አድባራተ ጥበብ

የቋንቋ የጽሑፍ የሒሳብ እና የገንዘብ መንስዔ በፍንጃል

(ክፍል ሁለት)

ሂሳብ

ጽሑፍ የአስተዳደርን ችግር በከፊል ብቻ ነበር የቀረፈ። ጽሑፍ ብቻውን ለሂሳብ ስሌት አያገለግልም፣ ስለሆነም የሂሳብ ቀመር ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። የሰው ልጅ አዳኝ እፅዋት ሰብሳቢ በነበረበት ዘመን ብዙ የሂሳብ ስሌት ጣጣ አይገጥመውም ነበር። በምድር ውስጥ ያሉ ስራ ስሮችንም ሆነ በዛፍ ላይ የተንዠረገጉ ፍሬዎችን በሜዳ ላይ ውርውር የሚሉ ሚዳቆዎችን ጥንቸሎችን ቁጥር ማስላት አያሻውም ነበር። የሚያስፈልገውን ያህል አድኖ ሰብስቦ ወደ ቤተሰቡ መጓዝ ነበር ቁም ነገሩ።

የሰው ልጅ በግብርና ላይ ከተሰማራ በኋላ ግን የሚያሰላው ተግባር እየበዛ መጣ፤ ስንት ማሳ ስንት ጎተራ፣ ስንት ዓይነት እህል፣ ስንት በግ በሬ ወዘተ፣ ብሎ ማስላት ጀመረ። ቁጥር ስሌት የሕልውና ግብዓትነት ሚናው እየጎላ ሄደ። በዚያን ወቅት ሂሳብ ለሰው ልጅ አዕምሮ እንግዳ ነበር፤ እንቅፋትነቱም እየከፋ እየጠና መጣ።በተለይ ከግብርና አብዮት ጋር ተዳምሮ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ የሂሳብ አስፈላጊነትም እየጎላ መጣ።

 ጠላቴን ለማጥቃት ስንት ወታደር ያሻኛል፣ ለወታደሩስ ልብስ እና ጉርስ ስንት ገንዘብ ያሻል፣ ስንት ግብር የሚከፍል ሕዝብ አለኝ፣ መንግሥቴን ለማስተዳደር እና እኔም ከነቤተሰቦቼ ተንደላቅቄ ለመኖር ስንት ገንዘብ ያስፈልገኛል፣ ከግዛቴ ሕዝብ ስንት ገንዘብ ልሰብስብ፣ በእያንዳንዱ አባል ላይ ስንት ግብር ልጣል፣ የመሰለ ሂሳብ የሚያሻ አስተዳደር ተገነባ። ይህን ሁሉ ውስብስብ ስሌት እንደ ቋት ሆኖ የሚያገለግል አንጎል (ጭንቅላት) የለም። የግድ የውጭ እገዛ ያሻል። ከሰው አካል ውስጥ ካለ አንጎል በተጨማሪ ከአካሉ ውጭ የሆነ የስሌት የመረጃ ክምችት ቋት አስፈለገ።

 የመጀመሪያ ጽሑፍ ከሂሳብ ጋር የተዛመደ በቁጥር ላይ ያነጣጠረ፣ ያተኮረ ነበር ይባላል። ከዚያም ሳምራውያን ቁጥርን የሚወክሉ ምልክቶችን በሸክላ ላይ ስለው (ስዕል) የሂሳብ ማቀነባበሪያ አደረጓቸው፣ ምልክቶችም የሚወክሉ 1, 10, 60, 600, 3600, 36,000 ነበር። እነኝህን ምልክቶች በማቀናጀት ሂሳብ ማስላት ይቻላል። ለምሳሌ

123

456

789

0

622 ለማስላት አንድ የስድስት መቶን፣ ሁለት የአሥርን እና ሁለት፣ የአንድን ወኪል (ስዕል/ ቅርፅ) በማቀናጀት ነበር። በታሪክ ሂደት ይህ ስድስትን (6) መሠረት ያደረገ ስሌት፣ ቅርስ ጥሎልን አልፏል። አንድ ደቂቃ 60 ሰኮንድ ነው፣ አንድ ሰዓት 60 ደቂቃ ነው፣ አንድ ቀን 24 ሰዓት ነው፣ የክብ ልክ 360 ዲግሪ ነው (3600)፣ 12 ኢንች አንድ ጫማ (ፉት)፣ የአሥራ ሁለት ጥንድ አንድ ደርዘን ነው፣ ወዘተ።

 ከዚህ ለየት ያለ የሂሳብ ስሌትም በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ተሰናድቶ ነበር፤ ያም «አንዲያን ስክሪፕት» በመባል ይታወቃል። የሂሳብ ስሌቱ የተመሠረተ በክር ላይ በተበጁ ቋጠሮዎች እና በክሩ የቀለም ዓይነት ላይ ነበር፤ ስሙም ኪውፑስ ይባላል። በአንድ ክር ላይ ብዙ ቋጠሮዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ቋጠሮችም የተለያዩ ቀለማት ባሏቸው ክሮች ላይ የተገመዱ ሊሆኑ ይችላሉ፣ የክሮችም ቁጥር ብዙ ሊሆን ይችላል፣ ወዘተ.

