ጥበብ እና ባህል

የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሳንካዎችና ጸጋዎች በኢትዮጵያ

(ክፍል ሶስት)

በባለፈው ክፍል አንድ ጽሑፍ እንዲህ ብዬ ነበር “ይህ ጽሑፍ መሠረታዊ ይዘቱ እውቀትን ከማበልጸግ፣ የጋራ ተግባቦትን ከማረጋገጥ፣ የመንፈስ ትስስርንና አገራዊ አንድነት ከማሳካት፣ ሥነምግባራዊ በጎነትንና በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወዘተ ያሉ አገር በቀል እውቀትን ከማጎልመስ አንጻር ባጭሩ ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ ከማድረግ አኳያ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እያደረገው ያለውን መልካም አስተዋጽኦ ወይም እያስከተለብን ያለውን ተግዳሮቶች መገምገም ነው።” ከዚህ ዓላማ አንጻር በክፍል ሁለት እንደተመለከትነው ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አያሌ ጸጋዎች እንደነበሩ አይተናል። በጎ ተግባቦትን በመፍጠር ለዲሞክራሲ ባህል መፋፋትና ለተሻለ የጋራ በጎነት ሳይሰለቹ የሚጽፉ ጎበዝ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተሳታፊዎች አሉ። የሚታገሉለትን ህዝብ ከጭቆና ለማውጣት ከጦር መሳሪያ የጠነከረ ትጥቅና ስንቅ፣ ከጦር ሰራዊት ያልተናነሰ አባል አሰልፈው ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅመውበታል ለማለት ያስደፍራል። በዚህም የማይታሰቡ፣ ይሆናሉ ያላልናቸው ለውጦች ተከስተዋል።

 በዚህኛው ክፍል ጽሑፌ ደግሞ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይዞብን የመጣቸው ሳንካዎችና ተግዳሮቶችን ለማየት እሞክራለሁ። በዚህ ጽሑፍ ለመተቸት የተሞከረው እንደነዚህ ዓይነቶቹን ለዲሞክራሲና ለህዝቦች ነጻነት ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው የሚሰሩትን ሳይሆን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ላልተገባ እኩይ ዓላማ የሚያውሉትንና በህዝቦች መካከል ቁርሾ እንዲፈጠርየሚያደርጉትን ነው። ሁሉንም ለማብራራት የጊዜና ቦታ ውስንነቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም እንዲያስብበት ለመነሻ የሚሆን አጠር ያለ ሐተታ ነው የቀረበው።

 ወደ ሰውነት ክብር የመጓዝ “አቀንጨራ”

“አቀንጨራ” በገጠር አካባቢ የሚገኝ ሰብልን የሚያቀጭጭ የአፈርን ለምነት የሚቀንስ (የሚያደርቅ) አደገኛ አረም ነው። ከላይ ሲታይ ያማረ አበባ አለው። የአበባው ማማር ተወዳጅ ያደርገዋል። እንዲያውም እኔ ባደግሁበት አካባቢ ከአበባው ቀጥፈን ድዳችንን ስናሸው ያጠቁረውና ባለሙያ የነቀሰችው ንቅሳት ያስመስለዋል። እናም የልጅ ነገር ነውና በዚሁ የአቀንጨራ አበባ ንቅሳት “አጊጠን” እንስቅ ነበር። አቀንጨራ ሰፋፊ ቅጠል የለውም፤ ግዝፍ ቅርንጫፍና ግንድም የለውም። መጠኑ ቀጫጫ ሲሆን ቁመቱ ቢረዝም ከ30-50 ሳንቲ ሜትር ነው። ነገር ግን ግዙፍ የሆነውን (እስከ ሁለት ሜትር) የሚረዝመውን የማሽላ ዝርያና የበቆሎ ሰብልን ከስሩ ጨምድዶ በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ቁመቱም እንዲኮሰምን ያደርገዋል። የአቀንጨራ ልዩ አመሉ ታርሞ፣ ተነቅሎ የሚጠፋ አለመሆኑ ነው። መሬት ውስጥ ተቀብሮ (ሸምቆ) ለዘመናት ይቆያል። አቀንጨራ የተነፈሰበት መሬት የተዘራውን ዝርያ ከበቀለ በኋላ ከአረሙ መከላከል አይቻልም። ምክንያቱም በተፈጥሮው የኬሚካልነት ባኅርይ ስላለው የአፈሩን ይዘት ነው የሚመርዘው። በሳሎቹ አርሶ አደሮች ታዲያ መላ ይዘይዳሉ። እንደ ጤፍ ዓይነቶቹን የሳር ሰብሎች ስለማያጠቃ ማሳቸውን በፈረቃ ይዘራሉ። እንዲያውም እነዚህ ሰብሎች በአቀንጨራ የተጎዳውን አፈር እንዲያገግም ስለሚያደርጉት ሰብልን እያቀያየሩ በመዝራት አቀንጨራን ይከላከላሉ።

