ጥበብ እና ባህል

“አጌም”፡- “ንጉሥ ይገረፋል፤ ሰማይ ይታረሳል”

ክፍል ሦስት

“ንጉሥ አይከሰስ፣ ሰማይ አይታረስ” የሚለው በአኙዋዎች ትውፊታዊ እውቀትና ተሞክሮ በግልባጩ የሚተረጎም ፈሊጥ ነው!

የዚህ ፅሑፍ ዓላማ በአኙዋዎች ዘንድ በታሪክ የሚጠቀሙበት “አጌም” በሚል የሚጠቀሰው ትውፊታዊ እውቀት፣ የረዥም ዘመናት ተሞክሮና ባህላዊ ዘዴ ወይም መንገድ ለዲሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ዕድገትና ሥርፀት በሀገራችን መሠረት ሆኖ ምን ያህል ሊያገለግል እንደሚችል ለአንባብያን እንደ ምሳሌ ማስገንዘብ ነው።

 ባለፈው እትም “አጌም” ማለት ምን እንደሆነ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። ለማስታዎስ ያህልም ከባህላዊ ፍችው አንፃር ሲታይ “አጌም”በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፈው የመጡና በህብረተሰቡ ዘንድ እንደ ትልቅ እሴት ተቆጥረውና ተከብረው የኖሩ ጥንታዊ አባቶች የመሠረቷቸው ሕጎች በባህላዊ የአስተዳር ተቋማት መሪዎች መጣሳቸው ሲታወቅ ሰላምን ለመመለስ የሚከናወን “ህዝባዊ ዐመፅ” ማለት ነው። አጌም በባህል የተፈጠረ፣ በታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ፣ አኙዋዎች ከጥንታዊ አባቶቻቸው ከተረከቧቸው ድንቅ የሰላም ጥበቃ መንገዶች አንዱና ዋነኛው እሴት ነው።

ይህን የአኙዋዎች ድንቅ ባህል አንዳንድ ተመራማሪዎች በየበኩላቸው እንዴት እንደተገነዘቡትም ለመግለፅ ሞክሬያለሁ። አንዳንዶች አጌም መነሻ ምክንያቱም ሆነ መድረሻ ውጤቱ የማይታወቅ በ“ግርግር” የሚነሳ “ብጥብጥ” (“riot”) አድርገው ሲመለከቱት ሌሎች ደግሞ “የህዝብ አብዮት” የሚል ትርጉም እንደሰጡት ተመልክቷል። ነገር ግን ፅንሰ-ሀሳቡ ከሁለቱም አተረጓጎሞች የተለየ መንፈስ እንዳለው አይተናል። ይህም አጌም በግብታዊነት ወይም በደመ-ነፍስ ስሜት የሚመራ፣ በግርግር የሚፈጠር ብጥብጥ አለመሆኑ፣ መነሻ ምክንያት ያለውና መድረሻ ውጤቱም አስቀድሞ የሚታወቅ ሂደት መሆኑን የሚገልፅ ነው። በአፈፃፀም ሂደቱም ምን ደረጃዎችን ጠብቆ እንደሚጠናቀቅ፣ ምን ርምጃዎችን እንደሚከተል፣ በአጠቃላይም፣ እንዴት እንደሚከናወን በባህል የሚታወቅ ዐመፅ ነው።

አጌም “ህዝባዊ አብዮት” ሊባል አይችልም። “አብዮት” የማያሰኘውም በባህል የተፈጠረ፣ የተዋቀረና የተለየ ዓላማ ኖሮት በታሪክ በአገልግሎት ላይ የቆየ የባህሉ አካል በመሆኑ ምክንያት ነው። በተጨማሪም አፈጣጠሩ ከሥነ-ኅላዌ ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚገለፅ፣ መለኮታዊነት ያለው፣ ከሰማያዊ ኃይል ጋር የሚቆራኝ፣ ከርዕዮተ-ዓለማዊ አመለካከትና ከእምነት የሚመነጭ፣ ለማህበራዊ ደህንነትና ሰላም፣ በአጭሩ፣ ትውፊታዊ ባህሉን በመጠበቅ ለመቀጠል የሚከናወን ህዝባዊ ዐመፅ በመሆኑ ነው።

አጌም የሚካሄደው በህዝቡና በ“ኜያው” (በንጉሡ) ወይም በ”ኜያው” ጥላ ሥር በተዋረድ በሚገኙ ባህላዊ የአስተዳደር መሪዎች መካከል ነው። ይህ የሚሆነውም በ”ሮኒ” ማለትም ህዝብ በሚሳተፍበት በሥርዓተ-ንግሥ ጉባኤ፣

