ጥበብ በታሪክ ገፅ

ነባሩና አዲሱ፡- የባሕል ፍልሚያ (በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥራዎች)

(በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ሥራዎች)

1. እንደ መነሻ

ኢትዮጵያ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከአዳዲስ ሥልጣኔዎች ጋር የተዋወቀችበት፣ ልጆቿን ለትምሕርት ወደ ውጭ ሀገር መላክ ያበዛችበት፣ ከፍተኛ ሹማምንቷም ወደ ሩቅ ምስራቅ፣ አውሮፓና አሜሪካ መመላለስ ያዘወተሩበት፣ደርሰው ሲመለሱም ኢትዮጵያ እንደምን መሰልጠን እንዳለባት የሚያብሰለስሉበት ዘመን ነበር። በዚሁ ዘመን ነው፣ የሀገር ፍቅር ማኅበር የተመሰረተው፤ ተፈሪ መኮንን የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የተቋቋመው፤ ብርሃንና ሰላም (ድርጅቱም፣ ጋዜጣውም) የተከፈተው፣ በሙዚቃውም፣ በሥነጽሑፉም፣ በቴአትሩም መስክ እንቅስቃሴው የተሟሟቀው፤ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ትዳር የሚጠቁም መጽሐፍ የታተመው ወዘተ…

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ደግሞ በአማርኛ ሥነጽሑፍ ስማቸው ከሚጠሩ ከሃያኛው ክፍለዘመን መባቻ ደራሲዎች መካከል አንዱ ናቸው። በኢትዮጵያ ሃይማኖት፣ባህል፣ታሪክ፣ ቋንቋና ሥልጣኔ ዙሪያ ልብወለዶች፣ የጉዞ ማስታወሻዎች፣ የታሪክ መጻሕፍትና ለጠቅላላ ዕውቀት የሚረዱ ድርሳናትን ጽፈው አሳትመዋል። በደራሲነት ብቻ ሳይሆን፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣንነት ተሰይመው እስከ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ደርሰው፣ በ60 ዓመታቸው፣ በ1931 ዓ.ም ያረፉ ትጉና ንቁ ደራሲ ናቸው።

 ብላቴን ጌታ ኅሩይ ዘመናዊነት፣ እግሩን ሰድዶ በሀገሪቱ ላይ እንዲተከል ሁነኛ ሚና ከተጫወቱ ደራሲዎች መሃል አንዱ ሆነው በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የመጽሐፎቻቸውም ዐቢይ ቁም ነገር ለውጥ ነው። ‹የተሳሳተውንና በልማድ የቆየውን ነገር በማሻሻል ለማደስ ነው እንጂ ሌላውን ሰው ለመጉዳት ራስን ብቻ ለመጥቀም የታሰበ ነገር የለበትም።› ይላሉ፣በ‹አዲስ ዓለም› መግቢያ።

በየልብወለዶቻቸው ውስጥ የሚያነሱት ጭብጥ በተመለከተ ስመጥሩው የሥነጽሐፍ ባለሙያ ቴዎድሮስ ገብሬ፣አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣በ2002 ዓ.ም ባሳተመው፣‹ወዳጄ ልቤና ሌሎችም› መጽሐፍ ውስጥ፣‹‹የኅሩይ ድርሰቶች ማኅበራዊ ለውጥ ነው ግባቸው። ለውጥን ይናፍቃሉ፤ለውጥን ይጠራሉ፤ለውጥን ያሰፍናሉ።›› በማለት ያስተዋውቃቸዋል።

 ይህ መጣጥፍ፣ ነባሩ ከአዲሱ ባህል ጋር ያደርገው ስለነበረ ፍልሚያና ስለፍልሚያው ውጤት፣‹አዲስ ዓለም (የቅኖችና የደግ አድራጊዎች መኖርያ)› እና ‹የልብ አሳብ(የብርሃኔና የጽዮን ሞገሳ ጋብቻ)› በተሰኙ ሁለት ድርሰቶቻቸው ውስጥ መነሻነት በጨረፍታም ቢሆን የሚያሳይ ነው።

 2. የባሕል ጽንሠ ሃሣብ

 Edward Taylor የተባለ ተመራማሪ ‹Primitive culture› በሚለው መጽሐፉ ውስጥ እንዳስቀመጠው፣ ባሕል ውስብስብ ነው። ባሕል፣ ዕውቀትን፣ እምነትን፣ ሀገረሰባዊ ትውን ጥበባትን፣ ማኅበረሰባዊ ሕገ ደንቦችን፣ ልማዶችንና ማንኛውም ተቧድኖ የሚኖር ማኅበረሰብ በጋራ የሚያደርገውን ነገር ይጨምራል።

