አጭር ልብወለድ

እግዜር ትክክል ይፈርዳል ግን ይዘገያል

ደራሲ፡- ሊኦ ቶልስተይ

ትርጉም፡- መኮነን ዘገዬ

ወጣቱ ነጋዴ ኢቫንዲሚትሪች አክሲዮኖቭ በቭላድሚር ከተማ ይኖራል። ሁለት ሱቆች እና አንድ የራሱ መኖሪያ ቤት አለው። አክሲዮኖቭ መልከመልካም እና ፀጉሩ ዞማ ነው። ቀልድ ያውቃል/። መዝፈን ይወዳል። በወጣትነቱ ጠጪ ነበር። በጣም ከጠጣ ደግሞ ይረብሻል። ካገባ በኋላ የመጠጥ ነገር እርም አለ። አንድ በጋ ላይ አክሲዮኖቭ ወደ ኒዝህኒ የንግድ ትርኢት ወደ አለበት ሄዶ መሳተፍ ነበረበት። ቤተ-ሰቡን ተሰናብቶ ለመሄድ ሲነሳ ሚስቱ “ኢቫን ዲሚትሪች በህልሜ ስለአንተ መጥፎ ነገር ስለአየሁ ከቤትህ ባትወጣ ይሻልሃል” በማለት አስጠነቀቀችው።

 አክሲዮኖቭ ሳቀና “ሁልጊዜ እኔ ወደ ንግድ ትርኢት ለመሄድ ስነሳ ለፈንጠዝያ የምሄድ እየመሰለሽ ትፈሪያለሽ” አላት።

“ለምን እንደምፈራ አላውቅም ብቻ አሁን የማውቀው ነገር መጥፎ ህልም ማየቴ ነው። ከሄድክበት ተመልሰህ መጥተህ ኮፍያህን ከራስህ ላይ ስታነሳ ፀጉርህ እንዳለ ሸብቶ ጥጥ መስሎ ነው ያየሁት።”

ሚስቱ የነገረችውን ሲሰማ አክሲዮኖቭ ሳቀ። “ይሄማ የጥሩ ዕድል ምልክት ነው። እውነቴን ነው የምልሽ ይዤ የምሄደውን ሁሉ ሸቀጥ ሽጬ ብዙ አትርፌ ስመለስ ለአንቺ ስጦታ የሚሆን ነገር ይዤልሽ እመጣለሁ፤ አንቺ እንደምትይው ምንም ክፉ ነገር አይገጥመኝም።”

 ቤተ-ሰቡን ተሰናብቶ ወጣ። ግማሽ መንገድ እንደተጓዘ አንድ የሚያውቀውን ነጋዴ አገኘ። በአንድ ቡና ቤት ሌሊቱን እንዲያሳልፉ ወሰኑ። በልተው ጠጥተው ጎን ለጎን ካሉት ክፍሎች ተከራይተው ተኙ።

አክሲዮኖቭ ተኝቶ የማርፈድ ልምድ አልነበረውም። ቀዝቀዝ ሲል ለመገስገስ አስቦ ረዳቱን በጧት ቀስቅሶ በቅሎዎቹን እንዲጭን አዘዘው። ለሆቴል ቤቱ ባለቤት ሒሳቡን ከፍሎ ጉዞውን ቀጠለ። ሃያ አምስት ማይል ያህል ከተጓዘ በኋላ ፈረሶቹን ሳር እንዲግጡ በማሰብ አሳረፋቸው። ትንሽ ካረፈ በኋላ የሚጠጣ ነገር አዝዞ እስኪቀርብለት ጊታሩን አውጥቶ መጫወት ጀመረ። ድንገት በሶስት ፈረሶች የሚጎተት ሠረገላ የጥሩንባ ድምፅ እያሰማ ብቅ አለ። ወዲያውኑ ከውስጡ አንድ ባለ ሥልጣን ዱብ አለ። ሁለት ፖሊሶች ተከተሉት። ወደ አክሲዮኖቭ ተጠጋና ስሙንና መቼ እንደመጣ ጠየቀው። ወጣቱ “አረፍ ብለህ አብረኸኝ ቡና አትጠጣም?” አለው።

 ባለሥልጣኑ እያከታተለ ይጠይቀው ጀመር። “ትናንትና የት ነበር ያደርከው? ብቻህን ነበርክ? ወይስ ሌላ ነጋዴ አብሮህ ነበር? አብሮህ የነበረውን ነጋዴ ዛሬ ጧት አይተኸዋል? ያደርክበትን ሆቴል ለምንድነው በጥዋት ለቀህ የሄድከው?”

