ጥበብ በታሪክ ገፅ

ሐጅና የሐጅ ከበራ መንፈሳዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ታሪካዊ ፋይዳ

የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከእስልምና መሰረቶች አምስተኛው ነው። ከመላው አለም ከሚገኙ ሙስሊሞች መካከልም ከሶስት ሚሊዮን የሚበልጡት በየአመቱ የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ። ይህ መንፈሳዊ ጉዞ በአለም ከሚታወቁ፣ በተሳታፊ ብዛት፣ ባለመቋረጥ፣ በሰላምና በመረጋጋት፣ በጊዜ ርዝመትና ቀጣይነት ቀዳሚው እንደሆነ ይታመናል። የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ በጊዜና በቦታ ውስጥ በልዩ ልዩ ድርጊቶች፣ ተረኮች፣ እምነቶች፣ የሰብዕና ቀረጻዎች፣ ወዘተ የሚገለጽ ከበራ ነው። በዚህ አጭርና የዳሰሳ ጽሑፍ የተዘረዘሩ የሐጅ ይዘቶችን ከቦታ አንጻር ቀሪ ይዘቶችን ለመግለጽ ይሞከራል።

 ሐጅ በእስልምና አውድ መካ የሚገኘውን የአላህን ቤት መጎብኘት ማለት ነው። ይህ መንፈሳዊ ጉዞም ከእስልምና አምስቱ ማእዘናት አንደኛው ሲኾን ለስንቅና ለመጓጓዣ እንዲሁም ለቤተሰቡ ቀለብ ያለው ሙስሊም ሁሉ (ወንድም ሴትም) በእድሜው አንድ ጊዜ የሐጅን ስነ ስርዓት መፈጸም አለበት። የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ በሂጅራ አቆጣጠር በአስራ ሁለተኛው የዙልሒጃህ ወር ከስምንተኛው እስከ አስራ ሶስተኛው ባሉት ስድስት ቀናት ውስጥ ይፈጸማል።

የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ በአላህና በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) የታዘዘ ነው። አላህ በቁርአኑ ስለ ሐጅ እንደሚከተለው ያዛል፡ – ‹‹ለሰዎች (መጸለያ) መጀመሪያ የተኖረው ቤት ብሩክና ለዓለማት ሁሉ መመሪያ ሲኾን ያ በበካህ (በመካ) ያለው ነው። … ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መኼድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግደታ አለባቸው፤ የካደም (ያስተባበለም) ሰው (ከራሱ ውጭ ማንንም አይጎዳም)። አላህ ከዓለማት ሁሉ የተብቃቃ ነው (3፡ 96-97)።››

 ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.አ.ወ) ሙስሊሞች ሐጅን እንዲፈጽሙ ማዘዛቸው ተዘግቧል። ‹‹ ሰዎች ሆይ! አላህ ሐጅን በናንተ ላይ ግደታ አድርጓል። ስለሆነም ሐጅ አድርጉ።›› አንድ ሰው ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! በየአመቱ ነውን?›› ሲል ጠየቃቸው። ዝም አሉ። ሰውየው ጥያቄውን ሶስት ጊዜ ደጋገመ። የአላህ መልዕክተኛም (ሰ.አ.ወ) ‹‹አዎ ብያችሁ ቢሆን ኖሮ በየአመቱ ሐጅ ማድረግ ግደታ ይሆንባችሁ ነበር፤ ይህን ማድረግ ደግሞ አትችሉም ነበር።››

የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ የተለያዩ ከበራዎችን ይጨምራል። እነዚህም ኢህራም ማድረግ ጠዋፍ – ከዕባን መዞር ሳዒ – ሶፋና ማርዋህ ከፍታ ቦታዎች መካከል መሮጥ ጀበል አረፋት መቆም ሙዝደሊፋ አዳር በሚና ቆይታ ጀመራት ጠጠር መወርወር እርድ ወይም መስዋዕት ማረድ ጸጉር መላጨት የስንብት ጠዋፍ ማድረግ የነብዩን (ሰ.አ.ወ) መስጊድ መዘየር ይገኙበታል። ከእነዚህ የሐጅ አላባውያን መካከል ኢራህም፣ሳዒ፣ ሶፋና፣ ማርዋህ፣ ከፍታ ቦታዎች መካከል መሮን ጀበል አርፋት መቆም፣ እርድ ወይም መስዋዕት ማረድ የከበራው መሰረቶች ሲሆኑ አንዳቸው ሳይፈጸሙ ከቀሩ ሐጁ በአላህ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። የተቀሩት የከበራ አይነቶች ደግሞ መፈጸማቸው የተወደደ፣ ባይፈጸሙ የሐጁን ተቀባይነት የማያሳጡ ናቸው። እነዚህ የሐጅ ይዘቶች ሚቃት፣ ከዕባ፣ ሚና፣ ጀበል አረፋ በሚባሉ ቦታዎች የሚፈጸሙ ናቸው።

