ፍልስፍና

ለመሆኑ “የአፍሪካ ፍልስፍና” ከወዴት ነው (ወደ አፍሪካ ፍልስፍና የሚወስዱ መንገዶች)

(ክፍል ሁለት)

ይህ ጽሑፍ የአፍሪካ ፍልስፍና ይኸ ነው ብሎ ሙሉ ምስሉን ያሳያል ተብሎ አይጠበቅም። ይልቁን አንዳንድ ተምሳሌታዊ የሆኑ የአፍሪካውያን አገር በቀል አስተሳሰቦች ላይ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱ የአፍሪካውያን ምሁራን እና ፖሊሲ አውጭዎች ግብአትና የምርምር አጀንዳዎችን ለማንሳት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ አገር በቀል የፖለቲካ፣ የባህልና የሃይማኖት አስተሳሰቦች ውስጥ መሠረታዊ የፍልስፍና ጥያቄዎችን የሚመልሱ አስተሳሰቦችን ፈልፍሎ ለማምውጣት የሚያስችሉ መንገዶችን ለመጠቆም ነው። በርግጥ ፍልስፍናው በሥርዓት ተሰንዶ በማይገኝበትና በእንደዚህ በባህል ብዛት ሃብታም የሆኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ግልጽ የወጣ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብን ለማግኘት ትንሽ ትዕግስትንና ጠንካራ ጥናትን ይጠይቃል። “ዘፈቀዳዊና ኢ-ምክንያታዊ” በሚመስሉ የሕይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ መሠረታዊውን ገዥ አስተሳሰብና ጥልቅ ምርምር ፈልጎ ማውጣትም በመስኩ ጥናት ከሚያደርጉ ሰዎች የሚጠበቅ ምሁራዊ ግዴታ ነው።

 በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “የአፍሪካ ፍልስፍና” ሲባል ሁሉንም አፍሪካውያን አንድ የሚያደርጋቸው የአስተሳሰብ ወይም የአእምሮ ካርታ ለማለት ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካ ምድር የሚገኙ ቱባ ባህሎች ውስጥ የሚገኙ የፍልስፍና ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን የሚያሳይ ነው። በዚህ አረዳድ የአፍሪካ ፍልስፍና ይህን ይመስላል፣ ከሌላው ዓለም የተለየ ነው መለያ ባሕርያቶቹም እነዚህ ናቸው ብሎ ድንበር ለማበጀት ሳይሆን በአፍሪካውያን ማኅበራዊ ስነ ልቡናና ባህላዊ የሕይወት ውቅር ውስጥ የሚገኙትን ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦች ለመረዳት የሚደረግ ጥረት ነው። ሲጀመር በእውቀት ላይ ድንበር ማበጀት አይቻልም። ከተወሰነ የባህል ልዩነትና አካባቢያዊና ነባራዊ ሁኔታና የሳይንስና የዘመናዊነት ተጽእኖ መፈራረቅ የፈጠራቸው የኑሮ ዘይቤና የአስተሳሰብ መንገድ የሚስተዋሉ ልዩነቶች ይኖራሉ እንጅ በመሠረታዊ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ላይ ይህ ነው የሚባል ድንበር ማግኘት አይቻልም። እንዲያውም ትክክለኛው እውቀት ይህ ነው፤ ይህ እውቀትም የነእከሌ የግል ንብረት ነው ማለት የሰዎች ልጆችን የዘመናት ታሪክ የርስ በርስ ግንኙነትን እና ያ ግንኙነት ባጠቃላዩ የሰው ልጆች የሳይንስና የፍልስፍና እድገት ውስጥ ምን ያክል የጋራ እሴትን እንዳበለጸገ መታየት እንዳለበት የሚከራከሩ አካላት አሉ። እውቀት ሁሉ የሰው ልጆች ንብረት እንደሆነ ሁሉ ለዚህ እውቀት እውን መሆን ሁሉም ባህሎች ባንድም በሌላም መንገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ መዘንጋት የለብንም።