ለምሳሌ አንድ አረንጓዴ ቀለም ባለው ክር ላይ 70 ቋጠሮዎች፣ በጥቁር ክር ላይ 50 ቋጠሮዎች፣ በቀይ ክር ላይ 100 ቋጠሮዎች ቢኖሩ እና የአንድ አረንጓዴ ክር ቋጠሮ ዋጋ 10 (አሥር ቢሆን)፣ የአንድ ጥቁር ክር ቋጠሮ ዋጋ 20 (ሃያ) ቢሆን እና የአንድ ቀይ ክር ቋጠሮ ዋጋ 100 (አንድ መቶ) ቢሆን፤ አንድ አረንጓዴ፣ አንድ ጥቁር፣ እና አንድ ቀይ ክር ብንወስድ፣ በነኝህ ክሮች ላይ የተመሰረተው ዋጋ ስሌት ውጤት እንደሚከተለው ነው፤ (70 X 10) + (50X 20) + (100X 100) =700 +1000 + 10,000 = 11,700 (አሥራአንድ ሺ ሰባት መቶ ሆነ ማለት ነው)።የገመዶችን ስብጥር በመቀያየር ብዙ ስሌት ማካሄድ ይቻላል።

 የአእምሮ ውጥረት በጽሑፍ ተቀንሶለት ሰነዶች ከአካል ውጭ የሆኑ የማስታወሻ ቋቶች ሆኑ። ከዚያም ማስታወሻ መያዙ ብቻ ለአስተዳደራዊ ሂደት በቂ ሆኖ አልተገኘም። በቋት ውስጥ የተጠራቀመውን መረጃ (ሰነድ) በተፈለገ ጊዜ ማግኘት በአስተዳደር ውስጥ ያለው ሚና እየጎላ መጣ።

ይህም መረጃውን በሥነ ሥርዓት አዘጋጅቶ ማስቀመጥ ያሻል፣ አሁንም ለዚህ ችግር ምሳሌነት ጽሑፍ ወደጀመረባቸው አካባቢዎች እንመለስ። ሁለት የአካባቢው (ምሥራቅ የሜዲትራንያን ጠረፍ አገር ሰዎች) ተወላጆች ዮሴፍ እና ያዕቆብ በአንድ የስንዴ ማሳ ባለቤትነት ጥያቄ ይካሰሳሉ፣ የእኔ ማሳ ነው የለም የእኔ ማሳ ነው በማለት። ያዕቆብ ማሳውን ከዮሴፍ ገዝቻለሁ ብሎ ነው የሚከራከር፣ ይህም ከክርስቶስ ልደት በፊት 2000 ዓመት ገደማ ነበር እንበል።

ይህን ውዝግብ ለመፍታት ንብረት መዝጋቢው መሥሪያ ቤት በመንግሥት ሰነድ ጠባቂው መሪነት ሰነድ (ጽሑፍ ያለባቸው ሸክላዎች) ከተቀመጠበት ክፍል ይገቡና በሸክላ ላይ የሰፈረውን መረጃ መፈለግ ይጀምራሉ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በሸክላ ላይ የሰፈረውን ማስረጃም ቢያገኙ ከዚያ በኋላ ስለዚሁ ማሳ ሌላ ማስረጃ እንዳለ ወይም እንደሌለ ማረጋገጫ ዘዴ የለም። እነዲሁ በድንገት ሸክላው ተሰባብሮ ከሆነ (ምሳሌ በዝናብ በስብሶ) ያዕቆብ ማሳውን አልገዛውም ብሎ ለመፍረድ ያዳግታል። ገዝቶ ነበር ለማለትም ማስረጃ የለም። ይህንን ተግባር የሚያስተናግድ ሥርዓት መዘርጋቱ ጽሑፍ ከማዘጋጀቱ የከበደ ችግር ሆኖ ተከሰተ።

መረጃን በሥርዓት አስቀምጦ በተፈለገ ጊዜ፣ ጊዜ ሳይፈጅ ለማግኘት የሚያስችል ዘዴ መፍጠር አስፈለገ። አሁን በየመጽሐፍት ቤቶች የምናየው የካታሎግ ሥርዓት መሰል መዘርጋት ያሻል። በዘመናት ለእዚህ ተግባር የሚውሉ ብዙ መሣሪያዎች ተበጅተዋል ለምሳሌ ሰነድ ለማባዛት ፎቶኮፒ የኮምፒውተር አልጎሪዝም ወዘተ። የመንግሥት ሰራተኞችም ሆኑ ሌሎች በተመሳሳይ ተግባር የተሰማሩ ሰዎች፣ ከጽሑፍ ችሎታ በተጨማሪ በካታሎግ በመዝገበ ቃላት በዘመን ሰሌዳዎች በሰንጠረዞች የመጠቀምን ክህሎት ማዳበር ነበረባቸው።

በቢሮክራሲያዊ ተግባር ውስጥ የተለያዩ ተግባራት ተለያይተው ነው የሚያዙ (የሚቀመጡ)። የጋብቻ ሰነዶች፣ የመሬት ባለቤትነት መረጃዎች፣ የልደት መረጃዎች ወዘተ በተለያዩ ቦታዎች በሥርዓት ይቀመጣሉ። በተፈለጉ ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላጥ አርጎ ማውጣት ይቻላል። የዚህ ሥርዓት ተግባር እየተደራረበ እየተሸራረበ ሲመጣ፣ ጉዳዮችን በፋይል በማለያየት ወይም የሰዎችን ተግባር በመወሰን ብቻ የማይፈታ ሆኖ ተገኘ። ያም ለየተግባሩ የተለያዩ ሰዎች ቢመደብም የፋይል ማስቀመጫ በሽዎች የሚቆጠሩ ካቢኔቶች (መደርደሪያዎች) ቢደረደሩም ለችግሩ መፍትሄ መስጠት አልተቻለም።