 የግብርና ባለሙያዎች ወይም በዙሪያው ጥናት ያደረጉ አካላት ስለ ሰብሉ ባኅርያትና እርሱን ስለመከላከል የሚሉን ነገር ካለ ቦታውን ለነርሱ በመልቀቅ ወደ ተነሳንበት ጉዳይ እንግባ። የአቀንጨራ ተምሳሌታዊ ውክልና በከፊልም ቢሆን ለዘመናችን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ባህርይ የሚሰራ ይመስለኛል። በአንድ በኩል የመረጃ ቅልጥፍናውና የተደራሽነት ቅለቱ ሁሉም እንዲወደውና እንዲማረክለት ሆኗል። በሌላ በኩል ከበስተጀርባ በሚዘውሩት አካላት ዓላማ የሥነ ምግባር፣ የሥነ-እውቀት፣ የምርምርና የሰብዓዊነት ሰብሎችን በማቀጨጭ ወደ ሰውነት የሚደረግን የብልጽግና ጉዞ አፍኖ በመያዝ በስሜት ብቻ እንድንነዳ፣ ብዙ አማራጮችን እንዳናይ እንደ ጋሪ ፈረስ ጅው ብለን እንድንጓዝ አስገድዶናል። በርግጥም ይህ አቀንጨራ በስሜት መነዳት ብቻ ሳይሆን የጥላቻ መርዝን በመርጨት በሰዎች ለሰዎች የሚደረግን ተግባቦትና ግዴታ ያኮላሸዋል። ለምንድን ይህንን ሊያደርግ ቻለ? ሲባል የመገናኛ ብዙኃን ባህርይ በራሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። መገናኛ ብዙኃን የጋራ ስሜትን ለመፍጠርና ሰዎችን የቦታና የጊዜ ገደብ ተሻግሮ በማጣመር ግዝፍ ነስቶ ታላላቅ ውሳኔዎችን የመቀልበስ አቅም አለው። እንደ Benedict Anderson አገላለጽ ይህ ዓይነቱ የመገናኛ ብዙኃን ሚና የጋራ መግባቢያ ቋንቋን እና ዓላማን በመጠቀም ሐሳባዊ ማኅበረሰብ (Imagined Community, Ideal Society) በመፍጠር ጠንካራ የመንፈስ ትስስርን ያመጣና በወካዮቹ አማካኝነት ወደ መሬት ይወርዳል። ከዚያ በኋላ የራሱ የማይነካ ርዕዮተ ዓለማዊ ዶግማና ቀኖና ያላቸውን አባላት ይፈጥራል። እነዚህን አካላት በመድፍ፣ በመትረየስ ለመመለስ የሚያዳግት ቁርጠኝነትና የዓላማ ጽናት ያጎናጽፋቸዋል።

ይህ እንግዲህ የዚያ ማኅበረሰብ አባላት የሚተዳደሩባቸው የራሱ የሆኑ መርሆዎችን አርቅቆ ዓለምን የሚገመግምበት የራሱ የሆነ የቦታና ጊዜ ምህዳር ፈጥሮ፣ ከሌሎቹ ጋር ለመገናኘት እንደየ አስፈላጊነቱ የሚከፈቱና የሚዘጉ ጠባብ በሮችን ወይም መስኮቶችን አብጅቶ (ወይም ከናካቴው በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ)፣ የራሱን ወጥመዶች ይፈጥራል። በመጨረሻም ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን በራሱ ገዥ መንፈስ ይፈጥርና ሁሉ በእርሱ የሆነ ብይን ያስተላልፋል። እዚህ ላይ የፖለቲካ ቅይጥ አስተሳሰባዊ ምኅዋሩ ሌሎቹን የሚቆጣጠርበት መነጽርና ራዳር ገጥሞ ይንቀሳቀሳል።

በጊዜ ሂደት ውስጥ ይህንን ሐሳባዊ ማኅበረሰብ የሚመሩ አካላት እውቀትንና ጉልበትን በቁጥጥ ስር በማዋል ሌሎቹን የሚመሩበትን የቁጥጥር ድር ይዘረጋሉ። እንደ ሚሼል ፉኮ (Michael Foulcault) አገላለጽ ይህ Governmentality ወይም Statism መጨረሻ ላይ ሰውን ወደ ሰውነት ክብሩ ከፍ እንዳይል ጨቁኖ የሚይዝበት ውቃቤ ወይም አባዜ ይሆናል። ይህ በእንጭጩ ካልተገታ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ሁሉ እንደፈለገ የሚነዳበት ጠንካራ ጡንቻው ነው ማለት ነው።

