየካምፑ ተሰባስበው የነበሩት ልጆች 18 ዓመት ሲሞላቸው፣ ሰባት ዓመት ሞልቷቸው ወደየካምፑ የገቡትን ህፃናት፣ ቀደም ሲል እነርሱ ራሳቸው የተማሩትን ትምህርት በተማሩበት ዘዴ እንዲያስተምሩ ይደረጋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ትልልቆቹ ልጆች 20 ዓመት ሲሞላቸው ለመንግስታቸው የታማኝነት ቃለ-መሃላ ይፈጽሙና፣ ሀገሪቱ በጦርነት ላይ ከሆነች ወደ ጦር ሜዳ፣ አሊያም ወደ ውትድርና  ስልጠናው ይመለሳሉ። ሰላሳ ዓመት ሲሞላቸው ሙሉ (ብቁ) ዜጋ በመባል በየህዝባዊ ስብሰባው የመቀመጥ መብት ይኖራቸዋል።

የስፓርታ ህብረተሰብ ይህን በመሰለው የትምህርት ስርዓት ውስጥ ማለፍ ስለነበረበት፣ አሁን የምናውቀው ዓይነት የቤተሰብ ስርዓት በስፓርታ አልነበረም። የስፓርታ ሴቶች ቀዳሚ ተግባር ልጆችን መውለድ በመሆኑ፣ የስፓርታ እናቶች ጠንካራ ልጆችን መውለድ እንዲችሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲሰሩ ይደረግ ነበር።

 ጠንካራ ወታደሮች ማፍራትን ቀዳሚ ተግባር ያደረገው የስፓርታ

“ከሁለት ዓመት በኋላ ትልልቆቹ ልጆች 20 ዓመት ሲሞላቸው ለመንግስታቸው የታማኝነት ቃለ- መሃላ ይፈጽሙና፣ ሀገሪቱ በጦርነት ላይ ከሆነች ወደ ጦር ሜዳ፣ አሊያም ወደ ውትድርና ስልጠናው ይመለሳሉ። ሰላሳ ዓመት ሲሞላቸው ሙሉ (ብቁ) ዜጋ በመባል በየህዝባዊ ስብሰባው የመቀመጥ መብት ይኖራቸዋል”

የትምህርት ስርዓት፣ ለስነጽሑፍና ለኪነጥበብ ምንም ስፍራ አልነበረውም። አንድም ባለቅኔ፣ ወይ ፈላስፋ፣ ወይ ደግሞ የስነጥበብ ሰው በስፓርታ አልበቀለም። ጥንታውያኑ የግሪክ ፈላስፎች፣ ባለቅኔዎችና የስነጥበብ ሰዎች ሁሉ ምንጫቸው የአቴንስ ከተማ ነበረች።

 ትምህርት በአቴንስ

አቴንስና ስፓርታ በፖለቲካና በትምህርት ስርዓት ፍልስፍና እጅግ የተፈራረቁ ፖሊሲዎች ነበሯቸው። አምባገነናዊው የስፓርታ የትምህርት ስርዓት ግብ ጠንካራና የሰለጠነ ወታደር ማፍራት ሲሆን፣ ዴሞክራሲያዊው የአቴንስ የትምህርት ስርዓት ግን በህግና በስርዓት የታነጸ ነፃ አስተሳሰብ ያለው የተማረ ዜጋ ማፍራት ነበር። ይህ በአምባገነናዊና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መካከል ያለው የማሰልጠንና የማስተማር (ትሬይኒንግ እና ኤጁኬሽን) ልዩነት እስካለንበት ዘመን ድረስ ጉልህ ሆኖ ይታያል።