 ለዚህ ችግር መፍትሄነት የሂሳብ ሚና እየጎላ መጣ። ለዚህ ለየት ያለ የሂሳብ ጽሑፍ ተገኘ። አሥር ምልክቶችን ያዘለ የሂሳብ ስሌት ተፈጠረ። ከ0 ጀምሮ 9፣ ዘጠኝ ላይ የሚቋጭ (1,2,3,4,5,6,7,8 እና 9)። እነኝህ ምልክቶች የአረብ ቁጥሮች በመባል ቢታወቁም እውነቱ የሂንዱስ (Hindus) መሆናቸው ነው። ለነኝህ መስሎች ማዳበሪያ የሚሆኑ ምልክቶች ታክለው ማለት የመደመር (+) የመቀነስ (-) የማባዛት (X) እና የማካፈል (÷)፣ እነኝህ የሂንዲ ግን የአረብ ተብለው የሚታወቁ ምስሎች የሂሳብ መሠረት ሆኑ።

ስለሆነም ከቋንቋ በዘለለ ሁኔታ፣ ከዚያም «አረብኛ» ተናጋሪም ሆነ «ኢስፓኛ» ወይም «ሚሊ» «ኡርዱ» ወዘተ፣ መግባቢያ የሂሳብ ሰነድ እነኝህ ምልክቶች ሆኑ። ሰነዶች በጠቅላላ በነኝህ ምልክቶች ላይ የሚስተናገዱ ሆኑ። ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች ሁሉ በሂሳብ መልክ (በነኝህ ምልክቶች) በመጠቀም መመዝገብ ብሎም መሰራጨት ጀመሩ። ስለሆነም ተግባራት ሁሉ በቁጥር ተተበተቡ። የቁጥሮችን ትርጉም መልእክት የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪ ካለ አስተርጓሚ ሊረዳቸው ይችላል።

 የሂሳብ ሚና እየጎላ ሲሄድ ሂሳብን በሰው አንጎል ማስተናገድ አዳገተ። ምንም የጽሕፈት ዘዴ ደብዛዛ ሆኖ ቢጀመርም፣ በዘመናችን ከተራ ጽሕፈት በኋላ የመጣው «የሂሳብ ዘዴ» የዓለም ሕዝቦች መግባቢያ ቋንቋ ሆኗል። ይህ የመግባቢያ ዘዴ፣ «ቋንቋ» በፊደላት ቅርጽ አይገረገርም፣ በቁጥር ማስላት የዓለም ሕዝቦች ቋንቋ ሆኗል።

 አንዳንድ የሂሳብ ቅምሮች በሰው ጭንቅላት ብቻ ሊተነተኑ አይችሉም፣ ስለሆነም ከሰው አንጎል ውጭ የሆነ ሌላ መሣሪያ ኮምፒዩተር ተፈብርኳል። እያንዳንዱ ጥቃቅን መረጃ ከመቅጽበት ከሌሎች ተመሳሳይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ጥቃቅን መረጃዎች ጋር ተቀናጅቶ፣ ተሰልቶ፣ ተዘጋጅቶ፣ ለማሰብ በሚያዳግት ፍጥነት እና ሂደት ለግንዛቤ ማዳበሪያነት ይቀርባል። ብዙ የእውቀት መስኮች በሂሳብ ብቻ የሚተረጎሙ ሆነዋል፣ ምሳሌ ፊዚክስ፣ ምህንድስና ወዘተ መግባባት የሚቻለው ከመደበኛ ቋንቋ ውጭ ነው፣ በሂሳብ ስሌት ብቻ።

 ገንዘብ

በማህበራዊ ትስስር ሂደት በዕቃ ልውውጥ የሚደረገው የመገበያየት ሥርዓት ውስብስብ እየሆነ መጣ፤ ፍላጎት እና ሕዝብ በጨመረ መጠን ውስብስብነቱ እየተባባሰ ሄደ። የቁሳ ቁስ ፍላጎት በጨመረ መጠን፣ የገበያ ሥርዓት እየደራ፣ መገበያየት እየተጧጧፈ መጣ። በዚህ ደረጃ የግድ የመገበያያ ገንዘብ ማበጀት አስፈላጊነቱን መገመት ይቻላል።

 ይህን ዓይነት ሥርዓት (የልውውጥ ሥርዓት) ለማስተናገድ ስለተሳነ የዕቃ ልውውጥሥርዓቱ ከስሞ በሌላ በተሻለ ሥርዓት ተተካ። ገንዘብ የሚባል በእምነት ላይ የተመሠረተ መሰናዶ ተበጀ። ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የእምነት ተገዥ ነው። በመጀመሪያ ሰጭም ገዥም ዋጋ አሏቸው ብለው በገመቷቸው እንደ ዛጎል ፍራ ፍሬ አሞሌ ጨው እንደ ገንዘብ ተጠቅመው ይገበያዩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ለመገበያያነት አንዲያገለግል በልዩ መልክ የግብይይት ቁስ በገንዘብ መልክ ተቀረፀ።