 ባለሥልጣኑ ለምን እንደሚጠይቀው ግራ ገባው። የተጠየቀውን ሁሉ መልሶ “ግን ለምንድር ነዉ ሌባ ወይም ሽፍታ ይመስል እንዲህ ያለ ጥያቄ የምትጠይቀኝ? ለግል የሥራ ጉዳይ እየሄድኩ ነው። እኔን የምትጠይቅበት ምንም ምክንያት ያለህ አይመስለኝም።”

 አዛዡ ወታደሮቹን እየጠራ “የዚህ አውራጃ የፖሊስ አዛዥ ነኝ። ትናንት ምሽት አብሮህ የነበረው ነጋዴ አንገቱ በስለት ተቆርጦ ተገኝቷል። ለዚህ ነው አንተን መጠየቅ ያስፈለገበት ምክንያት። አሁን እቃህን መፈተሸ አለብን” ኮስተር አለ።

 የአክሲዮኖቭን የዕቃ መያዣ ሻንጣ ፈተሹ። ድንገት የፖሊስ አዛዡ አንድ ቢላዋ ከሚፈትሸው ሻንጣ ውስጥ መዝዞ እያወጣ “የማነው ይሄ?” አክሲዮኖቭ ድንግጦ በፍራቻ አፍጥጦ ደም የነካ ቢላዋ ከሻንጣዉ ዉስጥ ሲወጣ ተመለከተ።

“እንዴት ደም ሊነካዉ ቻለ?” የፖሊስ አዛዡ ጥያቄ ነበር። አክሲዮኖቭ መልስ ለመስጠት ሞከረ ግን እየተንተባተበ “እኔ … ምንም የማዉቀው ነገር የለም” አለ።

“ዛሬ ጠዋት ነጋዴው አልጋው ላይ አንገቱ ተቆርጦ ሞቶ ተገኝቷል። ይህን ከአንተ ሌላ ማንም አያደርገውም። ቤቱ ከውስጥ ተቆልፏል። በደም የተነከረ ጩቤ ሻንጣህ ውስጥ ተገኝቷል። ሁኔታህ መደናገጥህን ይመሰክራል። እንዴት እንደገደልከው እና ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰድክበት ንገረኝ።”

አክሲዮኖቭ “ ድርጊቱን እንዳልፈፀመ ማለ። ከነጋዴው ጋር ማታ ሻይ ከጠጣ በኋላ እንዳላየው ተናገረ። ስምንት ሺህ ሩብል ብቻ እንደያዘና ጩቤውም የእሱ እንዳልሆነ ጨምሮ አስረዳ። ድምፁ ይቆራረጣል። ፊቱ በአንዴ ገረጣ። ወንጀሉን የፈፀመ ይመስል በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።

አዛዡ፤ ፖሊሶቹ አክሲዮኖቭን አስረው ሰረገላው ውስጥ እንዲያስገቡት አዘዘ። እንደተባሉት ሰረገላው ውስጥ ሲወረውሩት አክሲዮኖቭ ፀለየና አለቀሰ። በእጁ የነበረው ገንዘብና ንብረት ተወሰደበት። በአቅራቢያው ወደሚገኝ እስር ቤት ተላከ። ስለባህሪይው መረጃ ተፈለገ። የአካባቢው ነጋዴዎችና ሌሎች ሰዎች በፊት ጠጪና ጊዜዉን በከንቱ ያባክን እንደነበረ መረጃ ሰጡ። ኋላ ላይ ግን ስነስርአት ያለው ሰው እንደነበረ አልደበቁም። አክሲዮኖቭ የሪያዛን ነጋዴ በመግደልና ሃያ ሺህ ሩብል በመዝረፍ የወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