 ሚቃት

 ‹‹ሚቃት›› ሐጅ ለማድረግ የወሰነ ሙስሊም የሚነሳበት ቦታ የወል ስያሜ ነው። ኢትዮጵያውያን ሑጃጆች የሚነሱበት ቦታ ‹‹ለምለም›› ይባላል። ይህ ቦታ በየመን አቅጣጫ ይገኛል። ሐጃጁ ለምለም የተባለው ቦታ ሲደርስ ወይም ቀደም ብሎ ኢህራም ያደርጋል። አንድ ሙስሊም ሐጅ ለማድረግ ሲወስንና ወደ ስርዓቱ ሲገባ (ሲነይት)፣ እንዲሁም በሐጅ ወቅት ከተከለከሉ ድርጊቶች ሲታቀብና እንዲፈጽማቸው የታዘዙት ሲፈጽም ኢህራም ይባላል። እነዚህም ለሐጅ የነየተው ሰው አጠቃላይ ንጽህናውን ጠብቆ ሁለት ነጭ ብትን ጨርቆች ብቻ ይለብሳል። እግሮቹን የማይሸፍን ጫማ ይጫማል። ኢህራም ውስጥ ከተገባ በኋላ ከኢህራሙ እስኪመጣ ከባለቤት ጋር መተኛት፣ ጥፍርን መቁረጥ፣ ጸጉርን መላጨት፣ ጌጣጌት ማድረግ፣ ሽቶ መቀባት፣ ከሰው ጋር ጥል መፍጠር፣ ምድራዊ ከሆኑ ንግግሮች መቆጠብ፣ እንስሳት ማደን ወይም መግደል፣ ዛፍ መቁረጥ ወይም የዛፍ ቅርንጫፍ መዘንጠፍ፣ ወዘተ ይከለከላል።

ከዕባ። ከዕባ በመካ የሚገኝ የተቀደሰ ቤት ቁርአን እንደሚለው ‹‹ጥንታዊው ቤት›› ይባላል። ይህ የተቀደሰ ጥንታዊ ቤት የቀደመ ታሪክ ቢኖረውም አብዛኛው ታሪኩ ከነብዩ ኢብራሂም ጋር ይተሳሰራል። ነብዩ ኢብራሂም በእርጅና እድሜያቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ኢስማኤልን ከሐጀር እንደወለዱ ከመጀመሪያ ሚስታቸው ከሳራ ጋር አለመግባባት ይፈጠራል። ይህ አለመግባባት ሰበብ ሆኖ ነብዩ ኢብራሂም ሐጀርንና ኢስማኤልን ይዘው ከሶሪያ ወደ አሁኗ ሳውዲ አረቢያ ጉዞ ይጀምራሉ። ከረጅም ጉዞ በኋላም እዚህ የተቀደሰ ቦታ ሲደርሱ ያርፋሉ። ባለቤታቸውን ሐጀርንና ልጃቸውን ኢስማዒልን እዚህ የተቀደሰ ምድረ በዳ ትተውና የሚከተለውን ዱዓ ወይም ጸሎት አድርገው ይመለሳሉ። ‹‹ጌታችን ሆይ! እኔ አዝመራ በሌለው ሸለቆ ውስጥ በተከበረው ቤት (በከዕባ) አጠገብ ከዘሮቼ አስቀመጥሁ፤ ጌታችን ሆይ! ሶላትን ያቋቁሙ ዘንድ (አስቀመጥኳቸው)፤ ከሰዎችም ልቦችን ወደነሱ የሚናፍቁ አድርግ፤ ያመሰግኑህም ዘንድ ከፍሬዎች ስጣቸው፤ … ለዚያ ከሽምግልና በኋላ ኢስማዒልን ኢስሐቅንም ለኔ ለሰጠኝ አላህ ምስጋና ይገባው፤›› (14፡ 35-39)

ኢስማኢል ካደጉ በኋላ አላህ ነብዩ ኢብራሂምን በዚህ በተቀደሰ ቦታ ሰዎች አላህን ያመልኩ፣ ያመሰግኑት ዘንድ ከዕባን እንዲያቆሙ አዘዛቸው። በታዘዙትም መሰረትም ነብዩ ኢብራሂምና ልጃቸው ኢስማኤልም ካዕባን አቆሙ (2፡127)። ‹‹ቤቱንም (ከዕባን) ለሰዎች መመለሻና ጸጥተኛ ባደረግን ጊዜ (አስታውስ)፤ ከኢብራሂምም መቆሚያ መስገጃን አድርጉ፤ ወደ ኢብራሂምና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን ለዘዋሪዎቹም፣ ለአጎንባሾቹም፣ አሰጋጆቹም አጥሩ ስንል ል ኪዳን ያዝን (2፡125›› ። አባትና ልጁ ከዕባን ካቆሙ ወይም ከገነቡ በኋላ አላህ ነብዩ ኢብራሂምን ‹‹በሰዎችም ውስጥ በሐጅ ትእዛዝ ጥራ፤ እግረኞች፣ ከየሩቅ መንገድ ከሚመጡ ግመሎችም ሁሉ ላይ ኾነው ይመጡሃልና (22፡ 26)። በዚህ መንገድ ከእስልምና አንደኛው ማዕዘን የሆነው ሐጅ ተጀመረ። አብሮ የመካ ከተማ መሰረቱ ተጣለ። ነብዩ ሙሐመድም (ሰ.አ.ወ) በዚቹ የመካ ከተማ ተወልደውና አድገው የእስልምናን ጥሪ የመሩበት ቦታ ነው።

