አድባራተ ጥበብ

የተደባለቀው የማስታወቂያ ስራና ጋዜጠኝነት

ሚዲያ፣ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢ በሌሎች ጫና ስር ሳይወድቅ ራሱን ችሎ እንዲሰራ ያግዘዋል። በተጨማሪም በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠኑ ሞያተኞች ለማደራጀት እንዲችል ይረዳዋል። በሌላ በኩል የንግዱ ማህበረሰብ ምርትና አገልግሎቱን ይዞ ህዝቡ ጋ እንዲደርስ ያስችለዋል። ማስታወቂያ ኢኮኖሚውን በማነቃቃት በኩል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ጥበብ ሆኖ ከቀረበ ደግሞ ባህልን ከማሳደግ አንፃር ድርሻው ይጎላል።

 በተለይም የግል ሚዲያው ለማህበረሰቡ አስፈላጊ መሆኑ ቢታወቅም ራሱን ችሎ ገበያ ውስጥ ለመቆየት በቂ የሆነ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ይህም ህልውናው የሚመሠረተው ከንግዱ ማህበረ-ሰብ በሚገኝ የማስታወቂያና የስፖንሰር ገቢ ላይ በመሆኑ ነው።

 ሚዲያን እንደ ንግድ የሚያስቡ ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ ከሌላው ምርትና አገልግሎት የሚለየው ምርቱን ለሁለት ገበያዎች በመሸጡ ነው። በአንድ በኩል ያዘጋጃቸውን ዜናዎች በማቅረቡ በሌላ በኩል በተመሳሳይ ጊዜ የተደራሹን ቀልብ ምርቶቻቸውን ለሚያስተዋውቁ ድርጅቶች በመሸጥ ይሆናል። ምሁራን እነዚህን የሚዲያ ተቋማት፤ ተደራሹን (audiences) ከመጋረጃ ጀርባ ለማስታወቂያ ባለቤቶች እንደሚያሻሽጡ ይናገራሉ። ሚዲያ ሳቢ የሆነ ዝግጅት ካቀረበ በኋላ ተማርኮ የመጣውን ቀልብ (attention) ለማስታወቂያ ባለቤቶች በተተመነ የድርድር ገንዘብ አሳልፎ ይሸጠዋል። ለምሳሌ የቴሌቪዥን ተመልካች ብንሆን ሳናውቀው ለአንዱ የምርት ወይም አገልግሎት አቅራቢ ተሽጠናል። የሚገርመው ማንም ሰው ማስታወቂያ ለማየት ብሎ ቴሌቪዥኑን አይከፍትም። ስፖንሰሮች ብዙ ማትረፍ በፈለጉ ቁጥር ተጎጂው ከሚዲያው ጠቃሚ ነገር አገኛለሁ ብሎ የሚከታተለው ማህበረሰብ ነው። ስለዚህ ሚዲያው ስርአት ባልጠበቀ መልኩ ተደራሹን ለምርትና ሸቀጥ ማሻሻጫ መድረክ ሊያጋልጠው ይችላል።

ይህ በሚዲያና በስፖንሰሩ መካከል የሚደረግ ግብይት ለሚዲያው አስፈላጊ ቢሆንም የተደራሹን (audiences) መብቶች የሚጋፋ መሆን የለበትም። ተደራሹ በመረጃነት የሚጠቅሙ፤ በአስተማሪነት የሚያሳውቁ እና አዝናኝ የሆኑ ዝግጅቶች እንዲቀርቡለት ይፈልጋል። ማንኛውም የሚዲያ ድርጅት የግልም ሆነ የህዝብ የአገልግሎት ፈቃዱን ከሚመለከተው አካል ሲወስድ እነዚህን ይዘቶች ህግንና ስነምግባርን በተከተለ መልኩ ለማቅረብ ቃል በመግባት እንደሆነ ይታወቃል። ችግሩ በአብዛኛው የሚዲያ ተቋም ዘንድ ይህን የተከበረ የማህበረሰብ አገልግሎት ከምርት ማስታወቂያ ጋር አጣጥሞ መጓዙ ላይ ነው። መደበላለቁ የሚታየው አንድ ጋዜጠኛ መረጃን በእውነት ላይ ተመስርቶ ሲያቀርብ ቆይቶ ድንገት የማያውቀውንና በቂ መረጃ የሌለውን የግለሰብ ምርትና አገልግሎት ወደ ማሞገስና ማሻሻጡ ሲገባ ይሆናል።

 በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአንዳንድ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በጋዜጠኞች አማካኝነት ከትክክለኛ መረጃዎች ጋር ተደባልቀው የሚሰሙ የምርትና የአገልግሎት የማግባቢያ ገለፃዎች፣ የጋዜጠኝነትን ሙያ ያረከሱ በማህበረሰቡ ላይ ህግን የጣሰ በደል የሚያደርሱ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ለምሳሌ የማስታወቂያ አሰራርን ለመቆጣጠር በ2004 የወጣው አዋጅ አንቀፅ 15 ቁጥር 1 ፕሮግራም በእስፖንሰር ተፅእኖ ስር መውደቅ እንደሌለበት ከገለፀ በኋላ አንድ ጋዜጠኛ በፕሮግራሙ ይዘት ውስጥ የእስፖንሰሩን ምርትም ሆነ አገልግሎት እንዲሸጥ ወይም እንዲከራይ መቀስቀስ የለበትም ይላል።