 ሚስቱ ተስፋ ቆረጠች። የሰማችውን አላመነችም። ልጆቿ ገና ሕፃናት ናቸው። አንደኛው ገና ጡት ይጠባል። ምንም ማድረግ አልቻለችም። ልጆቿን ይዛ ባሏ ወደታሰረበት ከተማ ሄደች። መጀመሪያ ባሏን ለማየት ተከለከለች። ኋላ ላይ ከብዙ ልመና በኋላ ባለስልጣኖቹ እንድታየው ፈቀዱላት። ባሏ የእስረኛ ልብስ ለብሶ፣ አጆቹ በካቴና ተጠፍረው ከሌቦችና ከወንጀለኞች ጋር ስታየው ደንግጣ ወደቀች። ለረጅም ጊዜ ራሷን ስታ ከቆየች በኋላ እንደምንም ተረጋግታ ልጆቿን ሰብስባ ባሏ አጠገብ ተቀመጠች። ስለቤታቸው ነገረችው። ቀስ በቀስ የገጠመውን ጠየቀችው። የደረሰበትን ችግር ነገራት። “ምን ማድረግ ነው የምንችለው?”

 “ለዛሩ ንጉሥ የአቤቱታ ማመልከቻ ማቅረብ አለብን”። ከተለየችው በኋላ ለንጉሡ የአቤቱታ ማመልከቻ ማስገባቷንና ማመልከቻውም በንጉሡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ነገረችው። አክሲዮኖቭ መልስ አልሰጣትም። አቀርቅሮ መሬት መሬቱን ማየት ጀመር።

 “ለካስ በህልሜ ፀጉርህ ሸብቶ ያየሁት ይህን ሊያሳየኝ ኑሯል! አልሰማሃኝም እንጂ የዚያን እለት ከቤት መውጣት አልነበረብህም:: ምን ያደርጋል አሁን መቼም አልፏል።

 የምወድህ ቫንያ ወንጀሉን አንተነህ እንዴ የፈፀምከው? እስቲ እዉነቱን ንገረኝ!”

 “አንቺም ትጠረጥሪኛለሽ ማለት ነው?” አክሲዮኖቭ ፊቱን በመዳፎቹ ሸፈነና ማልቀስ ጀመረ። ወዲያውኑ አንድ ፖሊስ ገባና ሚስቱና ልጆቹ እንዲሄዱ ትዕዛዝ ሰጠ። አክሲዮኖቭ ከቤተሰቡ ጋር የመጨረሻውን ስንበት ተለዋወጠ።

ቤተሰቦቹ ከሔዱ በኋላ አክሲዮኖቭ ከባለቤቱ ጋር የተነጋገሩትን አስታወሰ። እንደጠረጠረችው ትዝ ሲለው “እግዜር ብቻ ነው እውነቱን የሚያውቅ፣ ማመልከትም የሚገባ ለእሱ ብቻ ነው፣ ምህረትም የሚጠበቀው ከእሱ ብቻ ነው::” አክሲዮኖቭ ከእዚህ ወዲህ ለማንም ማመልከቻ ለመፃፍ አልሞከረም። ተስፋ ቢቆርጥም፣ ወደ እግዜር መፀለዩን አላቋረጠም።

 ተገረፈ። ማዕድን እንዲቆፍር ተደረገ። በመጨረሻም ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር ወደ ሳይቤሪያ ተላከ።

ለሃያ ስድስት ዓመታት እስረኛ ሆኖ ሳይቤሪያ ቆየ። ፀጉሩ ሸብቶ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ፂሙ አድጎ፣ ረዝሞ፣ ግራጫ መሰለ። ለዛና ፈገግታው ጠፋ። አጎንብሶ በዝግታ መራመድ ጀመረ። ንግግሩ ተቆጠበ። መሳቅ ተወ። መፀለዩን ብቻ አላቋረጠም።

እስር ቤት ሆኖ ጫማ መስራት ተማረ። በሥራው ትንሽ ገንዘብ ማግኝት ጀመረ። በገንዘቡ የቅዱሳን ሕይወት የሚል መፅሐፍ በመግዛት ማንበብ ቀጠለ። እሁድ እሁድ እስር ቤት ወደ ሚገኘው ቤተክርስቲያን እየሄደ ይፀልያል፣ ይዘምራል።