ለምሳሌ ሳንድራ ሃርዲንግ፣ የአውሮፓ ብቻ የሚባል የሳይንስ ምጥቀት የለም። የዓለም እውቀት ከሁሉም ባህሎች የተውጣጣ እንጂ ለአንዱ ብቻ የሚሰጥ አይደለም ስትል ትከራከራለች። በሌላ በኩል ሳንቶስ፣ ዘመናዊውን እውቀት ከባህላዊ እውቀት ጋር ግንኙነት የለውም፣ ባህላዊ እውቀት ጊዜው ያለፈበት ነው ማለት በራሱ እውቀትን መግደል እንደሆነ ሲከራከር ወርቅነህ ቀልቤሳና ሌሎች በአገር በቀል እውቀት ላይ ጥናት ያደረጉ አካላት ደግሞ ባህላዊና ዘመናዊው እውቀት ተደጋግፈው መሄድ እንዳለባቸውና እርስ በርሳቸው መሞላላት እንዳለባቸው የይሁንታ ሐሳብ ያቀርባሉ። እንግዲህ የአፍሪካ ፍልስፍና ሲባል ለዓለም ልጆች የአስተሳሰብ ብልጽግና የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገና ማድረግ የሚችል የአገር በቀል እውቀቶች ክምችት እንደሆነ የሚገልጽ ነው።

በመልክአ ምድር አፍሪካ ተብሎ በሚታወቀው አህጉር ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የኖሩባቸውን የፍልስፍና አስተሳሰቦች የሚወክል እንጂ ይህ የአፍሪካውያን ብቻ ነው ወደ ሚል የባለቤትነት መብት የማስከበር ጉዳይ አይደለም። አፍሪካውያን ያስባሉ ወይስ አያስቡም? ከሚለው መሠረታዊ የአፍሪካውያንን “ሰውነት” ከሚገዳደረው ጥያቄ ጀምሮ አፍሪካውያን በአስተሳሰብ ደረጃ ለዓለም የብልጽግና ጉዞ ምንም አስተዋጽኦ አላደረጉም የሚሉ ጉንጭ አልፋ ክርክሮች ለብዙ ዘመናት በአፍሪካ ፍልስፍና ምዕራፎች ግዙፍ ቦታን ይዘው ኖረዋል። ይህ ክርክር አፍሪካውያን ራሳቸውን እንዲመለከቱ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ዋናው ቁም ነገር ግን የአፍሪካውያን ፍልስፍና ምንድን ነው? የአጠናን ዘዴውስ ምን መሆን አለበት? ከአፍሪካ ፍልስፍናን ምን ዓይነተኛ የአስተሳሰብ አብነቶችን ማግኘት እንችላለን? ለዘመናችን ችግሮች መፍትሔነትስ በምን መልኩ ተሰድረው ቢቀርቡ አጉራዊና ዓለማቀፋዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች ቅድምና መስጠቱ እንደሚበጅ ይታመናል። ይህ ጽሑፍም ማጠንጠኛው ያደረገው እነዚህን ጥያቄዎች ነው።

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስም የአፍሪካን ጓዳ ጎድጓዳ መፈተሹ ይበጃል። ከአጠናን ዘዴው እንጀምር። ስለ የአፍሪካ ፍልስፍና የአጠናን ዘዴ በርካታ መላ ምቶች አሉ።