ማኅበረሰቡ በጋርዮሽ ያመነበትን ጉዳይ፣በድንገት ቸል ማለትና መንቀፍ በነዋሪው ዘንድ ያስቀጣል፤ ያስወግዛል። የሚታደሰው ቀስ በቀስ ነው። ነባሩን ባህል ማፍረስ አዲሱን ባህል ማነጽ ደግሞ ፍልሚያ ይኖረዋል። ነባሩ እንዳይለወጥ የአሮጌው ባህል ተከታዮች ሲታገሉ፣ የአዲሱ ባህል አቀንቃኞች ደግሞ አሮጌውን ለመጣል ባላቸው አለመስማማት ሰበብ ይጣላሉ፤ በዚህም ይጠላሉ፤ እስኪያሸንፍም – ብዙውን ጊዜ አሸናፊ ይሆናሉ – ይንገላታሉ፤ ይሰደባሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይሠደዳሉ፤ ይገደላሉም። ለዚህም ነው፣ ባሕልን ነባሩና አዲሱ በማለት በሁለት መክፈል ተገቢ የሚሆነው።

 3. የነባሩ ባሕልና የአዲሱ ባሕል ፍልሚያ (በብላቴን ጌታ ኅሩይ ድርሰቶች)

ነባሩ ባህል ተሽሮ አዲሱ ባህል እንዲነግስ የሚያደርጉት ብዙውን ጊዜ የተማሩ፣ ውጭ ሀገር ደርሰው የተመለሱ፣ የሌላውን አኗኗር የሚያውቁ ምሁራን፣ነጋዴዎችና ሀገር አሳሾች እንዲሁም ሰባኪያን ናቸው።

“ማኅበረሰቡ ግን፣ ከዚህ ቀደም እንዲህ ባለ መንገድ ሃሳቡን የገለፀ፣ ጢሙን ተላጭቶ፣ ኮቱን ለብሶ የተቀላቀላቸው አልነበረምና፣ በእንግዳ ባህርይው ተደናግጠው ከመሸሽ ይልቅ፣ ካደረበት ጋኔል ነፃ ይወጣ ዘንድ፣ ከእብደቱም እንዲፈወስ፣ አስረው ፀበል ወሰዱት”

ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ቴክኖሎጂ የራሱን ባሕል በማኅበረሰቡ ውስጥ ይተክላል።

ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ፣ ‹ባሕልና ልማት፣ ምንነታቸውና ትስስራቸው› (2004፡ 22)፣ በሚለው ጥናታቸው፣‹የዘመናዊ ባሕል ይዘቶች ከውጭ በተውሶ መውሰድ ምንም ችግር የለውም። በመላው ዓለም በየሥርዓተ-ባሕሉ ለምተውና ሰፍነው የሚገኙ እጅግ አብዛኛዎቹ የባሕል ይዘቶች ከውጭ የተወሰዱ ሆነው ሳለ፤ በየገቡበት ስርዓተ-ባሕል ውስጥ ፍፁም ከመዋሃዳቸው የተነሳ፤ የባዕድነት ደብዛቸው ጭራሹን ጠፍቶ የየሥርዓተ ባሕሉ አካልና አምሳል ሆነው ይኖራሉ› ይላሉ።

 በኅሩይ ልቦለዶች ላይ የምናገኛቸው መሪ ገፀባሕርያትም፣ የአዲሱ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎችና የአዳዲስ ሃሳብ አራማጆች ናቸው። መጀመርያ የሚፋለሙት ከቤተሰባቸው ነው። ቀጥሎ ከማኅበረሰቡ፣ ቀጥሎ ከቀሳውስቱ። ከሥራዎቻቸው መካከል ለአብነት ያህል ሁለቱን መርጠናልና፣‹አዲስ ዓለም›ንና ‹የልብ አሳብ›ን ነጥለን እንይ።

 በ‹አዲስ ዓለም› የተሰኘ መለስተኛ ልቦለዳቸው ውስጥ የምናገኛቸው አውቀን እንይ። አወቀ ስልጡን ነው። የሰለጠነውን ዓለም አይቷል። ያየውን አዲስ ነገር ወድዶታል። የወደደውን አዲስ ዓለም ደግሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲታወቅ፣እንዲለመድና የህይወታቸው አካል እንዲሆን ይፈልጋል። አወቀ፣ ዕውቀት አሳሽ ነው። ወደ አውሮጳ የተጓዘው፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ አውሮጳ ወሬ ይሰማ ስለነበረ ነው። ተራኪው፣ ‹ከልጅነቱ ጀምሮ ብልህ ነበረና […] ጥበብና ዕውቀትን ለመማርና እንደ አውሮጳ ሕዝብ ለመሰልጠን ይመኝ ነበር።› ይለናል።