 በሐጅ ወቅት በዚህ ከዕባ የጠዋፍና የሳዒይ ከበራዎች ይፈጸማሉ። ጠዋፍ ከዕባን መዞር ማለት ነው። የጠዋፍ ከበራ በሶስት ሁነቶች ይፈጸማል። አንደኛው ሐጃጁ ከአገሩ ተነስቶ መካ እንደገባ፣ ሁለተኛው በሐጅ አስረኛው ቀን ላይ ከሚና ተመልሶ፣ ሶስተኛው የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ አልቆ ወደ አገር ሲመለሱ ጠዋፍ ይፈጸማል፣ የመሰናበቻ ጠዋፍ ወይም ጠዋፉል ወዳ ይባላል። የጠዋፍ አፈጻጸሙ ከዕባን ሶስት ጊዜ በሩጫ፣ አራት ጊዜ በጉዞ በድምሩ ሰባት ጊዜ መዞር ነው። ከዚያም ሁለት ረከዓ ሶላት ሰግዶ ዱዓ ወይም ጸሎት ያደርጋል። ከሚና ተመልሰው የሚፈጸም ጠዋፍ ከሐጅ መሰረቶች አንደኛው ሲሆን ጠዋፈ አል ኢፋዳህ ይባላል።

በዚህ በተቀደሰ ቦታ የሚፈጸመው ሌላኛው ከበራ ሳዒይ ይባላል። ሳዒይ ከዕባ አቅራቢያ በሚገኙ የሶፋና መርዋህ ከፍታ ቦታዎች መካከል በመሮጥ የሚፈጸም ከበራ ነው። ‹‹ሶፋና መርዋ ከአላህ (ትእዛዝ መፈጸሚያ) ምልክቶች ናቸው (2፡158)›› የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ አድራጊው ጠዋፍ ካደረገ በኋላ ከሶፋ ተራራ በመጀመር ወደ መራዋህ፣ ከመራዋህ ወደ ሶፋ ለሰባት ጊዜ ይሮጣል።

የሳዒይ ከበራ ከነብዩ ኢብራሂም ባለቤትና ከልጃቸው ከኢስማዒል እናት ከሐጀር ጋር የተሳሰረ ነው። ነብዩ ኢብራሂም ባለቤታችውን ሐጀርንና ልጃቸውን ኢስማዒልን ጥንታዊው ቤት ትተዋቸው እንደተመለሱ እናትና ልጁ በውሃ ጥም ይያዛሉ። ሐጀር በተለይ ልጇ ኢስማዒል በውሃ ጥም ሲሰቃይ ሁኔታውን መቋቋም ይሳናታል። ፈጣሪ የሆነ መፍትሄ ይሰጣት ዘንድ ከሶፋ ወደ መረዋ ለሰባት ጊዜ ያህል ስትሮጥ በመጨረሻ በፈጣሪ ፈቃድ የዘምዘም ውሃ ፈልቆ ከነበረችበት ጭንቅ ትገላገላለች። ይህ የዘምዘም ውሃ እስካሁንም አለ። ሑጃጆችም ይህን በሐጀር የተፈጸመውን የአላህ ተአምር በማሰብ እነርሱም ወደ ተራሮቹ በመሮጥ፣ በተራሮቹ ጫፍ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በመቆም ሀጃቸው እንዲሟላላቸው ወደ አላህ ዱኣ ያደርጋሉ።