 በርካታ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በአፍሪካውያን ጓዳ ውስጥ ተቀብረው፣ ተዘንግተው ወይም እንዳያንሰራሩ ተጨቁነው የቀሩ የአስተሳሰብ ክምችቶች ይገኛሉ። በቋንቋው፣ ባባህሉ፣ በሃይማኖቱ፣ በየየዕለት መስተጋብሩ ባጠቃላይ በአገር በቀል እውቀት ክምችቱ ውስጥ የነገረ መለኮት፣ የግብረገብ፣ የሥነ እውቀት፣ የምርምር፣ የሕይወት ትርጉምና የሐተታ ተፈጥሮ አስተሳሰቦች ይገኛሉ። በመሠረቱ አንድ ማኅበረሰብ በዘመናት ታሪኩ ውስጥ ለሚያጋጥሙት ውጣ ውረዶች፣ አካባቢያዊ ተግዳሮቶችና ጸጋዎች ምላሽ ለመስጠት ማስተባቃቱ፣ መተከዙ፣ መቆዘሙ ወይም ጥልቅ ተመስጦውስጥ መግባቱ፣ መምከሩ መዝከሩ አይቀሬ ነው። በዚህ የጋራ ወይም የተናጠል አስተሳሰብ ውስጥ የተፈጥሮን ምስጢር የሚገልጡ፣ የሕይወትን ትርጉም የሚያትቱ አስተሳበባዊ ቅርሶችን ማግኘት ይቻላል።

 ይህንን ለማድረግ ዓይነተኛ የጥናት ዘዴን መምረጥ የአጥኝው የመጀመሪያ ኃላፊነት ይሆናል። አንድን ነገር በትክክል ለመረዳት መጀመሪያ ችግሩን እንዴት መፍታት እንዳለብን መንገዱን መለየቱ ተቀዳሚው ተግባር ነው። የተመረጠው መንገድ ለርእሰ ጉዳዩ የሚስማማና የተፈለገውን ዓላማ ሊያሳካ የሚችል መሆኑን በጥንቃቄ መምረጥ ያስፈልጋል። ችግሩንና የችግሩን መፍትሔ መንገድ መለየት የችግሩን ክብደት ይቀንሰዋል። ወደ አፍሪካ ፍልስፍና የሚወስደው ትክክለኛው መንገድ የቱ ነው? የሚለው ጥያቄ የርዕሰ ጉዳያችንን ማዕካላዊ ስፍራ ከሚይዙት ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ነው።

የተለያዩ ፈላስፎች ይህንን ለማድረግ የሚረዱ በርካታ የአጠናን ዘዴዎች ይጠቁማሉ። በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቀውና በርካታ የዘመኑንና ከሱ በኋላ የመጡትን ምሁራን ያከራከረ እንዲሁም ጫና ፈጣሪ የነበረው ኬንያዊው ኦዴራ ኦሩካ ነው። እንደ ኦሩካ አስተሳሰብ የአፍሪካን ፍልስፍና ለማጥናት ቢያንስ አራት ዘውጎችን ወይም መንገዶችን (Four Trends of African Philosophy) ይጠቁመናል። እነሱም Ethnophilosophy, Philosophic Sagacity, Nationalist/ideological Philosophy, Professional Philosophy ናቸው።

 የመጀመሪያው እንደ አንትሮፖሎጂ፣ የቋንቋና የታሪክ፣ የባህል ጥናት ካሉ መስኮች ጋር በመተባበር በማኅበረሰቡ የየእለት እንቅስቃሴ ውስጥ መሠረታዊ አስተሳሰቡን ፈልፍሎ በማውጣት ዋናዋና የፍልስፍና እሳቤዎችን ማግኘት ነው። Ethnography የሚባለውን የተሳታፊ ጥናት በመከተል ፈላስፋው ወይም አጥኝው ከማኅበረሰቡ ጋር በሚያሳልፋቸው ጊዜያቶች ውስጥ የማኅበረሰቡን አባላት እውነት ምንድን ነው:: ሕልውና (existence), የሕይወት ትርጉም፣ ዲበ አካል ወይም የነገሮች መሠረታዊ ምንነት (Metaphysics and being), ነገረ መለኮት፣ የርስ በርስ ተግባቦትና ማኅበራዊ መስተጋብር፣ ሐተታ ጠፈጥሮና የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ የስነ እውቀትና ስነ አመክንዮ ሂደት፣ የፍርድ አሰጣጥና ክርክር፣ ፖለቲካና አስተዳደር ወዘተ የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ፍልስፍናቸውን ማግኘት ይቻላል የሚል ነው። በዚህም የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በታሪክ ጉዟቸው ውስጥ ያካበቱትን የእውቀት መካዝንና የአስተሳሰብ ክምችት እንዲሁም ማኅበራዊ ሥነ-ልቡና መረዳት ይቻላል።