የአቴንስ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንደ ስፓርታ አቻዎቻቸው ኑሮአቸው በመንግስት ካምኘ ውስጥ ሳይሆን በየቤታቸው ነበር። እስከ ሰባት ዓመት እድሜ ድረስ በእናታቸውና በተመረጠች ሴት አገልጋይ አማካይነት አስፈላጊውን ትምህርት በየቤታቸው ይቀስማሉ። ከሰባት ዓመት በኋላ ሴቶቹ በቤት ውስጥ ተገልለው እንዲቀሩ ይደረግና አብዛኛውን ጊዜ በእናታቸው አማካይነት የባልትናውን ትምህርት መከታተል ይቀጥላሉ። ከ7 እስከ 16 ዓመት የሚሆናቸው ወንዶች አቴናውያን ግን ወደተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመሄድ የተለያዩ ትምህርቶችን፣ ለምሳሌ ሙዚቃ፣ ስነጽሑፍ፣ የሰውነት ማጐልመሻ፣ ወዘተ ይማራሉ። የተቀረጸ ካሪኩለም አልነበረም። አቴናዊው ተማሪ የፈለገውን የትምህርት ዓይነት በፈለገው ትምህርት ቤት፣ መምህሩ እግር ስር ቁጭ ብሎ ይቀስማል። እነኚህ በአቴንስ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች በመንግስት ስር ቢሆኑም የግል ትምህርት ቤት ባህርይም ነበራቸው። የትምህርቱን ወጪ የሚሸፍነው የተማሪው ወላጅ ሲሆን ትምህርት ቤቶቹ ሳምንቱን ሙሉ ክፍት ነበሩ። ቅጣት (ግርፊያ) በአቴንስ ትምህርት ቤቶች የተለመደ ነበር። ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ወጣት አቴናውያን ‹‹ፔዳጐ›› በመባል የሚታወቁ አጃቢ ባሮች/ባሪያዎች ነበሯቸው።

 ከ16 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ወንድ አቴናውያን ትምህርታቸውን የሚከታተሉት ጂምናዚየም በሚባል ትምህርት ቤት ነበር። ይህ ትምህርት ቤት የመንግስት ድጋፍ የነበረውና በአመዛኙ የሰውነት ማጐልማሻ ትምህርት የሚሰጥበት ነው። በዚህ ትምህርት ቤት ምንም ዓይነት የጦር ትምህርት አይሰጥም።

 አንድ አቴናዊ ወጣት 18 ዓመት ሲሞላው ስሙ በዜጐች መዝገብ ላይ ከመስፈሩ በፊት የሚከተለውን ቃለ-መሃላ ይገባል።

 የተባረኩ እጆቼን ላላረክስ፣ ባልንጀሮቼንም ላልከዳ፣ ለህዝብ ንብረትና ለቤተመቅደሶች ክብር፣ ከወገኖቼ ጋርም ሆነ ብቻዬን ልዋደቅ፣ ከአባቶቼ የተረከብኩትን ሀገር፣ ምንም ሳላስደፍር አስፋፍቼና አበልጽጌ፣ ለመጪው ትውልድ ላስረክብ፣ የፀደቁትንና ወደፊትም ህዝቡ የሚያፀድቃቸውን የሀገሬን ህጐች ላከብርና ላስከብር፣ አይገሰሴነታቸውን ለማረጋገጥ ህግ አዋኪንና ህግ ደፋሪን ከወገኖቼ ጋርም ሆነ ብቻዬን ልታገል ቃል እገባለሁ።

 ይህ ግሩም የሆነ ቃለ-መሃላ የአቴንስ የትምህርት ስርዓት በባህርይው ማህበራዊ፣ ሰላማዊና ግብረገብነት የሰፈነበት እንደነበር ያመለክታል። በሌላ አነጋገር ግብረገብነት፣ ታማኝነት፣ ወገናዊነት (ማህበራዊነት)፣ ጀግንነትና ህግ አክባሪነት የአቴናውያን ክቡር እሴቶች ነበሩ።

ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 300 ዓ.ዓ ድረስ አቴንስ የዓለም የትምህርት ማዕከል ነበረች። የሮማው ቄሳር ጀስቲኒያን በአቴንስ የፍልስፍና ትምህርት እንዳይሰጥ እስካገደበት እስከ 529 ዓ.ም ድረስ፤ አብዛኞቹ የሮማ ነገስታት፣ ሮማውያን ወደ አቴንስ ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀስሙ ያበረታቱ ነበር።