 የእስር ቤት ሃላፊዎች አክሲዮኖቭ ሰላማዊ እስረኛ በመሆኑ ወደዱት። እስረኞችም “አያታችን፣ ቅዱሱ ሰው” እያሉ ጠሩት። አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም ሲፈልጉ ጥያቄያቸውን ለባለስልጣኖች የሚያቀርብላቸው። እስረኛ ሲጣላ አስታራቂያቸው ሆነ።

 ስለ ቤተሰቡ ደህንነት ምንም ወሬ አይሰማም። በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚያውቀው ነገር የለም።

አንድ ቀን ወደ እስር ቤቱ እስረኞች መጡ። ማታ ላይ ነባር አስረኞቹ አዲሶቹን ሰብስበው ከየት እንደ መጡ፣ ለምን እንደታሰሩ ጠየቁዋቸው። ከነባር እስረኞቹ መካከል አንዱ አክሲዮኖቭ ነበር። አጠገባቸው ተቀምጦ በእርጋታ ያዳምጣል።

ከአዲሶቹ እስረኞች መካከል አንድ ረጅም ጠንካራ በግምት እድሜው ስድሳ የሚሆን ሸበቶ ጢሙን በቅርቡ የተላጨ በተራዉ በምን ጉዳይ እንደታሰረ ገለፃ አደረገ።

“ጓደኞቼ አንድ ታስሮ የነበረ ፈረስ በመዉሰዴ ነው ለእስር የተዳረግሁት። ለመስረቅ አስቤ ሳይሆን እቤቴ በፍጥነት ከደረስኩበት በኋላ ልለቀው ነበር። በእዚያ ላይ ጠባቂውን አውቀዋለሁ። እነሱ ሰርቀሃል ብለው እንደምታዪት እስር ቤት ወረወሩኝ። ባይገርማችሁ የትና መቼ እንደሰረቅሁ እንኳን ምንም መረጃ የላቸውም። አንዴ ብቻ ወንጀል ሰርቼ ወደ ሳይቤርያ ተልኬያለሁ። ብዙ ሳልቆይ ተፈታሁ። አሁን ያለጥፋቴ ነው የታሰርኩት።”

“ከየት ነው ታስረህ የመጣህ?” ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ጠየቀው።

“ከቭላዲሚር! ቤተሰቦቼ እዚያ ነው የሚኖሩት። ስሜ ማካር ይባላል። ሲሚዮኒችም ይሉኛል።”

አክሲዮኖቭ ራሱን ቀና አድርጎ “እስቲ የምታዉቀው ነገር ካለ ስለ ቭላዲሚር ነጋዴዎች ንገረኝ! እስከአሁን በህይወት አሉ?”

 “ታውቃለህ ነው የምትለኝ? በደንብ ነዋ! የአክሲዮኖቭ ቤተሰቦች በጣም ሃብታሞች ናቸው:: አባታቸው ወደ ሳይቤርያ ተልኳል። ወንጀል ሳይፈፅም የቀረ አይመስለኝም። አንተስ ምን አድርገህ ነው ወደዚህ የመጣኸው?”

አክሲዮኖቭ የታሰረበትን ምክንያት መናገር አልፈለገም። ትንሽ እንደመተንፈስ አለና “በፈፀምኩት ወንጀል ለሃያ ስድስት ዓመታት በእስር አሳልፌያለሁ።”

“ምንድነው የፈፀምከው ወንጀል?”

 “ቅጣቱ የሚገባኝ ነበር” ሌላ ነገር አልተናገረም። አብረውት በእስር የቆዩት ጓደኞቹ አክሲዮኖቭ ለምን ወደ ሳይቤርያ ሊመጣ እንደቻለ ለአዲሱ እስረኛ ነገሩት። አንድ ያልታወቀ ሰው ነጋዴውን ገድሎ የገደለበትን ጩቤ አክሲዮኖቭ ሻንጣ ውስጥ በመክተት እንዴት ተጠያቂ እንዳደረገው አጫወቱት።

ማካር ሲሚዮኒች ወደ አክሲዮኖቭ ተመልክቶ፤ ጉልበቱን በእጁ መታመታ አደረገና “ይሄ መቼም በጣም በጣም አስገራሚ ነገር ነው! በጣም ያስገርማል! ለመሆኑ አያቴ እድሜህ ስንት ነው?”