 ይህንን ለማድረግ ደግሞ እንደ ንጉጊ ያሉት ልሂቃን አጥኚው አፍሪካዊና የባህሉ ባለቤት መሆን እንዳለበት ሲጠቁሙ ቋንቋውም በተጠኝው ማኅበረሰብ በራሱ ቋንቋ መሆን አለበት ይላሉ። ይህም የሆነው ”በባዕድ“ ቋንቋና የአስተሳሰብ መስፈርት አንድን አገር በቀል እውቀት በቀላሉ መረዳት ስለማይቻል ነው። ያንን ማድረግ መሞከር ደግሞ እውነተኛውን የአፍሪካውያን አስተሳሰብ ስለሚሸፍነውና ያልተገባ ድምዳሜ ላይ ስለሚያደርስ ነው። የዚህ አስተሳሰብ አራማጅ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከላይ የተጠቀሰው ዊረዱ ነው።

 ይህንን ሐሳብ በተግባር የገለጹ በርካታ ፈላስፎች መካከል ዊረዱ፣ ፕላሲድ ቴምፕልስ፣ ክላውድ ሳምነር ይገኙበታል። በባህል ጥናቱ መስክም እንደእነ ዶናልድ ሌቪን ያሉት ተጠቃሽ ናቸው። ዊረዱ መጀመሪያ የተጻፈ የአፍሪካ ፍልስፍና ባለመኖሩ እንደ አማራጭ የተጠቀመው የባህል ጥናት ውጤቶችን እንደነበር ከላይ አይተናል። የነዚህ አጥኝዎች ሥራዎችም ለአፍሪካ ፍልስፍና ውይይት የመነሻ ግብአቶች ነበሩ። ሳምነር

“በዚህ ረገድ በግንባር ቀደምትነት የሚታወቀውና በርካታ የዘመኑንና ከሱ በኋላ የመጡትን ምሁራን ያከራከረ እንዲሁም ጫና ፈጣሪ የነበረው ኬንያዊው ኦዴራ ኦሩካ ነው። እንደ ኦሩካ አስተሳሰብ የአፍሪካን ፍልስፍና ለማጥናት ቢያንስ አራት ዘውጎችን ወይም መንገዶችን (Four Trends of African Philosophy) ይጠቁመናል”

በበኩሉ በኦሮሞ ቃላዊ ጽሑፎች ውስጥ ያሉ አስተሳሰቦችን በመተንተን አንድ መጽሐፍ (The Oromo Wisdom Literature?) መጻፍ ችሏል። ቴምፕልስ በበኩሉ የባንቱ ህዝቦችን አስተሳሰብ የተነተነበት ሥራው ተጠቃሽ ነው። ዶናልድ ሌቪል በአማርኛ ስምና ወርቅ ላይና በጣቃላይ ባኅላዊ መስተጋብር ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ የሰነደበት Wax and Gold የተሰኘው መጽሐፉ ከዚሁ ጎራ ያስመድበዋል ለማለት ያስደፍራል።