“በአኙዋ ባህል መሠረት ‹ኦቶችንግ› በግለሰቦች ወይም በመንደር ነዋሪዎች፣ በማህበረስብ (ኮሚኒቲ) ቡድኖች፣ ወዘተ፣ መካከል የተፈጠረን ከባድ ጥል ወይም ግጭት መፍቻ መንገድ የሆነው የ”ክዎር” ሕግ አንዱ ገፅታ ነው። ‹ኦቶችንግ› ሜታፈራዊ ወይም ስለምናዊ ትርጉም አለው። በሌጣው ሲተረጎም ግን ‹የእጅ-ማሠሪያ› እንደማለት ነው”

የንጉሥ ምርጫ ምክክር ጉባኤ አማካይነት በህዝብ የተመረጡ ባህላዊ የአስዳደር መሪዎች ሥልጣንን መከታ በማድረግ ጥንታዊ አባቶች ያቋቋሟቸውን “ቅዱስ” ሕግጋትና ደንቦች ጥሰው በተገኙ ጊዜ መሆኑን ተመልክተናል። የሮኒ የምርጫ ሥርዓተ-ክንዋኔም የተወሰኑ መሥፈርቶች አሉት። ከእነዚህ መካከልም ለንጉሥነት ወይም ለሹመት የታጨው ሰው ሰብዕና አንዱና ዋናው አጀንዳ ነው። ከሰብዕና የመመዘኛ መሥፈርት መካከልም ግለሰቡ በመራጮች ዘንድ በሕይወት ዘመኑ አጋጣሚዎች ያሳየው ትዕግሥት፣ ትኅትና፣ አክብሮት፣ ርኅራኄ፣ ለጋሥነት፣ ሚዛናዊነት፣ የንግግር ችሎታ (ተናግሮ የማሳመን)፣ ወዘተ. መሆናቸውን ለመጠቆም ተሞክሯል። አጌም በባህሉ የተፈጠሩ፣ ያደጉና የተዋቀሩ የአፈፃፀም ደረጃዎችና ደረጃዎቹ የሚከተሏቸው ደንቦች አሉት። ዓላማውም ጥፋት የተገኘበትን ኜያ ወይም ኳሮ አስወግዶ በምትኩ በሌላ ለመተካት ወይም ደግሞ በሠራው ጥፋት ተፀፅቶ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ለማድረግ ህዝቡ እንደ ግዴታ ወስዶ የሚያከናውነው እንቅስቃሴ ነው።

 ይህን ካስታወስን በኋላ በዚህ ፅሁፍ ትኩረት በመስጠት የምንመለከታቸው ዋና ጉዳይ የ“አጌም” ዐመፅ የሚካሄደው ለምንድን ተግባር ነው? ዐመፁ በማን ላይ ያነጣጥራል? አጌምን የሚያቀጣጥሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚሉት ላይ ነው።

 ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው የ“አጌም” ዐመፅ ዒላማ የሚያደርገው ‹ቅዱስ› ሕግ/ ሕጎችን በመጣስ ጥፋት በተገኘበት “ኜያ” (ንጉሥ) ወይም በሥሩ በሚያስተዳድረው “ኳሮ” (የአካባቢ ባህላዊ መሪ) ላይ ነው። ዐመፁ የሚካሄድበት ምክንያትም ንጉሡ ወይም ኳሮው ‹ቅዱስ› ሕጎችን በመጣሱ የተነሳ ጥንታዊ የአኙዋ አባቶች ሙታን መናፍስት በሀዘንና በቁጣ ዛሬ በሕይወት በሚገኘው ትውልድ በአጠቃላይም በሀገሩ ላይ ታይቶ የማያውቅ “አሼኒ” (ምጣት የሚያስከትል እርግማን) ያወርዳሉ” ከሚል እምነት የመነጨ ብርቱ ሥጋት ወይም ፍርሀት ለመከላከል ነው። በቆየው ትውፊታዊ (ፎክ) እምነት መሠረት በሕይወት ያለውን ትውልድ ከክፉ አደጋ የሚጠብቁት የሙታን አባቶች መናፍስት ናቸው። ይህን የሚያደርጉት ግን ትውልዶች መናፍስቱ በሕይወት እያሉ ለትውልድ ያወረሷቸውን ሕጎች፣ ትእዛዞች፣ ምኞትና ፈቃድ በመጠበቅ፣ በማሟላትና ደስ በማሰኘት ማረጋገጥ እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ሙታን መናፍስቱ ይከፋሉ፤ ይበሳጫሉ፤ በቁጣም የ“አሼኒ” ቅጣት ለማውረድ ይገደዳሉ። ይህ ከሆነ ደግሞ ድፍን አኙዋ በቋያ እሳት ሊወድም ይችላል፣ በውሀ ሊጥለቀለቅ ይችላል፣ በወራሪ ሊወረር፣ በወረርሽኝ በሽታ ወይም በድርቅና በረሀብ ሊያልቅ፣ ወዘተ. ይችላል። ስለዚህ ይህን ከመሰለው የ”አሼኒ” ቅጣት እንዳይደርስ በሥልጣን ላይ ሆኖ ሕግ ጥሶ በተገኘ ኜያ ወይም ኳሮ ላይ የአጌም ዐመፅ የሰላምና የደህንነት ዋስትና ተደርጎ ይከናወናል ማለት ነው።