 ይህን ምኞቱን ለማሳካትም፣ ወደ አውሮጳ የመሄድ ፍላጎቱ በአጭሩ እንዳይቀጭበት በማሰብ፣ በስውር ኮብልሎ ሄደ። ሄዶም ተማረ። ፓሪስ ሲሄድ የገጠመው ፈተና በትምህርቱ ጉድለት ወይም በአስተሳሰቡ ድክመት አልነበረም። አወቀ ፈተና የሆነበት መልኩ ነበር – ጥቁረቱ።

 አወቀ፣ ለሰባት ዓመታት ያህል ፓሪስ ቢቆይም፣ ስለተማረው የትምህርት ዓይነት በስፋት አልተተረከም። በመጀመርያው የልቦለድ ገጽ ላይ፣ ስለመሄዱና መመለሱ ተነግሮናል። የተመለሰ ዕለት ነው ፈተና የገጠመው።

 አባቱ አባቱን ጥየቃ፣ ወደ ተጉለት ሲሄድ መንገዱ አልመች ይለዋል። ፓሪስ ይንሸራሸር የነበረው በአውቶሞቢልና በሰረገላ። ተጉለት ደግሞ በበቅሎ። የፓሪስ መንገድ እንደ መተኛ ምንጣፍ የለሰለሰ፣ የተጉለት መንገድ ደግሞ ዳገት ቁልቁለት የበዛው። እንደ አብዛኛው ማኅበረሰብ በእግሩ እንዳይሄድ የፓሪስ ጫማ አጥልቋል።

 ከብዙ ጭንቀት በኋላ፣ አባቱ ዘንድ ሲደርስ፣ ደርሶም ከዘመዶቹ ጋር ሲገናኝ፣ በለበሰው ኮት የተነሳ ሊለዩት አልቻሉም። ተራኪው፣ ‹እንደ ፈረንጅ ኮት በመልበሱ ወንድማቸው መሆኑን አጡት› ይላል። ኮት በዘመኑ በሀገሪቱ ውስጥ የሚመረጥና የሚዘወተር አልነበረም። አወቀ ባደገበት አካባቢ፣ ኮት የሚያደርግ፣ ጫማ የሚጫመት ፈረንጅ ነው – መጤ።

 አወቀ ገና ዘመዶቹን እንደተገናኛቸው እነሱን የማይመስል ነገር እንዳለው ገባው። ጠፍቶ በመገኘቱ፣ ከተሰወረበት በመገለጡ፣ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ፣ ማረፊያ ወዳደረገው አባቱ ቤት ሲገባ፣ በተነወረ ዓይን ታየ፣ ተገለለ፤ እንደ እንግዳ ሆነ፤ ኮት ለበሰ።

 እንደኔ እንደኔ ኮቱ ምልክት ነው – ትዕምርት። ከምዕራባውያን እውቀት መጎንጨቱን፣ ማኅበረሰቡ መጤ ከሚለው፣ ባዕድ ብሎ ከሚያወግዘው አዲስ ባሕል ጋር መስማማቱን፣ ማዕድ መጋራቱን ያሳየበት ትዕምርት። አለባበሱ የእነሱን አልመሰለም። ‹ኮቱ› በሀገር ውስጥ ሙያተኛ በሸማኔ አልተበጀም፤ በጥጥ አልተፈተለም፤ መልኩም ቅርፁም የሀበሻ አይመስልም።

በሰባት ዓመት ውስጥ አወቀ ከማኅበረሰቡ ተለይቶ ወጣ። በእሱና በወጣበት ማኅበረሰብ መካከል ያለው ልዩነት፤ ቀስ በቀስ የሚገለጥና ገሀድ የሚወጣ ሳይሆን ወዲያው የሚታወቅ ሆነ። ስለዚህም፣ አወቀ፣ ‹እንደ ፓሪስ ሰዎች ጢሙን ሁሉ በሙሉ ላጭቶት ነበረና በጦርነት ውስጥ የተጎሳቆለ መስሏቸው ደነገጡ› (ገጽ 3)፣ ወንድማቸው መሆኑንም ተጠራጠሩ፤ በትክክልም አወቀ መሆኑን ባወቁ ጊዜ፣ በአለባበሱ ተቹት፤ ተዘባበቱበት፤ ‹እንዴት እንደ እብድ ጥብቆ ብቻ ለብሰህ ትሄዳለህ› አሉት።

