ዘባሪቆም

ሞትና ሎተሪ

ቢል ሞርጋን የተባለ አውስትራሊያዊ በደረሰበት አሰቃቂ የመኪና አደጋ በህክምና ቋንቋ ‘ሞቷል’ ከተባለ ከደቂቃዎች በኋላ ነፍስ ዘራ። ለ12 ቀናት ‘ኮማ’ ውስጥ ከቆየ በኋላ በመትረፉ ተስፋ ያጡ ሃኪሞች ቤተሰቦቹ የህይወት ማቆያውን ነቅለው ከስቃይ እንዲገላግሉት መከሩ። የ37 ዓመቱ ጎልማሳ ግን ያለ አንዳች አካላዊ እንከን ዳግም ወደ ህይወት ተመለሰ። በዓመቱ ሊዛ ዌልስ ለተባለች ፍቅረኛው የጋብቻ ጥያቄ አቅርቦ የአዎንታ ምላሽ አገኘ። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ደግሞ ሎተሪ ሲፍቅ 17 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር ዋጋ ያለው መኪና አሸነፈ።

 ይህን አስገራሚ ክስተት ምክንያት በማድረግ አንድ የሜልቦርን ቴሌቪዥን በሞርጋን ዙሪያ ፕሮግራም ለመስራት አሰበ። በፕሮግራሙ መሰረት ሞርጋን አዲስ የሎተሪ ትኬት ገዝቶ ካሜራ ፊት በመፋቅ መኪናውን ሲያሸንፍ የተሰማውን ስሜት ለማሳየት ተስማማ። ሞርጋን ትኬቱን ገዝቶ የቴሌቪዥን ካሜራ ፊት መፋቅ እንደጀመረ ግን ድንገት ቀጥ አለ። በዕቅዱ መሰረት “መኪና አገኘሁ!” እያለ በደስታ በመጮህ ፋንታ “250 ሺህ ዶላር ደረሰኝ! እየቀለድኩ አይደለም!” ሲል ባዲስ ደስታ ፈነጠዘ። ሁኔታውን የሚቀርፁት የቴሌቪiዥን ሰዎች በዚህ አስደማሚ ክስተት ሌላ የሰባ ወሬ ይዘው ተመለሱ። እጮኛው ሊዛ በበኩሏ “ዕድሉ ሁሉ በዚህ ተሟጦ እንዳላለቀ ተስፋ አለኝ” በማለት ቀሪ ዘመናቸው የተድላ እንዲሆን ተመኘች።

 *** ፍራንኮ ስላክ ሞትን ለ7 ጊዜ ያመለጠ ክሮሽያዊ የሙዚቃ መምህር ነው! ተዓምረኛው ፍራንኮ ከሞት ጋር የድብብቆሽ ድራማ የጀመረው በ1962 እ.አ.አ. ገና የ33 ዓመት አፍላ ጎልማሳ እያለ ነበር። ወቅቱ ፍራንኮ ከሳራየቮ ወደ ደብሮቭኒክ የተባለ ቦታ ይጓዝበት የነበረው ባቡር ከመስመሩ ወጥቶ በረዷማ ወንዝ ውስጥ በመውደቁ የ17 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ እርሱ ግን ከደረሰበት የክንድ ስብራትና ሃይፖተርሚያ (hypothermia) የተሰኘ ከሰውነት ቅዝቃዜ ጋር የተገናኘ ህመም በስተቀር በዋና ነፍሱን ሊያተርፍ ችሏል።