ገንዘብ በእምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንደገና ልዳስሰው። አንድ ግለሰብ፣ በወረቀት መልክ የተሠራን ብር ተቀብሎ አንድ በግ ለማያውቀው ሰው ያስረክባል (ይሸጣል)። ያ በግ የሸጠ ግለሰብ፣ በጉን የሸጠበትን ገንዘብ (ገንዘብ የተባለ ወረቀት) ወስዶ ሱቅ ገብቶ ጫማ ሊገዛ ቢፈልግ እና ጫማ ሻጩ ያን ወረቀት አልቀበልህም ቢለው፣ በግ ሻጩ፣ ገንዘብ በተባለው ወረቀት እምነት ያጣል።ከዚያ በኋላ ይህ ግለሰብ በግ አስረክቦ ወረቀት አይወስድም። እምነት ካጣበት ‹‹ወረቀቱ›› ወረቀት እንጂ ገንዘብ አይሆንም። ይህ ስለሆነም ነው በገነዘብ ልውውጥ ገበያ በእምነት ላይ ነው የተመሠረተ የሚባለው።

የገንዘብ አስፈላጊነት

 ገንዘብ ከብረት አስተኔ ከመበጀቱ (ከመሠራቱ) በፊት የነበሩ መገባብያዎች ነበሩ፣ ለምሳሌ አሞሌ ጨው ወይም ዛጎል። አሞሌ ጨው ለምግብ ግብዓት ይሆናል ዛጎል ደግሞ ከባህር ዳር ነው የሚገኝ። ለማኻል አገር ሰው ሁለቱ መገባብያዎች ብርቅዬ ሊሆኑ ይችላሉ ለዚያም ይሆናል የንግድ መለዋወጫ ተግባር እንዲውል የተደረገ።

 ከብረት አስተኔ (መዳብ፣ ብር፣ ወርቅ) የሚቀረፁም የገንዘብ ዓይነቶች ከተቀረፁበት ብረት አስተኔ ዋጋ ጋር አይመጣጠኑም። የብረት አስተኔዎች በገንዘብ መልክ ሲቀረፁ የሚያገኘው የገንዘብ አቅም ከተሠሩበት የብረት አስተኔ ዋጋ (የመግዛት አቅሙ) ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍ ያለ ነው፣ በማኻላቸው ብዙ ልዩነት አላቸው። ለገንዘቡ የሚሰጠው ዋጋ ከወረቀት የተሠራ ገንዘብም እንዲሁ ነው። ገንዘቡ የታተመበት ወረቀት ሆነ ገንዘቡን ለመሥራት የፈሰሰው ጉልበት፣ ቀለም፣ ወዘተ. ከዋጋው ጋር አይመጣጠንም፣ ለገንዘቡ የሚሰጠው ዋጋ በጣም ከፍ ያለ ነው። አንድ ብር ለመሥራት የተጠቀምንበት ወረቀት መቶ ብር ለማተም ከምንጠቀምበት ወረቀት ጋር ሲነፃፀር ልዩነታቸው ብዙ አይደለም፣ ቢለያዩም በመቶ እጅ አይለያዩም፣ ሰለሆነም የገንዘቡን ዋጋ ከፍ ያደረገው እምነት እንጂ የታተመበት ወጭ ስሌት አይደለም።

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ጠቅለል ብሎ ሲታይ ገንዘብ መተማመን ነው፣ በሓሳባዊ ታአማኒነት ላይ ነው የተመሠረተ። ገንዘቡ እንደምልክት ነው የሚያገለግል፣ ዋጋው በእምነት ላይ ነው የቆመ። ይህ ዓይነት እምነት እንዴት ተመሠረተ? ብሎ መጠየቅ ያሻል።

 በአንድምታ ተምሳሌነት ብንጓዝ እኔ ፍየሌን ለምን በ40 ዛጎል ለወጥኩ (ቀየርኩ) ብዬ ራሴን ብጠይቅ መልሱ ጎረቤቴ የኔን ዓይነት ፍየል በ40 ዛጎል ስለለወጠ (ስለሸጠ) ሊሆን ይችላል ። ለልብስ መሸመኛ የሚሆን ጥጥ ፍየሌን በሸጥኩበት ዛጎል ለመግዛት ስለቻልኩ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም በዛጎል ስለሚገበያዩ እኔስ በዛጎል ብገበያይ ምን እጎዳለሁ? ሊሆንም ይችላል መልሱ። በተጨማሪ እግዚአብሔር ለመረጠው ንጉሥም ግብር የሚከፈል በዛጎል ነው፣ ንጉሡም ለወታደሮች ደመወዝ የሚከፍል በዛጎል ነው፣ እሱ ካመነበት እኔስ ለምን አላምንበትም ሊሆንም ይችላል። ስለሆነም የዛጎል ገንዘብነት በሁሉም አካባቢ ተአማኒነትን ስለተጎናጸፈ አኔም «የዛጎልን ገንዘብነት» ተቀብያለሁ ብዬ ወደ ሌላ የዕለት ተዕለት ተግባር ልሰማራ እችላለሁ።