 በአንድ Miniwats Marketing Group የተሰኘ ድርጅት በDecember, 31/2017 ይፋ በተደረገ ጥናት መሠረት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 16, 437 811 የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 4.5 ሚሊየን የሚሆነው ፌስቡክ ተጠቃሚ ወይም Subscribe ያደረገ ነው። ይህንን የሚያክል ህዝብ ፌስቡክን ለተለያየ ዓላማ ያውለዋል ማለት ነው። ቁጥሩ ምናልባትም በተለያየ ሥም በሚጠቀሙ ግለሰቦች ምክንያት ሊቀንስ ይችላል ብለን ልንገምት እንችላለን። ነገር ግን ከአገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከግምትውስጥ በማስገባት ቁጥሩን በእጥፍ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችልም መገመት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በቀጥታ ፌስቡክን የማይጠቀሙ ነገር ግን ከተጠቃሚዎች የሚደርሳቸውን የእጅ አዙር ወሬ እንደወረደ የሚቀበሉትን ቤት ይቁጠራቸው። ባጠቃላይ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባንድም በሌሌላም እጅግ በጣም በርካታ የማኅበረሰባችንን ክፍሎች ያዳርሳል።

 መገናኛ ብዙኃን ባጠቃላይ በተለይ ደግሞ የዘመናችን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይህንን የገዥ መንፈሶች ድር በሚተበትቡ አክቲቪስቶች እጅና እነርሱን በጭፍን በሚደግፉ በርካታ ተከታዮቻቸው ህሊና ላይ የተደላደለ ስፍራን ይይዛል። ታላቁ ሊቅ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ስለ መገናኛ ብዙኃን ባተቱበት “ብቻየን ቆሚያለሁ” በተሰኘ ድርሰታቸው ክፍል መገናኛ ብዙኃን ከመንግስት አካላት እንደ አራተኛው ክንፍ [ከህግ አውጭ፣ ህግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካላት እኩል] በመቁጠር አሜሪካዊውን ዊንዊል ፊሊፕስን ጠቅሰው እንዲህ ይላሉ:- “በአንድ ሳንቲም የሚሸጡ ኒው ወርክ ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ዋሽንግተን ካለው የኋይት ሀውስ ቤተ መንግስት ይበልጥ አገሪቱን ማስተዳደር ይችላሉ::” ታዋቂው የጦር ጀነራል ናፖሊዮን ቦናፓርቲ ደግሞ “ሦስት ተቃዋሚ ጋዜጦች ከአንድ ሽህ ሳንጃዎች ይበልጥ ያስፈራሉ::” እንዳለ ሊቁ ያስነብቡናል። በርግጥም ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነትን ለመቃወምና ጨቋኝ ተቃርኖዎችን ለማጋለጥ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሁነኛ መንገድ ነው። ነገር ግን ከበስተጀርባው የሚዘዉሩቱን አካላት ገዥ መንፈስ አስፈጻሚ መሆኑ የራሱ የሆነ የኢፍትሐዊነትና የጭቆና ጠንካራ ክንድ እንደሆነም ያትታሉ አምባሳደሩ። ስለዚህ መገናኛ ብዙኃን የሚነቀፉትን ሲያመሰግን የሚመሰገኑትን በመንቀፍ እውቀትን በመሸፈን ትልቅ አሉታዊ ሚናን ይጫወታል።

 የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ሳንካዎች ከመተንተናችን በፊት ስለ ንግግር ነጻነትና የሰዎች መረጃን የማግኘት መብት ጉዳይ ትንሽ እንነጋገር። የሰው ልጅ ከተሰጠው የተፈጥሮ ጸጋ ውስጥ አንዱ የመናገር ነጻነትና ሐሳብን የመግለጽ መብት ነው። በተለይ መናገር እንዲሁም ቋንቋን መጠቀም ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ ይመስላል። ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ንግግሩ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስረዳ እንዲያውም የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ወይም ምክንያታዊ እንስሳ ነው ከሚለው ይልቅ የሰው ልጅ የሚናገር እንስሳ ነው ማለት ይቻላል። Freedom of Speeach ሚዲያን ባጠቃላይ የሚያካትት ነው። ይህም ማወቅን፣ማዳመጥን፣ ማንበብን፣ መተዋወቅን የሚያካትት ነው። ከዚያ ሐሳብን መጻፍ፣ መተንተን ማስረዳትን ያካትታል። የንግግር ነጻነት (Free Speech) የሚባለው ሰዎች የሚያስቡትን በሌሎች ሥነ-ልቡና ላይ ቅሬታ የማይፈጥር ጉዳይ ላይ እንዲናገሩ መፍቀድ ነው። ሁሉም ሰው የመናገር ነጻነቱ የሚጠበቅለት የሌሎቹን መብት የሚጋፋ ነገር እስካልተናገረ ድረስ ነው።

BELCHATOW POLAND – MAY 02 2013: Modern white keyboard with colored social network buttons.