 ሌሎቹ እስረኞች ጠያቂው ለምን እንደተገረመና ከእዚህ በፊት አክሲዮኖቭን የት እንዳየው አጥብቀው ጠየቁት። መልስ አልሰጣቸውም።

 “ብቻ ለማንኛውም እዚህ መገናኘታችን በጣም አስገራሚ ነገር ነው ሰዎች!”።

 አክሲዮኖቭ አዲሱ እስረኛ በተናገረው ነገር ነጋዴውን ማን እንደገደለው ያዉቀው ይሆን የሚል ጥርጣሬ አደረበት። “ስለ ወንጀሉ የምታውቀው ነገር አለ? እኔንስ አይተኸኝ ታውቃለህ?”

 “ማወቄማ እንዴት ይቀራል? ዓለምኮ በአሉ የተሞላች ነች። ጊዜው ስለቆየ የሰማሁትን ረስቸዋለሁ።”

 “ ምናልባት ነጋዴውን ማን እንደገደለው ሳትሰማ አትቀርም?”

 ማካር ሲሚዮኒች ሳቀና “ሻንጣህ ውስጥ ጩቤ የተገኘው ሰው አንተ ሳትሆን አትቀርም። ጩቤውን ሻንጣህ ውስጥ የደበቀው ሰው መቼም እንደ ተረቱ እስካልተያዘ ድረስ ወንጀለኛ ነው ሊባል አይችልም። ሻንጣህ አጠገብህ እያለ እንዴት ሆኖ ነው አንድ ሰው ሻንጣህን ከፍቶ ዉስጡ ጩቤ ሊደብቅ የሚችለው? ምክንያቱም አንተ መንቃትህ አይቀርም?”

 አክሲዮኖቭ የተናገረውን ሲሰማ በእርግጠኝነት ነጋዴውን ሳይገድለው አይቀርም ብሎ በማሰብ ከተቀመጠበት ተነስቶ ሄደ። ሌሊቱን እንቅልፍ አልወሰደውም። ክፉኛ ሃዘን ተሰማው። የተለያዩ ምስሎች በአእምሮው መጡ። ወደ ንግድ ትርኢቱ ለመሄድ የሚስቱ ገፅታ መጣበት። በአካል አጠገቡ ያለች ይህል ተሰማው። ፊቷና ዐይኖቿ ታዪት። ተናግራ ስትስቅ ድምፅዋ ተሰማው። ከዚያ ትናንሽ የነበሩት ልጆቹ ታዪት። አንዱ ካባ ለብሷል። አንደኛው እናቱ ታቅፋው ጡት ይጠባል። አክሲዮኖቭ በወጣትነቱ ደስተኛ እንደነበረ ታወሰው። ከመታሰሩ በፊት ከቡና ቤቱ ጥግ ተቀምጦ ጊታሩን ሲጫወት ነፃና ደስተኛ እንደነበር ትዝ አለው። እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ሰዎች በተሰበሰቡበት ሲገረፍ የነበረበትን ቦታ እንዲሁም ዳኛውም ጭምር በህሊናው ታየው። የግር ብረቱ፣ ያሳለፈው የሃያ ስድስት ዓመት፣ ያለ ዕድሜው ማርጀቱ፣ እነዚህ ሁሉ ሀሳቦች ተዥጎድጉደው ሲመጡበት ምስኪንነት ተሰማውና እራሱን ለማጥፋት ተዘጋጀ።

ይህ ሁሉ የሆነው በእዚያ ተንኮለኛ ሰው ምክንያት ነው! ብሎ አሰበ። እናም በሲሚዮኒች ላይ ጥላቻው እያየለ ሄደ። የመበቀል ስሜቱ ጨመረ። ለሕይወቱ ደንታም አልሰጠውም። ሌሊቱን ሙሉ ሲፀልይ አደረ። ሰላም አላገኘም። በቀጣዪ ቀን ማካር ሲሚዮኒች አጠገብ አልደረሰም። ሊያየውም አልፈለገም።