የግሪክ ስልጣኔ በሮማውያን ወረራ ሲደመሰስ፣ በፍርስራሹ ላይ የሮማ የቄሳር ግዛት ተመሰረተ። አብሮትም የሮማ የትምህርት ስርዓት ብቅ አለ። ይሁን እንጂ የሮማ የትምህርት ስርዓት ራሱን የቻለ ወጥ የትምህርት ስርዓት አልነበረም። የሮማውያን መምህራን ግሪኮች ሰለነበሩ የትምህርቱም ስርዓት ከግሪኮች የተኮረጀ ነበር። ሮማውያን ያሻሻሉት ነገር ቢኖር የዳንስና የጅምናስቲክ ትምህርቶችን በማስቀረት ‹‹የንግግር ችሎታ ማዳበሪያ›› ወይንም ‹‹አንደበተ ርቱዕነት›› (ኦራቶሪ) የተሰኘ የትምህርት መስክ መፍጠራቸው ነው።

 ከሰሜን በፈለሱት የተለያዩ የጀርመን ጐሳዎች ወረራ የሮማ ቄሳራዊ ግዛት ሲፈራርስ ከረዥምና አዝጋሚ የለውጥ ሂደት በኋላ በክርስትና ሃይማናት ላይ የተመሰረተ የትምህርት ስርዓት ብቅ አለ። ይህ ደግሞ በተራው በመካከለኛው ዘመን የትምህርት ስርዓት ተረማምዶ አሁን አለንበት የኢንተርኔት ዘመን ድረስ፣ ትምህርት ባልተቋረጠና እጅግ አዝጋሚ በሆነ፤ ኋላ ግን እጅግ ፈጣን በሆነ ሂደት ውስጥ አልፏል። ሂደቱም የሚቀጥል ነው።

ትምህርት በዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ በዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ማስተማር ክቡር ከሆኑት ሙያዎች አንዱ ነው። ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ የወደፊት ትልሙን ለመወሰን የሚችለው በነደፈው የትምህርት ስርዓተ ባህርይና በመምህራኑ ጥራት ነው። የትምህርትን ጥቅም ያልተረዳና በሀገሩ እየተገነባ በሚገኘው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን የማይሻ ዜጋን ማስተማር እጅግ አታካች ነው። በዚህ ላይ ብዙ አብነቶችን በማንሳት ብዙ ልንወያይ እንችላለን።

መልካም የትምህርት ፍልስፍናን የሰነቀ መምህር ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች ጋር ማለፊያ መስተጋብር ሊኖረው ከመቻሉ ባሻገር ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልሶች አሉት፡-

 • በዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ የትምህርት ተቋማት የመኖራቸው ምክንያት ምንድን ነው?

• የትምህርት ዘርፍ ሚና ምን መሆን አለበት? የእውቀትና የክህሎት ፋይዳስ ምን ድረስ ነው? • የትኛው ዓይነት እውቀት ወይንም ክህሎት ነው የበለጠ ጥቅም ያለው?

 • ተማሪዎች ሊያገኙት የሚገባው ነፃነት እስከምን ድረስ መሆን ይኖርበታል?

• ከስነስርዓት ጋር የተያያዘው ዋነኛው ችግር የትኛው ነው?

• ከወላጆች ጋር ሊኖረኝ የሚገባው ግንኙነትስ ምን መምሰል ይኖርበታል?

• ከትምህርት ክፍል ውጭ ለተማሪዎቼ ያለኝ ሃላፊነት እስከምን ድረስ ነው?

• በክፍል ውስጥ የሚታየውን የተማሪዎች ችሎታ መበላለጥ ለማስተካከል ልከተለው የሚገባው ሰልት ምን መሆን ይኖርበታል?