ከዚህ ጋር የተያያዘው የጥላቻ ንግግር የምንለው ነው። በሰዎች መካከል ያለ ቁርሾ በአንዱ ወገን ዘንድ መጥፎ ስሜትን ወይም ንዴትን ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ወቅት ታዲያ ሌሎቹን የሚያናንቅ የጥላቻ ንግግር (Hate Speech) ሊናገር ይችላል። ይህም ያልተገባ ንግግር እንጅ የንግግር ነጻነትን አያመላክትም። በህግም የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው። ነጻ ንግግር ፍጹም ነጻነት አይደለም። የራሱ የሆነ ገደብም አለው። ማንናኛውም መብትና ነጻነት የራሱ ገደብ እንዳለው ሁሉ ንግግርም ገደብ ሊኖረው ይገባል። ልቅ የሆነ ንግግር የግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን የአንድን ማኅበረሰብ ደኅንነት የሚጋፋ ከሆነ ንግግር ላይ መጠነኛ የሕግ ቁጥጥር ያስፈልጋል። “There should be no ambiguity on the point: free speech is not an absolute.” ይለናል Cass R. Sunstein። በርግጥ የመጀመሪያው ቁጥጥር የተናጋሪው የራሱ ነው። “የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” እንዲሉ አበው ተናጋሪው ሰከን ብሎ የአድማጭን ሁኔታ አገናዝቦ ቃላትን መርጦ መናገር እንዳለበት ይመከራል። ባለፈው ክፍል እንዳየነው ተናጋሪ እኔምኮ ልሳሳት እችላለሁ! የሚል ትንሽዬም ቢሆን የውስጥ ማዕቀብ ማበጀት አለበት። ሁለተኛው ደግሞ አድማጩ ነገሩን የሚረዳበት መንገድና ስህተቶችን ለማረም የሚከተለው ትዕግስት ይሆናል። ለዚህም ምክንያታዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ ነው። ከዚያ ውጭ ግን ሕግን የሚተላለፉትን መቅጣት ደግሞ የሚመለከተው አካል ድርሻ ይሆናል።

 ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከነጻ ንግግር ትንሽ ይለያል። ነጻ ንግግር ምናልባትም ስሜታዊ ንግግርን የሚያካትት ይሆናል። ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ግን በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለ ሙያዊ አስተያየት፣ ክርክር ወይም ሙግት፣ ትችት ሊሆን ይችላል። ይህ ለዲሞክራሲ ብልጽግና አስተዋጽኦ ያለው በተጨባጭ ማስረጃና በሙያዊ አገላለጽ ሥነ- አመክንዮን የተከተለ ሙግት ነው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ንግግሮች ወይም ጽሑፎች ለሰው ልጆች ሕይወት መሻሻል አማራጭ ሐሳብን ስለሚያበለጽጉ ካለው ገዥ መንፈስ ጋር ተቃራኒ ቢሆኑም በመንግሥት ወይም በሌላ አካል መከልከል የለባቸውም ባይ ነኝ። ሥርዓቱን ተከትሎ መሞገት ወይም ማጣጣል ይቻላል። ይህም የሐሳቡን አራማጅ ወይም አመንጭ በመቅጣት፣ በማስፈራራት ወይም በማንገላታት መሆን የለበትም። የነዚህ ግብሮች የጡት አባት ሐሳቡን ከሐሳቡ ባለቤት አለመለየት የሚያመጣው ሥነ-አመክንዮአዊ ሕጸጽ ነው። ተናጋሪውም የሐሳብ ነጻነት በሚል ባርኔጣ ኢምክንያታዊ ስሜቱን ማንጸባረቅ የለበትም። የሐሳብ ነጻነት ሲባል የስሜት ነጻነት ማለት አይደልምና።

 ሌላውና ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሰዎች ሁሉ መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው የታመነ ነው። ታዲያ ነጻ ንግግር ላይ ገደብ ሲደረግ የሰዎቹ መረጃ የማግኘት መብትም አይገደብም ወይ? የሚል ክርክር መነሳቱ አይቀርም። እዚህ ላይ የአድማጩን ብስለት፣ እድሜ፣ ነባራዊ ሁኔታ፣ የጉዳዩን ባሕርይ፣ እንዲሁም የመረጃውን ባለቤትና የሚያስተላልፍበትን መንገድ መለየት ያስፈልጋል። አንዳንዴ መረጃ ከማግኘት መብት ይልቅ መረጃ መከልከል በሰሚው ዘንድ ጥቅም ሊኖረው ይችላል። ያንን ሁኔታ ያላገናዘበ የመረጃ መለቀቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያይላል።