 ሚና። ሚና ከመካ 7.5 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚገኝ ሁሉ ነገር ተሟልቶ የሚገኝበት የድንኳን ከተማ ነው። ልዩ ልዩ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የቁሳቁስ ወዘተ አገልግሎት በገፍ ይገኝበታል። በዚህ ቦታ ሑጃጆች ልዩ ልዩ ከበራዎችና ድርጊቶችም እየፈጸሙ ለሶስት ቀኖች ያህል ይቆያሉ። ሑጃጆቹ በዙል ሂጃህ ስምንተኛው ቀን ከመካ ነቅለው ወጥተው አዳራቸውን ሚና ያደርጋሉ። በማግስቱ ወደ አረፋ ሄደው በእስረኛው ቀን ወደ ሚና ተመልሰው ለሁለት ወይም ሶስት ቀናት ይቆያሉ። በእነዚህ ቀናት በአስረኛው ቀን የመስዋእት እርድ ያርዳሉ ወይም ለዚሁ አገልግሎት ለተቋቋሙ ክፍሎች በወቅቱ የተተመነውን ገንዘብ ይከፍላሉ። ጸጉራቸውን ይላጫሉ ወይም ያሳጥራሉ። መካ ሄደው ጠዋፍና ሳኢይ ይፈጽማሉ። ከአስረኛው ቀን ጀምሮ በሶስቱ ጀመራት ጠጠር ይጥላሉ። በተለይ የመሥዋእቱን እርድ ከፈጸሙ አንስቶ መደበኛ ልብሳቸውን መልበስ፣ ጥፍሮቻቸውን ማሳጠር የመሳሰሉ የተከለከኩ ማእቀቦች ይነሱላቸዋል። እነዚህ በሚና የሚፈጸሙ የሐጅ ከበራ ክፍሎች ከነብዩ ኢብራሂምና ከልጃቸው ኢስማዒል ጋር ታሪካዊና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው ናቸው። ታሪኩ እንዲህ ነው፡- ነብዩ ኢብራሂም ከአላህ የሆነ ህልም ያያሉ። ህልሙ በእስተ እርጅና እድሜያቸው ያገኙትን ልጃቸውን፣ ኢስማዒልን እንዲያርዱ የሚያዝ ነበር። ነብዩ ኢብራሂም ከሳቸው ፍላጎት ይልቅ ለፈጣሪያቸው ትእዛዝ ቅድሚያ በመስጠት ስለ ሁኔታው ልጃቸውን ኢስማኤልን ያማክራሉ። ኢስማዔልም እንደ አባቱ ከእሱ ህይወት ይልቅ ለፈጣሪው ትእዛዝ ቅድሚያ ሰጠ። ለመታረድም እራሱን አዘጋጀ። ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለማረድ እርግጥ ከሆኑ በኋላ አላህ በኢስማዒል ምትክ በመሥዋእት ታደገው። አላህ በቁርአኑ ክስተቱን እንዲህ ያወሳዋል፡- ‹‹ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ እኔ የማርድህ ኾኜ አያለሁ፤ ተመልከትም፤ ምን ታያለህ? አለው፤ አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ስራ፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ። ሁለቱም ትእዛዙን በተቀበሉና በግንባሩም ጎን ላይ በጣለው ጊዜ፤ ጠራነውም፤ (አልነው) ኢብራሂም ሆይ! ራእይቱን በውነት አረጋገጥክ፤ … በታላቅ ዕርድም (መሥዋዕት) ተቤዥነው (37፡102)››

 ጀበል አረፋ። ‹‹ጀበል አረፋ›› ማለት የአረፋ ተራራ ማለት ነው። ይህ ተራራ ከመካ ደቡብ ምስራቅ ሀያ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ተራራ ከነብዩ አደምና ሀዋ፣ እንዲሁም ከነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ጋር የተያያዘ ታሪካዊ ዳራ አለው። አደምና ሀዋ የአላህን ትእዛዝ ጥሰው፣ እንዲሁም የአላህ ኸሊፋ ሆነው ወደ መሬት ሲላኩ ምድር ላይ የተገናኙት በዚህ የአረፋ ተራራ እንደሆነ ይታመናል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) እ.ኤ.አ በ632 ከመሞታቸው በፊት ሐጅ አድርገው ነበር። ይህ ሐጅም ‹‹የመሰናበቻ ሐጅ/ ሒጀቱልወድዕ›› በሚል ስያሜ ይታወቃል።

ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) በዚህ የመሰናበቻ ሐጅ፣ የሐጁን ስነ ስርዓት እራሳቸው በመምራት ተከታዮቻቸው ስርዓቱን እንዲያውቁ አድርገዋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚፈጸመው የሐጅ ከበራ ሂደት እሳቸው ማስተማሩት መሰረት ነው። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) በአረፋ ተራራ ላይም ሆነው ለሑጃጆችና ለትውልድ የተሸገረና ህያው ምክር ሰጥተውበታል። በዚህ ወቅት ከሰጧቸው ምክሮች መካከል እንዲህ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡- ‹‹ሰዎች ሆይ! ከአሁኑ አመት ወዲያ አታገኙኝምና የሃይማኖታችሁን ጉዳይ ሁሉ ከኔ ያዙ። ገንዘብን በወለድ (ባራጣ) ማራባት ክልክል ነው። እርስ በርሳችሁ አትበዳደሉ። የሴቶችን ነገር አደራ እላችኋለሁ፣ ደካሞች ናቸውና እንዳታጠቋቸው።… አላህ ይመስክር። ቁርአንንና ሐዲስን ትቸላችኋለሁ። እነሱን ካልለቀቃችሁ በጭራሽ አትሳሳቱም››።