 አወቀ፣ ከቤተዘመዶቹ ጋር፣ እንኪያ ሰላንቲያ የገጠመው በመጀመርያው ቀን ነው። ‹እንደተያዩ ተለያዩ› እንዲሉ። ነባሩን ባሕላዊ ልብስ ተቸው። ነጭ በመሆኑ እድፍ አይችልም አለ። ጥቅሙንም ውስን አደረገው – ለብርድ መከላከያ ብቻ። የአውሮጳን ልብስ ግን ከፍ ከፍ አደረገው። እነሱን የመምሰልና ኩታ የመልበስ ፍላጎት እንደሌለው በንግግሩ አስታወቃቸው። ‹እናንተም፣ ኩታ መልበሳችሁ – (እስኪበቃው ካጥላላ፣ ከጠላሽና ኋላ ቀር ካስደረገ በኋላ) – እኔም እንዲህ መልበሴ የምርጫ ጥያቄ ነው፤ የሚያነቃቅፍ ነገር የለበትም› አለ። ማኅበረሰቡ ግን፣ ከዚህ ቀደም እንዲህ ባለ መንገድ ሃሳቡን የገለፀ፣ ጢሙን ተላጭቶ፣ ኮቱን ለብሶ የተቀላቀላቸው አልነበረምና፣ በእንግዳ ባህርይው ተደናግጠው ከመሸሽ ይልቅ፣ ካደረበት ጋኔል ነፃ ይወጣ ዘንድ፣ ከእብደቱም እንዲፈወስ፣ አስረው ፀበል ወሰዱት።

 ‹አወቀ ዕውቀቱ በትምህርት የፀና ስለሆነ በዘመዶቹ ማስፈራራት የለበሰውን ኮት ለመለወጥ አልወደደም።› ኮቱን አለመለወጡ፣ በአቋሙ ፀንቶ የመቆየቱ፣ እነሱን ለመምሰል አለመፈለጉ፣ ከስልጣኔ አካሄድ ለማፈግፈግ አለመሻቱ ማሳያ ምልክት ነው። ከአንድ ወር እስራት በኋላ፣ ወደ ቀደመ ልማዱ የማይመለስ መሆኑን ተገንዝበው፣ እንደ ፈቃዱ ይሁን!› ብለው ፈቱት። አወቀ ‹በተማረው ትምህርት ለመንግሥቴ አገለግላለሁ፤ ሰውነቴን ደስ አሰኛለሁ እያለ ሲያስብ ገና በመጀመሪያ እንደዚህ ያለ ሁከት ስለአገኘው እጅግ አዘነ› (ገጽ 5)፣ ከፓሪስ ተነስቶ ወደ ሀገሩ ለመግባት በመወሰኑም ተቆጨ።

በዚህ የሀዘንና የቁጭት ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ አባቱ፣ አቶ እንደልቡ ታመሙ። ሕክምና ያገኙም ዘንድ አዲስ አበባ ደርሶ ሐኪም አስከትሎ ተጉለት ገባ። የሐኪሙ

“በሥራዎቻቸው ውስጥ እንዳየነው፣ያለ ቀሳውስቱ ይሁንታ ልማድ አይጣስም፤ ሥርዓት አይታደስም፤ ለውጥ አይታወጅም። ቀሳውስቱ ሕዝቡን ከፈጣሪ ጋር ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ከመንግስት ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ነበሩ”

መምጣት ግን እጅግ አስቆጣቸው። የፈረንጅ መድኃኒት ከሚጠጡ፣ ደብተራ ዘንድ ሄደው መጽሐፍ ተገልጦላቸው፣ ባህላዊውን መድኃኒት ቢወስዱ የተሻለ እንደሚሆን ነገሩት። ‹… መጽሐፍ አስገልጥላቸው። የሐኪም መድኃኒት ግን ምንም ቢሆን አናቀምሳቸውም› አሉት። ሃሳቡ ተቀባይነት አጣ። ድካሙ በከንቱ ሆነ። በዚህም የተነሳ ሀዘኑ በዛ። ‹አሳቡና አሳባቸውም ባለመጋጠሙ እጅግ ተበሳጨ› (ገጽ 6)