እነዚህን ነጥቦች ሳንዘነጋ የመገናኛ ብዙኃንን ውስጠ ወይራ የሆነ ለርዕዮተ ዓለማዊ አጎብዳጅነት ወይም የተጠቃሚዎችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላልተገባ ዓላማ ሲያውሉት ይስተዋላል። በዘመናችን በኢትዮጵያ ያጋጠሙ የመገናኛ ብዙኃን አቀንጨራዎችን በጥቂቱ እንመልከት:-

አንደኛ:- ሙጠኝነትን ወይም የኔ ብቻ ማለትን (Fundamentalism) አባዜ እንደ ሰደድ እሳት በማሰራጨት ሁሉ በየራሱ ጥግ እንዲቆም ያደርጋል። ከላይ እንደተገለጸው የራሱ የሆኑ አካላዊና መንፈሳዊ አባላት በማሰባሰብ በብሔር፣ በፖለቲካ እርዮተ ዓለም፣ በሃይማኖት፣ ባጠቃላይ በማንኛውም የዘውገኝነት አኮፋዳ በመደበቅ ለፍቅርና ጥላቻ ሚዛኑ ሰው ሳይሆን የአባልነት መታወቂያ ካርድ እንዲሆን አድርጓል። እውነትም፣ ሥነ

“ፌስቡክን እንደ ብቸኛውና ታማኙ የመረጃ ምንጭ በመቁጠር ሁሉም አዳዲስ ነገር ሲፈልግ ፌስቡኩን እየከፈተ ያገኘውን እንዳለ የሚውጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህ የመረጃ ፍሰት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ላይ ከማን እንደሆኑ የማይታወቁ፣ እውነተኝነታቸው የማይታመን መረጃዎች መጥለቅለቅ እነርሱን ተከትሎ የሚመጣው የሰዎች እንግልት ሕይወትን ከባድ እንዲሆን አድርጎታል”

ምግባርም የሚገመገሙት በአባላቱ “ማንነት” የጋራ እሴታችን በሚሉት መስፈርት ይሆናል። ከዚህ የማንነት ካስማ ውጭ ያለውን የሰው ልጆች ከአስመሳይነት ልዝብ ፍቅር እስከ ጭልጥ ያለ ጥላቻ የሚደርስ አትኩሮት ይሰጣቸዋል። እንዲያውም አንዳንድ እውነትን የሚናገሩ አካላት ሲኖሩ እያሸማቀቁ፣ ወይም ከነርሱ አቋም ውጭ ያሉትን እንኳን ምን እንደጻፉና ምን ዓይነት “ፖስት፣ ላይክና ሼር; እንዳደረጉ በመከታተል ማሳደድ፣ ማሸማቀቅ ወይም መክሰስ የፌስቡክ የርስ በርስ ሴንሰር እየሆነ ሁሉም ድምጾች ተሰሚነት ኖሯቸው አማራጭ ሐሳቦችን እንዳናገኝ የራሱ የሆነ ልጓም አበጅቷል። በዚህም በአንድ አገር እየኖሩ የጎሪጥ የሚተያዩ ባለ ዝግ በር ቡድኖችን መፈብረክ ችሏል።

 ሁለተኛ:- ይሉኝታ ቢስነትና ለህዝብ ባህልና እሴት ክብር የማይሰማቸው ሀፍረተቢሶችን ፈጥሯል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጸሐፊ አክቲቪስትና እርሱን የሚከተለው መንጋ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት እንዳላቸው እንኳን ይዘነጋሉ። በሚያገኙት Like እና share እንዲሁም አስተያየት ወይም በሚከተሉት የዘውገኝነት መንፈስ በመታወር የሚናገሩት፣ የሚጽፉት ሐሳብና የሚጠቀሙበት ቋንቋና አገላለጽ የመጡበትን ማኅበረሰብ ባህልና እሴት፣ የሚሰሩበትን ተቋም መርህ፣ የሚኖሩበትን ሙያ ክብርና ኃላፊነት የሚጋፉ ነገሮችን ሲያደርጉ ምንያክል ይሉኝታ ቢስነት የዘመናችን መገለጫ እንደሆነ ያሳያል። ይህ ይሉኝታ ቢስነት የሌሎቹን ሰብአዊነት ክብር ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን እንኳን መገንዘብ እንዳይችሉ አድርጓል። በሰፊው ማኅበራዊ ገጽታው ካየነው አሁን ላይ public shame ወይም ይሉኝታ የሚባል ነገር ጠፍቷል። ይህም በሰዎች ለሰዎች ግንኙነት ውስጥ ስነ ልቡናዊ መራራቅን፣ መጠላላትንና መናናቅን አትርፏል።