ሁለተኛው ደግሞ Sages ወይም ጠቢባን፣ ልሂቃን፣ አዋቂዎችን ወዘተ ያንድን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ይወክላሉ ተብለው የሚታሰቡትን በቃለ መጠይቅ ወይም መደበኛ ባልሆነ መልኩ ከነሱ ጋር አዘውትሮ በመገናኘት አስተሳሰባቸውን መቅሰም፣ መረዳት ነው። እያንዳንዱ ማኅበረሰብ የራሱ የሆኑ ጠቢባን ወይም አዋቂዎች አሉት። በእድሜ ወይም በልዩ ጥረትና ተመስጦ ወይም በተሰጥኦ አንዳንድ ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ላቅ ያለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል። እነዚህ ጠቢባን አስተሳሰባቸው የተገነባው ከዚያ ማኅበረሰብ የባህል እሴቶችና ልምዶች ስለሆነ ባንድም በሌላም የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ ይወክላሉ። እናም የአፍሪካን ፍልስፍና ለመረዳት የነዚህን ሰዎች አስተያየትና ግንዛቤ መረዳት አስፈላጊ ነው።

ከነዚህ ግለሰቦች ጋር በተደጋጋሚ በመገናኘትና ከጥበባቸው በመቋደስ የሚኖሩበትንና የኖሩበትን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ በጥቂት ጭንቅላቶች ተከማችቶ እንደሚገኝ መረዳት ይቻላል። Azenabor ይህንን የጠቢባኑን ወካይ ፍልስፍና “a reflective evaluation of thought by an individual African elder who is a repository of wisdom, knowledge and rigorous critical thinking [of a given socio-cultural community]” ሲል ይገልጸዋል። የኢትዮጵያ ልኂቃን፣ አበጋሮችና አባገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎችና ያገር ሽማግሌዎች ከነዚህ የሚመደቡ ናቸው። የእንደነዚህ ዓይነቶቹን ጠቢባን እውቀት መሰብሰቡና መተንተኑ ለአፍሪካ ፍልስፍና ትልቁ ምንጭ ነው።

 ሶስተኛው በአብዝሃኛው ከአፍሪካ የነጻነት ትግል ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ልሂቃኑ ሲያቀነቅኑት ከነበረው አስተሳሰብ የሚቀዳ ፍልስፍና ነው። አንዳንድ የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮች መሠረታዊ ነጻነትንና የአፍሪካውያንን ጠንካራ የርስ በርስ ግንኙነትና ሕብረትን እውን ለማድረግ ከአፍሪካውያን አስተሳሰቦች ውስጥ አማራጮችን ይፈልጉ ነበር። የነጻነት ትግል መሪዎቹ በሚበትኗቸው አጫጭር ጽሑፎች፣ በጋዜጦች፣ በሚያደርጓቸው ንግግሮች ወዘተ አፍሪካዊ ለዛ የተዋሃዳቸው አስተሳሰቦች ይንጸባረቁ እንደነበር እሙን ነው። ለምሳሌ የነኔሬሬ ኡጃማ (ቤተሰባዊነት፣ ወንድማማችነት) ፣ የነንክሩማህ የአፍሪካ ኮሙኒዝምና የስምምነት ዲሞክራሲ (African Communism and Consensus)፣ የነ ሴንጎር ኔግሪትዩድ ፍልስፍና ወዘተ አስተሳሰቦች ስለ ማኅበራዊ ውሕደትና ደኅንነት የሚበጁ ሐሳቦችን የሚጠቁሙ ናቸው። ከዚህም መልካም የፖለቲካ ፍልስፍናና ተምሳሌታዊ የዲሞክራሲ ባህልን ማግኘት እንደሚቻል ያሳያል። የአእምሮ ወይም የአስተሳሰብ ነጻነት ከፖለቲካዊ ነጻነት ይቀድማል የሚል እሳቤ ያነገበ ነው። “Nationalist/ideological philosophy basically tries to develop a new political theory based on traditional African familyhood. It advocates mental liberation and a return to African humanism. It arose out of the conviction that political independence must be accompanied by “a true mental liberation” (Bodunrin 1991, 64).” (Oswell Hapanyengwi- Chemhuru፣ 2013፣ ገጽ 47)