ከዓመት በኋላ ደግሞ በህይወቱ የመጀመሪያ በሆነው የአውሮፕላን ጉዞው ላይ ሳለ የአውሮፕላኑ በር ይገነጠልና [እግዚአብሔር ያሳያችሁ] ወደ ምድር ይከሰከሳል። በአደጋው 19 ሰዎች ሲሞቱ አውሮፕላኑ ከወደቀበት ስፍራ ራቅ ያለ የሳር ክምር ላይ በሰላም የማረፍ እድል የገጠመው ፍራንኮ ያላንዳች ጉዳት ተረፈ። በአደጋና ተዓምራዊ ገጠመኝ የተሞላው የፍራንኮ ህይወት በዚህ አላቆመም። በ1966 ይጓዝበት የነበረ አውቶቡስ አሁንም ወንዝ ውስጥ ይገባና 4 ሰዎች ሲሞቱ ልማደኛው ፍራንኮ ዋኝቶ ነፍሱን አዳነ። አነስተኛ ጉዳት ብቻ ነበር የደረሰበት።

 በ1970 እንዲሁ ይነዳው የነበረው የገዛ መኪናው በእሳት ይያያዝና ሙሉ ለሙሉ ከመፈንዳቱ ከሰከንዶች በፊት አቁሞ በመውጣቱ አሁንም ራሱን ከሞት ሊታደግ ችሏል። በተመሳሳይ ከሶስት ዓመታት በኋላ በነዳጅ መቅጃ ችግር ምክንያት የጋለ ሞተሩ ላይ ጋዝ ይፈስና አየር ማስወጫው በእሳት ነበልባል ይነዳል። ይህም አብዛኛውን የፍራንኮ ፀጉር ከመብላት ባለፈ ህይወቱን አንዳች ሳይፈታተን እንደሌሎቹ ጊዜያት ሁሉ አደጋውን አለፈው።

በ1995 ፍራንኮ ዛግሬብ ውስጥ በአውቶቡስ ተገጨ፣ ሆኖም በአነስተኛ ጉዳት ህይወቱ ቀጠለ። በመጨረሻም በዓመቱ ማለትም በ1996 በተራራማ መንገድ መኪናውን እያሽከረከረ ባለበት አንድ ጥግ ላይ ሲታጠፍ ከፊት ለፊቱ ከሚመጣ የተባበሩት መንግስታት ከባድ መኪና ጋር ፊትለፊት ይገጣጠማል። በዚህ ጊዜም ፈጥኖ በመውጣት መኪናው ከስሩ በ300 ጫማ ርቀት ወደታች ወድቆ ሲጋይ አደጋውን ዛፍ ላይ ቁጭ ብሎ በማየት አሳለፈው።

 ከዚህ ሁሉ ፈተናና ዕድል በኋላ በ2005 የ76 ዓመቱ አዛውንት ፍራንኮ ስላክ ለ40 ዓመት የተወውን ሎተሪ ቆረጠ። ከብዙ መዓትና ፈተና ያወጣው ዕድሉ አሁንም ከርሱ ጋር ነበር። ፍራንኮ የ600,000 ፓውንድ ወይም 1 ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ ሆነ! ይህን ተከትሎ 5ኛ ጋብቻውን ያከበረው ፍራንኮ “እንደምገምተው ያለፉት ትዳሮቼም ራሳቸው አደጋዎች ነበሩ” ሲል ፈገግታ አጫሪ አስተያየት ሰጠ።

 በርካቶች የዚህን ሰው ህይወት ከእድል ጋር በማገናኘት ፍራንኮን የዓለማችን ዕድለኛ ሰው ቢሉትም እርሱ ግን እድለኛ ነኝ ብዬ አላምንም ይላል። “ከዚህ ሁሉ የሞት አደጋ በመትረፌ እድለኛ ነኝ አልልም- ይልቁንም ከመጀመሪያው እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መግባቴ ዕድለቢስነት ነው ባይ ነኝ” ይላል። ሎተሪው እንደደረሰው ሁለት ቤቶችና አንድ ጀልቫ የገዛ ቢሆንም፣ “ገንዘብ ብቻውን ደስታን እንደማይገዛ” የተረዳው ፍራንኮ አብዛኛውን ገንዘብ ለወዳጆቹና ለዘመዶቹ አከፋፍሎ ኑሮውን በቁጠባ መምራት ቀጠለ። ͱ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top