 በዘመናችን ያለውን የዓለም መገበያያ የሆነውን የአሜሪካን ዶላር በምሳሌነት እንውሰድ። የገንዘብ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ፣ ምንም ልቅ አረንጓዴ ቀለም ባለው ወረቀት የአንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምስል እና የገንዘብ አስተዳደርን የሚመራው የበላይ ሹም በአንድ በኩል ቢፈርምም፣ በሌላው ገጽ የተጻፈው መለኮታዊ እምነት ነው። ከዚያ የበለጠ አስተማማኝ የሆነ ጉዳይ የለም።

በተጨማሪ የገንዘቡ ተአማኒነት ገንዘቡን ባሳተመው መንግሥት የፖለቲካ ጥንካሬ ላይ የተመሠረተ ነው። በዚህ ምክንያት በዘመናችን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሲያነጥስ እና ሰውነቱ ሲናጥ፣ የዶላርም ዋጋ አብሮ ይናጣል ይባላል። በአንዳንድ የቅርብ ምሥራቅ አገሮች ከክርስቶስ ልደት በፊት 3,000 ዓመት ገደማ ገብስ እንደገንዘብ ተወሰዶ ነበር (አንድ ማሰሮ፣ ሁለት ማሰሮ እየተባለ) ። ጽሑፍ የአስተዳደር አንቃራዎች ለመቅረፍ በተፈጠረበት ወቅት፣ ገብስም የገበያን ልውውጥ ውስብስብነት ለመግታት እንዲያገለግል ሆኖ በሜዲትራንያን ምሥራቅ ዳርቻ በተለይ በባቢሎን አካባቢ ባሉ አገሮች መሠረታዊ የመገበያያ ቁስ (ቅርስ) ነበር።

በባቢሎን አካባቢ የገብስ መጠን መለኪያ እቃዎች በብዛት እየተበጁ (እየተሠሩ) የሁሉም ኣከባቢ እንደ ንግድ መለዋወጫ የሚያገለግሉ የገብስ መጠን እኩል መሆኑ እንዲታመን እንዲረጋገጥ፣ ብዙ ጥረት ተደርጓል። ጥረቱም ተሳክቶ የትኛውም ዓይነት ክፍያ በገብስ ይስተናገድ ነበር። ለእቃ መግዣነት ብቻ ሳይሆን ለጉልበት (ሥራ) ክፍያ እንዲሁም ደመወዝ የሚከፈል ገብስ በማሰሮ እየተለካ ነበር።

በዚህ ሂደት ጠንካራ እና በሙያው የተካነ ግምበኛ በወር እስከ 5,000 “ማሰሮ ገብስ” ይከፈለው ነበር እንበል። አንድ ግምበኛ ከነቤተሰቡ በወር ያንን ያህል ገብስ ሊመገብ (ሊበላ) አይችልም መጠነ-ብዙ ገብስ ይተርፈዋል። ከምግብ የተረፈውን ገብስ በማሰሮ እየለካ ለሚፈልጋቸው እቃዎች የምግብ ዓይነቶች ለልብስ ፣ ወዘተ. መግዣ ያውለው ነበር። ይህ ሌላ ችግር አስከተለ። ያም ብዙ ገብስ ከቦታ ቦታ ማጋዙ እና በተጨማሪ ገብሱን መስፈሩ (በማሰሮ) ነበር። ቤት ውስጥም ገብስ ሲቀመጥ ሊበሰብስ ወይም በአይጥ ሊበላም ይችላል። የብር አስተኔ የተሠራ ገንዘብ ሊበላ ወይም ሊጠጣ ባይችልም፣ እምነት ከተጣለበት ይህን ዓይነት ችግር ይፈታል፣ አይጥም አይበላውም ዝናብም አያበሰብሰውም። ገንዘብ በመጀመሪያ የተበጀ ከውድ ብረት አስተኔዎች ነበር ለምሳሌ ወርቅ። በመጀመሪያ ገንዘብ ከብረት አስተኔ ሲሠራ፣ የተሠራበትም ቁስ የራሱ የገንዘቡ ዋጋ መጠን እንዲሆን ተደርጎ ነበር።

 በዓለማችን በመጀመሪያ የተበጀው ገንዘብ ከብር ነበር ይባላል።ያም በምሥራቅ ሜዲትራንያን አገሮች አካባቢ ሲሆን የብሩ ክብደት የገንዘብ መጠን መለኪያ ተደርጎ ነበር የተሠራ። ያም አዲስ ገንዘብ «የብር ሸከል» ይባል ነበር። በብሉይ ኪዳን በገንዘብ መገበያየት ሲወሳ፣ ይህን ያህል ብር እንጂ ይህን ያህል «የብር ሸከል» አይልም፣ የብሩ ጠቅላላ ክብደት ነበር ዋጋውን የሚወስነው።

 ዮሴፍን ወንድሞቹ በ20 «የብር ሸከል» ቢሸጡትም፣ ሽያጩ የሚወሳው ብሩ በተቀረፀበት የብረት አስተኔ በ166 ግራም ብር እንደሸጡት ነው። ሁሉም ሳንቲም እኩል መጠን የብር ማዕድን ያለው ሆኖ በሳንቲም መልክ ብር መቅረፅ የተጀመረ ከዚያ በኋላ ነበር። የብሩ (ማዕድን) ክብደቱም 8.33 ግራም ነበር፣ ገንዘቡ የተበጀተበት ብር ክብደት 8.33 ግራም እስከ ሆነ ድረስ ለዘመናት የገንዘቡ ቅርፅ ፋይዳ ቢስ ነበር።