 ሦሥተኛ:- በማኅበረሰቡ ዘንድ የዓላማና የፍላጎት እንዲሁም የሕይወት ትርጉም ልዩነትን ከመፍጠሩም ባሻገር የመጠቋቆም፣ የመካሰስ፣ የመጠላላት፣ የመሰዳደብ ባኅልንና የመንጋ ፍርድን በማፋፋት ማኅበራዊ ውህደትን በመሸርሸር የመበታተን (Disintegrity) አደጋ ይዞብን መጥቷል። ይህም የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ታላቁ ተቃርኖ ነው። ሰዎችን ማቀራረብ፣ በጋራ እሴት ላይ የሚመክሩበት መድረክ ከመፍጠር ይልቅ በተቃራኒው እንዲበታተኑ፣ የነበረው ባኅላዊ ትስስርና መልካም ጉርብትና ድባቅ እንዲመታ አድርጎታል። አንድነትን የሚበጣጥስ ቁንቁንና የጋራ ብልጽግናን አፍኖ የሚይዝ አቀንጨራ በመሆን መርህ አልባና “ምን አገባኝ?!” ባይ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እያደረገ ነው። የስርዓት አልበኝነት ምልክቶቹም ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ አመላካች ናቸው።  

አራተኛ:- ይህ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሱስና ተገዥነት ነባር የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በማፈን ሁሉ እጁ ላይ ያለ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ወይም ፊቱ ላይ በተደቀነው ኮምፒተር ላይ በማፍጠጥ ከጎኑ ያሉ ሰዎችን እስኪዘነጋ ድረስ ነባሩን ማኅበራዊ መስተጋብር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እያጠፋው ነው። ከዚህ በተጨማሪ የንባብ ባህልን በማቀጨጩ እንኳን መጻሕፍትንና ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ረዘም ያለ ጽሑፍን እንኳ የማንበብ ትዕግስትን ያጡ ተበራክተዋል። እንግዲህ አብዝሃኛው የፌስቡክ ቤተሰብ የሚባለው እንዲሁ በስሜት ብቻ አጫጭር መረጃዎችን እየቃረሙ የሚውሉና የእውቀት ጥማታቸውን ያረኩ የሚመስላቸው አንባብያን፣ በሚጽፏቸው አጫጭር ጽሑፎች በሚሰጣቸው አስተያየት ከነሱ በላይ አዋቂ የሌለ የሚመስላቸው እብሪተኛ ጸሐፍት መንጋ ጥርቅም ነው። ይህም ቀልበ ቢስ ተከታታዮችን በመፍጠር የማያውቁትን፣ ያልመረመሩትን ሐሳብ በማድነቅ፣ የማያውቁትና ያላዩትን በመዝለፍ እንዲሁ በስሜት ብቻ እየተመሩ እንዲሁ የሚኖሩ ተንቀሳቃሽ ሮኆቦት የሆኑ ሰዎችን እንድናይ መንደርደሪያው ላይ ያለን ይመስለኛል። ቀልበ ቢስ ጸሐፍት፣ ቀልበ ቢስ ተከታታዮቻቸው የግብረ-ገብ በጎነትንና አዋቂነትን የተጠየፉ እስኪ መስል ድረስ ርጋታ ቢስ ያልተማሩ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ መንጋዎችን ለማየት ተገደናል። እንዲያውም ለዘመናት የተደከመባቸውና ብዙ ወጭ የወጣባቸው ትምህርት ተቋሞቻችን ፌስቡክ ያሌቃቸውን አካላት መቋቋም አልቻሉም። ምክንያቱም ትምህርቱ ሰዎችን ሰው መሆንን አላስተማራቸውምና። (ብርሃኑ ድንቄ)

 አምስተኛ:- በሐሰት ስም የሚለቀቁ “የባለቤት አልባ” መረጃዎችና ወሬዎች ከቁጥጥር ውጭ መሆን ተጠያቂነት እንዲጠፋና በየጊዜው በሚወጡ የሐሰት ዜናዎች ትክክለኛ የመገናኛ ብዙኃንን ሥነ-ምግባርና የሰዎችን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት በእጅጉ ተገዳድሮታል። ፌስቡክን እንደ ብቸኛውና ታማኙ የመረጃ ምንጭ በመቁጠር ሁሉም አዳዲስ ነገር ሲፈልግ ፌስቡኩን እየከፈተ ያገኘውን እንዳለ የሚውጥበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በዚህ የመረጃ ፍሰት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት ዘመን ላይ ከማን እንደሆኑ የማይታወቁ፣ እውነተኝነታቸው የማይታመን መረጃዎች መጥለቅለቅ እነርሱን ተከትሎ የሚመጣው የሰዎች እንግልት ሕይወትን ከባድ እንዲሆን አድርጎታል። አንድ ግለሰብ ትክክለኛ ማንነቱ በማይታወቅባቸው ካንድ በላይ የፌስቡክ ስሞች በየወቅቱ የሚለቃቸው መረጃዎችና የተከታዮቹ ብዛት ውሸቱን እውነት እስኪመስል ድረስ በታላላቅ ምሁራን ሳይቀር በየ ሻይ ቤቱ፣ በየ መሸታ ቤቱ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሲገኝ ምን ያክል ህዝባዊ እብደት ላይ እንደምንገኝ ማረጋገጫ ነው። በዚህ ረገድ ሁሉም ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ እንደወረደ በመቀበል እንዲሁ ወሬው በህዝብ አደባባይ ላይ ነፍስ ዘርቶ ተግባራዊ ሲሆን ይስተዋላል።