 በእርግጥ ለእነኚህ ጥያቄዎች ሁሉ አዎንታዊ መልስ የሚሰጥ መምህር በቀላሉና በብዛት ማግኘት የዋዛ ነገር አይደለም።

 በመሰረቱ ትምህርት በማንኛውም የሰለጠነ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ ተቋም ነው። ነገር ግን የትምህርት ማህበራዊ ፋይዳ በሁሉም ህብረተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ አይደለም። የትምህርት ስርዓት መርሆዎችና የመጨረሻ ግቦች ከተዘረጋው ማህበራዊ ስርዓት ዓላማና ፍልስፍና የሚመነጩ ናቸው። እንደሚታወቀው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በዜጎች እኩል ነፃነትና መብት ላይ የተመሰረተ ነው። በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በሙያ፣ በሃብት፣ በስልጣን፣ ወዘተ ላይ የተመሰረቱ ልዩነቶች የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫዎች አይደሉም። እዚህ ላይ፣ እነኚህ ልዩነቶች የሉም ማለት ሳይሆን ለዕለት ተለት የኑሮ ዘይቤ የገረሩ የመለያያ ምክንያቶች አይደሉም ለማለት ነው። ይልቁንም በዜጎች እኩልነት ላይ ለተመሰረተው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሁለት ዋና ዋና የመገለጫ ባህርያት የህግ ልዕልና እና የትምህርት ፍትሃዊነት ናቸው።

የአስተሳሰብ፣ የሃይማኖት፣ የሙያና የመደራጀት ነፃነትን አይገሰሴነት ለማረጋገጥና ለማጐልበት፣ ትምህርት እጅግ ወሳኝ ድርሻ አለው። በመሆኑም በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የትምህርት ማህበራዊ ፋይዳ የተለያዩ ዜጎች ወይንም የእነርሱ ስብስቦች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ማህበራዊ ነፃነት እውን ማድረግ፣ ዜጎችም ይህንኑ በውል ተገንዝበው ለነፃነት ልዕልና የየበኩላቸውን ንቁ አስተዋጽኦ በማድረግ መሰረቱ ይበልጥ ጽኑ፣ ጥርጊያውም የተሻለና ደልዳላ እንዲሆን ማስቻል ነው።

 በሌላ በኩል የሶሻሊስት/የኮሚኒስት ስርዓት ተከታይ በሆኑ/ በነበሩ ሀገሮች የትምህርት ዋና ትኩረት የመንግስትን የበላይነት ማረጋገጥና ይህንኑ እየሰበኩ ማጽናት ነው። የኮሚኒስት ፓርቲ ስልጣን ላይ ባለበት/በነበረበት ሀገር ውሳኔዎችን ‹‹ለምን?›› ብሎ መርምሮ አቋም መውሰድ ሳይሆን ‹‹አሜን›› ብሎ መቀበል የግድ ነው። የህፃናት ትምህርትም የተቃኘው በዚህ መሪ ሃሳብ ላይ ነው። ይህ ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ትምህርት ካለው ዓላማ በእጅጉ የተለየ ነው።

 በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመንግስት አስተዳደር አመርቂ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው የተማረ ህዝብ ሲኖር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለዜጐች የሚቀርበው የትምህርት ዓይነትም ለመልካም አስተዳደርና በጐ ውጤቱ የማይናቅ ድርሻ አለው። ህፃናትና ወጣቶች በራሳቸው የሚያስቡና ለችግሮች መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ ንቁ ዜጎች እንዲሆኑ ከማስቻል ይልቅ ትዕዛዝ ብቻ የሚቀበሉ ‹‹የአቤት – ወዴት ትውልድ›› አባላት አድርጐ መቅረጹ የኋላ ኋላ ውጤቱ ራሱን ማስተዳደር የማይችል አስቦ የሚፈጽም ሳይሆን ትዕዛዝ የሚጠባበቅ ዜጋ ማፍራት ይሆናል።

ትምህርትና ዴሞክራሲ በጠንካራ ሰንሰለት በጽኑ የተቆራኙ፣ በሳቢያና በውጤት የተቆላለፉ ናቸው። ሰፊ ዴሞክራሲ ማለት የተስፋፋ መሰረታዊ ትምህርት፤ በትክክለኛው መንገድ የተቃኘና የተስፋፋ ትምህርት ማለት ደግሞ የተንሰራፋ ዴሞክራሲ ማለት ነው።