 አስራ አምስት ቀን አለፈ። አክሲዮኖቭ ሌሊት እንቅልፍ አጥቷል። ምን ማድረግ እንዳለበት አላወቀም።

አንድ ሌሊት እስር ቤቱ ውስጥ በመንጎራደድ ሳለ አነስ ያለ አፈር ወደቀ። ምክንያቱን ለማወቅ ቆም ብሎ ተመለከተ። ድንገት ማካር ሲሚዮኒች ብቅ አለና በፍርሃት ስሜት ተዉጦ አክሲዮኖቭን ተመለከተው። አክሲዮኖቭ እንዳላየ ለማለፍ ሞከረ። ማካር እጁን ያዘው “በግድግዳው በኩል ወደ ዉጭ የሚያስወጣ ቀዳዳ እየቆፈርኩ ነው። አፈሩን እስረኞች ቀን ለሥራ ሲሄዱ ወደውጭ ወስደው ይደፉታል። ለማንኛዉም አሁን ካንተ የሚጠበቀው ዝም ማለት ብቻ ነው። ከተሳካ አንተም የማምለጥ ዕድል ታገኛለህ። ፖሊሶቹ ካወቁብኝ መቼም ልቤ እስኪ ጠፋ ነው የሚገርፉኝ። እኔ ደሞ ከሁሉም በፊት መጀመሪያ አንተን ነው የምገልህ። ስለዚህ እንዳትናገር በማለት አስጠነቀቀው።

 አክሲዮኖቭ ጠላቱን እያየ በንዴት ተንቀጠቀጠ። እጁን ወደላይ ከፍ አድርጎ “እኔ የመጥፋት ፍላጎት በፍፁም የለኝም። እኔን ልትገለኝ አትችልም። ከገደልከኝ ቆይተሃል!”

 በሚቀጥለው ቀን እስረኞች ሲሰማሩ ፖሊሶች አንድ ሁለቱ ካደረጓቸው ቦት ጫማዎች ውስጥ አፈር ሲያራግፉ ተመለከቱና ሪፖርት አደረጉ። እስርቤቱ ሲፈተሸ ለማምለጫ የሚያገለግል የተቆፈረ መሹለኪያ ተገኘ። የእስር ቤቱ አዛዥ ድርጊቱን ማን እንደፈፀመው እንዲነግሩት እስረኞቹን ቢመረምርም መልስ አላገኘም። በመጨረሻም የእስር ቤቱ አዛዥ ወደ አክሲዮኖቭ እየተመለከተ “አንተ መቼም አትዋሽም እስቲ ስለ እግዚአብሔር ብለህ ይህን ድርጊት ማን እንደፈፀመው ንገረኝ” አለው፡፡

ማካር ሲሚዮኒች ምንም ነገር እንደማያውቅ ትኩር ብሎ ወደ እስር ቤቱ አዛዥ ተመለከተ። የአክሲዮኖቭ ከንፈሮችና እጆቹ ተንቀጠቀጡ። ለረጅም ጊዜ አንድም ቃል ሳይተነፍስ ዝም ብሎ ቆየ። “ሕይወቴን ያበላሸ ሰው ለምን ብዬ ነው የምደብቀዉ:: እኔን እንዳሰቃየ እሱም መሰቃየት አለበት። ግን ደሞ ካጋለጥኩት ነፍሱ እስኪወጣ ነው የሚገርፉት። ግምቴም ትክክል ላይሆን ይችላል። ደግሞስ እሱን በመበቀል ምን አተረፋለሁ” ብሎ አሰበ።

 “እሺ አንተ ሽማግሌ” አለ የእስር ቤቱ አዛዥ “እውነቱን ንገረኝ! ማነው ይህን ማምለጫ የቆፈረው?”