“አጌም”ን በኜያው ወይም በኳሮው ላይ የሚያስነሱ ዐበይት ምክንያቶች በርካታ ናቸው። ቢያንስ ከ27 አያንሱም። ሁሉንም እዚህ ላይ ለመዘርዘር አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ የሚከተሉትን የተወሰኑ ምሳሌዎች ለአብነት ያህል ለአንባብያን እጠቅሳለሁ።

 1. አድልዖ መፈፀም፣ ፍርድ ማጓደል አንዱ ምክንያት ነው። ኜያው ወይም ኳሮው ሰዎችን በእኩል ዓይን በማየት ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት ይኖርበታል። ከዚህ ውጭ በሥጋ ዝምድና ወይም በቅርብ ወዳጅነት ተመርቶ በሰዎች መካከል አድልዖ ፈፅሞ ወይም ፍርድ አጓድሎ በተገኘ ጊዜ አጌም ይቀሰቀሳል።

2. “አጉዋጉዋ” አዘጋጅቶ ህዝቡን አለማገናኘትና አለማብላት ሌላው ምክንያት ነው። አጉዋጉዋ ንጉሣዊ ግብር፣ ድግስ፣ ማለት ነው። በደንቡ መሠረት አጉዋጉዋ (ንጉሣዊ ግብር) በዓመት ከተቻለ አራት ጊዜ፣ ካልተቻለ ሁለት ጊዜ በመደገስ አንድ ሰው ሳይቀር ትንሽ ትልቁን መጋበዝ፣ ማብላትና ማገናኘት ግዴታ ነው። ይህን በማያደርግ ኜያ ወይም ኳሮ ላይ የአጌም ዐመፅ ይቀራል ተብሎ አይታለምም።

 3. በጦርነት ጊዜ የአኙዋ በትረ- መንግሥት አርማዎችን (emblems of power) በፍርሀት ሥፍራ ሳያሲዙ (ሳይደብቁ) መሄድ ወይም ይዞ አለመሸሽና ለጠላት ምርኮ አሳልፎ መስጠት ሌላው የአጌም ዐመፅ ዋና መነሻ ምክንያት ነው።

 4. ስስታምነት (greediness):: ለጋስነት የኜያ ወይም የኳሮ የሰብዕና መለኪያ ተደርጎ ይታያል። ከዚህ ውጭ ስስታምነት በአኙዋዎች ዘንድ ውጉዝና የተጠላ ‹አሸኒ› ሊያወርድ የሚችል ክፉ ባሕርይ ተደርጎ ይታመንበታል። ለምሳሌ አጉዋጉዋ አራት ጊዜ፣ ካልሆነም ሦስት፣ ሁለት ጊዜ እያዘጋጀ ህዝቡን ማብላት፣ ማጠጣት፣ ማገናኘት፣ ማስደሰት ሲገባው ከስስታምነቱ የተነሳ የሚጠበቅበትን አሟልቶ ካልተገኘ በራሱ ላይ አጌም ይቀጣጠልበታል።

5. ኜያው ወይም ኳሮው ከሌሊቱ 6 ሰዓት በፊት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ፈፅሞ ሲገኝ። በእምነቱ መሠረት ከሌሊቱ 6 ሰዓት በፊት በተፈፀመ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ተፀንሶ የተወለደ ልጅ “ች-ጆቅ” ማለት ለሰው፣ ለሀገር የማይበጅ ፍጡር ይሆናል። ስለዚህ ኜያው ወይም ኳሮው ከሌሊቱ 6 ሰዓት በፊት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት

“ቆየው ትውፊታዊ (ፎክ) እምነት መሠረት በሕይወት ያለውን ትውልድ ከክፉ አደጋ የሚጠብቁት የሙታን አባቶች መናፍስት ናቸው። ይህን የሚያደርጉት ግን ትውልዶች መናፍስቱ በሕይወት እያሉ ለትውልድ ያወረሷቸውን ሕጎች፣ ትእዛዞች፣ ምኞትና ፈቃድ በመጠበቅ፣ በማሟላትና ደስ በማሰኘት ማረጋገጥ እስከቻሉ ድረስ ብቻ ነው”

መፈፀሙ ከተረጋገጠ አጌምን በማቀጣጠል ከስልጣኑ የሚያስወግድ ወይም የሚያስገርፍ ምክንያት ይሆናል።

 6. “ኦቶችንግ”ን በአግባቡ አለማከናወን። ከዚህ ላይ ‹ኦቶችንግ› የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ በቅድሚያ ለአንባብያን ማስታወስና ግልፅ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል። በአኙዋ ባህል መሠረት ‹ኦቶችንግ› በግለሰቦች ወይም በመንደር ነዋሪዎች፣ በማህበረስብ (ኮሚኒቲ) ቡድኖች፣ ወዘተ፣ መካከል የተፈጠረን ከባድ ጥል ወይም ግጭት መፍቻ መንገድ የሆነው የ”ክዎር” ሕግ አንዱ ገፅታ ነው። ‹ኦቶችንግ› ሜታፈራዊ ወይም ስለምናዊ ትርጉም አለው። በሌጣው ሲተረጎም ግን ‹የእጅ-ማሠሪያ› እንደማለት ነው። በጥልቅ ትርጉሙ ሲታይ ”ኦቶችንግ” (“የእጅ ማሠሪያ”) በቀል ላለመውሰድ ቃል ኪዳን መግቢያ” ማለት ነው። ከዚህ ላይ የማን እጅ ነው የሚታሠረው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱ እጃቸው የሚታሠረው የነፍሰ-ገዳይ ቤተሰብ አባላት (ወንድም፣ አጎት፣ አባት፣ ወዘተ)፣ በበቀል ደም እንዳይመልሱ ነው የሚሆነው። በባህሉ ደንብ መሠረት አንድ በእጁ ነፍስ የጠፋበት ሰው ወዲያው ሁኔታው እንደተፈፀመ ወደ ቤተሰቡ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ መደበቅ የለበትም። ይህ በፍፁም የተፈቀደ አማራጭ ባለመሆኑ አስነዋሪ ድርጊት ተደርጎ ይታያል። ከዚህ ይልቅ ማድረግ የሚኖርበት ችግሩ እንደተፈጠረ በተቻለ መጠን ጊዜ ሳያባክን በቅርብ ወደሚገኝ ወደ ንጉሡ ወይም ወደ ኳሮው “ቡራ” (ሠፈር) እየሮጠ በመሄድ እጁን መስጠት ይሆናል። እጁን በሚሰጥበት ጊዜም ስለተፈጠረው አደጋ መንስዔ ነገርና ውጤት ሳይጨምር፣ ሳይቀንስ፣ ለንጉሡ ወይም ለኳሮው ሪፖርት በማድረግ ጥግ እንዲሰጠው መጠየቅ አለበት። በዚህ ሁኔታ ፈጥኖ በመድረስ የሚገባውም በመንገድ ላይ በመዘግየት ወይም ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ በሚወስደው ጊዜ ውስጥ የሟች ወገን አግኝቶ የደም መመለሻ እንዳያደርገው ነው። የደም መመለሻ ከሆነ ግን ሰውየው ደመ-ከልብ ሆኖ ይቀራል። ስለዚህ በፍጥነት ደርሶ እንደተገለፀው የድርጊቱን ታሪክ አንድ በአንድ ዘርዝሮ ለንጉሡ ወይም ለኳሮው ሪፖርት በማድረግ መሣሪያውን አስረክቦ ለተወሰነ ጊዜ በቡራው ውስጥ ጥግና ከለላ ያገኛል። አሁን ወደተነሳንበት ዋና ነጥብ እናተኩር። ይህም ንጉሡ ወይም ኳሮው በበኩሉ ሰውየው ሪፖርት እንዳደረገ፡-