እንደገና በፊት ያወሳነውን ጥያቄ አንስተን ገንዘብ ምንድን ነው? የገንዘብ ዋጋ ከየት የመነጨ ነው? ብንል መልሱ ገንዘብ በሁለት የተንቦራቹ (የተዘረጠጡ) እግሮች ላይ ነው የቆመ፣ አሳባዊ ዋጋ የተላበሰ ቁስ ነው፣ ብሎም የተለያዩ ተግባራትን ለማስፈጸም የሚያስችል ሃብት ነው ብሎ መልስ መስጠት ይቻላል።

 አንደኛው ለመገበያያነት (ንብረት የመለዋወጫ ዘዴ) ማገልገሉ ነው። በገንዘብ ተአማኒነት ላይ ተመሥርቶ ሕክምናን (ጤናን) በገንዘብ መግዛት፣ ለሰላም አስጠባቂ ደመወዝ በገንዘብ ከፍሎ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ፣ ዳኞች ሰይሞ (ቀጥሮ) ፍትህ ማግኘት (ዳኛው ሃቀኛ ከሆነ) ነው። ስለሆነም ገንዘብ ወደ ጤና ወደ ሰላም ወደ ፍትህ ሊመነዘር ይችላል ማለት ነው።

 ሁለተኛው የሕዝቦች የትስስር የግንኙነት ሙጫ (ማጣበቂያ) ሆኖ ማገልገሉ ነው። ሁለት ወይም በዛ ያሉ ሰዎች ገንዘብ በህብረት አዋጥተው አንድ ተግባር ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ፣ ለምሳሌ በቤት ግንባታ አርኪቴክት፣ መሐንዲስ፣ አናጺ፣ ግንበኛ፣ የቀን ሠራተኛ፣ ለሠራተኛ ሻይ በአካባቢ አቅራቢ፣ ንብረት ጠባቂ ዘበኛ፣ ወዘተ፣ ሁሉንም ገንዘብ ያስተሳሥራቸዋል።

ይህም ገንዘብ የማይተዋወቁ ሰዎችን አገናኝቶ በአንድ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ አደረገ ማለት ነው።

ገንዘብ ለብዙ አንዳንዴም በጣም አስደናቂ ለሆነ ተግባር እየዋለ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች ሰርቀው አጭበርብረው ሽፍጠው፣ ያገኙትን ገንዘብ፣ ለቤተ ክርስቲያን መገንቢያነት በከፊል ያውላሉ። ያም ገንዘቡ «ለአንተም ለእኔም ይተርፋል» እንደማለት ይቆጠራል። በዚህ እይታ ገንዘብ ፈርጀ-ብዙ ችግር ፈች፣ እንደ ዘይት የትም ቦታ ሰርስሮ የሚገባ ነው፣ ያንት ያለህ! ያሰኛል።

 በገንዘብ መልክ እኩል መጠን ያሏቸው በከበረ ማዕድን የታነፁ መገበያያዎች የተሠሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ640 ዓመት ገደማ ነበር። ያም በቱርክ አካባቢ ሲሆን፣ ገንዘቡ ሲቀረጽ (ሲሠራ) ሁለት ምልክቶች ነበሩት (በሁለቱ ገጾቹ)። በአንድ ገጽ የነበረው ማዕድን ስንት እንደሚመዝን ሲያረጋግጥ፣ ሌላው ገጽ በማን ትዕዛዝ ያ ገንዘብ እንደተሠራ፣ እንደተሰራጨ ያስረዳ ነበር። በዚህ ዘዴ የተሰጠው መረጃ ገንዘቡን አስተማማኝ ያደርገዋል።

 በተለይ በሮማውያን የተቀረፀው ገንዘብ እስከ ሩቅ ምሥራቅ ድረስ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በዚያም ገንዘብ ያለምንም ችግር የትም ቦታ መገበያየት ተችሎ ነበር። ስለሆነም ሰፊውን ዓለም ያቀራረበው (ያጠጋጋው) አንዱ የንግድ ግንኙነት ሲሆን ማስተሳሰሪያውም ገንዘብ ነበር።

 ገንዘብ ባይቀረፅ እና ግብይት በገብስ በስንዴ በቡና፣ ወዘተ. በአገራችን ቢስተናገድ ኖሮ ስንት ዳውላ ጤፍ ገብስ ስንዴ፣ ስንት ፈረሱላ ቡና ወደ አዲስ አበባ በመንግሥት ግብር መልክ ይጫን ነበር። ከዚያ እየተሰፈረ እንደየማዕረጉ ለዳኛው ለጦር አበጋዙ ለወታደሩ ለአጋፋሪው ይከፈል ነበር። ለዚህ ተግባር ስንት የጭነት ከብት ስንት ጫኚ ስንት እህል ሰፋሪ ያስፈልግ እንደነበረ መገመት ለማንም እያዳግትም። ገንዘብ መቅረፅ ማተም ይህንን ሁሉ ችግር አቃለለ።

 ገንዘብ «የእኛ» እና «የእኔ» የሚባለውን አንድ ያደርጋል፣ የአንድ አገር ሕዝብ የሚጋራው የአንድን አገር ሕዝብ አንድነት ማንፀባረቂያ መሣሪያ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።በዘመናችን ቀስ በቀስ ዓለም በጠቅላላ በአንድ ዓይነት ገንዘብ መገበያየት ጀመረች፣ ያም የአማሪካን ዶላር ነው።