 የአባቱ ህመም እየጠነከረ ሄደና አረፉ። በጌምድር ያሉ እህቶቹ ለመቃብር እንዲደርሱ ጥሪ ይሰደድላቸው ተባለ። መልዕክተኛ እንላክ ብለው ሲማከሩ፣ አወቀ አሽከሩን ጠርቶ፣ በቅሎ አስጭኖ፣ አንኮበር ስልክ ቤት ሄዶ፣ የአባታቸውን መታመም ተናግሮ በፍጥነት እንዲደርሱ እንዲናገር ላከው። ስልክ በዘመኑ እንግዳ ነገር ነበር። ስሙም  አገልግሎቱም መታወቅ የጀመረው ከነፃነት መመለስ በኋላ ነው። ፋሽስት ጣልያን ድል ተደርጎ ከወጣ በኋላ ስልክ እንግዳ መሆኑ ቀረ።

 አወቀ፣ የአዲሱ ባህል ተቋዳሽ ነውና፣ መልዕክተኛን ከማድከም ይልቅ በቴክኖሎጂ ታግዞ መልዕክት ማስተላለፍን መረጠ። መልዕክቱ የደረሳቸው የበጌምድር ሰዎች ግን ስለ ስልክ የሚያውቁት ነገር አልነበረምና ግራ መጋባትና መደናገጥ በመካከላቸው ሰፈነ።

እህቶቹ ግን የውሃ ሽታ ሆኑ። የስልኩ መልዕክት ባይደርሳቸው ነው ተባለ። አወቀ እግረኛ፣ አንድ ወር የሚፈጅበትን መንገድ፣ ስልከኛው በፍጥነት መልዕክት እንደሚያስተላልፍ በነገራቸው ጊዜ ግራ ተጋቡ። ‹ፓሪስ ደርሶ የተመለሰ ሁሉ እየዞረ መበላሸቱን ስናውቅ አንተን አምነን መላክተኛ ሳንልክ መቅረታችን እብዶቹ እኛ ነን› አሉት።

 በዚህ ዘመን፣ አውሮጳ ደርሰው የተመለሱ የተነወሩ፣ የተገለሉና እንደዞረባቸው የሚቆጠሩ ነበር፡ ሌላው ቀርቶ፣ ሰሜን ሸዋ፣ አወቀ በተወለደበት አካባቢ የተወለዱ፣ የፓሪስን ሕይወት የቀመሱ፣ ዘመናዊውን ባህል የቀሰሙ፣ እንደ ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም ያሉ ልሂቃን ነበሩ።

 የአወቀ ፈተና ብዙ ነው። አወቀ ሥራውና ሃሳቡ ያሟግት የነበረ ሰው ነው። የሰማው ላልሰማው፣ ያየው ላላየው ሥራውንና ሃሳቡን እየተረከለት፣ዝናው ከተወለደበት አካባቢ ወጥቶ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ዘመተ። ከፊሉ ይቀበለዋል፤ ከፊሉ ይቃወመዋል። በይበልጥ አባቱ አርፈው፣ ትልቅነታቸውበን የሚመጥን የአርባ ድግስ/ተዝካር ይዘጋጅ ሲባል፣ የተዝካርን ልማዳዊ ስርዓት ማጣጣሉ፣ ‹ዘመድ ወዳጆቼን የሰብል ሥራችሁን ትታችሁ ድግስ አሰናዱልኝ አልልም፤ ባይሆን ገንዘቡን ለቤተክርስቲያን እሰጣለሁ፤ለነዳያን እመጸውታለሁ› ማለቱ፣ታላቅ ቅሬታና ጉርምርምታ ፈጠረ። በተለይ መምሬ ሰባጋዲስ፣ እንዲህ ያለው ልማድ ሲደረግ አይተው አያውቁምና ተቆጡ። ‹በአቶ እንደልቡ ተዝካር ካህናቱ ካልተሳከሩበትና በዋንጫ ካልተማቱበት ምን ተዝካር ወጣ ይባላል፤ እናንተ የኋላ ልጆች ወደ ፓሪስ መሻገር ከጀመራችሁ ወዲህ የምታመጡት ፈሊጥ ሁሉ ለእኛ አይገባንም።› አሉት። (ገጽ 14) ‹እንገዝትህሃለን!› ቢሉትም ከአቋሙ አልተመለሰም። ካህናቱ ለተጋነነ መብልና መጠጥ የሚሰጡት ከበሬታ እጅጉን አስተከዘው። የገዛ እህቶቹ እንኳን የሃሳቡ ተጋሪ አልሆኑም። ከመምሬ ጋር ሆነው አዘኑበት፤ አደሙበትም።