ሑጃጆች በዙልሒጃህ አስረኛው ቀን በዚህ ጀበል አረፋ ክልል ውስጥ ይሰባበባሉ። ናሚራ ተብሎ በሚጠራው መስጂድ የዝሁርንና የአስርን ሶላት በቡድን ከሰገዱ በኋላ እስከ ምሽት ድረስ የመጨረሻ የሚባለውን ዱኣ ወይም ጸሎት በቡድንም ሆነ በተናጠል ያደርጋሉ። ነብዩ ሙሐመድ (ሶ.አ.ወ) በአረፋ ቀንና ቦታ ስለሚደረግ የዱዓ ደረጃና ምንዳ ‹‹ከዱዓዎች ሁሉ በላጩ በዓረፋ ቀን የሚደረግ ዱዓ ነው። የአረፋን ቀን ያህል አላህ ባሮቹን በብዛት ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ሌላ ቀን የለም›› ማለታቸው ተዘግቧል። በዚህ ወቅት ከሚዘወተሩ ጸሎቶች መካከል ‹‹ከአላህ በቀር ሌላ አምልኮት የሚገባው አምላክ የለም። አላህ አንድ ነው፤ አጋር (ሸሪክ) የለውም። ንግስናም ምስጋናም የርሱ ነው። እርሱ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው። ጌታችን ሆይ! በምድረ ዓለም ደግን ነገር (ጸጋን) በመጨረሻይቱም አገር ደግን ነገር (ገነትን) ስጠን፤ የእሳትንም ቅጣት ጠብቀን›› የሚለው ይገኝበታል።

 ሑጃጆች ከአረፋ ተራራ ጸሀይ ሳትጠልቅ በሚናና በአረፋ ተራራ መካከል በሚገኝ ሙዝደሊፋ በሚባል ቦታ አዳራቸውን ያደርጋሉ። በዚህ ቦታ የመግሪብና የኢሻ ሶላት ይሰግዳሉ። በግልም ሆነ በቡድን ጸሎትና ዱዓ ያደርጋሉ። ሚና በሚገኙ ሶስት ‹‹ጀመራት ወይም ሸለቆዎች›› ውስጥ የሚጥሏቸውን አርባ ዘጠኝ ጠጠሮች ይለቅማሉ። ንጋት ላይ የፈጅር ሶላት ከተሰገደ በኋላ ወደ ሚና ይመለሳሉ። ከዚያም በሚና የተዘረዘሩትን የጠጠር ውርወራ፣ የመስዋእት እርድ፣ ወዘተ ከበራዎች ይፈጽማሉ።

 የነብዩ ሙሐመድን (ሰ.አ.ወ) መስጊድ መዘየር። የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ እንዳለቀ ወይም ከሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ አስቀድሞ ወደ መዲና በመሄድ የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) መስጊድ ዚያራ ወይም ጉብኝት ይረጋል። በእስልምና ጉብኝት የሚፈቀድባቸውና በዚህም ምንዳ ከሚያስገኙ የተቀደሱ ቦታዎች ከዕባ፣ የነብዩ መስጂድና መቅደሰል አንሷር እንደሆኑ ይታመናል። እነዚህን መስጂዶች የጎበኘና በቦታቸው የሰገደ ሰው ሌላ ቦታ ሰግዶ ከሚያገኘው ምንዳ እንደ አቀማመጣቸው የ500፣ የ1000፣ የ10000 ብልጫ አላቸው። በሐጅ ጊዜ የነብዩን (ሰ.አ.ወ) መስጊድ መዘየር ግደታ እንዳልሆነ ይታመናል። ሆኖም ከሩቅ አገር የሚመጡ ሑጃጆች አጋጣሚውን ለመጠቀምና የሚገኘውን ምንዳ ፍለጋ ሲሉ የሐጅ ስርዓታቸውን እንደጨረሱ ወይንም ቀድመው የነብዩን (ሰ.አ.ወ) መስሂድ ይጎበኛሉ። 

ኢደል አድሐ

ኢደል አድሐ በጥሬ ትርጉሙ ‹‹የመስዋእት ከበራ›› እንደ ማለት ነው። እንዲሁም ኢድ አልከቢር ወይም ታላቁ በዓል እየተባለም ይጠራል። ሐጅ ያላደረጉ ሰዎች ባሉበት ሆነው ከዙል ሂጃህ አስረኛው ቀን ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ያከብራሉ። በአስረኛው ቀን ከፈጅር ሶላት በኋላ ሁሉም ሙስሊም አደባባይ ወጥቶ የሶላት ስግደት ይፈጽማል። ከዚያም አሰጋጁ ወይም ኢማሙ ስለ ሐጅ እንዲሁም የሙስሊሙን ወቅታዊ ጉዳዩች የምክር ድስኩር ያደርግና ሁሉም ወደ ቤቱ ይመለሳል። በዚሁ እለት ወይም በተከታዮቹ ሁለት ቀኖች የመእዋእት እርድ አርዶ አንድ ሶስተኛውን ለቤቱ አስቀርቶ አንድ ሶስተኛውን ለድሆች ይሰጣል፤ ቀሪውን አንድ ሶስተኛ ደግሞ ከቤተሰቡ ጋር በመመገብ ቀኑን ያከብርበታል።