ስለዚህ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ትልቁ ሳንካ እንዲያውም ይኸው የሐሰት ስሞችና የማስመሰል ቅንብራዊ ዜናዎች ዘባተሎ የወለደው ሰዎች እንዳይመራመሩ እንዲሁ በደመነፍስ ስሜት ወለድ ሐሳቦች ተጠልፈው እንዲናውዙ ማድረጉ ነው።

 ስድስተኛ:- ታላላቅ አገራዊና የግል ምስጢሮች ያለ ገደብ ሲለቀቁ ማየት የተለመደ ነው። የመገናኛ ብዙኃን ትልቁ ክፍተት የተጠቃሚዎቹ ስነ ምግባራዊ ብልሹነት የወለደው ሲሆን ይኸውም ለህዝብ ይፋ የማይደረግ የቤት ገመናን የሚያጋልጥ ወይም የግለሰብ ነጻነት (Privacy) የሚጋፋ ምሥጢር ሆን ተብሎ አፈትልኮ እንዲወጣ ማድረጉ ነው። ህይም በprivate Use of Reason and Public Use of Reason መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ ያሳያል። በውስጥ የሚያዝ፣ ሁሉም ሊጠነቀቅለት በሚገባ የውስጥ ምስጢርና ይፋ በሚወጣ ጉዳይ መካከል አለመለየት ሰዎች ገመናቸውን ከእንስሳት በታች ሲያጋልጡ የሚታየው በዚሁ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን መድረክ ላይ ነው። የተለያዩ ግላዊ ወይም ተቋማዊ ፍላጎት ያላቸው አካላት ከባድ የአገር ምሥጢር የያዘ መረጃን ወይም የግለሰቦችን የግል ምስጢር በመዘክዘክ የሃገርን ዜጎች ከባድ አደጋ ላይ የሚጥል ቅሌት ውስጥ ይከታል። ለማየት ከሚዘገንኑ የወንጀል ዓይነቶች እስከ በዋጋ የማይተመኑ መረጃዎች እንዲሁ እርቃናቸውን ሆነው የፌስቡክ መንደሩ ላይ ሲዘዋወሩ ማየት አዲስ አይደለም። ይህም እንደ አገር ዜጋ ሆኖ ለሚያየው በዓለም መድረክ ሐፍረትን ያከናንባል። ከሀገር ፍቅር ይልቅ አገርህን እንድትጠላ የሚያደርጉ ተስፋ አስቆራጭ ድርጊቶችን ታያለህ፣ የሰው ልጅ ምን ያክል አረመኔ እንደሆነ ትገነዘባለህ። ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ ወራዳ ተግባራት ምን ዓይነት ትርፍ እንደሚገኝ በራሱ ግራ ይገባል።

ሰባተኛ:- የነዚህ ችግሮች ሁሉ ድምር ውጤት የሰው ልጅ ወደሰውነት ክብሩ ከፍ እንዳይል ጠፍሮ በመያዝ በባህል፣ በሃይማኖት በታሪክ የኖርንባቸውን አሉን የምንላቸውን የመከባበር እሴቶች፣ የጋራ ታሪካዊ ዳራንና ምናልባትም ነገ ለምንገነባው ማኅበረሰብ የምናስብ ከሆነ ለልጆቻችን ምን ዓይነት ሃገር ማውረስ እንዳለብን ቆም ብለም ያየን አይመስልም። ሰው ኢመዋቲ ነው ብለናል። ይህ ዘለዓለማዊነቱ ደግሞ በሁለት መልኩ ይገለጣል። እንደየ ግላችን ካየነው የያንዳንዳችን ነፍስ ዘለዓለማዊት ናት ብለን ካመንን ይህንን የነፍስን ኢመዋቲነትና ቀጣይነቷን የበጎ  የሚያደርግበት የግብረገብ ግዴታ አለብን።