አራተኛው መንገድ በዘመናዊ የአውሮፓ ፍልስፍና የተካኑ አፍሪካውያን በዓለም መድረክ የሚያደርጓቸውን የሐሳብ አበርክቶዎችን የሚመለከት ነው። በትውልድ ወይም በአስተዳደግ የአፍሪካ ባህል ውጤቶች፣ በትምህርት ዝግጅት ደግሞ የዘመናዊ ሳይንስና ፍልስፍና አስተሳሰብ ባለቤቶች የሆኑ ልኂቃን በአስተሳሰባቸው ውስጥ የሚገኘውን ፍልስፍና በማጥናት ስለ ዘመናዊ የአፍሪካ ፍልስፍና ፍንጭ ማግኘት ይቻላል የሚል እሳቤ ነው ይህ። የነዚህ በፍልስፍና ሙያ የሚኖሩ ልኂቃን ዋናው አስተዋጽኦ ከላይ በሶስቱ መንገዶች የተገለጹትን አስተሳሰቦች ፈልፍሎ በማውጣት ከሌላው ዓለም ፍልስፍና ጋር በማመሳከርና በማሞላላት ለአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ የሚበጅ ፍልስፍናዊ የይሁንታ ሐሳብ ማምጣት ነው። ለአብዛኞቹ የአፍሪካ ልሂቃን በአፍሪካ ፍልስፍናና በሌላው ፍልስፍና መሠረታዊ ልዩነት የለም። ምክንያታዊነትና ፍልስፍናዊ ሕይወት ለሰው ልጆች ያለልዩነት የተሰጠ ሲሆን በፍልስፍና ልዩነቱ የሚፈጠረው እንደየ አካባቢው በሚነሳው ጥያቄ፣ የችግሩ ዓይነትና ጥያቄውን ለመመለስ በሚደረገው ዘዴ የባህል ልዩነት ነው ይላሉ። (Oswell Hapanyengwi- Chemhuru) እነ ሁንቶጅ፣ ዊረዱ፣ መሳይ ከበደ፣ በቀለ ጉተማ፣ ፍራንሲስ ፋኖን ወዘተ በዚህ ጎራ ይመደባሉ።

ከላይ ከተብራሩት ዘዴዎች በተጨማሪ ሌሎች መንገዶችን መጠቀም የአፍሪካን ፍልስፍና ሙሉ ገጽታ ማግኘት ይቻላል። ለምሳሌ እጓለ ገብረ ዮሐንስ አገላለጽ “በተዋሕዶ ከበረ” የሚሉትና የውጭውን ሳይንስና ፍልስፍና ከባህላዊው አስተሳሰብ ጋር በማዋሃድ ዘመናዊ የአፍሪካን ፍልስፍና ወይም የአስተሳሰብ ንቃተ ኅሊና ማጠንከር ይቻላል። ኋላ ላይ እነጸናይ (ሰናይ?) ሰረቀብርሃን Hermeneutics in Africa Philosophy ያሉት መንገድ ነው። የዚህ መሠረታዊ አስተሳሰብ የአፍሪካ ነባሩ እውቀት መሠረታዊ እሴቶች በዘማናዊ የሳይንስና የፍልስፍ ታሽተው ሲቀየጡ ከአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተስማሚ የሆነ የእውቀት ክምችት ይፈጠራል የሚሉት ናቸው። በዚሁ ጎራ የሚሰለፉት እነፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ በበኩላቸው የባኅሎች ተግባቦትና ውህደት (Intercultural Philosophy) ለዘመናችን የአፍሪካ ፍልስፍና ተመራጭ መንገድ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ሌሎች የአፍሪካን ፍልስፍና እሴቶች ለማግኘት እንደ ተጨማሪ አማራጭ የሚወሰዱት በጥበባዊ ሥራዎችና በሥነ-ጽሑፎቹ ውስጥ ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን መፈለግ ነው። እርግጥ ነው በተለያዩ ባኅላዊ ትወናዎች እንዲሁም ጥበባዊ ሥራዎች ላይ የፍልስፍና ጥያቄዎች መንጸባረቃቸው እሙን ነው። አንድ ማኅበረሰብ በጥበባዊ ሥራዎቹና በቃላዊና ፊደላዊ (በቃልና በጽሑፍ የሚገለጹ ሥነ- ጽሑፎች አማካኝነት ስለ ሐተታ ተፈጥሮ፣ የሕይወት ትርጉም፣ የኑሮ ዘይቤ፣ የርስ በርስ ተግባቦት፣ ወዘተ መግለጹ አይቀርም። ለምሳሌ በርካታ ጥንታዊ ቅርጻቅርጽ፣ ስዕሎች፣ የዘፈን እንጉርጉሮዎች፣ ቅኔዎችና ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ ታሪክ ነገራዎች፣ የብራና ጽሑፎችና ዘመናዊ የጥበብ ሥራዎች የደራሲዎቻቸውንና የታዳሚያኑን ማኅበረሰብ ፍልስፍናዊ ርዕዮተ ዓለም ይገልጻሉ። ስለዚህ ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ በነዚህ ጥበባዊ ሥራዎችና ሥነ-ጽሑፎች ውስጥ የአፍሪካን ፍልስፍና ማሰስ የራሱ የሆነ ሚና አለው። በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑት የነ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ የነችንዋ አቸቤ፣ የነሐዲስ ዓለማየሁ፣ ዳኛቸው ወርቁ አደፍርስ፣ አቤ ጉበኛ ወዘተ ጽሑፎችን ማግኘት እንችላለን። የገብረ ክርስቶስ ደስታ የክርስቶስ ሥዕል በራሱ ብዙ ፍልስፍናዊ የነገረ መለኮት ይዘት አለው።