 በአገራችን የኢደል አድሐ ክብረ በአል አከባበር ሶስት ደረጃዎች እየተከበረ እስካሁን ደርሷል። የመጀመሪያው ደረጃ ክብረ በአሉ እንዳይከበር

“አጼ ኃይለ ሥላሴ በአንድ በኩል የጣሊያን ቅኝ ገዥ ከሙስሊሞች ጋር ፈጥሮት የነበረውን ግንኙነት እንደ ክህደት በመቁጠር፣ በሌላ በኩል ክርስትናን የአገሪቱ ብቸኛ የመንግስትና የህዝብ ሃይማኖት የማድረግ ፖሊሲ ስለነበራቸው፣ ይህንኑ ጥላቻና ፖሊሲ ለማስፈጸም በሙስሊሞች ላይ ጫና ይፈጥሩ እንደነበር ይታመናል”

ይደረግ የነበረበት የጫና ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ሙስሊሞች አደባባይ ወጥተው እንዲያከብሩ አይፈቀድላቸውም። የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው እንዳያከብሩ ፈቃድ ይነፈጉ ነበር። በእለቱ ትምህርት ቤቶች ፈተና በመስጠት ወጣቶች እቤታቸው እንዳይውሉና በቤት ውስጥ እንዳያከብሩ ጫና ይደረግባቸው፣ ወዘተ ነበር። ይህ የጫና ጊዜ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ ፍጻሜ ድረስ ያለውን ይሸፍናል።

 በአገራችን የኢደል አድሐ ክብረ በአል አከባበር ሁለተኛው ደረጃ ኢደል አድሐ መንግስታዊ እውቅና አግኝቶ በመስጂድ መከበር የተቻለበት ነው። በዚህ ደረጃ በበአሉ ምክንያት መስሪያ ቤቶች ይዘጋሉ። ህዝበ ሙስሊሙም በየመስጂድ ተገኝቶ የኢድ ሶላቱን በህብረት ይሰግድ፣ ቀኑን በጋራ በድስታ ያሳልፍ ነበር። ይህ ጊዜም የደርግ ዘመነ ስርዓትን የሚሸፍን ነው።

 ሶስተኛው የኢደል አድሐ ክብረ በአል ደረጃ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ አደባባይ ወጥቶ ክብረ በአሉን ማክበር የቻለበት፣ አሁን የምንገኝበት የኢህአዴግ ስርዓት ነው። በአሁኑ ወቅት ህዝበ ሙስሊሙ በሚገኝበት አካባቢ አደባባይ ወጥቶ የኢድ ሶላቱን ይሰግዳል። ለዚህም ሲባል የጸጥታ ጥበቃ ይደረግለታል። መንገዶች ክፍት ይሆኑለታል። በየአካባቢው የሚገኙ የመንግስት ሃላፊዎች አደባባይ በእንግድነት እየተገኙ የእንኳን አደረሳችሁና ሌሎችም መልእክቶች ያስተላልፉበታል። ልዩ ልዩ ድርጅቶችና ተቋማት የመልካም ምኞት መግለጫ ይሰጣሉ። የመገናኛ ብዙሃን ሽፋንም ይሰጠዋል። በልዩ ልዩ መንፈሳዊና ባህላዊ ዝግጅቶች ደምቆ ይውላል።

እንዲህ ሲባል ፍጹም ጫና ያልነበረበት ከበራ አድርጎ ማሰብ አይቻልም። አጠቃላይ ከበራው በመንግስት አካሎች ቁጥጥር እንደነበር ሁላችንም የኖርንበት ነው። የመንግስት ሙስሊሙ የፈተናው ጊዜ እንዲራዘም ሲጠይቅ የሚሰማው አጥቶ በአክትቪስቱ ጃሐር ሙሐመድ አማካኝነት እልባት ማግኘቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ በኢትዮጵያ

የአገራችንን የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ አስመልክቶ የተካሄደ ጥናት፣ የተሰበሰበ መረጃ ለማግኘት ስለተቸገርኩ ዳሰሳው ምናልባት የጥናት ርእስ በሚሆን መልኩ የቀረበ እንደሆነ ነው። በአገራችን የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከጣሊያን ወረራ በፊት እንደነበረ ይታመናል። በተለይ በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከሐረር ተወላጅ ሙስሊሞች የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ የማድረግ እድሉ እንደነበራቸው፣ በተለይ በጨለንቆ ጦርነት ሽምግልና ላይ በሐጅ ማእረግ የሚጠሩ የአካባቢው ወኪሎች እንደነበሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