ይህ የተዝካር ጉዳይ ዕጨጌ ጆሮ ደርሰናም፣ በቀሳውስቱ ዘንድ ምክርና ሙግት ተካሄደበት። ካህናት ወደ ተዝካር ቤት ከሚሄዱ ይልቅ፣ካህናቱ የተዝካሩን ገንዘብ እየተቀበሉ፣በገንዘቡ የወደዱበትን ቢገዙበት፣ ቤተሰቦቻቸውን ቢጠቅሙበት፣ ራሳቸውን ከስካር ቢያቅቡበት የተሻለ እንደሆነ ታመነበት። ጉባኤም ተጠራ። ሁለቱ ባህሎች – ነባሩና አዲሱ – በሊቃውንቱ ይዳኙ ጀመር። አዲሱ ባህል ተቀባይነት አገኘናም፣ ተዝካር ምን መምሰል እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተው ቋሚ ደንብ አወጡ። ‹በስህተት ገብቶ ልማድ ሆኖ የኖረውን ሁሉ ተማክረን ብናሻሽለው አይሻልምን› ተባባሉ። እግረ መንገዳቸውንም፣ አንድ ወንድ ላንዲት ሴት ብቻ መሆን እንዳለበትና በየጊዜው እያገቡ የሚፈቱትን ካህናት መቃወም፣ የግዕዝ ቋንቋ ሣይችሉ በሃይማኖቱ መሰረት ያለው ዕውቀት ሳይኖራቸው አገልግሎት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑትን መቃወም፣ባለጸጋ ሲሞት ረዘም ያለ ፍታት፣ ለደሃው ግን ጸሎቱን በአጭር የሚደረገውን አድልዎ መቃወም፣ ካህናቱ በግዕዝ የሚያቀርቡትን ስብከት ምዕምኑ በቅጡ ስለማይረዳው፣ በአማርኛ

“የኅሩይ ድርሰቶች በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ናቸው። መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እሳቸውም ሆኑ የሚፈጥሯቸው መሪ ገፀባህርያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ናቸው።”

ተተርጉሞ እንዲቀርብና ይህን በመሰለው ተራማጅ ሃሳብ ዙርያ መወሰንና መወያያት ጀመሩ። አወቀ ምክንያት ሆኗቸውም፣ልማዱን ከሃይማኖት አበጥረው ለመመለየት ለተጨማሪ ጉባኤ ተቀጣጠሩ።

 አወቀ፣ ለአባቱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ፣ አንድ ጎጆ ከመስራት ይልቅ፣ የአባቱን ስም፣ የተወለዱበትና የሚቱበትን ቀኝ የሚጠቅስ 80 ሳንቲም ጥርብ ድንጋይ በማቆሙም በመምሬ ሰባጋዲስ ዘንድ ተወግዟል። ከአወቀ በፊት በቤተክርስቲያን ጓሮ ይህን የመሰለውን መታሰቢያ ያቆመ አልነበረምና፣ወደ ቤቱ ገስግሰው ቅሬታቸውን በከበደ ሁኔታ ሲገልጹለት፣ ‹በአባቴ መቃብር ላይ ቤት ብሰራ ከእንግዴህ ወዲህ አባቴ ተነስተው አይበሉበት፣አይጠጡበት፣ ተድላ ደስታ አያደርጉበት፤ ከዘመድ ወዳጅ ጋራ አይጫወቱበት። ለስማቸው መታሰቢያ እንደሆነ ያቆምሁት ደንጊያ እስከ አስር ሺህ ዓመት ሳይጠፋ ይቆያል። የእንጨትና የሳር ጎጆ ባቆምበት ግን ባመቱ አርጅቶ ይወድቃል(ገጽ 32-33)

 የአወቀ ሌላኛው ጸብ ከዘመዶቹ ጋር ነበረ። ዘመዶቹ ሚስት አጩለት። እሱ ግን ያላየኋትን፣ የማላውቃትን፣ እኔን ለማግባት ፍቃደኛ ትሁን አትሁን የማላውቀውን፣ አብረን ተስማምተን ለጋብቻ ዝግጁ መሆናችን ሳንወስን እንዴት ሃሳባችሁን እቀበላለሁ ብሎ ምርጫቸውን ተቃወመ። ዘመዶቹም፣ ‹በፊትም ነገሩን ማሳወቃችን አንተ ከፓሪስ ከተመለስህ ወዲህ አመልህ ተለውጦአልና ብንፈራህ ነው እንጂ እንደ ሀገራችን ልማድ ቢሆን የሰርጉ እለት ብቻ ተነሳ ብለን እንወስድህ ነበረ አሉት› (ገጽ 34) አወቀ በራሷ ስልጣን የምትወስነውን እንጂ ለጋብቻ እጅ ሲዘረጋላት ቤተሰቦቼ ያውቃል የምትለውን የማግባት ፍላጎት አልነበረውም።በዚህም ዳግም ጭቅጭቁ አገረሸ። ወደ ታጨችው ልጃገረድ አባት ሄደው ይቅርታ ጠየቁ።