 ገንዘብ በኢትዮጵያ

 ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በአካባቢያችን ከወርቅ እንዲሁም ከብር ተቀርፆ በገንዘብ መጠቀም ተጀምሮ ነበር። በአክሱም ዘመነ መንግሥት ገንዘብ በተግባር ላይ የዋለው ከሦስተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እንደነበረና የአክሱም መንግሥት የራሱን ገንዘብ ከመቅረፁ በፊት በግሪክ አገር አካባቢ በተሰራጩ የግሪክ ገንዘብ በብዛት ይጠቀም እንደነበረ ማስረጃ ተገኝቷል። ይህ የግሪክ ገንዘብ በቀይ ባህር አካባቢ ብዙ ንግድ ይስተናገድበት ነበር።

 አክሱም የራሱን ገንዘብ ማሰራጨት በጀመረበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ከብዙ የአካባቢው ኃያላን መንግሥታት (ሮማ፣ ፋርስ፣ ግሪክ ወዘተ)፣ ጋር የንግድ ግንኙነት ነበራት። ለዚህም ማስረጃ የሆነው የእነኝህ አካባቢ መንግሥታት የገንዘብ ዓይነቶች በአከሱም አካባቢ ስለተገኙ ነው። አክሱም ምንም እንኳን በመጀመሪያ የቀረፀው ከወርቅ የተሠራ ገንዘብ ቢሆንም፣ ወደ ኋላ ዘመን ከብር እንዲሁም ከመዳብ የተቀረፁ የገንዘብ ዓይቶች ነበሩት።

የኢትዮጵያ ነገሥታት የክርስትናን እምነት ከተቀበሉ በኋላ ቀደም ሲል ኮከብ እና ጨረቃ ይታዩበት የነበረው ገንዘብ አንዱ ገፅ ላይ የሚሰፍረው ቅርፅ በመስቀል ተተካ። ገንዘብ የሚቀረፅበትም የወርቅ መጠን ቆስታቲኒያ (ኮስጣንጢኖስ) ገንዘብ ከሚቀረፅበት የወርቅ መጠን ተመሳሳይ ነበር። ገንዘቡ የሚቀረፅበት የወርቅ መጠን ቀደም ብሎ 4.54 ግራም ከዚያም የወርቁ መጠን ወደ 2.5-2.8 ግራም ዝቅ አለ፣ ስፋቱም 15-21 ሚሊሜትር ገደማ ነበር።

በአክሱም ዘመነ መንግሥት በማእከላዊ መንግሥት ለመገበያያነት ያገለግል የነበረው ከወርቅ የተሠራው ገንዘብ፣ የአክሱም መንግሥት የቱን ያህል ኃብታም እና ጠንካራ እንደነበረ.፣ ለዓለም ለማሳወቅ እንደ «ፕሮፓጋንዳ» መሣሪያነት ያገለግል ነበር ተብሎ ይታመናል። የእዚያን ዘመን መንግሥታት ኃያልነታቸው የሚገለጠው በሚያስቀርፁት የገንዘብ ዓይነት ነበር። ከመጠነ ብዙ ወርቅ መገበያያ ያሰቀረፀው ነጉሥ፣ የኃያል መንግሥት መሪ እንደሆነ ይወሰድ ነበር።

 በተጨማሪም በዘመኑ ሰፍኖ የነበረ እምነት (አምልኮት) በቀደመ-ክርስትና የተለያዩ አማልክትን፣ ድህረ-ክርስትና አምላክን ለማሳመኛነት ያገለገለ መሣሪያ እንደነበረም ይገመታል።ቀደም ሲል የካሌብ ፊት ምስል እና ጨረቃ ዓይነት ቅርፅ የሰፈረበት የገንዘብ ዓይነት ነበር፣ ከዚያም ጨረቃ በመስቀል ተተካች።

 ከስምንተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ የአክሱም መንግሥት እየተዳከመ ሄደ፣ የመንግሥቱ ግዛት ከባህር እየራቀ መጣ፣ ቀይ ባህር እንደ ሩቅ ቦታ መታየት ጀመረ። ከዚያ በፊት ገበያ ላይ ውለው የነበሩ የገንዘብ ዓይነቶች ለጥቂት ተጨማሪ ዓመታት ከታዩ በኋላ ደብዛቸው ጠፋ።

ንግዱም ቀዘቀዘ፣ በጠረፍ አካባቢ የነበረው እንቅስቃሴም ቀነሰ። ከዚያም በኋላ በገንዘብ መጠቀም እየመነመነ መጥቶ ወደ ስምንተኛው መዕተ ዓመት አካባቢ ባገር ቤት የተቀረፀ ገንዘብ ስርጭት ከሰመ፣ ድራሹ ጠፋ። ከስምንተኛው ምዕተ ዐመት በኋላ ዋናው የአካባቢ መገበያያ ገንዘብ በመቃዲሾ ሱልጣኖች የተቀረፀው የሞቃዲሹ ገንዘብ የሚባለው ነበር።