 ጣሊያን በቅኝ ግዛት ለያዘቻቸውም ሆነ ለመያዝ በወረረቻቸው አገሮች ለሚገኙ ሙስሊሞች ድጋፍ የማድረግ ፖሊሲዋ መሰረት፣ በጣሊያን የወረራ ዘመን ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሐጅ እንዲያደርጉ ድጋፍ ተደርጎ ነበር። በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ በ1933 አስራ አንድ፣ እ.ኤ.አ. በ1934 ሀያ ዘጠኝ፣ እ.ኤ.አ. በ1936 ሰባት፣ እ.ኤ.አ.1937፣ 275፣ እ.ኤ.አ. 1938፣ 230፣ እ.ኤ.አ. 1938/9፣ 265 የሚሆኑ ሙስሊሞች የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ አድርገዋል።

 በንጉሱ ዘመን ስለነበረው የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ የጣሊያኑን የቅኝ ግዛት ዘመን ያህል የሚያመለክት መረጃ አላገኘሁም። ነገር ግን ሐጅ አብዱረህማን በሚባሉ ሰው የሚመራ የሐጅ ኮሚቴ እንደነበር መረጃዎች አሉ። እ.ኤ.አ. በ1945 ላይ ስድሳ ሁለት ሙስሊሞች ሐጅ ማድረጋቸው ተዘግቧል።

አጼ ኃይለ ሥላሴ በአንድ በኩል የጣሊያን ቅኝ ገዥ ከሙስሊሞች ጋር ፈጥሮት የነበረውን ግንኙነት እንደ ክህደት በመቁጠር፣ በሌላ በኩል ክርስትናን የአገሪቱ ብቸኛ የመንግስትና የህዝብ ሃይማኖት የማድረግ ፖሊሲ ስለነበራቸው፣ ይህንኑ ጥላቻና ፖሊሲ ለማስፈጸም በሙስሊሞች ላይ ጫና ይፈጥሩ እንደነበር ይታመናል። በዚህ የተነሳ በዘመናቸው ሐጅ የሚያደርጉ ሙስሊሞች በንጉሱ ችሮታ ልክ ቁጥሩ ይወሰን እንደነበር ይገለጻል። ከዚህም አልፈው ሐጅ ከማል ሐጅ በተባሉ ሰው አመካኝነት ‹‹የድሬ ሸኽ ሁሴን የመቃብር ቦታን›› መጎብኘት መካ ሄዶ ሐጅ ከማድረግ እኩል እንደሆነ በማስነገር፣ በጽሁፍም በማሳተምና በማሰራጨት ከፍተኛ ተጽእኖ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።

 በደርግ ዘመን የመጀመሪያው ክፍል የሐጅ ኮሚቴው ‹‹የሐጅና ዑምራ ኮሚቴ›› ስም እንዲታደስ ተደርጎ፣ በዚሁ የሐጅ ኮሚቴ አማካኝነት ሙስሊሞች ሐጅ እንዲፈጥሙ ከንጉሡ የተሻለ እድል ተገኝቶ ነበር። በዚህም መሰረት እ.ኤ.አ. በ1974፣ 3000 የሚደርሱ ሙስሊሞች የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ለመፈጸም በቅተው ነበር። ሆኖም የሐጅና ዑምራ ኮሚቴው በሙስናና በአቅም ማነስ ሰበብ የሐጅና ዑምራ አገልግሎቱ የመንግስት ተቋም በሆነው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር እንዲሆን ተደረገ። በየአመቱ የሐጅ ተጓዦችም ቁጥር ከ2000 እንዳይበልጥ ማእቀብ ተጣለ። እንዳም ሆኖ በ1978 ሐጅ ለማድረግ ያገኙ ሙስሊሞች ቁጥር ከ120 አልበልጡም።

 በዚህ በምንኖርበት የኢህአዴግ ዘመን የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከቀደሙት አንጻራዊ መሻሻል የታየበት እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በኩል እስከ 10000 የሚደርሱ ሑጃጆች ወደ መካ የመሄድ እድል ያገኙበት አጋጣሚ አለ። እንዲህም ሆኖ የመንፈሳዊ አገልግሎቱ አልጋ ባልጋ ሆኖ አያውቅም። በየጊዜው በሑጃጆች ላይ ጫና በሚፈጥሩ ችግሮች የተተበተበ አገልግሎት ውስጥ እስካሁንም ይገኛል። በፓስፖርትና ቪዛ ሰበብ ሑጃጆች ላልተገባ ወጭና እንግልት የተጋለጡበት ክስተት ነበር። የሐጁ ጉዞ ከአዲስ አበባ መነሳት ሲኖርበት ሑጃጁ መቀሌ ከዚያው ውቅሮ የነጃሺን መካነ መቃብር እንዲዘይር ተጨማሪ የጉዞ ዕዳ ተጥሎበት ነበር። የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከሚጠይቀው በላይ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ። በጉዞ ወኪል ሰበብ፣ በቤት ኪራይ ሰበብ፣ ወዘተ በኔት ወርክ የተሳሰረና የተጠናከረ ሙስና ተተብትቦ የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ማነቆ ሆኖ ዘልቋል።