ይህንን ዘለዓለማዊነት በማኅበራዊ ሕይወት ከተመለከትነው ደግሞ በትውልዶች መካከል ቀጣይነት ያለው የተግባቦት ሰንሰለት በመፍጠር ለነገ የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር የጋራ ግዴታን ያጎናጽፋል። ምክንያቱም “ሰው ከመወለዱ በፊት፣ በልደቱ እለት፣ በሕይወት ዘመኑ፣ በሞቱ እለትና ከሞቱ በኋላ የሚደረጉ ባኅላዊ ክዋኔዎች የጋራ መጠሪያ ሥም ነው” እንዳሉን ፈቃደ አዘዘ ወደንም ጠልተንም በልጆቻችን የነገ ሕይወት ላይ መልካሙን አሻራ ለማሳረፍ መስራት ይጠበቅብናል። በእኛ የዛሬ ሕይወት ላይ የትናንት መጥፎም ጥሩም አሻራ እንደሚገኝ ሁሉ የዛሬ ተግባራችን በመጭው ትውልድ ላይ ሊያመጣው የሚችለውን መልካም እሴትና እኩይ ቅሪት መለየት የተሳነን ይመስላል።

 እውቀትን የመሻት፣ የመመራመር ሰዋዊ ባህል እየኮሰመነ፤ የርስበርስ መከባበርና ግብረገብነት እየተመናመነ በመሄዱ ወደሰውነት ልዕልና የሚደረገው ጉዞ በመኮላሸት ላይ ይገኛል። ከጋራ ደህንነት አንጻር ስናየው ደግሞ አገር አፍርሰው አገር ለመገንባት የተሰለፉ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ዓርበኞችና ተከታዮቻቸው ቆም ብለው ያሰቡበት አይመስልም። ከየቦታው የሚስተዋሉት መናቆሮችና መገዳደሎች ስናይ ደግሞ እንኳንም ነገን እንድናልም፣ እንኳን የጋራ ጠንካራ አገር ልንገነባና፣ እንኳን ጠንካራ የመንፈስ ትስስርና የዓላማ ጥምረት ለማረጋገጥ የዛሬንም ሕይወት ትርጉም አልባ በማድረግ እየናወዝን እንገኛለን።

የዘመናችን መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ብዙዎቹን ማርኮ በመያዝ ምዕመናኑ እያደረጋቸው ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ መሬት ላይ ያለውን ሐቅ የሚያስረሳ ሐሳባዊ የጦርነት ቀጠና የምንኖር አስመስለው የሚስሉልን አሉባልተኞች ምድራዊውን ሕይወት ትርጉም አልባ ያደርጉታል። ይህም ለማኅበራዊ ሥነ-ልቡናና የርስ በርስ ተግባቦት ትልቅ ደንቀራ በመሆን ንቡርን አብሮነት በእጅጉ ተገዳድሮታል። ይህንን እንደ ጅብራ የተገተረ ትልቅ ችግር ለመገንዘብና መፍትሔ ለማምጣት መፈለግ ካሁኑ ጊዜ በላይ በእጅጉ አስፈላጊ አይሆንም። ብዙ ነገራችንን ከማበላሸቱ በፊት “ሳይቃጠል በቅጠል” መባል ያለበት ወቅት ቢኖር ጊዜው አሁን ነው።

 እንዲያው በዚህ ዘመን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጋጋታ የሚበረግግ መንፈሰ ብኩንና በመንጋ የሚያስብ ልበ ቀሊል ተጠቃሚ ከየት መጣ? እንዲህ እርስ በርሳችን እንድንባላ ያደረገን የታሪካችን፣ የባህላችን ወይም የአስተሳሰባችን ስብራት የቱ ጋ ነው? ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ጥፋቶችና ተግዳሮቶችን ለመፍታትስ ምን መደረግ አለበት? ኃላፊነቱስ የማንነው? እነዚህንና ሌሎች ተግዳሮቶችን ቀርፎ የተሻለ ማኅበራዊ መስተጋብር (Best Social Order) ለማረጋገጥ ከዘመናችን ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚ ምን ይጠበቃል? ዘመኑ የሚጠይቀው መሠረታዊ የሰው ልጆችን የሕይወት ደኅንነት፣ የዲሞክራሲ፣ የማኅበራዊ ፍትሕ፣ የጋራ ብልጽግና እንዲሁም የአስተሳሰብ ልኅቀት ጥያቄዎችን ለመመለስ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚኖረው ሚና ምን መሆን አለበት? የጀመርነው ችግር እንደምናስበው ቀላል አይደለምና ነገርን ነገር እየወለደው ሐተታችን እንቀጥላለን። እነዚህን ጥያቄዎች ለአንባቢ ከማኪያቶ ጋር እንዲያጣጥማቸውና ስልካቸው ላይ ከማፍጠጥ ትንሽ ታቅበው ከጎኑ ካሉት ጋር እንዲወያይ በመጠየቅ የኔዎቹን ይሁንታዎች በቀጣዩ ይዤ ለመመለስ የዚያው ሰው ይበለን።

ይቀጥላል! …

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top