ይሁን እንጂ አንድ ካፊቴሪያ ስፖንሰር በሆነበት ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛው የካፌውን አድራሻ ገልፆ፣ አድማጩን ሄዶ ማኪያቶ እንዲጠጣ፤ ማኪያቶውም ጣፋጭ እንደሆነ ሲጋብዝ መስማት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ታዳሚው የማይፈልገውን አሰልቺ የገበያ መረጃ እንዲከታተል ከማስገደዱ ባሻገር ባለምርቱ አግባብ የሌለው ጥቅም እንዲያገኝ ያደርጋል።

ጋዜጠኝነት የተከበረ ሙያ ነው። መረጃ በእውነት ላይ ተመስርቶ ይቀርባል። ከጋዜጠኛው ይህን ማረጋገጥ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው “ከእንቶኔ የእንጨት ስራ ድርጅት የሚገዛ አልጋ ጥንካሬው ወደር የለውም። ከልጅ ልጅ ይተላለፋል” ብሎ መስበክ ከጀመረ ነገሩን ሁሉ አበላሸ ማለት ነው። በማስታወቂያና በጋዜጠኛነት ስራ መካከል ድንበር መበጀት አለበት የሚባለው ለእዚህ ነው። አንድ የሚዲያ ድርጅት ፕሮግራም በሚያቀርብበት ጊዜ ማስታወቂያ ለማስነገር የተፈቀደለት ሰአት አለ። በዚህ ሠዓት ስለሚተዋወቀው ምርትም ሆነ አገልግሎት መነገር የሚገባው ቀደም ብሎ በስፖንሰር ድርጅቱ ወይም በማስታወቂያ ስራ ድርጅት የተዘጋጀ እንጂ ጋዜጠኛው በፕሮግራም መሃከል ራሱ ስለ ምርቶቹ ማስተዋወቅ በህግም በስነምግባርም አይፈቀድለትም። ስነምግባሩ ተጥሶ የምናገኘው በተለይ የእግር ኳስ ስፖርትን በቀጥታ በሚያስተላልፉ የኤፍ ኤም ሚዲያ ተቋማት ፕሮግራም ላይ ነው። ጋዜጠኛው ጎል መግባቱ እስኪያመልጠው ድረስ በማስታወቂያ መንገር ሲጠመድ እናያለን። በህጉ በእንደዚህ አይነት ፕሮግራሞች ማስታወቂያ መቅረብ ያለበት በጫዋታው መጀመሪያ፤ በዕረፍት ሰአትና ጫዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው። በውጭ ሀገር የጫዋታ ፕሮግራሞች ላይ ይህን እናያለን። ያለአግባብ ገንዘብ ለማሰባሰብ በማለም የሚደረግ አካሄድ ህዝቡን ከተመሳሳይ ፕሮግራሞች ያርቃል።

በመሆኑም የማስታወቂያ ስራ በጥንቃቄ ካልተመራ ሚዲያውን ከሚጠበቅበት ዋና አገልግሎት በማሳት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል።

 መጠኑንና ስርአቱን ጠብቆ በሚቀርብ ማስታወቂያ ላይ ተመልካቾች ወይም አድማጮች ብዙ ቅሬታ ያላቸው አይመስልም። አስፈላጊነቱ ገብቷቸው ለመታገስ የሚችሉ ብዙ ናቸው። ይህን ትዕግስትን የሚፈታተን የማስታወቂያ አቀራረብ በመጀመሪያ የሚዲያ ድርጅቱን ይጎዳል ምክንያቱም ተመልካች ወይም አድማጭ ጣቢያ ለመቀየር ይገደዳል። በተጨማሪም አድማጩና ተመልካቹ በምርቱ ላይ አትኩሮት እንዳያሳድር በማድረግ የስፖንሰሩን ልፋት መና ሊያስቀር ይችላል።

 ብዙዎቹ የህግና የስነምግባር መተላለፎች የሚከሰቱት ሆን ተብሎ ባይሆንም፤ የህግና የስነምገባር መተላለፎች መታረም አለባቸው። ማንም ጋዜጠኛ ሆነ የሚዲያ ተቋም የሀገሪቱን የማስታወቂያ የአዋጅ ህግጋትና ድንጋጌዎች በሚገባ አውቆ መስራት ይጠበቅበታል። ህግ አስከባሪው ሳታውቅ ነው የተላለፍከው ብሎ ማንንም እንደማያልፍ ሊሰመርበት ይገባል። በሚዲያ ተቋማት የሚሰጡ ፈቃዶች ሚዲያ ህዝብን እንዲያገለግል እንጂ ማስታወቂያ አስነጋሪው በህዝብ ያለአግባብ እንዲገለገል አለመሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም ህግ ለማስጠበቅ ሃላፊነት የተሰጠው አካል ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲባል በጋዜጠኝነትና በማስታወቂያ መካከል የተፈጠረውን ቅጥ ያጣ መደበላለቅ ማጥራት ይጠበቅበታል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top