የሐጅ ፋይዳ

 የሐጅን መንፈሳዊና ምድራዊ ፋይዳ በእዚህች ገጽ አሟልቶ ማቅረብ አይታሰብም። የተወሰኑ አንኳር ፋይዳዎችን ብቻ አስተዋውቆ የሐጅ መሰረታዊው ፋይዳ መንፈሳዊ ተግባሩ ነው። ከላይ እንዳየነው ሐጅ በአላህ የታዘዘ የእስልምና አምስተኛው ማዕዘን ነው። የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከሚያስገኛቸው ፋይዳዎች መካከል ከወንጀል ስርዬት ወይም ምህረት ማግኘት፣ ከኃጢያት ስርዬት ወይም ንጽህና ማግኘትና ጀነት የመግባት ምንዳ ይጠቀሳሉ። ከወንጀል ስርዬት ስለማግኘት ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ‹‹ሐጅ ያደረገና በሐጅ ወቅት ጸያፍ ነገር ያልተናገረ፣ ወይም ያልፈጸመ፣ እንዲሁም ኃጢአት ያልሰራ እናቱ እንደወለደችው ቀን ከወንጀል የጸዳ ሆኖ ይመለሳል›› ብለዋል። ጀነት የመግባትን ምንዳ በሚመለከትም ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.አ.ወ) ‹‹በትክክል የተፈጸመ ሐጅ ከጀነት ውጭ ሌላ ምንዳ የለውም›› ማለታቸው ተዘግቧል።

 የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ሌላኛው ፋይዳ የሰላም ተምሳሌት መሆኑ ነው። ስለ ሐጅ አፈጻጸም ዘርዘር ተደርጎ ለማሳየት እንደተሞከረው በሐጅ ወቅት እያንዳንዱ ሐጃጅ ከፈጣሪው ጋር፣ ከራሱ ጋር፣ ከሰው ጋር ከእንስሳት ጋር፣ ከአእዋፍትና ነፍሳት ጋር እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ሰላም እንዲፈጥር የሚያስችል፣ በድምሩ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለሰላም የሚደረግ ታላቁ ጉባኤ ነው።

 ሐጅ የሙስሊሞች ወንድማማችነትና እኩልነት ፋይዳ መግለጫና ተምሳሌትም ነው። በሁሉም የአለም ማእዘናት የሚገኙ በሶስት ሚሊዮን የማያንሱ ሙስሊሞች በየአመቱ በሐጅ ስርዓት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የስርዓቱ ተካፋዮች የአገር፣ የጂኦግራፊ፣ የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የፖለቲካ፣ የሙያ፣ የሀብት፣ የቀለም ወዘተ ድንበር፣ አጥንና ኬላ ሳይወስናቸው ሁሉም በእኩልነት ለአላህ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሐጅ ከበራ ላይ ይገኛሉ። አንድ አይነት ተራ ልብስ ለብሰው፣ አንድ አይነት ስርዓተ ጸሎት ይፈጽማሉ፣ ወዘተ።

 ሐጅ የመስዋዕት እንደሆነ ተወስቷል። ይህ ትርጓሜም በኢደል አድሃ ከበራ ይገለጻል። ሑጃጆች ሚና ላይ ሐጅ ማድረግ ያልቻሉ በቤታቸው ሆነው መስዋዕት ወይም እርድ ይፈጽማሉ። እርዱን ለሶስት ከፍለው አንድ ሶስተኛውን ለድሃ ያካፍላሉ። በዚህም ያለው የሌለውን በማሰብ የማህበራዊ ትስስራቸውና የመረዳዳት ባህላቸው እንዲታደስ፣ እንዲጠናከርና እንዲቀጥል ያደርጋል። ይህም ሌላኛው የሐጅና የኢደል አድሃ ማህበራዊ ፋይዳ ነው።

 የኢደል አድሃ ከበራ ከእርድ በተጨማሪ ስግደትና የዲስኩር እንደሚከናወንበት አይተናል። በተለይ በዲስኩሩ ወቅት ወቅታዊ የሙስሊሙ ጉዳዮች የሚንጸባረቁበት ነው። በዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የታፈነ ድምጻቸውን ሲያሰሙበት፣ በዚህም የድብደባና የእንግልት ፍዳ የከፈሉበት አጋጣሚ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል።

 የሐጅ መንፈሳዊ ጉዞ ከአደምና ሀዋ፤ ከነብዩ ኢብራሂም፣ ከባለቤታቸው ሐጀርና አልጃቸው ኢስማዒል ታሪካዊ ክስተት ጋር ግንኙነት እንዳለው ተመልክተናል። በዚህ ረገድ ሐጅ ታሪክን የማቆየት፣ የመተረክና የማስተላለፍ ፋይዳ እንዳለው ማስተንተን ይቻላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top