 በ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ በኋላ በመጀመሪያ አፄ ዮሐንስ አራተኛ በአንድ በኩል የእሳቸው ምስል «ዮሐንስ ራብዓዊ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» በሌለው ገፅ የይሁዳ አንበሳ ሰንደቅ ዓላማ ተሸክሞ የሚታይበት የብር ገንዘብ ተቀርፆ ነበር። ከዚያም ተመሳሳይ ገንዘብ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ተቀረፀ። ይህም ገንዘብ በ20 ገርሽ (ከቱርክ ቅርሽ የተወረሰ ይመስላል) በአርባ ቤሳ (ከመዳብ የተሠራ ሳንቲም) ይመነዘር ነበር። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ገንዘብ ዓይነቶች መገበያያ ሆነው አገልግለዋል

“በተለይ በሮማውያን የተቀረፀው ገንዘብ እስከ ሩቅ ምሥራቅ ድረስ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በዚያም ገንዘብ ያለምንም ችግር የትም ቦታ መገበያየት ተችሎ ነበር። ስለሆነም ሰፊውን ዓለም ያቀራረበው (ያጠጋጋው) አንዱ የንግድ ግንኙነት ሲሆን ማስተሳሰሪያውም ገንዘብ ነበር።”

መደምደሚያ

ሕያው በሙሉ የሚመሩት ሕይወት በዳረገቻቸው በበራሂ ሰንሰለት መዋቅር ሕግ ተገርግረው ነው። የሰው ልጅ በምን መጠን እንደሚያድግ፣ የት ላይ መኖር እንደሚችል (የብስ)፣ ምን ሙቀት መቋቋም እንደሚችል፣ ወዘተ. በበራሂዎች የሚወስኑ መሠረታዊ የተፈጥሮ ሕጎች ናቸው። ድንች ዘርቶ በቆሎ ማምረት አይቻልም። ከበራሂ ሰንሰለት የሚመነጨውን የህያው አካል ተግባር ባጭር ጊዜ ለመለወጥ አይቻልም። ያ ሊከሰት የሚችለው በዝግመተ ለውጥ ብቻ ነው።

ቋንቋ አንዲሁም ጽሑፍ በሂደት የሰውን ልጅ ከበራሂ ወህኒ ቤት ለመውጣት የበራሂን እግር ብረት ለመስበር አስቻሉት። የሰው ልጅ በከፊል በቋንቋ ብሎም በጽሑፍ ታግዞ በፊት ከነበረው የተለየ ከበራሂ ቁጥጥር ነፃ ሆኖ የራሱን ዓለም ለመፍጠር ቻለ ብሎም እምነቶችን ለማሰራጨት በቃ። በተጨማሪ አዲስ የተከሰተውን እምነት ሰብሮ ለመውጣት እንደ በራሂ እግር-ብረት አስቸጋሪ አይደለም። አዲሱ የተከሰተው እምነት ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊቀያየር ይችላል። ትናንት ሶሽያሊስት የነበረ፣ ዛሬ የጦፈ ካፒታሊስት ሊሆን ይችላል፣ ትናንት ዓለማዊ ዘፋኝ የነበረ፣ ዛሬ ሃይማኖታዊ ሰባኪ ሊሆን ይችላል።

 ለዘመናት በበራሂ ሕጎች ታስሮ ተገርግሮ የነበረን ሥርዓት፣ በዓመታት ውስጥ ለመቀየር ተቻለ። እስኪ እምነት ብሎም ባህልን አስተያየትን እንዴት ባጭር ጊዜ ውስጥ ሊቀየር እንደሚችል ለማብራራት እንድንችል ያገራችንን ገበሬ እንውሰድ። ትላንት ስፓጌቲ ሲያይ ሌላ ነገር መስሎት ይበረግግ የነበረ፣ በንግድ ላይ ተሰማርቶ አዲስ አበባ ከሰፈረ በኋላ፣ ያንን ጠያፍ መሰል ስፓጌቲ፣ በእንጀራ እየጠቀለለ ይጎርሳል። የእኔን እድሜ አከል ግለሰብ ብንወስድ፣ በግርማ መንግሥትህ እያለ ንጉሠ ነገሥት ሲያሞካሽ ያደገ፣ በመኻል እድሜ ላይ ሰፊው ሕዝብ ያሸንፋል ብሎ የዘመረ፣ አሁን «ካፒታሊዝም» ነፃ ገበያ ለእድገት መሠረት ነው ተብሎ ሲሰበክ ይሰማል።

 እንግዲህ በዚህ መንገድ፣ ቋንቋ፣ ጽሕፈት፣ ሂሳብ፣ የሰው ልጅ ኑሮን ቀየሩት፣ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ መተዳደሩ ተገታ፣ በከፊል ነፃ ወጣ። ይህ ይሆን የሰውን ልጅ «ልዩ ፍጡር ነኝ» ለማለት ያበቃው? ጸሑፌን ከመቋጨቴ በፊት «ማርጋሬት ታቸር» የምትባል የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒሰትር የነበረች፣ ሥራ መልቀቋን ለንግሥቲቷ ለማብሰር ልትሄድ ስትል ለሚኒስትሮች ካቢኔ ያለችው እነሆ፤በግርድፉ «የአረጀ የአፈጀ ተረበኛ ዓለም ነው»፣ዘረዘር አርጎ በአንድምታ እይታ ሲታይ «ዓለማችን በሰው ሰራሽ ጽሕፈት፣ በሰው ሰራሽ የሂሳብ ስሌት፣ በሰው ሰራሽ ሥርዓት፣ በልብ ወለድ ተረት፣ የተተበተበች ዓለም ናት» ብሎ መገንዘብ ይቻላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top