ይሁን እንጂ ማንኛውም ዓይነት ትምህርት የዴሞክራሲ ዓላማዎችን የማያበለጽግ ነው ማለት አይደለም። በታሪክ ተደጋግሞ እንደታየው አንዳንድ የትምህርት ስርዓት የዴሞክራሲ ሂደትን የሚያከስምና ዓላማዎቹን የሚያመክን ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ትምህርት ‹‹ባለብዙ ሎሌ ጌታ ነው›› የሚባለው። በአጭሩ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ትምህርት ለዴሞክራሲ የሚያገለግል መሳሪያ ነው።

 የትምህርት ፍልስፍና እና መምህሩ

 ጆርጅ ዊላርድ የተባለ ምሁር ‹‹አን ኢንትሮዳክሽን ቱ ዘ ስተዲ ኦፍ ኤጁኬሽን›› በተባለ መጽሐፉ በመምህርና በትምህርት ፍልስፍና መካከል ስላለው ወሳኝ ግንኙነት የሚከተሉትን ቁምነገሮች ያስቀምጣል።

 አንድ እጩ መምህር ስለ ትምህርት ያለውን ፍልስፍና ማዳበር የሚጀምረው ገና በስልጠና ተቋም (በኮሌጅ ወይንም በዩኒቨርሲቲ) ሳለ ነው። እጩ መምህሩ ስለ ትምህርት ያለው ፍልስፍና ወደፊት ምን ዓይነት መምህር እንደሚሆን ለመወሰን ይረዳዋል። ለማንኛውም መምህር እጅግ ጠቃሚውና አስፈላጊው ነገር እንደ መምህርነቱ ስለ ትምህርቱ ስርዓትና ስለ ማስተማር ሙያ ችግሮች፣ ከዚያም አልፎ ስለ ህይወት ያለው አመለካከት ነው። በዚህ ረገድ የሚኖር የአመለካከት ልዩነት አንዳንድ መምህራንን የለውጥ ሞተሮች፣ ሌሎችን ደግሞ ተራ፣ ግልብና የቸከ (‹‹ሩቲን የሆነ››) አስተሳሰብ አነብናቢዎች ሊያደርጋቸው ይችላል። ለእያንዳንዱ የትምህርት ዘርፍ የሚኖረው አመለካከት እንኳ እንደየመምህሩ የትምህርት ፍልስፍና የተለያየ ነው። አንዳንድ መምህራን ትምህርትን በየዲሲኘሊኑ ወይንም በየትምህርት ዘርፉ ተከፋፍሎ እንደሚቀርብና በተማሪዎች ዘንድ መጠናት እንዳለበት የአእምሮ ሃብት ወይንም ቅርስ አድርገው ይወስዱታል። ሌሎች ደግሞ የትምህርት ጥቅሙ የቀደመው የዕውቀት ቅርስ የአሁኑን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ ለመረዳትና መጪውንም በአግባቡ ለመተንበይ እማስቻሉ ላይ ነው የሚል እምነት አላቸው። ዊላርድ እንደሚለው፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ በክፍል ውስጥ የሚከሰትን የስነ ስርዓት ጉድለት በአግባቡ የመያዝና ያለመያዝ ችሎታ፣ ከዚህም አለፍ ሲል፣ አንዳንድ መምህራን በክፍል ውስጥ የትምህርቱን ዓይነት ሲያስተምሩ ሌሎቹ ግን ተማሪዎቹን የማስተማራቸው ጉዳይ፣ መምህራን ለትምህርት ፍልስፍና ካላቸው የአመለካከት ልዩነት የሚነሳ ነው››።

 በአጠቃላይ የመምህሩ የትምህርት ፍልስፍና ለህይወት ካለው ግምት ባሻገር ለማህበራዊ እሴቶች ከሚሰጠው ትርጉም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ጠንከር ባለ የምሁራን አነጋገር ለገንዘብ ሲሉ ማስተማር ወይንም ሌላ አማራጭ ስላጡ ብቻ መምህር መሆን ለህይወት ካለ ደካማ ፍልስፍና የሚመነጭ ነው ይባላል። ነገር ግን በቂ የስራ እድል በሌለበት ድሃ ሀገር ይህን ፍልስፍና በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ አቀበት መሆኑ ግልጽ ነው። ወደ ፍልስፍናው መሄድና በዚያው አግባብ መስራት ግን የተሻለው አማራጭ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top