ቀዳሚ ቃል

የሚነበቡ እና የሚያነቡ ቁጥራቸው ይጨምር

በንባብ ስም በርካታ “ክበቦች” ተመሥርተው ሳይቆዩ ከስመዋል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የልቦለድ መጽሐፎች ብዛት ቀንሷል።

የኢ-ልቦለድ መጽሐፎች በአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ እያተኮሩ ከርመዋል።

 መጽሐፎች በገጽ ሽፋናቸው ብቻ ተቸብችበዋል። የፀሐፊዎች “ስሞች” መሻሻጫ ሆነዋል።

ይነበባል ተብሎ ለገበያ የቀረበ መጽሐፍ ጥቂቱ ተሸጦ “አንባቢ የለውም” በሚል ተመልሷል። የተስማማ ፀሐፊ በአነስተኛ ዋጋ ለነጋዴዎች ሸጧል። “እንዳያመልጣችሁ መጽሐፍ በማኪያቶ ዋጋ” የሚሉ ድምፆች በየጎዳናው መስማት ከጅምሩ ሰነባብተዋል።

 አንባቢ ምን ዓይነት መጽሐፍ እንደሚፈልግ እና ምን መጻፍ እንዳለባቸው በነጋዴዎች የሚመከሩ “ደራሲዎች” ተፈጥረዋል።

አዲስ በሚወጡ መጽሐፎች ላይ ከሚሰጡ አስተያየቶች አብዛኞቹ መጽሐፎቹ እንዲነበቡ ሳይሆን እንዲሸጡ የታሰቡ ይመስላሉ።

 በየሳምንቱ ከሚታተሙ ጋዜጦች እና መጽሔቶች መካከል ብዙዎቹ በተለያዩ ምክኒያቶች ጠፍተዋል። በየ አሥራ አምስት ቀኑና በየወሩ ለንባብ የሚቀርቡ መጽሔቶች ቁጥራቸው አንሷል።

እንደ “ብሌን” ያሉ መጽሔቶች በብዛት ይታያሉ ተብለው ሲጠበቁ አልታዩም።

 ኪነ-ጥበብ ደብዝዛለች። በገፆች መካከል የሚሰጣት ሥፍራ አንሷል። በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚኖራ የአየር ሰዓት ጠብቧል።

 ሳንሱር በነበረበት ዘመን በርካታ ደራሲዎች ልቦለዶች ፅፈዋል። በየሳምንቱ በሚወጡ ሁለት ጋዜጦች ላይ በመጽሐፍ፣ በቴያአትር እና በግጥሞች ላይ ባለሙያዎች አስተያየት አቅርበዋል። በወር አንዴ በሚወጣ መጽሔት ላይ የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን አስተዋውቀዋል።

 በዓለም የታዋቂ ደራሲያን ሥራዎችን ተርጉመዋል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የደራሲያንን ጽሑፎች በመፈተሽ ተወያይተዋል።

አሁን ኪነ-ጥበብ ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎች ጥቂት ናቸው። መጽሐፎችን በጥልቀት የሚመረምሩ፣ በተለየ መልኩ የሚያዩ መምህራን ቢኖሩም፤ እንደ በፊቱ በተመረጡ መጽሐፎች ላይ ተሰብስበው፣ ተወያይተው የተወያዩበትን ለአንባቢያን የሚያደርሱበት መንገድ ያገኙ አይመስልም።

“የንባብ ባህላችን ለማሳደግ” በሚል መፈክር ሰቅሎ፣ መጽሐፎች ደርድሮ መወያየቱ፤ ንግግርን መቋጨት እስኪያቅት መነጋገሩ ብቻ የአንባቢያንን ስሜት፤ መርጦ የማንበብ ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። ያነበቡትን ለማካፈል፣ ያጠኑትን ለማዳረስ መሰብሰቡ እንዳይቀዘቅዝ፣ መድረክ እያዘጋጁ፣ ባለሙያዎች እየጠሩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እንዲያቀርቡ የሚጋብዙ እንደ “ሙዚክ ሜዴይ”፣ “የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ” ዓይነቶች በብዛት ሊኖሩ ይገባል።

 በኪነ-ጥበብ ዘርፍ በስፋት የሚጽፉ አንባቢያንን የሚስቡ፣ ጸሐፍትን የሚጋብዙ፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጽሐፎች ያስፈልጋሉ።

 በአዲስ ዓመት የሚነበቡ እና የሚያነቡ በዝተው እንዲታዩ ምኞታችን ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top