አወቀም ሚስት ፍለጋ ወደአዲስ አበባ መጣ። የምትመጥነውንም አገኘ። ሃይማኖታዊ በሆነ ሥርዐት ጋብቻቸው ተፈጸመ።ወደ ተጉለትም ሥራውን ይዞ ጓደኞቹን አስከትሎ መጓዝ ቀጠለ። ዘመዶቹ ቀደም ሲል ስላሳፈራቸው፣ ያለእነሱም ዕውቅና ሚስት ስላጨ፣ በሰርጉ ለመገኘት አመነቱ። ስማችን ይጠፋል፤ አገሉሉት እንባላለን ብለው እቤቱ ቢገኙም የሚያውቁት ዓይነት መስተንግዶና ቸበርቻቻ አልጠበቃቸውም። ግርግሩም፣ ምግቡም ደበዘዘባቸው። የተጣለ የተንጣለለ ዳስ ቀርቶ ከወትሮ የተለየ መቀመጫም አልተሰናዳ። በራሳቸው ፈቃድም፣ ዘመድ የሌለው አናስመስል ብለው በእኩለ ሌሊት ድለቃውን ጀመሩት። አወቀ ከእንቅልፉ በዘፈናቸውና ዳንኪራቸው ብዛት በርግጎ ተነሳ፤ ዘፈናቸውን የአረማውያን፣የዘማውያንና የመሃይማን እንጂ የክርስቲያን አይደለም ብሎ ተቃወመ። ተጫውተው ማደር ከፈለጉም፣ ምን በሰርጉ ምን ሊሰማበት እንደሚፈቅድ ለማሳወቅ፣ በግራማፎን ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ በግዕዝ የተደረሰ የጋብቻ መዝሙር ከፍቶ አሰማቸው። እነሱ ግን፣ እኛ ባገራችን ባልና ሚስት ሲጋቡ የሚዘፍነው ጫጉላሽ አብቧል ዛሬ እየተባለ ነው፤ከስብስቴና ከአብየ አምሃ ኢየሱስ አስቀድሞ የነበረውን የሰርግ ዘፈን አሁን አንተ ልትለውጠው ነውን ያንተ ሰርግ የሰርግ መጀመርያ አይደለም አሁንም አትጨቅጩቀን እንሄድልሃለን ዛሬ ሙሉ ጨረቃ ናትና፤ እስቲነጋም አንቆይም ብለው እየተቆጡ ሔዱ(ገጽ 47)የአወቀ ጉዳይን እርም ብለው፣እንደ ሞተ ዘመድ ለመቁጠር ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደረሱ።

ሆኖም፣ከብዙ ቆይታ በኋላ፣ሃሳቡ ከሃሳበቸው ይስማማ ጀመረ። ቀስ በቀስም ደጋፊ ተከታይ አገኘ፤የጋብቻ ስርዓት እንዳይፈረስ፣ተላላፊ በሽታዎች እንዳይበዙ መግቻ የሚያበጅ መሆኑን ይመሰክሩለት ያዙ። ይቅርታም ጠየቁት። አወቀም ይህን በሰማ ጊዜ ከደስታው ብአዛት የተነሳ ደነገጠ። እርቃቸውም በመሃላ ተፈጸመ። ከመምሬ ሰባጋዲስ ጋር ለማስታረቅም ስምምነት ላይ ደረሱ። መምሬም፣ ‹ዛሬ ዘመኑም፤የሰው እውቀት ተለዋውቷልና እንደ ዘመኑ መሥራት ይሻላል ዘመንየማይለውጠው የሃይማኖትን ነገር ብቻ ነው፣እንጂ የልማድ ነገር ንጉሥንና መንግሥትን ወይም ሕዘእብን የሚጎዳ ካልሆነ በቀር ጥቅሙን እያመዛዘኑ ቢለውጡት አያስቸግርም ተብለው በአንኮበር አለቃ ተመክረው ወደ አወቀ ሃሳብ መጠጋት ጀመሩ። ታሪኩም፣የአወቀ ተልዕኮም ተጠናቀቀ።