ባጭሩ እነዚህና ሌሎች ምቹ የአጠናን ዘዴዎችንበመከተል ከአፍሪካ ምድር የፍልስፍና ወለላንመቅሰምና የተደበቀውን፣ የተዘነጋውንአስተሳሰብ እንዲያንሰራራና ተግባራዊ ፋይዳውጎልቶ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል። ይህንንመድረግ ደግሞ ለአፍሪካውያን ምሁራንለራሳቸው ወይም በአፍሪካ ጥናትና ምርምርላደረጉ ቀና ልኂቃን የተተወ ነው። እስከዛሬበርካቶች ይህንን ኃላፊነት ወስደው በርካታየፍልስፍና አስተሳሰቦችን ከየጓዳቸው እየመዘዙእንካችሁ ብለውናል። በኢትዮጵያ ፍልስፍና ጓዳእንኳ ካናዳዊውን ሳምነርን መጥቀስ ይቻላል።የግዕዝን ቋንቋ ተምሮ፣ የኦሮሞዎችን ቃላዊጥበብ ተንትኖ ከኢትዮጵያውያን በላይየኢትዮጵያን ፍልስፍና አሳይቶናል። ሊመሰገንይገባዋል። ሌሎችም እንዲሁ በርካታየአፍሪካ ፍልስፍናዎችን ለዓለሙ ማኅበረሰብአሳይተዋል። በሚቀጥለው ከእነዚ ጥናቶችእየጨለፍን የአፍሪካን ተምሳሌታዊ ፍልስፍናአስተሳሰቦችን ለመቃኘት እንሞክራለን። ለቀጣዩጽሑፍ ማጠንጠኛዎችም የአፍሪካውያንፍልስፍና የጋራ መገለጫዎች ምን ምንናቸው? ከአፍሪካ ፍልስፍናን ምን ዓይነተኛየአስተሳሰብ አብነቶችን ማግኘት እንችላለን?ለዘመናችን ችግሮች መፍትሔነትስ በምንመልኩ ተሰድረው ቢቀርቡ አህጉራዊናዓለማቀፋዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል? የሚሉትጥያቄዎች እንደሆኑ ልብ ይሏል። ይቀጥላል…..

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top