አክሲዮኖቭ ወደ ማካር ሲሚዮኒች መልከት አደረገና “ምንም የምለው ነገር የለኝም ጌታዬ። እንድናገር እግዜር አላዘዘኝም! የፈለከውን አድርገኝ በአንተ እጅ ነው ያለሁት”

የእስር ቤቱ አዛዥ ደጋግሞ ሙከራ ቢያደርግም አክሲዮኖቭ ምንም ፍንጭ መስጠት አልቻለም።

የዚያን እለት ምሽት አክሲዮኖቭ መኝታው ላይ ጋደም ብሎ ነበር። አንድ ሰው አልጋው ጫፍ ላይ ቁጭ አለ። ቀና ብሎ ተመለከተ። ማካር ነበር።

“ዛሬ ጠዋት ነጋዴው አልጋው ላይ አንገቱ ተቆርጦ ሞቶ ተገኝቷል። ይህን ከአንተ ሌላ ማንም አያደርገውም። ቤቱ ከውስጥ ተቆልፏል። በደም የተነከረ ጩቤ ሻንጣህ ውስጥ ተገኝቷል። ሁኔታህ መደናገጥህን ይመሰክራል። እንዴት እንደገደልከው እና ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰድክበት ንገረኝ።”

“አሁን ደግሞ ከኔ ምን ትፈልጋለህ?” “ ለምን ወደዚህ መጣህ ?” ማካር ሲሚዮኒች መልስ አልሰጠውም። አክሲዮኖቭ ከተጋደመበት ቀና አለ። “ምንድነው የምትፈልገው? ካጠገቤ ሂድልኝ እምቢ ካልክ ጠባቂውን ነው ምጠራው።”

 ማካር ሲሚዮኒች ወደ አክሲዮኖቭ ተጠግቶ ድምፁን ቀንሶ ተናገረ። “ኢቫን ዲሚትሪች ይቅርታ አድርግልኝ!”

 “ ለምኑ ነው ይቅርታ የማደርግልህ?”

 “ነጋዴውን ገድዬ ጩቤውን ሻንጣ ውስጥ የከተትኩት እኔ ነኝ። ሃሳቤ አንተንም ለመግደል ነበር። ከውጭ ድምፅ ስለሰማሁ ጩቤውን አንተ ሻንጣ ውስጥ ከትቼ በመስኮት አመለጥኩ።

አክሲዮኖቭ ፈዝዞ ቀረ። ማካር ሲሚዮኒች ቀስ ብሎ ከመኝታው ላይ ተነስቶ ወለሉ ላይ ተንበርክኮ “ስለእግዜር ብለህ ይቅር በለኝ! እንደነገርኩህ ነጋዴውን የገደልኩት እኔ ነኝ። አሁን አንተ ተፈተህ ወደ ቤተሰቦችህ ትሄዳለህ።”

“አንተ ስታወራው እንደዚህ ቀላል ነው። እኔ ግን በአንተ ምክንያት ሃያ ስድስት ዓመት በእስር ተሰቃይቻለሁ። ከዚህ ወጥቼ ወዴት እሔዳለሁ። ሚስቴ ሞታለች። ልጆቼም ረስተውኛል። የምገባበት የለኝም።”

ማካር ሲሚዮኒች ከተንበረከከበት አልተነሳም። በፀፀት ራሱን ከወለሉ ጋር ያጋጭ ጀመር። “ኢቫን ዲሚትሪች እባክህ ይቅርታ አድርግለኝ” እያለ መጮህ ጀመረ። “ሲገርፉኝ እንኳን እንደዚህ የአንተን ፊት እንደማየት አላመመኝም ። እባክህ ለክርስቶስ ስትል ልመናዬን ስማኝና ይቅርታ አድርግልኝ” ማልቀስ ጀመረ። ለቅሶውን ሲሰማ አክሲዮኖቭ ማልቀስ ጀመረ።

 “እግዜር ይቅር ይበልህ! ምናአልባት እኔም ብሆን ካንተ የባስኩ ልሆን እችላለሁ።” ቃላቱ ከአፉ ሲወጡ ልቡን ቀለለው። እፎይታ አገኘ። ወደ ቤት የመመለስ ጉጉቱ ጥሎት ሲጠፋ ተሰማው። ከእስር ቤት ወጥቶ የመሄድ ፍላጎት ከውስጡ ወጣ። አሁን የሚጠብቀው ያችን የመጨረሻዋን ሰዓት ብቻ ነው።

አክሲዮኖቭ ያለውን ቢልም ማካር ሲሚዮኒች ጥፋተኝነቱን አምኗል። መፈታቱን የሚያበሥረው ትዕዛዝ ሲመጣለት አክሲዮኖቭ ሞቶ ነበር።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top