 የኅሩይ ድርሰቶች በአብዛኛው ሃይማኖታዊ ናቸው። መሰረታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እሳቸውም ሆኑ የሚፈጥሯቸው መሪ ገፀባህርያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ናቸው።

“ከብዙ ቆይታ በኋላ፣ሃሳቡ ከሃሳበቸው ይስማማ ጀመረ። ቀስ በቀስም ደጋፊ ተከታይ አገኘ፤የጋብቻ ስርዓት እንዳይፈረስ፣ተላላፊ በሽታዎች እንዳይበዙ መግቻ የሚያበጅ መሆኑን ይመሰክሩለት ያዙ። ይቅርታም ጠየቁት። አወቀም ይህን በሰማ ጊዜ ከደስታው ብአዛት የተነሳ ደነገጠ”

ኅሩይ፣ የቤተክህነት ዕውቀታቸው ከፍ ያለ ነው። በየአብያተ ክርስቲያናቱም አገልጋይ ሆነው ሰርተዋል። ያም ሆኖ ግን፣ እሳቸው በሚከተሉት፣ ገፀባህርያታቸውም በሚያምኑት ሃይማኖትና ቀሣውስቱ በሚሰብኩት ልማዳዊ እምነት መካከል ልዩነት ነበረ።ሁለቱም በየአዋልዱ ላይ የተጻፈውን ይሞግታሉ፤ ያንኳስሳሉም። በተረት የተበረዘ የመሰለ ሃይማኖታቸውን ለማጥራትና ወደ ነባር ክብሩ ለመመለስ እጅጉን ይጥራሉ። ገፀባህርያቱ የሚሞግቱት ሃይማኖቱ ለዘመናት ሲከተለው የቆየውንና በልማድ ተለውሶ የቆየውን ነው። ደራሲው ያረጀ የሚሉት ባህል ተሸሽጎ ያለው ቀሳውስቱ ጉያ ውስጥ ነው የሚል እምነት አላቸው።

በሥራዎቻቸው ውስጥ እንዳየነው፣ያለ ቀሳውስቱ ይሁንታ ልማድ አይጣስም፤ ሥርዓት አይታደስም፤ ለውጥ አይታወጅም። ቀሳውስቱ ሕዝቡን ከፈጣሪ ጋር ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ከመንግስት ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ነበሩ። የሚፈሩትም የሚያፍሩትም የለም። በ‹አዲስ ዓለም› ውስጥ ያየነው እውነትም ይህንን ነው። ለውጡ በአወቀ ጠንሳሽነት ቢንሰራፋም፣ጸንቶ የቆመው ግን፣በቀሳውስቱ ይሁንታና የለውጡ ደጋፊ ለመሆን ድምጻቸውን በማሰማታቸው ነው።

 በነገራችን ላይ፣‹አዲስ ዓለም›፣ ለመጀመርያ ጊዜ ደራሲው ራሳቸው በከፈቱትና ‹ጎሃ ጽባሕ› ተብሎ በሚጠራው ማተሚያ ቤት በ1925 ዓ.ም የታተመ ድርሰታቸው ሲሆን፣ ይህ ልቦለድ ለመጀመርያ ጊዜ ለንባብ ሲበቃ፣ የደራሲውን ስም ከመጥቀስ ይልቅ፣ ‹ያገሩን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን መታደስ ከሚወድ ካንድ ሰው የተጻፈ› የሚል ቃል ነበር የሰፈረበት። ይህን ማለታቸው በአንድ በኩል፣ ከዚያን ዘመን ቀደም ብሎ ለኅትመት ይቀርቡ የነበሩ አንዳንድ ድርሰቶች የደራሲውን ስም ከመግለጽ ይልቅ፣ ይህን ወይም ይህን መሰል አገላለጽ መጠቀም የተለመደ ሆኖ ስለነበር ይሆናል። በሌላ በኩል፣አንዳንዶች ይህን አገላለጽ፣ ኅሩይ ሊጠቀሙ የቻሉት፣ መጽሐፉ ያነሳው ጭብጥ በቤተክርስቲያኒቱ ቁጣ ሊያስነሳ እንደሚችል ገምተውና ከስማቸው ይልቅ ሃሳባቸው ትኩረት እንዲስብ ፈልገው ነው ይላሉ። (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ‹ወዳጄ ልቤና ሌሎችም› በሚል ርዕስ ይህን መጽሐፍ ከሌሎች አራት መጽሐፎቻቸው ጋር አዳብሎ ሲያወጣው፣ አውቆ በድፍረት ወይም ሳያውቅ በስህተት ይህን መረጃ ገድፎታል።) ይቀጥላል …

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top