 አንደኛ፣ በግቢው ጥግና ከለላ የመስጠት፣ በሚቆይበት ጊዜ ምግብና መጠጥ እንዲሰጠውና ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ የማድረግ ግዴታ አለበት።

ሁለተኛ፣ የችግሩ ባሕርይ እንዳወቀ ወዲያው ለገዳይና ለሟች ቤተሰቦች መልእክተኛ በመላክ ወደ ቡራው ጊዜ ሳያጠፉ በቶሎ እንዲመጡ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።

ሦስተኛ፣ በቸልታ ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ወይም መልእክተኞቹ ዘግይተው በመካከሉ የሟች ቤተሰቦች በገዳይ ቤተሰቦች ላይ የበቀል እርምጃ ቢወስዱ ተጠያቂው እሱ ይሆናል። ይህ ከሆነ መዘዙ ብዙ ነው። ‹አጌም› አስነስቶ ሊገረፍ ወይም ከስልጣኑ ሊወርድ ይችላል። በመሆኑም ንጉሡ ወይም ኳሮው የላካቸው መልእክተኞች የሟችንና የገዳይን የቅርብ ዘመዶች ስለተፈጠረው ችግር ነግረው ጊዜ ሳይወስዱ ወደ ቡራው ይዘው መምጣታቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።

አራተኛ፣ ለግራ ቀኙ ቤተሰቦች መልእክተኞችን ሲልክም ንጉሡ ወይም ኳሮው በተጓዳኝ ማከናወን የሚገባው ተግባር ጀዶንጎዎችን (የሀገር ሽማግሌዎችን) በያሉበት አስጠርቶ እንዲመጡ ማድረግ አለበት።

 አምስተኛ፣ የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች እንደመጡ በጆዶንጎዎች ፊት ካለው ከራሱ ገንዘብ ከሌለውም ከአካከባቢው ነዋሪዎች ተበድሮ በገንዘብም ይሁን በጥሬ ዕቃ መልክ ለሟች ቤተሰብ ”ኦቶችንግ” (“የእጅ-ማሰሪያ”) የሚሆን ስጦታ የማበርከትና ጀዶንጎዎች በክወር ሕግ መሠረት እርቀ-ሰላም እንዲያወርዱ፣ ካሣም ለሚገባው እንዲያስከፍሉ ትእዛዝ የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል። በደንቡ መሠረት ለሟች ቤተሰብ ”ኦቶችንግ” የሚከፍለው ንጉሡ ወይንም ኳሮው ነው። በእጅ ማሠሪያነት የሚከፈሉት ባህላዊ ዕቃዎች ወይም ገንዘቦች “ዲሙኝ” ወይም “የኦቴኖ ጦር” ናቸው። “ዲሙኝ” ልዩና ውድ የሆነ ጨሌ ነው። ጦሩ ኦቴኖ የተባለ የአኙዋ ጥበበኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው ጥንታዊ ጦር ነው። በአሁኑ ጊዜ ወደ ብር እየተለወጠ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ ወይም ኳሮው ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን በቸልታ ወይም በግድ የለሽነት ሳያሟላ ቀርቶ ተጨማሪ ደም የፈሰሰ እንደሆን ህዝቡ በቁጣ አጌም በማቀጣጠል ከስልጣኑ በማስወገድ ገርፎ ሊያባርረው ይችላል ማለት ነው።

7. ኜያው (ንጉሡ) ወይም ኳሮው ሥልጣኑን መከታ በማድረግ የሀገር ሽማግሎች በሚያካሂዱት የሽምግልና ሂደት ጣልቃ በመግባት ፍትኅ እንዲጓደል ማድረጉ ከታወቀ የአጌም ዐመፅ በህዝብ ዘንድ ይቀጣጠላል። በአጠቃላይ አጌም እንዲቀጣጠል ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች እነዚህና የመሳሰሉ ባህላዊ መሪዎች በሚያደርጓቸው የትውፊታዊ ሕጎች ጥሰቶች የሚቀሰቀሱ ሲሆኑ በሚቀጥለው ፅሑፍ ህዝባዊ ዐመፁ የሚያልፍባቸውን ደረጃዎች፣ የሚከተላቸውን ደንቦችና የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ምን እንደሆኑ፣ ዐመፁ በየደረጃው በማን እንደሚመራ፣ እንዴት፣ መቼና የት እንደሚከናወን፣ የአጌም አማራጭ መፍትሔዎችና ውጤቶች ምን እንደሆኑ፣ ወዘተ፣ እንመለከታለን። እስከዚያው በደህና ቆዩ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top